2ኛ ነገሥት 18-25

ለእግዚአብሔር ሕዝቦች በጣም ጥሩ መምህራን ከሆኑት ነገሮች አንዱ ታሪክ መሆን አለበት። ከዚህ ቀደም የተፈጸሙ ነገሮች ብዙ ጊዜ ወደፊትም ይደገማሉ። ከዚህ ቀደም በነበረው ዘመን የእግዚአብሔር ሰዎች ችግር ገጥሟቸው ከነበረ ወደፊትም ተመሳሳይ ችግር እንደሚገጥማቸው ጥርጥር የለውም። የሐሰት ትምህርቶችን በምሳሌነት ውሰድ። ዛሬ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስቸግሩ የሐሰት ትምህርቶችን፥ በአብዛኛው ከዚህ ቀደም የእግዚአብሔርን ሕዝብ ያስቸግሩ የነበሩ ናቸው። ቤተ ክርስቲያን ከዚህ ቀደም የሐሰት ትምህርቶችን ያስተናገደችበት መንገድ፥ ዛሬ የሐሰት ትምህርቶችን በሚመለከት ትምህርት ሊሆንን ይገባል። የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ ማጥናት አስፈላጊ የሆነበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው። እንደዚሁም በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝብ የሆኑትን የአይሁድ ታሪክ ልናጠና አስፈላጊ የሆነበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው። እንደዚሁም እነርሱም ልክ እንደ እኛ ሰዎች ስለነበሩ፥ የገጠሟቸው ችግሮችና ፈተናዎች እኛንም ይገጥሙናል። እነርሱን በአስቸገሯቸው ተመሳሳይ ኃጢአቶች የመውደቅ ዝንባሌ በእኛም ላይ ይታያል ማለት ነው (1ኛ ቆሮ. 10፡11 ተመልከት)። 

የይሁዳ ሕዝብ ከታሪክ ለመማር አልቻለም። ወገኖቻቸው የሆኑ እስራኤላውያን ወደ ምርኮ የተወሰዱት ለእግዚአብሔር መታዘዝና እርሱን ምምለክ እምቢ ስላሉ ነበር። ከዚህ ተምረው ወደ እግዚአብሔር ከመመለስ ይልቅ፥ ልክ በሰሜኑ መንግሥት እንደነበሩት እስራኤላውያን ተማርከው እስኪሄዱ ድረስ በኃጢአታቸው ቀጠሉ። ታሪክ ራሱን በመድገም፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደ ወገኖቻቸው እስኪማረኩ ድረስ የወገኖቻቸውን ኃጢአት አደረጉ። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የቀድሞ አባቶቻችን በወደቁበት ተመሳሳይ በሆነ ኃጢአትና ችግር ስለ መውደቅ ዝንባሌ ከዚህ ምን እንማራለን? ለ) የራስህን ቤተ ክርስቲያንና በዘመናት ሁሉ የነበሩ አብያተ ክርስቲያናትን ታሪክ ማጥናት እጅግ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? ሐ) ስለ ታሪካችሁ በቤተ ክርስቲያንህ የሚገኙ ሌሎች መሪዎችን ማስተማር የምትችሉት እንዴት ነው? መ) ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች ልታቀርብ ስለምትችላቸው ነገሮች አሳብ ስጥ።

የውይይት ጥያቄ፥ 2ኛ ነገሥት 18-25 አንብብ። ሀ) በእነዚህ ዓመታት በይሁዳ የነገሡትን ነገሥታት ዘርዝር። ለ) የእያንዳንዳቸው ባሕርይ ምን ይመስል ነበር? ሐ) የእነዚህ ነገሥታት ዘመናት ዋና ዋና ተግባራት ምን ነበር? መ) የይሁዳን ውድቀትና ሕዝቡ ለምን ወደ ምርኮ እንደተወሰዱ ግለጥ።

እስራኤል በምርኮ የተወሰደችው በ722 ዓ.ዓ. ነበር። እስራኤላውያን በሕዝብነት ወደ አገራቸው ጨርሶ አልተመለሱም። ይልቁንም በዓለም ሁሉ ባሉ ሕዝቦች መካከል ተበተኑ። ይህ ሕዝብ ምን እንደደረሰባቸው ስለማይታወቅና ወደ አገራቸው ጨርሶ ስላልተመለሱ፥ አንዳንድ ሰዎች «የጠፉት አሥሩ የእስራኤል ነገዶች» በማለት ጠርተዋቸዋል። እግዚአብሔር ወደፊት አንድ ቀን ወደ አገራቸው እንደሚመልሳቸው ተስፋ ሰጥቶአቸዋል (ኢሳ. 11፡11-16)። ዘመናዊው የእስራኤል መንግሥት በ1948 ዓ.ም. መመሥረቱ የዚህ ቃል ኪዳን ከፊል ፍጻሜ ነው።

ይሁዳ የተባለው የእስራኤላውያን ደቡባዊ መንግሥት፥ አገራቸውን ለ136 ዓመታት ለማቆየት ችሉ ነበር። የይሁዳ መንግሥት ወደ ምርኮ የተወሰደው በ586 ዓ.ዓ. ነበር። በእግዚአብሔር ጸጋ ምክንያት ግን የዚህ ሕዝብ ቅሬታዎች ከ50 ዓመታት በኋላ በ539 ዓ.ዓ. ወደ አገራቸው ለመመለስ ችለዋል። ይህንን ጉዳይ በይበልጥ በመጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ ውስጥ እናጠናለን። 

  1. የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ፡- (716-687 ዓ.ዓ.) 

ሕዝቅያስ ወጣት በነበረ ጊዜ፥ የእስራኤልን ሕዝብ ውድቀትና እንዴት ወደ ምርኮ እንደ ተወሰዱ በዓይኑ ተመልክቷል። ይህ ነገር ሕይወቱን በጣም ሳይነካው አልቀረም፤ ስለዚህ ወደ ንጉሥነት ሥልጣኑ በመጣ ጊዜ እንደ አባቱ እንደ አካዝ ሳይሆን፥ እግዚአብሔርን ፈራ። ሕዝቅያስ ታላቅ ሃማኖታዊ መሪ ነበር። የይሁዳን ሕዝብ እግዚአብሔርን ወደ ማምለክ ለመመለስ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ አድርጓል። ከዳዊት ቀጥሉ እግዚአብሔርን በመፍራት ከሁሉ የተሻለ በመሆኑ የሚጠቀስ ታላቅ መሪ ሕዝቅያስ ነው።

ሕዝቅያስ በአሦር መንግሥት ቁጥጥር ሥር ቢሆንም፥ የሕዝቡን ሃይማኖታዊ ሕይወት ለመለወጥ የሚሠራበት ነፃነት ነበረው። እስራኤላውያን ወደ ምርኮ የተወሰዱት እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ላደረገው ቃል ኪዳን ባለመታዘዛቸው እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር፡ ስለዚህ ሕዝቅያስ ለእግዚአብሔር ለመታዘዝ አጥብቆ ጣረ። ለረጅም ጊዜያት ተዘግቶ የነበረውን ቤተመቅደስ በመክፈት እና በመጠገን ለአምልኮ የሚመች መልካም ስፍራ አደረገው። በእስራኤል ቀርተው የነበሩ አይሁዳውያንን ለፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም በመምጣት እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ ጋበዛቸው። የሐሰተኛ አምልኮ መሣሪያ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ ለማጥፋት ጣረ። ሙሴ ከብዙ ዓመታት በፊት ሠርቶት የነበረውንና በኋላ እስራኤላውያን የአምልኮ መሣሪያ አድርገውት የነበረውን የነሐስ እባብ አጠፋ (ዘኁ. 21፡4-9 ተመልከት)። የቤተ መቅደሱ አምልኮ በሥርዓት እንዲካሄድ ሕዝቅያስ የሌዋውያንን አገልግሎትና አሥራትን የመሰብሰቢያ ዘዴዎችን በሚገባ አደራጀ። ሕዝቅያስ በዚያን ዘመን ከነበረው ከኢሳይያስ ጋር በቅርበት ሳይሠራ አልቀረም። 

ሕዝቅያስ በመጨረሻ ከአሦራውያን ጋር እንደሚዋጋ ያውቅ ነበር፣ ስለዚህ የይሁዳን ብሔር ለመከላከል በከተሞች ምሽግ ሠራ። አሦራውያንንም ለማረጋጋትና ለማስደሰት ከቤተ መቅደስ ወርቅ አውጥቶ ሰጣቸው፤ ሆኖም በ701 ዓ.ዓ. አሦራውያን ወረሩትና ከኢየሩሳሌም ከተማ በቀር የይሁዳን መንግሥት በጠቅላላ ወሰዱ። በግንቦች የታጠሩ አርባ ስምንት ከተሞች ተደመሰሱና 200000 አይሁድም በምርኮ ተወለዱ። ሕዝቅያስ ግን በእግዚአብሔር ስለታመነ፥ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ከጥፋት አዳነ። የአሦር ንጉሠ ነገሥት ግዛት አንዱ ክፍለ ሀገር በነበረው በባቢሎን በተነሣው ዓመፅ የአሦር ጦር ወደ አገሩ ለመመለስ ግድ ሆነበት። 

በኋላም ሕዝቅያስ በጠና ታመመ። በእግዚአብሔር ምሕረት ግን 15 ዓመታት በዕድሜው ላይ ተጨመረለት። በዚህ ጊዜም ልጁ ምናሴ አብሮት መግዛት ጀመረ። ከበሽታው በማገገሙ ደስታቸውን ሊገልጹለት ለመጡት ለባቢሎን ልዑካን ባለማስተዋል ሀብቱን በሙሉ አስጎበኛቸው። ባቢሎናውያን አንድ ቀን ኢየሩሳሌምን እንደሚያጠፉና ወርቁን እንደሚወስዱበት ለመገንዘብ አልቻለም ነበር። 

  1. የይሁዳ ንጉሥ ምናሌ፡- (692-642 ዓ.ዓ.)

በይሁዳ ላይ ከነገሡ ነገሥታት ሁሉ ረጅም ዘመን የነገሠው ምናሴ ነው። ለ55 ዓመታት በሥልጣን ላይ ቆይቷል። ይህ ዘመን ከሕዝቅያስ ጋር አብሮ የገዛበትን ጊዜንም ይጨምራል።

ምናሴ ሕዝቅያስ ከሞተና ብቻውን ንጉሥ መሆን ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ በእግዚአብሔር ላይ ፊቱን በማዞር ጀርባውን ሰጠው። ሕዝቅያስ በይሁዳ ያደረጋቸውን ተሐድሶዎች በሙሉ ለማበላሸት አሰበ። ሕዝቡን ወደ ጣዖት አምልኮ መራ። ትላልቅ የአምልኮ ስፍራዎችንና የጣዖታት መሠዊያዎችን ለበአልና የአሞናውያን አምላክ ለሆነው ለሞሎክ አሠራ። ከኢየሩሳሌም ከተማ ውጭ ለሞሎክ ጣዖት ልጆቹን ሳይቀር ሰዋ። በቤተ መቅደሱ ውስጥ የጣዖት አምልኮን አቆመ። እግዚአብሔርን ለማምለክ የፈለጉትን እጅግ ብዙ ሰዎችን ገደለ። እንዲያውም የአይሁድ አፈ ታሪክ ኢሳይያስ የሞተው በምናሴ ትእዛዝ በመጋዝ ለሁለት ተሰንጥቆ ነው ይባላል። በምናሴ ዘመነ መንግሥት የእግዚአብሔር ሕዝብ የሥነ-ምግባር ሕይወት ተበላሸ። እንዲያውም አብረዋቸው ከነበሩት ከነዓናውያን የባሰ ተበላሹ።

በምናሴ ዘመነ መንግሥት ይሁዳ ለአሦር መንግሥት እንደ ባሪያ ነበር፤ ነገር ግን ባቢሎን በአሦር ላይ በምታምፅበት ጊዜ ምናሴም በአሦር ላይ ለማመፅ ሞከረ። ሆኖም ወደ አሦር በምርኮ ተወሰደና በኋላ ተለቀቀ (2ኛ ዜና 33፡10-13 ተመልከት)። ምናሴ በምርኮ ላይ በነበረበት ጊዜ ከክፉ ተግባሩ ሁሉ የተመለሰ ይመስላል። ወደ ይሁዳ በተመለሰ ጊዜም ሕዝቡ እግዚአብሔርን ወደ ማምለክ እንዲመለሱ አበረታታ፤ ነገር ግን በዚህ ተግባሩ ብዙ ውጤታማ መሆን አልቻለም።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የአንድ ሰው መንፈሳዊ እምነት ወደ ልጆቹ ሊተላለፍ እንደማይችል፥ የምናሴ ሕይወት ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን እንዴት ነው? ለ) ወላጆች ልጆቻቸውን የእግዚአብሔርን መንገድ ሊያስተምሯቸው የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? 

  1. የይሁዳ ንጉሥ አሞን፡- (643-641 ዓ.ዓ.)

ስለ አሞን አገዛዝ ብዙ የምናውቀው ነገር የለም፤ ነገር ግን እንደ አባቱ እንደ ምናሴ የመጨረሻ የሕይወት ዘመን ሳይሆን፥ ምናሴ ሕዝቡን ወደ ጣኦት አምልኮ እንደመራባቸው እንደ መጀመሪያው ዘመን ኖረ። አሞን በይሁዳ ሰዎች ተገደለና ልጁ ኢዮስያስ በእርሱ ፈንታ ነገሠ። 

  1. የይሁዳ ንጉሥ ኢዮስያስ (641-609 ዓ.ዓ.) 

ኢዮስያስ በይሁዳ ላይ በነገሠ ጊዜ የ8 ዓመታት ልጅ ነበር። በይሁዳ ላይ ከነገሡና እግዚአብሔርን ይፈሩ ከነበሩ መሪዎች ኢዮስያስ የመጨረሻው ነበር። ከኢዮስያስ ሞት በኋላ፥ በባቢሎናውያን ወደ ምርኮ እስኪወሰድ ድረስ የይሁዳ ብሔር በጣም ፈጣን በሆነ ሁኔታ እየተዳከመ ሄደ።

ኢዮሳያስ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የአሦር መንግሥት መውደቅ ጀምሮ ነበር። ይህም ኢዮሳያስ የእስራኤል ግዛት የነበረውን አንዳንድ ምድር ለመውሰድ እስኪችል ድረስ ግዛቱን ለማስፋፋት ረዳው። በዘመነ መንግሥቱ መጨረሻ አካባቢ፥ በ612 ዓ.ዓ. የአሦር ዋና ከተማ የሆነችው ነነዌ በባቢሎናውያን እጅ ወደቀች።

ኢዮስያስ ከነገሠ ከ10 ዓመታት በኋላ አንድ ነገር ልቡን ለወጠውና እግዚአብሔርን እንዲከተል አደረገው። ኢዮስያስ እግዚአብሔርን መፈለግና የሕዝቡን ልብ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ መሥራት ጀመረ። ሕዝቡ ቤተ መቅደሱን በመሥራት ላይ ሳሉ፥ ከስምንት ዓመታት በኋላ ፔንታቱክ ብለን የምንጠራቸው የሙሴ ሕግጋት በቤተ መቅደሱ ተገኙ። ለብዙ ዓመታት ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ለማንበብ ያልቻሉ ይመስላሉ። ይልቁንም የእግዚአብሔር ቃል በምናሴ ዘመነ መነግሥት በቤተ መቅደሱ ውስጠኛ ክፍል ሳይሸሸግና ሳይጣል፥ ሳይረሳም አልቀረም።

የእግዚአብሔር ቃል ተገኝቶ በዘዳግም 27-28 የተጻፉት መርገምቶች ሁሉ በተነበቡ ጊዜ፥ በይሁዳ ሕዝብ ላይ ፍርዱ በደጅ እንደ ቀረበ ኢዮስያስ አወቀ። እግዚአብሔርም ነቢያትን ወደ ኢዮስያስ ላከና የኢየሩሳሌም ጥፋት የማይቀር እንደሆነና እርሱ እግዚአብሔርን ስለፈራ ግን በእርሱ ዘመነ መንግሥት ይህ እንደማይፈጸም አስታወቀው። ኢዮስያስም ሕዝቡን ወደ እግዚአብሔር ለመመለስና ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸውን ቃል ኪዳን ለማደስ ተግቶ ሠራ። ለጣዖት አምልኮ የሆኑ መሣሪያዎችን በሙሉ አጠፋ። እስከ ቤቴል ድረስ ሳይቀር ሄዶ ቀዳማዊ ኢዮርብዓም ከ300 ዓመታት በፊት ያቆማቸውን ጣዖታት አፈራረሰ። ይህንንም በማድረጉ አንድ ያልታወቀ ነቢይ የተነበየውን ትንቢት ከፍጻሜ አደረሰው፤ (1ኛ ነገሥት 13 ተመልከት)። ኢዮስያስ ለጣዖት አምልኮ የሚያገለግሉ ውጫዊ ነገሮችን ሊያጠፋ ቢችልም፥ በሰዎቹ ውስጣዊ ሕይወት ላይ ተጽዕኖ ማድረጉ ግን እጅግ አጠራጣሪ ነው። ምክንያቱም ኢዮስያስ እንደሞተ ሕዝቡ ወደ ጣዖት አምልኮ ተመልሰዋል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የሐሰተኛ አምልኮ አካሄድን ወይም የሰዎችን ውስጣዊ ልብን መለወጥ ከውጫዊ ነገሮች ይልቅ የበለጠ አስቸጋሪና ከባድ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) ለማያምኑ ሰዎች በምንመሰክርበት ጊዜ ወይም የቤተ ክርስቲያን ሰዎችን በምናስተምርበት ጊዜ በውጫዊ ለውጥ ላይ ከማተኮር ይልቅ በውስጣዊ ለውጥ ላይ የማተኮር አስፈላጊነት ይህ ምን ያስተምረናል?

በኢዮስያስ ዘመን ያገለግል የነበረው ዋና ነቢይ ኤርምያስ ነበር።

በ609 ዓ.ዓ. ኢዮስያስ ብልህነት የጎደለው ስሕተት ፈጸመ። የግብፅ ንጉሥ ከአሦር ጋር በመተባበር አዲሱን ኃያል መንግሥት ባቢሎንን ለመውጋት ወደ ሰሜን በሚጓዝበት ጊዜ በይሁዳ በኩል ያልፍ ነበር። ኢዮስያስ ከግብፅ ንጉሥ ምንም ዓይነት ጠብ አጫሪነት ሳይኖር የግብፅን ንጉሥ ለመውጋት ሄደ፤ በጦርነቱም ቆሰለና ቆይቶ ሞተ።

  1. የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአሐዝ (ሻሉም) (609 ዓ.ዓ.)

ኢዮስያስ በሞተ ጊዜ፥ በእርሱ ምትክ ልጁ ኢዮአሐዝ ነገሠ፤ ነገር ግን በሥልጣን ላይ ለረጅም ጊዜ ሊቆይ አልቻለም። ከሦስት ወራት በኋላ ግብፃውያን ከባቢሉን ጦርነት ሲመለሱ፥ ኢዮአሐዝ ቆይቶ ወደ ሞተበት ወደ ግብፅ ማርከው ይዘውት ሄዱ። 

  1. የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም (609-598 ዓ.ዓ.)

ግብፃውያን ኢዮአሐዝን ማርከው ሲወስዱ፥ ኢዮአቄም የተባለውን ወንድሙን በዙፋኑ ላይ አስቀመጡት። በዚያን ጊዜ ስሙን ወደ ኢዮአቄም ለወጡት። ግብፃውያን በተጨማሪ የይሁዳ መንግሥት ከባድ ቀረጥ እንዲከፍል አደረጉት።

በ605 ዓ.ዓ. የባቢሎን ንጉሥ የሆነው ናቡከደነፆር ብዙም ሳይቆይ ኢየሩሳሌምን አጠቃ። ኢዮአቄም ለእርሱ ራሱን ማስገዛት ግድ ሆነበት። በዚህ ጊዜ ናቡከደነፆር የይሁዳ ዋና ዋና ሰዎችን ማርኮ ወደ ባቢሎን ወሰደ፡፡ ከእነዚህም መካከል ዳንኤል፥ ሐናንያ፣ ሚሳኤልና አዛርያ ይገኙበታል። ይህ በይሁዳ ላይ ከደረሰው ምርኮኝነት የመጀመሪያው ነበር።

ኤርምያስ በንጉሡ ኢዮአቄም ዘመንም አገልግሎአል። ኢዮአቄም ግን የኤርምያስን ቃል መስማት እምቢ አለና የጻፈውን የተቀደሰ ጽሑፍ አቃጠለ። ኢዮአቄም የጣዖት አምልኮን ከማበረታታቱም ሌላ አባቱ እንዳደረገው የእግዚአብሔርን መንገድ ሳይከተል ቀረ። ከዚህ የተነሣ እግዚአብሔር በኢዮአቄም ላይ ፈረደና ተገቢ የሆነው የንጉሣውያን ቤተሰብ የቀብር ወግ ሳያገኝ ቀረ። አንዳንድ ምሁራን በ598 ዓ.ዓ. ባቢሎንን ለመውጋት በተደረገ ጦርነት እንደሞተ ያስባሉ። 

  1. የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን (597 ዓ.ዓ.)

የኢዮአቄም ልጅ የሆነው ዮአኪን በሥልጣን ላይ የቆየው ለሦስት ወራት ብቻ ነበር፡፡ እርሱ የመንግሥት ሥልጣን በያዘ ጊዜ ይሁዳ ከባቢሎን ጋር በጦርነት ላይ ነበረች። ዮአኪን እጁን ለባቢሎን ሰጠ። ናቡከደነፆር በቤተ መቅደሱ ውስጥ የነበሩ የከበሩ ነገሮችን ሁሉ ዘረፈ። ዮአኪንና ሌሎች የይሁዳ ትላላቅ ሰዎችን በምርኮ አጋዛቸው። ሕዝቅኤል ተማርኮ የሄደው በዚህ ጊዜ ነበር። ዮአኪን በባቢሎን መልካም እንክብካቤ ተደረገለት። ከናቡከደነፆር ሞት በኋላ ከታሠረበት ከመለቀቁም በቤተ መንግሥት በእንክብካቤ ተያዘ። ወደ እስራኤልም ጨርሶ ሳይመለስ ቀረ። 

  1. የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ (ማታንያህ) (597-586 ዓ.ዓ.) 

ሴዴቅያስ የኢዮአሐዝ የመጨረሻ ልጁ ነበር። በሥልጣን ላይ ያስቀመጠው የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ሲሆን፥ ማስተዳደር የሚችለውም በባቢሎን መንግሥት ሥልጣን ሥር ነበር። ለጊዜው ሴዴቅያስ ለባቢሎን መንግሥት ታማኝ ነበር፤ ነገር ግን ግብፅ በ588 ዓ.ዓ. በባቢሎን ላይ ስታምፅ ሴዴቅያስም ዓመፀ። ይህም በእርሱና በኢየሩሳሌም ከተማ ላይ የባቢሎንን ሙሉ ቁጣ አስከተለ። በ586 ዓ.ዓ. ኢየሩሳሌም ተሸነፈች። የሴዴቅያስ ልጆችም በእርሱ ፊት ተገደሉ። ለዴቅያስንም ዓይኑን አውጥተው ወደ ባቢሎን በምርኮ ወሰዱት። ሌሎች ብዙ ሰዎችም ተማርከው ተወሰዱ። የኢየሩሳሌም ቅጥር፥ የሰሎሞን ቤተ መቅደስና አብዛኛው የከተማይቱ ክፍል ተደመሰሰ፡፡

በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ኤርምያስ ለንጉሥ ሴዴቅያስ ምክር ሊሰጠው ቢሞክርም ሴዴቅያስ ኤርምያስን መስማት እምቢ አለና ኤርምያስን አሳደደው። 

  1. የይሁዳ ገዥ ገዳልያ 

ኢየሩሳሌም ከተደመሰሰች በኋላ ናቡከደነፆር ገዳልያን የይሁዳ ገዥ አደረገው፤ ይሁን እንጂ እስማኤል የተባለው የንጉሣውያን ቤተሰብ ዝርያ የነበረ ሰው ሥልጣኑን ስለፈለገ ገዳልያን ገደለው። በዚህ ምክንያት ሊመጣ ያለውን የባቢሎናውያንን ቁጣ በመፍራት፥ አብዛኛዎቹ አይሁዳውያን ወደ ግብፅ ሸሽተው ሄዱ። ኤርምያስንም ከእነርሱ ጋር እንዲሄድ አስገደዱት። እርሱም በዚያው በግብፅ ሞተ።

በ2ኛ ነገሥት የተጻፈው ታሪክ እጅግ አሳዛኝ ታሪክ ነው። የእግዚአብሔር ሕዝብ ያለማቋረጥ ልባቸውን እንዳደነደኑና እውነተኛውን አምላክ ከማምለክ ይልቅ ሐሰተኛ አማልክትን እንዴት እንዳመለኩ ይናገራል፤ በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር የሰሜኑም ሆነ የደቡቡ መንግሥታት ወደ ምርኮ እንዲሄዱ አደረገ። ለደቡብ መንግሥት ግን ፍርዱ ጊዜያዊ ነበር። የኢየሩሳሌም ቅጥር ከፈረሰ ከ50 ዓመታት በኋላ እግዚአብሔር በአሕዛብ መንግሥታት ልብ ውስጥ በመሥራት፥ የራሱ ሕዝብ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለሱ አደረገ። የሚያሳዝነው ግን አብዛኛዎቹ አይሁድ በምርኮ በነበሩበት ስፍራ ኑሮአቸው የሚያረካ ስለሆንላቸው ለመመለስ ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀሩ። እግዚአብሔር በሰጣቸው ምድር በድኅነት ከመኖር ይልቅ የዓለምን ምቾት መረጡ። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከ2ኛ ነገሥት የተማርካቸውን መንፈሳዊ ትምህርቶች ዘርዝር። ለ) እነዚህ ትምህርቶች በቤተ ክርስቲያንህ አባላት መንፈሳዊ ዕድገት ውስጥ እንዴት አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ? ሐ) እነዚህን ትምህርቶች በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ለሚገኙ ሌሎች ሰዎች የምታስተምርባቸውን መንገዶች ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: