ስውርነት – ግልጽነት (2ኛ ቆሮ. 3፡12-18)

መጽሐፍ ቅዱስ መልእክቱን ለማስተላለፍ በተምሳሌቶች፥ በዘይቤዎችና በሌሉችም ሥነ ጽሑፋዊ ዘዴዎች ስለሚጠቀም፥ በመሠረቱ «(ሥዕላዊ) ገላጭ መጽሐፍ» ነው። ጳውሎስ በዚህ አንቀጽ ውስጥ፥ ክብር የሞላበትን ነጻነትና ግልጽነት ተጎናጽፎ ከጸጋ ሥር የሚገኘውን የክርስትና ሕይወት ለማብራራት፥ በሙሴና በፊት መጋረጃው ዓይነ-ርግብ ታሪክ ይጠቀማል። ጳውሎስ ከሙሴ ልምምድ ውስጥ ያገኘው ግንዛቤ፥ እኔና አንተ በዘጸአት 34፡29-25 ያለውን ክፍል በማንበብ ልናገኝ ከምንችለው በላይ የጠለቀ መንፈሳዊ ትርጉም ያዘለ ነው። 

1. ታሪካዊ ክስተት (2ኛ ቆሮ. 3፡12)። በአገልግሉትህ ላይ የእግዚአብሔር ክብር እያበራ ሲሄድ ለምትናገረው ነገር ድፍረት ሊኖርህ ይችላል፤ ጳውሎስ ደግሞ ይህንን ድፍረቱን አልሸሸገውም፡፡ ከሙሴ በተቃራኒጳውሎስ የሚሸሽገው አንዳችም ነገር አልነበረውም። 

ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ሲነጋገር ቆይቶ ሲመለስ፥ ፊቱ የእግዚአብሔር ክብር በማንጸባረቅ ያበራ ነበር። ለሰዎች ንግግር በሚያደርግበት ጊዜ፥ ከፊቱ ላይ ክብሩን ያዩና ይደነቁ ጀመር። ዳሩ ግን ሙሴ ክብሩ እንደሚደበዝዝ ያውቅ ነበረና ሕዝቡን አስተምሮ ሲያበቃ፥ ፊቱን ሰዓይነ-ርግብ ይሸፍን ነበር። ይህም ክብሩን ከእርሱ መለየት እንዳይመለከቱ አደረጋቸው። ታዲያ ክብሩን እያጣ ያለውን መሪ መከተል የሚፈልግ ሰው ይኖር ይሆን? 

በቁጥር 13 ላይ «መጨረሻ» ተብሎ የተተረጎመው ቃል ሁለት ትርጉሞች አሉት – «ዓላማ» እና «ፍጻሜ» የሚሉ። ዓይነ-ርግቡ ሰዎቹ የሙሴ ክብር እየደበዘዘ ሂዶ «ከፍጻሜ» የሚደርስበትን ሁኔታ እንዳይመለከቱ ማዕቀብጣለባቸው። እንዲሁም ደግሞ ይኸው ዓይነ-ርግብ ከሚደበዝዘው ክብር በስቲያ ያለውን «ዓላማ» እንዳይረዱ አሁንም ጋረዳቸው። ከዚህ በተጨማሪም ሕጉ በቅርቡ የተሰጠ ስለ ነበር፥ ሕዝቡ ይህ የከበረው ሥርዓት ጊዜያዊ ስላ መሆኑ ይነገራቸው ዘንድ አልተዘጋጁም ነበር። የሕጉ ቃል ኪዳን ወደፊት ለሚከሰት ለአንድ ከዚያ በላይ ለላቀ ነገር መዘጋጃ የመሆኑ እውነት አልተገለጸላቸውም ነበር። 

2. ብሔራዊ ተዛምዶ (2ኛ ቆሮ. 3፡14-17)። ጳውሎስ ለእስራኤል ልዩ ፍቅር የነበረው ሲሆን፥ ወገኖቹ በክርስቶስ አምነው ሲድኑ ለማየት ከፍተኛ ሸክም እንዳለበትም ይሰማው ነበር (ሮሜ 9፡1-3)። ዳሩ ግን የአይሁድ ሕዝብ መሢሐቸውን ያልተቀበሉት ለምን ነበር? ጳውሎስ የአሕዛብ ሚሲዮናዊ እንደ መሆኑ፥ በርካታ አሕዛቦች በጌታ ሲታመኑና ዳሩ ግን አይሁዶች – የራሱ ወገኖች – እውነትን በመግፋት እርሱንና ቤተ ክርስቲያንን ሲያሳድዱ ይመለከት ነበር። 

ለዚህስ ምክንያቱ ምን ይሆን? ምክንያቱ፥ አእምሮአቸውንና ልባቸውን የከለለው «መንፈሳዊ መጋረጃ» ስለ ነበረ ነው። «መንፈሳዊ ዓይኖቻቸው» ስለ ታወሩ፥ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ሲያነቡ፥ ስለ ገዛ መሢሐቸው የተገለጸውን እውነት ለማየት አይችሉም ነበር። ምንም እንኳ ቅዱሳት መጻሕፍት በምኩራቦች ውስጥ ሥርዓት ባለው መንገድ ቢነበቡም፥ አይሁዳውያን ግን እግዚአብሔር የሰጣቸውን መንፈሳዊ መልእክት አልተረዱም ነበር። በገዛ ሃይማኖታቸው ታውረው ነበር። 

ከደኅንነት ርቀው ለባዘኑት የእስራኤል ልጆች አንዳች ተስፋ ይኖር ይሆን? አዎን፥ አለ! «ወደ ጌታ (ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ) ግን ዘወር ባለ ጊዜ ሁሉ መጋረጃው ይወሰዳል። (2ኛ ቆሮ. 3፡ 16)። 

በመጋቢነት ባገለገልሁባቸው በሦስት አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑትን አይሁዳውያን ማጥመቅ ደስ ይለኝ ነበር። ዳግም ከተወለዱ በኋላ አእምሮአቸው በሚያስደንቅ ሁኔታ ለቅዱሳት መጻሕፍት ይከፈታል። አንድ ሰው ስለዚሁ ልምምዱ ሲያጫውተኝ «ልክ ቅርፊት ከዓይኔ እንደሚወድቅ ያህል ማለት ነው። እንዲያውም እኔ የማየውን ነገር ሁሉም ሰዎች ለምን እንደማያዩት በማሰብ እደነቃለሁ! » ብሉኛል። መጋረጃው በእግዚአብሔር መንፈስ አማካኝነት ስለሚወገድ፥ መንፈሳዊ ዕይታን ያገኛሉ። 

ዳሩ ግን ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አገልግሉት ውጭ ማንኛውም ኃጢአተኛ – አይሁዳዊ ወይም አሕዛብ – ወደ ክርስቶስ ሊመለስ አይችልም። «ጌታ ግን መንፈስ ነው» (ቁ. 17)። ይህ ዓረፍተ ነገር መንፈስ ቅዱስ አምላክ መሆኑን የሚያመለክት ነው። በቆሮንቶስ ውስጥ ቤተ ክርስቲያንን የሚያውኩ የአይሁድ ትምህርት አጥባቂዎች የሰዎችን ሕይወት ለመለወጥ በሕግ ላይ ይመረኮዙ ነበረ፤ ዳሩ ግን መንፈሳዊ መለወጥን የሚያመጣው የእግዚአብሔር መንፈስ ብቻ ነው። ሕግ የሚሰጠን ነገር ቢኖር እስራትን ብቻ ነው፤ ዳሩ ግን መንፈስ ቅዱስ ወደ ነጻነት ሕይወት ያስገባናል። «አባ አባት ብለን የምንጮህበትን የልጅነትን መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ፥ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና» (ሮሜ 8፡15)። 

ዛሬ የእስራኤል ሕዝብ በመንፈሳዊ ዕውርነት ይኖራል። ዳሩ ግን ይህ ማለት ደግሞ ከአይሁዶች መካከል አንዳንድ ግለሰቦች አይድኑም ማለት አይደለም። ዛሬ ቤተ ክርስቲያን ባለውለታዋ ለሆነው ለእስራኤል ሕዝብ ሊኖራት የሚገባውን ሸክም እንደገና ማንሣት አለባት። ይህ ሁሉ ያገኘነው መንፈሳዊ በረከት በእስራኤል በኩል ስለ መጣልን፥ የእነርሱ ባለዕዳዎች ነን። «መዳን ከአይሁድ ነውና» (ዮሐ 4፡22)። ይህንን ዕዳ «ልንከፍል» የምንችለበት ብቸኛው መንገድ ወንጌሉን ለእነርሱ በማካፈልና ይድኑ ዘንድ በመጸለይ ነው (ሮሜ 10፡1)። 

3. ግላዊ ተዛምዶ (2ኛ ቆሮ. 3፡18)። «እኛም ሁላችን በመጋረጃ በማይከደን ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን።» ይህ ጥቅስ የምዕራፉን ፍሬ አሳብ የምንጨብጥበት ከፍተኛ ደረጃ ሲሆን፥ በበኩሌ ብዙ አማኞች ስተውታል ወይም ገሸሽ አድርገውታል ብዩ የምደነቅበትን ታላቅ እውነት ያዘለ ነው። እኔና አንተ የኢየሱስ ክርስቶስን አምሳል ተቀብለን፥ በእግዚአብሔር መንፈስ አገልግሉት አማካኝነት «ከክብር ወደ ክብር» ልንለወጥ እንችላለን። 

በአሮጌው ኪዳን ዘመን፥ ወደተራራው በመውጣት ከእግዚአብሔር ጋር ህብረት ያደረገው ሙሴ ብቻ ሲሆን፥ ዳሩ ግን በአዲሱ ኪዳን አማኞች ሁሉ ከእርሱ ጋር ህብረት የማድረግ ዕድል አላቸው። በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት፥ ወደ ቅድስተ-ቅዱሳን ልንገባ እንችላለን (ዕብ 10፡19-20) -ገደል እየቧጠጥን ከተራራ ራስ መውጣት ሳያስፈልገን! 

መስተዋት የእግዚአብሔር ቃል ተምሳሌት ነው (ያዕ. 1፡22-25)። ወደ እግዚአብሔር ቃል በመመልከት የእግዚአብሔርን ልጅ በምናይበት ጊዜ፥ መንፈስ ቅዱስ ወደ እግዚአብሔር ቅድስና ይለውጠናል፡ ይሁንና ምንም ነገር ከእግዚአብሔር መሸሸግ የለብንም፡፡ ከእርሱ ጋር ግልጽና ታማኝነት ያለበት ህብረት ማድረግ እንጂ፥ ማንነታችንን «መሸፋፈን» የለብንም። 

በዚህ ስፍራ መለወጥ ተብሎ የተተረጎመው ቃል፥ በተራራው የጌታችን መልክ ያንጸባረቀበትን ሁኔታ ከሚገለጸው ቃል ጋር አንድ ዓይነት ነው (ማቴ. 17፤ ማር. 9)። ቃሉም አንድ ኃይል ከውስጥ ፈልቆ በመውጣት በውጭ የሚታየውን ለውጥ ማስከተሉን የሚገልጽ ነው። ይህም የዕድገት ሂደትን «መለወጥን» (ሜታሞርፎሲስ) የሚያመለክት የግሪክ ቃል ሲሆን፥ ይኸውም አንድ እንደ ቢራቢሮ ያለ በራሪ ፍጡር፥ እንዴት ከዕንቁላልነት ወደ ሽጋትነትና እጭነት ከዚያም ወደ ብስል እንስሳነት እንደሚለወጥና ቀጥሉ ወደ መብረር ደረጃ የሚደርስበትን የዕድገት ሂደት ሁሉ ይወክላል። ለውጦቹ በሙሉ የሚመጡት ከውስጥ ነው፡፡ 

ሙሴ የእግዚአብሔርን ክብር ያንጸባርቅ እንጂ፥ ዳሩ ግን እኔና አንተም የእግዚአብሔርን ክብር በውስጣችን ማስተላለፍ እንችላለን። የእግዚአብሔር ቃል በማሰላሰል በውስጡ የእግዚአብሔርን ልጅ በምንመለከትበት ጊዜ፥ መንፈስ ቅዱስ ይለውጠናል! «ከክብር ወደ ክብር» ስንሸጋገር ሳለ፥ ይበልጥ ጌታ ኢየሱስን እየመሰልን እንሄዳለን። ይህ አስደናቂ ሂደት ሕግን በመጠበቅ ሊመጣ አይችልም። የሕግ ክብር ደብዝዞ ጠፍቷል፤ ዳሩ ግን የእግዚአብሔር የጸጋ ክብር በሕይወታችን ውስጥ እየጨመረ ይሄዳል። 

ጳውሎስ የሚያነጻጽረው አሮጌውንና አዲሱን ኪዳን ብቻ ሳይሆን፥ የአሮጌውን ኪዳን አገልግሎት ከጸጋው አገልግሉት ጋር ጭምር መሆኑን ከልብ አጢነው። የአሮጌው ኪዳን አገልግሎት ግብ ለውጫዊ መመዘኛ መታዘዝ ሲሆን፥ ዳሩ ግን ይህ መታዘዝ የሰውን ባሕርይ ሊለውጥ አይችልም። የአዲሱ ኪዳን አገልግሎት ግብ ኢየሱስ ክርስቶስን መምሰል ነው። ሕገ ወደ ክርስቶስ ሊያመጣን ሲችል (ገላ 3፡24)፡ ዳሩ ግን ክርስቶስን እንድንመስል የሚያደርገው ጸጋ ብቻ ነው። የሕግ አስተማሪዎችና ሰባኪዎች አድማጮቻቸውን እስከ ተወሰነው መመዘኛ ድረስ ሊያስኬዱዋቸው ቢችሉም፥ ዳሩ ግን የእግዚአብሔርን ልጅ እንዲመስሉ ለመለወጥ በፍጹም አይችሉም። 

የአሮጌው ኪዳን አገልግሎት መሣሪያ ሕግ ሲሆን፥ ዳሩ ግን የአዲሱ ኪዳን አገልግሎት መሣሪያ የእግዚአብሔርን ቃል በመጠቀም የሚሠራው የእግዚአብሔር መንፈስ ነው። (የ«ሕግ» ስል ብሉይ ኪዳንን ማለቴ ሳይሆን፥ ዳሩ ግን በሙሴ የተሰጡትን ሕግጋት በሙሉ ማለቴ ነው። በርግጥ፥ መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስ ክርስቶስን ለእኛ ለመግለጽ በአሮጌውና በአዲሱ ኪዳን በሁለቱም ሊጠቀም ይችላል።) 

ቃሉን የጻፈው መንፈስ ቅዱስ ስለ ሆነ፥ ሊያስተምረን የሚችለው እርሱ ነው። ከዚህም በላይ፥ መንፈስ ቅዱስ ከውስጣችን ስለሚኖር፥ በልባችን ቃሉን እንድንታዘዝ ሊረዳን ይችላል። ይህም ከፍርሃት የመነጨ የሕግ መታዘዝ ሳይሆን፥ ከፍቅር የመነጨ የልጅነት መታዘዝ ነው። 

በመጨረሻም፥ የአሮጌው ኪዳን አገልግሎት ውጤት ባርነት ሲሆን፥ ዳሩ ግን የአዲሱ ኪዳን አገልግሉት ውጤት በመንፈስ አርነት መውጣት ነው። ሕጋዊነት ሰውን በእንጭጭነት ደረጃ የሚያቆይ ስለ ሆነ፥ ከሕግ ሥር መኖር ያለባቸውም ያልበሰሉ ሰዎች ናቸው (ገላ 4፡1-7)። እግዚአብሔር ልጆቹ እንዲታዘዙት የሚፈልገው፥ ከውጫዊ ፊደል (ሕግ) የተነሣ ሳይሆን፥ ከውስጣዊ ባሕርይ የተነሣ ነው። ክርስቲያኖች ከሕግ በታች ባይሆኑም ዳሩ ግን ይህን ማለት ደግሞ ሕግ-አልባዎች ነን ማለት አይደለም! የእግዚአብሔር መንፈስ የእግዚአብሔርን ቃል ከልባችን ላይ ስለሚጽፍ፥ በውስጣችን ካስቀመጠው አዲስ ሕይወት የተነሣ አባታችንን እንታዘዛለን። 

ዛሬም ቢሆን የሕጋዊነት መስህብ ከእኛ ጋር አብሮ ያለ ነው። በጳውሎስ ዘመን የአይሁድን ሃይማኖት የሚያስፋፉ ሰዎች እንዳደረጉት፥ ዛሬም በመናፍቃን ትምህርቶች የታወቁ ክርስቲያኖችና የቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ይነጠቃሉ። ስለ ሆነም የሐሰት ትምህርቶችን ልንለይና አንገዋለን ልንጥላቸው ይገባል። እንዲሁም ደግሞ ላይ ላዩን ወንጌል-ሰባኪ አብያተ ክርስቲያናት ቢመስሉም፥ ዳሩ ግን በሕግ-አጥባቂነት አዝማሚያቸው ምዕመኖቻቸውን አስተሳሰበ ጨቅላዎች፥ የበደለኛነት ስሜት የተጫናቸው መንፈሰ፥ ኩልሽዎችና ፈሪዎች አድርገው የሚያኖሩ ብዙዎች አሉ። ጊዜያቸውን በአብዛኛው በውጫዊ ጉዳዮች ላይ ስለሚያጠፉ፡ ውስጣዊውን ሕይወት የማነጹን ተግባር ችላ ይላሉ። ሃይማኖታዊ መመዘኛዎችን ከፍ ከፍ ሲያደርጉና ኃጢአትን ሲኮንኑ፥ ዳሩ ግን የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ታላቅነት ለመመስከር ይዘነጋሉ። በአንዳንድ የአዲስ ኪዳን አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የአሮጌው ኪዳን አገልግሎት ሲሰጥ መመልከቱ አሳዛኝ ነገር ነው። 

ጳውሎስ የራሱን አገልግሎት ሁለት ገጽታዎች አብራርቷል፡ አገልግሉቱ ድል-ነቪ (ምዕራፍ 1-2) እና የከበረ (ምዕራፍ 3) ነው። ሁለቱ አብረው ይሄዳሉ፡- «ስለዚህ ምክንያት ምህረት እንደ ተሰጠን መጠን፥ ይህ አገልግሎት ስላለን አንታክትም» (4፡1)። 

የአንተም አገልግሉት የእግዚአብሔርን ክብር የሚያንጸባርቅ እስከ ሆነ ድረስ፥ ልታቆመው አትችልም!

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading