ትንቢተ ናሆም መግቢያ

የእግዚአብሔር ፍትሐዊ ወፍጮ የሚፈጨው በዝግታ ቢሆንም ጥሩ አድርጎ ይፈፃል የሚል አባባል አለ። ይህ ማለት በሰብአአዊ አመለካከት የእግዚአብሔር ፍትሕ በምድር ላይ የሚሠራ አይመስልም ማለት ነው። በሁሉም ስፍራ ጦርነት፥ ድኅነት፣ ፍትሕ-አልበኝነትና ክፋት አለ። ኃጢአተኞች እንዲሳካላቸውና ኑሮ እንዲሰምርላቸው ጉቦን፥ ዛቻንና ሰውን ማሠቃየትን ይጠቀማሉ። ብዙውን ጊዜ የእግዚአብሔርን ሕግጋት በግልጽ ከሚጥሱ ሰዎች ይልቅ ጻድቃን የበለጠ ሥቃይ የሚቀበሉ ይመስላሉ። እንዲህ ባሉ ጊዜያት እግዚአብሔር ቅን ፈራጅ በመሆኑ፥ እያንዳንዱን ሰው ወይም አገር እንደየሥራው ይቀጣዋል ወይም ይሸልመዋል የሚለውን አሳብ የማጣጣል ፈተና ይጋጥመናል። ታዲያ “የእግዚአብሔርን ሕግጋት መከትል ለምን ይጠቅማል?” ሌላው ሰው የእግዚአብሔርን ሕግ ሳይጠብቅ መበልጸጉን ከቀጠለ ለምን እንደ እርሱ አልሆንም? የተሻለ ነገር ለማግኘት ለምን ጉቦ አልሰጥም? በትምህርት ቤት ለምንስ አላጭበረብርም?

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እንደዚህ ለማሰብ እንዴት እንደተፈተንህ ግለጽ። ለ) ብዙ ክርስቲያኖች በማታለል፥ ጉቦን በመቀበል ወይም ሌሎችን የእግዚአብሔር ሕግጋት ባለመጠበቅ እየተመላለሱና በሰይጣን ወጥመድ ውስጥ እየገቡ ያለው እንዴት ነው? ሐ) አማኞች እንደዚህ ለማሰብ በሚፈተኑበት ጊዜ እንዴት ትመክራቸዋለህ? 

ትንቢተ ናሆም እግዚአብሔር ክፋትን ለመቅጣት ቢዘገይም፥ መቅጣቱ ግን እንደማይቀር ያስተምረናል። እርሱ ጻድቅና ቅን ፍርድ የሚያደርግ አምላክ ስለሆነ እኛም ሆንን ሌሎች የሚያደርጓቸው ነገሮች በቸልታ አይታለፉም። ቅጣቱን እኛው ራሳችን እንቀበላለን ወይም እግዚአብሔርን ይቅርታ በመጠየቅ ኢየሱስ ክርስቶስ ቅጣታችንን በመስቀል ላይ እንዲሸከምልን እናደርጋለን።

ትንቢተ ዮናስን ስናጠና፥ እግዚአብሔር ዮናስን የአሦር መንግሥት ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ነነዌ እንደላከውና የምትጠፋ መሆንዋን እንዳመለከተ አይተናል። ዳሩ ግን ሕዝቡ ንስሐ በገቡ ጊዜ እግዚአብሔር ፍርዱን ለሌላ ጊዜ አስተላለፈው። በትንቢተ ዮናስ የተመለከትነው፥ ሕዝቡ በንስሐ ወደ እርሱ በሚመለሱበት ጊዜ እግዚአብሔር ምን ያህል መሐሪ እንደሆነ ነበር፡፡

ትንቢተ ናሆም የተጻፈው ከ100 ዓመታት በኋላ ነው። አሁን ግን የንስሐ ጊዜ አልፎ ነበር። የእግዚአብሔር ትዕግሥትና ቻይነት ወደ ፍጻሜ ደርሶ ነበር። ትንቢተ ናሆም ነነዌ ሙሉ በሙሉ እንደምትጠፋ ይናገራል። ብዙ ሳይቆይ የናሆም ትንቢት በመፈጸሙ፥ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ነነዌ በባቢሎን መንግሥት ተደመሰሰች።

የውይይት ጥያቄ፥- የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከት፡- ማቴዎል 12፡35-37፤ ሮሜ 2:4-11፤ 14፡12። 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡10። ሀ) በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ የሚገኘው ማስጠንቀቂያ ምንድን ነው? ለ) ዓለምን እንመስልና የእግዚአብሔርን ሕግጋት እንጥስ ዘንድ ስንፈተን ይህን እውነት ማስታወስ የሚጠቅመን ለምንድን ነው?

የትንቢተ ናሆም፥ አብድዩና ዮናስ መልእክቶች ተቀዳሚ ትኩረት በአሕዛብ መንግሥታት ላይ ትንቢት መናገር ነበር። ናሆም በአሦር መንግሥት ላይ የተነገረ ትንቢት ነው። 

የትንቢተ ናሆም ጸሐፊ 

ትንቢተ ናሆም የተጻፈው በናሆም ነበር፡፡ እንደ አብዛኛዎቹ የታናናሽ ነቢያት መጻሕፍት ስለ ናሆም ያለን መረጃ ጥቂት ነው። ናሆም ከኤልቆሻ ከተማ እንደነበር እናውቃለን። አንዳንድ ምሁራን ኤልቆሻ በደቡብ ይሁዳ የሚገኝ ቦታ ነው ቢሉም፥ ከተማው የነበረበትን ቦታ አናውቅም። ናሆም ከይሁዳ የነበረ ሳይሆን አይቀርም። እርሱ ባገለገለበት ዘመን የነበሩ የይሁዳና የእስራኤል ነገሥታት እነማን እንደነበሩ አልተጠቀሰም። ስለዚህ የተጻፈበትን ጊዜ ለመወሰን፥ በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኙትን መረጃዎች መመልከት አለብን።

ትንቢተ ናሆም የተጻፈው ከነነዌ ውድቀት በፊት ስለሆነ፥ ነነዌ በባቢሎን ከተያዘችበት ከ612 ዓ.ዓ. አስቀድሞ ነው ማለት ነው። ትንቢተ ናሆም የተጻፈው የግብፅ ከተማ ከሆነችው ከኖእ አሞን መደምሰስ በኋላ መሆኑንም እናውቃለን (ናሆም 3፡8)። ይህ የሆነው አሦራውያን ወደ ግብፅ ዘልቀው ገብተው ከተማይቱን በያዙበት በ663 ዓ.ዓ. ነበር። ስለዚህ ትንቢተ ናሆም የተጻፈው ከ663-612 ዓ.ዓ. ባለው ጊዜ ነበር። በ650 ዓ.ዓ. አሦራውያን ከግብፅ ተባረው ወጡና ኖእ አሞን ከተማ እንደገና ተቆረቆረች። ስለዚህ ናሆም ያገለገለው በክፉው ንጉሥ በምናሴ ዘመነ መንግሥት (609-642 ዓ.ዓ.) ወይም በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት (640-609 ዓ.ዓ.) ነው ማለት ነው። ብዙ ምሁራን ይህ መጽሐፍ የተጻፈው በምናሴ ዘመነ መንግሥት መጨረሻ ገደማ ምናልባትም ከ655-650 ዓ.ዓ. ባለው ጊዜ እንደሆነ ይገምታሉ።

የትንቢተ ኢሳይያስና ናሆም የአጻጻፍ ሥልት መመሳሰሉን መመልከት አስገራሚ ነው (ናሆም 1፡15 ና ኢሳይያስ 52፡7 አወዳድር)። ናሆም ምናልባት ትንቢተ ኢሳይያስን አንብቦት ይሆናል። 

የትንቢተ ናሆም ታሪካዊ ሥረ መሠረት 

አሦር ለብዙ መቶ ዓመታት በመካከለኛው ምሥራቅ የምትገኝ ኃያል አገር ነበረች። እግዚአብሔር በሰሜኑ የእስራኤል መንግሥት የሚገኙትን ሕዝቡን ለመቅጣት የተጠቀመው በአሦራውያን ነበር (722 ዓ.ዓ.)። አሦራውያን የእስራኤልን ሕዝብ በክፋትና በተንኮል ማርከው ወሰዱአቸው። አሦር የታወቀችው በጭካኔዋና ሌሉች ሕዝቦችን በቁጥጥር ሥር በምታውልበት የማስፈራሪያ ኃይሏ ነበር። በአሦር ላይ ለማመፅ የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ ምልክት የሕዝቡ ሁሉ ተነቅሉ መበተን፥ መሠቃየትና መቀጣት ነበር።

ይሁዳ በአሦር ባትያዝም እንኳ ለብዙ ዓመታት በእርስዋ ቁጥጥር ሥር ሆና አንድ ቅኝ መንግሥት መከፈል የሚገባውን ግብርና ቀረጥ ትከፍል ነበር። በሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት፥ አሦር ይሁዳን አጥቅታ ከኢየሩሳሌም በስተቀር የቀሩትን ክፍሎች በሙሉ ይዛ ነበር። ኢየሩሳሌምም የዳነችው እግዚአብሔር በጉዳዩ ውስጥ ጣልቃ በመግባቱና የአሦር ሠራዊት በመደምሰሱ ነበር (2ኛ ነገሥት 19፡35-36)። ንጉሥ ምናሴ የአሦርን ጣዖት ለማምለክ ወደ አሦር ሄዶ ነበር። የአሦርን የጣዖት አምልኮ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ይሁዳ ያመጣ እርሱ ነው። በኋላም በአሦር ላይ ዓመፀና በምርኮ ተወሰደ። በመጨረሻም ከምርኮ ተለቆ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።

እግዚአብሔር ናሆምን ለነቢይነት በጠራው ጊዜ አሦር እጅግ ገናናና ኃያል በመሆኗ፤ ማንም ሊያሸንፋት የማይችል ትመስል ነበር። ንጉሥ አሱርባኒፓል በትረ ሥልጣኑን ይዞ ባደረጋቸው በርካታ ጦርነቶች መንግሥቱን እስከ ግብፅ ድረስ እንኳ ዘልቆ አስፋፍቶ ነበር። ነነዌ ጨርሶ ልትነካ በማትችልበት ሁኔታ ላይ የምትገኝ ትመስል ነበር። ታሪክን ሁሉ የሚቆጣጠረው እግዚአብሔር ግን የሚደርስባትን ነገር ያውቅ ነበር። ከአሱርባኒፓል ሞት በኋላ የአሦር መንግሥት በፍጥነት ማሽቆልቆል ጀመረ (ከ669-627 ዓ.ዓ.)። የተለያዩ ገዥዎች ሥልጣን ለመጨበጥ በሚያደርጉት ጥረት በአገሪቱ የእርስ በርስ ጦርነት ይካሄድ ጀመር። ከዚያም በ627 ዓ.ዓ. የባቢሎን ከተማ ከአሦር ነፃ ሆና ራሷን ቻለች። የባቢሎን መንግሥት በ612 ዓ.ዓ. ከሜዶን ሠራዊት ጋር በመተባበር የአሦርን መንግሥት አሸንፋ ተቆጣጠረች። በጥንት ታሪክ ውስጥ ከባቢሎን ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ እጅግ ገናና የነበረችው፥ ታላቅ ግንቦች፥ የመናፈሻ ቦታዎች፥ ሙዝናኛዎች፥ የእንስሳት መጠበቂያዎች ወዘተ. የነበሯት ታላቋ የነነዌ ከተማ ተደመሰሰች። ከዚያ በኋላ በዓለም ኃያል መንግሥት ሆና ከቶ አልተነሣችም አትነሣምም፡፡ እግዚአብሔር በነነዌ ላይ ያወጀው ፍርድ ተፈጸመ።

የውይይት ጥያቄ፥ በነነዌ ላይ ተነግሮ ከነበረው ትንቢት ፍጻሜ ስለ እግዚአብሔርና ስለ ቃሉ ኃይል ምን እንማራለን?

ናሆም ያገለገለው ሶፎንያስ ባገለገለበትና በመጀመሪያዎቹ የኤርምያስ የአገልግሎት ዘመናት ነበር። 

የትንቢተ ናሆም አስተዋጽኦ 

1. ስለ ፈራጁ እግዚአብሔር የተሰጠ መግለጫ (ናሆም 1፡1-8)። 

2. ስለ ነዌ መደምሰስ የተነገሩ ትንቢቶች (ናሆም 1፡9-14)፥ 

3. የይሁዳ ነፃ መውጣት (ናሆም 1፡15)፥

4. የነነዌ ውድቀት መግለጫ (ናሆም 2-3)።

የውይይት ጥያቄ፥ ስለ ናሆም ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ተመልከት። በዚያም ስለ ናሆም የተጠቀሱትን አንዳንድ ጠቃሚ እውነተች ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: