በትንቢተ ዮናስ ውስጥ ዐበይት መንፈሳዊ ትምህርቶች

ትንቢተ ዮናስ እጅግ ጠቃሚ በሆኑ መንፈሳዊ እውነቶችና ከሕይወታችን ጋር ሊዛመዱ በሚችሉ ቁም ነገሮች የተሞላ ነው። ከዚህ መጽሐፍ ልንማራቸው ከምንችል ትምህርቶች አንዳንዶቹ ቀጥሉ ተዘርዝረዋል፡-

1. የእግዚአብሔር ባሕርይ

ሀ. እግዚአብሔር ፈቃዱን ለመፈጻም ነገሮችን ሁሉ የሚቆጣጠርበትን ኃይል እንመለከታለን። እግዚአብሔር ማዕበሉን፥ ዓሣ ነባሪውን፥ ትሉን ሳይቀር ሲቆጣጠር እንመለከታለን። ሁሉም እርሱ የሚፈልገውን ነገር አድርገዋል።

ለ. የእግዚአብሔርን ታላቅ ርኅራኄ መመልከት እንችላለን። እግዚአብሔር የነዌ ሰዎች እንዲሞቱ አልፈለገም ነበር። ዳሩ ግን ንስሐ የሚገቡበትን ዕድል እንዲያገኙ ፈለገ። እግዚአብሔር የነነዌ ሰዎች ባሳዩት አነስተኛ የንስሐ ምልክት በእነርሱ ላይ ተዘርግቶ የነበረውን የፍርድ እጁን አነሣ። 

ሐ. ጽድቅ የሆነውን የእግዚአብሔር ቁጣ እንመለከታለን። እግዚአብሔር ክፋትን ስለሚጠላ ኃጢአትን ይቀጣል። እግዚአብሔር ለቁጣ የዘገየ ነው (ዮናስ 4፡2)። እግዚአብሔር መራራቱን የሚተውበትንና የሚፈርድበትን ጊዜ ይወስናል።

መ. ትንቢተ ዮናስ መሠረታዊ የሥነ-መለኮት ጥያቄ ያነሣል። «እግዚአብሔር ክፉዎችንና ኃጢአተኞችን የማይቀጣው ለምንድን ነው?» (ዮናስ 4፡4፥9)። ብዙ ጊዜ ከፉና ኃጢአተኛ የሚበለጽግ፥ ጻድቅ ደግሞ መከራን የሚቀበል ይመስላል። ክርስቲያኖች ዘወትር የሚፈልጉት እግዚአብሔር ክፉና ኃጢአተኛ የሆ፥ ጠላቶቻቸውን ፈጥኖ እንዲቀጣላቸው ነው። እግዚአብሔር እነርሱ በሚፈልጉት ፍጥነት ይህን ሳያደርግ ሲቀር ግራ ይጋባሉ። ትንቢተ ዮናስ እግዚአብሔር ይቅር ለማለት ወይም ለመቅጣት መብት እንዳለው ይናገራል። እግዚአብሔር ክፉዎችና ኃጢአተኞች የሆኑትን ሰዎች ፈጥኖ ለመቅጣት ወይም የፍርድ እጆቹን ሳይሰነዝር ለዘላለም ለመቆየት አይገደድም። መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ኃጢአተኞችንና ክፉዎችን እንደሚቀጣ ያስተምረናል። ፍርዱ በኃጢአት ላይ ይፈጸማል (ኤርምያስ 13፡14)። ዳሩ ግን መቼ መፈጸም እንዳለበት የመወሰን መብት ያለው እግዚአብሔር ራሱ ነው፤ በዚህ ሕይወት ወይም በዘላለማዊነት ሊሆን ይችላል።

2. የእግዚአብሔር ሕዝብ ባሕርይ 

ዮናስ የእግዚአብሔር ሕዝብ ምሳሌ ነው። እኛ ብዙውን ጊዜ ልክ እንደ ዮናስ ነን።

ሀ. የተረጋገጠ ማስረጃ ሳይኖረን እንደ ዮናስ በሌሉች ላይ መጥፎ አስተያየት የምንሰነዝር ሰዎች ነን። ከሌሎች ነገዶች የሆኑ ሰዎችን በመጥላት ወንጌል እንዲደርሳቸው ባለመፈለግ የዘር መድልዎ የምናሳይ ሰዎች ነን። ከዳኑ በኋላም ቢሆን በየቤተ ክርቲያኖቻችን ሙሉ በሙሉ አንቀበላቸውም። ከእነርሱ ጋር ጋብቻ አንመሠርትም። በኢኮኖሚ ዓቅማቸው ከእኛ ጋር የማይመጣጠኑትን ሰዎች አድልዎ በማድረግ እናገላቸዋለን። ሀብታሞች ከሆንን ከሀብታሞች ጋር ብቻ ኅብረት በማድረግ ድሆችን እንንቃለን። ድሆች ከሆንን ደግሞ፥ ከድሆች ጋር ብቻ ኅብረት በማድረግ ከሀብታሞቹ ይልቅ መንፈሳዊ የሆንንን ይመስለናል። ወንዶች ከሴቶች ይልቅ የተሻሉ እንደሆኑና በእግዚአብሔር ዘንድ ተፈላጊነት እንዳላቸው የሚያስቡበት የጾታ ልዩነትም አለ። እግዚአብሔር እነዚህን ሁሉ ይጠላል። እነዚህ ሁሉ መንፈሳዊ ብስለት የሌለንና ከእግዚአብሔር የራቅን መሆናችንን የሚያሳዩ ምልክቶች ናቸው። አዲስ ኪዳን የመለያየትና የአድልዎ ግድግዳዎች ሁሉ በክርስቶስ አካል የፈራረሱ መሆናቸውን ያስተምረናል (ገላትያ 3፡28፤ ቈላስይስ 3፡11 ተመልከት)።

ለ. የእግዚአብሔር ሕዝብ እርሱ ለሕይወታቸው ካለው ዓላማና ፈቃድ ብዙ ጊዜ ይሸሻሉ። የእግዚአብሔር ፈቃድ ከባድ ወይም የማይወዱት እንደሆነ ያስባሉ። ስለዚህ በራሳቸው ውሳኔ በመሸሽ ሌላ ነገር ያደርጋሉ። በዚህም ማድረግ የሚችሉት ከሁሉ የላቀ ነገር እንደሚያመልጣቸው አይገነዘቡም። እውነተኛ ደስታ ለማግኘት የምንችለው እግዚአብሔር የሚፈልገውን ነገር ስናደርግ ብቻ ነው። ከእግዚአብሔር መሸሽ አደገኛ ነው። ጉዳቱ ለእኛ ብቻ አይደለም፤ በሌሎች ሰዎች ሕይወት ላይም አደጋ ሊያመጣ ይችላል። ምንም በማያውቁ የመርከብ ላይ መንገደኞች፥ በሚስቶቻችን፥ በልጆቻችን፥ ወዘተ. ሠራተኞች አደጋ ሊያስከትል ይችላል። 

ሐ. የእግዚአብሔር ሕዝብ ብዙውን ጊዜ ለሌሎች ወንጌልን የማዳረስ አስፈላጊነት ዘንግተው በራሳቸው ጉዳዮች ላይ ብቻ ያተኩራሉ። ብዙ ክርስቲያኖች የሚጐዳኙትና አብረው የሚውሉት ከክርስቲያኖች ጋር ብቻ ነው። የዓለም ብርሃን ይሆኑ ዘንድ እግዚአብሔር እንደጠራቸው ይዘነጋሉ። ዮናስ ከሕዝቡ ይልቅ ለቅሏ እንዳዘነ፥ እኛም በየቀኑ ያለ ክርስቶስ እየሞቱ ወደ ገሃነም ከሚሄዱት ከብዙ ሺህ ሰዎች ይልቅ፥ ለሥልጣናችን ወይም ለቁሳዊ ሀብታችንና ለምቾት ኑሮአችን ልንጨነቅ እንችላለን። 

3. እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ያለው ግንኙነት

ትንቢተ ዮናስ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ስላለው ግንኙነት በርካታ ትምህርቶችን ይሰጠናል።

ሀ. እግዚአብሔር ሕዝቡን ወደ ፈቃዱ ለመመለስ በትጋት ሲሠራ እንመለከታለን። 

ለ. የቀድሞ ስሕተቶቻቸውን እየረሳ ሰዎችን እንደገና ለመጠቀም የሚያስችለውን የእግዚአብሔር ጸጋ እናያለን። 

ሐ. እግዚአብሔር በፈቃዱ ውስጥ ባይሆኑም እንኳ በከፍተኛ ደረጃ በሰዎች ለመጠቀም ያለውን ችሎታ እንመለከታለን። ዮናስ ከእግዚአብሔር ሸሽቶ በመሄድ ላይ ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ለመርከበኞቹም ኃይሉን ለማሳየት ተጠቀመበት። ዮናስ በእግዚአብሔር ላይ ተቆጥቶ ነበር፤ እግዚአብሔር ግን አንዲት ትልቅ ከተማን ለማዳን ተጠቀመበት።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እነዚህን እውነቶች በራስህ ሕይወት ወይም በሌሎች ሕይወት ያየህባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ለ) እነዚህ እውነቶች ለክርስቲያኖች የሚያስፈልጓቸው ለምንድን ነው?

በአዲስ ኪዳን ውስጥ የዮናስ ታሪክ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ሆኖ እናያለን። ዮናስ ለነነዌ ሰዎች ምልክት እንደነበር፥ ኢየሱስም ለአይሁድ ምልክት ነበር (ሉቃስ 11፡30)። ዮናስ በዓሣ ነባሪ ሆድ ውስጥ ለሦስት ቀንና ሌሊት እንደነበር፥ ኢየሱስም በመቃብር ውስጥ ለሦስት ቀንና ሌሊት ነበር (ማቴዎስ 12፡39-41)። ኢየሱስ «የዮናስ ምልክት» በማለት በማቴዎስ 16፡4 የተናገረው፥ ልክ ዮናስ በዓሣ ነባሪው ሆድ ውስጥ ከነበረበት ተምሳሌታዊ ሞት እንደተነሣ ክርስቶስም መነሣቱን የሚያሳይ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ዮናስ 1-4 አንብብ። ሀ) ዮናስ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ግንኙነት ግለጽ። ለ) እግዚአብሔር ካልዳኑ ሰዎች ጋር ያለውን ግንኙነት ግለጽ።

ዮናስ በእስራኤል ሕዝብ መካከል የሚኖር የእግዚአብሔር ነቢይ ነበር። ምናልባት እግዚአብሔር በኃይል ተጠቅሞበት ይሆናል። ነገር ግን እግዚአብሔር ለዮናስ ሌሎች ዕቅዶች ነበሩት። የአሦር ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ነነዌ እንዲሄድ ፈልጎ ነበር። እግዚአብሔር በዮናስ በኩል ለነነዌ ያስተላለፈው መልእክት የፍርድ መልእክት ነበር። ምናልባት ዮናስ ለባዕዳን እጅግ ጨካኞች የነበሩትን አሦራውያንን ፈርቶ ይሆናል። ነገር ግን የፈራው ሌላው ነገር ወደ አሦር ከሄደና ከሰበከላቸው፥ ንስሐ ይገቡና እግዚአብሔር ይቅር ይላቸዋል የሚለውን አሳብ ይመስላል። ዮናስ አሦራውያን በንስሐ ተመልሰው እንዲኖሩ ሳይሆን፥ እንዲጠፉ ፈልጎ ነበር።

አሦር የምትገኘው ከእስራኤል በስተሰሜን ምሥራቅ 1200 ኬሎ ሜትሮች ያህል ርቃ ነበር። ወደዚያ ለመድረስ ብዙ ወራቶችን ይወስድ ነበር። ዮናስ ግን ወደ ምዕራብ ሄደ። በምዕራብ ከሚገኙና ከሚያውቋቸው ከተሞች ራቅ ብላ ወደምትገኘው ወደ ጠርሴስ የሚሄድ መርከብ አገኘ። ጠርሴስ በስፔይን ውስጥ የምትገኝ ሳትሆን አትቀርም። 

ዮናስ ከእግዚአብሔር ሸሽቶ ለማምለጥ የሚችል መስሉት ነበር። እግዚአብሔር ግን ለዮናስ ዓላማ ነበረው። በታላቅ ትዕግሥት ዮናስን ለማስተማርና እንዲታዘዝ ለማድረግ ጣረ። አውሎ ነፋስን፥ ዓሣ ነባሪን፥ ቅልንና ትልን በመጠቀም እግዚአብሔር ዓላማውን ፈጸመ። የእግዚአብሔር ዓላማዎች በአንድ ነገር ብቻ የተወሰኑ አለመሆናቸውን መመልከቱ አስደናቂ ነው። እግዚአብሔር ጉዳይ ያለው ከነነዌ ሰዎች ጋር ብቻ ሳይሆን በመርከቡ ላይ ከተሳፈሩት ሰዎች ጋርም ነበር። እግዚአብሔር ከአሕዛብ ጋር ጉዳይ ያለው ቢሆንም፥ በዚህ አጋጣሚ ዮናስም እንዲያድግ ይፈልግ ነበር።

እግዚአብሔር አውሎ ነፋስን በመጠቀም፥ በመርከቡ ውስጥ የነበሩ ሠራተኞች ዮናስን ወደ ባሕሩ እንዲጥሉት አደረገ። እግዚአብሔር ዓሣ ነባሪን በማዘጋጀት ዮናስን እንዲውጥና መልሶ ወደ ባሕር ዳርቻ እንዲወስደው አደረገ። ዮናስም በዓሳው ሆድ ውስጥ ሆኖ ወደ ነነዌ ተጓዘ። እግዚአብሔር የዮናስን መልእክት ይሰሙ ዘንድ አሦራውያንን አዘጋጅቶ ስለነበር መልእክቱን ሰሙና ፈጥነው ንስሐ ገቡ። ዮናስ አሁንም ቢሆን የሚፈልገው አሦራውያን ሲጠፉ ማየት ነበረና ወደ ተራራማ ስፍራ በመሄድ በከተማይቱ ላይ የሚሆነውን መጠባበቅ ጀመረ። እግዚአብሔር የነነዌን ሰዎች ባለመቅጣቱ እጅግ ተቆጣ። እግዚአብሔር ቅልና ትንሽ ትልን በመጠቀም ሰዎች ከሌሎች ቁሳዊ ነገሮች የላቁና የተሻሉ መሆናቸውንና ከሕዝቡ ሥጋዊ ምቾት ይልቅ የአሕዛብ ንስሐ መግባት እንደሚገደው ለዮናስ አስተማረው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከትንቢተ ዮናስ የተማርሃቸውን አንዳንድ መንፈሳዊ ትምህርቶች ዘርዝር። ለ) እነዚህን ትምህርቶች በቤተ ክርስቲያንህ ለሚገኙ ለሌሉች ሰዎች ለማስተማር ዐቅድ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: