የ1ኛ ሳሙኤል ዋና ዋና ትምህርቶች 

ቀደም ሲል እንደ ጠቀስነው፥ 1ኛ ሳሙኤል በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ስለሚሆን መንፈሳዊ መሪነት የሚናገር መጽሐፍ ነው። የመጽሐፉ መግቢያ ዔሊና ሳሙኤል የተባሉትን ሁለት ካህናት ያነጻጽራል። የእግዚአብሔርን አምልኮ በንጽሕና ባለመጠበቁ እግዚአብሔር ዔሊን ናቀው፡፡ ሳሙኤል ደግሞ ሕዝቡን ከእግዚአብሔር ጋር አስቀድመው ወደገቡት ቃል ኪዳን ለመመለስ በመወሰኑ አከበረው። ሳሙኤልን ልዩ የሚያደርገው በእስራኤል ላይ ሊቀ ካህን፥ ሕዝቡን የሚያስተዳድር መስፍንና የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለሕዝቡ የሚያሳውቅ ነቢይ መሆኑ ነው። እንዲያውም ሳሙኤል የእስራኤልን ሕዝብ ከግብፅ ባርነት እንዲያወጣ ካደረገው ነቢይ ከሙሴ በኋላ የመጣ ተወዳዳሪ የሌለው ነቢይ ነበር።

ቀጥሎም 1ኛ ሳሙኤል ሳኦልና ዳዊት የተባሉት ሌሎች ሁለት መሪዎችን ያወዳድራል። ሁለቱም በእግዚአብሔር የተመረጡ ነበሩ። ሁለቱም ሰዎች የእግዚአብሔርን ቅዱስ መንፈስ ተቀብለዋል። እግዚአብሔር ሁለቱንም ጠላቶቹን ለማሸነፍ ተጠቅሞባቸዋል። እግዚአብሔር ግን የተከበረው በአንዱ ብቻ ሳይሆን በሌላውም ነበር። ሳኦል የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስላልተከተለና በመንፈሳዊ ነገርና በልቡ ንቁ ስላልነበረ፥ በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንዳይሆን እግዚአብሔር ናቀው። በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአቱን አምኖ ከመቀበልና ከመናዘዝ ይልቅ፥ ሁልጊዜ ለድርጊቱ ምክንያት ያቀርብ ነበር። በራሱ ኃይል ለመዋጋት ሞክሮ ነበር። ትኩረቱ በራሱ ዝነኛነት ላይ ብቻ ነበር። በመጨረሻም ሳኦል በእስራኤል ሕዝብ ላይ ጥፋትን በራሱና በልጆቹም ላይ ሞትን አመጣ። በቅንዓቱ ምክንያት የመሪነት ችሎታው በሙሉ ተወሰደበት። 

ዳዊት ግን ተራ የከብቶች ጠባቂ (እረኛ) ቢሆንም እንኳ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለመምራት እግዚአብሔር የሚፈልገው ዓይነት ልብ ነበረው። ዳዊት ድል የሚገኘው በእግዚአብሔር መሆኑን ስለ ተገነዘበ በጦርነት ድልን እንደሚሰጠው በእግዚአብሔር በመታመን ይዋጋ ነበር። ዳዊት እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ንጉሥ ይሆን ዘንድ በቀባው በማንኛውም መሪ ላይ የበቀል እጁን ላለማንሣት ወሰነ። ሳኦልን በመግደል የእርሱን ሞት ለግል ጥቅሙ ሊጠቀምበት ሳይፈቅድ ቀረ። በኋላም እንደምንመለከተው፥ ኃጢአትን በሚያደርግበት ጊዜ ልቡን ወደ እግዚአብሔር የሚያቀናና ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቅርታን የሚጠይቅ እንደ ነበር እናያለን። የዳዊት ታላቅነት በታላቅ ተግባሩ ወይም ያለ ኃጢአት በመሆኑ አይደለም፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን ለመከተል፥ ለእግዚአብሔር ለመታዘዝና በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት በሚሠራበት ጊዜ ንስሐ ለመግባት በነበረው ጽኑ ፍላጎት ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ልክ እንደ ሳኦል የሚሆኑት እንዴት ነው? ለ) ልክ እንደ ዳዊት ያሉ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጥቂት የሆኑት ለምንድን ነው? ሐ) ከሳኦልና ከዳዊት ሕይወት ስለ መንፈሳዊ አመራር የምንማራቸውን አንዳንድ መመሪያዎች ዘርዝር። መ) እነዚህን ነገሮች ከሕይወትህ ጋር የምታዛምደውና በቤተ ክርስቲያንህ ላሉ ሌሎች መሪዎች የምታስተምረው እንዴት ነው?

የውይይት ጥያቄ፥ 1ኛ ሳሙ. 2፡30 አንብብ። ሀ) ይህ ጥቅስ በሳኦልና በዳዊት ሕይወት የተፈጸመው እንዴት ነው? ለ) በቤተ ክርስቲያን ባለህ አመራር ውስጥ እግዚአብሔርን ልታከብር የምትችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች ጥቀስ። ሐ) በቤተ ክርስቲያን ባለህ አመራር ውስጥ የእግዚአብሔርን ስም ልታስነቅፍ የምትችልባቸውን መንገዶች ዘርዝር። 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d