ትንቢተ ዮናስ መግቢያ

አንድ ሰባኪ ወይም አገልጋይ እግዚአብሔር እንደሚፈልገው ባይመላለስ ያንን ሰው እግዚአብሔር ሊጠቀምበት ይችላልን? እግዚአብሔር ብዙዎችን ወደ ራሱ ለማምጣት ዓለማዊነት በሚያጠቃው ወንጌላዊ ሊጠቀም ይችላልን? አንድ ክርስቲያን እርሱ ሳይባረክ፥ እግዚአብሔር ሌሎችን ለመባረክ ሊጠቀምበት ይችላልን?

የውይይት ጥያቄ፥ እነዚህን ጥያቄዎች እንዴት ትመልሳቸዋለህ? መልስህን አብራራ።

ትንቢተ ዮናስ ዓለም እስካሁን ካየቻቸው የተሳካላቸው ሰባኪዎች መካከል አንዱ ስለሆነው ሰው ታሪከ ይገልጣል። በመልእክቱ ንጉሡን ጨምሮ የአንዲት ከተማ ሕዝብ በሙሉ ንስሐ እንዲገቡ አደረገ። ይሁን እንጂ የዮናስ ልብ በእግዚአብሔር ፊት ትክክል አልነበረም። ለአገልግሎቱ የነበረው ዝንባሌ እጅግ መጥፎ ነበር። ስለዚህ ራሱ ሊያገኝ የሚችለውን በረከት አጣ። ትንቢተ ዮናስ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለሆንን ሰዎች ከባድ ማስጠንቀቂያ ይዟል። ሕይወታችንን በሙሉ በእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት ልናሳልፍ፥ እግዚአብሔር በኃይል ሊጠቀምብንና ለሌሎች በረከት ልንሆን እንችላለን። ነገር ግን እግዚአብሔር የሚፈልገን ዓይነት ሰዎች ላንሆን፥ አገልግሎትን በሚመለከት የተሳሳተ ዝንባሌ ሊኖረንና እግዚአብሔር የሚሰጠንን በረከት ልናጣ እንችላለን። 

የትንቢተ ዮናስ ጸሐፊ

ከታናናሽ ነቢያት ሁሉ ላቅ ብሉ የታወቀው ዮናስ ነው። ታሪኩን ሁላችንም የምናውቀው ነው። ትንቢተ ዮናስ ከታናናሽ ነቢያት የሚመደብ ቢሆንም፥ ከሌሉች የትንቢት መጻሕፍት ሁሉ ፍጹም የተለየ ነው። የትንቢት መጻሕፍት በሙሉ ነቢያት ለሕዝቡ የተናገሯቸው መልእክቶች የተጻፉባቸው ናቸው። ትንቢተ ዮናስ ግን ነነዌ በጥቂት ቀናት ውስጥ እንደምትጠፋ የሚገልጽ መልእክት ከመያዙ ሌላ ምንም ዓይነት ትንቢት አልያዘም። ይልቁንም መጽሐፉ ከነቢያት አንዱ የሆነውን የዮናስን ታሪክ የያዘ ነው።

ትንቢተ ዮናስ የተሰየመው የመጽሐፉ ዋና ባለታሪክ በሆነው በዮናስ ስም ነው። መጽሐፉን ዮናስ እንደጻፈው የሚገልጽ አሳብ በመጽሐፉ ውስጥ ስለሌለና የተጻፈው በሦስተኛ ሰው ስለሆነ፥ ማን እንደጻፈው ማረጋገጥ አንችልም። በግምት ግን የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ ዮናስ ሳይሆን አይቀርም። እንዲሁም የዮናስን ታሪክ በሚያውቅ በሌላ ሰውም ተጽፎ ሊሆን ይችላል።

እንደ አብዛኛዎቹ ታናናሽ ነቢያት፥ ስለ ዮናስ የምናውቀው ነገር በጣም ጥቂት ነው። ዮናስ ነቢይ እንደሆነ በ2ኛ ነገሥት 14፡25 ተጠቅሷል። በእስራኤል ይኖር የነበረና በዳግማዊ ኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት የነበረ ነቢይ ነው። ለእስራኤል ሕዝብ ለማስተላለፍ የፈለገው መልእክት ምን እንደ ነበረ አናውቅም። ስለ እርሱ የምናውቀው ነገር ቢኖር፥ እግዚአብሔር የአሦር ዋና ከተማ ወደነበረችው ወደ ነነዌ የፍርድ መልእክት እንዲያደርስ በላከው ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ግንኙነት ብቻ ነው።

በትንቢተ ዮናስ ከተመዘገበው ታሪክ ቀጥሎ ምን እንደተፈጸመ የምናውቀው ነገር የለም። ዮናስ ከኃጢአቱ በንስሐ ተመልሶ ይሆን? 

ካሳለፈው የሕይወት ልምድ ተምሮ ይሆን? ወደ እስራኤል የተመለሰው በንስሐ በተለወጠ ልብ ካልሆነ በቀር መጽሐፉን አይጽፍም ነበር የሚል እምነት ስላለን፥ ለእነዚህ ጥያቄዎች ልንሰጥ የምንችለው ምላሽ ቢኖር አዎንታዊ ግምት ብቻ ነው። 

የትንቢተ ዮናስ መጽሐፍ 

የትንቢተ ዮናስ ታሪክ እውነተኛነት በብዙ ምሁራን ዘንድ አጠያያቂ ሆኖአል። ዮናስ በዓሣ ነባሪ ሆድ ውስጥ ለሦስት ቀናት እንዴት በሕይወት ሊቆይ ይችላል? ጥላ የሆነችው ቅል እንዴት በፍጥነት ልታድግ ቻለች? ይህ ሊሆን የሚችል ነገር አይደለም በማለት ምሁራን መጽሐፉን በተለያዩ መንገዶች ይተረጉማሉ። 

1. ተምሳሌታዊ አተረጓጐም፡- የመጽሐፉ ታሪክ እያንዳንዱ ክፍል አንድን እውነት የሚወክል ነው። ታሪኩንም ሆነ ለታሪኩ የሚሰጠውን ትርጉም በቁሙ (በቀጥታ) ልንረዳው አይገባም።

2. ምሳሌያዊ አተረጓጐም፡- አንዳንዶች ደግሞ ይህ ታሪክ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ከተናገራቸው ምሳሌዎች ጋር ተመሳሳይ ነው ይላሉ። (ለምሳሌ፡- የመልካሙ ሳምራዊ ታሪክ)። ይህ ታሪክ እውነተኛ አይደለም። ነገር ግን የሥነ-ምግባር ትምህርት ለማስተማር የተዘጋጀ የፈጠራ ታሪክ ነው ይላሉ። የዚህ ዓይነቱ ታሪክ ልጆች እውነትን በሚገባ እንዲረዱ ለማድረግ የሚነገር እውነተኛ ያልሆነ ታሪክ የሚመስል ነው)። 

3. እውነትን ለማስተማር ተጋንኖ የቀረበ ታሪክ፡- አንዳንዶች የዚህ ታሪክ የተወሰነ ክፍል እውነተኛ ነው ይላሉ። ወደ ነነዌ የሄደ ዮናስ የሚባል ሰው ነበር። ይሁን እንጂ በታሪኩ ውስጥ የተጠቀሱት ዝርዝር ጉዳዮች ታሪኩን የበለጠ ልብ የሚነካ ለማድረግ ተጋንነው የቀረቡ ናቸው። ይህም የተመለከትነውን አደጋ ለመግለጥ ወይም የሠራነውን ታላቅ ሥራ ለማስረዳት በማጋነን እንደምንናገራቸው ነገሮች ያለ ነው። የተመሠረተው በእውነተኛ ታሪክ ላይ ቢሆንም፥ ይበልጥ ሕይወት እንዲኖረው ለማድረግ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ ነገሮችን እናክላለን። 

4. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተጻፈው በቀጥታ በዮናስ ሕይወት የተፈጸም ታሪክ ነው። መጽሐፉን የምንረዳበት ከሁሉም የተሻለው መንገድ ተአምራቱን ጨምሮ የተጻፈው ሁሉ እንዳለ የተፈጸመ እውነተኛ ታሪክ መሆኑን ማመን ነው። ኢየሱስ በዚህ ታሪክ እንዳመነና ዮናስ በዓሣ ነባሪ ሆድ ውስጥ ለሦስት ቀንና ሌሊት የቆየበትን ታሪክ የሞቱና የትንሣኤው መግለጫ አድርጎ እንደተጠቀመባት ግልጽ ነው (ማቴዎስ 12፡40-41)። በዓሣ ነባሪ ሆድ ውስጥ በርካታ ቀናት የቆዩና ዓሣ ነባሪው ተይዞ ከውስጡ ሲወጡ በሕይወት የተገኙ የሌሎች ሰዎች ታሪኮች አሉ። 

ታሪካዊ ሥረ መሠረት

ዮናስ የኖረው በዳግማዊ ኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት ነው (782-753 ዓ.ዓ.)። ኢዮርብዓም እግዚአብሔርን የማያመልክ ክፉና ኃጢአተኛ ቢሆንም፥ ኃይለኛ ንጉሥ እንደነበር የሚታወስ ነው። የእስራኤልን ድንበር በዳዊትና በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት ወደነበረበት ስፍራ ሊመልስ ችሎ ነበር። ይህ የሆነበት አንዱ ምክንያት በዚያ ዘመን ከነዓንን የሚቆጣጠር ኃያል መንግሥት አለመኖር ነው። ወደ ሰሜን ምሥራቅ ርቃ ትገኝ የነበረችውና ሶርያን ያሸነፈችው አሦርም ደካማ ነበረች። ይህም ለእስራኤል ሕዝብ ታላቅ ሰላምንና ብልጥግናን አስገኝቶ ነበር። እስራኤል ታላቅ አገር በሆነች ጊዜ በብርታትዋ ትታበይ ጀመር። ኃይሏንና ብልጥግናዋን ያገኘችው የእግዚአብሔር ምርጥ በመሆኗ መሰላት፡፡ በውስጧ የነበረውን የጣዖት አምልኮ እያወቀች ካለማስወገዷም ንስሐ ለመግባት አልፈለገችም።

እስራኤላውያን የእግዚአብሔር ሕዝብ ስለሆኑ እግዚአብሔር ለሌሎች አሕዛብ፥ በተለይም በጭካኔያቸው አንድ ጊዜ ለታውቁ ሕዝቦች ግድ የለውም የሚል እምነት ነበራቸው። አሦር ኃያል አገር እንደሆነችና በማንኛውም ጊዜ የእነርሱ ጠላት ልትሆን እንደምትችል እስራኤላውያን ያውቁ ነበር። ነቢዩ አሞጽ በኋላም ሆሴዕ በኃጢአታቸው ምክንያት እግዚአብሔር ከደማስቆ ባሻገር (አሞጽ 5፡27) ትገኝ ወደነበረችው ወደ አሦር (ሆሴዕ 9፡3) እንደሚያስማርካቸው ለእስራኤል ሕዝብ መናገር ጀምረው ነበር፡፡ እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ የሚቀጣው በአሦር አማካይነት እንደሆነ ዮናስ ያውቅ እንደነበረ መገመት ይቻላል።

አሦራውያን ለጠላቶቻቸው ከፍ ያለ ጭካኔን በማሳየት ቀድሞውኑ እውቅናን ያተረፉ ነበሩ። አንዳንድ ጊዜ ጠላቶቻቸውን ከነሕይወታቸው ይቀብሩ፥ ቆዳቸውን ይገፍፉና ምላሳቸውን ጎልጉለው በማውጣት ይቆርጡ ነበር። ዮናስ ወደ ነነዌ ሰዎች ሄዶ ለመስበክ ያልፈለገባቸው ምክንያቶች እነዚህ ነበሩ።

እግዚአብሔር በዮናስ በኩል ለሚያመጣው መልእክት አሦራውያንን አዘጋጅቶአቸው ነበር ማለት ይቻላል። በ765ና በ759 ዓ.ዓ. አሦርን የመቱ ሁለት ከባድ መቅሠፍቶች ወርደው ነበር። በ763 ዓ.ዓ. ደግሞ የጥንት ሰዎች ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔር ፍርድ ምልክት ነው ብለው የሚያምኑት የፀሐይ ግርዶሽ ተከስቶ ነበር። አንዳንዶች ደግሞ የመሬት መንቀጥቀጥ ሳይፈጸም አልቀረም ይላሉ። ዮናስ ራሱ ያልተለመደ ምልክት ነበር ማለት ይቻላል። ዮናስ በዓሣ ነባሪ ሆድ ውስጥ ለሦስት ቀናት ስለቆየ፥ የዓሣ ነባሪው የጨጓራ አሲድ ፀጉሩንና ቆዳውን ወደ ነጭነት ቀይሮት ይሆናል። አሦራውያን ዮናስ ላመጣው መልእክት ፈጣን ምላሽ የሰጡት በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ሳይሆን አይቀርም። 

የትንቢተ ዮናስ አስተዋጽኦ 

1. ዮናስ ለአሦራውያን እንዲሰብክ ከተሰጠው ተልእኮ ሸሸ (ዮናስ 1-2)፤ 

2. ዮናስ ለአሦራውያን እንዲሰብክ የተሰጠውን ተልእኮ ፈጸመ (ዮናስ 3-4)፤ 

ሀ. የሕዝቡ በንስሐ መመለስ (ዮናስ 3)፥ 

ለ. ለእግዚአብሔር ምሕረት ዮናስ የሰጠው ምላሽ (ዮናስ 4)፥ 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

https://forms.gle/XHdAurZZ8HYf6Koq7

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading