1ኛ ቆሮ. 11፡27-34

ጥያቄ 1. በቁጥር 27 ላይ ሳይገባው ማለት ምን ማለት ነው? 

ማሳሰቢያ፡- ሳይገባው የሚለው ቃል ትክክለኛ ትርጉም አይደለም። ትክክለኛው ትርጉም «በማይገባ መንገድ» ወይም «በማይገባ አኳኋን» ነው። ይህን ትርጉም ተክተህ ጥያቄውን መልስ። 

ጥያቄ 2. በቁጥር 28 ላይ «ራሱን ይፈትን» የሚለውን ከቁጥር 19 ላይ «የተፈተኑት» ከሚለው ጋር በማወዳደር አስተያየትህን ጻፍ። 

ጥያቄ 3. ቅዱስ ቁርባንን በማይባ አኳኋን በወሰዱ በቆርንቶስ ምእመናን ላይ ምን ደረሰባቸው? 

ቁጥር 27፡- «ሳይገባው» የሚለው ቃል ትክክለኛ ትርጉም አይደለም። ትክክለኛው ትርጉም በማይገባ መንገድን ወይም በማይገባ አኳኋን» ነው። ይህም የጌታን እራት በማይገባ መንገድ መካፈል ፍርድን ያስከትላል ማለት ነው። የቆሮንቶስ ሰዎች በጌታ እራት ጊዜ ይፈጽሙት የነበረው መከፋፈል የጌታን እራት በማይገባ መንገድ መቀበል ማለት ነበር። ሌላም ያለአገባብ የጌታ እራት የሚወሰድበት መንገድ አለ፤ ለምሳሌ ሰው በልቡ ጌታን ሳይቀበልና የጌታ ፍርሃት በሕይወቱ ሳይኖር ቢሳተፍ የጌታን እራት በማይገባ መንገድ ይካፈላል። እንዲሁም ክርስቲያን በሕይወቱ ያልተናዘዘበትና ያልተወው ኃጢአት እያለ የጌታን እራት ቢካፈል የጌታን እራት በማይገባ መንገድ ይካፈላል። ነገር ግን ማናችንም ፍዱም ሆነን መቅረብ አንችልምና ሁላችንም ሕይወታችንን ለጌታ በመስጠትና ከበደላችን ንስሐ በመግባት ጌታም ይቅር ብሎ እንደሚቀበለን በእምነት በመረዳት ብንቀርብ በሚገባ መንገድ ተሳታፊዎች እንሆናልን። 

ጥያቄ 4. የጌታን እራት በማይገባ መንገድ ልንካፈል የምንችልበት ሌላ መንገድ ምንድነው? 

ቁጥር 28፡- «ሰው ግን ራሱን ይፈትን» የሚለው ቃል ከቁጥር 19 ጋር ይመሳሰላል። ያም መፈተን ማለት ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን ፈተናውን ማለፍ ማለት ነው። ሰው ራሱን መርምሮ ሕይወቱ ከላይ በተጠቀሰው መንገድ ካልተስተካከለ ፈተናውን አላለፈምና የጌታን እራት መካፈል አይገባውም። ስለዚህ ይህ ራሱን ይፈትን የሚለው ሰው ልቦናውን ይመርምር እንደማለት ነው። 

ቁጥር 29፡- የጌታን ሥጋ አለመለየት ማለት የጌታን እራት እንደተራ ምግብ መቁጠር ነው። በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ይህ በደል ተፈጸመ። የጌታን እራት የግል ማዕድ አድርገው የጌታን አካል የሚያመለክት መሆኑን በተግባራቸው ስለካዱት የጌታ ሥጋ ባለዕዳዎች ሆኑ። 

ከቁጥር 30-32፡- ይህም ስሕተታቸውና ድፍረታቸው የጌታን ፍርድ አስከተለባቸው። ይህ ፍርድ በሕመምና በሞት ተገለጠ። ራስን መመርመር ከዚህ ፍርድ ያድን ነበር። ራስን መመርመር ማለትም ከላይ በተጠቀሰው መንገድ ሰው ራሱን ከማይገባ አቀራረብ ለይቶ በሚገባ ለማቅረብ ሕይወቱን መርምሮ ማዘጋጀት ማለት ነው፡፡ ሰው ይህን ባላማድረጉ በቆሮንቶስ አማኞች ላይ እንደደረሰው በእግዚአብሔር ይገሠጻል። ይህም ተግሣድ የኩነኔ ተግሣድ ሳይሆን እግዚአብሔር የሚወዳቸውን ከጥፋት ለማዳን የሚሰጣቸው የፍቅር ተግሣድ ነው፤ (ዕብ.12፡5-11)። 

ቁጥር 33 እና 34፡- «እርስ በርስ ተጠባበቁ » አንዱ ያለልክ በልቶ ወጥቶ እንዳይበድል ሌላው ደግሞ ተንገዋሎ እንዳያፍር እርስ በርስ እንክብካቤ ማሳየት፤ (ቁጥር 21 እና 22) ማለት ነው። ክርስቲያን አንዱን ሕብስት በመካፈል ከምእመናን ጋር ራሱን ስላቆራኘ የወንድሙ ጠባቂ መሆኑን መዘንጋት የለበትም፤ ( 1ኛ ቆሮ. 10፡17፤ ዘፍ.4፡9)። 

ጥያቄ 5. ሀ/ በቤተ ክርስቲያንህ ሥነ ሥርዓት ውስጥ በእግዚአብሔር ከማመንና ልባችንን ከኃጢአት ከማንጻት ሌላ የጌታን እራት እንድንበላ መሟላት ያለባቸው ሌላ ምን ተጨማሪ ጉዳዮች አሉ? ለ/ እነዚህ ግዴታዎች ወይም ሥነ ሥርዓቶች በምን ላይ የተመሠረቱ ናቸው?

(ምንጭ፤ በትምህርተ መለኮት ማስፋፊያ (ትመማ) መልክ የተዘጋጀ ጽሑፍ፡- በቄስ ኃይሉ መኮንን)

1 thought on “1ኛ ቆሮ. 11፡27-34”

Leave a Reply

%d bloggers like this: