የውይይት ጥያቄ፥ የቃል ኪዳኑ ታቦት ምን እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ውስጥ ተመልከት።
የእስራኤል ሕዝብ ለረጅም ጊዜ ከከነዓናውያን ጋር ስለኖሩ፣ ከነዓናውያን በእግዚአብሔር ላይ ባላቸው አመለካከት ተጽዕኖ ሥር ወደቁ። ስለሆነም የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ ጦር ሜዳ በመውሰድ፥ በጦርነቱ ድልን እንዲሰጣቸው እግዚአብሔርን ማስገደድ እንደሚችሉ ገመቱ። እንደምታስታውሰው፥ የቃል ኪዳኑ ታቦት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የሚገኝ ከሁሉም የሚበልጥ የተቀደሰ ዕቃ ነው። በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ በመቀመጥ፥ እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ጋር የመኖሩ ምልክት ሆኖ ያገለግል ነበር። በምድር ላይ ያለው የእግዚአብሔር ሰማያዊ ዙፋን ምልክት ተደርጎ ይቆጠር ነበር።
አንዳንድ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያን ሕንጻ በመንግሥት ሲፈርስ ዝም ብሉ አያይም የሚል ግምት እንዳላቸው ሁሉ፥ እስራኤላውያንም እግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት በጠላት እንዲጠፋ አይፈቅድም የሚል የተሳሳተ ግምት ነበራቸው። የቃል ኪዳኑን ታቦት ወደ ጦር ሜዳ ይዘውት ቢሄዱ፥ እግዚአብሔር ድልን እንደሚሰጣቸው እርግጠኞች ነበሩ። እግዚአብሔር ለእነርሱ ይሠራ ዘንድ በተሳሳተ መንገድ ሊጠቀሙበት ሞከሩ። ይገዟቸው ዘንድ፥ እግዚአብሔር ፍልስጥኤማውያንን የላከባቸው፥ በኃጢአታቸው ምክንያት እንደሆነ ዘነጉ። በእውነት በንስሐ ቢመለሱ እግዚአብሔር ይቅር እንደሚላቸውና ከጠላቶቻቸው ነፃ እንደሚያወጣቸው ሊገነዘቡ ይገባቸው ነበር። እግዚአብሔር ግን ለእነርሱ በመሰላቸው መንገድ አልሠራም፤ ስለዚህ የቃል ኪዳኑ ታቦት ይማረክ ዘንድ ፈቀደ።
የውይይት ጥያቄ፥ ዛሬ ክርስቲያኖች አንዳንድ ነገሮችን እንዲያደርግላቸው እግዚአብሔርን በዘዴ ሊጠቀሙበት የሚፈልጉባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው?
ከፍልስጥኤማውያን ጋር ያደረጉት ጦርነት በእስራኤላውያን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳደረባቸው። የመጀመሪያው፡- እግዚአብሔር ለዓሊ የላከውን የትንቢትን ቃል አከበረ። የዔሊ ልጆች በጦርነቱ ተገደሉ። ዔሊ ራሱ የጦርነቱን ውጤት በሰማ ጊዜ ሞተ። የዔሊ ልጅ ሚስት ሳትቀር በወሊድ ሞተች። የእግዚአብሔር ክብር ከእነርሱ መወሰዱን በመገንዘብ ልጇን «ኢካቦድ» ብላ ጠራችው። ትርጉሙም «ክብር ለቀቀ» ማለት ነው።
ሁለተኛው፡- የእግዚአብሔር መነቀፍ ነበር። በጥንት ዘመን አንድ ሕዝብ ሌላውን በሚያሸንፍበት ጊዜ፥ ሕዝቡ የእነርሱ አምላክ ከተሸነፈው ሕዝብ አምላክ ስለበለጠ እንደሆነ ያስቡ ነበር፤ ስለዚህ የእስራኤላውያን አለመታዘዝ፥ በአሕዛብ መካከል የእግዚአብሔር ስም እንዲሰደብ አደረገ። ፍልስጥኤማውያንም የቃል ኪዳኑ ታቦት ዳጎን ወደሚባለው አምላካቸው ወሰዱት።
ሦስተኛ፡- እግዚአብሔር ለፍልስጥኤማውያን ኃይሉን አሳያቸው። ፍልስጥኤማውያን አምላካቸው የእስራኤልን አምላክ እንዳሸነፈ ቆጥረው ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ይህ እንዳልሆነ አሳያቸው። በመጀመሪያ ልክ እግዚአብሔርን የሚያመልክ ሰው እንደሚያደርገው፥ ዳጎን በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት በፊቱ እንዲደፋ አደረገ። ሁለተኛ፥ በፍልስጥኤም ምድር ሁሉ መቅሠፍት እንዲሆን አደረገ። ሦስተኛ፣ እግዚአብሔር ፍልስጥኤማውያንን የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ እስራኤል እንዲመልሱ አደረገ። ከተለመደው ነገር በተቃራኒ፥ ላሞች የሚያጠቧቸውን ጥጆቻቸውን ትተው ታቦቱን የተሸከመውን ሰረገላ ወደ እስራኤል ምድር እየጎተቱ ሄዱ።
አራተኛ፡- እግዚአብሔር ስላላከበሩት አንዳንድ እስራኤላውያንን ቀጣ። ይኸውም እነኝህ እስራኤላውያን ስለ ታቦቱ ያልተፈቀደላቸውን ለማወቅ ስለፈለጉ ተገደሉ።
አምስተኛ፡- የሴሎ ከተማና የመገናኛው ድንኳን ተደመሰሱ። አስቀድሞ ከነበረው የመገናኛ ድንኳን ውስጥ የዳነው ብቸኛው ነገር የቃል ኪዳኑ ታቦት ነው። የእስራኤላውያን የአምልኮ ማዕከል ሴሉ መሆኑ ቀረና ኖብ ሆነ (1ኛ ሳሙ. 21፡1)። ታቦቱም ወደ ተለያዩ ቦታዎች ይንቀሳቀስ ጀመር። ታቦት በነበረበት ስፍራ ሁሉ እስራኤላውያን እግዚአብሔርን ያመልኩ ነበር። ከብዙ ዓመታት በኋላ ዳዊት የቃል ኪዳኑን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም በመውሰድ በድንኳን ውስጥ አኖረው። በኋላ ደግሞ ሰሎሞን የቃል ኪዳኑ ታቦት ይኖርበት ዘንድ እጅግ ታላቅ ቤተ መቅደስ አሠራ።
ከዘመናት በኋላ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምና ቤተመቅደሱ እንዲደመሰሱ አይፈቅድም፤ ምክንያቱም ቤተ መቅደሱ የእርሱ ነውና ብለው እስራኤላውያን አሰቡ (ኤር. 7፡1-15 ተመልከት)። ሰዎች የራሳቸውን የስግብግብነት ዓላማዎች ለማሳካት እግዚአብሔርን በዘዴ ሊጠቀሙበት እንደማይችሉ አሳያቸው። ሕዝቡ ወደ ምርኮ እንዲሄዱ ፈቀደ። እግዚአብሔር መንፈስ ስለሆነ፥ በአንድ ሕንጻ ውስጥ ሊገደብና ሰዎች ሊጠቀሙበት ወይም አንድ ነገርን እንዲያደርግ በዘዴ ሊያስገድዱት አይችሉም። ለእግዚአብሔር አንድ ታላቅ ነገር በማድረግ፥ አንድን ነገር እንዲያደርግልን ለማስገደድ አንችልም። አንድ ሰው በኢየሱስ ስም ተፈውሷል ብለን በማወጃችን፥ ወይም በመጸለያችን ብቻ እግዚአብሔር ያንን ሰው እንዲፈውሰው . ልናስገድደው አንችልም። ደግሞም የቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ባለቤት መሆናችን ስደት እንደማይደርስብን ማረጋገጫ ሊሆንልን አይችልም ወይም ቤተ ክርስቲያን እንደማይዘጋ ዋስትና ሊሆን አይችልም። እግዚአብሔር ሉዓላዊና የሚፈልገውን ነገር በሚፈልገው ጊዜ የሚያደርግ አምላክ ነው። በምንም ነገር ልናስገድደው ወይም ልንቆጣጠረው አንችልም።
የውይይት ጥያቄ፡ ሀ) አንዳንድ ሰዎች በእግዚአብሔር በዘዴ ለመጠቀም ሲሞክሩ ያየኸው እንዴት ነው? ለ) ምን አደረጉ? ሐ) ይህ ስሕተት የሆነው ለምንድን ነው? መ) አንዳንድ ክርስቲያኖች፥ እግዚአብሔር የማደሪያውን ሕንጻ እንዲደመሰስ ከቶ አይፈቅድም ብለው ለምን ያስባሉ?
ሳሙኤል ለእስራኤል ሕዝብ እንደ መስፍን ነበር (1ኛ ሳሙ. 7)
ከብዙ ዓመታት በኋላ፥ ሳሙኤል ሕዝቡን በምጽጳ ሰበሰበ። በዚያ እግዚአብሔር የሰዎችን ልብ መለወጥ ጀመረ። በፍልስጥኤማውያን የባርነት ቀንበር ሥር መኖራቸው አሰልችቷቸው እንደ ነበር አንዳችም ጥርጥር የለም። ሳሙኤል ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱና ለእግዚአብሔር ቃል ኪዳን እንዲታዘዙ ለመምከርና ለማሳመን ሞከረ።
ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር ሲመለሱና ንስሐ በመግባት እግዚአብሔርን ሲያመልኩ፥ ፍልስጥኤማውያን ሊያጠቋቸው ወሰኑ። ዳሩ ግን ሳሙኤል ወደ እግዚአብሔር ጸለየና ፍልስጥኤማውያን ተሸነፉ። በሳሙኤል ዘመነ መንግሥትን እስራኤላውያን ከፊሉን የፍልስጥኤም መንግሥት ለማሸነፍ ችለው ነበር።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)