1ኛ ሳሙኤል 21-31

የውይይት ጥያቄ፥ ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ብንኖር ከማንፈልገው ነገር ሁሉ ይጠብቀናልን? ይህስ ማለት የሚያጋጥሙን መልካም ነገሮች  ብቻ ናቸው ማለት ነውን? መልስህን አብራራ።

ብዙ ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን ከታዘዝንና በእግዚአብሔር ከተባረክን ነገሮች ሁሉ በሕይወታችን በመልካም ሁኔታ ይከናወናሉ ብለው ያስባሉ። ለእግዚአብሔር እየታዘዝን የመኖራችን ምልክት ያለ ችግሮችና ያለምንም ሳንካ መኖራችን እንደሆነ ይመስላቸዋል። አንታመምም፤ ልጆቻችን አይሞቱም፤ ሰብላችንም አይበላሽም፤ ወዘተ. ይላሉ፤ ነገር ግን ይህ ስሕተት ነው። እንዲያውም ብዙ ጊዜ ነገሮች ሁሉ ያለምንም ችግር መከናወናቸው ለእግዚአብሔር ያለመታዘዛችን ምልክት ነው። ጌታ ኢየሱስ እንዳለው በመታዘዝ በምንኖርበት ጊዜ ስደትና ችግር ይገጥመናል (ዮሐ. 15፡18-21 ተመልከት)፤ ስለሆነም በሕይወታችን ችግር የመኖሩ ነገር፥ እግዚአብሔር እንደሚወደንና በእምነታችን እንድንጎለምስ ለማድረግ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እንደሚጠቀም ነው (ያዕ. 1፡2-4 ተመልከት)፤ ስለዚህ ማንኛውም ዓይነት ችግር ያለመታዘዝ ውጤት ነው በማለት ፈጥነን ከመፍረድ ልንቆጠብ ይገባናል።

የ1ኛ ሳሙኤል የመጨረሻው ክፍል በመሠረቱ በሳኦልና በዳዊት መካከል ያለውን ግጭት የሚተነትን ክፍል ነው። ዳዊት ንጉሥ እንዲሆን በእግዚአብሔር ተመርጦ ነበር። በእግዚአብሔር ዓይን የእግዚአብሔር ሕዝብ ትክክለኛ ንጉሥ ዳዊት ነበር፤ ነገር ግን ዳዊት በበርካታ ዓመታት ኮብላይ (ተሳዳጅ) ሆኖ በዋሻ ተደብቆ ኖረ። ከሳኦል የግድያ ሙከራ ለማምለጥ ከቦታ ወደ ቦታ ይዘዋወር ነበር። ንጉሥ ለመሆን ምንም ዓይነት ኃይልን ለመጠቀም ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ። ጥላቻና ብቀላ ወደ ሕይወቱ እንዲገባ አልፈቀደም። ይልቁንም እግዚአብሔር ራሱ በሳኦል ላይ እስኪፈርድና መንግሥቱን እስኪሰጠው ድረስ ለመጠበቅ ወሰነ። ይህ ለእኛ ብርቱ ማስጠንቀቂያ ሊሆነን ይገባል። ነገሮችን በራሳችን እጅ በማከናወን የጎበጠውን ለማቃናት ከመፍጨርጨር ይልቅ እግዚአብሔርን በትዕግሥት ልንጠብቀው ይገባል። በተጨማሪ ከእግዚአብሔር ጋር በፍጹም ታዛዥነት በምንኖርበት ጊዜ እንኳ በብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ማለፍ እንደምንችል ያስተምረናል።

የውይይት ጥያቄ፥ 1ኛ ሳሙ. 21-31 አንብብ። ሀ) በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ የምታገኘውን የሳኦልና የዳዊት ሕይወት አነጻጽር። ሳኦል ለመሪነት የማይገባ መሆኑ የታየው እንዴት ነው? ዳዊት በእስራኤል ላይ መንገሥ የሚገባው መሪ መሆኑ የታየው እንዴት ነው? ለ) በእነዚህ ምዕራፎች፥ የእግዚአብሔር እጅ በዳዊት ሕይወት ውስጥ የታየው እንዴት ነው? ሐ) እግዚአብሔርን የሚያስደስቱ ዳዊት ያደረጋቸው ወይም ሊያደርጋቸው የሞከራቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? መ) ዳዊት የሠራዊት አዛዥ እንደመሆኑ መጠን ኃይሉ የታየው እንዴት ነው? ሀ) ሳኦል ያላማቋረጥ ለእግዚአብሔር ሳይታዘዝ መኖሩ በእግዚአብሔር፥ በራሱና በልጆቹ ሕይወት ያመጣው ውጤት ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ስሕተት ከመደበቅ ይልቅ ያደረጉትን መልካምም ሆነ ክፉ ወይም የሞኝነት ነገር ሁሉ በግልጥ ይናገራል። በእነዚህ ምዕራፎች በሳኦልና በዳዊት መካከል ያሉ በንጽጽር የቀረቡት ጉዳዮችን እናያለን። በአንድ ወቅት በእስራኤል ላይ ታላቅ መሪ የነበረው ሳኦል በቅንዓት ዳዊትን ለመግደል በመሞከር ጊዜውን ሁሉ ሲያጠፋ እንመለከተዋለን። ፍልስጥኤማውያንን ከመውጋት ይልቅ ሳኦል ከዳዊት ጋር ተዋጋ፤ ደግሞ የዳዊትን ድካምና ጥንካሬ የሚገልጡ ነገሮችን እንመለከታለን። 

የሳኦል ሕይወት ፍጻሜ በጣም አሳዛኝ ነው። ከእግዚአብሔር ጋር አንዳችም ግንኙነት ላያደርግና ከእርሱም እርዳታ ሳያገኝ ከሞተው ከሳሙኤል ጋር ለመገናኘት ሞከረ። ሙታንን የማናገር ችሎታ እንዳላት ወደሚነገርላት አንዲት ጠንቋይ ዘንድ ሄደ። ጥንቆላና ጠንቋዮች በእግዚአብሔር ዘንድ ፈጽሞ የተከለከሉ መሆናቸውን ታስታውሳለህ። ሳኦል ግን የሳሙኤልን ምክር ፈለገ፤ ስለዚህ ይህች ሴት ከሳሙኤል ጋር እንድታገናኘው ፈለገ፡፡ ከዚህ በኋላ የተፈጸመው ነገር ምን እንደሆነ በትክክል ማወቅ አስቸጋሪ ነው። አንዳንድ ሰዎች የሳሙኤል መንፈስ መጥቶ ከሳኦል ጋር እንዲነጋገር እግዚአብሔር ፈቅዶ ይሆናል ይላሉ።” ሌሎች ሰዎች ደግሞ በሳሙኤል መንፈስ ቅርጽ የተገለጠ ርኩስ መንፈስ ነው ይላሉ። ለዚህ ጉዳይ የምንሰጠው ምላሽ ምንም ይሁን ምን፥ እግዚአብሔር ይህንን ክፉ ሁኔታ ሳኦል የሚሞትበት ጊዜ የቀረበ መሆኑን ለመናገር ተጠቀመበት። ለጠንቋይዋ ሳይቀር አንድ ያልተለመደ ነገር እንደተፈጸመ የሚያሳየው ሳሙኤልን ባየች ጊዜ በታላቅ ፍርሃት መሽበሯ ነው። በመጀመሪያ ያልተለመደውን የሳሙኤልን መንፈስ ፈራች። በሁለተኛ ደረጃ ጠንቋዮችን ለመግደል የሞከረውን ሳኦልን ፈራች። በዚህ ታሪክ ውስጥ ዋናው ነገር ይህ እንዴት ተፈጸመ የሚለው አይደለም፤ ነገር ግን አለመታዘዝ የሚያስከትለውን ውጤት ነው። እግዚአብሔር በብዙ መንገድ ያልታዘዘውን የሳኦልን ሞት ተንብዮአል።

ሳኦል ለእግዚአብሔር መታዘዝ እምቢ ስላለ፥ ብዙ አሳዛኝ ነገሮች ተፈጸሙ። በመጀመሪያ፥ የእስራኤል ሕዝብ ስለተሸነፈ፥ ብዙ እስራኤላውያን በጦርነት ሞቱ። ሁለተኛ፥ አብዛኛዎቹ የሳኦል ልጆች ሞቱ። ሦስተኛ፥ ሳኦል በፍልስጥኤማውያን እጅ ከመሞት ይልቅ ራሱን ገደለ።

አንድ መሪ ለእግዚአብሔር አለመታዘዝ ሲጀምር፥ ነገሩ ቀላል መስሎ ሊታይ ይችላል፤ ዳሩ ግን የእርሱ አለመታዘዝ ወዲያውኑ ሌሎች በርካታ ሰዎችን መንካት ይጀምራል። ሕዝቡን የሚመራው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መሆኑ ቀርቶ በራሱ የግለኝነትና የስስት ኃይል ስለሚሆን፥ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት በችግር ላይ ይወድቃሉ፥ ብዙዎች ቤተ ክርስቲያንን ይተዋሉ። እንዲያውም የሐሰት ትምህርት ይቀበላሉ፥ በቤተሰቡም ላይ ችግር ይደርሳል። ልጆቹም የእርሱን ግብዝነት በማየት፥ የክርስቶስን ስም እያሰደቡ፥ ቤተ ክርስቲያንን ትተው ይሄዳሉ፡፡ በመጨረሻም አገልግሎቱ በሙሉ ይጠፋል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህ ነገር በቤተ ክርስቲያን ሲፈጸም እንዴት አይተሃል? ለ) ቤተ ክርስቲያንን ለመምራት ከሳኦል ሕይወት የምንማራቸው አንዳንድ ማስጠንቀቂያዎች ምንድን ናቸው? ሐ) ለእግዚአብሔር ክብርን ለማምጣትና ለብዙ ሰዎች በረከትን ለማስገኘት በሚያስችል ሁኔታ ለመምራት ውሳኔ የምናደርግባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

እነዚህ ምዕራፎች ዳዊትን ኃጢአት ያልነካካው ፍጹም ሰው አድርገው አያቀርቡትም። ስላለፉት የእግዚአብሔር ሰዎች በምናስብበት ጊዜ፥ ፍጹም እንደነበሩና ከኃጢአት ጋር እንዳልታገሉ አድርገን እንገምታለን፤ ይህ ግን እውነት አይደለም። በእነዚህ ምዕራፎች፥ ዳዊትም ራሱ ኃጢአተኛና እንደ እኛው ፍጹምነት የሌለው ሰው እንደነበር እናያለን። ይህም ቢሆን እንኳ ዝንባሌው እግዚአብሔርን ደስ ስላሰኘው፥ እግዚአብሔር በመሪነት አከበረው።

ከእነዚህ ምዕራፎች ስለ ዳዊት የሚከተሉትን ነገሮች አስተውል፡-

  1. ዳዊት ሳይፈልግ ለበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሆነ (1ኛ ሳሙ. 21)። ዳዊት ከሴሉ በኋላ የአምልኮ ማዕከል ወደሆነችው ወደ ኖብ በሚሄድበት ጊዜ ንጉሥ ሳኦል እንደሚከታተለው ያውቅ ነበር። እርሱን የረዱትን ሰዎች ሳኦል እንዳይገድላቸው ወደ ሌላ ስፍራ መሄድ ነበረበት። ዳዊት ግን ወደ ካህኑ ስለ ሄደ፥ 85 ካህናት በሳኦል ተገደሉ። 
  2. ዳዊት ከፍልስጥኤማውያን ጋር በሚኖርበት ጊዜ እግዚአብሔር እንደሚጠብቀው ባለማመኑ ራሱን እንደ ዕብድ አስመሰለ (1ኛ ሳሙ. 21፡13)። 
  3. ዳዊት የሳኦልን ሕይወት ሁለት ጊዜ አዳነ። ዳዊት የእስራኤልን ዙፋን ለማግኘት ሲል ነፍስ ለማጥፋት አልፈለገም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የተስፋ ቃሉን በጊዜው እንዲፈጽም ታግሦ ጠበቀ (1ኛ ሳሙ. 24 እና 26)።
  4. ዳዊት በበቀል አንድን ቤተሰብ ሊያጠፋ ምንም ያህል አልቀረውም ነበር (1ኛ ሳሙ. 25)። የአቢግያ ባል ዳዊት ስላደረገለት ነገር ሁሉ ስላላመሰገነ፥ ዳዊት ቤተሰቡን ሊያጠፋ ነበር። ይህ ቢደረግ ኖሮ ለራስ ጥቅም በስግብግብነት ሥልጣንን አላግባብ መጠቀም እንደ መሆኑ፥ ከፍተኛ የፍርድ መዛባት ይሆን ነበር። እግዚአብሔር ግን በአቢግያ የብልህነት ተግባር በመጠቀም የዳዊት እጅ አንዳችም ጥፋት በሌለባቸው ሰዎች ደም እንዳይበከል ጠበቀው። ኋላም እግዚአብሔር ራሱ የአቢግያን ባል ቀጣው። የእስራኤል ዙፋን አንድ ቀን በዳዊት እጅ እንደሚገባ አቢግያ ቀድማ ተርድታ እንደ ነበር ማየት የሚገርም ነው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: