እያንዳንዱ ክርስቲያን በልሳን መናገር አለበት?

ከታሪክ አንፃር በልሳኖች መናገር ምን ይመስል እንደነበረ ለመናገር አስቸጋሪ ነው፡፡ ከሐዋሪያት ሥራ ምዕራፍ 2 አንጻር ልሳን ያለምንም ቅድመ ትምሕርት የሰዎችን ቋንቋ የመናገር ተዓምር ይመስላል፡፡ በ 1ኛ ቆሮንቶስ ውስጥ ደግሞ ልሳን በምድር ላይ የማይነገር (አንዳንዶች እንደሚያስቡትም የመላእክትን ቋንቋ) መናገር ይመስላል፡፡

በልሳኖች የመናገር ስጦታ በሐዋሪያት ሥራ ውስጥ አማኞች በመንፈስ ቅዱስ ከመሞላታቸው ወይም መጠመቃቸው ጋር ተያይዞ ከመቅረቡ (ሐዋ 2 4 ፣ ሐዋ 10፡46 እና ሐዋ 19፡6 ይመልከቱ) የንጻር፣ አንዳንድ ክርስቲያኖች በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ እያንዳንዱ አማኝ በልሳኖች የመናገር ስጦታ ሊኖረው ይገባል ብለው እንዲያስቡ አድርጓቸዋል፡፡

ሆኖም፣ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ የምናነባቸው እነዚያ ታሪኮች ትረካዎች (descriptive) (ማለትም በጊዜው ክርስቲያኖች ያደርጉት የነበረውን ነገር ያሚዘግቡ) እንጂ ትእዛዞች (descriptive) ስላይደሉ ርዕሰ ጉዳዩን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ማገናዘብ ይኖርብናል፡፡ 

የተነሳንበት ጥያቄ መልስ በግልጽ በ1 ቆሮንቶስ 12፡7-11 ውስጥ ተካቶ ይገኛል፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ ጳውሎስ አንድ አካል ስትሆን ብዙ ብልቶች ስላሏት የክርስቶስ አካል ወይም ቤተ ክርስቲያን ስጦታዎች ያወራል፡፡ ክፍሉ፣ ብልቶች በተሰጣቸው ስጦታ እንዴት አካሉን እንደሚያንጹ የሚያሳይ ነው፡፡ 

  “ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ለጥቅም ይሰጠዋል። ለአንዱ ጥበብን መናገር በመንፈስ ይሰጠዋልና፥ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እውቀትን መናገር ይሰጠዋል፥ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፥ ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፥ ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ፥ ለአንዱም ትንቢትን መናገር፥ ለአንዱም መናፍስትን መለየት፥ ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፥ ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም ይሰጠዋል፤ ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል።”

በዚህ ክፍል ውስጥ ጳውሎስ የቆሮንቶስን ቤተክርስቲያን (እና እኛንም) እያንዳንዱ የአካል ክፍል (ብልት) የተለያየ ቢሆንም እያንዳንዱ ለአካሉ እድገት አስፈላጊ መሆኑን ይናገራል፡፡

በመቀጠልም፣ “ሁሉ ሐዋርያት ናቸውን? ሁሉስ ነቢያት ናቸውን? ሁሉስ አስተማሪዎች ናቸውን? ሁሉስ ተአምራትን ይሠራሉን? ሁሉስ የመፈወስ ስጦታ አላቸውን? ሁሉስ በልሳኖች ይናገራሉን? ሁሉስ ይተረጉማሉን?” ሲል ጥያቄ ያነሳል(1ኛ ቆሮ 12፡29-30)፡፡

ጳውሎስ እነዚህን ቃላት በጻፈበት ቋንቋ (በጥንታዊው ግሪክ) ጥያቄዎቹ ሁሉ በአሉታዊ ቅርጽ የተጻፉ ናቸው፡፡ በሌላ አገላለጽ እነዚህ ጥያቄዎ በሚከተለው መንገድ ሊቀርቡ ይችላሉ፡- “ሁሉም ሐዋርያት አይደሉም፤ አይደል? ሁሉ በልሳኖች አይናገሩም፤ አይደል? መልሱም – አዎ፣ ሁሉም ሐዋሪያት አይደሉም፡፡ አዎ፣ ሁሉም በልሳኖች አይናገሩም ይሆናል፡፡ ሁላችንም አንድ ዓይነት ስጦታዎች የለንም፡፡ ቤተ ክርስቲያን አንድ ዓይነት እና ወጥ እንድትሆን አልተፈለገም፡፡ ሁላችን በክርስቶስ አካል ውስጥ ልዩ ስፍራ አለን፡፡ 

ሲጠቃለል፣ “እያንዳንዱ ክርስቲያን በልሳን መናገር አለበት?” ወይ ለሚለው ጥያቄ መልሱ የለበትም የሚል ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን ይህ መልስ ወደ ሌላኛው ጽንፍ ይዞን ሊሄድና በልሳኖች መናገር ያለውን ጠቀሜታ አሳንሰን እንድናይ ሊያደርገን አይገባም፡፡ እዚህ ላይ፣ ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮ 14፡5 ውስጥ “ሁላችሁ በልሳኖች ልትናገሩ እወድ ነበር” ሲል ምኞቱን የገለጽበትን ክፍል ማሰቡ ጠቃሚ ነው፡፡ በልሳኖች የመናገር ስጦታ እግዚአብሔር ለብዙ ልጆቹ የሰጠው መልካም ስጦታ ነው፤ እናም በዚህ ስጦታ ለመጠቀም መፈለግ ምንም ችግር የለውም። 

1 thought on “እያንዳንዱ ክርስቲያን በልሳን መናገር አለበት?”

  1. በፕሮቴስትአንት እየተነገረ ያለው የልሳን ቋንቋ በአለም ወስጥ ያለ ቋንቋ ከሆነ ሊታወቅ ወይም ሊተረጎም የሚችል መሆን የለበትም ወይ?

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading