ከእግዚአብሔር ጋር አብረን መሆናችን በምን ይታወቃል?

ብዙ ጊዜ ክርስቲያኖች፣ አማኝ ከእግዚአብሔር (ከመንፈስ ቅዱስ) ጋር ያለውን ጤናማ ግንኙነት የሚለኩበት መሣሪያ የተሳሳተ ነው፡፡ ለአብነት፣ የተሻለ ደሞዝ፣ ጥሩ መኖሪያ ቤት፣ ልጆች፣ አካላዊ ጤና፣ ወዘተ ያሉት አማኝ ይህ የሆነለት ከእግዚአብሔር ጋር መልካም ግንኙነት ስላለው እንደሆነና እነዚህ የጎደሉት ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር በትክክለኛ መንገድ ላይ እየሄደ አለመሆኑን ያሳያል ሲሉ ይደመጣል፡፡ ከላይ የተዘረዘሩት መለኪያዎች ከእግዚአብሔር ጋር መሆናችንን የሚያሳዩ ከሆነ ወንጌልን ለባለጠጎች መስበካችንን አላስፈላጊ አያደርገውም ወይ? ከዚህ በተጨማሪስ እግዚአብሔር የለም የሚሉ ኢአማኒያንን ጨምሮ በእስልምና፣ በቡድሃ፣ ወዘተ ቤተ እምነቶች ስር ያሉ እና ከላይ የተዘረዘሩትን ነገሮች የሚያሟሉ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር በመልካም መንገድ ላይ እየተጓዙ ያሉ ሰዎች ናቸው ወይ? መልሱ ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ መመዘኛዎቹ የተሳሳቱ ናቸው፡፡

ሁላችን በእድገት ላይ ያለን ነን፡፡ ሁላችን በግንባታ ላይ ያለን መንፈሳዊ ሕንጻዎች ነን፡፡ እናም ከሕይወታችን ፍጹም ነገር መጠበቅ ስላለንበት ሁኔታ በትክክል ካለመገንዘብ የሚመጣ ነው፡፡ ሕይወታችን በብዙ ውጣ ውረድ የተሞላች ናት (ኢዮብ 7፣1)፡፡ መውደቅና መነሳት፣ መድከምና መበርታት፣ መሳቅ እና ማዘን የሕይወቶቻችን መገለጫዎች ናቸው፡፡ እናም ከእግዚአብሔር ጋር አብሮ ስለመጓዝ ስናወራ፣ ከሃጢአት ፈጽሞ ነጻ የሆነ ሕይወት ወይም አልጋ በአልጋ ስለሆነ መንገድ እያወራን ስላለመሆኑ መጀመሪያ ግንዛቤ መውሰድ ጠቃሚ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር አብረን እየትጓዝን መሆናችንን ፍንጭ የሚሰጡ አንዳንድ ነገሮች ከዚህ በታች ቀርበዋል፦

  • የማንንም እርዳታ ከመጠየቃችን በፊት አስቀድመን ፈጣሪያችንን በጸሎት እንጠይቃለን፣ “አቤቱ፥ በመልካሙ ጊዜ ጸሎቴ ወደ አንተ ነው፤ አቤቱ፥ በምሕረትህ ብዛት በማዳንህም እውነት አድምጠኝ።” (መዝ 69፡13)
  • የእግዚአብሔርን ቃል ለማንበብና ለማጥናት ረሃብ ይኖረናል፣ “ከአፉ ከወጣው ትእዛዝ አልራቅሁም፣ የአንደበቱን ቃል ከእለት እንጀራዬ አብልጬ ይዣለሁ፡፡” (ኢዮብ 23፡12 አ.መ.ት.)
  • ስለውጫዊው ሳይሆን ስለውስጣዊው የልብ ዝንባሌያችን እና ምኞቶቻችን ከፍተኛ ትኩረት እንሰጣለን፣ “በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ፤ ወይስ ምናልባት የማትበቁ ባትሆኑ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ እንዳለ ስለ እናንተ አታውቁምን?” (2ቆሮ 13፡5)
  • በአለም ካሉትን አለማዊ ነገሮች እለት እለት እየራቅን እንሄዳለን፣ “የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።” (ሮሜ 12፡2)
  • በቀላሉ አንበሳጭም፣ “በነፍስህ ለቍጣ ችኩል አትሁን፥ ቍጣ በሰነፍ ብብት ያርፋልና።” (መክ 7፡9)
  • በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ስናልፍ ከመስጋት ይልቅ በእርሱ ተስፋ እናደርጋለን፣ “ለእግዚአብሔር ተገዛ ተስፋም አድርገው። መንገድም በቀናችለትና ጥመትን በሚያደርግ ሰው አትቅና።” (መዝ 37፡7)

እነዚህም ነገሮች ቢሆኑ በሕይወታችን የሚቋረጡበት ጊዜ ሊመጣ ይችላል፡፡ ያ ማለት በጊዚያዊነት ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያለን ሕብረት ታውኳል ማለት እንጂ ድነታችንን (ደኅንነታችንን) አጥተናል ማለት አይደለም፡፡ ይህን ለማደስ ንስሃ መግባትና ትጋታችንን መቀጠል ነው፡፡ ትግሉ እና ውጣ ውረዱ እስከ ሕይወታችን ዘመን ፍጻሜ የሚቀጥል ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን አንድ መርሳት የሌለብን ነገር አለ፡፡ ተስፋችንም ሆነ መተማመናችን በእኛ ጥረትና ትጋት ላይ ሳይሆን በእርሱ ጸጋ ላይ መሆን አለበት፡፡ በእኛ የጀመረውን መልካም ሥራ እስኪፈጽም ድረስ ከእኛ ጋር እንደሚሆን የተናገረውን ተስፋ አምነን በትእግስት ሩጫችንን እንሮጣለን ፡፡ “በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንዲፈጽመው ይህን ተረድቼአለሁና፤” (ፊል 1፡6)

አዳነው ዲሮ

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading