ስለ ጋብቻ ምክር (1ኛቆሮ.7:1-16) 

ጥያቄ 8. በምን ዓይነት መንገድ ነው ይህ ትምህርት ዛሬ ላሉት ወጣቶች፥ ለተጋቡት፥ ወዘተ ጠቃሚ ሊሆን የሚችለው? 

ጥያቄ 9. በቁጥር 1 ላይ «ከሴት ጋር አለመገናኘት ለሰው መልካም ነው» ሲል ሐዋርያው ምን ማለቱ ነው? 

ጥያቁ 10. ዝሙትን ለማስወገድ ጋብቻ ተሰጥቷል በማለት ሐዋርያው ሲያስተምር የጋብቻ ዓላማ ለዚህ ብቻ ነው ማለት ነው? ለመልስህ ከመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ ስጥ፡፡

ጥያቄ 11. በቁጥር 4 ላይ ባል በገዛ ሥጋው ላይ ሥልጣን የለውም» ሲል ምን ማለቱ ነው? 

ጥያቄ 12. በቁጥር 6 ላይ “እንደፈቃድ እንጂ እንደ ትእዛዝ አልልም” ሲል ምን ማለቱ ነው? 

ጥያቄ 13. ከቁጥር 10-15 ባለው ክፍል ወስጥ «አትለያይ»፥ «አይተዋት» ፥ «አትተወው»፥ «ቢለይ» እያለ ሲናገር ጋብቻንና መፋታትን በመመልከት ለእነዚህ ቃላት ትርጉም ስጥ። 

ከዚህ በፊት እንደተጠቀሰው የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ሐዋርያውን ብዙ ጥያቄዎች ጠይቀውታል። ለመጀመሪያው ጥያቄአቸው በዚህ ክፍል መልስ መስጠት ይጀምራል። 

ቁጥር 1 እና 2:- በባሕላቸው አለማግባት እንደ ትልቅ ጽድቅ ይቆጠር ስለነበር አለማግባት ወይም “ከሴት ጋር አለመገናኘት” መልካም ነው፤ ብሎ ሙሉ በሙሉ ሳይሆን በመጠኑ በሃሳቡ ይስማማል። ግን ሰው ይህን መልካም ነገር አገኛለሁ ብሎ ራሱን ባለመግዛት በዝሙት እንዳይጠመድ ያስጠነቅቃል። 

ሰው እግዚአብሔር የሰጠውን መውጫ ንቆ ቢጠመድ በእግዚአብሔር ፍርድ ሥር ይወድቃል። ያለሚስት ለመኖር ሰው ራስን የመቆጣጠር ችሎታ ከእግዚአብሔር የተሰጠው መሆኑን ማጣራት አለበት፤ (ቁጥር 7 እና ማቴ.19፡11-12 ተመልከት)። 

“ለራሱ ሚስት ትኑረው፤ ለራስዋ ባል ይኑራት” ሲል አንድ ወንድ ለአንድ ሴት እንጂ «ለራሱ ሚስቶች ይኑሩት» ባለማለት ከአንድ በላይ ማግባትን ይከለክላል። 

ቁጥር 3-4:- «ሚስት በገዛ ሥጋዋ ላይ ሥልጣን የላትም፤ ባል በገዛ ሥጋው ላይ ሥልጣን የለውም»። ይህ አነጋገር በባልና ሚስት መካከል እኩልነት ያለ መሆኑን ያስገነዝበናል። ባል ሚስቱን የራሱ ስሜት ማርኪያ ዕቃ አድርጎ መጠቀም የለበትም። ነገር ግን ራሱን ለሚስቱ እርካታ እንደ አገልግሎት አድርጎ ማቅረብ እንዳለበት ይህ ሐዋርያዊ ቃል ያስተምረናል። ሚስትም ለባልዋ እንዲሁ በማድረግ በጋብቻቸው መተሳሰብን ማሳየት አለባቸው። 

ጥያቄ 14. ይህ ነገር እንዴት ነው ዛሪ ስለ ባልና ሚስት ካለው ሃሳብና ባሕል ጋር ሊቃረን የሚችለው? 

ቁጥር 5፡- “እግዚአብሔርን አገለግላለሁ” ብሉ ሰው ሚስቱን ቢተው አገልግሎቱ በአግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት አይኖረውም። በቃሉ የነገረንን ትእዛዝ በመናቅ እግዚአብሔርን ማገልገል አንችልም። በዚህ ላይ ሐዋርያው ባልና ሚስት መለያየት እንደሌለባቸው ያዛል። መለየት የተፈቀደው ለጾምና ለጸሎት ብቻ ያውም በስምምነትና ለአጭር ጊዜ ብቻ መሆኑን ማስተዋል አለብን። ባልየው ወይም ሚስትየዋ ያሰቡት ሃሳብ ሌላውን ቅር ካሰኘ ሃሳቡ መሰረዝ አለበት። 

«ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ» በማለት ሐዋርያው ስለመለያየት ወይም ስለመከላከል ይናገራል። ባል ወይም ሚስት በሆነው ምክንያት እርስ በርስ ቢከለከሉ፥ የተከለከለው ወገን በሰይጣን ፈተና ቢወድቅ የወደቀውም፥ በመከልከል ፈተናውን ያስከተለውም በእግዚአብሔር ፊት ጥፋተኛ ናቸው። ስለዚህ ከላይ በቁጥር 3 እና 4 ላይ የተሰጠውን መምሪያ ባልና ሚስት በጥንቃቄ መከተል አለባቸው። 

ቁጥር 6፡- ሐዋርያው ለጾምና ለጸሎት እርስ በርስ መለያየት እንደሚችሉ በቁጥር 5 ላይ ተናግርአል። ይህን ንግግሩን በፈቃዳቸው እንጂ ነገሩን አንደ ትእዛዝ ቆጥረው መጾምና መጸለይ ስላለብን መለያየት አለብን» ብለው የግዴታ እርምጃ መውሰድ እንዳይጀምሩ ቁጥር 6ን ጨምሮ ይጽፋል። 

ቁጥር 7ን ከላይ ቁጥር 2ን ስንዘረዝር ጠቅሰነዋል። ሳያገቡ በንጽሕና መኖር ለሁሉ ያልተሰጠ መሆኑን ያስጠነቅቃል። እርሱ ራሱም ይህ ሳያገቡ በንጽሕና የመኖር ስጦታ እንደተሰጠው ይመሰክራል። 

ከቁጥር 8-9፡- በዚህ ክፍል ውስጥ ሐዋርያው ላላገቡና ለመበለቶች ምክር ይሰጣል። ሳያገቡ መኖር ተመራጭ ለመሆኑ ጌታችንም በወንጌል ተናግሯል፤ ነገር ግን ይህ ለተሰጣቸው እንጂ ለሁሉ ስላልሆነ ሰው ባለማግባት ራሱን በፈተና ላይ መጣል የለበትም። ማግባት አለበት። ይህ ትምህርት በወንጌል ጌታችን እንዳስተማረው ስለተጠቀሰ ሐዋርያው «እኔ ግን አላዝም ጌታ እንጂ» ይላል። ይህን ሲል በሐዋርያነቱ ለክርስቲያኖች ትእዛዝ ለመስጠት መብት የለውም ማለት አይደለም። 

ቁጥር 10 እና 1 1:- ባልና ሚስት መለያየት የለባቸውም። መለያየት ቢመርጡ ግን ሳያገቡ በነጠላ ኑሮ መኖር አለባቸው። «ሚስትም ከባልዋ አትለያይ፤ ባልም ሚስቱን አይተዋት።» ይህ ትእዛዝ ሁለቱም ክርስቲያኖች ለሆኑ ነው የተሰጠው፡፡ ሐዋርያው ይህ ትእዛዝ በጌታችን የተሰጠ መሆኑን ይናገራል። የጌታም ትምህርት በወንጌል ውስጥ ተጽፎ ይገኛል፤ (ማቴ. 5፡32፤ 19፡3-9)። እንግዲህ በዚህ ላይ የምንመለከተው ጋብቻን መተው አንድ ራሱን የቻለ በደል ነው፤ «ሚስትም ከባልዋ አትለያይ፤ ባልም ሚስቱን አይተዋት።» ግን ከዚህ የበለጠው ሁለተኛው ደረጃ በደል አለ፤ ያም እንቢ ብሉ ከተለያዩ በኋላ ሌላ ማገባት ነው። ይህንንም ሐዋርያው «ብትለያይ ግን ሳታገባ ትኑር ወይም ከባልዋ ትታረቅ » ብሎ ይከለክላል። 

ስለመፋታት ሊነገር ያለውን ሁሉ ሐዋርያው እዚህ አይዘረዝረውም። ለምሳሌ ጌታችን «ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን የሚፈታ» ያለውን ሐዋርያው አይጠቅስም። ያልጠቀሰበትም ምክንያት እዚህ የሚናገረው የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የጠየቁትን ለመመላስ ብቻ እንጂ ስለ ጋብቻ ዝርዝር ትምህርት ለመስጠት ስላልሆነ ነው። እኛ ግን ያንንም ጨምረን ማየት አለብን። 

ከቁጥር 12-16፡- የተቀላቀለ ጋብቻ ማለት ባል ወይም ሚስት ሳያምኑ ሲቀሩ ነው። በመጀመሪያው ሁለቱም አማኞች ሳይሆኑ በኋላ ግን አንደኛው በወንጌል ካመነ ማለቱ ነው እንጂ ክርስቲያን ያላመነችውን በማግባት የተቀላቀለ ጋብቻ ማለቱ ይደለም። 

እንዲህ ባለ ጋብቻ ውስጥ የማያምነው ወይም የማታምነው ለመለየት ብትፈልገ አማኝ መጨነቅ የለበትም። “ወንድም ቢሆን ወይም እህት እንዲህ በሚመስል ነገር አይገዙም።” አይገዙም ማለቱ አይታሰሩም፥ ነፃ ናቸው ማለቱ ነው። ይህ ከሆነ አማኙ ሌላ ለማግባት እንደተፈቀደለት እንገነዘባለን። ያም በጌታ የሆነ ጋብቻን ለመመስረት እድል ስለሚሰጥ የማያምን ባለማግባት ዳግምኛ በተመሳሳይ ወጥመድ መውደቅ የለበትም። ይሁን እንጂ አማኝ ለጋብቻው መፍረስ ምክንያት መሆን የለበትም። «ያላመነች ሚስት ከእርሱ ጋር ልትቀመጥ ብትስማማ አይተዋት።» አማኝ “አሁን እኔ አማኝ ነኝ አንቺ ግን አታምኚም፤ ስለዚህ ከአንቺ ጋር በጋብቻ ታስሬ መኖር አልፈልግም” ሊል አይገባውም። እንዲህ ታግሶ መኖር ምናልባት የማያምነውን ወገን ወደ እምነት ሊያመጣ ይችል ይሆናል፤ «አንቺ ሴት ባልሽን ታድኚ እንደሆንስ ምን ታውቂያለሽ?»። 

ምናልባት ከማያምን ጋር በጋብቻ ታስሮ መኖር አማኝን የሚያረክስ መስሉ ታይቷቸው ሳይሆን አይቀርም፤ ምክንያቱም ሐዋርያው «ያላመነ ባል በሚስቱ ተቀድሷልና» ይላል። ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ፥ አማኝ ከማያምን መለየት አሁንም በአንዳንዶች ዘንድ እንደሚገኝ ይሰማል። ማንም በመንፈስ ቅዱስ ተመራሁ ብሎ ይህንን የሐዋርያውን ቃል በመናቅ ከማታምን ሚስቱ መለየት የለበትም። ይህ ከፈሪሳውያን የበለጠ ግብዝነትና የዲያብሎስ ትምህርት እንጂ የመንፈስ ቅዱስ ትምህርት አይደለም። አማኝ ከማያምን ባሏ ጋር በጋብቻ ብትኖር የእርሷ ቅድስና እሱን ይባርከዋል እንጂ የእርሱ አለማመን እሷን አያረክሳትም። 

ይህ የመቀደስ አነጋገር ከአማኝ ልጆች ቅድስና አንፃር የተነገረ ነው። «ልጆቻችሁ የተቀደሱ ናቸው»። የአማኝ ልጆች በወላጆቻቸው እምነት ምክንያት የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ወራሾች በመሆናቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፤ (ዘፍ.17:7)። ስለሆነም እንደ ክርስቲያን በጌታ ትምህርትና ተግሣጽ ሊኮተኮቱ ይገባቸዋል፤ (ኤፌ. 6፡4)፡፡ ሆኖም ይህ ማለት ክርስትና በዘር ይተላለፋል ማለት አይደለም። የአማኝ ልጅ ራሱ ጌታን በግሉ ካልተቀበለ የወላጆቹ እምነት አያድነውም፤ (ሕዝ. 18፡10-13)፡፡

(ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading