የመጽሐፈ መክብብ ዓላማ
የምናጠናው የጥበብ መጻሕፍት በመባል የሚታወቁትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እንደሆነ ታስታውሳለህ። መጽሐፈ መክብብ ከጥበብ መጻሕፍት አንዱ ነው። የመጀመሪያው፥ የጥበብ መጽሐፍ የሆነው መጽሐፈ ኢዮብ ጻድቅ ለምን መከራ ይቀበላል? ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ይሞክራል። መዝሙረ ዳዊት እግዚአብሔርን በማምለክ የሚገኘውን የጥበብ መሠረት ሲሰጠን፥ መጽሐፈ ምሳሌ ደግሞ በሕይወታችን እንዴት መኖር እንዳለብን የሚያሳዩ ተግባራዊ መልሶች በማቅረብ የጥበብን መሠረት ይሰጠናል። መጽሐፈ መክብብ በሕይወት ዓላማ ላይ በማተኮር፥ ያለ እግዚአብሔር ሕይወት ከንቱ እንደሆነ ያስተምረናል። መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ደግሞ ጥበብ የሞላበት የጋብቻ ግንኙነት የሚመሠረተው በእውነተኛ ፍቅር ላይ እንደሆነ ያስተምረናል።
መጽሐፈ መክብብ የተጻፈው፥ «አንድ ሰው ደስታንና የዓላማን መከናወን በሕይወቱ ውስጥ እንዴት ሊያገኝ ይችላል?» (መክብብ 1፡3) ለሚል ዐቢይ የፍልስፍና ጥያቄ መልስ ለማስገኘት ነበር። «ከፀሐይ በታች» ባለ ነገር ውስጥ ሁሉ የሕይወትን ዓላማ ስለሚፈልግ ሰው የተጻፈ መጽሐፍ ነው። «ከፀሐይ በታች» የሚለው ሐረግ ከእግዚአብሔር ውጭ ላሉ ለማናቸውም ነገሮች የተሰጠ ስም ነው። በመሠረቱ ጸሐፊው «እግዚአብሔር ባይኖር ኖሮ ወይም እኔ የምኖረው እግዚአብሔር እንደሌለ ቆጥሬ ቢሆን ኖሮ፥ ምን እሆን ነበር? ሕይወት ትርጕም ይኖራት ነበርን? » በማለት ይናገራል። ስለዚህ ጸሐፊው በሕይወት ውስጥ ምናልባት ትርጉም ባገኝ ብሉ የተለያዩ ነገሮችን መመልከት ይጀምራል። ምናልባት ሕይወት ያለ እግዚአብሔር ትርጕም ይኖረው እንደሆነ በማለት የተለያዩ የታወቁ የዓለም ፍልስፍናዎችን መርምሯል ለማለት እንችላለን። ማጠቃለያው «ሁሉም ከንቱ ነው» የሚል ነው። (በመጽሐፉ ውስጥ ይህንን ዓረፍተ ነገር 25 ጊዜ ተደጋግሞ እናገኘዋለን)።
1. ጸሐፊው ትኲረቱን ወደ ሳይንስ በማድረግ በምድር ላይ ያሉ ነገሮች ትርጕም ይኖራቸው እንደሆነ ለመረዳት ምርምር አድርጓል። ሳይንስ ማድረግ የሚችለው ችግሮችን ማየት እንጂ መፍትሔ መስጠት አይደለም (መክብብ 1፡4-10።
የውይይት ጥያቄ፥ ለእግዚአብሔር ክብርን ሳይሰጥ ነገሮችን ሁሉ ለማብራራት በሚሞክረው ዘመናዊ ሳይንስ ላይ ከሚገባ በላይ እንዳንደገፍ ይህ እንዴት ሊያስጠነቅቀን ይገባል?
2. ጸሐፊው ዓለማዊ ጥበብ፥ ፍልስፍናና ትምህርት ለሕይወት ትርጕም ይሰጡ እንደሆነ ለማየት ምርመራ አካሄደ፤ ነገር ግን ዓለማዊ ጥበብ እውነተኛ መልሶችን ለመስጠት አይችልም። ጥበበኛውም ሆነ ሞኙም ሳይቀር ሁሉንም ሰው ሞት ይጠባበቀዋል። ችግሮች በሁሉም ስፍራ አሉ።
3. ጸሐፊው፥ ሰው ራሱን ለማስደሰት ሲል ብቻ በራስ ወዳድነት የሚገፋውን የምቾት ሕይወት ተመልክቷል፤ ነገር ግን ያም ደስታ በራሱ ከንቱ መሆኑን ለማየት ጊዜ አልወሰደበትም።
4. ቀጥሎ ጸሐፊው፥ ሰዎች ለሕይወት ደስታና ትርጒም ይሰጣል ብለው የሚያስቡትን አንድ ነገር ይመለከታል። ይህም ሀብት ነው። ሀብት እርካታ ይሰጣልን? ጸሐፊው አይሰጥም ይላል፤ ምክንያቱም ሰው በሚሞትበት ጊዜ የአንድ ሰው ሀብት ወደ ሌላው ስለሚተላለፍ ሰውዬው በሙላት ደስታን አያገኝበትም።
5. ጸሐፊው የሰውን ሕይወት መለወጥ ወደማይችል፥ ሆኖም እግዚአብሔርን የማምለክ ሥርዓት ወደሚታዩበት ሃይማኖት ሳይቀር ተመልክቶ ነበር። ከእግዚአብሔር ጋር እውነተኛ ግንኙነት የሌለበት ሃይማኖትም ከንቱ ነው።
የውይይት ጥያቄ፥ እነዚህን እውነቶች ክርስቲያኖች ያስታውሷቸው ዘንድ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው?
ጸሐፊው፥ የሰው ልጅ ዋጋ ያለው ነው ብሎ የሚቈጥረውን ነገር ሁሉ በመመርመር፥ የሚከተሉትን ማጠቃለያዎች ይሰጣል፡-
1. ሕይወት ትርጕም እንዲሰጥና ዓላማ እንዲኖረው፥ እግዚአብሔር የነገሮች ሁሉ ማዕከል መሆኑን በመገንዘብ መኖር ይገባናል። ሕይወት የራሱ የሆኑ ስንክሳራዊ ሁኔታዎችና ችግሮች ሲኖሩት የእግዚአብሔርን ዓላማ በማንረዳበት ጊዜ እንኳ እርሱ ዓላማውን በመፈጸም ላይ መሆኑን ማስታወስ ለእኛ ለክርስቲያኖች አስፈላጊ ነው። ያለ እግዚአብሔር፥ ማንኛውም ነገር ትርጕም የሌለው ከንቱ ነገር ነው።
2. የሕይወትን ትርጒም ለማወቅ መሠረታዊው ነገር በእግዚአብሔር መታመን ነው። ነገሮች ሁሉ በእግዚአብሔር ቁጥጥር ሥር መሆናቸውን ማመን አለብን (መክብብ 3፡1-15፤ 6፡1-2፤ 9፡1)።
3. ሕይወት በአብዛኛው ዓላማ ያለው ባይመስልም፥ አስተማማኝ በሆነ ትዕግሥት በእግዚአብሔር ላይ ተደግፈን፥ እርሱ በሰጠን መልካም ነገሮች ሁሉ ደስ እየተሰኘን ልንኖር ይገባል (መክብብ 2፡24-26፤ 11፡8)።
4. ሕይወት ትርጒም የሚኖረው፥ እግዚአብሔርን በመታዘዝና በምናደርገው ነገር ሁሉ እርሱ ፈራጅ እንደሆን በመገንዘብ የምንኖር ስንሆን ነው (መክብብ 8፡8-9፤ 12፡13)። እግዚአብሔር ደስታንና ዓላማን ይሰጣል። የእውነተኛ ጥበብ መሠረት እግዚአብሔርን መፍራት ነው (መክብብ 3፡14፤ 5፡7፤ 7፡18)። ክርስቲያን ባለው ነገር የሚረካ መሆን አለበት (መክብብ 2፡24-25፤ 3፡10-13)።
መጽሐፈ መክብብ የተጻፈው በዓለም የሚኖሩ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዲመረምሩና ከንቱ መሆኑን እንዲያዩ ለመገፋፋት ነው። ከዚያም ጸሐፊው ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱና በእርሱ የሕይወትን ትርጒም እንዲሹ ይፈልግ ነበር። ያለ እግዚአብሔር፥ የሕይወት ትርጒምና እውነተኛ ደስታ የለም።
የውይይት ጥያቄ፥ ለእኛ እነዚህን እውነቶች ማስታወስ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
ዋና ዋና ትምህርቶች፡-
1. እንደ ሌሎቹ የጥበብ መጻሕፍት ሁሉ፥ መጽሐፈ መክብብ ጻድቅ እንደሚባረክና ኃጢአተኛ ሰው እንደሚቀጣ በሚናገረው መመሪያ ላይ ያተኲራል። መጽሐፈ መክብብ ይህንን እውነት የሚደግፍ ቢሆንም እንኳ ሰዎች የሌሎችን ጽድቅ ወይም ክፋት በዚህ መመሪያ በመመዘን እንዳይፈርዱ ያስጠነቅቃል። ጸሐፊው ጻድቃንም ሆኑ ኃጥአን እንደሚሞቱ ይናገራል። ብዙ ጊዜ ጻድቃን በግፍ የገደሉ፥ ድሆች፥ የተጨቆኑና ወዘተ. ናቸው።
2. መጽሐፈ መክብብ መጽሐፍ ቅዱስ በሚያስተምረው መሠረት ዓለምን መመልከት አስፈላጊ እንደሆነ ያስተምራል። ከእግዚአብሔር ውጭ («ከፀሐይ በታች») ያለውን የዓለምን አመለካከት ያቀርባል። በትክክል ስንመዝናቸው ሁሉም ትርጕም አልባና ከንቱዎች ናቸው። ክርስቲያን ስለ ዓለም ያለው አመለካከት አንድን ሰው በእግዚአብሔር ምክንያት ደስ ወደሚሰኝበት ሕይወት እንደሚመራው ያስተምራል። እግዚአብሔር መልካም ነገሮችን ይሰጠናል። ለምናደርገው ነገር ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ተጠያቂዎች ስለሆንን እርሱን በመፍራትና በመታዘዝ መኖር ይገባናል።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እነዚህ ሁለት ትምህርቶች በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የሚያስፈልጉት ለምንድን ነው? ለ) ክርስቲያኖች ብዙ ጊዜ በዓለም አስተሳሰብ የሚሳቡባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው? ሐ) እነዚህ እውነቶች ክርስቲያኖች ለእግዚአብሔር ከመኖር ውጭ፥ የዓለም ነገሮች ሁሉ ጥቅም የሌላቸው ከንቱዎች እንደሆኑ እንዲያውቁ እንዴት ይረዷቸዋል? መ) እነዚህን እውነቶች በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች እንዴት ልታስተምራቸው ትችላለህ?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)
ዘመናችሁ ይባረክ🖐🖐❤❤