የአንድ መሪ መንፈሳዊ ሕይወት በአጠቃላይ በሰዎች መንፈሳዊ ሕይወት ላይ ታላቅ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ተመልክተናል። ብዙ ጊዜ መሪው ለእግዚአብሔር ታዛዥ በሚሆንበትና ራሱን ለእግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ አሳልፎ በሚሰጥበት ጊዜ፥ ሕዝቡም ለእግዚአብሔር ራሱን አሳልፎ በመስጠት ታዛዥ ይሆናል። መሪው ለእግዚአብሔር በሙላት በማይታዘዝበት ጊዜ፥ ሕዝቡን ከእውነት በቀላሉ ያርቀዋል። 1ኛና 2ኛ ነገሥትን በምናነብበት ጊዜ፥ የእስራኤልና የይሁዳ ነገሥታት የሕዝቡን መንፈሳዊ ሕይወት በከፍተኛ ደረጃ እንዴት እንደነኩት እንመለከታለን።
የምንኖርበት ዘመን በርካታ ስጦታ ያላቸው የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ወይም ሰባኪዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚሠሩበት ዘመን ነው። ራሳቸውን ለእግዚአብሔር በሰጡት ጥቂቶች፥ እግዚአብሔር በከፍተኛ ሁኔታ ይጠቀምባቸዋል። ለራሳቸው ጥቅም በስግብግብነት የሚሠሩና ብዙዎችን የሚያስኮበልሉም አሉ። ጳውሎስ ለእግዚአብሔር መንጋ የማይራሩ «ጨካኝ ተኩላዎች» እንደሚነሡ አስጠንቅቋል። እንዲያውም እነዚህ ሐሰተኛ አስተማሪዎች የሚነሡት ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደሆነ ተናግሯል (የሐዋ. 20፡29-30 ተመልከት)። በዚህ ዘመን በርካታ ሐሰተኛ አስተማሪዎችና መሪዎች ስላሉ፥ የእውነትን መንገድ ለመከተል ራሳችንን የሰጠን ሰዎች፥ የራሳችንና የመንጋችንን ሕይወት ከጥፋትና ከኩብለላ መጠበቅ አለብን። በዚህ ዘመን የቤተ ክርስቲያን መሪዎች መሥራት ከሚገባቸው ዋና ዋና ሥራዎች አንዱ ምዕመናን በስሕተት ትምህርት እንዳይወድቁ መጠበቅ ነው። ይህንን ለማድረግ ግን መንፈሳዊ ሕይወታችን መንጋው ክርስቶስን ለመከተል የሚችልበትን መልካም ምሳሌነት የሚያሳይ እንዲሆን እርግጠኞች መሆን አለብን። የሐሰት አስተማሪዎች በቤተ ክርስቲያኖቻችን ያሉትን ምዕመናን እምነት ለማጥፋት እንዳይችሉ፥ የመሪዎች ሕይወት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) አንድ መሪ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሕይወቱ መልካም ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው? ለ) ይህ በቤተ ክርስቲያንህ እንዴት እንደተፈጸመ መግለጫ ስጥ። ሐ) አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሕይወቱ ከፍተኛ የክፋት ተጽዕኖ ሊያደርግ የሚችለው እንዴት ነው? መ) ይህ ነገር በቤተ ክርስቲያንህ እንዴት እንደተፈጸመ መግለጫ ስጥ።
የውይይት ጥያቄ፥ 1ኛ ነገሥት 12-16 አንብብ። ሀ) በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ያገለገሉ ነገሥታትን ዘርዝር። ለ) ከየትኛው መንግሥት እንደነበሩ ጥቀስ። ሐ) ምን ዓይነት መንፈሳዊ ባሕርይ እንደነበራቸውም ጥቀስ። መ) በነገሡበት ዘመን የተፈጸሙትን ጠቃሚ ነገሮች ዝርዝር።
- ሮብዓም፡- የይሁዳ ንጉሥ (931-913 ዓ.ዓ.)
አባቱ ሰሎሞን ከሞተ በኋላ ሮብዓም በእስራኤል ሁሉ ላይ ነገሠ። የእስራኤል ሕዝብ ሊያነግሡት በመጡ ጊዜ አንድ ቅድመ ሁኔታ ጠየቁት። ያለባቸውን የሥራ ጫናና ግብር ቢቀንስላቸው እንደሚያነግሡት ቃል ገቡለት። ይህንን ባያደርግ ግን እንደሚያምፁበት አስታወቁት። ሮብዓምም በዕድሜ የገፉትን ሰዎች ምክር ሳይሆን፥ የወጣቶቹን ምክር ስለሰማ ቀንበራቸውን የባሰ እንደሚያከብድባቸው ነገራቸው። በዚህ ጊዜ አሥሩ ነገዶች ዓመፁበትና ቀዳማዊ ኢዮርብዓምን ንጉሣቸው ይሆን ዘንድ መረጡት። የይሁዳና የብንያም ነገዶች ግን ከሮብዓምና ከዳዊት ሥርወ መንግሥት ከመጡ ነገሥታት ጋር ቆዩ።
በሮብዓም ዘመነ መንግሥት፥ የእስራኤል ሕዝብ በሁለት ታላላቅ መንግሥታት ተከፈለ። የመጀመሪያው፥ አሥሩን ነገዶች የያዘው የሰሜኑ መንግሥት ሲሆን፥ እስራኤል ተብሎ ተጠራ። አንዳንድ ጊዜ ኤፍሬም ተብሎም ይጠራል። ከሰሜኑ ክፍል የሚበዛው የኤፍሬም ነገድ ነበርና። በነቢያት መጻሕፍት በኋላ ዋና ከተማቸው ባደረጉት በሰማርያ ስምም ይጠራል። የነቢያትን መጽሐፍ በምናነብበት ጊዜ፥ የእስራኤልን ስም ስናገኝ ያ ቃል የሚናገረው በአጠቃላይ ለእስራኤል ይሁን ወይም ለሰሜኑ የእስራኤል መንግሥት መወሰን በጣም አስፈላጊ ነው።
ሁለተኛ፥ የደቡብ መንግሥት ደግሞ ይሁዳ ተብሎ ተጠራ፥ አንዳንድ ጊዜ የዚህ መንግሥት ዋና ከተማ በሆነችው በኢየሩሳሌም ስምም ይጠራል። የብንያም ነገዶችም ከይሁዳ ጋር ነበሩ።
እስራኤልና ይሁዳ በተከፋፈሉ ጊዜ ብዙዎች ካህናትና ሌዋውያን እንደዚሁም እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሌሎችም ሰዎች ከእስራኤል ወደ ይሁዳ ተሰደዱ።
በሮብዓም ዘመን በእስራኤልና በይሁዳ መካከል ብዙ ጊዜ ጦርነት ይካሄድ ነበር። በመጀመሪያ ሮብዓም የጌታን መንገድ ተከተለ። መንግሥቱ የበለጠ በጸናች ጊዜ ግን በእግዚአብሔር ላይ ዓመፀና በመንግሥቱ ውስጥ የጣዖት አምልኮ እንዲንሰራፋ አደረገ። ውጤቱም እግዚአብሔር ግብፃውያን እንዲመጡና እንዲወጉት፥ ከከተሞቻቸውም አብዛኛውን ከይሁዳ መንግሥት እንዲወሰዱ ማድረጉ ነበር። በሮብዓም ዘመነ መንግሥት የደቡብ መንግሥት ኃይል ቀስ በቀስ እየቀነሰ ሄደ።
- ቀዳማዊ ኢዮርብዓም የእስራኤል ንጉሥ (931-910 ዓ.ዓ.)
የሰሎሞን አስተዳዳሪዎች ከነበሩ ሰዎች መካከል አንዱ የሆነው ኢዮርብዓም የሰሜኑ መንግሥት ንጉሥ ይሆን ዘንድ በአሥሩ ነገዶች ተመረጠ። ለእግዚአብሔር፥ የሚታዘዝ ከሆነ ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን እንደሚያደርግ እግዚአብሔር ለኢዮርብዓም ነገረው (1ኛ ነገ. 11፡38)። ኢዮርብዓም ግን ይህንን ሥልጣን እንደጨበጠ ወዲያውኑ በእግዚአብሔር ላይ ዓመፀ። በሰሜኑ የእስራኤል መንግሥት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ እግዚአብሔርን እንዳያመልኩ፥ ኢዮርብዓም ሁለት የማምለኪያ ማዕከሉችን አሠራ፤ ከእነዚህም አንዱ በስተሰሜን የሚገኘው ዳን የሚባለው ስፍራ ሲሆን፥ ሌላኛው ደግሞ በስተደቡብ ቤቴል ተብሉ የሚጠራው ስፍራ ነው። በሁለቱም ማዕከሎች ሕዝቡ የሚያመልኩትን የጥጃ ምስል ሠራላቸው። በዚህም ኢዮርብዓም ሕዝቡን ወደ ጣዖት አምልኮ መራቸው።
እስራኤላውያን በምድረ በዳ የጥጃ ምስል እንዳመለኩ ታስታውሳለህ። ይህ የጥጃ ምስል አምልኮ ከግብፅ የመጣ ነው። ይህ አፒስ የሚባለው ለእንስሳት፥ ለሰዎችና ለእርሻ ጭምር ሕይወትን፥ ጤንነትን፥ ብርታትንና ፍሬያማነትን ይሰጣል ተብሎ የሚታሰበው አምላክ (ጣዖት) ምስል ነበር። አንዳንድ ምሁራን ኢዮርብዓም የግብፃውያንን አምልኮ ከከነዓናዊያን ጥጃን ከማምለክ ጋር ቀላቅሉአል ይላሉ። የኢዮርብዓም ፍላጎት ሕዝቡ ለአምልኮ ወደ ኢየሩሳሌም ከሚሄዱ ይልቅ፥ በዚህ ስፍራ ጣዖትን በመሥራት የእግዚአብሔር ምልክት ብቻ እንዲሆንና ሕዝቡ እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ ቢሆንም፥ እነዚህ የጥጃ ምስሎች ወዲያውኑ ጣዖት ሆነው መመለክ ጀመሩ። በኋላም ከባዓል አምልኮ ጋር ተቀይጦ፥ ሰዎች በመሥዋዕትነት የሚቀርቡበት ቦታ ሆነ (2ኛ ነገ. 17፡15-17)።
ኢዮርብዓም ይህንን ባደረገ ጊዜ እግዚአብሔር ነቢይ ላከና እንዲገሥጸውና መንግሥቱም ለረጅም ጊዜ እንደማትቆይ እንዲነግረው አደረገ። መሠዊያው እንደሚረክስ የተነገረው ትንቢትም ከ300 ዓመታት በኋላ በኢዮስያስ ተፈጸመ (2ኛ ነገ. 23፡15-20 ተመልከት)።
የውይይት ጥያቄ፥ ይህ ትንቢትና ፍጻሜው ስለ እግዚአብሔር ቃል ኃይል ምን ያስተምረናል?
ከይሁዳ የሆነው የዚህ ያልታወቀ ነቢይ ታሪክ በጣም አሳዛኝ ነው። እግዚአብሔርን ከመስማት ይልቅ ሌላውን ነቢይ ሰማና ስላለመታዘዙ ሞተ፤ ስለዚህ በአልታወቀ ነቢይ ላይ የደረሰው ነገር ኢዮርብዓምንና የእግዚአብሔርን ሕዝብ በሙሉ፥ ለእግዚአብሔር ቃል በጥንቃቄ ስለ መታዘዝ አስፈላጊነት አስተምሯል።
- የይሁዳ ንጉሥ አቢያ (913-910 ዓ.ዓ.)
አቢያ የነገሠው ለሦስት ዓመታት ብቻ ነበር። ልክ እንደ አባቱ እንደ ሮብዓም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገርን አደረገ። የጣዖት አምልኮ እንዲስፋፋ ፈቀደ።
በእነዚህ ሦስት ዓመታት በእስራኤል ከነገሠው ከቀዳማዊ ኢዮርብዓም ጋር ከፍተኛ ጦርነት አካሂዷል። አቢያ አንዳንዶቹን የእስራኤል ግዛቶች በጦርነት ለመያዝ ችሉ ነበር።
- የይሁዳ ንጉሥ አሳ (910-869 ዓ.ዓ.)
በይሁዳ ከነገሡ ነገሥታት መካከል መልካም ከነበሩት አንዱ ነው። አባቱና አያቱ የሠሩትን ክፉ ነገር ሁሉ ከአገሪቱ ለማስወገድ ሞከረ፡፡ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው እንደ መሆኑ መጠን የባዕድ አምልኮ መሠዊያዎችን አፈራረሰ። ጣዖታትን ሁሉ ነቃቅሉ ጣለ። የጣዖት አምልኮ የሚፈጸምባቸውን ከፍተኛ ስፍራዎች ሁሉ አጠፋ። ሕዝቡንም ለሙሴ ሕግ እንዲታዘዙ ነገራቸው። በይሁዳ ምድር መንፈሳዊ መነቃቃት ስለነበረ፥ በእስራኤል ያሉ እግዚአብሔርን በታማኝነት ያመልኩ የነበሩ ሰዎች ወደ ይሁዳ ምድር መጡ።
አሳ ያስተዳድር በነበረባቸው በመጀመሪያዎቹ አሥር ዓመታት ፍጹም ሰላም ነበር። በዚህ ጊዜ የይሁዳ ከተሞችንና ጦሩን አደራጀ፤ ነገር ግን ከእስራኤል ጋር በተደረገው ጦርነት የእስራኤል ንጉሥ አሳን ድል ለማድረግና አንዳንድ ከተሞችን ከይሁዳ መንግሥት ለመውሰድ ቻለ። ከኢየሩሳሌም 8 ኪሎ ሜትር በስተ ሰሜን ርቃ የምትገኘውን የራማ ከተማን ለመውሰድም በቃ። ይህንን ያደረገበት አንዱ ምክንያት የእስራኤል ሰዎች እግዚአብሔርን ለማምለክ ወደ ይሁዳ እንዳይሄዱ ነበር። አሳ በእስራኤል በተጠቃበት ጊዜ የሶርያን እርዳታ ጠየቀና በአንድነት እስራኤልን አጥቅተው ከይሁዳ እንዲወጡ አደረጉ።
የሚያሳዝነው በዘመነ መንግሥቱ መጨረሻ አሳ ፊቱን ከእግዚአብሔር መለሰ። እንዲያውም በሶርያ ላይ መደገፉን በመቃወም ስለተናገረው የእግዚአብሔር ነቢይ የነበረውን አናኒን አሰረው(1ኛ ዜና 16፡7-10 )።
- የእስራኤል ንጉሥ ናዳብ (910-909 ዓ.ዓ.)
የቀዳማዊው ኢዮርብዓም ልጅ የነበረው ናዳብ በሰሜኑ መንግሥት ላይ ለመንገሥ የቻለው ሁለት ዓመት ብቻ ነበር። ልክ እንደ አባቱ ክፉ መሪ ነበር። ባኦስ ገደለውና ልክ ነብዩ እንደተነበየው መንግሥቱ ከቀዳማዊ ኢዮርብዓም ቤት ተወሰደ (1ኛ ነገ. 14)።
- የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ (909-886 ዓ.ዓ.)
ናዳብን ገድሉ በእስራኤል ላይ የነገሠ ሰው ነበር። በመጀመሪያ የወሰደው እርምጃ በእስራኤል ላይ ባገኘው የንጉሥነት ሥልጣን ችግር ይፈጥሩብኛል ብሎ ያሰባቸውን የኢዮርብዓምን ዝርያዎች ሁሉ መፍጀት ነበር።
ባኦስ ከይሁዳ ጋር የተዋጋ መሪ ሲሆን፥ ሶርያ ከሰሜን መጥታ እስክትዋጋው ድረስ ተሳክቶለት ነበር። ባኦስ ክፉ ነበርና በቀዳማዊ ኢዮርብዓም የተጀመረው የጣዖት አምልኮ እንዲቀጥል ስላደረገ፥ እግዚአብሔር መንግሥቱን እንደሚወስድበት ተናገረው።
- የእስራኤል ንጉሥ ኤላ (886-885 ዓ.ዓ.)
የባኦስ ልጅ ኤላ በእስራኤል ላይ የነገሠው ለሁለት ዓመታት ብቻ ሲሆን፥ የእኩሌቶቹ ሰረገሎች አለቃ በሆነው በዘምሪ ተገደለ። በኤላ ሞት የባኦስ ቤተሰብ ነቢዩ ኢዩ በተናገረው መሠረት ተደመሰሰ (1ኛ ነገ. 16፡1-4)።
- የእስራኤል ንጉሥ ዘምሪ (885 ዓ.ዓ.)
ዘምሪ የተባለው ሰው በኃላፊነት ለሰባት ቀናት ብቻ ነገሠና የጦሩ አዛዥ በነበረው በዘንበሪ ተገደለ።
- የእስራኤል ንጉሥ ዘንበሪ (885-874 ዓ.ዓ.)
ስለ ዘንበሪ አገዛዝ በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ የተነገረን ነገር ባይኖርም፥ ከእስራኤል ታላላቅ ነገሥታት አንዱ እንደነበር በዓለም ታሪክ ተጽፎ እንመለከታለን። ሥርወ መንግሥቱም የሰሜኑን መንግሥት ጥንካሬ ሊጨምርና ዝነኛ ሊያደርገው ችሎ ነበር። ዘንበሪ የጦሩ አዛዥ ሆኖ በሚነግሥበት ጊዜ የመጀመሪያው ዐቢይ ትኩረቱ የሰሜኑን መንግሥት ማጠናከር ነበር። ያደረገው የመጀመሪያ ነገር ዋና ከተማውን ወደ ሰማርያ ማዞርና ከጥቃት ለመከላከል በዙሪያዋ ምሽግ መሥራቱ ነበር። የሰማርያ ከተማ እስከ 722 ዓ.ዓ. ድረስ የሰሜኑ መንግሥት ዋና ከተማ ሆና ነበር። በበርካታ የነቢያት መጻሕፍት ውስጥ የሰሜኑ መንግሥት በዋና ከተማው ስም ሰማርያ በመባል ይታወቅ ነበር።
ዘንበሪ ሞአባውያንን ለማሸነፍና በጣም ሀብታም ለመሆን የቻለ ሰው ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ከይሁዳ ጋር የተደረገ አንዳችም ጦርነት ያለ አይመስልም።
ዘንበሪ አገዛዙን ለማስፋፋት ይችል ዘንድ ከፎኔሽያ ጋር ስምምነት አድርጎ ነበር። ፍኔሺያ በሰሜን ምዕራብ የሚገኝ የጢሮስና የሲዶና ግዛት ነበር። ጢሮስና ሲዶና እጅግ ጠንካራ አገር የነበሩና በሜዴትራኒያን ባሕር አካባቢ ከሚገኙ አገሮች ሁሉ በዓለም አቀፍ ንግዳቸው የታወቁ ነበሩ፤ ደግሞም የበአል አምልኮ ማዕከልም ነበሩ።
ስምምነቱን ሕጋዊ ለማድረግ ዘንበሪ ልጁን አክዓብን ከፎኔሺያ (ሲዶና) ንጉሥ ሴት ልጅ ከኤልዛቤል ጋር አጋባው። ይህ ስምምነት ለሕዝቡ መልካም ሊሆን ቢችልም፥ በመንፈሳዊ አንጻር ግን ለሰሜኑ መንግሥት እጅግ የከፋ ነገር አስከትሏል። የአክዓብ ሚስት የነበረችው ኤልዛቤል የበአልን አምልኮ ወደ እስራኤል ስላመጣች፥ አብዛኛዎቹን የእግዚአብሔር ነቢያት አስገደለች። በዚህ ምክንያት ዘንበሪ «ከእርሱ አስቀድሞ ከነበሩት ይልቅ እጅግ ከፋ» ተብሎ ተጽፏል (1ኛ ነገ. 16፡25)።
- የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ (874-853 ዓ.ዓ.)
አክዓብ ጥሩ የፖለቲካ መሪ ነበር። የሰሜኑን መንግሥታት የግዛት ክልል ለማስፋፋት፥ ለመከላከል ምቹ የሆኑ ከተሞችን ለመገንባት፥ ወዘተ. ችሉ ነበር።
አክዓብ ከደቡብ የይሁዳ መንግሥት ጋርም ጥሩ ኅብረት ለመፍጠር ችሎ ነበር። ሴት ልጁን አታሊያህን በእርሱ ዘመን የይሁዳ ንጉሥ ለነበረው ለኢዮሳፍጥ ልጅ ለኢዮራም ድሮለት ነበር። ይህም የግንኙነታቸው ማሰሪያ ነበር። ይህ በይሁዳ ሕዝብ ሁሉ ላይ ታላቅ ጥፋት የሚያስከትል ክፉ ተግባር እንደነበረ ኢዮሳፍጥ አላስተዋለም ነበር። ከሞላ ጎደል የዳዊትን ቤት በሙሉ ሊያጠፋ ተቃርቦ ነበር።
አክዓብ የበአል አምልኮን ስላስፋፋና ይህም እጅግ ክፉ ተግባር ስለነበር «ከእርሱ በፊት ከነበሩት ሁሉ ይልቅ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ» ተብሉ ስለ እርሱ ተጽፏል (1ኛ ነገ. 16፡30)።
በአክዓብ ዘመነ መንግሥት መጨረሻ አካባቢ ከሶርያ ጋር ጦርነት የተደረገ ቢሆንም፥ በኤልያስ እርዳታ አክዓብ ጦርነቱን በድል ለመወጣት ችሏል። በኋላም ከይሁዳ ጋር በአንድነት በመተባበር በብሉይ ኪዳን ብዙ ጊዜ አራም ተብሎ ከሚጠራውና በአሁኑ ጊዜ በመስጴጦምያ ዋናው ኃይል ከሆነው ከሶርያ ጋር ተዋግቷል። በዚህም ጦርነት አክዓብ ተገደለ።
የእስራኤል ንጉሥ የነበረው አክዓብ ከእግዚአብሔር ነቢይ ከኤልያስ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ነበረው።
የውይይት ጥያቄ፥ ከእነዚህ የእስራኤልና የይሁዳ ነገሥታት ልትማር የምትችላቸውን አንዳንድ መንፈሳዊ ትምህርቶች ዘርዝር።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)