ኢየሱስ የዳዊት ልጅ ነው ማለት ምን ማለት ነው?

ኢየሱስ ፍጹም አምላክ፣ ፍጹም ሰው ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ከሚነሱ በርካታ ጥያቄዎ መካከልለ አንዱ፣ “ኢየሱስ እንዴት የዳዊት ልጅ ሊሆን ይችላል?” የሚለው ነው፡፡ በአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ውስጥ ኢየሱስን፣ “የዳዊት ልጅ” በማለት የሚገልጹ አስራ ሰባት ጥቅሶች እናገኛለን፡፡ ይህ አገላለጽ ጥያቄ የሚያጭርበት ዋነኛ ምክንያት፣ ዳዊት ኢየሱስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከመወለዱ 1,000 ዓመታት በፊት ገደማ የኖረ ሰው መሆኑ ነው፡፡ በ 2ኛ ሳሙኤል 7፡12-16 ውስጥ በትንቢት የተገለጸውና ከዳዊት ቤት እንደሚነሳ ተስፋ የተባለው መሲህ፣ ኢየሱስ ነው፡፡ ማቴዎስ በወንጌሉ የመጀመሪያ መዕራፉ ላይ፣ የኢየሱስ ሕጋዊ አባት (legal father) የነበረውን የዮሴፍን የዘር ሐረግ በማስረጃነት በመጥቀስ፣ ኢየሱስ በሰውነቱ የአብርሃምና የዳዊት ዘር እንደሆነ ገልጿል፡፡ በሉቃስ መዕራፍ 3 ላይ የሰፈረው የኢየሱስ የትውልድ ሐረግ ደግሞ የኢየሱስን የትውልድ ሐረግ በእናቱ ማርያም በኩል የሚቆጥር ነው፡፡ ኢየሱስ፣ በዮሴፍ በኩል በዮሴፍ ሕጋዊ አባትነት ምክንያት በማሪያም በኩል ደግሞ በደም፣ ከዳዊት ዘር ነው (ሮሜ 1፣3)፡፡

በመሠረቱ፣ “የዳዊት ልጅ” የሚለው ማዕረግ ከአካላዊ የትውልድ ሃረግ መግለጫነት የዘለለና የ “መሲሐዊ ማዕረጉ” ስያሜ በግለጫ ነው፡፡ ሰዎች ኢየሱስን በ “ዳዊት ልጅ” ስያሜ ሲጠቅሱ፣ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው ነፃ አውጪ (ታዳጊ) እና የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች ፍጻሜ መሆኑን ማመልከታቸው ነው፡፡
ኢየሱስ፣ ብዙ ጊዜ ከእርሱ ምሕረትን ወይም ፈውስን በሚሹ ሰዎች፣ “የዳዊት ልጅ ሆይ” በሚል መጠሪያ ተጠርቷል፡፡ ፈሪሳውያን ግን፣ እውሮች እንኳ ያዩት የነበሩትን እና እነርሱ ደግሞ እድሚያቸውን በሙሉ ይጠብቁት የነበረውን ይህን እውነት በትዕቢታቸው ምክንያት ሊያዩት አልቻሉም ነበር፡፡ ይገባናል ብለው ያስቡት የነበረውን ክብር ከኢየሱስ ስላላገኙ በእጅጉ ይጠሉት ነበር፡፡ ከዚህም የተነሳ፣ ሰዎች ኢየሱስን እንደ አዳኛቸው ሲቀበሉት ሲያዩ በመበሳጨት (ማቴዎስ 21፣15) ሊያጠፉት ያሴሩበት ጀመር (ሉቃስ 19፣47)፡፡
ኢየሱስ፣ “የዳዊት ልጅ” ስለሚለው ማዕረግ ምንነት ጸሐፍትንና ፈሪሳውያንን፣ “ዳዊት ራሱ (ክርስቶስን) ‘ጌታ’ ካለው፣ እንዴት ተመልሶ ልጁ ይሆናል?” ሲል ሞግቷቸው ነበር (ማርቆስ 12:35-37፤ መዝ 110:1)፡፡ የሕጉ አስተማሪዎች ግን ለዚህ ጥያቄ መልስ ሊሰጡ አልቻሉም፡፡ ኢየሱስ፣ በዚህ መንገድ የአይሁድ መሪዎች ለማስተማር የማይበቁና ብሉይ ኪዳን ስለ መሲሁ እውነተኛ ማንነት የሚናገረውን ጠንቅቀው የማይገነዘቡ መሆናቸውን በመግለጡ ከእርሱ ይበልጡኑ እንዲርቁ አደረጋቸው፡፡
ኢየሱስ በማርቆስ 12:35 ጥያቄ ውስጥ፣ መሲሁ ከዳዊት ዘርነት ያለፈ መሆኑን ሊያስገነዝባቸው ፈልጎ ነበር፡፡ ዳዊት መሲሁን (ክርስቶስን) “ጌታ” ብሎ ከጠራው፣ መሲሁ ከዳዊ የሚበልጥ መሆኑን ያሳያል፡፡  ኢየሱስ በዮሐንስ ራዕይ 22:16 እንደተናገረው፣ እርሱ “የዳዊት ሥርና ዘር” ነው፡፡ ይህም ማለት ክርስቶስ የዳዊት ዘር ብቻ ሳይሆን የዳዊት ፈጣሪም ጭምር ነው፡፡ ሥጋን ከለበሰው ከእግዚአብሔር ልጅ በቀር ይህን ሊል የሚችል ማንም የለም፡፡

ምንጭ፣ https://www.gotquestions.org/

ጸሐፊ፣ አዳነው ዲሮ

1 thought on “ኢየሱስ የዳዊት ልጅ ነው ማለት ምን ማለት ነው?”

  1. ዮሴፍ እንዴት የኢየሱስ ህጋዊ አባት /legal father/ ይባላል? ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ የተፀነስ ነው፡ ስለዚህ
    የዮሴፍ ልጅ አይደለምም አይሆንምም

Leave a Reply to Solomon FollaCancel reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading