2ኛ ሳሙኤል 5፡6-12፡31

አንድ ጊዜ አንድ ታላቅ ሚሲዮናዊ እንዲህ ብሎ ተናገረ፡- “ዓለም ራሱን ሙሉ ለሙሉ ለእግዚአብሔር በሰጠ ሰው ሕይወት ውስጥ እግዚአብሔር ምን እንደሚሠራ ገና ታያለች”። ራሱን ሙሉ ለሙሉ ለእግዚአብሔር የሰጠ ሰው ሙሉ የእግዚአብሔር ኃይል አለው። ራሱን የሰጠ መሪ የእግዚአብሔር ኃይል በሙሉ በእርሱ ዘንድ አለና እዚአብሔር ታላላቅ ነገሮችን በእርሱ ውስጥ ማድረግ ይችላል። የእግዚአብሔር ኃይል በውስጣችን እንዳይሠራ የምንከላከለው፥ ሕይወታችንን ሙሉ ለሙሉ ለእግዚአብሔር ካልሰጠንና ኃጢአትና ራስ ወዳድነት ወደ ሕይወታችን እንዲገባ ከፈቀድን ነው። 

ዳዊት ራሱን ለእግዚአብሔር የሰጠ ሰው ነው፤ ስለዚህ እግዚአብሔር እጅግ አስደናቂ በሆነ መንገድ በሕይወቱ የሚጠቀምበት ሰው ሊሆን ችሏል። ዳዊት ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ስለኖረ፥ እግዚአብሔር በንጉሥነቱ ባረከው። የእግዚአብሔርን ጠላቶች ሁሉ ድል በማድረግ ለእግዚአብሔር ሕዝብ ሰላምን አስገኘ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ለእግዚአብሔር ራሳቸውን አሳልፈው በመስጠታቸው እግዚአብሒር በከፍተኛ ሁኔታ ስለተጠቀመባቸው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሥዕላዊ መግለጫ ስጥ። ለ) ለእግዚአብሔር ያላስረከብካቸው የሕይወትህ ክፍሎች የትኞቹ ናቸው? ሐ) ራስህን ሙሉ ለሙሉ ለእግዚአብሔር በመስጠት ለራሱ ክብር በከፍተኛ ሁኔታ ሊጠቀምብህ እንዲችል ለመጸለይ ጊዜ ይኑርህ።

የውይይት ጥያቄ፥ 2ኛ ሳሙኤል 5፡6-12፡31 አንብብ። ሀ) በእነዚህ ቁጥሮች የተጠቀሱትን ዳዊት ያከናወናቸውን ልዩ ልዩ ነገሮች ዘርዝር። ለ) ዳዊት የቃል ኪዳኑን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም በመውሰዱ ከዳዊት ባሕርይ የምንማረው ነገር ምንድን ነው? ሐ) እግዚአብሔር ለዳዊት የገባለትን የተስፋ ቃሎች ዘርዝር፡ መ) ዳዊት ለዮናታን የገባውን ቃል ኪዳን የጠበቀው እንዴት ነበር? ሠ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ብንሆም እንኳ በትልቅ ኃጢአት ልንወድቅ እንደምንችል፥ ዳዊት ከሠራው ኃጢአት ምን እንማራለን?

የ1ኛና የ2ኛ ሳሙኤል እንዲሁም የ1ኛ ነገሥት ጸሐፊዎች የሳኦልን፥ የዳዊትንና የሰሎሞንን ታሪክ ለማቅረብ የተከተሉት መንገድ ተመሳሳይ ነው። በመጀመሪያ ጸሐፊዎቹና፥ እነዚህ መሪዎች ንጉሥ እንዲሆኑ እንዴት እንደተቀቡ ይናገራሉ። ቀጥሉ እነዚህ መሪዎች የፈጸሙአቸውን ተግባራት ይተነትናሉ። በመጨረሻ በእነዚህ ጸሐፊዎችና መሪዎች ሕይወት ውስጥ በኃጢአት ምክንያት ስለሆኑ ክፉ ነገሮች ይዘግባሉ። ዳዊት ንጉሥ ይሆን ዘንድ የተቀባው ከብዙ ዓመታት በፊት ቢሆንም እንኳ በመጨረሻ በይሁዳና በእስራኤል ላይ እንዴት ንጉሥ ለመሆን እንደበቃ ተመልክተናል፡፡ በመቀጠል ደግሞ ዳዊት ስለ ፈጸማቸው የተለያዩ ነገሮችና ታላቅ ስላደረጉት ተግባሮቹ እነመለከታለን።

  1. ዳዊት በጠላቶቹ ሁሉ ላይ ድልን ተቀዳጀ። እርሱ ድል ያደረጋቸውን የሚከተሉትን ሕዝቦች ተመልከት፡-

ሀ. ኢያቡሳውያን፡- በመካከለኛው እስራኤል ጠንካራ ከተማ በነበረችው በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦች ናቸው። ለብዙ መቶ ዓመታት አይሁዳውያን የኢየሩሳሌምን ከተማ ለመያዝ አልቻሉም ነበር። ዳዊት ግን ከተማይቱን አሸነፈና የእስራኤል መንግሥት አዲሲቱ ዋና ከተማ አደረጋት። ኢየሩሳሌም «የዳዊት ከተማ»፥ «ጽዮን» በመባልም ትታወቃለች (2ኛ ሳሙ. 5፡7)። 

ለ. ፍልስጥኤማውያን (2ኛ ሳሙ. 5፡17-25፤ 8፡1)። ዳዊት እንደገና ሊያስቸግሩት በማይችሉበት መንገድ ፍልስጥኤፃውያንንም አሸነፋቸው። 

ሐ. ሞአባውያን (2ኛ ሳሙ. 8፡2)።

መ. በሶርያ ውስጥ የሚገኘው የሱባ ንጉሥ (2ኛ ሳሙ. 8፡3-10)፡- ዳዊት በእስራኤል በስተሰሜን የሚገኙትን ነገሥታት በሙሉ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ አሸንፎአቸዋል። 

ሠ. ኤዶማውያንና አሞናውያን (2ኛ ሳሙ. 8፡11-14፤ ምዕራፍ 10)። 

ሳኦል በምርኮ ያገኘውን ነገር ለራሱ የወሰደ ሲሆን፥ ዳዊት ግን በምርኮ የበዘበዘውን ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ያመጣ ነበር፤ ዳዊት ድል የሰጠው እግዚአብሔር እንደሆነ የተገነዘበ ሰው ነበር፤ ስለዚህ ምርኮውን ሁሉ ለእግዚአብሔር ሰጠ (2ኛ ሳሙ. 8፡7-12)። ይህን ከምርኮ የተገኘ ነገር በኋላ ለቤተ መቅደሱ ግንባታ አውሎአል። 

የውይይት ጥያቄ፥ ከዚህ ነገር ስለ ዳዊት ባሕርይ የምንማረው ምንድን ነው?

  1. ዳዊት የቃል ኪዳኑን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም አስመጣ (2ኛ ሳሙኤል 6)። ዳዊት መንግሥቱን ካጸናና ዋና ከተማውን ከመሠረተ በኋላ፥ የነገሥታት ንጉሥ የሆነው እግዚአብሔር በኢየሩሳሌም እንዲገዛ ፈለገ። የቃል ኪዳኑ ታቦት የእግዚአብሔር ዙፋን እንደሆነ ይታሰብ ነበር፤ ስለዚህ ዳዊት የእግዚአብሔር ዙፋን በኢየሩሳሌም እንዲሆንና በእስራኤል መንግሥት ላይ እንዲገዛ ይፈልግ ነበር። ይህ ማለት ሰብአዊ የሆነው ንጉሥና መለኮታዊ የሆነው ንጉሥ በአንድነት በኢየሩሳሌም ሊገዙ ነበር። 

ዳዊት የቃል ኪዳኑን ታቦት ከአሚናዳብ ቤት በታላቅ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም አስመጣው። እግዚአብሔርን በዚህ መንገድ ያከበረው ቢሆንም፥ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በጥንቃቄ መከተልን ግን ዘነጋ። እግዚአብሔር የቃል ኪዳኑን ታቦት ካህናት ረዘም ባሉ መሎጊያዎች ማንም ሊነካው በማይችል ሁኔታ እንዲሸከሙ አዝዞ ነበር (ዘጸ. 25፡12-15፤ ዘኁ. 4፡15)። ካህናቱ ግን ታቦቱን በሠረገላ ጭነው፥ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። ሠረገላው በሚንቀሳቀስበት ጊዜ መንገዱ አመቺ ባለመሆኑ እንዳይወድቅ ዖዛ የእግዚአብሔርን ታቦት ያዘ፤ እግዚአብሔርም ወዲያውኑ በሞት ቀሠፈው። 

የውይይት ጥያቄ ሀ) እግዚአብሔር በዖዛ ላይ በብርቱ የተቆጣው ለምን ይመስልሃል? ለ) ይህ ታሪክ ስለ እግዚአብሔር የሚያስተምረን ነገር ምንድን ነው?

ይህንን ታሪክ በምናነብበት ጊዜ፥ በእግዚአብሔር ሥራ እንደነቅ ይሆናል። ዳዊት ሳይቀር ተደንቆና አዝኖ ነበር። ታቦቱ እንዳይወድቅ ለማድረግ መሞከሩ መልካም ሆኖ ሳለ፥ እግዚአብሔር ዖዛን የገደለው ለምንድን ነው? እግዚአብሔር ይህንን ያደረገበት ሁለት ምክንያቶች አሉ፡ 

  1. ዖዛ አሳቡ መልካም ቢሆንም፥ ተግባሩ ግን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በቀጥታ የሚጻረር ነበር። እግዚአብሔር ታቦቱን ማንም ሰው እንዳይነካ አስጠንቅቋል። እግዚአብሔር ራሱን ለመጠበቅ ስለሚችል፥ ዖዛ ታቦቱን ለማዳን ያደረገው ሙከራ የተሳሳተ አሳብ ነበር። እግዚአብሔር ራሱን መጠበቅ ስለሚችል የማንንም እንክብካቤ አይፈልግም። 
  2. እስራኤላውያን እግዚአብሔርን ማገልገል ያለባቸው በፍጹም ቅድስና መሆኑን ለማሳየት ነበር። ይህ ለእስራኤላውያን አዲስ ዘመን ነበር። አሁን ለእነርሱ ጻድቅ ንጉሥ አላቸው። ሕዝቡ እግዚአብሔርን መውደድና ማገልገል ጀምረዋል። ሰማያዊ ንጉሣቸውንም በኢየሩሳሌም እንዲኖር እያመጡት ነበር፤ ነገር ግን ንጉሣቸው እንዲመጣና በመካከላቸው ተገኝቶ እንዲባርካቸው አጥብቀው ከፈለጉ፥ ራሳቸውን ሙሉ ለሙሉ ለእግዚአብሔር ሊሰጡና በፍጹምነት ለእርሱ ሊታዘዙ ይገባ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ይህ ትምህርት ዛሬም ለእኛ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? 

ዳዊት ከስሕተቱ ተማረ። ከሦስት ወራት በኋላ ካህናቱ ልክ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት የእግዚአብሔርን ታቦት ተሸክመው ወደ ኢየሩሳሌም አመጡት (ዘጸ. 25፡15፤ ዘኁ. 1፡50-53)። 

ታቦቱ ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ቀን ዳዊት ያደረገውን ነገር መመልከት በጣም የሚያስደስት ነው። ቀኑ የታላቅ በዓል ቀን ሆነ። የነገሥታት ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም የመጣበት ቀን ነበር፤ ስለዚህ ዳዊት በሙሉ ኃይሉ ይጨፍር ነበር። የሳኦል ልጅ የሆነችው ሚስቱ ሜልኮል፥ ያሳየው የነበረው ሁኔታ ልክ እንዳልነበር ብትነግረውም እንኳ ዳዊት ልቡ በእግዚአብሔር ፊት ትክክል እንደ ነበር ያውቅ ነበር። ሌሎች ከሚያስቡት ነገር ይልቅ እግዚአብሔርን በማክበር ደስታውን በሙሉ ኃይሉ በመግለጥ ላይ ትኩረት አድርጎ ነበር። ሜልኮል ለእግዚአብሔር ከሚቀርብ አምልኮ ይልቅ ለባሏ ክብር ከፍተኛ ስፍራ በመስጠቷ እግዚአብሔር መሃን በማድረግ ቀጣት። 

ዳዊት ሌሉች እንዲጨፍሩ አላደረገም። ሌሎች ስላልጨፈሩም አልወቀሳቸውም። የእርሱ ጭፈራ በልቡ ይፈስስ የነበረው የታላቅ ደስታ መግለጫ ነበር። ሌሎች በአምልኮአቸው እንደማይጨፍሩና እንደማያጨበጭቡ ተመልክተን በምንተችበት ጊዜ፥ እኛም የምንጨፍረውና የምናጨበጭበው ለተሳሳተ ዓላማ እንደሆነና መንፈሳዊ ትዕቢት በሕይወታችን ውስጥ እንዳለ ምልክት ነው። እያንዳንዱ ሰው በሚፈልገው መንገድ እግዚአብሔርን የማምለክ ነጻነት አለው። አንዱ በሌላው ላይ ሊፈርድ አይገባም። አምልኮ የግል ጉዳይ ነው። በልቤ ያለውን የአምልኮ መንፈስ ትክክል መሆንና አለመሆን የሚያውቅ እግዚአብሔር ብቻ ነው። በሌላው ሰው አገልጋይ ላይ እንዴት እንደምንፈርድ እንጠነቀቅ (ሮሜ 14፡4 ያዕ. 4፡12)። 

የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለ አምልኮ ያለን ሚዛናዊ አመለካከት፥ አምልኮአችን ተገቢ እንዲሆንና መከፋፈል (ልዩነት) ከቤተ ክርስቲያናችን እንዲጠፋ እንዴት ይረዳናል? ለ) ሰዎች በሚያጨበጭቡበት፥ በሚጨፍሩበትና እልል በሚሉበት ጊዜ ዓላማቸው ምንድን ነው? ሐ) እነዚህ ነገሮች በመልካም ዓላማ የሚፈጸሙት መቼ ነው? መ) እነዚህ ነገሮች በመጥፎ ዓላማ የሚፈጸሙትስ መቼ ነው?

  1. እግዚአብሔር የዳዊትን ፍላጎት እንደሚያከብር ከእርሱ ጋር የዘላለም ቃል ኪዳን በማድረግ ገለጠ (2ኛ ሳሙኤል 7)። የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም ከተወሰደ በኋላ ዳዊት ታቦቱ ይኖርበት ዘንድ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስን ለመሥራት ፈለገ። እግዚአብሔር ግን ዳዊት ይህንን እንዲያደርግ አልፈቀደም። ዳዊት ቤተ መቅደሱን እንዳይሠራ የተከለከለበት ዋና ምክንያት እርሱ የጦር እንጂ የሰላም ሰው ስላልነበረ ነው (1ኛ ዜና 28፡3፤ 22፡8)። እግዚአብሔር ቤቱን እንዲሠራለት የፈለገው የሰላም ሰው ነበር። ሆኖም እግዚአብሔር በዳዊት ጥያቄና መሻት ደስ ተሰኝቷል፤ ስለዚህ ቤተ መቅደሱን የሚሠራው የእርሱ ልጅ እንደሚሆን እግዚአብሔር ነገረው። ቤተ መቅደሱን የሠራው የዳዊት ልጅ ሰሎሞን ቢሆንም እንኳ ለቤተ መቅደሱ ሥራ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ እንዲዘጋጅ ያደረገው ዳዊት ነበር (1ኛ ዜና 22)። 

እግዚአብሔር ዳዊት ቤተ መቅደሱን እንዲሠራ ከመፍቀድ ይልቅ፥ ለእርሱ ቤቱን እንደሚሠራለት፥ ዘላለማዊ መንግሥትን፥ ዘላለማዊ ዙፋንና ዘላለማዊ ቤትን እንደሚሰጠው ቃል ገባለት (2ኛ ሳሙ. 7፡16)። 

  1. ዳዊት ከዮናታን ልጅ ጋር የነበረው ግንኙነት (2ኛ ሳሙ. 9) 

ከብዙ ዓመታት በፊት፥ ዳዊት ለእርሱና ለቤተሰቡ በጎ በማድረግ ለዮናታን ቃል ኪዳን ገብቶለት ነበር። ዳዊት ኢየሩሳሌምን ከያዘና ጠላቱን ካሸነፈ በኋላ የገባውን ቃል ኪዳን አስታወሰ፤ ስለዚህ ከሳኦል ዘር የቀረ ሰው እንዳለ ማፈላለግ ጀመረ። የሳኦል ቤተሰብ በተደመሰሰ ጊዘ ሜምፊቦስቴ የሚባል ሽባ የሆነ የዮናታን ልጅ ተገኘ። ዳዊትም ሜምፊቦስቴን ወደ ኢየሩሳሌም ካስመጣ በኋላ የሳኦልን ቤትና ንብረት ሁሉ መለሰለት። በቤተ መንግሥትም ሁልጊዜ ከዳዊት ጋር በገበታ እንዲቀርብና እንዲበላ አደረገ፤ እንደተከበረ እንግዳውም ቆጠረው።

  1. ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር የፈጸመው ኃጢአት (2ኛ ሳሙ. 11-12) 

2ኛ ሳሙኤል 11 በመጽሐፉ ውስጥ ያለ የሽግግር ምዕራፍ ነው። ዳዊት ያደረጋቸውን ታላላቅ ነገሮች ከሚገልጠው ክፍል በመንግሥቱ ውስጥ ወደ አጋጠመው ችግር የሚያሸጋግር ምዕራፍ ነው። የዚህ ችግር ዋና ምክንያት ዳዊት የፈጸመው ኃጢአት ነበር። ቀድመን የዳዊትና የቤርሳቤህን ኃጢአት እንመለከታለን። በመቀጠልም ይህ ኃጢአት በመንግሥቱ ላይ ስላስከተለው ችግር እናያለን። 

ዳዊት ኢየሩሳሌምን በጦርነት አሸንፎ ከያዘ አሥር ወይም ከዚያ በላይ ዓመታት ተቆጥረዋል። ዳዊት የአገሪቱ ንጉሥ እንደመሆኑ የአገሪቱ የጦር አዛዥም ነበር፤ ስለዚህ ጠላቶቹን ለመዋጋት ከሠራዊቱ ጋር አብሮ ይሄድ ነበር። በጥንት ዘመን እስራኤላውያን ጦርነቱን የሚያካሄዱት፥ የዝናብ ወቅት ካለፈና ሰብል ከተሰበሰበ በኋላ በሚያዝያ ወር ነበር፤ ነገር ግን ዳዊት በዚህ ዓመት እንደ ልማዱ ወደ ጦርነት አልሄደም ነበር። 

አንድ ምሽት (ተሰላችቶ መሆን አለበት) ዳዊት ወደ ቤቱ ሰነት ላይ ወጣ። በመካከለኛው ምሥራቅ ብዙ ቤቶች የሚሠሩት ባለሰገነት እየተደረጉ ነበር። በጣም ሞቃት በሚሆንበት ጊዜ ሰገነት የሚተኙበት አለበለዚያም የሚዝናኑበት ስፍራ ነበር። በሰገነቱ ላይ በነበረ ጊዜ ዳዊት በጎረቤቱ ቤት በመታጠቢያ ቤቷ ሆና ሰውነቷን ስትታጠብ ቤርሳቤህን ተመለከታት። ዳዊትም የንጉሥነት ሥልጣኑን ያለ አግባብ በመጠቀም እንድትመጣና ከእርሱ ጋር እንድትተኛ አደረገ። የእግዚአብሔር ሰውና የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት አመነዘረ። ቤርሳቤህም አረገዘች ስለዚህም ከዚህ አሳፋሪ ነገር ለማምለጥ ዳዊት የሚችለውን ሁሉ አደረገ። ሁለት ነገሮችን ሞከረ፡- 

  1. በበዓል ቀን የቤርሳቤህን ባል ኦርዮን ከጦርነት ስፍራ ወደ ቤቱ እንዲመጣ አደረገ። ይህንን በማድረጉ ኦርዮ ወደ ቤቱ እንደሚገባና ከሚስቱ ጋር እንደሚተኛ ተስፋ አድርጎ ነበር። ኦርዮ ግን ስለ እስራኤል ጦር ገዶት፥ ይህንን ግብዣ እምቢ ብሎ ወደ ቤቱ ሳይገባና ሚስቱን ሳይጎበኝ ወደ ጦር ሜዳ ተመለሰ። 
  2. ዳዊት ለጦሩ መሪ ለኢዮአብ ኦርዮንን ከጦሩ ፊት ለፊት እንዲያሰልፈውና ተመትቶም እንዲሞት ጥለውት እንዲሸሹ እንዲያደርግ አዘዘው፤ ስለዚህ ዳዊት ኦርዮንን ለመግደል ጦርነቱን ተጠቀመበት። ዳዊት አመንዝራ ብቻ ሳይሆን ነፍሰ ገዳይም ሆነ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ብዙ ጊዜ አንድ ኃጢአት ሠርተን እርሱን ለመሸፈን ስንሞክር፥ ወደ ሌላ ኃጢአት የሚመራን እንዴት ነው? ለ) ይህ ነገር እንዴት እንደሚሆን፥ ከራስህ ሕይወት ሥዕላዊ መግለጫዎችን ስጥ። ይህን የምናደርገው ለምንድን ነው?

ስለዚህ ጉዳይ በጣም የሚያሳዝነው ነገር ኦርዮ ከዳዊት ምርጥ ወታደሮች አንዱ የነበረ መሆኑ ነው። ኦርዮ ምርጥ ተብለው ከሚጠቀሱት ከ30 የዳዊት ወታደሮች አንዱ ነበር (2ኛ ሳሙኤል 23፡39 ተመልከት)።

እግዚአብሔር የዳዊትን ኃጢአት ሳይቀጣ አልተወውም። ምናልባት ዳዊት ወደ አመንዝራነትና ነፍሰ ገዳይነት እንደተመለሰ ማንም ሰው አያውቅም ይሆናል። ዳዊት ግን ያውቅ ነበር። ከመዝሙራቱ በአንዱ ኃጢአቱን ለእግዚአብሔር ባለመናዘዙ ምክንያት፥ የተሰማውን የውስጥ መቃተትና ሥጋዊ ሕመም ይናገራል [መዝ. (50]። 

እግዚአብሔር ደግሞ ይህን ያውቅ ነበር፤ ስለዚህ የፈጸመውን ተግባር ክፉነት አስረግጦ ሊነግረው ነቢዩ ናታንን ላከበት። የዳዊትን ኃጢአት ታላቅነት በሚገልጥ መንገድ አንድ ምሳሌ ነግሮት ስለ ኃጢአቱ ወቀሰው። ዳዊት በፍርድ መሞት እንኳ እንደሚገባው ያውቅ ነበር። ዳዊት ከኃጢአቱ ንስሐ ቢገባም እንኳ በቀረው የሕይወት ዘመኑ በቤቱ መከፋፈልና ችግር እንደማይጠፋ እግዚአብሔር ነገረው። የቀረው የ2ኛ ሳሙኤል ታሪክ የሚናገረው ይህ ፍርድ በዳዊት ላይ እንዴት እንደተፈጸመ ነው። የእግዚአብሔር ፍርድ የዳዊትና የቤርሳቤህን የመጀመሪያን ልጅ ሞት የሚያካትት ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የጎለመሱ ክርስቲያኖች እንኳ በኃጢአት ሊወድቁ እንደሚችሉ ይህ ታሪክ ምን ያስተምረናል? ለ) የዚህ ዓይነት ኃጢአት እንዳንሠራ ራሳችንን እንዴት መጠበቅ እንችላለን? ) ስለ እግዚአብሔር ይቅር ባይነት ከዚህ ታሪክ የምንማረው ነገር ምንድን ነው? መ) ኃጢአት ይቅር ከተባለ በኋላ እንኳ ስለሚያስከትላቸው ነገሮች ከዚህ ምን እንማራለን?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d