ነህምያ 1-4

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ለአንድ የተዋጣለት የቤተ ክርስቲያን መሪ በጣም አስፈላጊ ባሕርይ ምን ይመስልሃል? መሪው ምን መሆን አለበት? ምንስ ማድረግ አለበት? ወዘተ. ለ) በኢትዮጵያ ውስጥ የተዋጣላቸው የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ናቸው ብለህ የምታስባቸውን አንዳንድ ሰዎች በምሳሌነት ጥቀስ። ሐ) ውጤታማ ያደረጋቸው ነገር ምንድን ነው?

በመሪነት እግዚአብሔር የሚጠቀምበት ሰው ምን ዓይነት ነው? የፈረሱ መንፈሳዊ ቅጥሮችን እንደገና በመሥራት ጠንካራ ቤተ ክርስቲያንን መመሥረት በሚያስችል መንገድ የእግዚአብሔርን ሕዝብ መምራት የሚችል ምን ዓይነት ሰው ነው? መጽሐፈ ነህምያ ስለ እንደዚህ ዓይነት ሰው ይነግረናል። ይህ ሰው ነህምያ ነበር። ነህምያ ውጫዊና የሚታይ የነበረውን የኢየሩሳሌምን ቅጥር ለማሠራት ኃላፊነት የነበረበት ፖለቲካዊ መሪ ቢሆንም፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ የፈረሱ የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ቅጥሮችን እንደገና ሊሠሩ በሚችሉበት መንገድ እንዴት መምራት እንደሚቻል በርካታ ነገሮችን ከእርሱ እንማራለን። በነህምያ ጥናታችን እግዚአብሔር ነህምያን ሊጠቀምበት የቻለው በእግዚአብሔር ፊት በነበረው መንፈሳዊ ሕይወትና የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለመምራት በነበረው የአስተዳደር ችሉታ እንደነበረ እንመለከታለን። 

የውይይት ጥያቄ፥ ነህምያ 1-4 አንብብ። ሀ) ስለ ነህምያ ግለጥ። ስለ ነህምያ መንፈሳዊ ሕይወት ከእነዚህ ቁጥሮች የምንማረው ነገር ምንድን ነው? ለ) ከእነዚህ ቁጥሮች ስለ ነህምያ የማቀድና የመምራት ችሎታ ምን እንማራለን? ሐ) የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች እንደገና ለመሥራት በሞከረ ጊዜ፥ ነህምያን ያጋጠሙትን የተለያዩ ችግሮችና ትግሉች ጥቀስ።

የንጉሥ አርጤክስስ ጠጅ አሳላፊና አማካሪ የነበረው ነህምያ የሚኖረው በፋርስ መንግሥት ዋና ከተማ በሱሳ ባለው ቤተ መንግሥት ውስጥ ነበር። አንዳንድ ዘመዶቹና ሌሎች አይሁዶች ከኢየሩሳሌም ወደ ፋርስ ነህምያን ለመጎብኘት መጡና የኢየሩሳሌም ከተማ የነበረችበትን ሁኔታና የእግዚአብሔር ሕዝብም በዚያ እንዴት እንደሚኖሩ ነገሩት።

ነህምያ እግዚአብሔርን የሚፈራ ታላቅ መሪ ያደረጉትን የሚከተሉትን ነገሮች ተመልከት፡-

  1. ነህምያ የእግዚአብሔር ሕዝብ ስለ ነበሩበት ሁኔታ የሚገደው ሰው ነበር። የሚኖረው በኢየሩሳሌም አካባቢ ባይሆንም ጉዳዩ ያሳስበው ስለ ነበር ሕዝቡን በሚመለከት ወደ እርሱ የመጡትን አይሁድ ጠየቀ። ነህምያ ሕዝቡ ስለ ነበሩበት አሳዛኝ ሁኔታ ሲሰማ አለቀሰ። እንዲሁም በእግዚአብሔር ፊት ጾመና ጸለየ። 
  2. ነህምያ የጸሎት ሰው ነበር። በመጽሐፈ ነህምያ በአጠቃላይ ሁኔታዎች አስቸጋሪ በሚሆኑበት ጊዜ ነህምያ ፊቱን ወደ እግዚአብሔር ሲመልስ እንመለከተዋለን።

የውይይት ጥያቄ፥ የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከት፡- ነህ. 1፡4፤ 2፡4፤4፡9፤6፡9 ሀ) በእነዚህ ጥቅሶች ነህምያ የጸለየባቸውን ጊዜያትና ስለምን እንደጸለየ ዘርዝር። ለ) ከእነዚህ ጥቅሶች ስለ ጸሎት የምንማረው ነገር ምንድን ነው? 

  1. ነህምያ የእግዚአብሔርን ቃል ያውቅ ነበር። በምዕራፍ 1 የተጻፈውን የነህምያን ጸሎት ስንመለከት፥ ነህምያ የይሁዳን ታሪክ እንደሚያውቅ ማለትም የሙሴን ሕግ፥ እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር የገባውን ቃል ኪዳንና እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደገና ለማደስና ለማነጽ የሰጠውን ተስፋ በሚገባ ማወቁን እንመለከታለን።
  2. ነህምያ ኃጢአቱንና የአባቶቹን ኃጢአት የሚናዘዝ መሪም ነበር። ነህምያ ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ኅብረት የሚያበላሽና የሚያጠፋ፥ እግዚአብሔር ለጸሎቱ ሊሰጠው ያለውን መልስ የሚያግድ አንዳችም ነገር እንዳይኖር የሚፈልግ ሰው ነበር። ኃጢአት ይህንን ሊያደርግ እንደሚችል ያውቅ ሰለ ነበረ ኃጢአቱን ተናዘዘ። 
  3. ነህምያ ሥራው ውስጥ ለመግባት ራሱን በማዘጋጀት፥ ሕዝቡን እንደገና ለመሥራት እንዲጠቀምበት እግዚአብሔርን ለመነ። እግዚአብሔርን ሌላ ሰው እንዲያስነሣ አልጠየቀውም፤ ግን ለእግዚአብሔር ምን መሥራት እንደሚችልና ያንን ለማድረግ ምን እንደሚጠበቅበት ጠየቀ። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እነዚህ አምስት መንፈሳዊ መመዘኛዎች ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሚያስፈልጉት ለምንድን ነው? ለ) በሕይወትህ ውስጥ የሚኖሩትስ እንዴት ነው? ሐ) በእነዚህ አምስት የሕይወትህ አቅጣጫዎች ለማደግ የምትችለው እንዴት ነው?

ነህምያ 2-3 የነህምያን የአስተዳደር ብቃቶች ይነግሩናል። በመጨረሻም ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚመልሰውና የፈረሰውን ቅጥር እንደገና የመሥራት ሥራውን ሊያከናውን የሚችለው እግዚአብሔር እንደሆነ ቢያውቅም፥ እግዚአብሔር በሰዎች መገልገል ደስ እንደሚለውም ያውቅ ነበር፤ ስለዚህ ነህምያ ጸለየና ዕቅድ አወጣ። ነህምያ መጸለይ በጀመረበት በኪስሊቭ፥ በኅዳር ወርና ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ፈቃድ በጠየቀበት በኒሳን፥ በመጋቢት ወር መካከል የአራት ወራት ልዩነት አለ። እግዚአብሔር የንጉሡን ልብ ሲከፍት፥ ነህምያ ለመንቀሳቀስ ዝግጁ ነበር።

ነህምያ እግዚአብሔር ጸሎቱን እንደሚመልስ ስላመነ፥ በኢየሩሳሌም ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይና ሥራውን ለመሥራት ምን እንደሚያስፈልገው፥ ሄዶም ምን እንደሚሠራ ለንጉሡ ለመናገር ተዘጋጅቶ ነበር። ነህምያ የዕቅዱን ምንነት በሚመለከት ንጉሡ እስኪጠይቀው ድረስ አልጠበቀም፤ ነገር ግን በእምነት አስቀድሞ ዐቀደ። እግዚአብሔር በሮችን እስከሚከፍትለት ድረስም ጠበቀ። ጥሩ የቤተ ክርስቲያን መሪ ሁልጊዜ የእግዚአብሔርን ሥራ እንዴት እንደሚሠራ የሚያቅድ፥ ሥራውን ለማሻሻል ምን መደረግ እንዳለበትና እንዴት ማደረግ እንዳለበት የሚወስን የተግባር ሰው ነው። 

ቅጥሮቹን እንደገና ለመሥራት ምን እንደሚያስፈልግ ለማወቅ የፈረሱትን የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች እየዞረ በመጎብኘቱ የነህምያን የአስተዳደር ብቃት እንመለከታለን። ከዚያም ሕዝቡን በሥራው ውስጥ እንዲሳተፉ ጠየቃቸው። አንድ ጥሩ መሪ ሁልጊዜ እንደሚያደርገው፥ ነህምያ ሥራውን ብቻውን ለመሥራት ጥረት አላደረገም፤ ነገር ግን በርካታ ሰዎች በሥራው እንዲሳተፉ የተቻለውን አደረገ። ነህምያ እያንዳንዱ ሰው አንድ የተወሰነ ኃላፊነት እንዲወስድ ሥራውን ከፋፈለ። በነህምያ ምዕራፍ 3 በቅጥሩ ሥራ ላይ የተሰማሩትን ሰዎች ስም ዝርዝር እናገኛለን። ሥራውን የሠሩት ሰዎች ምን ዓይነት እንደነበሩ መመልከት መልካም ነው። የከተማ ሹማምንት፥ ነጋዴዎች፥ ድሆች፥ የሃይማኖት መሪዎች፥ ወንዶች፥ ሴቶች ወዘተ ነበሩ። ሥራውን አንሠራም ያሉ የቴቁሔ መኳንንት ብቻ ነበሩ (ህ. 3፡5)። እነርሱ ትዕቢተኞች ነበሩ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ መሠራት ካለባቸው ሥራዎች አንዱን ጥቀስ። ለ) ይህ ሥራ ከፍጻሜ እንዲደርስ መወሰድ ያለበት እርምጃ ምንድን ነው? ሐ) ይህ ሥራ በሚገባ ወደ ፍጻሜ እንዲደርስ ለተለያዩ ሰዎች ሥራዎችን ለማከፋፈል የሚቻለው እንዴት ነው? መ) በዚህ ሥራ ውስጥ ለመሳተፍ ትችል ዘንድ እግዚአብሔር በሩን እንዲከፍትልህ በጸሎት ጠይቀው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ኤፌ. 4፡11-13 አንብብ። ሀ) እነዚህ ቁጥሮች የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለአባላት ማድረግ ስላለባቸው ነገሮች የሚናገሩት ምንድን ነው? ለ) ይህ በቤተ ክርስቲያንህ የተፈጸመው እንዴት ነው?

በነህምያ ምዕራፍ 4 ቅጥሩ መሠራት ከተጀመረ ወዲህ ስለ ተፈጠረው የመጀመሪያ ተቃውሞ እንመለከታለን። ማንኛውም ሰው ለእግዚአብሔር ለመሥራት ሲጀምርና የእግዚአብሔር ሕዝብም ለመሥራት ሲደራጁ፣ ሥራውን ለማቆም ተቃውሞ መፈጠር ይጀምራል። ይህ ተቃውሞ በቤተ ክርስቲያን ክልል ውስጥ በሚገኙ፥ ወይም ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ከሚገኙ ሰዎች ሊመጣ ይችላል። መሪዎች ማረጋገጥ ያለባቸው ነገር የእግዚአብሔር ሥራ በተቃውሞ ውስጥ ሁሉ የሚቀጥል መሆኑን ነው። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ስለተቃውሞ የሚከተሉትን ነገሮች ተመልከት፡-

  1. በመጀመሪያ፥ ተቃውሞ የመጣው ፌዝ በተቀላቀለበት ንግግር መልክ ነበር። የአይሁድ ሕዝብ ጠላቶች የነበሩት ጦቢያና ሰንባላጥ ሌሎችም፥ ሕዝቡ በሚሠሩት ሥራ ላይ በመቀለድ ተስፋ ቆርጠው ሥራውን እንዲያቆሙ ለማድረግ ሞከሩ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ሰዎች ሌሎች ስለ እነርሱ የሚሉትን ነገር በሚመለከት የሚገዳቸውና በሚቀልዱባቸውም ጊዜ ተስፋ ቆርጠው የጀመሩትን ሥራ የሚያቆሙት ለምንድን ነው? ለ) የዚህ ዓይነት ተቃውሞ በክርስቲያኖች ላይ ሲሠራ ያየኸውን ምሳሌ ስጥ። 

  1. ሁለተኛ፥ ተቃውሞው በሕዝቡ ላይ ችግር የማድረስ ወይም ጥቃት የማምጣት መልክ ያዘ። በእርግጥ ጠላቶቻቸው በዚህ ስፍራ የማጥቃት ዛቻ ብቻ ነው ያሰሙት። ብዙ ጊዜ ለቤተ ክርስቲያን የሚከብደው በቀጥታ የሚመጣው ስደት ሳይሆን የጥቃትና የስደት ዛቻ ነው። ከኢየሩሳሌም በስተ ሰሜን ይገኝ የነበረው የሰማርያ ገዥ ሰንባላጥና ሌሎችም ግብረ አበሮቹ ሠራተኞቹን ባልጠበቁት ሰዓት ሊያጠቋቸው አስፈራሯቸው። የነህምያ መልስ ግን የሚያስገርም ነበር። በመጀመሪያ፥ ሊጠብቃቸው የሚችል እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ የተገነዘበበትን ጸሎት ነህምያ ጸለየ። ሁለተኛ፥ ነህምያ ሕዝቡ ሊደርስ ከሚችል ጥቃት ለመከላከል በተጠንቀቅ እንዲቆሙ አደረገ። ሦስተኛ፥ ነህምያ የሕዝቡን ትኩረት ይጠብቀናል ወዳለው ወደ እግዚአብሔር መለሰ። አራተኛ፥ ሕዝቡ ሥራውን መቀጠላቸውን አረጋገጠ። ሕዝቡ ራሳቸውን ለመጠበቅ ብለው፥ ሥራቸውን ከማቆም ይልቅ ሥራውን እንዲቀጥሉ አደፋፈረ። ነህምያ ሰይጣን ሥራውን ለማስቆም እንደሚጥር ያውቅ ስለ ነበር፥ ሕዝቡ ሥራውን እንዲቀጥሉ አበረታታቸው።

እነዚህ ሁለት ዘዴዎች ሰይጣን የእግዚአብሔርን ሥራ ለማስቆም ብዙ ጊዜ የሚጠቀምባቸው መንገዶች ናቸው። ሁለቱም ዘዴዎች ያነጣጠሩት በእግዚአብሔር ሕዝብ እንጂ በመሪው ላይ አልነበረም። በሚቀጥለው ጥናታችን ደግሞ ሰይጣን ሥራውን ለማስቆም መሪውን ነህምያን እንዴት እንዳጠቃ እንመለከታለን።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ቤተ ክርስቲያንህን ስለ መምራት ከእነዚህ ምዕራፎች የተማርካቸውን ትምህርቶች ዘርዝር። ለ) እነዚህ እውነቶች በሕይወትህ በተግባር ላይ የሚውሉባቸውን መንገዶች ዘርዝር። 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: