ዳንኤል 7-12

የትንቢተ ዳንኤል የመጀመሪያ ክፍል የሆነው ምዕራፍ 1-6፥ በዳንኤል የሕይወት ዘመን በተፈጸሙ ታሪካዊ ድርጊቶች ላይ ያተኩራል። ራእዮቹም ስለ አሕዛብ ነገሥታት እንጂ ስለ ዳንኤል አልነበሩም። ከምዕራፍ 7-12 ያለው የመጽሐፉ ሁለተኛ ክፍል እግዚአብሔር የአሕዛብ መንግሥታትንና የእስራኤልን ሕዝብ የወደፊት ሁኔታ ለዳንኤል በገለጣቸው ልዩ ራእዮች ላይ ያተኩራል። የመጀመሪያዎቹ ስድስት ምዕራፎች በቅድሚያ አሕዛብን የሚመለከቱ ከመሆናቸው የተነሣ የተጻፉት በአራማይክ ቋንቋ ሲሆን፥ የመጨረሻዎቹ ስድስት ምዕራፎች የአሕዛብ መንግሥታት ከአይሁድ ጋር ባላቸው ግንኙነት ላይ ያተኩራሉ። ስለዚህ ዳንኤል 8-12 የተጻፈው በዕብራይስጥ ቋንቋ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ዳንኤል 7፡13-14 አንብብ። ሀ) እነዚህ ቁጥሮች በመጨረሻዎቹ ዘመናት ስለሚሆነው ነገር ምን ያስተምሩናል? ለ) «የሰው ልጅ የሚመስለው» ማን ነው? ) እነዚህ ቊጥሮች ዛሬ በዘመናችን ማበረታቻ የሚሆኑን እንዴት ነው? መ) አንድ ሰው የዚያ ዘላለማዊ መንግሥት አባል የሚሆነው እንዴት ነው?

ትንቢተ ዳንኤል በሰዎች የግል ሕይወትም ሆነ በዓለም ገዥዎችና መንግሥታት ላይ እግዚአብሔር ሉዓላዊ የሆነ ቍጥጥር እንደሚያደርግ በማሳየት ላይ የሚያተኩር መሆኑን ተመልክተናል። መጽሐፍ ቅዱስ ጌታ ኢየሱስ ዘላለማዊ መንግሥቱን ለመመሥረት ከመመለሱ በፊት ዘመናት ሁሉ ስለሚፈጸሙ ዝርዝር ጉዳዮች ሰፊ ትንተና ባይሰጥም፥ ስለ መጨረሻው ዘመን ግን ግልጽ የሆኑ አሳቦችን ይሰጣል። ዘላለማዊ ፈራጅ የሆነው እግዚአብሔር የፍርድ ዙፋኖችን ይመሠርታል። ጠላቶቹ ሁሉ ይፈረድባቸውና ለዘላለም ወደ ገሃነም ይጣላሉ። የእግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግሥት «የሰው ልጅ» ለተባለው ለኢየሱስ ክርስቶስ ይሰጣል። ያ መንግሥት ዘወትር የሚኖር ሲሆን፥ ከሰዎች መንግሥታት በተለየ መንገድ ዘላለማዊና የማይጠፋ ይሆናል። የቀሩት መንግሥታትና ሰዎች ሁሉ እግዚአብሔርን ያመልካሉ። ክርስቲያን የእምነቱ ጠላቶች ምንም ያህል ቢበረቱና ጊዚውም እጅግ ቢከፋ፥ ጸንቶ እንዲቆይ የሚያደርገው ይህ «ተስፋ» ነው። እያንዳንዳችን ልንጠይቀው የሚገባን በጣም አስፈላጊ ጥያቄ «በኢየሱስ ክርስቶስ አምነን የዘላለማዊው መንግሥት አካል ሆነናልን?» የሚል ነው። በኢየሱስ ያላመኑ ሰዎች ከዚህ መንግሥት ስለተገለሉና የእግዚአብሔር ጠላቶች ስለሆኑ ከእርሱ ዘንድ ቅጣታቸውን ይቀበላሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ዳንኤል 7-12 አንብብ። ሀ) በምዕራፍ 7 የምናገኘውን የዳንኤልን ራእይ ግለጽ። የአራቱን እንስሳት ስምና የትኛውን መንግሥት እንደሚወክሉ አብራራ። ለ) ስለ «ትንሹ ቀንድ» መግለጫ ስጥ። ሐ) ዳንኤል ስለ አውራ በግና ስለ ፍየል ያየውን ራእይ ግለጽ። የትኞቹን መንግሥታት ይወክላሉ? መ) የሰባ ዓመቱ ምርኮ ፍጻሜ ከደጅ መቃረቡን እንዲገነዘብ ያደረገውና ዳንኤል በምዕራፍ 9 ያነበበው ነገር ምን ነበር? ሠ) በዘመን መጨረሻ የሚሆኑትን ስድስት ነገሮች ዝርዝር (ዳንኤል 9፡24)። ረ) ስለ ሰባ ሱባዔዎች የተነገረውን ትንቢት በአጭሩ ግለጽ። ሰ) በሰሜንና በደቡብ ነገሥታት መካከል ስለተደረጉት ጦርነቶች ግለጽ። ሸ) ከሞት የሚነሣው ማን ነው?

የትንቢተ ዳንኤል መጨረሻ ክፍል ከዳንኤል በኋላ እስከ ዘመኑ መጨረሻ ስለሚፈጸሙት ነገሮች በርካታ ጠቃሚ ትንቢቶችን የያዘ ነው። እያንዳንዱ ራእይ ቀደም ሲል በተነገረው ራእይ ላይ ተጨማሪ እውነቶችን በማከል፥ በታሪክ ውስጥ በሚከሰቱ ልዩ ልዩ ጊዜያት የሚፈጸሙትን ድርጊቶች በዝርዝር ይገልጻል። እነዚህ ትንቢቶች ከመፈጸማቸው በፊት በመቶ የሚቈጠሩ ዓመታት ያለፉ ቢሆንም፥ አብዛኛዎቹ ከተነገሩበት ሁኔታ ምንም ሳይዛነፉ መፈጸማቸውን መመልከት የሚያስደንቅ ነው። ጥቂቶቹ ደግሞ ገና ወደፊት ይፈጸማሉ። 

1. ዳንኤል ስለ አራቱ አራዊት ያየው ራእይ (ዳንኤል 7)

ዳንኤል በምዕራፍ 7 ያየው ራእይ ናቡከደነፆር በምዕራፍ 2 ካየው ሕልም ጋር ተመሳሳይ ነው። ሁለቱም ሕልሞች የአይሁድ መንግሥት በአሕዛብ መንግሥታት ሥር በሚሆንበት ጊዜ የሚገዙትን አራት መንግሥታት ያሳያሉ። የሁለቱም ሕልሞች ማጠቃለያ በመጨረሻ የቀሩትን መንግሥታ ሁሉ የሚደመስሰው የእግዚአብሔር መንግሥት መሆኑን ያሳያል። ይሁን እንጂ ዳንኤል 7 የእግዚአብሔር መንግሥት ከመምጣቱ አስቀድሞ ስለሚገለጠውና ከሁሉም የከፋ ስለሚሆንው ስለ መጨረሻው ንጉሥ ሰፊና ዝርዝር ጉዳዮችን ይሰጣል። አዲስ ኪዳን ይህንን ሰው «ሐሰተኛው ክርስቶስ» በማለት ይጠራዋል (1ኛ ዮሐንስ 2፡18)። በዚህ የትንቢተ ዳንኤል የመጨረሻ ክፍል ስለዚህ ክፉና ጨካኝ መሪ በዝርዝር ተገልጾአል።

ዳንኤል ያየውን ራእይ ትርጕም ከሚከተለው ሠንጠረዥ ተመልከት፡

የእንሰሳው ዓይነት፣ አንበሳ 

የሚወክለው መንግሥት፣ ባቢሎን

በሥልጣን ላይ የቆየበት ጊዜ፣ 626-539 ዓ.ዓ.

የእንሰሳው ዓይነት፣ ድብ 

የሚወክለው መንግሥት፣ ሜዶንና ፋርስ

በሥልጣን ላይ የቆየበት ጊዜ፣ 539-330 ዓ.ዓ.

የእንሰሳው ዓይነት፣ ነብር 

የሚወክለው መንግሥት፣ ግሪክ

በሥልጣን ላይ የቆየበት ጊዜ፣ 330-63 ዓ.ዓ. 

የእንሰሳው ዓይነት፣ የምታስፈራ አውሬ

የሚወክለው መንግሥት፣ ሮም

በሥልጣን ላይ የቆየበት ጊዜ፣ 63 ዓ.ዓ.- 400 ዓ.ም.

የእንሰሳው ዓይነት፣ አሥር ቀንዶችና ትንሽ ቀንድ

የሚወክለው መንግሥት፣ ያንሰራራ የሮም መንግሥት

በሥልጣን ላይ የቆየበት ጊዜ፣ መጪው ጊዜ

የእንሰሳው ዓይነት፣ ለሰው ልጅ የተሰጡ ዙፋኖች

የሚወክለው መንግሥት፣ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግሥት

በሥልጣን ላይ የቆየበት ጊዜ፣ መጪው ጊዜ

ስለዚህ መንግሥት የሚከተሉትን ነገሮች አስተውል፡-

ሀ. ድቧ ሦስት የጐድን አጥንቶች ነበሯት። በአንድ ወገንም ከፍ ብላ ቆማ ነበር። ይህ የሚያመለክተው የፋርስ መንግሥት ከሜዶን መንግሥት የሚበልጥ መሆኑን ነው። ሦስቱ የጎድን አጥንቶች የሜዶንና የፋርስ መንግሥት ከግዛቱ አብዛኛውን ክፍል ያገኘባቸውን ሦስት ታላላቅ ጦርነቶች የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። 

ለ. የነብሩ አራት ራሶች የግሪክ መንግሥት ለአራት መከፈልን የሚያሳዩ ናቸው።

ሐ. የመጨረሻው አውሬ ሊገለጽ የማይችልና በምድር ላይ ከሚገኙ ከማናቸውም ዓይነት አራዊት የተለየ ነበር። ከሁሉም የላቀ ኃይለኛና አጥፊ አውሬ ነበር።

መ. ምሁራን ስለ አሥሩ ቀንዶችና ስለ ትንሹ ቀንድ በሚሰነዝሩት አስተያየት ይለያያሉ። አሥሩ ቀንዶች የሮም መንግሥት ለአሥር እንደሚከፋፈል የሚያሳዩ ሊሆኑ ይችላሉ። ትንሹ ቀንድ ደግሞ ስለ አንድ የተለየ ክፉ መሪ የሚናገር ሊሆን ይችላል። እነዚህ ቀንዶች ቀድሞ የሮም መንግሥት በነበረበት አካባቢ ስለሚመሠረት የመንግሥታት የኮንፌዴሬሽን (ትብብር) የሚያመለክቱ ሊሆኑ ይችላሉ። ትንሹ ቀንድ በእግዚአብሔርና በሕዝቦቹ ላይ የመጨረሻውን ጦርነት ስለሚከፍተው ስለመጨረሻው የዓለም ገዥ ስለ «ሐሰተኛው ክርስቶስ» የሚናገር ሳይሆን አይቀርም። 

ሠ. የሰውን መንግሥት ፍጻሜ የሚወሰንና ዘላለማዊውን መንግሥት የሚመሠርት እግዚአብሔር ነው። ያንን መንግሥት «ለሰው ልጅ» የሚሰጠውም እርሱ ነው። ዘላለማዊ መንግሥት ለሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን፥ ለእግዚአብሔር ቅዱሳንም ይሰጣል። ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ዘመን ብዙ ጊዜ ይጠራበት የነበረው ስም «የሰው ልጅ» የሚል መሆኑ የሚገርም ነው። ይህ የአዲስ ኪዳን አጠራር በቅድሚያ የሚያመለክተው የኢየሱስን ሥጋ ለባሽነት ሳይሆን በዳንኤል 7፡13 የተጻፈው ፍጻሜ ሳይሆን አይቀርም።

2. ዳንኤል ስለ አውራ በግና አውራ ፍየል ያየው ራእይ (ዳንኤል 8)

ዳንኤል 8 የሚያተኩረው የባቢሎን መንግሥት ከወደቀ በኋላ በሚነሡት ሁለት የአሕዛብ መንግሥታት ላይ ነው። እነዚህም የሜዶንና የፋርስ ጥምር መንግሥትና የግሪክ መንግሥት ናቸው። ሜዶንና ፋርስ በአውራ በግ ተመስሎ የቀረበ ሲሆን፥ የግሪክ መንግሥት ደግሞ በአውራ ፍየል ተመስሉ ቀርቧል። በራእዩ ውስጥ የተጠቀሱትን የሚከተሉትን እውነቶች አስተውል፡-

ሀ. አውራው ፍየል በመጀመሪያ አንድ ቀንድ የነበረው ሲሆን፥ ከምዕራብ ወገን በከፍተኛ ፍጥነት በመምጣት ጥቃት ሰነዘረ። ቀንዱ በሦስት ዓመታት ውስጥ ከግሪክ እስከ ግብፅ ድረስ የነበሩትን አገሮች ሁሉ ወርሮ የያዘውን ታላቁን እስክንድር የሚያመለክት ነው። ዳሩ ግን ቀንዱ ድንገት እንደተሰበረ ሁሉ እስክንድርም በድንገት ሞተ። 

ለ. አንዱ ቀንድ በነበረበት ስፍራ አራት ቀንዶች በቀሉ። ይህ የሚያመለክተው የግሪክ መንግሥት ከእስክንድር ሞት በኋላ ለአራት የተከፈለ መሆኑን ነው። 

ሐ. ከታናናሾቹ ቀንዶች መካከል አንዱ ታዋቂና ገናና እስኪሆን ድረስ ከፍ አለ። እርሱም በተለየ ሁኔታ እጅግ ክፉ የነበረ፥ «መልካሚቱ ምድር» በተባለችው በእስራኤል የነበሩትን ቅዱሳን ያሳደደና አይሁድ በቤተ መቅደስ ሲፈጽሙት የነበረውን አምልኮ ያልቆመ ነበር። ይህ ትንሽ ቀንድ በዳንኤል 7 ከተመለከትነው ከአስፈሪው አውሬ ከሮም መንግሥት ከወጣው ቀንድ የተለየ ነው። ይህ ቀንድ የወጣው ከአውራው ፍየል ከግሪክ መንግሥት ነው። ይህ ቀንድ ከ168-164 ዓ.ዓ. የነገሠው ክፉና ጨካኝ ስለነበረው ስለ «አንቲየኪስ ኢጲፋነስ» የተነገረ ትንቢት ነው። እርሱ በኢየሩሳሌም ላይ ጦርነትን አውጆ በቤተ መቅደስ ውስጥ የጣዖት አምልኮ እንዲፈጸም አድርጎ ነበር። በእርሱ ላይ ያመፁ በሺህ የሚቈጠሩ አይሁዳውያንን ገድሏል። ዳሩ ግን ወዲያውኑ በድንገት ስለሞተ አይሁድ ሮማውያን እስኪመጡባቸው ድረስ ለጥቂት ጊዜ ከግሪክ አገዛዝ ነፃ ወጥተው ነበር። 

3. ዳንኤል ስለ ሰባ ሱባዔዎች ያየው ራእይ (ዳንኤል 9)

የትንቢቶችን የጊዜ ሰሌዳ ይዘት ለማዘጋጀት ከሚያገለግሉ ቁልፍ ምዕራፎች አንዱ ዳንኤል 9 ተደርጎ በብዙዎች ዘንድ ይታያል። ምሁራን የተለያዩ አመለካከቶችን በመያዝ በከፍተኛ ሁኔታ የሚከራከሩበት ክፍል ስለሆነም፥ ይህን የጊዜ ሰሌዳ ለመንደፍ የተለያዩ መንገዶች አሉ።

ይህ ምዕራፍ የሚጀምረው ዳንኤል ወደ እግዚአብሔር በጸለየው ጸሎት ነው። ዳንኤል ከትንቢተ ኤርምያስ በማንበብ ምርኮው የሚቆየው ለሰባ ዓመታት ብቻ መሆኑን ተገነዘበ። ዳንኤል ከሞላ ጐደል ለሰባ ዓመታት ያህል በምርኮኛነት እንደኖረና ይህም ሰባ ዓመት ሊጠናቀቅ እንደቀረበ ተረዳ። ዳንኤል ይህን ራእይ ያየው ዳርዮስ በነገሠበት በመጀመሪያ ዓመት፥ ቂሮስ አይሁድ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የሚፈቅደውን አዋጅ ባወጁበት ዓመት መሆኑን አስተውል። ዳንኤል ለሕዝቡ ይገደው ስለነበር፥ እግዚአብሔር ለዳንኤል የሰባ ሱባዔን ትንቢት ሰጠው። ስለ ራእዩ የሚከተሉትን ነገሮች አስተውል፡-

1. ራእዩ ስለ «ሕዝብህና ቅድስት ከተማህ» የሚናገር ነበር (ዳንኤል 9፡24)። ይህ ማለት የራእዩ ዐቢይ ርእስ የሚመለከተው የአይሁድን ሕዝብ ነው ማለት ነው። 

2. በዘመኑ መጨረሻ ሰባው ሱባዔ ሲፈጸም፥ ስድስት ነገሮች ይሆናሉ፡-

ሀ. ዓመፃ ያበቃል፤

ለ. ኃጢአት ያከትማል፤ 

ሐ. በደል ይሰረያል፤ 

መ. የዘላለም ጽድቅ ይጀመራል፤ 

ሠ. ራእይና ትንቢት ይታተማል፤ 

ረ. ቅድስተ ቅዱሳንም በዘይት ይቀባል። 

ብዙ ምሁራን እነዚህ የኢየሱስን ሞት እንደሚያመለክቱ ቢያስቡም፥ ከዚህም የላቀ ታላቅ ነገር የሚወክሉ ይመስላል። እነዚህ ነገሮች የሚያመለክቱት፡- ክፋት ሁሉ የሚወገድበትን፥ የእግዚአብሔር ዕቅድ ለዘላለም የሚመሠረትበትንና በዘመኑ ፍጻሜ የሚቋቋመውን የእግዚአብሔር መንግሥት ይመስላል። 

3. የአይሁድ ሕዝብ ታሪክ ሰባ ሱባዔዎችን ወይም የሰባ ሳምንት ዓመታትን የያዘ ነው። ብዙ ምሁራን እያንዳንዱ ሰባት ማለት ሰባት ዓመት (የአንድ ሳምንት ዓመታት) እንደሆነ ያምናሉ። ስለዚህ ሰባ ሱባዔ 490 ዓመት ነው።

ስለ ሰባ ሱባዔ የሚከተሉትን ነገሮች አስተውል፡-

ሀ. ሰባ ሱባዔዎች በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ተከፍለዋል። የመጀመሪያው ሰባት ሱባዔ ወይም 49 ዓመታት፥ ሁለተኛው 62 ሱባዔ ወይም 434 ዓመታት፥ ሦስተኛው ደግሞ አንድ ሱባዔ ወይም ሰባት ዓመታት ናቸው።

ለ. የመጀመሪያው ክፍለ ጊዜ «ኢየሩሳሌምን ለማደስና እንደገና ለመሥራት በወጣ አዋጅ» ይጀምራል። ይህም ንጉሥ አርጤክስስ በ444 ዓ.ዓ. ነህምያ ኢየሩሳሌምን እንደገና ይሠራ ዘንድ ፈቃድ የሰጠበት አዋጅ ሳይሆን አይቀርም። ይሁን እንጂ ቂሮስ አይሁድ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ በ539 ዓ.ዓ. የፈቀደበትን አዋጅም ሊያመለክት ይችላል። ይህ አዋጅ ቤተ መቅደሱ እንደገና እንዲሠራ የሚፈቅድ ነው፤ በመሆኑም የንጉሥ አርጤክስስ አዋጅ ነው ቢባል ይመረጣል። 

ሐ. የሁለተኛውን ክፍለ ጊዜ ፍጻሜ ልዩ የሚያደርገው የመሢሑ መምጣትና መሞት ነው። «መሢሕ» ማለት የተቀባ ማለት ነው። ስለዚህ ይህ የአይሁድ ንጉሥ የሆነው የመሢሑ የኢየሱስ ስም ነው።

መ. ከ62ኛው ሱባዔ በኋላ የኢየሩሳሌም ከተማና ቤተ መቅደስ ይደመሰሳሉ ተብሉ ነበር። ይህም ሮማውያን በ70 ዓ.ም. ኢየሩሳሌምን ያጠፋበትን ሁኔታ የሚያመለክት ይመስላል። ያ ጊዜ በጦርነትና በጥፋት የታወቀ ይሆናል። 

ሠ. የመጨረሻው አንድ ሱባዔ ክፍለ ጊዜ በምሁራን መካከል ከፍተኛ ክርክርን የፈጠረ ነው። ከ62ኛው ሱባዔ በኋላ ወዲያውኑ የሚሆን ነው ወይስ በ62ኛው ሱባዔና በመጨረሻው አንድ ሱባዔ መካከል ያልተወሰነ የጊዜ ርዝመት አለ? እነዚህ ጥቅሶች የሚያመለክቱት፡- በሞቱ የብሉይ ኪዳንን የመሥዋዕት ሥርዓት ከፍጻሜ የሚያደርሰውን መሢሕ ነው ወይስ አይሁድ በመጨረሻው ዘመን በሚሠሩት ቤተ መቅደስ ውስጥ እንዳያመልኩ የሚከለክላቸውን ሐሰተኛ ክርስቶስ ነው? ይህ ጉዳይ ኢየሱስ እስከሚመለስ ድረስ አከራካሪ ሆኖ እንደሚቆይ አያጠራጥርም። ዳሩ ግን እነዚህን ጥቅሶች በሰባዎቹ ሱባዔዎች መካከል «የአሕዛብ ዘመን» (ሉቃስ 21፡24) የሚባል ርዝመቱ በግልጽ የማይታወቅ ዘመን እንዳለ አድርጎ መተርጐሙ በጣም የተሻለ ይመስላል። የመጨረሻው ሱባዔ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመመለሱ በፊት ስለሚሆነው የታላቁ መከራ የመጨረሻ ጊዜን የሚያመለክት ነው። ስለዚህ ገዥው «ሐሰተኛው ክርስቶስ» ሲሆን ድርጊቶቹም በእነዚያ ታላቅ የመከራ ዓመታት የሚፈጽማቸው ናቸው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ስለ እነዚህ ጥቅሶች ከዚህ በፊት ምን ዓይነት አተረጓጐም ሰምተሃል? ለ) የትኛውን ታምናለህ? ለምን? 

4. ዳንኤል በደቡብና በሰሜን መንግሥታት መካከል ስለሚደረጉ ጦርነቶች ያየው ራእይ (ዳንኤል 10-12) 

ዳንኤል ያየው የመጨረሻ ራእይ የሜዶንና የፋርስ መንግሥት ወድቆ የግሪክ መንግሥት ስለተመሠረተበት ጊዜ ሰፊ ትንተና ይሰጣል። ራእዩ በሰሜንና በደቡብ ነገሥታት መካከል ያለማቋረጥ ስለተደረጉ ጦርነቶች ይናገራል። የሰሜኑ ነገሥታት ከተከፋፈለው የግሪክ መንግሥት ሴሉስድ ከተባለው ክፍል የወጡና ከደማስቆ ውጭ ሶሪያን ይገዙ የነበሩ ነገሥታት ናቸው። የደቡብ ነገሥታት ደግሞ ቶሌማይክ የተባሉ ግብፅን ይገዙ የነበሩ የግሪክ ነገሥታት ናቸው። እነዚህ ነገሥታት አንዱ የሌላውን ግዛት ለመቆጣጠር በሚደረግ ትግል ያለማቋረጥ ተዋግተዋል። ከነዓንና አይሁድ በእነዚህ ሁለት መንግሥታት መካከል ስለነበሩ ጦርነቶች የሚካሄድባቸው ቦታዎች ነበሩ። በዚያን ጊዜ በጣም ትንሽና ከቍጥር የማይገቡ የነበሩት አይሁድ ምንኛ ተዋክበው እንደነበር መገመት ይቻላል።

የራእዩ አብዛኛው ክፍል የሚያተኩረው በሁለት ክፉ መሪዎች ላይ ነበር፡፡ የመጀመሪያው መሪ ከሰሜን ነገሥታት መካከል የነበረው አይሁድን በመጥላት ጦር ኃይሉ ያሸነፋቸውና በቤተ መቅደስ ውስጥ ጣዖትን ያቆመው አንቲዩከስ ኤጲፋነስ ነበር (ዳንኤል 11፡10-33)። ሁለተኛው ንጉሥ ግን በዘመናት መጨረሻ በመገለጥ በአይሁድ ላይ ከፍተኛ ጥፋት የሚያመጣውን «ሐሰተኛው ክርስቶስ»ን የሚያመላክት ይመስላል (ዳንኤል 11፡36-46)። እነዚህ ጥቅሶች ስለ አንቲዩከስ ከምናውቀው ታሪክ ጋር የሚስማሙ አይደሉም። ይህን የመጨረሻ ክፉ ገዥ እግዚአብሒር ያጠፋዋል።

የራእዩ ማጠቃለያ መልአኩ ለዳንኤል እንዳይጨነቅ የነገረው ነገር ነው። ይህ ራእይ ራቅ ብሎ ስላለው መጪ ጊዜ የሚናገር ነበር። የዳንኤል ማረጋገጥ፥ ስማቸው በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኝ ሰዎችን እግዚአብሔር እንደሚታደጋቸው ነው። በእዚህ የስደት ጊዜያት ከሥጋዊ ሞት አይድኑም ይሆናል። ነገር ግን በመጨረሻው ዘላለማዊ መንግሥት ሐሤትን ለማድረግ ከሞት ይነሣሉ። ጨለማና ክፋት በሞላባቸው ጊዜያት የእግዚአብሔር ሕዝቦች በቅድስና በመድመቅ ጽድቅ በመሆን ኑሮ መኖር አለባቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህ ተመሳሳይ ዋስትና በዚህ ዘመን ላሉ ክርስቲያኖችም ማበረታቻ የሚሆነው እንዴት ነው? ለ) በዚህ ክፉ ዘመን በአስጨናቂው ዓለም ውስጥ ያሉት ክርስቲያኖች ደምቀው የሚያሰሩበትን መንገዶች ግለጽ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከትንቢተ ዳንኤል የምንማራቸውን ዋና ዋና ጠቃሚ ትምህርተች ዘርዝር። ለ) እነዚህን ትምህርቶች ለቤተ ክርስቲያንህ አባላት በመልእክት ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካይነት እንዴት ልታስተምር እንደምትችል ዐቅድ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

Leave a Reply

%d