ትንቢተ ሆሴዕን የሚመለከቱ ዋና ዋና ጉዳዮች

1. የሆሴዕና የጎሜር ጋብቻ

የአብዛኛው የትንቢተ ሆሴዕ ታሪክ መሠረት የሆሴዕና የጎሜር ታሪክ መሆኑን ተመልክተናል። ዳሩ ግን ምሁራን ይህንን ታሪክ የሚረዱበት መንገድ የተለያየ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ይህንን ታሪክ ከሚረዱባቸው መንገዶች መካከል ጥቂቶቹ ቀጥለው ተዘርዝረዋል፡-

ሀ. ተምሳሌታዊ አተረጓጐም፡- አንዳንድ ምሁራን ይህ ታሪክ እውነተኛ መሆኑን አያምኑም። ይህ ታሪክ በእግዚአብሔርና በእስራኤል መካከል የነበረውን አመንዝራነት የተሞላበት ግንኙነት የሚያሳይ ለነቢዩ የተሰጠ ራእይ ወይም ምሳሌ ነው ይላሉ።

ለ. ቀጥተኛ አተረጓጐም፡- አብዛኛዎቹ ምሁራን ይህ ታሪክ በሆሴዕ ሕይወት በእርግጥ የተፈጸመ ነው ይላሉ። ይሁን እንጂ ታሪኩን የሚተረጕሙበት መንገድ ግን ይለያያል።

1. ትንቢተ ሆሴዕ ምዕራፍ 1ና 3 ሆሴዕ ከጎሜር ጋር ስለፈጸመው ጋብቻ ይናገራሉ። የሁለቱም ምዕራፎች ድርጊቶች በአንድ ጊዜ የተፈጸሙ እንጂ ሁለት የተለያዩ ድርጊቶች አይደሉም። ሆሴዕ 3 እርስዋን ከማግባቱ በፊት ጎሜር ምን ዓይነት ሴት እንደነበረች ተጨማሪ ዝርዝር አሳቦችን ያቀርባል ብለው ያምናሉ።

2. ሆሴዕ ሁለት ሴቶችን አገባ። ሆሴዕ 1 የሚገልጠው ከጎሜር ጋር ስላደረገው ንጹህ ጋብቻ ነው። ሆሴዕ 3 ግን ለሁለተኛ ጊዜ ማንነቷ ካልታወቀ ከአንዲት አመንዝራ ሴት ጋር ስለፈጸመው ጋብቻ የሚገልጥ ነው። 

3. ሆሴዕ ጎሜር የተባለች አንዲት ሴት አገባ። የመጀመሪያው ጋብቻ በሆሴዕ 1 ተገልጧል። የጎሜር አመንዝራነት በባርነት መውደቋና ከሆሴዕ ጋር እንደገና መጋባቷ ደግሞ በምዕራፍ 3 ተገልጧል። ይህ አመለካከት ሁለቱን ምዕራፎች በሚመለከት እጅግ በጣም ትክክለኛ የሆነ ግንዛቤን የሚያስጨብጥና የተለመደ ይመስላል። ይሁን እንጂ እነዚህ ሊቃውንት ሆሴዕ ባገባት ጊዜ ምን ዓይነት ሰው ነበረች? ስለሚለው ጥያቄ የተለያየ አመለካከት አላቸው።

ሀ. አንዳንድ ምሁራን ጎሜር ከሆሴዕ ጋር በጋብቻ ስትጣመር ድንግል እንደነበረችና ከተጋቡ በኋላ ግን አመንዝራ እንደሆነች አበክረው ይናገራሉ።

ለ. ሌሎች ምሁራን ጎሜር እንደ ብዙሐኑ የእስራኤል ሕዝብ ጣዖታትን የምታመልክ «መንፈሳዊ አመንዝራ» ብቻ ነበረች ብለው ያስባሉ።

ሐ. በመጨረሻም፥ ሌሎች ምሁራን ጎሜር ሆሴዕን ከማግባቷ በፊት አመንዝራ ነበረች ይላሉ። አመንዝራ ብትሆንም እንኳ ሆሴዕ እንዲያገባት እግዚአብሔር አዘዘው። በኋላም ሆሴዕ ለእርሷ የነበረውን ታላቅ ፍቅር ትታ ወደ ቀድሞ የምንዝርና ኑሮዋ ተመለሰች። ይህም በእርሷ ላይ ከፍተኛ ችግር አመጣ። ሆሴዕ ከባርነቷ እንደገና በመዋጀት ሚስት አድርጎ ወሰዳት።

እነዚህ አመለካከቶች ሁሉ የአተረጓጐም ችግር ቢኖርባቸውም፥ ታሪኩን የምንረዳበት እጅግ የተለመደው መንገድ ግን ይህ የመጨረሻው አመለካከት ነው፤ ከእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ጋርም በሚገባ የሚስማማ ነው። እስራኤላውያን፥ አብርሃም ሳይቀር፥ እግዚአብሔር ሳይጠራቸው በፊት ጣዖት አምላኪዎች እንደነበሩ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። እግዚአብሔር በፍቅሩ መጥቶ ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን በገባ ጊዜ መንፈሳዊ አመንዝራዎች ነበሩ። ከዚያ በኋላ ባለው ታሪካቸው ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ቢያደርጉም እንኳ ለጣዖት መስገዳቸውን ቀጠሉ። ስለዚህ ጎሜር ካገባች በኋላ በምንዝርናዋ እንደቀጠለች እነርሱም መንፈሳዊ አመንዝራዎች ነበሩ (ለምሳሌ ሕዝቅኤል 16 እና 23)። 

2. የበአል አምልኮ 

እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን ባደረገ ጊዜ እስራኤላውያን ከእርሱ በቀር ሌሎች አማልክትን ላለማምለክ ቃል ገብተው ነበር (ዘጸአት 20፡1-6)። ይሁን እንጂ እስራኤል ለእግዚአብሔር በሚቀርበ አምልኮ ላይ የጣዖታትን አምልኮ ለማከል በተከታታይ ይፈተኑ ነበር። ይህም የተጀመረው እስራኤላውያን በታዘዙት መሠረት ከነዓናውያንን መሉ በሙሉ ባልደመሰሱበት በኢያሱ ጊዜ ነበር። ስለዚህ ከከነዓናውያን ጋር ወዲያውኑ በመጋባት፥ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ አምልኮን ለከነዓናውያን አማልክት ከሚቀርብ አምልኮ ጋር አደባለቁ (ለምሳሌ፡- መሳፍንት 2፡11-15)።

ከከነዓናውያን ዐበይት አማልክት አንዱ በአል ነበር። ኤልያስ ትግል ያደረገው የበአልን አምልኮ በመቃወም እንደነበር ይታወሳል። የስሙ ትርጉም «ጌታ» ወይም «የምድር ባል» ሲሆን፥ የዝናብና አውሎ ንፋስ አምላክ፥ ደግሞም ምድር ፍሬያማ እንድትሆን የሚያደርግ አምላክ ተደርጎ ይቆጠር ነበር። ሰዎች ልጆችን እንዲወልዱ የሚያደርገውም እርሱ እንደሆነ ይታመን ነበር። በአል ሞት የተባለ ጠላት ነበረው። በአል ኃያልና ብርቱ በሚሆንበት ጊዜ የከነዓን ምድር እጅግ ብዙ ምርትና ሰብል ታገኝ ነበር። ሞት በሚበረታበት ጊዜ ድርቅ ይሆን ነበር። በአል ጠንካራና ብርቱ መሆኑንና የማያቋርጥ ምርታማነት መኖሩን ማረጋገጥ የሰዎቹ ኃላፊነት ነበር። ይህንን የሚያደርጉት በአልን በማምለክ ነበር። ይህ አምልኮ የእንስሳትን፥ የእርሻ ፍሬንና በተለይም የሰውን መሥዋዕትን የመሳሰሉ የተለያዩ ዓይነት መሥዋዕቶችን የሚያጠቃልል ነበር። ይህ አምልኮ የምንዝርና ሥርዓትንም የሚጨምር ነበር። በእያንዳንዱ የተቀደሰ ወይም ከፍተኛ የአምልኮ ስፍራ የወንድና የሴት አመንዝራዎች ይገኙበት ነበር። በአልን ለማምለክ የሚመጡ ሰዎች ከእነዚህ የበአል ወንድና ሴት ካህናት ከሆኑት አመንዝራዎች ጋር ዝሙት መፈጸም ነበረባቸው።

እስራኤላውያን እግዚአብሔርን ከማምለክ አኳያ በአልን ከዋና ዋና አማልክት እንደ አንዱ ተቀብለውት ነበር። ከእውነተኛው አምላክ ከእግዚአብሔር ሌላ ሐሰተኛ አምላክ በማምለክ መንፈሳዊ ምንዝርና መፈጸም ብቻ ሳይሆን፥ ከእነዚህ አመንዝራዎች ጋር ዝሙት በማድረጋቸው ሥጋዊ አመንዝራዎችም ሆነው ነበር። ሆሴዕ የበአልን አምልኮ አጥብቆ ይቃወም ነበር (ሆሴዕ 4፡10-12፤ 13፡3-4)። እግዚአብሔር ለእርሱ የሚቀርብ እውነተኛ አምልኮ ለሌሎች ጣዖታት በሚቀርብ የሐሰት አምልኮ እንዲረክስ የማይፈልግ መሆኑን ሆሴዕ አሳይቶአል። የተቀየጠ አምልኮ ሐሰተኛ እንጂ እውነተኛ አምልኮ ሊሆን የሚችልበት ምንም መንገድ የለም።

እስራኤላውያን በአል ይሰጠናል ብለው ያሰቡትን ነገር እግዚአብሔር የወሰደባቸው መሆኑን መመልከት የሚያስገርም ነው። እርሻቸው በቂ ፍሬ እንዳይሰጥ አደረገ (ሆሴዕ 8፡7-10)። ቍሳዊ ብልጽግናቸውን (ሆሴዕ 9፡1-4) እና ፍሬያማነታቸውን (ሆሴዕ 9፡10-17)፣ የአምልኮ ስፍራዎችንና ጣዖቶቻቸውን (ሆሴዕ 10፡ 1-6)፥ የጦር ኃይላቸውን (ሆሴዕ 10፡9-15) ሁሉ አጠፉ። እግዚአብሔር ሐሰተኞች አማልክት ክብሩን እንዲሰርቁ አይፈቅድም። ባዶና የማይጠቅሙ መሆናቸውን እንዲያውቁ እነዚህ የሐሰት ሃይማኖቶችና አማልክት እንሰጣለን የሚሉትን ተስፋዎች ሁሉ ይወስዳል።

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ሁሉ፥ ሃይማኖትን የመቀያየጥ ተመሳሳይ ዝንባሌ እንመለከታለን። ብዙ ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን፥ ቍሳዊ ሀብትና ንብረታቸውን በአንድነት ለማምለክ ሲሞክሩ እንመለከታለን። ይህ መንፈሳዊ ምንዝርና ነው (ያዕቆብ 4፡4)። ክርስቲያኖች ነን የሚሉ ሌሉች ደግሞ ወደ አስማተኞች፥ ጠንቋዮች፥ ቃልቻዎች፥ ኮከብ ቈጣሪዎችና ወደ አባቶቻቸው ውቃቢ ወዘተ. ይሄዳሉ። የእግዚአብሔርን አምልኮ ከባህላዊ አምልኮ ጋር ይደባልቃሉ። ይህም ሰይጣንን እንደማምለክ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በአሁኑ ጊዜ በርካታ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን አምልኮ ከሌሎች አምልኮ ጋር እንዴት እንደሚቀይጡ የሚያሳዩ ምሳሌዎችን ስጥ። ለ) የቤተ ክርስቲያንህ አባሎች ንጹሕ አምልኮ የሚያቀርቡ እንጂ መንፈሳዊ አመንዝራዎች አለመሆናቸውን ለማረጋገጥ ምን ማድረግ ትችላለህ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: