ለ የክርስቶስ የፍርድ ወንበር (ቤማ) ወይም የሽልማት ዶክትሪን

(ከ http://www.bible.org የተወሰደ)

(ደምቀው የተፃፉና የተሰመረባቸው ቃላት ትኩረትን የሚሹ ጉዳዮች ናቸው፡፡) 

በሐዲስ ኪዳን ከሚገኙ ታላላቅ ትምህርቶች አንዱ የሽልማት ዶክትሪንና የክርስቶስ የፍርድ ወንበር ትምሕርት ነው፡፡ ይህ አስተምህሮ ብዙ ጊዜ የተዘነጋና፣ በትምሕርት መልክ የሚሰጥ ሲሆንም ከግሪኩ ላይ ተተርጉሞ ከተወሰደው ‹‹ፍርድ›› ከሚለው ቃል የተነሳ በተሳሳተ መንገድ ሲቀርብ ይስተዋላል፡፡

ሳሙኤል ሆይት ስለዚህ ጉዳይ ሃሳቡን ሲሰጥ፣ በአሁኑ ጊዜ ስለ ክርስቶስ የፍርድ ወንበር ባሕሪ በርካታ ንትርኮችና ግርታዎች ይስተዋላሉ፡፡ በእንግሊዘኛ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ‹‹የክርስቶስ የፍርድ ወንበር›› ተብሎ የተቀመጠው አገላለፅ አንዳንዶች ስለ ጉዳዩ አላማና ባሕሪ የተሳሳተ ማጠቃለያ ላይ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህ የእንግሊዘኛ ትርጉም ምክንያት ከሚስተዋሉ የተለመዱና የተዛቡ አመለካከቶች አንዱ በዚህ ወቅት እግዚአብሔር በአማኙ ሕይወት ውስጥ በታዪት ኃጢአቶች አንጻር አማኙን ይቀጣል የሚለው ነው፡፡

ምንም እንኳን ኃጢአት ያለው ዘላለማዊ አሉታዊ ፋይዳ በቀላል የሚታይ ባይሆንም፣ የክርስቶስ የፍርድ ወንበር ጌታ እግዚአብሔር፣ በእርሱ ልጆች የተሰራውን ኃጢአት የሚቀጣበት ጊዜ እና ቦታ አይደለም፡፡ ሕይወታችን ለጌታ ስራ እንደዋለ መጠን ሽልማት የምናገኝበት ወይም የምናጣበት ስፍራ እንጂ፡፡

በሌላ አገላለጽ ሽልማት፣ መንፈስ ቅዱስ በሕይወቴ ውስጥ ፍሬ እንዲያፈራ ከእርሱ ጋር በሕብረት በመጣመር በእምነት የኖርኩበት ኑሮ ውጤት ነው፡፡ በ 1ተሰሎንቄ 2፡19-20 ላይ ጳውሎስ ለዚህ ሽልማት ራሱንና ቤተ ክርስቲያንን ሲያበረታታ እንመለከታለን፡፡ የመጀመሪያው የተሰሎንቄ መልዕክት የዚህን ሽልማት ጉዳይ በእያንዳንዱ ምዕራፍ ላይ ይጠቀስና በሁለተኛው መልዕክት ላይ ደግሞ ዋናኛ የደብዳቤው ትምሕርት ይሆናል፡፡ የጌታ ዳግም ምፅአት ለአለም ብቻ ሳይሆን ለእኛ ለምናምን ለእያንዳንዳችን ታላቅ ትምሕርት የያዘ የሐዲስ ኪዳን እውነት ነው፡፡ በመጨረሻው የራዕይ መጽሐፍ ክፍል ላይ እነዚህን የጌታ ቃሎች እናገኛለን፡፡ ‹‹እነሆ በቶሎ እመጣለሁ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ፡፡›› (ራዕ. 22፡12)

ድነት፣ የእግዚአብሔር ነጻ ስጦታ ነው፤ እያወራን ካለው ሽልማት ጋርም ምንም ግንኙነት የለውም፡፡ ከምግባሮቻችን በመነሳት በሕይወታችን ላሳየነው ታማኝነት ሽልማት የምናገኝበት እና ታማኝ ላልሆንበት ደግሞ ሽልማት የምናጣበት ጊዜ ከፊታችን አለ፡፡ ሽልማት በክርስትና ሕይወት ውስጥ ዋነኛ አነሳሽ ምክንያት/motivation ከሚሆኑን ነገሮች መካከል አንዱ ነው፤ እየሆነ ካልሆነም ከዚህ በኋላ መሆን አለበት፡፡ ስለ አነሳሽ ምክንያቶች ባህሪ ከማውሳታችን በፊት የእነዚህን ሽልማቶች ባሕሪ ልንገነዘብ ይገባል፡፡ አንዳንዶች ይህንን ጉዳይ ለመረዳት የሚቸገሩበት ምክንያቶች አንዱ የሽልማት አስተምህሮ ‹‹ፀጋ›› ን ወደጎን በማድረግ ‹‹ሽልማት ስለሚገባው ችሎታ›› ትኩረት የሚሰጥ ነው ብለው ስለሚያስቡ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በማያያዝ እግዚአብሔርን፣ ከፍቅር በመነሳትና ለእርሱ ክብር ስንል ብቻ ልናገለግለው ይገባል ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ በእርግጥ ነው እግዚአብሔርን ከፍቅር በመነሳትና ለእርሱ ክብር ስንል ልናገለግለው ይገባል፡፡ የሽልማት ባህሪንም መረዳት እንዲሁ እንድናደርግ ያስተምረናል፡፡

እግዚአብሔር ድነትን ይሰጠናል፡፡ ይህን በእምነት የምንቀበለው ነው፡፡ ደግሞም ስለ መልካም ሥራችን ይሸልመናል፡፡ እግዚአብሔር ፀጋውን እስከተጠቀምንበት ድረስ መፈለግንና ማድረግን በእኛ ውስጥ ሆኖ ይሰራል (ፊል 2፡12-13)፡፡ ነገር ግን ለማገልገል መፍቀድና ይህንንም ለማድረግ ትጋት ከእኛ የሚጠበቁ የእኛ ድርሻዎችና የእኛ አስተዋፅኦዎች ናቸው፡፡ እናም እግዚአብሔር ይህንን ነገራችንን፣ ሽልማት እንደሚገባው አድርጎ ይቆጥረዋል፡፡

1ቆሮ. 15፡10 ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ የሆንሁ እኔ ነኝ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋው ከንቱ አልነበረም ከሁላቸው ይልቅ ግን ደከምሁ፣ ዳሩ ግን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም፡፡

ቆላ. 1፡29 ለዚህም ነገር ደግሞ፣ በእኔ በኃይል እንደሚሠራ እንደ አሠራሩ እየተጋደልሁ፣ እደክማለሁ፡፡

ቁልፍ ጥቅሶችሮሜ. 14፡10-11፤ 1ቆሮ. 3፡11-15፤ 2ቆሮ. 5፡9-10፤ 1ዮሐ. 2፡28፤ ራዕ. 3፡11-12

የፍርድ ወንበር (ቤማ) ትርጓሜ

የሮሜ መልክት 14፡10 እና 2ቆሮንቶስ 5፡10 ስለ ‹‹ፍርድ ወንበር›› ያወራሉ፡፡ ይህ ሀሳብ የአንድ «bema›› የተሰኘ የግርክ ቃል ትርጓሜ ነው፡፡ በወንጌላትና ሐዋሪያት ስራ ላይ «bema›› የሚለው ቃል የሮማዊያኑ ፈራጆች ወይም ገዥዎች ውሳኔ ለመስጠት እና ብይን ለማድረግ የሚቀመጡበትን ጉብታ ስፍራ የሚያመለክት ሲሆን (ማቴ. 27፡19፣ ዮሐ. 19፡13)፣ ጳውሎስ በደብዳቤዎቹ የተጠቀመበት አጠቃቀም ግን የግሪክ አትሌቶችን ውድድር በሚያወሳ መልኩ እና ግሪካዊያን ‹እንደ ወረደ› (original use) በሚጠቀሙበት አግባብ ነው፡፡ ይህ ቃል የ Isthmian ጨዋታ ከሆነውና ዳኞች የዚህ ጨዋታ ሕጎች በተወዳዳሪዎች በአግባቡ መፈፀማቸውን በጥብቅ ከተከታተሉ በኋላ ለተወዳዳሪዎች ሽልማት ከሚሰጡበት የጨዋት ሃሳብ የተወሰደ ነው (2ጢሞ. 2፡5)፡፡ 

ሕጉ በሚፈቅደው መልኩ ጨዋታውን ያጠናቀቀው አሸናፊ በዳኛው ወደዚህ ጉብታ (bema) ፊት እንዲቀርብ ይደረግና የድሉ ተምሳሌት የሆነው ከለምለም ሳር የተሰራ አክሊል በራሱ ላይ ይቀመጥለታል (1ቆሮ. 9፡24-25)፡፡ በእነዚህ ጥቅሶች ሁሉ ‹‹ጳውሎስ አማኙን መንፈሳዊ ውድድር ውስጥ ያለ አድርጎ ያስቀምጠዋል፡፡ ልክ ድል የነሳው የግሪክ አትሌት በ bema ፊት ቀርቦ የሚገባውን እንደሚቀበል፣ አማኝም በክርስቶስ bema ፊት የማይጠፋውን አክሊል ለመቀበል ይቀርባል፡፡ በ bema ያለው ዳኛ፣ ድል ለነሱት ሽልማት የሚያበረክት እንጂ ተሸናፊዎችን የሚገርፍ አይደለም፡፡ 

በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ወቅትም፣ ተገቢው ምርመራ ከተደረገ በኋላ ተሸላሚውና የማይሸለመው ተወዳዳሪ ማን እንደሆነ ይፋ የሚሆንበት እንጂ አማኞች ስለሰሩት ኃጢአት ቅጣት የሚቀበሉበት ጊዜ አይደለም፡፡ ጉዳዩ በዚህ መንገድ ካልታሰበ፣ ከተጠናቀቀው ከክርስቶስ የመስቀል ሥራ ጋር የሚጋጭ ሃሳብ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም እርሱ የኃጢአታችንን ዋጋ ሁሉ ከፍሏልና፡፡

ኃጢአትን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ትምሕርት፣ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነ ሁሉ በፀጋው አማካኝነት ከፍርድ ነፃ መሆኑን ነው (ዮሐ. 3፡18፣ 5፡24፣ 6፡37፣ ሮሜ. 5፡1፣ 8፡1፣ 1ቆሮ. 11፡32)፡፡ ክርስቶስ የአማኙ ፍፁም ተለዋጭ/ቤዛ ስለሆነ አማኙ ካለፈ፣ ከአሁንና ከወደፊት ጊዜ የኃጢአት (ቆላ 2፡13) ፍርድ ሁሉ ነፃና በክርስቶስ በመሆኑ እንደ ክርስቶስ ያለ ነውር ሆኖ በእግዚአብሔር ፊት ይታያል (1ቆሮ. 1፡30፣ ኤፌ. 1፡6፣ ቆላ. 2፡10፣ ዕብ. 10፡14)፡፡ አማኝ፣ ክርስቶስ በእግዚአብሔር እንደ ተወደደ እንዲሁ የተወደደ ነው (ዮሐ. 17፡23)፡፡

የ ቤማ ጊዜ

ይህ የሚሆነው፣ የቤተ ክርስቲያን መነጠቅ ወይም ትንሳኤን ተከትሎ ጌታን በአየር ለመቀበል በደመና ከተነጠቅን በኋላ ነው (1ተሰ. 4፡13-18)፡፡ 

ይህን አመለካለት በመደገፍ የሚሰጡ ምክንያቶች፡- 

በሉቃስ 14፡12-14፡- መሠረት ሽልማት፣ የቤተ ክርስቲያን ትንሳኤና መነጠቅን ተከትሎ የሚሆን ነገር ነው፡፡

ራዕይ 19፡8፡- ከታላቁ መከራ ፍጻሜ በኋላ ጌታ ከሙሽሪት ጋር ሲመለስ የተሸለመች ሆና እንደምትመጣ ያሳያል፡፡ ሽልማቱም እንደ ቀጭን የተልባ እግር (እርሱም የቅዱሳን የጽድቅ ስራ) ሆኖ ተገልጧል፡፡ ይህ፣ ያለ ጥርጥር የሽልማት ውጤት

እንደሆነ ያሳያል፡፡ 

2ጢሞ. 4፡18 እና 1ቆሮ. 4፡5፡- ሽልማቶች ከ ‹ያን ቀን› እና ከ ‹ጌታ መምጣት› ከሚሉ ሐረጎች ጋር ተያይዘው ቀሪበዋል፡፡ 

ለቤተ ክርስቲያን ይህ ጊዜ ማለት የ 1ተሰ. 4፡13-18 ተዕይንት ጊዜ ማለት ነው፡፡ የትዕይንቱ ቅደም ተከተል ይህን ይመስላል፡- (1) መክበራችንንና የትንሳኤ አካል መልበሳችንን የሚያበስረው መነጠቅ፣ ከዛም (2) በሰማያት ከጌታ ጋር ከፍ ማለት፣ በመቀጠልም (3) በ bema ፊት መመርመርና፣ በመጨረሻም (4) ሽልማቶችን ማግኘት ይሆናል

ማለት ነው፡፡ 

የ ቤማ ስፍራ

ይህ ትዕይንት በጌታ መገኘት፤ በሰማያዊ ስፍራ የሆነ ቦታ ላይ ይፈጸማል፡፡ 1ተሰ. 14፡17፣ ራዕ. 4፡2 እና 19፡8 ይመልከቱ፡፡

በ ቤማ ተሳታፊ የሚሆኑት

ከ ቤማ ጋር ተያያዥ የሆኑ ጥቅሶች ሁሉ የሚያወሱት በዚህ ስፍራ ላይ የሚገኙት አማኞች ናቸው (ሮሜ. 14፡10-12፣ 1ቆሮ. 3፡12፣ 2ቆሮ. 5፡9፣ 1ዮሐ. 2፡29፣ 1ተሰ. 2፡19-20፣ 1ጢሞ. 6፡18-19፣ ቲቶ 2፡12-14 (ለመልካም ምግባር የተሰጠውን ትኩረት አስተውል)፡፡

የትንሳኤ ፕሮግራም እና የብሉይ ኪዳን ቅዱሳት ሽልማት የሚሆነው ከታላቁ መከራ በኋላ፣ ቅዱሳን በሰማያት ከታዩና ከተሸለሙ በኋላ ከዛም ከጌታ ጋር ሊገዙ ወደ ምድር ከመጡ በኋላ ይሆናል (ራዕ. 19፡8ን ከ ዳን. 12፡1-2 እና ማቴ. 24 ጋር በጋራ ይመልከቱ)፡፡

በየትኛውም መንፈሳዊ ሁኔታ ውስጥ ያሉ አማኞች ሁሉ በ ቤማ ፊት ስለ ሕይወታቸው ምላሽ ይሰጡ ዘንድ እንደ ስራቸው መጠንም ዋጋን ይቀበሉ ወይም ያጡ ዘንድ ይቀርባሉ፡፡ አንዳንድ የከፊል መነጠቅ አስተምህሮ ተከታዮች እንደሚያስቡት፣ በመነጠቅ ሂደት የሚተባበሩት ከጌታ ጋር ሕብረት ያላቸው ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው፡፡ ይህም የሚሆነው በተቀሩት ክርስቲያኖች ላይ የኃጢአት ቅጣት ለማስተላለፍ ነው ይላሉ፡፡ ከላይ እንደ ተመለከትነው ይህ ሃሳብ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለኃጢያታችን ዋጋ ከከፈለው ከክርስቶስ የመስቀል ስራ ጋር የሚጣረስ ብቻ ሳይሆን ከ 1ተሰ. 5፡8-11 ትምሕርትም ጋር ይቃረናል፡፡… እግዚአብሔር ለቁጣ አልመረጠንምና፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መዳንን ለማግኘት ነው እንጂ፡፡

የዚህ ክፍል አውድ የሚያሳየን ጳውሎስ፣ የጌታን ዳግም መመለስ እና የቤተ ክርስቲያንን መነጠቅ ትኩረቱ አድርጎ እንደጻፈ ነው (1ተሰ 4፡13-18)፡፡ መነጠቅ፣ ጳውሎስ በ 1ተሰ. 5፡1-3 ላይ እነደ ገለፀው ከእግዚአብሔር ቁጣ የምንድንበት መንገድ ነው፡፡ በተጨማሪም በቁጥር 10 ላይ የተገለፁት መንቃት እና ማንቀላፋት የሚሉት ቃሎች መንፈሳዊ ወይም ሞራላዊ ሁኔታን የሚያመለክቱ እንጂ በ 4፡13-14 ላይ እንደተገለፀው ክርስቶስ በሚመጣበት ወቅት በሕይወት ያሉ ወይም የሞቱ ሰዎችን ሁኔታ አያመለክትም፡፡ የዚህን እውነታ ከ 5፡4-8 አውድ እና ለመተኛት ከተጠቀመበት ቃሎች መለወጥ አንፃር መረዳት እንችላለን፡፡ በ 5፡10 ላይ koimao የሚለውን ቃል ሳይሆን Katheudo የሚለውን የግሪክ ቃል ተጠቅሟል፡፡ ይህን በ 4፡13-14 ላይ ከተገለፀው አካላዊ ሞት ጋር ዘይቢያዊ ትስስር እንዲኖረው አድርጓል፡፡ ምንም እንኳን Katheudo የሚለው ቃል (5፡10 ላይ የተገለጸው) አካላዊ እንቅልፍና ሞትንም ጭምር የሚያሳይ ቢሆንም ከመንፈሳዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ መልኩ ከመንፈሳዊ ደንታ ቢስነት ወይም ከሥጋዊ ስሜት አልባነት/ባዶነት ጋር በተያያዘ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ይህ ነው እንግዲህ የምዕራፍ 5 አውድ፡፡ እንግዲያው ዋናው ቁም ነገር የሚከተለው ይሆናል፡- በክርስቶስ ፍፁምና የተጠናቀቀ ሞት ባህሪ ምክንያት (ቁጥር 10 ላይ ያለውን ስለ እኛ ሞተ ለሚለው ሃሳብ ትኩረት ሰጥተው ይመልከቱ) መንፈሳዊ ሁኔታችን ንቁም ይሁን አይሁን ሁላችን አብረን ከእርሱ ጋር ለመኖርና በ ቤማ ፊት ስለ ሕይወታችን መልስ ለመስጠት እንነጠቃለን፡፡ 

በ ቤማ ያለው መርማሪ ወይም ፈራጅ 

ይህ ፈራጅ አሁን ባለው ሕይወት አንኳ ሳይቀር ሥራችንን ወደ ብርሃን እያወጣ ጉዟችን ከእውነት ስለመሆኑ እየመረመረ ያለው ኋላም በ ቤማ ፊት ስንገኝ ይህንኑ የሚያደርገው ኢየሱስ ብቻ ነው (ራዕ. 1-2፣ 1ቆሮ. 4፡5፣ 2ቆሮ. 5፡10፣ 1ዮሐ. 2፡28)፡፡ በሮሜ. 14፡10 ላይ ይህንን የምርመራ ወቅት ሐዋርያው የ እግዚአብሔር ቤማ ሲለው በ2ቆሮ. 5፡10 ላይ ደግሞ የክርቶስ ቤማ ብሎ ይገልፀዋል፡፡ ሁለቱን ሃሳቦች አጋጥሞ በማየት እግዚአብሔር የሆነው ኢየሱስ መርማሪያችንና ሸላሚያችን ነው የሚለውን ቁም ነገር ማግኘት እንችላለን፡፡

የ ቤማ አላማና መሰረተ ሃሳብ

የ ቤማ አላማና መሰረት ሃሳብ፣ ከሃሳቦቹ ሁሉ ዋና እና ከ ቤማ ተግባራዊ አተያይ ጋር ፊት ለፊት እንድንገናኝ የሚያደርገን ይሆናል፡፡ በዚህ ረድፍ ስር ከሚነሱት አበይት ጥያቄዎች መካከል፡- ለምንድን ነው በ ቤማ ፊት የምንቀርበው? ለሽልማት ብቻ ነው ወይስ ማጣትም አለው? የቅጣት ብይን ይሰጥበታል? ታላቅ ሐዘንስ ይኖራል? ቤማ ተግባራዊ የሚሆንበት መሰረት ምንድን ነው? በኃጢአት ላይ ተመስርቶ ነው? ወይስ በመልካም ተግባራችን ላይ? ወይስ በሌላ? የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡

ችግሩ፡- በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቤማን በተመለከተ ትንሽ የማይባሉ ንትርኮችና ግራ መጋባቶች አሉ፡፡ ‹‹የፍርድ ወንበር›› የሚለው ቃል ትርጉም፣ የቃሉን ታሪካዊና ባህላዊ ዳራ ጠንቅቆ ካለማወቅና የክርስቶስን የተጠናቀቀ የመስቀል ስራ በብዥታ ከተመለከተ የስነ-መለኮት አስተምህሮ በመነሳት በተዛባ መልክ ይቀርባል፡፡ ይህም አስተሳሰብ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ይህ ትዕይንት (ቤማ) እግዚአብሔር ቢያንስ ላልተናዘዝነው ኃጢአት አልያም ለኃጢአታችን ተገቢውን ቅጣት የሚሰጥበት ስፍራ እንደሆነ እንዲገነዘቡ አድርጓቸዋል፡፡

ቤማን በተመለከተ 3 ምልከታዎች፡-

የሦስቱ ምልከታዎች ማጠቃለያ ሃሳብ በአጭሩ ለማቅረብ የሳሙኤል ሆይትን አባባል ከ bibliotheca sacra ላይ እንጠቅሳለን፡፡ 

አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች፣ የፍርድ ወንበርን – ከአስጨናቂ መከራ ቦታ እና ከፍርሀት ስፍራ ጋር ከማዛመዳቸው በተጨማሪ ክርስቶስ የእያንዳንዱን አማኝ ኃጢአቶች (ቢያንስ ኑዛዜ ያልቀረበባቸውን) በትንሳኤ በተባበረችውና በተነጠቀችው ቤተ ክርስቲያን ፊት የሚገልጥበት ስፍራ አድርገው ይቆጥራሉ፡፡ አንዳንዶች እንደውም ከዚህ አልፈው፣ በዚህ የምርመራ ወቅት ክርስቲያኖች ስለ ኃጢአታቸው የተወሰነ መከራን ይቀበላሉ ሲሉም ይደመጣሉ፡፡ 

በሌላ አንፃር፣ ሌላው ቡድን ይህንን ትዕይንት የሽልማት ሥነ ሥርዐት ወቅት አድርጎ ያቀርባል፡፡ ሽልማት ለእያንዳንዱ ክርስቲያን ይሰጣል፡፡ የዚህ ፍርድ ውጤት፣ ይላሉ እነዚህ ቡድኖች፣ እያንዳንዱ አማኝ ባገኘው ሽልማት አመስጋኝ ይሆናል፤ በተጨማሪም ጥቂት እፍረት ያጋጥመዋል ወይንም ከነጭራሹ አያጋጥመውም፡፡ 

ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች ደግሞ ማዕከላዊውን ስፍራ በመያዝ፣ ለምርመራው ጊዜ ከባድነት ተገቢ ስፍራ በመስጠት፣ የፍርድ ቀኑ ያለውን የሽልማት አላማ ያንፀባርቃሉ፡፡ በዚህ ምድር ላይ ታማኝ ሆኖ ስለ መኖር አስፈላጊነትና ጠቃሚነት ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ ሆኖም በ ቤማ ወቅት በአማኞች ላይ አለ ተብሎ በሚታሰበው የቅጣት ሀሳብ አይስማሙም፡፡ ‘እያንዳንዱ አማኝ ሁሉን በሚያውቅ ቅዱሱ ክርስቶስ ፊት ስለ ሕይወቱ መልስ ይሰጣል’- ለሚለው አስተሳሰብ ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ በሥጋ ኃይል የተሰራ ሥራ ሁሉ ዋጋ የሚያሳጣ ሲሆን በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የተሰሩ ሥራዎች ሁሉ ግን ሽልማት የሚያስገኙ ናቸው ይላሉ፡፡ ይህንን አስተሳሰብ የሚጋሩ ቡድኖች፣ ክርስቲያን አስቀድሞዉኑ ፃድቅ ተደርጎ ስለተቆጠረ ያለ ምንም ኩነኔ በክርስቶስ ፊት መቆም ይችላል ይላሉ፡፡ ክርስቶስ የአማኞችን ኃጢአት ሁሉ ተሸክሟልና ምንም አይነት ቅጣት/ፍርድ ለአማኞች አይገባም የሚለውንም ሃሳብ ያሰምሩበታል፡፡ 

ይህን መጨረሻ ላይ የቀረበው አመለካከት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጠቅላላ ሀሳብ ጋር የሚዛመድ ነው ብለን እናምናለን፡፡ የ ቤማን አላማ መሠረተ ሃሳብ ባሕሪ ስናጠና የዚህን ሀሳብ ዋቤዎች እንመለከታለን፡፡ ለአሁኑ ግን የተሳሳተ ማጠቃለያ ላይ እንዳንደርስ ይረዳን ዘንድ የእግዚአብሔር ቃል፣ ኃጢአት ወይም አለመታዘዝ ስለ ሚያስከትለው ጊዜያዊና ዘላለማዊ ከባድ ውጤቶች በግልፅ እንደሚናገር ማስገንዘብ እንወዳለን፡፡ ክርስቶስ ኃጢአታችንን ሁሉ ስለ ተሸከመልን በ ቤማ ፊት አማኝ የሚቀበለው የኃጢአት ቅጣት ባይኖርም ክርስቲያኖች ለኃጢአት አነስተኛ ግምት ሊሰጡ ፈፅሞ አይገባም፡፡ ምክንያቱም ኃጢአት ከባድ ውጤቶች አሉትና፡፡ 

ኃጢአት ወይም አለመታዘዝ የሚያስከትለው የአሁን ጊዜ ውጤት 

ከዚህ በታች ያለው ዝርዝር ሁሉን ያጠቃለለ ባይሆንም ኃጢአት በአማኙ ሕይወት ውስጥ የሚናቅ ነገር አለመሆኑን በከፊል ያሳያል፡፡

1. ከጌታ ጋር ያለንን ሕብረት ያሳጣናል፡፡ በአንድ ሰው ውስጥ ያለ የታወቀ ኃጢአት ከጌታ ጋር ያለውን የቅርብ ግንኙነት ያውካል፤ የግለሰቡን ደስታና ሰላምን ያጠፋል (መዝ. 32፡3-4)፡፡

2. ከጌታ የሆነ መለኮታዊ ዲሲፕሊን/ሥነ ስርዓት መማር፡፡ የሥነ ስርዓት ትምሕርትን እንደ ቅጣት ማየት የለብንም፡፡ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ስነ ስርአት የማስያዝ ትምሕርት አብ ልጆቹን ለማሰልጠን እና ለማሳደግ የሚጠቀምበት መልካም መንገድ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር በፈተና፣ በመከራ፣ በውድቀት፣ በአስቸጋሪ ሁኔታና በመሳሰሉት ሁኔታዎች ያሰለጥነናል፡፡ በግትርነታችን መቀጠል ስንፈልግ ስቃይና መከራችን እያደገ እንዲመጣ ይፈቅዳል፡፡ የዚህ ሁሉ አላማው ደግሞ እኛን ወደ እርሱ መመለስ ነው (ዕብ. 12፡5-11)፡፡ አማኙ ባለመናዘዝ ፀንቶ ከኖረ እንደ አናንያ እና ሰፒራ (ሐዋ. 5) እንዲሁም በቆሮንቶስ እንደነበሩ አንዳንድ ኃጢአታቸውን መናዘዝ እምቢ እንዳሉ አማኞች ሞትን ሊቀምስ ይችላል (1ቆሮ. 11፡28 እንዲሁም 1ዮሐ. 5፡16-17)፡፡

3. ኃይልና ፍሬያማነትን ማጣት፡፡ ኃጢአታችንን በእውነተኛ ልብ መናዘዝ ስናቆም በውስጣችን ያለውን መንፈስ እናጠፋለን፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በእምነት በእግዚአብሔር አቅርቦት መኖር አቁመን በሥጋ ኃይል መኖር እንጀምራለን ማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር፣ በሥጋችን ማስተዋል ሕይወትን ወደ መምራት ዘወር እንላለን (ገላ. 3፡1-5፣ 5፡5፣ ኤር. 2፡12-13) የዚህ ውጤቱ ደግሞ የሥጋ ፍሬና ፍሬቢስ መዘዙ ይሆናል (ገላ. 5፡19-21.26)፡፡ የእምነትና የመታዘዝ ሕይወት ደግሞ በእርሱ ውስጥ ከመኖር (ከሕብረት) ውጪ የማይታሰብ ነው (ዮሐ. 15፡1-7)፡፡

4. ከአጋጣሚዎች ጋር መተላለፍ፡፡ ሕይወታችንን የሚመራው ጌታ ሳይሆን ራሳችን በሚሆንበት ወቅት፣ ስለ ሰዎችና ስለ አገልግሎት አጋጣሚዎች ግዴለሾች እንሆናለን- ራዕይ እናጣለን፡፡ ሥጋዊ አማኞች የራሳቸውን አጀንዳዎች ከማሟላትና የግላቸውን ግቦች ከመምታት ውጪ ሌላ ራዕይ አይኖራቸውም (ዮሐ. 4፡34)፡፡

5. ለአገልግሎት መነሳሳትና ፍላጎት ማጣት፡፡ ሥጋዊ አማኞች በራሳቸው የግል ፍላጎቶች ቁጥጥር ስር ያሉ ናቸው (ገላ. 5፡16)፡፡ እስቲ ስለ ራስ ወዳድነት ጥቂት እንበል፡፡ ዜን ሆገስ ራስ ወዳድነትን አስመልካቶ የሚለው ነገር አለ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ራሳችን ደስታና መልካም ነገሮች ግድ እንዳይኖረን አያስተምረንም፡፡ ፈንጠዝያዎችና እርካታዎች ሕገወጥ ድርጊቶች አይደሉም፡፡ እግዚአብሔር አዳምንና ሔዋንን በኤድን ገነት ሲያኖራቸው ‹‹ለማየት ደስ የሚያሰኘውን፣ ለመብላትም መልካም የሆነውን ዛፍ …›› ሁሉ አብቅሎላቸው ነበር (ዘፍ. 2፡9)፡፡ ከተከለከለው የዛፍ ፍሬ በቀር በሌላው ፍሬ ሁሉ መደሰት ይችሉ ነበር፡፡ ጳውሎስም በተመሳሳይ በ 1ጢሞ. 6፡17 ላይ እንዲህ ይለናል፡፡ እግዚአብሔር ‹‹ደስ እንዲለን ሁሉን ነገር አትርፎ …›› ይሰጠናል፡፡ ራስ ወዳድነት የራስን ጥቅም በማስጠበቅ መልኩ ሊበየን አይገባም፡፡ ነገር ግን ራስ ወዳድነት ማለት የራሱን ጥቅም በእግዚአብሔር መንገድ ከማስፈፀም ይልቅ በራስ መንገድ ማስፈፀምን ያመለክታል፡፡ ‹‹ፍቅር›› ከሁሉ የሚልቅ የክርስትና ምግባር እንደ መሆኑ መጠን እውነተኛ ራስ ወዳድነት ይህንን የፍቅር ህግ በመጣስ የሚደረግ የራስን ጥቅም የማስጠበቅ መንገድ ነው፡፡

በእግዚአብሔር መንገድ የራስን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚደረግ ጥረት፣ ሕጋዊ ነው፡፡ ራስ ወዳድነት የሌሎችንና የእግዚአብሔርን ፈቃድ ጨፍልቆ በራስ ጉዳይ ላይ ብቻ መጠመድን ያመለክታል፡፡ አዳምና ሔዋን መልካምንና ክፉን ዛፍ ለመብላት በወሰኑ ጊዜ የተንቀሳቀሱበት አነሳሽ ምክንያት ራስ ወዳድነትና በእግዚአብሔር ላይ ያለመደገፍ ዝንባሌ ነበር፡፡ ይህም የጣኦት አምልኮና ሐጢአት ይባላል፡፡ በተቀሩት የዛፍ ፍሬዎች እየተደሰቱ በነበሩበት ወቅት ደግሞ በእርሱ ላይ በመደገፍና በመታዘዝ ሆነው የራሳቸውን ጥቅም ያስጠብቁ ነበር፡፡

6. የተቋረጠ ሕብረትና የተስተጓጎለ ግንኙነት፡፡ ሥጋዊነት፣ በአካባቢያችን አብረውን ከሚኖሩ ቤተሰቦቻችን፣ ጓደኞቻችን፣ እና አብረውን የክርስቶስን አካል ከሚያገለግሉ አማኞች ጋር የተበላሸና ስቃይ ያለው ሕብረት እንድንገፋ ያደርገናል (ገላ. 5፡15፣ ዕብ. 12፡15)፡፡

7. ጤና ያሳጣል፤ ከፍተኛ ጥንካሬና ወኔን ይሰልባል፡፡ እርግጥ ነው ሁሉም ህመም፣ ድካምና ስቃይ የኃጢአት ውጤት ሊሆን አይችልም፤ አይደለምም፡፡ ሆኖም አንዳንድ ጊዜ የኃጢአት ውጤትም ሊሆኑ ይችላሉ (1ቆሮ. 11፡29-30፣ 1ዮሐ. 5፡16-17፣ ምሳሌ 17፡22፣ 14፡30)፡፡

8. በ ቤማ ወቅት ሽልማት ማጣትን ያስከትላል፡፡ 1ቆሮ. 3፡13-15 ‹‹የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል፤ በእሳት ስለ ሚገለጥ የ ቀን ያሳያልና፣ የእያንዳንዱም ሥራ እንዴት መሆኑን እሳቱ ይፈትነዋል፡፡ ማንም በእርሱ ላይ ያለጸው ሥራ ቢጸናለት ደመዎዙን ይቀበላል፤ የማንም ሥራ የተቃጠለበት ቢሆን ይጎዳበታል፣ እርሱ ራሱ ግን ይድናል፣ ነገር ግን በእሳት እንደሚድን ይሆናል››፡፡

የ ቤማ ዓላማ

ቤማ ለቅጣት የታለመ አይደለም፡፡ የተናዘዝነውም ሆነ ያልተናዘዝነውን የእኛን የአማኞችን ኃጢአት የመቅጣት አላማም አላነገበም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የኃጢአተኛውን ኃጢአት በተመለከተ እግዚአብሔር አንዴ፣ ለዘላለም የራሱን ፍትህ በመስቀሉ ላይ መግለጡን ያስተምረናል፡፡ እግዚአብሔር፣ ኢየሱስ ለአማኙ የከፈለውን የኃጢአት ዋጋ ከተቀበለ በኋላ እንደገና አማኙም እንዲከፍል የሚጠይቅ ከሆነ ለኃጢአት ሁለት ዋጋ እየጠየቀና ኢ-ፍትሀዊ እየሆነ ነው ማለታችን ነው፡፡ ቤማ ለቅጣት የታለመ ነው የሚለው ሃሳብ በቂና ሙሉ የሆነውን የክርስቶስን የመስቀል ስራ ፈፅሞ ይቃረናል፡፡ ክርስቶስ ለአማኙ ያለፈ፣ የአሁንና የወደፊት ኃጢአት ዋጋ ከፍሏል፡፡ አማኙ ሊቀበለው ይገባው የነበረውን ሽልማት ሊያጣ ይችላል እንጂ ለኃጢአቱ ዋጋ በመክፈል አንፃር አይቀጣም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረን ኃጢአት ሁሉ፣ የተናዘዝናቸውም ሆነ ያልተናዘዝናቸው፣ በክርስቶስ የመስቀል ስራ አማካኝነት ይቅር እንደተባለልንና፣ አማኝ በፍርድ ቀን ስለ ኃጢአቱ የቅጣት ዋጋ እንደማይከፍል ነው፡፡

ቁልፍ ጥቅሶች፡- የሚከተሉት ጥቅሶች የተሟላና የተጠናቀቀውን የክርስቶስን ስራ ባህሪ የሚገልፁ ናቸው፡፡

ዕብራዊያን 10፡14 አንድ ጊዜ በማቅረብ የሚቀደሱትን የዘላለም ፍጹማን አድርጎአቸዋልና፡፡

ሮሜ 5፡19 በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደ ሆኑ፣ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ፡፡

ቆላሲያስ 2፡10 (አ.መ.ት.) እናንተም የገዥነትና የሥልጣን ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ሙሉ ሆናችኋል፡፡

የሚከተሉት ጥቅሶች ደግሞ ፍፁም የሆኑ ውጤቶችና ማጠቃለያዎችን ያበስራሉ፡ 

ዕብራዊያን 8፡12 ዓመፃቸውን እምራቸዋለሁና፣ ኃጢአታቸውንም ደግሜ አላስብም፡፡

ዕብራዊያን 10፡17-18 … ኃጢአታቸውንና ዓመጻቸውንም ደግሜ አላስብም ይላል፡፡ የእነዚህም ስርየት ባለበት ዘንድ፣ ከዚህ ወዲህ ስለ ኃጢአት ማቅረብ የለም፡፡

ኢሳይያስ 44፡22 መተላለፍህን እንደ ደመና፣ ኃጢአትህንም እንደ ጭጋግ ደምስሼአለሁ፤ ተቤዥቼሃለሁና ወደ እኔ ተመለስ፡፡

ኢሳያስ 38፡17 እነሆ፣ ታላቅ ምሬት ለደኅንነቴ ሆነ፤ አንተም ነፍሴን ከጥፋት ጕድጓድ አዳንሃት፣ ኃጢአቴንም ሁሉ ወደ ኋላህ ጣልህ፡፡ 

የሚከተሉት ጥቅሶች ደግሞ ወደ ፍርድ እንደማንመጣ ያሳያሉ፡፡ ለምን? ምክንያቱም ክርስቶስ በእኛ ፈንታ ኃጢአታችንን በመሸከም እርግማን ሆኖልናልና፡፡

ሮሜ 5፡1 እንግዲህ በእምነት ከጸደቅን በእግዚአብሔር ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እንያዝ፤

ሮሜ 8፡1 እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም፡፡

ዮሐንስ 3፡18 በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል፡፡

ዮሐንስ 5፡24 እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፣ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም፡፡

ጥያቄ፡– ታዲያ በምድር የሕይወታችን ዘመን ለምን ስለ ኃጢአታችን እንናዘዛለን? ለምንድን ነው እግዚአብሔር በሃናንና ሰፒራ (ሐዋ. 5) እንዲሁም በአንዳንድ የቆሮንቶስ አማኞች በኑዛዜ ያልቀረቡ ኃጢአቶች (1ቆሮ. 11፡28) ላይ ፍርድ ያሳለፈው?

መልስ፡- ይህ ጉዳይ አሁን ከምናወራው ጉዳይ ጋር ፈፅሞ አይገናኝም፡፡

1. በኑዛዜ ያልቀረበ ኃጢአት፣ ግንኙነቱ አሁን በዚህ ምድር ላይ ካልን ሕብረት ጋር እንጂ በእግዚአብሔር ፊት ካለን የመታየት መብት ጋር አይደለም፡፡

ያልተናዘዝነው ኃጢአት ጌታ ከእኛ ጋር በሚያደርገው ሕብረት ላይ ጥላውን ያጠላል (እንቅፋት ይሆናል)፡፡ ሕይወታችንን ጌታ እንዳይቆጣጠረውም እክል ይሆናል፡፡ አሞጽ 3፡3 ላይ እንዲህ ይላል ‹‹በውኑ ሁለት ሰዎች ሳይስማሙ በአንድነት ይሄዳሉን?›› ምላሹ ‹‹ፈጽም›› የሚል ይሆናል፡፡ መናዘዝ ማለት ኃጢአታችንን በተመለከተ ከእግዚአብሔር ጋር መስማማትና በእግዚአብሔር ቁጥጥር ስር ለመሆን መመለስ ማለት ነው፡፡ በክርስቶስ ባመንበት ቅፅበት የተደረገልን አንዴ ለዘላለም በሆነው የኃጢአት ይቅርታ ( ማለትም በክርስቶስ ሆነን እግዚአብሔር ፊት ለመቅረብ ጻድቅ ሆነን በተቆጠርንበት) እና ሕብረት ከማድረግ አንጻር በየእለቱ በሚደረግልን የኃጢአት ይቅርታ መካከል ያለውን ልዩነት ጠንቅቀን ልናውቅ ይገባል፡፡ በየዕለቱ ያለንን ሕብረት ለማደስ የሚደረግ የኃጢአት ይቅርታና በክርስቶስ ውስጥ በመሆን በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም ብቃት ያገኘንበትን ይቅርታ ለይተን ማወቅ ይኖርብናል፡፡ 

ቁልፍ ጥቅሶች፡- ዕብ. 12፡5 እና 1ቆሮ. 11፡28-32 ይህ ክፍል እግዚአብሔር በምድር ላይ በአማኞች ላይ የሚያደርገውን የፍርድ ባህሪ ይገልፃል፡፡ ይህ፣ አማኞች ከሳቱበት ተመልሰው ዳግመኛ ከእግዚአብሔር ጋር ለመጓዝ ይችሉ ዘንድ እንዲሰለጥኑ ለማድረግ እግዚአብሔር የሚወስደው ስርአት የማስያዝ (የዲሲፕሊን) ቅጣት ነው፡፡ እነዚህ ጥቅሶች ስነ ስርዐት የማስያዝ ቅጣቶች፤ የተገለጡ ኃጢአቶችን ሳይናዘዙ ወደጎን የማድረግ ውጤቶች እንደሆኑ ያስተምሩናል፡፡ ኃጢአቶች ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ሕብረት ያውካሉና፡፡ ‹‹በተፈረደብን ጊዜ ከአለም ጋር እንዳንኮነን…›› (1ቆሮ. 11፡32) የሚለው ሀሳብ በሮሜ 1፡24 ላይ ከሰፈረው ሃሳብ ጋር የበለጠ አብሮ የሚሄድ ሲሆን ይህም ሰዎች ከእግዚአብሔር ፊታቸውን ባዞሩ መጠን የሚደርስባቸውን የሞራል ዝቅጠትና በሂደትም የሚደርስባቸውን ውድቀት ያመለክታል፡፡ ተመሳሳይ ነገር በአማኝ ሕይወትም ውስጥ ይከሰታል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ሂደቱ እንዳይከሰት የአማኙን ሕይወት ስነ ስርዐት ለማስያዝ ይቀጣል፡፡

2. ለሰራነው ኃጢአት ዋጋ በመክፈል አኳያ እግዚአብሔር በኃጢአታችን ላይ አይፈርድም፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ፣ እግዚአብሔር በአማኙ ሕይወት በተደረገው ኃጢአት ላይ ያለውን ቁጣ ለመመለስ የክርስቶስ ሞት ፍፁምና ሙሉ እንደሆነ ያስተምረናል፡፡ በልጁ ሙሉና ፍፁም መስዋዕት አማካኝነት እግዚአብሔር በኃጢአት ላይ የነበረው የፍትህ ጥያቄ በሙላት ተመልሷል፡፡ አማኙ በኃጢአቱ ምክንያት ከሚያገኘው ቅጣት በክርስቶስ የምትክ አገልግሎት ወይም ቤዛነት አምልጧል፡፡ እዳውም በክርስቶስ ደም ተከፍሏል፡፡ አማኙ በክርስቶስ ሆኖ ለፍርድ ቀርቧል፣ ተፈርዶበታል፣ ተቀጥቷልም፡፡

ቤዛነት ተከፍሏልና እግዚአብሔር ሁለተኛ ቤዛ አይጠብቅም፡፡ እግዚአብሔር አማኙን በክርስቶስ የፅድቅ ልብስ ተሸፍኖ ይመለከተዋል፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር በአማኙ ሕይወት ውስጥ ሊነቅፈው የሚችለውን ሕጸጽ ሊያገኝ አይችልም፤ ክርስቶስን ለብሷልና፡፡ ስለዚህ በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት አማኝ ስለ ኃጢአቱ አይቀጣም፤ ስለ ኃጢአቱም ወደፊት የሚከፍለው ዋጋ አልቀረለትም፡፡

በዚህ ምድር ላይ አማኝ ላይ የሚደርሰው ቅጣት፣ የፍርድ ጉዳይ ሳይሆን የቤተሰብ ጉዳይ ነው፡፡ አባት ልጁን ለማረም እንደሚቀጣ ሁሉ እግዚአብሔር የልጁን መልክ እንመስል ዘንድ ለጥቅማችን ይቀጣናል/ስነ-ስርዓት አስይዘናል፡፡

የ ቤማ አወንታዊ ገፅታ 

የ ቤማ አወንታዊ ገፅታ፣ የአማኝ ተግባር (ሥራ) መልካም መሆን አለመሆኑን ማለትም ተቀባይነት ያለውና ለሽልማት የሚያበቃ መሆን አለመሆኑን፣ ወይም የሚጣል ፍሬ ቢስና ለሽልማት የማያበቃ መሆን አለመሆኑን፣ የመለየትን ሥራ የያዘ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ምዘና በጌታ በየዕለቱ እየተከናወነ ነው (ዕብ. 3፡3)፡፡

በእንጨት፣ ገለባና አገዳ የተመሰሉት እና በእሳት ተፈትነው የማያልፉት የአማኙ ተግባራት ይቃጠላሉ፡፡ ማንኛውም የኃጢአት ተግባር፣ ሃሳብ፣ አነሳሽ ምክንያት እንዲሁም በሥጋ ጉልበት የተሰሩ ማናቸውም መልካም ተግባራት ሁለ እሳት እንጨትን፣ ገለባንና አገዳን እንደሚበላ እንዲሁ በእሳት ይበላሉ፡፡ ምክንያቱም ለሽልማት የሚያበቁ ተግባራት አይደሉምና፡፡ ለምን? የዚህን ምላሽ ሽልማት የሚሰጥበትን ወይም የሚታጣበትን መመዘኛ ስንመለከት ኋላ ላይ እናየዋለን፡፡ በወርቅ፣ ብርና የከበረ ድንጋይ የተመሰሉት እና በእሳት ተፈትነው የሚያልፉት የአማኙ ተግባራት ይሸለማሉ፡፡ ይህ ለሽልማት የተገባ ነውና፡፡

ጥቅሶች፡- 

1ቆሮ. 3፡13-15 ‹‹የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል፤ በእሳት ስለ ሚገለጥ የ ቀን ያሳያልና፣ እያንዳንዱም ሥራ እንዴት መሆኑን እሳቱ ይፈትነዋል፡፡ ማንም በእርሱ ላይ ያለጸው ሥራ ቢጸናለት ደመዎዙን ይቀበላል፤ የማንም ሥራ የተቃጠለበት ቢሆን ይጎዳበታል፣ እርሱ ራሱ ግን ይድናል፣ ነገር ግን በእሳት እንደሚድን ይሆናል››፡፡ 

‹‹ይገለጣል›› ማለት phaneros ማለት ሲሆን፣ ትርጓሜውም ‹‹የታወቀ፣ ግልጥ፣ የሚታይ፣ ይፋ›› ማለት ነው፤ ‹‹ያ ቀን›› የሚለው ሀረግ የሚያመለክተውም ከቤተ ክርስቲያን መነጠቅ በኋላ የሚሆነውን የ ቤማ ጊዜ ነው፡፡ ‹‹ይፈትነዋል›› ማለት dokimaze ማለት ሲሆን ትርጓሜውም ‹‹ዕውቅና ለመስጠት መመዘንን›› ያመለክታል፡፡

1ቆሮ 4፡5 «ስለዚህም በጨለማ የተሰወረውን ደግሞ ወደ ብርኀን የሚያወጣ፣ የልብንም ምክር የሚገልጥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ፣ ጊዜው ሳይደርስ አንዳች አትፍረዱ፤ በዚያን ጊዜም ለእያንዳንዱ ምስጋናው ከእግዚአብሔር ዘንድ ይሆናል፡፡›› 

ከላይ የቀረበው ጥቅስ ጌታ የእያንዳንዱን ሰው ሥራ ባህሪና ጥራት እንደሚመዝን በግልፅ ያሳያል፡፡ ይህንን እውነታ ከዚህ በታች ካለው ጥቅስ ጋር ያነፃፅሩ፡፡

2ቆሮ. 5፡10 «መልካም ቢሆን ወይም ክፉ እንዳደረገ፣ እያንዳንዱ በሥጋው የተሰራውን በብድራት ይቀበል ዘንድ፣ ሁላችን በክርስቶስ በፍርድ ወንበር ፊት ልንገለጥ ይገባናልና፡፡››

ራዕ. 22፡12 «እነሆ፣ በቶሎ እመጣለሁ፣ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ፣ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ፡፡››

የ ቤማ አሉታዊ ገፅታ

የ ቤማን አሉታዊ ገፅታዎች የሚያሳዩ፣ ሊብራሩ የሚገባቸው በርካታ ጥቅሶች አሉ፡፡ በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ፣ ‹‹ይጎዳበታል፣ በስጋው የተሰራውን በብድራት ይቀበል ዘንድ ስለ ሰራው ሥራ መልስ ይሰጣል፣ እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን ፣ በእርሱ ፊት እንዳናፍር›› የሚሉ ሐረጋት ይገኛሉ፡፡ አማኞች በ ቤማ ጊዜ እፍረት፣ ሃዘን፣ ፀፀት ይሰማቸዋልን? የሚሰማቸው ከሆነ እንዴት አድርገን ነው እነዚህን ሀሳቦች ከሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ጋር የምናስማማቸው?

ራዕይ 7፡17 «… እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፡፡››

ራዕይ 21፡4 ‹‹…እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል…››

ኢሳይያስ 65፡17 ‹‹እነሆ፣ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እፈጥራለሁና፤ የቀደሙትም አይታሰቡም፣ ወደ ልብም አይገቡም/shall not be remembered፡፡››

አሉታዊ ገፅታው የሚከተሉትን ያካትታል፡-

በ1ቆሮንቶስ 3፡15 ላይ የተገለፀው ሀሳብ ሽልማት ማጣትን ያመለክታል እንጂ ድነት ማጣትን አያሳይም፡፡

በ1ቆሮንቶስ 9፡27 የተጠቀሰውም ሀሳብ ከሽልማት መጉደልን (disqualified) መሆንን እንጂ ከድነት መጉደልን አያመለክትም፡፡ ይህንን ከክፍሉ አውድና ከግሪኮች የአትሌቲክስ ጨዋታ ምስስሎሽ መገንዘብ ይቻላል፡፡

በ2ቆሮንቶስ 5፡10 ላይ የተገለፀው የብድራት ፍሬ ሃሳብም በሽልማት ስለሚታጣው ጉዳይ እንጂ ከድነት ማጣት ጋር አይዛመድም፡፡ (ከማቴዎስ 25፡27 እና ኤፌሶን 6፡8 ጋር አነፃፅር)

በዚሁ ጥቅስ (2ቆሮንቶስ 5፡10) ላይ የሰፈሩት የግሪክ ቃሎች – [‹‹መልካም›› (agathvs- መልካም ፍሬ፣ ዋጋ ያለው) እና ‹‹ክፉ›› (phaulos- የበሰበሰ ፍሬ የማይረባ)] – ጥቅሱ ስለ ሽልማት እንደሚያወራ የበለጠ አስረጂዎች ናቸው፡፡

ምሳሌ፡- ይህንን ጉዳይ፣ አንድ ተማሪ ባሳየው ደካማ ጥረት ምክንያት ከሚሰጠው ‹‹ኤፍ›› ወይም ‹‹ዲ›› ውጤት ጋር ማዛመድ እንችላለን፡፡ ደካማ ስራው ተገቢ የሆነ የውጤት ብድራትን እንዲቀበል ያደርገዋል፡፡ ይህ ውጤት ለስራው የሚገባ ነው፡፡

1ዮሐ. 2፡28 “አሁንም፥ ልጆች ሆይበሚገለጥበት ጊዜ እምነት እንዲሆንልን በመምጣቱም በእርሱ ፊት እንዳናፍር በእርሱ ኑሩ።” ይህ ጥቅስ ያለጥርጥር ስለ ቤማ ነው የሚያወራው፡፡ ጥቅሱ፣ በቤማ ወቅት በእርሱ ውስጥ በመኖር ምክንያት ስለሚገኝ ድፍረትና በእርሱ ውስጥ ባለመኖር ስለሚኖረው እፍረት ያወሳል፡፡ እስቲ ጥቅሱን ዘርዘር አድርገን እንመልከት፤

‹‹አሁንም ልጆች ሆይ›› ዮሐንስ ለአማኞች ነው የሚፅፈው፡፡ ደብዳቤውን ለሚያነቡ ዳግም ለተወለዱ ሕዝቦቹ የተጠቀመበት የፍቅር መግለጫ ነው፡፡

‹‹በእርሱ ኑሩ›› ይህ ሀረግ ሕብረት ከማድረግ ፍሬ ሐሳብ ጋር ተመሳስሎ አለው፡፡ የ1ኛ ዮሐንስ ደብዳቤ ርዕሰ ጉዳይም ይኸው ነው (1፡3-7)፡፡ ‹‹በእርሱ ኑሩ›› የሚለው ሃሳብ የእርሱን ሕይወት የእኛ ሕይወት ምንጭ አድርገን በእርሱ ላይ ‘እንደጥገኛ መኖር’ የሚለውን መልዕክት ያስተላልፋል፡፡ በክርስቶስ ላይ ጥገኛ የሆነ ሕይወት (ማለትም በእርሱ መኖር)፣ ሽልማት ለመቀበል የምንኖረው ሕይወት መሰረት ነው፡፡ 

‹‹በሚገለጥበት ጊዜ›› እዚህ ላይ ሁለት ነገሮችን ማየት እንችላለን፤ (1ኛ) ‹‹ጊዜ›› የምትለዋ ቃል የጌታን መምጣት አይቀሬነት ያሳያል (2ኛ) ‹‹በሚገለጥበት›› የሚለው ቃል ደግሞ የመነጠቅንና ይህም የሚያስከትለውን የ ቤማ ን ጉዳይ ያሳያል፡፡ 

«እምነት እንዲሆንልን›› በሚለው ሀረግ ውስጥ፣ በአማርኛው እምነት ተብሎ የተተረጎመው ቃል መሰረታዊ ሃሳብ ድፍረት ነው፤ ‹‹ድፍረት›› parresia ማለት ሲሆን ትርጓሜውም ልበ ሙሉነት፣ ለመናገር አቅም ማግኘትን ያመለክታል፡፡ ምንም እንኳ ሁላችንም አሁንም ሆነ ወደፊት ፍፁም ባንሆንም፣ በእርሱ ለመኖር ያደረግነው ታማኝነት ግን ሽልማት ለመቀበል ድፍረት ይሆነናል፡፡ 

‹‹በመምጣቱም (በመገኘቱ) በእርሱ ፊት እንዳናፍር›› እዚህ ላይ የሰፈሩትን በርካታ ቁም ነገሮች ልብ እንበል፡፡

1. በዚህ ክፍል ላይ የተጠቀሰው የግሪክኛው ግስ aorist subjunctive የሚሰኝ ግስ ነው፡፡ ግሱም የሚያስተላልፈው ሃሳብ ቀጣይ ያልሆነ የወደፊት ጊዜን ሲሆን ይህም ማለት በቋሚነት የሚቀጥል ድርጊት አለመሆኑን ያስረዳል፡፡

2. የግሱ ግብር ደግሞ ተደራጊ ነው፡፡ ባለቤቱ የድርጊቱ አድራጊ ሳይሆን ተቀባይ ነው፡፡ ይህ ማለት እንዲያፍር ተደርጓል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን እንዴት?

3. ሁለት አይነት ምልከታዎች አሉ፡- በእርሱ ያልኖረ አማኝ ጌታ እንዲያፍር ያደርገዋል፡፡ ይህ በተወሰነ መልክ የቅጣት ይዘት ስለሚኖረው ክርስቶስ ካዘጋጀልን ከፍርድ ነፃ የመሆን ፍሬ ሃሳብና ከ ቤማ አላማ ጋር ይጣረሳል፡፡ በእርሱ ያልኖረ አማኝ ኃጢአቱ ያስከተለበትን የሽልማትና ክብር ማጣት ውጤት በማየት ያፍራል፡፡ በራዕይ 7፡17፣ 21፡4 እና ኢሳይያስ 65፡17 መሰረት ይህ ጊዚያዊና የሚያልፍ ክስተት እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ 

ሆይት ስለዚህ ጉዳይ እንዲህ ይላል፡- መጽሐፍ ቅዱስ፣ በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት እንደ አማኙ ታማኝነት ልክ፣ መጠኑ የሚለያይ እፍረት በአማኞች ሕይወት እንደሚኖር ይናገራል፡፡ ስለዚህ አማኝ በማናቸውም ጉዳዮች ጌታን ደስ የሚያሰኝ ሆኖ ለመኖር የዘወትር ምኞቱ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ምንም እንኳን አማኞች በአንዳንድ ተግባሮቻቸው ምክንያት በምድራዊ ሕይወታቸው ዘመን እፍረትን እንደሚቀበሉ በሰማያዊውም ሕይወት ይህን መሳይ ነገር፣ በሚያልፍ ቅፅበት፣ መቀበላቸው አይቀሬ ነው፡፡ ይህንን ተከትሎ ግን ቁጥር ስፍር የሌለው ደስታ ይገለጣል፡፡

ኢንግሊሽ የተሰኘው ሰው በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ደስታ፣ ከጌታ ጋር ባለን ሕይወት በይበልጥ የሚታየው ስሜት ነው፡፡ ይህ ብቻ ስለ መሆኑ ግን እጠራጠራለሁ፡፡ ተግባራችን በፍርድ ቀን ሲገለጥ አንዳንድ ደስታዎች ከእፍረት ጋር የተቀላቀሉ ይሆናሉ፡፡ ሽልማት በምናጣባቸው ነገሮች ሁሉ እፍረትን እናውቃለን፡፡ የክርስቶስ የፍርድ ወንበር ከምረቃ ስነ ስርዓት ጋር ሊነፃፀር ይችላል፡፡ በምረቃ ስነ ስርዓት ወቅት ተመራቂው ባሳየው አነስተኛ ትጋት ምክንያት የተወሰነ መጠን ያለው ፀፀት ይሰማዋል፡፡ ነገር ግን በዚህ ወቅት በገዢነት የሚንፀባረቀው ስሜት ከፀፀት ይልቅ ደስታ ነው፡፡ የተሻለ ውጤት ባለማግኘታቸው ተመራቂዎች ከአዳራሹ እያለቀሱ አይወጡም፡፡ ከዚህ ይልቅ በመጨረሳቸውና ባገኙት ስኬት እርካታ ይኖራቸዋል፡፡ ሀዘን ያለውን ድርሻ ማግዘፍ መንግስተ ሰማይን ገሀነም እሳት ማድረግ ሲሆን ሀዘን ያለውን ድርሻ ማቃለል ደግሞ ታማኝነት ያለውን ውጤት ከንቱ ማድረግ ነው፡፡

የሽልማቶች ባሕሪ 

በመጽሐፍ ቅዱስ መሰረት እነዚህ ሽልማቶች ምንድን ናቸው? እንዴት ተደርገው ነው የተገለፁት? የተገለፁበት መንገድ በግርድፉ ሲሆን እነርሱም የሚከተሉት ናቸው፡፡ 

የአክሊሎች ተስፋ – ይህ የድል፣ የስልጣን እና የሃላፊነት ምሳሌ ይመስላል፡፡

የሰማይ መዝገብ ተስፋ – (ማቴ. 6፡20፣ 1ጴጥ. 1፡14) ያላቸውን ዘላለማዊ ዋጋ የሚያሳይ ይመስላል፡፡ 

ይሁንታ/አክብሮት ወይም ሙገሳ የማግኘት ተስፋ – ‹‹መልካም አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ …›› ወዘተ በሚሉ ቃላት ሽልማት የተሰጠበትን ሁኔታ ያሳያል፡፡ (ማቴ. 25፡21፣ ሉቃስ 19፡17፣ 1ቆሮ. 4፡5)፡፡

ድል ለነሱት ተስፋ – ይህ ሽልማት ሁሉን አማኝ የተመለከተ ተስፋ ሳይሆን የተለየ ፈተናንና መከራን በድል ላለፉ አማኞች የተዘጋጀ የተለየ ሽልማትን ይመለከት ይሆናል፡፡ (ራዕ. 2፡7፣ 2፡11፣ 17፡26 ወዘተ ይመልከቱ)፡፡ 

በጌታ ቤት ላይ የተለየ ኃላፊነትና ስልጣን የማግኘት ተስፋ – (ማቴ 19፡28፣24፡45- 47፣25፡21.23፣ ሉቃስ 19፡17-19፣22፤29-30፣ ራእ2፡26) 

የአዲስ ኪዳን ዘውዶች

ለዘውዶች የተሰጡ ቃሎች

Stephanos፡፡ ይህ የድል ዘውድ ነበር፡፡ በ ቤማ ስፍራ በዳኛው ፊት፣ ድል ለነሳው አትሌት የሚሰጥ ከጉንጉን አበባና ቅጠል የተሰራ አክሊል ነው፡፡ በታማኝነታቸው ምክንያት ለአማኞች የሚሰጥ ዘውድን አስመልክቶ ጥቅም ላይ የዋለ ቃልም ነው፡፡ 

Diadem፡፡ ይህ ደግሞ ንጉሳዊ አክሊል ነበር፡፡ በራዕይ 12፡3 እና 13፡1 ላይ ከተጠቀሰው የአውሬው 7 ዘውዶች ጋር በተያያዘ ተጠቅሷል፡፡ ነግር ግን ክርስቶስ የነገሥታት ንጉስ መሆኑን ለማስረገጥ፣ ይህ ቃል ጌታ ሲመለስ የሚያደርጋቸውን በርካታ ዘውዶች ለመጥቀስ ጥቅም ላይ ውሏል (ራዕ. 19፡12)፡፡ 

መርህ፡ ድል አድራጊው ጌታ ነው፡፡ የእኛ ድል በእርግጥ የእርሱ ነው፡፡ እኛ ያደረግነው ነገር ቢኖር ይህን የእርሱን ድል በእምነት በእኛ ሕይወት ውስጥ መኖር ነው፡፡ አክሊል (ዘውድ)፣ የክርስቶስ ድል፣ በእግዚአብሔር ፀጋ፣ በእኛ ሕይወት ይገለጥ ዘንድ ላሳየነው ታማኝነት የሚደረግ ሽልማት ነው፡፡ 

አክሊሎቹ/ዘውዶቹ እና ፋይዳቸው

የእሾህ አክሊል (ማቴ. 27፡29፣ ማር. 15፡17፣ ዮሐ. 19፡2.5) የክርስቶስን የመስቀል ላይ ሥራ የሚናገር ሲሆን በኃጢአት፣ ሰይጣንና ሞት ላይ ያገኘውን ድል ይናገራል፡፡

የማይበሰብስ አክሊል (1ቆሮ. 9፡25) ሁለት ነገሮችን ያመለክታል፡- (1ኛ) ይህ አክሊል የሁሉንም አክሊሎች ባሕሪይ ይወክላል፡፡ በሰማይ የምንቀበለውን አክሊል በዚህ ምድር ላይ ከምንቀበላቸው ጊዜያዊና ጠፊ አክሊሎች ጋር ያለውን ንፅፅሮሻዊ ግንኙነት ያሳያል፡፡ (2ኛ) በተጨማሪም ጌታን ለማገልገልና ሩጫችንን ለመፈፀም ስንል ራሳችንን በማስገዛት ላሳየነው ታማኝነት የሚሰጠንን አክሊል ያመለክታል፡፡

የደስታ ወይም የትምክህት አክሊል (1ተሰ. 2፡9፣ ፊሊ. 4፡1) ይህ አክሊል ለመመስከር፣ ለመከታተልና ሌሎችን ስለ ማገልገል የምንቀበለው አክሊል ነው፡፡ የተሰሎንቄ ሰዎች የጳውሎስ አክሊሎች ናቸው፡፡ 

የሕይወት አክሊል (ያዕ. 1፡12፣ ራዕ. 2፡10) ይህ አክሊል ፈተናና መከራን በመታገስ የሚገኝ አክሊል ነው፡፡ ይህ አክሊል በእምነት ብቻና በክርስቶስ ብቻ የምናገኘው የዘላለም ሕይወት አይደለም (ያዕ. 4፡10፣ ሮሜ. 3፡24፣ 5፡15-17፣ 6፡23፣ ኤፌ. 2፡8)፡፡ ይህ አክሊል ፈተናዎችን በማሸነፍና መከራዎችን በመታገስ የሚገኝ አክሊል ነው፡፡

የጽድቅ አክሊል (2ጢሞ. 4፡8) ይህ አክሊል ስጦታዎቻችንንና አጋጣሚዎቻችንን በታማንነት ለጌታ አገልግሎት በመጠቀማችንና የእርሱን መገለጥ በመውደዳችን የምንሸለመው ሽልማት ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ነገሮች እጅና ጓንት ናቸው፡፡ መገለጡን መውደድ በብረሃኑ መኖር ማለት ነው፡፡

የክብር አክሊል (1ጴጥ. 5፡4) ይህ አክሊል ሽማግሌዎች ሕዝብን በእረኝነት የማገልገል ሃላፊነታቸውን በታማኝነት ቢፈጽሙ ቃል የተገባላቸው ሽልማት ነው፡፡

አክሊሎችን ማኖር (ራዕ. 4፡10-11) ይህ ክብር ክርስቶስ ብቻ ስለሚገባው፣ እኛም ያገኘነው የፍሬያማነት ሕይወት ምንጩ በእርሱ የመኖራችን እና የእርሱ ሕይወት በእኛ ውስጥ የመፍሰሱ ምስጢር ስለሆነ፣ ያገኘነው አክሊል ሁሉ የእርሱ ፀጋ ውጤት መሆኑን ለማሳወቅ አክሊሎቻችንን ሁሉ በእርሱ እግር ስር እናኖራለን፡፡

ብዙ ዘውዶች ወይም Diadems (ራዕ. 19፡12) ኢየሱስ ክርስቶስ የነገሥታት ንጉሥ እና የጌቶች ሁሉ ጌታ መሆኑን፣ አለምንም የመግዛት መብት ያለው እርሱ ብቻ መሆኑን የሚያሳይ የንጉሥነት ዘውዶች ናቸው፡፡

የውይይት ነጥቦች

ክፍል 3 – በእርሱ መኖር እና የቤማ ወንበር

1. ሂደት በሂደት ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ባለን ሕብረት አማካኝነት የምንለማመደው የ ‹‹በእርሱ መኖር›› ልምምድ እኛ ክርስቲያኖች ከእርሱ በመወለዳችን ምክንያት ያገኘነው መብት እንደሆንና ይህም ልምመድ በመታዘዝ የሚገኝ መሆኑን አብራራ፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ሕይወት ያለማቋረጥ በሕይወቱ እንዲፈስ የሚወድ ክርስቲያን፣ እግዚአብሔር ለኃጢአት የሚሰጠውን ቦታ በአግባቡ ሊረዳ ይገባል፡፡ ኃጢአት ሕብረትን ያውካልና፡፡ የታወከ ሕብረት ደግሞ የእርሱን በረከትና እኔ ለእርሱ ያለኝን ጠቀሜታ ችግር ውስጥ ይጥላል፡፡ በተፈጥሯችን ያለው ዝንባሌ በአይምሮአችን ያለውን የ ‹‹አድርግ አታድርግ›› ዝርዝሮችን ለመፈፀም መሞከር ነው፡፡ ይህንንም የምናደርገው መታዘዝ በራሱ ግብ ስለሚመስለን ነው፡፡ መታደስ/ትኩስነት ከመታዘዝ ሳይሆን ከመንፈስ ቅዱስ ሕይወት የሚመነጭ ነው፡፡ ‹‹ድርጊቴ›› የማንነቴ ውጤት መሆን አለበት፡፡ የ ‹‹በእርሱ መኖር›› መርህ አማኙ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ስለሚኖረው ሕብረት ትኩረት ይሰጣል፡፡ በዚህ መንገድ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ተፈጥሯዊ በሆነ ሁኔታ መፍራት ይጀምራል፡፡

2. በርካታ ክርስቲያኖች ራሳቸውን በሮሜ 7 ልምምድ ውስጥ ያገኛሉ፡፡ ድካማቸውንም ሐዋርያው ጳውሎስ ራሱ በተመሳሳይ ትግል ውስጥ ነበረ በሚል ሰበብ ማመካኘት ይቀናቸዋል፡፡ እርግጥ ነው፣ ማንኛውም ክርስቲያን የሰው ተፈጥሮ ተስፋ ቢስ መሆኑን የሚረዳበት ደረጃ ላይ መድረስ አለበት ብለን እናምናለን፡፡ በሮሜ 7 ላይ ያለው ሕግ ይህንን አላማ ከግብ ለማድረስ ይጠቅማል፡፡ ጳውሎስ እንደማንኛውም ክርስቲያን በሮሜ 7 ውስጥ አልፏል፡፡ ነገር ግን የኖረው በሮሜ 8 ውስጥ ነው፡፡ እግዚአብሔር ተመሳሳይ አቅርቦት ለሁላችን አልሰጠንምን?

3. እግዚአብሔር ልጆቹ ‹‹የእርሱን›› ዘላለማዊ ሽልማት እንዲሹ እንደሚፈልግ እና ይህም አንዳንዶች ከሚያስቡት ማለትም – ‹ሽልማት መንፈሳዊ አይደለም›፣ ‹ተገቢ ያልሆነ አነሳሽ ምክንያት ነው›፣- ብለው ከሚያስቡት አስተሳሰብ ጋር ያለውን ተቃርኖ አብራራ፡፡ የምድራዊ ፍላጎቶቼን (ማለትም ቁሳዊ ነገሮች፣ ምስጋና፣ እርካታ፣ ወዘተ) መሳካት እንደ አላማ ይዤ የምኖር ከሆነ ስህተት ነው፡፡ ነገር ግን ምድራዊ ባህሪ የሌላቸውን የእርሱን ዘላለማዊ ሽልማቶች እንድንሻ ታዘናል፡፡ እነዚህ ሽልማቶች በስሜት፣ አካሎቼና በአእምሮዬ ሊለኩ የማይችሉ ናቸው፡፡ ከልጅነቱ ዘመን አንስቶ ማየት የተሳነው ሰው ስለ ቀለማት በቂ እውቀት ሊኖረው እንደማይችል ሁሉ እኛም ስለእነዚህ ሽልማቶች ያለን እውቀት እንዲሁ ነው፡፡ በዘላለም ሕይወት፣ የሽልማቱ ተካፋዮች እንድንሆን በራሱ መልካምነትና ፀጋ መረጠን እንጂ እኛ ስለተገባንና መልካም ስለሆንን አይደለም (ዕብ. 11፡6)፡፡

4. ራሳችንን እንደ መፃተኞችና እንግዶች በመቁጠር ዘላለማዊ በሆኑ ነገሮች ላይ ትኩረታችንን መጣል አለብን የሚለውን አስተሳሰብ፣ በተቃራኒው የእግዚአብሔር ልጆች በምድር ላይ ባላቸው ቆይታ ምቾቶቻቸውን፣ እርካታቸውንና ቁሳዊ ስኬቶቻቸውን ማሳደድ ምንም ችግር የለውም ብለው ከሚያስቡት ሃሳብ ጋር በማዛመድ አብራራ፡፡ የዚህ አለም ሃሳብና የባለጠግነት ምኞት፣ በርካታ ክርስቲያኖች ወደ መብሰል እንዳይደርሱ እንቅፋት የሚሆንባቸው መሰናክል ነው፡፡ (ሉቃስ 8፡4፣ ቆላ. 3፡1-3 ይመልከቱ)

5. መንፈስ ቅዱስ በእኔ ውስጥ ያቀደውን የእርሱን አላማ ለመፈፀም እንዲሁም እኔን ፍሬያማ ለማድረግና ጠቃሚ መሣሪያው አድርጎ ለማበጀት በእኔ ሕይወት ውስጥ ለሚያደርገው ሥራ የማሳየው ፈቃደኝነት በዘላለም ሕይወቴ ሁኔታ ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ አብራራ፡፡ እንደ ክርስቲያን በዚህ ምድር ላይ ስንኖር ‹‹ለእግዚአብሔር አንድ ነገር ማድረግ አለብኝ›› የሚለው የተሳሳተ አስተሳሰብ፣ እግዚአብሔር በሰማይ የስራ መዘርዝር መቆጣጠሪያ በመያዝ ‹‹እኔ›› ለ ‹‹እርሱ›› የማደርጋቸውን ተግባሮች እንደሚቆጣጠር አምላክ እንድንስለው ሊያደርገኝ ይችላል፡፡ በሂደት፣ እግዚአብሔር ከእኔ የሚጠብቀው አንዳች ነገር የለም – ወደሚል ግንዛቤ ከመጣሁ በኋላ ቀጣዩ ጥያቄ ‹‹ታዲያ ከእኔ ምን ይሻል?›› የሚለው ይሆናል፡፡ ይህ ማለት እኔ ምንም ማድረግ አልችልም ማለት ይሆን? ፈፅሞ፡፡ በርካታ ነገሮችን ማድረግ እችላለሁ (1ቆሮ. 13፡1-3 ይመልከቱ)፡፡ ጥያቄው ‹‹የምሰራው ሥራ ዘላለማዊ ዋጋ (የእርሱ ሕይወት) አለበት ወይ?›› የሚለው ነው፡፡ የማደርገው ነገር በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት ተደርጎ ቢሆን፣ የእርሱ ሕይወት አለበት፡፡ ነገር ግን ከእኔ መንጭቶ ቢሆን፣ ጊዜያዊና ለዚህ አለም ብቻ የሚረባ ነገር ይኖረዋል፡፡
6. መንፈስ ቅዱስ፣ ለእያንዳንዱ አማኝ የሰጠውን ሀብት/ችሎታ ይጠቀም ዘንድ እንዴት ልንፈቅድለት እንደምንችል አብራራ፡፡ እያንዳንዳችን መጠኑ የሚለያይ ሶስት ሀብቶች አሉን፡- ጊዜጉልበት እና ሃብት/ንብረት፡፡ አዲሱ አማኝ፣ መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ሕይወት ውስጥ እነዚህን ሀብቶች በመቆጣጠር መጠቀም እንዲችል ወሳኙን ሚና የሚጫወተው የአማኙ ፈቃድ እንደሆነ ሊያውቅ ይገባል፡፡ አማኙ በራሱ ምርጫ ላይ ሙሉ ቁጥጥር እንዲኖረው ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደተሰጠው ሊያውቅ ይገባል፡፡ መንፈስ ቅዱስ እነዚህን ሀብቶች (የግንባታ ጥሬ እቃዎች) እንዲጠቀም በፈቀድኩለት መጠን ዘላለማዊ መዋቅር ያለውን ቤት ከወርቅ፣ ብርና የከበረ ድንጋይ ለእኔው ይሰራል፡፡ ይህ እንዳይሆን መንፈስ ቅዱስን ስከላከል ደግሞ ከእንጨት፣ ሳርና አገዳ ዘላለማዊ መዋቅር የሌለውን ጊዜያዊ ቤት እኔው ለራሴ እገነባለሁ ማለት ነው፡፡ ብዙ ዘመን ከመሰንበቱ በፊት አማኙ ይህንን እውነታ ቢያውቅ የሚኖረው ጠቀሜታ ይታያችኋል?

1 thought on “ለ የክርስቶስ የፍርድ ወንበር (ቤማ) ወይም የሽልማት ዶክትሪን”

Leave a Reply

%d bloggers like this: