ትንቢተ ሶፎንያስ መግቢያ

የውይይት ጥያቄ፥ ሶፎንያስ 1፡12 አንብብ። ሀ) እግዚአብሔር እቀጣለሁ ያለው ምን ዓይነት ሰዎችን ነበር? ለ) ሰዎች ስለ እግዚአብሔር የነበራቸው የተሳሳተ አመለካከት ምን ነበር?

ለእግዚአብሔር ሕዝብ እጅግ አደገኛ ከሆኑ ነገሮች ዋናው በእግዚአብሔር ላይ በግልጽ ማመፅ አይደለም። ወደ ሐሰት ትምህርቶች ወይም ሃይማኖቶች መለወጥም አይደለም። የእግዚአብሔር ሰዎች በራሳቸው መርካታቸው እንጂ። ሶፎንያስ ባገለገለበት ዘመን በይሁዳ ላይ ችግር ከፈጠሩት ኃጢአቶች አንዱ ይህ ነበር። በዮሐንስ ራእይ፥ እግዚአብሔር የሉዶቅያን ቤተ ክርስቲያን፥ ባላት መንፈሳዊ ሕይወት በመርካቷና በራድ ወይም ትኩስ ባለመሆኗ ሲገሥጻት እንመለከታለን (ራእይ 3፡14-20)።

ቤተ ክርስቲያን ወይም ክርስቲያን ለብ የሚለውና በራሱ የሚረካው ለምንድን ነው? በርካታ ምክንያቶች አሉ፡- በመጀመሪያ፥ ቤተ ክርስቲያን ለብ የምትለው በግል ወይም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚደረግ አምልኮ ሁልጊዜ አዲስና ሕያው በሆነ መንገድ ከማምለክ ይልቅ የአምልኮ ሥርዓቶችን ብቻ የመከተል አዝማሚያ ሲኖር ነው። ሁለተኛ፥ ቤተ ክርስቲያን በራሷ የረካች የምትሆነው እርስዋ ወይም ክርስቲያን እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሌሎች ሰዎች ከመድረስ ይልቅ፥ ለራሳቸው ፍላጎትና ምቾት አጥብቀው ማሰብ ሲጀምሩ ነው። በቤተ ክርስቲያን ወይም በእያንዳንዱ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ራስ ወዳድነት ሲንሰራፋ በመንፈሳዊ ሕይወት ረገድ በራስ መርካትን ያስከትላል። ሦስተኛ፥ የጠፉትን የመፈለግና በወንጌል የመድረስ ፍላጎት ሲጠፋ ነው። ይህ የወንጌላውያን እንጂ የእኛ ሥራ አይደለም ብሎ ማሰብ ቀላል ነው። ወይም በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ልንመለከታቸው የሚገቡን ብዙ ችግሮች ስላሉ፥ የጠፉትን ለመፈለግም ሆነ ለመድረስ ጊዜና ገንዘብ የለንም ብሉ ማሰብ ቀላል ነው። አራተኛ፥ በመንፈሳዊ ሕይወታችን በመልካም ሁኔታ ላይ እንደምንገኝ በማሰብ ስለ እግዚአብሔር ባለን እውቀት ያለማቋረጥ ማደግ እንደማያስፈልገን ስናስብ በራስ መርካት ይመጣል።

ቤተ ክርስቲያን ወይም ክርስቲያን በራሱ መርካት ሲጀምር፥ በመንፈሳዊ ሕይወቱ ምውት ወደ መሆን ያዘግማል። ምክንያቱም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መንፈሳዊ ሕይወት ስለማይኖር ሰዎች ወደ ሌላ ቤተ ክርስቲያን ወይም እምነታቸውን ትተው ወደ ሌላ ሃይማኖት ይሄዳሉ። በራስ ከመርካት የተነሣ ክርስቲያን እግዚአብሔር አንድ ቀን እንደሚፈርድበት ይረሳል። ወዲያውኑ በኃጢአት ወጥመድ ይያዝና ከዚያ በማምለጥ ለእግዚአብሔር እንደገና መኖር በጣም አስቸጋሪ ከሚሆንበት ሁኔታ ውስጥ ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ክርስቲያን ወይም ቤተ ክርስቲያን በራሳቸው ወደ መርካት ሊመጡ የሚችሉባቸውን ሌሎች ምክንያቶች ዘርዝር። ለ) በራስ የመርካት ሌሎች ውጤቶችን ዘርዝር። ሐ) ይህ ነገር በሕይወትህ፥ በሌላ ሰው ሕይወት ወይም በቤተ ክርስቲያን እንዴት እንደተፈጸመ አንዳንድ ምሳሌዎችን ስጥ። መ) በመንፈሳዊ ረገድ በራስ መርካትን በሚመለከት ፈውስ የሚሆኑ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

የይሁዳ ሕዝብ በራስ ከመርካት የተነሣ ቀስ በቀስ በኃጢአት ወደቁ። አይሁድ እግዚአብሔር ለረጅም ጊዜ ስለታገሣቸውና ፈጥኖ ስላልፈረደባቸው እነርሱ ስለሚያደርጉት ነገር እግዚአብሔር ይገደው እንደሆነ መጠየቅ ጀመሩ። እግዚአብሔር ሕዝቡን ለማስጠንቀቅ መልእክተኞቹን ነቢያትን በትዕግሥት ይልካቸው ነበር። ይሁን እንጂ ሕዝቡ አንዳንድ ጊዜ ድርጊታቸውን ለጊዜው ለመለወጥ ፈቃደኞች ቢሆኑም፥ ልባቸውን ለመለወጥ አልፈለጉም ነበር። እገዳው እንደተነሣላቸው ፈጥነው ወደ ጣዖት አምልኮ ይመለሱ ነበር። በመጨረሻ እግዚአብሔር ሶፎንያስን ጠራ። ሶፎንያስ የእግዚአብሔር የፍርድ ጊዜ ደርሶአል ሲል አወጀ። እግዚአብሔር ሕዝቡ በራሳቸው በመርካታቸውና በኃጢአታቸው ምክንያት እንደሚቀጣቸው ተናገረ። 

የትንቢተ ሶፎንያስ ጸሐፊ

በሶፎንያስ 1፡1 የእግዚአብሔር ቃል ወደ ሶፎንያስ እንደመጣ ተጽፏል። ይህ ማለት የትንቢተ ሶፎንያስ ጸሐፊ ሶፎንያስ ነው ማለት ነው። ስለ ሶፎንያስ የምናውቀው ነገር ብዙ ባይሆንም፥ አመጣጡ ከንጉሣዊ ዘር ይመስላል። በሶፎንያስ 1፡1 የተጠቀሰው ሕዝቅያስ የተባለው ሰው ንጉሥ ሕዝቅያስ ከሆነ፥ ሶፎንያስ የንጉሥ ሕዝቅያስ የልጅ ልጅ ልጅ ነው ማለት ነው። ይህም ማለት ሶፎንያስ ባገለገለበት ዘመን በይሁዳ ነግሦ ከነበረው ከንጉሥ ኢዮስያስ ጋርም ይዛመዳል ማለት ነው።

ሶፎንያስ ያደገው በኢየሩሳሌም ሳይሆን አይቀርም። በሰው ሁሉ ዘንድ የተከበረ ያደረገውም የንጉሥ ዘር መሆኑ ይሆናል። በሚገባ የተማረና በይሁዳ ከሚኖሩ ሁሉ የተሻለ ቤተሰብ ውስጥ የነበረ ሰው ነው። ይህ ማለት ግን ሶፎንያስ ስለ ሕዝቡ ወይም ዘመዶቹ ስለሆኑት ንጉሣውያን ቤተሰብ ኃጢአት ግድ አልነበረውም ማለት አይደለም። የሕዝቡን ኃጢአት በመቃወም በድፍረት ይናገር ነበር። በድጋሚ የምንመለከተው እግዚአብሔር በሁሉም ዓይነት ሰዎች እንደሚጠቀም ነው። እንደ ሚክያስና አሞጽ ባሉ ተራ ሰዎች ይጠቀም ነበር። እንደ ሶፎንያስ ባሉ ሀብታምና የተማሩ ሰዎችም ተጠቅሟል።

ሶፎንያስ ያገለገለው በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት እንደ ነበረ ይነገራል (640-609 ዓ.ዓ.)። ኢዮስያስ ሥልጣን የጨበጠው ከክፉዎቹ ነገሥታት ከምናሴና ከአሞን ቀጥሎ ገና የስምንት ዓመት ልጅ እያለ ነበር። ኢዮስያስ ከስምንት ዓመት በኋላ የአሥራ ስድስት ዓመት ልጅ ሲሆን፥ የሕዝቡን ሃይማኖት ማደስ ጀመረ። ሶፎንያስ ያገለገለው በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ሳይሆን አይቀርም። ኢዮስያስ በነገሠበት ዘመን ሁለት የተሐድሶ እንቅስቃሴዎች ተካሂደዋል። አንዱ በ632 ዓ.ዓ. አካባቢ የነበረው ሲሆን፥ ሌላው ደግሞ በ622 ዓ.ዓ. ገደማ የነበረው ነው። ሶፎንያስ ከእነዚህ ሁለት የተሐድሶ ጊዜያት በአንዱ ሳይሠራ አልቀረም። ነገር ግን ዋና የአገልግሎት ዘመኑ 627 ዓ.ዓ. አካባቢ ሳይሆን አይቀርም።

ሶፎንያስ በንጉሥ ኢዮስያስ ሕይወት ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ በማሳደር ባካሄደው ተሐድሶ ረድቶት እንደሆነ የምናውቀው ነገር የለም። በሥልጣኑና ከንጉሡ ጋር በነበረው ግንኙነት ረድቶት ሊሆን ይችላል። የሚያሳዝነው ግን የሕዝቡ ንስሐ ውጫዊ ስለነበረ ንጉሥ ኢዮስያስ እንደሞተ ወደ ክፉ ሥራቸው ተመለሱ።

በዚህ ጊዜ በይሁዳ ያገለግል የነበረው ነቢይ ሶፎንያስ ብቻ አልነበረም። ኤርምያስ፣ ናሆምና ምናልባት ዕንባቆምም አገልግለዋል። ምርኮው ከመፈጸሙ አስቀድሞ በነበረው ጊዜ እግዚአብሔር ብዙ ነቢያትን በመላክ የኃጢአታቸውን ውጤቶች በመንገር ሕዝቡን እንዲያስጠነቅቋቸው አድርጎ ነበር። ሕዝቡን ለመለወጥና እግዚአብሔር የተናገረውን ፍርድ ለማስለወጥ ግን አልቻሉም። 

የትንቢተ ሶፎንያስ ታሪካዊ ሥረ-መሠረት 

ሶፎንያስ ይኖር የነበረው የአሦር መንግሥት እየከሰመ የባቢሎን መንግሥት ግን እያቆጠቆጠ ባለበት የሽግግር ወቅት ነበር። ከጥቂት ዓመታት በኋላ የይሁዳ ሕዝብ በባቢሎን ቁጥጥር ሥር በመውደቅ፥ በመጨረሻ በ586 ዓ.ዓ. ሊደመሰሱ ተዘጋጅተው ነበር።

የአሦር መንግሥት በመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካዊ ገጽታ ላይ የበላይነት ተጽዕኖን በማሳደር ለብዙ ዓመታት ቆይቷል። በዚያን ጊዜ የነበሩት መሪዎች ግን ብርቱዎች ስላልነበሩ በመንግሥቱ ሁሉ ውስጥ እየተባባሰ የሚሄድ ዓመፅ ነበር። የመጨረሻው የአሦር ዋና ንጉሥ አሱርባኒፓል ከሞተ በኋላ የአሦር መንግሥት መፈረካከስ ጀመረ። ባቢሎን ከአሦር ነፃ መውጣቷን አወጀች። በኋላም ባቢሎን ሜዶንን ከመሳሰሉ ሌሎች አገሮች ጋር በመተባበር አሦርን ማጥቃትና ማውደም ጀመረች። ይህ ከመሆኑ አስቀድሞ ሶፎንያስ የአሦርን ውድቀት አመልክቶ ነበር (ሶፎንያስ 2፡13-15)። ለጥቂት ዓመታት ይሁዳ ከውጭ መንግሥታት አንጻራዊ ሰላም አግኝታ ነበር። ባቢሎን በሰሜን በኩል ግዛቷን እያስፋፋችና ተጽዕኖዋን እያሳደገች ብትሄድም፥ እስካሁን ድረስ ወደ ከነዓን አልመጣችም ነበር። በዚህ በተገኘው ሰላም ንጉሥ ኢዮስያስ በይሁዳ ሕዝብ መካከል መንፈሳዊ ተሐድሶ ለማካሄድ ችሎ ነበር።

የንጉሥ ኢዮስያስ አያት የነበረው ንጉሥ ምናሴ በይሁዳ ከገዙት እጅግ ክፉ መሪዎች አንዱ የነበረ ሲሆን፥ ከ50 ዓመታት በላይ ነግሦአል (697-642 ዓ.ዓ.)። ምናሴ ወደ ኢየሩሳሌም አዳዲስ የጣዖት አምልኮ አመጣ። በውስጡ ጣዖትን በማኖር ቤተ መቅደሱን አረከሰ። የገዛ ልጁንም ለጣዖት መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ። ይህ ክፉ ንጉሥ በነገሠባቸው 50 ዓመታት ይሁዳን ልታንሰራራ ወደማትችልበት መንፈሳዊ አዘቅት ውስጥ ከቷት ነበር። በእርሱ ዘመነ መንግሥት የነበረው ትውልድ በአጠቃላይ የሚያውቀው ነገር ቢኖር የተደባለቀውን የበአልና የእግዚአብሔር አምልኮ ነበር። በዘመነ መንግሥቱ መጨረሻ ገደማ ምናሴ ተማርኮ ወደ አሦር ተወሰደና ሳይለቀቅ ለጥቂት ዓመታት ኖረ። በአሦር እያለ ልቡ ተለወጠና ወደ ጌታ ተመለሰ። ምናሴ ንስሐ ቢገባም እንኳ የይሁዳን ሕዝብ መንፈሳዊ ሕይወት ለመለወጥ ፈጽሞ አልቻለም። እርሱ ሲሞት ልጁ አሞን በምትኩ ነገሠ። አሞን ምናሴ ከነገሠባቸው የመጀመሪያ ዓመታት እንደነበረው በክፋት ሄደ። በልጅነቱ የአባቱን ክፋት ተመልክቶ ስለነበር እግዚአብሔርን ለማክበር አልቻለም። ስለሆነም፥ እግዚአብሔር እንዲነግሥ የፈቀደለት ለሁለት ዓመታት ብቻ ነበር። አሞን ተገደለና ትንሽ ልጁ ኢዮስያስ ነገሠ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ወላጆች በልጆቻቸው ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ልጆች በሚያድጉ ጊዜም የሚቀጥለው በምን መንገድ ነው? ለ) ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸው ትልልቆች እስኪሆኑ ድረስ ከመጠበቅ ይልቅ፥ ገና ትንንሾች እያሉ እግዚአብሔርን እንዲፈሩና ለእርሱ እንዲታዘዙ ማስተማር የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

ኢዮስያስ በይሁዳ ሕዝብ መንፈሳዊ ሕይወት ለውጦችን ለማምጣት የሞከረ ቢሆንም፥ አብዛኛዎቹ ለውጦች ውጫዊ እንጂ ውስጣዊ አልነበሩም። በእርሱ ተጽዕኖ ሕዝቡ ጣዖታትን ለማጥፋትና እግዚአብሔርን ለማምለክ ተስማምተው ነበር። ነገር ግን ኢዮስያስ በ609 ዓ.ዓ. እንደሞተ ወዲያውኑ ወደ ጣዖት አምልኮ ተመለሱ። ይህም ሶፎንያስና ሌሎች የተናገሩት ትንቢት እንዲፈጸምና ባቢሎን ይሁዳን እንድትማርክ አደረገ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በአንድ አገር ወይም ሕዝብ ሕይወት መንፈሳዊ ተሐድሶ ማምጣት አስቸጋሪ ስለመሆኑ ከይሁዳ ታሪክ ምን እንማራለን? ለ) ብዙ ጊዜ የሰውን ውስጣዊ ሕይወት (ልብን) ከመለወጥ ይልቅ ውጫዊ ድርጊቱን (መጠጣት፣ መደነስ፣ መቃም ወዘተ. ) መለወጥ የሚቀልለው ለምንድን ነው? ሐ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ውጫዊ ለውጥ ለማምጣት ብቻ ሳይሆን፥ በሰዎች ልብ ውስጥ እውነተኛ ለውጥን ለማምጣት ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር ምንድን ነው?

የትንቢተ ሶፎንያስ አስተዋጽኦ 

1. በሁሉም ላይ ስለሚመጣው ፍርድ የተሰጠ አጠቃላይ መግለጫ (ሶፎንያስ 1፡1-3)፥ 

2. በጌታ ቀን በይሁዳ ላይ የሚመጣው ፍርድ (ሶፎንያስ 1፡4-18)። 

3. በጌታ ቀን በአሕዛብ ላይ የሚመጣው ፍርድ (ሶፎንያስ 2፡1-3፡8፥)

ሀ. ሕዝቡ ንስሐ እንዲገቡ የቀረበላቸው ጥሪ (ሶፎንያስ 2፡1-3)። 

ለ. በፍልስጥኤም ላይ የተነገረ የፍርድ መልእክት (ሶፎንያስ 2፡4-7)፥ 

ሐ. በሞዓብና በአሞን ላይ የተነገረ የፍርድ መልእክት (ሶፎንያስ 2፡8-11)፥ 

መ. በኩሽ ላይ የተነገረ የፍርድ መልእክት (ሶፎንያስ 2፡12)። 

ሠ. በአሦር ላይ የተነገረ የፍርድ መልእክት (ሶፎንያስ 2፡13-15)፥ 

ረ. በኢየሩሳሌም ላይ የተነገረ የፍርድ መልእክት (ሶፎንያስ 3፡1-8)። 

4. በጌታ ቀን ስለሚመጡ በረከቶች የተነገረ መልእክት (ሶፎንያስ 3፡9-20)።

የውይይት ጥያቄ፥ ስለ ሶፎንያስ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። ስለ ሶፎንያስ የተመለከትሃቸውን አንዳንድ ጠቃሚ ትምህርቶች ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

https://forms.gle/t28poRp8wc3uYX3y9

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading