የመጽሐፈ አስቴር ዋና ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ የግለሰቦች ታሪክ ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔርና በሰይጣን መካከል የሚካሄድ ጦርነት ታሪክ ነው። ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ እስከ ዮሐንስ ራእይ ድረስ የዚህን ጦርነት ፍንጮች እናያለን። ሰይጣን በጦርነቱ ለመዋጋት የተለያዩ መንገዶችን ቢጠቀምም ዓላማው ሁልጊዜ አንድ ነው። የእግዚአብሔርን ዕቅድና የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለማጥፋት ይፈልጋል። 

በእግዚአብሔር ሕዝብ ታሪክ ውስጥ ሁሉ ሰይጣን የደኅንነት መስመር እንዲቋረጥ ለማድረግ በመሞከር የእግዚአብሔርን ዕቅድ ለማበላሸት ታግሏል። ከዘፍ. 3፡15 እንደምታስታውሰው፥ ከሴቲቱ ዘር ሰይጣንን የሚያጠፋ ሰው እንደሚመጣ እግዚአሔር ተስፋ ሰጥቷል። ሰይጣን የሴቲቱ ዘር ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ስለሚያውቅ የሚመጣበትን የዘር ግንድ ለማጥፋት የተቻለውን ሁሉ ያደርግ ነበር። እንደምታስታውሰው፥ የግብፅ ንጉሥ ሣራን በሚስትነት እንዲወስድ በማድረግ የአብርሃምን የዘር ግንድ ለማቋረጥ ሞክሮ ነበር። ርብቃንም መኻን በማድረግ የዘር ሐረጉ እንዲያበቃ ለማድረግ ሞክሮ ነበር። በኋላም ሰይጣን የእስራኤልን ሕዝብ ሁሉ በራብ ለመጨረስ የሞከረ ቢሆንም፥ እግዚአብሔር ግን በዮሴፍ በኩል እነርሱን ታድጎአቸዋል። በኋላም መሢሑ የሚመጣው በእርሱ በኩል መሆኑን እግዚአብሔር ለዳዊት ነግሮታል (2ኛ ሳሙ. 7፡14)። ሰይጣን ግን የዳዊትንም ዘር ለማጥፋት በመሞከር የእግዚአብሔርን ዕቅድ ሊያበላሽ ጥሮ ነበር። እንደምታስታውሰው፥ እግዚአብሔር ካዳነው ከአንድ ትውልድ በቀር ጎተልያ የዳዊትን ዘር በሙሉ አጥፍታ ነበር፤ (2ኛ ነገ. 11፡1-3)። አሁን ደግሞ በአስቴር ታሪክ ሰይጣን ሐማ የተባለውን የአንድ ሰው ጥላቻ በመጠቀም አይሁድን ሁሉ ለማጥፋት ሞክሮ ነበር። አይሁድ ተደምስሰው ቢሆን ኖሮ መሢሑ ባልተወለደና ዓለምም አዳኝን ባላገኘ ነበር። እግዚአብሔር ግን የሰይጣንን ዕቅድ አከሸፈ።

ይህ እውነት ከኢየሱስ ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያለውን አንዳንድ የአይሁድ ታሪክ ለመረዳት ይጠቅመናል። በየትኛውም ስፍራ ይሁኑ አይሁድ ሁልጊዜ የሚሰደዱ ሰዎች ነበሩ። ይህም በተለይ የታየው በ2ኛው የዓለም ጦርነት ሂትለርና ጀርመኖች ከ6 ሚሊዮን የሚበልጡ አይሁዳውያንን ቢገድሉም፥ እግዚአብሔር ግን አሁንም ቢሆን ለአይሁድ ሕዝብ ዕቅድ ስላለው ሙሉ በሙሉ ሊያጠፏቸው ባለመቻሉ ነው፤ ስለዚህ በአጠቃላይ በታሪክ ሁሉ ቅሬታዎችን በመጠበቅ አንድ ቀን ሊጎበኛቸውና በመካከላቸው ታላቅ ሥራን ሊያደርግ ዕቅድ አለው (ሮሜ 11 ተመልከት)።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የማያምኑ ሰዎች ከክርስቲያኖች ጋር የሚታገሉትና ሊያጠፏቸው የሚሹት ለምን እንደሆነ ለመረዳት ይህ እውነት እንዴት ይረዳናል? ለ) ይህ እውነት በተጨማሪ ሕዝቡ ሙሉ በሙሉ እንዲጠፉ እግዚአብሔር እንደማይፈቅድ ምን ያስተምረናል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading