1ኛ ቆሮ. 10፡1-13

ጥያቄ 1. ከቁጥር 1-5 ባለው ክፍል ውስጥ እሥራኤላውያን ወደ ተስፋው ምድር ጉዞ መጀምራቸው ግን ሳይደርሱ በምድረ በዳ ማለቃቸው ከቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ጋር ምን መመሳሰል አለው? 

ጥያቄ 2. ክፉ ነገር የሚለው ምኑን ነው? 

ጥያቄ 3. ቁጥር 12ን ከበፊተኛው ጥናት ጋር በማወዳደር ዝርዝር መልስ ስጥ።

ጥያቄ 4. በቁጥር 13 ላይ “ፈተና” የሚለው ምንድነው? በተለይ ከቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ሁኔታ ጋር በማወዳዳር ግለድ። 

በምዕራፍ 9 መጨረሻ ላይ ያገኘነው ሀሳብ ሐዋርያው “የተጣልሁ እንዳልሆን” በማለት የሚያደርገውን ጥንቃቄ ነው። አሁንም ያንኑ ሀሳብ በመቀጠል ከእሥራኤላውያን ታሪክ እየጠቀሰ ያስተምራል። 

እሥራኤላውያንም ወደ ተስፋው አገር እንደቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ጉዞ ጀምረዋል። ነገር ግን መጀመራቸው አላዳናቸውም፤ ጣኦትን በመውደዳቸው በምድረ በዳ ወድቀው ቀሩ እንጂ የተስፋውን አገር አልወረሱም። የቆሮንቶስም ክርስቲያኖች እንዲሁ መጠንቀቅ አለባቸው፤ “የቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ፤” (ቁጥር 12)። 

እሥራኤላውያን በደመናና በባሕር ተጠመቁ ይላል። ጥምቀት የአዲስ ኪዳን ምልክት ነው። ስለዚህ በብሉይ ለነበረው ደህንነት የምልክት አነጋር ያደርገዋል፤ (ዘፀ.14፡31)፡፡ ምናልባት የቆርንቶስ ሰዎች በጥምቀታቸው ይመኩ ይሆናል (1ኛ ቆሮ. 1፡13-17)። «የጥምቀትማ ነገር እሥራኤላውያንም ተጠምቀው ነበር፤ ግን ቃሉን ከልባቸው ተቀብለው እስከመጨረሻ ስላልጸኑ በምድረ በዳ ወድቀው ቀሩ እንጂ የተጠመቁለትን ተስፋ አላገኙም› እንደማለት ነው። 

መጠመቅ ማለት መተባበር እንደሆነ ይህ ቃል ይመሰክራል፤ “ሙሴንም ይተባበሩ ዘንድ ተጠመቁ”። ሙሴ የክርስቶስ ምሳሌ ስለነበር እርሱ ከምሳሌው ጋር በጥምቀታቸው እንደነበሩ እኛም በጥምቀታችን ከክርስቶስ ጋር እንተባበራለን፤ (ሮሜ 6፡3 እና 4)። 

ጥምቀትን ምሳሌ አድርጉ ለእሥራኤላውያን አንደተናገረው ሁሉ ቅዱስ ቁርባንንም እንዲሁ ይጠቀምበታል፤ (ቁጥር 3 እና 4፤ ዘፀ.16፡4 እና 13፤ ዘኁ.17፡1-7፤ 10፡2-13)። መናውና ከአለቱ ውስጥ የወጣው ውኃ ኢየሱስ በቅዱስ ቁርባን ውስጥ የሰጠውን መንፈሳዊ በረከት ያመለክታሉ። አሁንም ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ከቅዱስ ቁርባን ተሳታፊ መሆን የደህንነት ዋስትና እንደማይሰጥ ግን በክርስቶስ ጸንቶ መቆም እንደሚያስፈልግ ያስረዳል። 

በቁጥር 6 ላይ ክፉ ነገር የሚለው ያመለኩትን ጣዖት ማለቱ ነው። የቆርንቶስ ክርስቲያኖች በእውቀታቸው እየተመኩ ከጣዖት ጋር መቀረረብን ስለያዙ ሊያስጠነቅቃቸው ይህን ምሳሌ ከእሥራኤላውያን ተውሶ ለእነርሱ ያውለዋል። 

ቁጥር 7ን ከዘፀ.32፡6 ጋር አስተያይ። ቁጥር 8ን ከዘኁ.25፡1-9 ጋር አወዳድር። ቁጥር 9ን ከሐዋ.5፡9 ጋር አስተያይ። አለመፈታተን በዚህ ቦታ «እስኪ ይህን ባደርግ ምን ያደርገኝ ይሆን» እያሉ በኃጢአት መጽናት ማለት ነው። 

ስለዚህ የቆሮንቶስም ክርስቲያኖች ከጣዖት (ቁጥር 7)፣ ከመሴሰን (ከጣዖት አምልኮ ጋር የተያያዘ የዝሙት ሥራ ቁጥር 8)፣ ከመፈታተን (ቁጥር 9)፣ ከማጉረምረም (ቁጥር 10) መጠበቅ ነበረባቸው። አለበለዚያ በእሥራኤል ላይ የደረሰው የእግዚአብሔር ቁጣ በእነርሱ ላይ ይደርሳል። 

ጥያቄ 5. የእግዚአብሔርን ፍርድ በአንተ ላይ ሊያመጣ የሚችል እዚህ ከተጠቀሱት ኃጢአቶች መካከል ወይም ሌላ በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የሚታየው የትኛው ዓይነት ነው? 

ቁጥር 11 ላይ የእሥራኤል ጉዳይ እኛን ሊያስጠነቅቀን ይገባል። እኛም የምናመልከው አምላክ ያ በእነርሱ ሥራ ባለመደሰት የፈረደባቸው ስለሆነ እግዚአብሔርን እንፍራ። “ዘመኑ የተለያየ ነው፤ እኛ በአዲስ ኪዳን ስላለን ይህ ዓይነት ተግሣጽ አይደርስብንም” በማለት ራሳችንን ማታለል የለብንም፡፡ ያ በእነርሱ ላይ የደረሰው ተጽፎ የተቀመጠው እኛን ሊያስጠነቅቀን መሆኑን መገንዘብ አለብን። 

ቁጥር 12 ሃሳቡን ሰብስቦ ይሰጠናል። በብሉይ ኪዳን ዘመን ይኖሩ የነበሩ ሰዎች እኛ የምናገኛቸውን ብዙዎቹን በረከቶች አያገኙም ነበር። የነቢያት ትንቢቶች በተፈጸሙበትም ወቅት በሕይወት አይኖሩም ነበር። እኛ ግን የምንኖረው ኢየሱስ ከተወለደ፥ ከሞተና ከአረገ በኋላ ባለው ዘመን ውስጥ ነው። ስለዚህም ለእኛ ስለኢየሱስ ዘላለማዊ መንግሥት የተሰጠው ተስፋ እየተፈጸመልን ነው። 

የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በፈተና ውስጥ ነበሩ። ፈተና የሚለው ቃል በግሪክ ቋንቋ እንደስደት ላሉ ከውጭ በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚሰደዱ ችግሮችንም ሊያመለክት ይችላል፡፡ ወይም ከውስጥ ከልባችን ኃጢአት ለመሥራት ስንፈተንም ሊሆን ይችላል። እነዚህ ሁለት ፈተናዎች ብዙ ጊዜ በክርስቲያኖች ላይ ይከሰታሉ። በዚህ ሁሉ ግን በፈተና ውስጥ ላሉ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ብርታቱን ይሰጣል። 

በመጀመሪያ፡- ሁሉም ሰው ይፈተናል። በእኛ ሕይወት ውስጥ የሚያልፉትን ብዙዎቹን ፈተናዎች ከእኛ በፊት የነበሩ ክርስቲያኖች በድል አልፈዋቸዋል። የብሉይ ኪዳንም መድሐፍ በእሥራኤል ታሪክ ውስጥ ፈተና ስላጋጠማቸው ብዙ ሰዎች ይተርካል። 

ሁለተኛ፡- ወደ እኛ የሚመጣውን ፈተና የሚመራውና የሚቆጣጠረው እግዚአብሔር ነው፡፡ ፈተናዎቹም እኛ ልንቋቋመው ከምንችለው በላይ አይደሉም። በፈተናው ውስጥ እንኳን እያለን እግዚአብሔር በድል መንፈስ እንድንጋፈጠው ያደርጋል። ይህንን የሚያደርገው ፈተናውን ከእኛ ላይ ለማስወገድ ሳይሆን በፈተናው ውስጥ ልናልፍበት የምንችልበትን ኃይል ለመስጠት ነው። 

ጥያቄ 6. እግዚአብሔር እንዴት ነው ፈተና እንዳይደርስብህ በማድረግ ፈንታ ኃይሉን ሰጥቶ በፈተና ውስጥ ያሳለፈህ? ብዙ ምሳሌዎችን ስጥ።

(ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

Leave a Reply

%d bloggers like this: