ጌታን ከተቀበልኩ በኋላ ኃጢአት ሰርቼ ንስሃ ሳልገባ ብሞት ወዴት ነው የምሄደው?

ኃጢአት ከሠራሁ በኋላ ለመናዘዝ እድሉ ሳይኖረኝ ብሞት ምን እሆናለው የሚለው ጥያቄ የበርካታ ክርስቲያኖች ስጋት አዘል ጥያቄ ነው፡፡ ይህ ስጋት የድነታችንን መሠረት ጠንቅቆ ካለመረዳት የሚመነጭ ነው፡፡ ድነታችን የተመሠረተው በየዕለቱ የምንፈጽማቸውን ሃጢአቶች በሞላ ያለማቋረጥ በመናዘዛችን እና ንስሃ በመግባታችን ላይ ከሆነ በእርግጥም ስጋቱ ተገቢ ይሆን ነበር፡፡ ሆኖም ግን የድነታችን መሠርት የቆመው በዘላለም መንፈስ አንድ ጊዜ በቀረበው የክርስቶስ የቤዛነት ሥራ ላይ በመሆኑ እና ይህም መስዋዕት ያለፈውን፣ የአሁኑን፣ እና የወደፊቱን፣ “ትልቁን” ወይም “ትንሹን” ኃጢአታችንን ሁሉ ያስወገደ በመሆኑ ላይ ስለሆነ ሥጋቱን መሠረት ቢስ ያደርገዋል (ቆላስይስ 1:14 ፣ ሐዋ 10:43፣ 1ጴጥ 3:18)፡፡ እምነታችን ከዚህ መሠረት እስካልተናወጠ ድረስ ድነታችን የተረጋገጠ ነው፡፡    

ድነታችን በእግዚአብሔር መንፈስ ዳግመኛ ከመወለዳችን ጋር የተገናኘ ነው (ዮሐ 3:1-6)፤ ድነታችን የእግዚአብሔር ልጅ ከመሆን ጋር የተገናኘ ነው (ኤፌ 1፡5፣ 1ዮሐ 3፡2)፤ ድነታችን አዲስ ፍጥርት ከመሆን ጋር የተገናኘ ነው (2ቆሮ 5፡7)፤ ድነታችን በእግዚአብሔር ፊት ያለነውር (ያለሃጢአት) ከመታየት ጋር የተገናኘ ነው (ሮሜ 8፡1፣ 2ቆሮ 5፡21)፡፡ መዳናችን የእግዚአብሔር ቤተሰብ (relationship) የመሆናችን ጉዳይ እንጂ የዚህ ቤተሰብ አባል ከሆንን በኋላ ያለው አኗኗራችን ወይም ሕብረታችን (fellowship) ጉዳይ አይደለም (ኤፌ 2፡19)፡፡ አንድ ልጅ አባቱን በመታዘዝ የሚያስደስትበት ጊዜ እንዳለው ሁሉ ባለመታዘዝ የሚያሳዝንበትም ጊዜ ይኖራል፡፡ በሚታዘዝበት ጊዜ በመወለድ ካገኘው የልጅነት ማዕረግ በላይ ከፍ እንደማይል ሁሉ በማይታዘዝበት ጊዜም ከልጅነት ማዕረጉ አይጎድልም፡፡ አባቱን ይቅርታ ሲጠይቅ መልሶ የሚያገኘው ያጣውን ጤናማ ሕብረት እንጂ ልጅነቱን አይደለም፡፡ ለይቅርታ ቢዘገይ ደግሞ፣ የሚያጎድለው ይህን ሕብረት እንጂ ልጅ መሆኑን አይደለም፡፡ የእግዚአብሔርን ስጦታ በእምነት በመቀበል የእግዚአብሔር ልጆች ከሆን በኋላ (ዮሐ 1፡12) በምንሰራው ሃጢአት የምናጎድለው ነገር ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ጤናማ ሕብረት (1ዮሐ 1:5-10) እንጂ ዘላለማዊ አድራሻችንን አይደለም፡፡  

ክርስቶስን እንደ አዳኝ በተቀበልንበት ቅጽበት ሁሉም ኃጢአታችን ይቅር ከተባል፣ ታዲያ ለምን ደጋግመን ንስሃ እንገባለን? በየዕለቱ የምንሰራቸው ሃጢአቶች ከተቀበልነው ድነታችን ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው ማወቃችን ንስሃ መግባትን  አላስፈላጊ አያደርገውም ወይ? ለሚሉት ጥያቄዎች በቂ ምላሽ የሚሰጠን በድነታችን ወቅት የተፈጽሙትን ተግባራት በአግባቡ በመረዳት ነው፡፡ አንድ ጊዜ ባደረግነው የእምነት ውሳኔ የእግዚአብሔር ቤተሰብ መሆናችን የተጠበቀ ቢሆንም፣ በየእለቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የሚኖረን ሕብረት ባልተናዘዝነው ሃጢአት ምክንያት ሊታወክ ይችላል (1ዮሐ 1:5-10፣ ኤፌ 4፡30)፡፡ ይህ ያልተናዘዝነው ሃጢአት የሚያውከው ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ሕብረት እንጂ ቤተሰብነታችንን አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር ቤተሰብ ለመሆን (ለመዳን) በየዕለቱ ሃጢአታችንን መናዘዝ አያስፈልገንም፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን እና ሊቋረጥ የማይገባውን ሕብረት ጤናማነት ለማስቀጠል ግን መነፈስ ቅዱስ በወቀሰን ጊዜ ሁሉ ሃጢአታችንን መናዘዝ የግድ ነው (1ዮሐ 1፡9)፡፡ “መናዘዝ” የሚለው ቃል ትርጉም “መስማማት” ማለት ነው፡፡ ኃጢአታችንን ለእግዚአብሄር ስንናገር የተሳሳትን እንደሆንን፣ እንደበደለን አምነን ከእግዚአብሔር ጋር እየተስማማን ነው፡፡ እግዚአብሔር “ታማኝ እና ጻድቅ” በመሆኑ ሃጢአታችንን ይቅር በማለት ከእርሱ ጋር ወዳለን ሕብረት ይመልሰናል። 

ይህን ጉዳይ ይበልጥ ለማብራራት ሁለት ሥነ-መኮታዊ ቃሎችን መጠቀም አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለው፡፡ እነዚህ ቃላት አቋማዊ ቅድስ (possitional sanctification) እና ቀጣይነት ያለው ቅድስና (progressive sanctification) የሚባሉ ናቸው፡፡ ድነት የአቋማዊ ቅድስና ጉዳይ እንጂ ቀጣይነት ያለው ቅድስና ጉዳይ አይደለም፡፡ አቋማዊ ቅድስና በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ የቤዛ ሥራ ጻድቃን ተደርገን መቆጠራችንን (2ቆሮ 5፡21፣ 1ቆሮ 6፡12፣ ኤፌ 1፡4) የሚያመለክት ሲሆን ይህ ቅድስናችን በእለት ተዕለት የሕይወት ጉዞአችን በሚገጥመን መውደቅና መነሳት ከፍና ዝቅ የሚል አይደለም፡፡ ቀጣይነት ያለው ቅድስና ደግሞ በአቋማዊ ቅድስናችን ምክንያት በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት ካገኘን በኋላ በቀሪው የሕይወት ዘመናችን በእምነት ለመንፈስ ቅዱስ እየታዘዝን ከምንኖረው ሕይወት ጋር ይያያዛል፡፡ ስለሆነም፣ ድነታችን እውን የሚሆነው በየእለቱ ለምንሰራቸው ሃጢአቶች ንስሃ እየገቡ በመኖር የማያቋርጥ ተግባር ሳይሆን እግዚአብሔር አይናችንን ገልጦ ሃጢአተኛነታችንን ባሳየን ጊዜ አዳኝ እንደሚያስፈልገን በማወቅ በእርሱ የምሕረት ጥላ ሥር ለመሆን ወይም በክርስቶስ የቤዛነት ሥራ ለመደገፍ በምንወስነው ውሳኔ ነው፡፡ ይህ ውሳኔ ሂደት (process) ሳይሆን ቅስበት (evenet) ነው፡፡ በአንድ የሕይወታችን ጊዜ ላይ አይናችን በመንፈስ ቅዱስ በርቶ (ሐዋ 16:14) ተስፋ ቢስ ሃጢአተኞች፣ ጎስቋሎችና ምስኪኖች መሆናችንን ተረድተን የአዳኝ ያለህ የሚለውን የነፍሳችንን ጩኸት የሰማው ጌታ የሰጠን ነጻ ስጦታ ነው (ኤፌ 2:1-10)፡፡    

1 thought on “ጌታን ከተቀበልኩ በኋላ ኃጢአት ሰርቼ ንስሃ ሳልገባ ብሞት ወዴት ነው የምሄደው?”

Leave a Reply

%d