የ2ኛ ሳሙኤል ዓላማዎች 

ሀ. ከዳዊት በኋላ ለሚነሡ ነገሥታትና ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሁሉ እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ የእርሱን ሕዝብ እንዴት መምራት እንደሚቻል ምሳሌ ለመስጠት ነው። ዳዊት ከእርሱ በኋላ የሚነሡ መሪዎች፣ ልጆቹም ጭምር ሕዝቡን እንዴት መምራት እንዳለባቸው ሊከተሉት የሚገባ ምሳሌ ነበር። በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ የተሾመ ምድራዊ መሪ፥ ከሰማያዊው ንጉሥ ሥልጣን በታች እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ እንዴት እንደሚመራ የሚያሳይ ሕያው ምሳሌ ነው። የሚያሳዝነው ግን ከዳዊት ቀጥሎ ከነገሡት ዝርያዎቹ ጥቂቶቹ ብቻ የዳዊትን መንገድ ስለተከተሉ፥ ሕዝቡ ፈጥነው በኃጢአት ወደቁና በእግዚአብሔር ተፈረደባቸው።

የውይይት ጥያቄ፡ ሀ) በቤተ ክርስቲያንህ እንዴት ማገልገል እንዳለብህ መልካም ምሳሌዎች የሆኑህ የቤተ ክርስቲያን ወይም የሌሎች አብያተ ክርስቲያናት መሪዎችን ዘርዝር። ለ) እነዚህን ሰዎች በሕይወታቸውና በሥራቸው መልካም መሪዎች ያደረጋቸው ምንድን ነው? 

ለ. ዳዊት በእስራኤል ሕዝብ ላይ ሕጋዊ የሆነ መሪ እንደ ነበር ለማሳየት ነው። 1ኛ ሳሙኤል እና 2ኛ ሳሙኤል ዳዊት በእግዚአብሔርም ሆነ በሕዝቡ የተመረጠ ትክክለኛ መሪ እንደነበረ የሚያሳዩ በርካታ ሥዕላዊ መግለጫዎችን ለአይሁድ ይሰጣሉ። ንጉሥነቱን ያገኘው በማታለል፥ በሻጥር ወይም በኃይል አልነበረም። የመንግሥቱን ሥልጣን ለማግኘት የሳኦልን ቤተሰብ አላጠፋም። 

ሐ. እግዚአብሔር ከዳዊት ቤተሰብ ጋር ልዩ የሆነ ቃል ኪዳን በማድረግ፥ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ይሆኑ ዘንድ ግልጥ የሆነ

መብት እንደሰጣቸው ለማሳየት ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ 2ኛ ሳሙ. 7፡8-16 አንብብ። ሀ) እግዚአብሔር ለዳዊት የሰጠውን ልዩ ልዩ ቃል ኪዳኖች ዘርዝር። ለ) ዘፍ. 12፡1-3 አንብብ። እነዚህ ሁለት ቃል ኪዳኖች የሚመሳሰሉት እንዴት ነው? የሚለያዩትስ?

እስካሁን ድረስ ባለው የብሉይ ኪዳን ጥናታችን፥ እግዚአብሔር ከተለያዩ ሰዎች ጋር ስላደረጋቸው አራት ዋና ዋና ቃል ኪዳኖች ተመልክተናል፡- 1) ከኖኅና ከሰው ልጆች ሁሉ ጋር የተደረገ ቃል ኪዳን (ዘፍ. 9፡8-17)። 2) ከአብርሃም ጋር የተደረገ ቃል ኪዳን (ዘፍ. 15፡9-21፥ 3) ከእስራኤላውያን ጋር በሲና ተራራ የተደረገ ቃል ኪዳን (ዘጸ. 19-24 እና 4) ከሊቀ ካህኑ ከፊንሐስ ጋር የተደረገ ቃል ኪዳን (ዘኁ. 25፡10-13) ናቸው።

በዚህ ሳምንት በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ዐቢይ ስለሆነ አምስተኛ ቃል ኪዳን እንነጋገራለን፤ ይህም ከዳዊት ጋር የተደረገ ቃል ኪዳን ነው። ይህ ቃል ኪዳን በእስራኤል ሕዝብ ላይ ንጉሥ ወይም መሪ የመሆንን መብት የሚመለከት ቃል ኪዳን ነው። ለዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ፥ እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን የ2ኛ ሳሙኤል ዋና ትምህርት እንዲሁም 1ኛና 2ኛ ነገሥትን ለመረዳት የሚያስችል መሠረት ነው። በ2ኛ ሳሙ. 7፡5-16 እግዚአብሔር ለዳዊት የሰጣቸውን የሚከተሉትን የተስፋ ቃላት አስተውል፡

  1. «ታላቅ ስም አደርግልሃለሁ» (ቁ. 9)። ይህም እግዚአብሔር በዘፍ. 12፡2 ለአብርሃም ከሰጠው ቃል ኪዳን ጋር በጣም የሚመሳሰል ነው። ዳዊት በዚሁ መሠረት በዘመናት ሁሉ በእስራኤል ላይ ከነገሡ መሪዎች ጨርሶ ተወዳዳሪ የሌለው በመሆኑ እንደ አብርሃምና ሙሴ ስመ ገናና ሆነ። እንዲያውም የመጨረሻውና ዘላለማዊ የሆነው የእግዚአብሔር ሕዝቦች መሪ ኢየሱስ ክርስቶስ «የዳዊት ልጅ» ተብሎ ተጠራ (ማቴ. 1፡1፤ ማር. 10፡48)።
  2. «ለሕዝቤም ለእስራኤል ስፍራ አደርግለታለሁ፥ እተክለውማለሁ» (ቁ. 10)። እግዚአብሔር በዳዊት የአመራር ሥርዓት ውስጥ የእስራኤል ሕዝብ አዲስ ዘመን እንደሚመጣለት ተስፋ ሰጠ። ይህም ዘመን የተስፋ ምድር ከሆነችው ከአገራቸው ከነዓን ተገፍተን እንወጣለን ከሚል ፍርሃት ነጻ ሆነው የሚኖሩበት ጊዜ ይሆናል።
  3. «ከጠላቶችህም አሳርፍሃለሁ» (ቁ. 11)። እግዚአብሔር በዳዊት የአመራር ዘመን፥ ከጠላቶቻቸው ዕረፍትንና ደኅነትን ሰላምንም እንደሚሰጣቸው ለእስራኤላውያን ቃል ኪዳን ገባ። እግዚአብሔር ይህንን ቃል ኪዳን ፈጸመ። እግዚአብሔር፥ በከነዓን ምድር የሚኖሩትን ጠላቶቹን ሁሉ እንዲያሸንፍ ዳዊትን ረዳው። የከነዓን ምድር ድንበርም ከግብፅ ጀምሮ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ተስፋፋ። ከዳዊት በፊትም ሆነ በኋላ በእስራኤል ምድር ውስጥ እንዲህ ዓይነት ሰላምና ብልጽግና ታይቶ አይታወቅም፡

** ከላይ የተመለከትናቸው የእነዚህ ሦስት ቃል ኪዳኖች ዓላማ፡- እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን፥ ከአብርሃም ጋር በገባው በታላቁ ቃል ኪዳን ሥር አለመሆኑን ለማሳየት ነው። የዳዊት ቃል ኪዳን የአብርሃም ቃል ኪዳን አፈጻጸም ሁኔታ ተጨማሪ መግለጫ ነው። እነዚህ ሦስት ቃል ኪዳኖች መሠረታቸው የአብርሃም ቃል ኪዳን ነው፤ ነገር ግን በ2ኛ ሳሙ. 7፡12-16 የሚገኙ የተስፋ ቃሎች፥ በተለይ ለዳዊትና ለቤተሰቡ የተሰጡ አዲስ የተስፋ ቃሎች ናቸው።

  1. «እግዚአብሔርም ደግሞ፡- ቤት እሠራልሃለሁ ብሎ ይነግርሃል» (ቁ. 11)። ዳዊት ለእግዚአብሔር የሚሆን ቤት ወይም ቤተ መቅደስ ማሠራት ፈልጎ ነበር። ይህንን እንዲያደርግ እግዚአብሔር አልፈቀደለትም። ይልቁንም እግዚአብሔር ለዳዊት ቤት ሊሠራለት ቃል ገባለት። ይህም ቤት የንጉሣዊ ስርወ መንግሥት በእስራኤል ላይ ሁልጊዜ የመንገሥ መብት ነው (ቁ. 16 ተመልከት)። 
  2. «ከወገብህ የሚወጣውን ዘርህን ከአንተ በኋላ አስነሣለሁ» (ቁ. 12)። የንጉሥነት ሥልጣኑ ለልጆቹ እንዳልተላለፈው እንደ ሳኦል ሳይሆን እግዚአብሔር የዳዊት ልጆች ከእርሱ በኋላ በንጉሥነት እንደሚቀጥሉ ቃል ገባ። ከዳዊት በኋላ ሰሎሞን መንገሡ የዚህ ቃል ኪዳን ፍጻሜ ነበር። በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ለመጀመሪያ ጊዜ ለፖለቲካ አመራር ተከታታይ የሆነ የሥልጣን ውርስ ያደረገው በዚህ ስፍራ ነው።
  3. እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል» (ቁ. 13)። እግዚአብሔር ለዳዊት ቤተ መቅደስን ይሠራ ዘንድ አልፈቀደለትም፤ ነገር ግን ልጁ ቤተ መቅደሱን እንደሚሠራ ቃል ኪዳን ገባለት። በዚያም ክብሩን ያደርግ ዘንድ ተስፋ ሰጠ። ሰሎሞን ይህን በመፈጸም በጥንት ጊዜ እጅግ ታላላቅ ከሚባሉት ቤተ መቅደሶች አንዱ የነበረውን ቤተ መቅደስ ሠራ። የከርሰ ምድር ተመራማሪዎች በጥንት ዘመን ከነበሩ ሰባት አስደናቂ ነገሮች አንዱ ይህ ነው ይላሉ። 
  4. «እኔም አባት እሆነዋለሁ፥ እርሱም ልጅ ይሆነኛል» (ቁ. 14-15)። እግዚአብሔር ከዳዊት ልጅ ጋር ልዩ የሆነ ግንኙነት እንደሚኖረው ተስፋ ሰጠ። ይህ ግንኙነት በአባትና በልጅ መካከል እንዳለ ግንኙነት የቅርብና በፍቅር ላይ የተመሠረተ ነበር። ይህ ግንኙነት ጥፋት በሚፈጸምበት ጊዜ ቅጣትን የሚያስከትል ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ፍቅሩን እንደማይወስድ ቃል ገብቶ ነበር። ይህ ቃል ኪዳን በከፊል በሰሎሞን የተፈጸመ ሲሆን፥ ፍጹም በተሟላ መንገድ የተፈጸመው በኢየሱስ ክርስቶስ ነው (ማር. 1፡11፤ ዕብ. 1፡5 ተመልከት)።
  5. «ቤትህና መንግሥትህም በፊቴ ለዘላለም ይጠነክራል፥ ዙፋንህም ለዘላለም ይጸናል» (16)። እጅግ በጣም የሚያስደንቀውና እግዚአብሔር ለዳዊት የሰጠው ይህ የመጨረሻ ቃል ኪዳን ነው፤ ነገር ግን በሊቃውንት መካከል ከፍተኛ ውይይት ያስነሣ ነው። እግዚአብሔር ለዳዊት የገባለት ቃል ኪዳን ትክክለኛ መግለጫው ምንድን ነው? እግዚአብሔር ለዳዊት የገባለት ቃል ኪዳን ከዘሩ ሁልጊዜ በእስራኤል ላይ የሚነግሥ ሰው እንደሚኖር ነውን? ይህ ከሆነ ቃል ኪዳኑ አልተፈጸመም ማለት ነው፤ ምክንያቱም በ586 ዓ.ዓ. የደቡብ እስራኤል መንግሥት የሆነው የይሁዳ መንግሥት ከተደመሰሰ ወዲህ፥ እስራኤልን የሚገዛ ከዳዊት ወገን የተነሣ ምንም ዓይነት ንጉሥ አልነበረም። ታዲያ ይህንን ቃል ኪዳን የምንረዳው እንዴት ነው?

ሀ. «ለዘላለም» የሚለው ቃል በዕብራይስጥ የተለያየ ትርጉም ሊኖረው ይችላል። ይህ ቃል ፍጻሜ የሌለው ማለትም ልክ እንደ እግዚአብሔር መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው ማለት ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ያልተወሰነ ወይም ያልተለየና ያልታወቀ ጊዜ ማለትም ሊሆን ይችላል፤ (ለምሳሌ፡- 1ኛ ሳሙ. 1፡22፤ 2፡30-31፤ ኤር. 17፡4 ተመልከት)። የብሉይ ኪዳን ተጨማሪ ጥናት የሚያሳየን፥ እግዚአብሔር ለዳዊት የገባለት ቃል ኪዳን የእርሱ ዘር በእስራኤል ላይ ንጉሥ የመሆንና የመቀጠል ጊዜው ያልተወሰነ ዕድል እንደ ነበረው ነው። ይህ የመገዛት ሥልጣን ግን የተመሠረተው የዳዊት ዝርያዎች የመለኮታዊውን ንጉሥ ትእዛዛት ለመፈጸም በሚያሳዩት ፈቃደኝነት ላይ ነበር። ዳዊት በ2ኛ ሳሙ. 7፡29 ከጸለየው ጸሎት ግልጽ ሆኖ እንደምናየው የዳዊት ዝርያዎች ሁልጊዜ ለእግዚአብሔር በቅንነት ባይታዘዙ መግዛታቸውን እንደሚቀጥሉ ይህ ቃል ኪዳን አይናገርም፤ ስለዚህ ዳዊት የእርሱ ዘር በኃላፊነት እንዲቀጥል ያለማቋረጥ በረከቱን እንዲሰጠው እግዚአብሔርን ይጠይቃል።

ለ. ይህ ቃል ኪዳን በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ነበር ወይስ አልነበረም? ይህ ቃል ኪዳን በቅድመ-ሁኔታ ላይ የተመሠረተም ያልተመሠረተም ነው ለማለት እንችላለን። ለዳዊት ቃል ኪዳኑ በምንም ቅድመ-ሁኔታ ላይ ያልተመሠረተ ነበር። እግዚአብሔር ይህንን ቃል ኪዳን ለዳዊት ለመፈጸም ከዳዊት የጠየቀው ቅድመ-ሁኔታ አልነበረም፤ ነገር ግን የዘላለም ገዢነቱን የሚናገረውን የቃል ኪዳን ክፍል ለመፈጸም የተሰጡ ቅድመ-ሁኔታዎች ነበሩ። በ1ኛ ነገሥት 2፡2-4 ዳዊት ይህንን ቃል ኪዳን ለሰሎሞን ሲያስተላልፍ ግልጽ እንዳደረገው «የምታደርገውንና የምትሄድበትን ሁሉ ታከናውን ዘንድ፥ በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈ ሥርዓቱንና ትእዛዛቱን ፍርዱንና ምስክሩንም ትጠብቅ ዘንድ፥ በመንገዱም ትሄድ ዘንድ፥ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጠብቅ። ይኸውም ደግሞ እግዚአብሔር ስለ እኔ፡- ልጆችህ መንገዳቸውን ቢጠብቁ፥ በፊቴም በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው በእውነት ቢሄዱ ከእስራኤል ዙፋን ሰው አይቆረጥብህም ብሎ የተናገረውን ቃል ያጸና ዘንድ ነው» (በተጨማሪ 1ኛ ነገሥት 6፤ 12 9፡4-7 ተመልከት)። እግዚአብሔር ለዳዊት በእስራኤል ዙፋን ላይ እንደሚቀመጥና ሊያሸንፈው ወይም ከዙፋኑ ሊያወርደው የሚችል ማንም እንደሌለ ቃል ኪዳን ገብቶለት ነበር፤ ከዚህ ባሻገር ልጁ በሥልጣን ላይ የመቆየቱ ነገር በልጁ ወይም በዝርያዎቹ ሁሉ መታዘዝ ላይ የተመሠረተ ነበር።

ነገር ግን ይህ ነገር ዘላለማዊና በምንም ቅድመ ሁኔታ ላይ ያልተመሠረተ መሆኑን የምናይበት ሌላ መንገድም አለ። አለመታዘዝ ለጊዜው የዳዊትን ዝርያዎች የመንገሥ መብት ቢያሰናክልም፥ የዳዊት ዋና ልጅ የሆነው መሢሑ ይህንን ቃል ኪዳን ይፈጽማል። ነቢያት እንድ ቀን ታላቁ «የዳዊት ልጅ» እንደሚመጣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ተረድተው ነበር (ኢሳ. 9፡6-7 11፤ (ኤር. 23፡5-6፤ ሕዝ. 34፡23-24 ተመልከት)። እግዚአብሔር ሕዝቦችና ዓለምን ሁሉ ከዳዊት እጅግ በላቀ አኳኋን ይገዛል። የዳዊት ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ፥ በእግዚአብሔርና በዳዊት መካከል የተገባውን ቃል ኪዳን ይፈጽማል፤ ምክንያቱም እርሱ በሕዝቡ ላይ የሚገዛ የዘላለም ንጉሥ ነው (ለምሳሌ፡- በራእይ 21፡1-6፤ ሉቃስ 1፡32-33 ይህ ቃል ኪዳን በኢየሱስ ክርስቶስ እንደተፈጸመ ተመልከተው)። ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምሳያ የሌለው ንጉሥ ነው። እርሱ በጽድቅና በቅንነት ከእግዚአብሔር የንጉሥነት ዙፋን ሥር ሆኖ የሚያስተዳድር ነው፡፡ ዳዊት የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ምሳሌ ነው፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ በዳዊት ሕይወት ውስጥ በከፊል የታየውና እግዚአብሔር ከአንድ ንጉሥ የሚፈልገውን ነገር ስለሚፈጽም ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ከዳዊት ጋር ከተደረገው ቃል ኪዳን፥ ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ፥ ስለ እግዚአብሔር ተስፋ ቃልና ስለ መታዘዝ አስፈላጊነት የምንማረው ምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: