ሰቆቃወ ኤርምያስ መግቢያ

ክርስቲያኖች ነገሮች ሁሉ ለእነርሱ የጨለሙ በሚመስሉበት ጊዜ ምን ማድረግ አለባቸው? አገራቸው በእርስ በርስ ጦርነት በምትጠፋበትና ምንም ተስፋ የሌለ በሚመስልበት ጊዜ ምን ማድረግ አለባቸው? ከቤተሰቦቻቸው መካከል አንዳንዶች በበሽታ፥ በራብ ወይም በሌላ አሳዛኝ መንገድ በሚሞቱበት ጊዜ ምን ማድረግ ይገባቸዋልን? ተስፋ መቁረጥ አለባቸውን? እግዚአብሔርን መውቀስ ይገባቸዋልን? እምነታቸውን መተው አለባቸው? ችግሩን ሸሽተው ለማምለጥ ወደ ሌላ አገር መሰደድ ይገባቸዋል? ቀኖቹ ክፉዎች በሚሆኑበት ጊዜ ክርስቲያኖች አዘውትረው የሚያደርጉአቸው ነገሮች እነዚህ ናቸው። 

የውይይት ጥያቄ፥ እንደዚህ ተሰምቶህ ያውቃልን? ሁኔታውን ግለጽ። የዚህ ዓይነት ስሜት ተሰምቶህ የማያውቅ ከሆነ እንደዚህ ተሰምቶአቸው የሚያውቅ ሌሉች ክርስቲያኖችን ታውቃለህን? ለዚህ ስሜታቸው የሰጡት ምላሽ ምን ነበር?

ሰቆቃወ ኤርምያስ ከትንቢተ ኤርምያስ ጋር በቅርብ የተያያዘ መጽሐፍ ነው። ይህም የሆነው፥ ሰቆቃወ ኤርምያስ የይሁዳ ሕዝብ ከተማቸው ስትጠፋ በማየት የተሰማቸውን ከፍተኛ የሥቃይ ስሜት በቅኔ የገለጹበት በመሆኑ ነው። እንዲሁም ከሁሉ አብልጠው የሚያፈቅሩትን ነገር ያጡ ክርስቲያኖች ልብ ብዙ ጊዜ ሊሰማው የሚችለውን የሥቃይ ስሜት የሚገልጽ ነው። ለእግዚአብሔር የሚያቀርቧቸውን ጥያቄዎችና በልባቸው የሚፈጠረውን ጥርጣሬ የሚገልጽ ነው። እንዲሁም በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነትና በከፍተኛ ኃዘን ውስጥ የእግዚአብሔርን ምሕረት ለመጠበቅ ፈቃደኛ መሆንንም የሚገልጽ ነው። 

የሰቆቃወ ኤርምያስ ስያሜ

በዕብራይስጥ ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ሰቆቃወ ኤርምያስ ከሌሎች አራት መጻሕፍት ጋር በአንድነት ተቀናጅቶ «ጽሑፎች» የሚል ስያሜ ያለው የመጻሕፍት ክፍል መሥርቶ ነበር። እነዚህ አራት መጻሕፍት መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን፥ መጽሐፈ ሩት፥ መጽሐፈ መክብብና መጽሐፈ አስቴር ናቸው። እነዚህ አምስት መጻሕፍት እያንዳንዳቸው በተወሰኑ ሃይማኖታዊ በዓላት ጊዜ ይነበቡ ነበር። ሰቆቃወ ኤርምያስ ኢየሩሳሌም በ586 ዓ.ዓ. በባቢሎናውያን፥ በ70 ዓ.ም. በሮማውያን እጅ ለወደቀችበት ቀን መታሰቢያ በዓል ዕለት ይነበብ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ «ሰቆቃወ» የሚለው ቃል በግዕዝ ምን ማለት ነው? የዚህን ቃል ፍች ካላወቅህ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቄስን ጠይቅ።

ሰቆቃወ ኤርምያስ ከሙሾ ወይም አይሁዳውያን የታወቀ ዐርበኛ በሚሞትበት ጊዜ ከሚያዜሙት ዜማ ጋር ተመሳሳይ ነው። የዚህ ዓይነት መዝሙራት ብዙ ጊዜ የሚጀምሩት «እንዴት» በሚል ቃል ነው (ለምሳሌ፡፡ 2ኛ ሳሙኤል 1፡19፤ ኢሳይያስ 14፡12)። ስለዚህ የዚህ መጽሐፍ የዕብራይስጥ ርእስ «እንዴት» የሚል ነው። የአማርኛና የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ርእሶች የልቅሶ ወይም የዋይታ እንጉርጉሮን ያመለክታሉ። ይህም የሚያንጸባርቀው ሰቆቃወ ኤርምያስ የኢየሩሳሌምን መጥፋት ስለሚመለከት ልቅሶ የሚናገር መጽሐፍ መሆኑን ነው። 

የሰቆቃወ ኤርምያስ ጸሐፊ

የውይይት ጥያቄ፥ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ሰቆቃወ ኤርምያስ የሚለው ርእስ መጽሐፉን የጻፈው ማን ነው ይላል?

ሰቆቃወ ኤርምያስ መጀመሪያ ሲጻፍ ስለ ጸሐፊው የሚናገር ነገር አልነበረም። በኋላም የዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ በሴጵቱዋጀንት መጽሐፍ ቅዱስ እንደምናየው ወደ ግሪክ ቋንቋ ሲተረጐም ምሁራን የሰቆቃው ኤርምያስ ጸሐፊም ኤርምያስ እራሱ መሆኑን ጽፈዋል። ስለዚህ በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ርእሱ በኤርምያስ የቀረበ እንጕርጕሮ ነው ይላል።

እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ሰቆቃወ ኤርምያስን ማን እንደጻፈው በትክክል አናውቅም። የምናውቀው ነገር ቢኖር የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ ማን ይሁን ማንም፥ ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን ባጠፉ ጊዜ የነበረ ሰው እንደሆነ ነው። አይሁድም ሆኑ ክርስቲያኖች የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ ኤርምያስ እንደሆነ ያምናሉ። ኤርምያስ የኢየሩሳሌምን ጥፋት ያየ ሰው እንደሆነ እናውቃለን። ጸሐፊው ኤርምያስ እንደሆነ እንድናስብ የሚያደርጉትን አንዳንድ ተመሳሳይ ነገሮች በትንቢተ ኤርምያስና በሰቆቃወ ኤርምያስ መካከል ይገኛሉ። ዳሩ ግን አንዳንድ ልዩነቶች ስላሉ፥ ስለ መጽሐፉ ጸሐፊ ማንነት የሚካሄደው የምሁራን ውዝግብ ቀጥሎአል። ስለዚህ ጸሐፊው ኤርምያስ እንደሆነ መገመት ቢቻልም፥ እርግጠኛ መሆን ግን አይቻልም።

መጽሐፉ የተጻፈው ኢየሩሳሌም በተደመሰሰችበትና አይሁድ በተማረኩበት በ586 ዓ.ዓ. ሳይሆን አይቀርም። 

የሰቆቃወ ኤርምያስ አወቃቀርና አስተዋጽኦ

ሰቆቃወ ኤርምያስ አምስት የተለያዩ ግጥሞችን የያዘ ነው። የመጀመሪያዎቹ አራት ግጥሞች አይሁድ እንጕርጕሮውን ወይም ዜማውን ለማጥናት ይረዳቸው ዘንድ የሚጠቀሙበትን የአጻጻፍ ስልት የተከተለ ነው። እያንዳንዱ ጥቅስ ወይም ተከታታይ ጥቅሶች ተከታታይ ፊደላትን ይጠቀማሉ። ለምሳሌ በምዕራፍ አንድና ሁለት የግጥሞቹ 22 ቊጥሮች የሚጀምሩት በአይሁድ የፊደላት ሥርዓት ውስጥ ያሉትን ተከታታይ ፊደላት በመጠቀም ነው። ከመጽሐፉ ጠቅላላ ምዕራፎች ይበልጥ ጠቃሚ በሆነው በምዕራፍ ሦስት እያንዳንዳቸው ሦስት ተከታታይ ቍጥሮች በፊደላቱ ውስጥ ባሉ ተመሳሳይ ፊደል የሚጀምሩ ናቸው። 

የሚከተለው የሰቆቃወ ኤርምያስ አስተዋጽኦ ነው፡-

1. በኢየሩሳሌም ላይ ስለደረሰው ችግርና ኃዘን የተሰጠ ገለጻ (ሰቆቃወ ኤርምያስ 1)፥ 

2. ጌታ በኢየሩሳሌም ላይ ስለ መቆጣቱ የቀረበ ገለጻ (ሰቆቃወ ኤርምያስ 2)፥ 

3. የግጥሙ ጸሐፊ ስለሆነው ሰው ኃዘንና ተስፋ የቀረበ ገለጻ (ሰቆቃወ ኤርምያስ 3)፥ 

4. ስለ ኢየሩሳሌም መከበብ የቀረበ ገለጻ (ሰቆቃወ ኤርምያስ 4)፥ 

5. ስለ ኢየሩሳሌም መመለስ የግጥሙ ጸሐፊ የጸለየው ጸሎት (ሰቆቃወ ኤርምያስ 5)።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading