የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከዚህ ቀደም ያጋጠሙህን ጥፋቶች ወይም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ዘርዝር። ለ) ከእነርሱ ምን ተማርህ? ሐ) በኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ በፊት የደረሱትን ጥፋቶች ዘርዝር። መ) ከእነዚህ ጥፋቶች ሰዎች መማር ያለባቸው ትምህርቶች ምንድን ናቸው?
መጽሐፍ ቅዱስ፥ እግዚአብሔር በሕይወታችን የሚደርሱትን ክፉና በጎ ነገሮች ሁሉ እንደሚቆጣጠር ያስተምራል። እንደ ፀሐይና ዝናብ ያሉ በረከቶች የሚመጡት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው (ማቴዎስ 5፡44-45)። ደግሞም እግዚአብሔር ወደ ሕይወታችን የሚመጡትን አደጋዎች ሁሉ ይቆጣጠራል (ኢሳያይስ 45፡5-8 ተመልከት)። እኛ ወይም ከቤተሰቦቻችን አንዱ ሲታመም የምንወዳቸው በሞት ሲለዩን በአገራችን ድርቅ ሲኖር፥ እነዚህ ሁሉ እግዚአብሔር ለእኛ ካለው ፍቅር የተነሣ ሊመጡ ይችላሉ።
እግዚአብሔር አደጋዎችን በተለያዩ መንገዶች በመጠቀም በሕይወታችን ምሕረቱን ያሳየናል። አደጋ እግዚአብሔር በኃጢአት ላይ እንደሚፈርድ በማሳየት የከፋ ፍርድ ከመምጣቱ በፊት ወደ እርሱ በንስሐ እንድንመለስ የሚጋብዝ ሊሆን ይችላል። ብዙ ጊዜ ሰዎች ራሳቸውን እንዲመረምሩና ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ይሄዱ እንደሆነ በማረጋገጥ ወደ ንስሐ እንዲመጡ ለማድረግ የሚያስጠነቅቅ ነው። አንዳንድ ጊዜ አደጋ እግዚአብሔር በእምነታችን ሊያጠነክረን ማለትም ጽናትን፥ ራስ መግዛትንና ሌሎችንም ጠቃሚ የሕይወት ብቃቶች መፈለጉን የሚያሳይ ምልክት ሊሆን ይችላል (ያዕቆብ 1፡2-4)።
በኢዩኤል ዘመን እግዚአብሔር ታላቅ የአንበጣ መንጋ መቅሠፍት በእስራኤል ላይ አፈሰሰ። የምድሪቱ ሰብል ጠፋ። እንስሳት የሚግጡትን ሣር አጡ። ኢዩኤል ይህ የእግዚአብሔር ፍርድ መሆኑን ያውቅ ነበር። ስለዚህ የእግዚአብሔር ሕዝብ በንስሐ በመመለስ፥ በመታዘዝና በመቀደስ እንዲኖሩ ይለምናል።
ችግሮችና አደጋዎች በሕይወታችን በሚከሰቱበት ጊዜ የእግዚአብሔር ዓላማ ምን እንደሆነ ለመረዳት ትልቅ ጥበብና የመንፈስ ቅዱስ ምሪት ያስፈልገናል። ይህ የሚሆነው ለግል መንፈሳዊ ዕድገት ኃጢአትን ለመቅጣት ይሁን ወይም በእግዚአብሔር ላይ እንድንደገፍ ሊያስታውሰን በመፈለጉ፥ የምናውቀው እኛ ብቻ ነን። ሌሎች ሰዎች መከራን የሚቀበሉት ለምን እንደሆነ ከመፍረድ መጠንቀቅ አለብን። የእግዚአብሔር ዓላማ የተለያየ ስለሆነ፥ በሌሎች ላይ የምንፈርድ ወይም የመንፈስ ቅዱስን የመውቀስ ሥራ የምንሻማ መሆን የለብንም።
ትንቢተ ኢዩኤል ለይሁዳ ከተጻፉ ሦስት አነስተኛ የነቢያት መጻሕፍት አንዱ ነው። ሚክያስና ሶፎንያስ ሁለቱም ለይሁዳ ሕዝብ የተጻፉ ነበሩ።
የትንቢተ ኢዩኤል ጸሐፊ
በኢዩኡል 1፡1፥ «ወደ ባቱኤል ልጅ ወደ ኢዩኡል የመጣው ቃል ይህ ነው» ተብሉ በተገለጸው ቃል መሠረት ጸሐፊው ኢዩኤል እንደሆነ ይገመታል።
ከዚህ ሌላ ስለ ኢዩኤል ማወቅ አስቸጋሪ ነው። ኢዩኤል በብሉይ ኪዳን ውስጥ የተለመደ ስም ነበር። ቢሆንም በሌሎች ስፍራዎች የምናገኘው ይህ ስም የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ አይመስልም። ኢዩኤል የትና መቼ እንደተወለደና እንደኖረ አናውቅም። አብዛኞቹ ሊቃውንት ኢዩኤል በተደጋጋሚ የሚጠቅሰው ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ስለሆጎ (ኢዩኡል 2፡32፤ 3፡1፥6፥8) ከደቡብ፥ መንግሥት ከይሁዳ ነገድ ሳይሆን እንደማይቀር ይናገራሉ።
ትንቢተ ኢዩኤል ከሌሎች የትንቢት መጻሕፍት በተለየ ሁኔታ ኢዩኤል ማገልገሉን አይገልጽም። የይሁዳም ሆነ የእስራኤል ንጉሥ አልተጠቀሱም። የተጠቀሱት ነገሥታት ሳይሆኑ ካህናት ብቻ ነበሩ። ስለዚህ መጽሐፉ የተጻፈው ብቁ የሆነ ንጉሥ ባልነበረበት ጊዜ ይመስላል። ትንቢተ ኢዩኤል መቼ እንደተጻፈ በርግጠኝነት ለመናገር የሚቻልበት መንገድ ጨርሶ የለም። ትንቢተ ኢዩኤል ስለተጻፈበት ጊዜ ምሁራን ሁለት አሳብ አላቸው፡-
1. ትንቢተ ኢዩኤል የተጻፈው ከ 835-830 ዓ.ዓ. ባለው ጊዜ ነበር። በዚህ ጊዜ የዳዊት ንጉሣዊ የዘር ግንድ በክፉዋ ንግሥት በጎቶልያ አማካይነት ጨርሶ ሊጠፋ ደርሶ ነበር። ኢዮአስ ብቻ ተርፎ ነበር። ኢዮአስ የሰባት ዓመት ልጅ በሆነ ጊዜ በዙፋን ላይ ተቀመጠ። ኢዮአስ ንጉሥ ቢሆንም እንኳ ራሱን ችሎ እስኪያስተዳድር ድረስ አገሪቱ በካህናት ትመራ ነበር። እነዚህ ምሁራን ትንቢተ ኢዩኤል የተጻፈው በዚህ ጊዜ ነው ብለው የሚያምኑባቸው ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፡-
ሀ. አይሁድ ትንቢተ ኢዩኤልን ከታናናሽ ነቢያት መጻሕፍት መጀመሪያ አካባቢ ማድረጋቸው ልክ እንደ ትንቢተ ሆሴዕ ከምርኮ በፊት አንደተጻፈ ያምኑ እንደነበር የሚያሳይ ነው።
ለ. የአሦር ወይም የባቢሎን ስም አለመጠቀሱ፥ ታሪኩ ከእነዚህ ሁለት ታላላቅ መንግሥታት በፊት መፈጸሙን የሚያሳይ ነው።
ሐ. ኢዩኤል «የጌታ ቀን» የሚለውን ሐረግ የሚጠቀመው ከምርኮ በፊት ከተጻፉ መጻሐፍት ጋር በሚመሳሰል መንገድ ነው። ይህ አመላካከት እውነት ከሆነ፥ ትንቢተ ኢዩኤል ከመጽሐፍ ቅዱስ የትንቢት መጻሕፍት ሁሉ ቀዳሚ ይሆናል።
2. ሌሎች ምሁራን ደግሞ ትንቢተ ኢዩኤል የተጻፈው አይሁድ ተማርከው ከሄዱና ምርኮው ተፈጽሞ ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ነው ብለው ያምናሉ። ከትንቢተ ሐጌና ዘካርያስ በኋላ ቢሆንም፥ ነገር ግን ከትንቢተ ሚልክያስ በፊት ተጽፏል የሚል አስተሳሰብ አላቸው። ትንቢተ ኢዩኤል የተጻፈበት ጊዜ ከ525-475 ዓ.ዓ. ነው ብለው ይገምታሉ። ይህም በጊዜ ቅደም ተከተል፥ ትንቢተ ኢዩኤልን ከብሉይ ኪዳን የትንቢት መጻሕፍት መካከል ከመጨረሻው መጽሐፍ ብቻ ቀዳሚ ያደርገዋል። ትንቢተ ኢዩኤል በዚህ ጊዜ እንደተጻፈ የሚያምኑ ምሁራን የሚከተሉትን ምክንያቶች ያቀርባሉ፡-
ሀ. በትንቢተ ኢዩኤል 3፡1-2 የተጠቀሰው አሳብ፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ መበተን ያለፈ ጉዳይ እንጂ ገና የሚመጣ መሆኑን የሚያመለክት አይመስልም።
ለ. ከምርኮ በፊት እጅግ ተደጋግሞ ይታይ የነበረው፥ ከምርኮ በኋላ ግን ያልተከሰተው የጣዖት አምልኮ ኃጢአት አልተጠቀሰም።
ሐ. ከምርኮ በፊት በመካከለኛው ምሥራቅ ጨርሶ የማይታወቁ የነበሩት ግሪኮች ተጠቅሰዋል።
መ. የኢዩኤል አጻጻፍ ስልት ከኢየሩሳሌም ውድቀት በኋላ የተጻፉትን የታናናሽ ነቢያት መጻሕፍት እንጂ፥ የመጀመሪያዎቹን የነቢያት መጻሕፍት አይመስልም።
ሁለቱም አመለካከቶች የየራሳቸው የሆኑ ጠንካራ ጎኖች አሏቸው። እርግጥ ኢዩኤል ቀደም ሲል እንደተጻፈ የሚናገረው አመለካከት የተሻለ ቢመስልም፥ መቼ እንደተጻፈ አናውቅም ማለቱ ግን ከሁሉም የሚሻል ነው። ትንቢተ ኢዩኤል መቼ እንደተጻፈ አለማወቃችን ስለ መጽሐፉ የሚኖረንን ግንዛቤ ብዙ አይለውጠውም።
ታሪካዊ ሥረ መሠረት
ትንቢተ ኢዩኤል የተጻፈበትን ጊዜ ስለማናውቅ ስለ መጽሐፉ ታሪካዊ ሥረ-መሠረት እርግጠኞች ለመሆን አንችልም። ስለዚህ መጽሐፉን በሚገባ ለመረዳት ሁለቱን የታሪክ ቅደም ተከተሎች መገንዘብ ጠቃሚ ነው።
1. የኢዮአስ ዘመነ መንግሥት (835-796 ዓ.ዓ.)
የውይይት ጥያቄ፥ የዚህን ጊዜ ታሪክ ለመረዳት 2ኛ ነገሥት 11 አንብብ። ሀ) የዳዊት የዘር ግንድ ምን ሊሆን ተቃርቦ ነበር? ለ) ንጉሥ ኢዮአስን ያሳደገው ማን ነው? ሐ) ንግሥት ጎቶልያ ምን ዓይነት ሴት ነበረች?
ንጉሥ ኢዮራም ሲሞት ልጁ አካዝያስ ነገሠ። ይህ ሰው በእስራኤል ንጉሥ በኢዩ ከመገደሉ በፊት በሥልጣን ላይ የቆየው ለአንድ ዓመት ብቻ ነበር። ይህንን ሥልጣን ለመጨበጥ የደረሰ ሌላ ልጅ ስላልነበረ የኢዮራም ሚስት ጎቶልያ ዙፋኑን ያዘች። ዙፋኑን የሚወርስ ሌላ ሰው እንዳይኖር ወዲያውኑ የዳዊትን ዝርያዎች በሙሉ ለመግደል ሞከረች። ካህናቱ ኢዮአስ የተባለውን ሕፃን ብቻ አድነው ሰባት ዓመት እስኪሞላው ድረስ በቤተ መቅደስ ውስጥ ደብቀው አሳደጉት። ከዚህ በኋላ በሊቀ ካህኑ በዮዳሄ መሪነት ንግሥት ጎቶልያን ከሥልጣንዋ የማስወገድ ተግባር ተከናወነ። ዮዳሄ በሕይወት እስካለ ድረስ የይሁዳ ዋና የፖለቲካ መሪ ሆኖ አገለገለ። ዮዳሄ በኢዮአስ በመጠቀም መንፈሳዊ መነቃቃት ለማምጣት ቻለ። ዮዳሄ እንደሞተ ግን ኢዮአስ ከጌታ ፊቱን መለሰ።
ዮዳሄ ከዙፋኑ በስተኋላ የነበረውን ሥልጣን በሚገባ የተጠቀመበት በንግሥት ጎቶልያ ሞትና በንጉሥ ኢዮአስ መንገሥ መካከል በነበረው ጊዜ ነበር። እግዚአብሔር ነቢዩ ኢዩኤልን በማስነሣት ቃሉን እንዲናገር ያደረገውም በዚህ ጊዜ ነበር። ኢዩኤል ምድሪቱን የመታትን የአንበጣ መቅሠፍት በምሳሌነት በመጠቀም፥ እንደ አንበጣ ምድሪቱን የሚያጠፋ በሰዎች የተገነባ ሌላ የጦር ኃይል እንደሚመጣ ተናገረ።
2. ከምርኮው በኋላ የነበሩት ጊዜያት (500 ዓ.ዓ. ገደማ)
የውይይት ጥያቄ፥ ስለ መጽሐፈ ዕዝራ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። በዕዝራ ዘመን የፖለቲካ ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?
መጽሐፉ የተጻፈው ዕዝራ በነበረበት ዘመን ገደማ ከሆነ የፖለቲካ ሁኔታው የተለየ ነበር ማለት ነው። በይሁዳ ከነበሩት ምርኮኞች አብዛኛዎቹ ወደ ይሁዳ ለመመለስ ሳይሆን በባቢሎን ለመቆየት የመረጡ ቢሆኑም፥ በዘሩባቤል፥ በዕዝራና በነህምያ መሪነት አንዳንድ አይሁዳውያን ተመልሰዋል። በላያቸው የነገሠ ንጉሥ አልነበረም። ይልቁንም በሜዶንና በፋርስ መንግሥት ቁጥጥር ሥር ስለነበሩ በሕዝቡ ላይ የተሾሙ ገዥዎች ነበሩ። እንደ እውነቱ ከሆነ ሕዝቡን የሚመሩት እንደ ዕዝራ ያሉ ካህናት ነበሩ። እነዚህ ካህናት መንፈሳዊ አመራር መስጠት ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ መሪዎችም ሆኑ። ይህም የካህናቱን ሕይወት በማበላሸቱ፥ ከአመራር ስለሚያገኙት ሥጋዊ ጥቅም እንጂ፥ ስለ ሕዝቡ መንፈሳዊ ሕይወት የማይገዳቸው ሆኑ። ሕዝቡ በቃላቸው እግዚአብሔርን እንከተላለን እያሉ ቢናገሩም፥ የቅድስና ሕይወት የማይኖሩና የእግዚአብሔርን ሕግጋት በመታዘዝ የማይራመዱ ነበሩ። ኢዩኤል ነቢይ የነበረው በዚህ ዘመን ከሆነ፥ የተጠራው ወደ ምድራቸው የተመለሱት አይሁድ እግዚአብሔርን እንዳይተው፥ ነገር ግን ወደ እርሱ እንዲመለሱ የማስጠንቀቂያ መልእክት ለማድረስ ነበር። ኢዩኤል ወደፊት ሊያጠፋቸው ስለሚመጣ ጦር በመናገር አስጠነቀቃቸው።
ከእነዚህ ሁለት የፖለቲካ ዘመናት የትኛውም ቢሆን ለትንቢተ ኢዩኤል ሥረመሠረት ሊሆን ቢችልም፥ የምናውቀው ዐቢይ ነገር ቢኖር የይሁዳን ሕዝብ ከፍተኛ የአንበጣ መቅሠፍት ገጥሞአቸው እንደነበረ ነው። ከይሁዳ ሕዝብ አብዛኛዎቹ ገበሬዎች ነበሩ። እንደ ስንዴ ያሉ ሰብሎችን ይዘሩ ነበር። የወይን አትክልት ስፍራዎች፥ ከብቶችና በጎችም ነበሯቸው። አንበጦቹ ሰብሉን ሁሉ በማጥፋት በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ ጥፋት እንዲደርስ አደረጉ። የሕዝቡ ኢኮኖሚ ቢያንስ ለሁለት ዓመት አደጋ ላይ ወድቆ ሕዝቡ ለከፍተኛ ችግር ተዳረገ።
ኢዩኤል የአንበጣ መንጋ ያስከተለውን ጥፋት ወደፊት ሊመጣ ስላለው ታላቅ ጥፋት ለሕዝቡ ለማመልከት ተጠቀመበት። ይህ መቅሠፍት አይሁድ ከኃጢአታቸው ንስሐ ገብተው ካልተመለሱ ሌላ ከፍተኛ ፍርድ እንደሚጠብቃቸው ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ ማስጠንቀቂያ መሆኑን ተገነዘበ።
የትንቢተ ኢዩኤል አስተዋጽኦ
1. ኢዩኤል የጌታን ቀን ምንነት በአንበጣ መንጋ መቅሠፍት አወቀ (ኢዩኤል 1)።
2. ኢዩኤል የጌታን ቀን መምጣት ተነበየ (ኢዩኤል 2-3)፡-
ሀ. ሊመጣ ያለው የይሁዳ ምድር መወረር (ኢዩኤል 2፡1-11)፣
ለ. የንስሐ ጥሪ(ኢዩኤል 2፡12-17)፣
ሐ. የእስራኤል መመለስና የአይሁድ መታደስ (ኢዩኤል 2፡18-32)፥
መ. በአሕዛብ ላይ የሚመጣ ፍርድ (ኢዩኤል 3፡1-16)።
ሠ. ለእግዚአብሔር ሕዝብ የሚሆኑ በረከቶች (ኢዩኤል 3፡17-21)።
የውይይት ጥያቄ፥ ስለ ኢዩኤል ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። ስለ መጽሐፉ የሚናገሩትን ዋና ዋና መሠረታዊ እውነቶችን ዘርዝር።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)
የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡