የትንቢተ ዳንኤል ዓላማና መልእክት

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዳንኤል 2፡21፤ 4፡34-35 አንብብ። እነዚህ ቍጥሮች እግዚአብሔር የዓለምን መንግሥታት ጨምሮ የነገሮች ሁሉ ተቈጣጣሪ መሆኑን እንዴት ያስተምሩናል? ክርስቲያኖች ይህንን እውነት ማወቅ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

አይሁድ ከ1400 ዓ.ዓ. እስከ 586 ዓ.ዓ. እግዚአብሔር ለአብርሃም በገባው በቃል ኪዳን ምድር ላይ ኖረዋል። በ586 ዓ.ዓ. ግን በድንገት አይሁድ ከተስፋይቱ ምድር ተማርከው ተወሰዱ። በአሕዛብ ምድር ሆነው በአሕዛብ ቁጥጥር ሥር ይኖሩ ጀመር። አይሁድ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሳሉ የእግዚአብሔርን ኃይልና የበላይ ተቈጣጣሪነቱን በመጠራጠር ጥያቄ ማቅረብ መጀመራቸው የሚጠበቅ ነገር ነበር። አሕዛብ አንድን አገር ወይም መንግሥት ተዋግተው በሚይዙበት ጊዜ የእነርሱ አምላክ ካሸነፉት ሕዝብ አማልክት የበለጠ ብርቱና ኃይለኛ በመሆኑ እንደሆነ ያምኑ ነበር። ይህ ነገር ስለ እስራኤል አምላክም እውነት ነበርን? አይሁድ በአንድ ሉዓላዊ አምላክ ማመናቸው ስሕተት ነበርን? እግዚአብሔር አሕዛብን ሁሉ በእርግጥ ይቆጣጠራልን? ከሁሉም በላይ ደግሞ እግዚአብሔር እስካሁንም ድረስ በሕዝቡ ላይ የሚደርሱ ወይም የሚፈጸሙ ድርጊቶ ሁሉ የበላይ ተቈጣጣሪ ነውን?

ትንቢተ ዳንኤል የተጻፈው እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስና እግዚአብሔር የሁሉ ነገር ተቈጣጣሪ መሆኑን ለአይሁዳውያን ለማረጋገጥ ነበር። የምርኮው ሁኔታም በእግዚአብሔር ቁጥጥር ሥር ነበር። አሕዛብ ሁሉ በእግዚአብሔር ቍጥጥር ሥር ነበሩ። የእስራኤል ሕዝብ የወደፊት ሁኔታም ቢሆን በእግዚአብሔር ቁጥጥር ሥር የሆነና በእርሱ የሚወሰን ነበር። የትንቢተ ዳንኤል በተደጋጋሚ ለአይሁድ የሚያረጋግጠውና የሚያሳየው፥ ጊዜው ምንም ያህል እየከፋ ቢመጣም እግዚአብሔር የበላይ ተቈጣጣሪ መሆኑን ነው። የፓላስጢና ምድር ለብዙ መቶ ዓመታት እግዚአብሔር በነቢያቱ በኩል የሰጣቸው የተስፋ ቃሎች ሁሉ የሚፈጸሙት ወደ ከነዓን በሚመለሱበት ጊዜ ነው ብለው ያምኑ ነበር። የእግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግሥት እንደምትመጣ፥ መሢሑ በእነርሱ ላይ እንደሚገዛና እነርሱም በአሕዛብ ሁሉ ላይ የበላይ ለመሆን ተስፋ አድርገው ነበር። ዳሩ ግን ይህ ነገር አለመፈጸሙን ለማየት አይሁድ ብዙ ጊዜ አልወሰደባቸውም። ከአይሁድ መካከል ጥቂቶቹ ብቻ ወደ ከነዓን ሲመለሱ፥ የቀሩት በባቢሎን የጀመሩትን መልካም ሕይወትን መረጡ። አይሁድ በአሕዛብ መንግሥታት ሥር መሆናቸውን ቀጠሉ። ተስፋ የተሰጠው መሢሕ መምጣቱን የሚያሳይ አንዳችም ምልክት አልነበረም።

ስለዚህ እግዚአብሔር የእርሱ መንግሥት መምጣት ገና ከብዙ ጊዜ በኋላ የሚፈጸም መሆኑን ሊያሳያቸው ፈለገ። በቅድሚያ አራት የአሕዛብ መንግሥታት መምጣት ነበረባቸው። መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት 70 ሱባዔ (490 ዓመታት) ማለፍ ነበረባቸው። አዎን፥ መጨረሻው ይመጣል፤ ዳሩ ግን ይህ የሚሆነው ከረዥም ጊዜ በኋላ ነበር። በመካከሉ አይሁድ በአሕዛብ ዓለም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ይኖራሉ። ለእግዚአብሔር ታማኞች ሆነው መኖር ነበረባቸው። የእግዚአብሔር ዕቅድ የማይጠፋና የማይበላሽ ስለሆነ በሉዓላዊነቱ መበረታታት ነበረባቸው። እግዚአብሔር ለእርሱ ታማኞች ሆነው እስከኖሩ ድረስ ሊጠብቃቸውና በየትውልዶቹ ሁሉ ሊያጸናቸው ተስፋ ሰጥቶአቸው ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህ የመጨረሻ ዓላማ ብዙ ክርስቲያኖችን ዛሬ ከሚያጋጥማቸው ነገር ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ለ) የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስንና የዘላለማዊ መንግሥቱን መምጣት በምንጠባበቅበት ጊዜ፥ ከትንቢተ ዳንኤል ውስጥ የምናገኛቸው እነዚህ እውነቶች ታማኞች ሆነን እንድንቆይ የሚያበረታቱን እንዴት ነው?

የትንቢተ ዳንኤል ዓላማ «የእስራኤል አምላክ በሰው ልጆች ጉዳይ ላይ ሉዓላዊ» መሆኑን ማሳየት ነው። እግዚአብሔር የአሕዛብንና የራሱን ሕዝብ ታሪክ ይቆጣጠራል። ታሪክን ሁሉ ወደ ፍጻሜው የሚመራው እግዚአብሔር ነው። ይህ ፍጻሜ እግዚአብሔር በምድር ላይ በሙላት በመቆጣጠር የሚገዛበት የእግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግሥት መመሥረት ነው። የእግዚአብሔር ሉዓላዊነት በሁለት መንገዶች ተገልጿል፡-

1. በራሱ ሕዝብ ሕይወት ውስጥ ግላዊ ሉዓላዊነቱ ገልጿል። ትንቢተ ዳንኤል እግዚአብሔርን በሚጠሉና እርሱን በማያመልኩ ሕዝቦች መካከል ሰው በእግዚአብሔር በማመን እንዴት መኖር እንደሚችል የሚያሳዩ በርካታ አስደናቂ ታሪኮችን ይዞአል። እግዚአብሔር ጠላቶቻቸውን ስለሚቆጣጠር ለእርሱ የታመኑትን ሰዎች እንደሚታደግና እንደሚያከናውንላቸው ያሳያል።

የውይይት ጥያቄ ሀ) እግዚአብሔር በልጆቹ ሕይወት ውስጥ የሚፈጸሙ ግላዊ ድርጊቶች ተቈጣጣሪ መሆኑን የሚያሳዩትን አንዳንድ ታሪኮች ከትንቢተ ዳንኤል ውስጥ ዘርዝር። ለ) እነዚህ ታሪኮች ዛሬም ለእግዚአብሔር ታማኝ እንድትሆን የሚያበረታቱህ እንዴት ነው? 

2. እግዚአብሔር በዓለም ላይ የሚገኙ ሕዝቦችንና ኃያላን መንግሥታትን ሁሉ ይቆጣጠራል። በዓለም ላይ የሚነሡት አራት ታላላቅ የአሕዛብ መንግሥታት እነማን መሆን እንዳለባቸው የወሰነው እግዚአብሔር ነበር። ኃያሉን ናቡከደነፆር በትዕቢቱ ምክንያት ያዋረደውና ያሳበደው እግዚአብሔር ነበር። አሕዛብ ሁሉ የሚገዙለትን ዘላለማዊ መንግሥት የሚያመጣውም እግዚአብሔር ራሱ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ይህ እውነት ክርስቲያኖችን የሚያበረታታው እንዴት ነው?

ትንቢተ ዳንኤል አንድ ሌላ ጠቃሚ ዓላማ ነበረው። በዳንኤል ዘመን ይኖሩ የነበሩ አይሁድ ትንቢቱ የሚፈጸምበትን ጊዜና ወደ ከነዓን መቼ እንደሚመለሱ ለማወቅ ከፍተኛ ጒጒት ሳያድርባቸው አልቀረም። እግዚአብሔር በነቢያቱ በኩል የሰጣቸው የተስፋ ቃሎች ሁሉ የሚፈጸሙት ወደ ከነዓን በሚመለሱበት ጊዜ ነው ብለው ያምኑ ነበር። የእግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግሥት እንደምትመጣ፥ መሢሑ በእነርሱ ላይ እንደሚገዛና እነርሱም በአሕዛብ ሁሉ ላይ የበላይ ለመሆን ተስፋ አድርገው ነበር። ዳሩ ግን ይህ ነገር አለመፈጸሙን ለማየት አይሁድ ብዙ ጊዜ አልወሰደባቸውም። ከአይሁድ መካከል ጥቂቶቹ ብቻ ወደ ከነዓን ሲመለሱ፥ የቀሩት በባቢሎን የጀመሩትን መልካም ሕይወትን መረጡ። አይሁድ በአሕዛብ መንግሥታት ሥር መሆናቸውን ቀጠሉ። ተስፋ የተሰጠው መሢሕ መምጣቱን የሚያሳይ አንዳችም ምልክት አልነበረም።

ስለዚህ እግዚአብሔር የእርሱ መንግሥት መምጣት ገና ከብዙ ጊዜ በኋላ የሚፈጸም መሆኑን ሊያሳያቸው ፈለገ። በቅድሚያ አራት የአሕዛብ መንግሥታት መምጣት ነበረባቸው። መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት 70 ሱባዔ (490 ዓመታት) ማለፍ ነበረባቸው። በሉቃስ 21:24 እንደምናገኘው ኢየሱስ ይህን ዘመን “የአሕዛብ ዘመን” በማለት ሰይሞታል፡፡ አዎን፥ መጨረሻው ይመጣል፤ ዳሩ ግን ይህ የሚሆነው ከረዥም ጊዜ በኋላ ነበር። በመካከሉ አይሁድ በአሕዛብ ዓለም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ይኖራሉ። ለእግዚአብሔር ታማኞች ሆነው መኖር ነበረባቸው። የእግዚአብሔር ዕቅድ የማይጠፋና የማይበላሽ ስለሆነ በሉዓላዊነቱ መበረታታት ነበረባቸው። እግዚአብሔር ለእርሱ ታማኞች ሆነው እስከኖሩ ድረስ ሊጠብቃቸውና በየትውልዶቹ ሁሉ ሊያጸናቸው ተስፋ ሰጥቶአቸው ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህ የመጨረሻ ዓላማ ብዙ ክርስቲያኖችን ዛሬ ከሚያጋጥማቸው ነገር ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ለ) የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስንና የዘላለማዊ መንግሥቱን መምጣት በምንጠባበቅበት ጊዜ፥ ከትንቢተ ዳንኤል ውስጥ የምናገኛቸው እነዚህ እውነቶች ታማኞች ሆንን እንድንቆይ የሚያበረታቱን እንዴት ነው?

በትንቢተ ዳንኤል ውስጥ የሚገኙ ዐበይት የሥነ-መለኮት ትምህርት እውነቶች፡-

የውይይት ጥያቄ፥ ዳንኤል 2:44፤ 4፡3፤ 7፡9-14፥ 26-27 አንብብ። እዚህ ጥቅሶች ስለ እግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግሥት ምን ያስተምሩናል?

1. የእግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግሥት፡- ትንቢተ ዳንኤል የእግዚአብሔርን መንግሥት ከሰዎች መንግሥት ጋር በማነጻጸር ላይ ያተኩራል። የሰዎች መንግሥት ምንም ያህል ታላቅና ኃይለኛ ቢሆን ጊዜያዊ ነው። የሚቆየው ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነው፤ ኃይሉም የተወሰነ ነው። ሰዎችንና ሁኔታዎችን ሁሉ ሊቁጣጠር አይችልም። ዳንኤል ይህን እውነት ለማረጋገጥ የባቢሎንን (ምዕራፍ 4-5)፥ የሜዶንና የፋርስን (ምዕራፍ 8)፥ የግሪክን (ምዕራፍ 8 ና 11) እንዲሁም የሮምን መንግሥታት (ምዕራፍ 7) በምሳሌነት ያቀርባል። 

ከሰዎች መንግሥት ጋር በተነጻጻሪነት የቀረበው ደግሞ የእግዚአብሔር መንግሥት ነው። ትንቢተ ዳንኤል የእግዚአብሔር መንግሥት አመሠራረት እግዚአብሔር በታሪክ ውስጥ በአጠቃላይ ያለው የመጨረሻ ዓላማ እንደሆነ ያሳየናል። እግዚአብሔር ታሪክን ሁሉ ይቈጣጠራል፤ ዘላለማዊ መንግሥቱ ወደሚመጣበት ቀንም ያንቀሳቅሰዋል። ትንቢተ ዳንኤል የሚያስተምረው የእግዚአብሔር መንግሥት በብዙ ረገድ የተጀመረ መሆኑን ነው። እግዚአብሔር አሁንም ቢሆን በሰማይ ነግሦአል። መንግሥቱም ከዘለዓለም እስከዘለዓለም ነው (ዳንኤል 4፡3፥ 34-35)። እግዚአብሔር ምን ጊዜም የፍጥረታት ሁሉ የበላይ ገዥና ንጉሥ ሲሆን፥ ወደ ፊትም እንዲሁ ይቀጥላል። ዓላማዎቹን ሊለውጥና በመንግሥቱም ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችል ማንም የለም።

በተጨማሪም፥ ትንቢተ ዳንኤል የእግዚአብሔር መንግሥት በሙላት የሚገለጸው ገና ወደ ፊት መሆኑንም ያስተምራል። የታሪክ ጒዞ በመፋጠን ላይ ያለው ወደዚሁ መንግሥት ነው። የእግዚአብሔር መንግሥት በሚመጣበት ጊዜ የሰዎች መንግሥት ሁሉ ይደመሰስና የእግዚአብሔር መንግሥት ብቻ ጸንቶ ይቆማል (ዳንኤል 2፡44)። ይህ መንግሥት ሊደመሰስ የማይችል ዘለዓላማዊ መንግሥት ነው። ይህ መንግሥት «በሰው ልጅ በሚመስለው» (ለኢየሱስ ክርስቶስ) እና ለቅዱሳኑ ይሰጣል (ዳንኤል 7፡9-14፥ 21-22፥ 27)። ይህ መንግሥት በሚመጣበት ጊዜ ክፋት ሁሉ ይደመሰሳል (ዳንኤል 9፡24)። መንግሥቱ ከመገለጡ በፊት ግን ታላላቅ ጦርነቶች ይካሄዳሉ፤ የክፋት ልጅም ከእግዚአብሔር ቅዱሳት ጋር ለመዋጋት ይነሣል (ዳንኤል 9፡26-27፤ 11፡36-12፡13)። ዳሩ ግን እግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግሥቱን ለመመሥረት የክፋትን ልጅና ሠራዊቱን ይደመስሳል።

የውይይት ጥያቄ፥ ስለሚመጣው ዘላለማዊ መንግሥት የተነገረው እውነት [የዚህን ዘመን ክርስቲያኖች ሊያበረታታን የሚችለው እንዴት ነው? 

2. እግዚአብሔር ትዕቢትን እንደሚጠላና በእርሱም ላይ የሚያመጣው ፍርድ የኃጢአት ሁሉ እምብርት ትዕቢት ነው። ኃጢአት ሁሉ የትዕቢት ድርጊት ነው። ምክንያቱም ኃጢአት በምናደርግበት ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ዝቅ ብለን ለእርሱ በመስገድ በሕይወታችን እንዲነግሥ ከመፍቀድ ይልቅ የሕይወታችን ገዥዎች ራሳችን ነን እያልነው ነው። በእግዚአብሔር ላይ ወደ ማመፅ የሚመራን ትዕቢት ነው። እንዲሁም ኃጢአት ሁሉ እግዚአብሔር ሕይወታችንን እንዳይቈጣጠር በማለት የምንፈጽመው ዓመፅ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የሠራሃቸውን አሥር ኃጢአቶች ዘርዝር። ለ) እነዚህ ኃጢአቶች በሕይወትህ ውስጥ ትዕቢት ለመኖሩ ምልክት ወይም ማስረጃ የሚሆኑት እንዴት ነው? ሐ) እነዚህ ኃጢአቶች በእርግጥ በእግዚአብሔር ላይ የሚፈጸሙ የዓመፅ ተግባራት የሚሆኑትስ እንዴት ነው?

የትንቢተ ዳንኤል ትኩረት ወደ ዓመፅ በሚመራው የትዕቢት ኃጢአት ላይ ነው። ዓመፅም ሰውን ወደ ውድቀት ይመራል። ይህንን አካሄድ በእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ውስጥ አይተናል። በእግዚአብሔር ፊት ራሳቸውን ሲያዋርዱና ኃጢአታቸውን ሲናዘዙ እግዚአብሔር ያከብራቸው ነበር። ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ላይ በማመፅ ኃጢአት ሲያደርጉ ይጠፉ ነበር፤ ይህንን በመጽሐፈ መሳፍንት ውስጥ ተመልክተናል። እንዲሁም ስለ እስራኤል ሕዝብ መጥፋት በተጻፈው ታሪክ ውስጥም አይተነዋል። በትንቢተ ዳንኤል፥ እግዚአብሔር እንዳይታበዩ ነገር ግን የተቀደሰ ሕይወት እንዲኖሩ አይሁድን ሊያስጠነቅቃቸው ፈለገ፤ አለበለዚያ እንደሚፈረድባቸው ተናገረ።

ዳሩ ግን ትንቢተ ዳንኤል በአብዛኛው የሚያተኩረው በአሕዛብ ገዥዎችና መንግሥታት ትዕቢት፥ ዓመፅና ጥፋት ላይ ነው። ናቡከደነፆር በታበየ ጊዜ እግዚአብሔር እንደ ዱር አውሬ እንዲኖር አደረገው (ዳንኤል 4)። ብልጣሶር በታበየ ጊዜ እግዚአብሔር መንግሥቱን ወሰደበት (ዳንኤል 5፡18-23)። አራተኛው አውሬ (ዳንኤል 7)፥ ትንሹ ቀንድ (ዳንኤል 8)፥ የሚመጣው አለቃ (ዳንኤል 9) እና የደቡብ መንግሥት ንጉሥ (ዳንኤል 1) በታበዩና ባመፁ ጊዜ እግዚአብሔር አጠፋቸው።

ይህ አፈጻጸም በዓለም ታሪክ ሁሉ የምናየው ነው። እነዚያ የታበዩት መንግሥታት ወዲያውኑ ምግባረ ብልሹዎች ሆኑ፤ እግዚአብሔርም አዋረዳቸውና ታናናሽ መንግሥታት ሆኑ። ባቢሎን፥ ሜዶንና ፋርስ ግሪክ፥ ሮም፥ እንግሊዝ፥ ፈረንሳይና ሩስያ ልንጠቅሳቸው ከምንችል ብዙ ምሳሌዎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በመታበያቸውና በማመፃቸው፥ እግዚአብሔር ካወረዳቸው መንግሥታት መካከል ጥቂት ሌሎች ምሳሌዎችን ጥቀስ። ለ) በመታበያቸው ምክንያት እግዚአብሔር ካዋረዳቸው ሰዎች መካከል (ገዥዎች፥ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች፥ ወዘተ)፥ ጥቂቶችን ጥቀስ። ሐ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንደመሆናችን ስለ ትዕቢት ምን ልንማር ይገል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: