አንድነት – የመንፈስ ስጦታ (1ኛ ቆሮ. 12፡1-13)

ከመብሰል ምልክቶች አንዱ ስለ ገዛ ሰውነት እያደገ የሚመጣ እውቀት እና አድናቆት ነው። በመንፈሳዊ ሕይወት በተመሳሳይ ሁኔታ የሚፈጸም ነገር አለ። በክርስቶስ እየበሰልን በምንሄድበት ጊዜ፥ የክርስቶስ አካል ስለ ሆነችው ስለ ቤተ ክርስቲያን የበለጠ እውቀት እናገኛለን። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ «በአካለ ሕይወት» ላይ የሚደረገው አጽንኦት እሰየው የሚያሰኝ ነው። ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ወደ መገለል የሚመራውን «በግላዊ ክርስትና» ላይ የሚደረገውን የተሳሳተ አጽንኦት ለመቋቋም ረድቶአል። 

በእርግጥ ጳውሎስ ስለ ቤተ ክርስቲያን በሚያወሳበት ጊዜ የተጠቀመው የአካል»ን ምሳሌ ብቻ አይደለም። ስለዚህ በጣም ወደ ጽንፍ እንዳንሄድ መጠንቀቅ አለብን። ቤተ ክርስቲያን ቤተሰብ፥ ሠራዊት፥ ቤተ መቅደስ እና ሙሽራም ናት። የተጠቀሰው እያንዳንዱ ምሳሌ የሚያስተምረን ጠቃሚ ትምህርት አለው። ይሁንና ጳውሎስ በሦስቱም ደብዳቤዎቹ ትኩረት ያደረገው ቤተ ክርስቲያን አካል በመሆኗ ላይ ነው። ደግሞም በእያንዳንዳቸው በእነዚህ ምንባቦች፥ እነዚህኑ ሦስት ጠቃሚ እውነቶች አንድነት፥ ልዩነት እና ብስለትን አሳይቷል። የሚቀጥለው ሠንጠረዥ ይህን ግልጽ ያደርገዋል። 

የመንፈስ ቅዱስን አገልግሎት ሳያወሱ ስለ እካል ማውሳት የማይቻል ነው። በጴንጤቆስጤ ዕለት ለአካል ልዩነት የሰጠውና በአካል ውስጥ ና በአካል አማካኝነት ያገለገለው መንፈስ ቅዱስ ነበር። 

1ኛ ቆሮንቶስ

አንድነት፡ 12፡1-13

ልዩነት፡ 12፡14-31

ብስለት፡ 13፡1-13 

ሮሜ 

አንድነት፡ 12፡1-5 

ልዩነት፡ 12፡6-8

ብስለት፡ 12፡9-21 

ኤፌሶን 

አንድነት፡ 4፡1-6  

ልዩነት፡ 4፡7-12

ብስለት፡ 4፡13-16 

የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን መንፈሳዊ ስጦታዎችን በሥጋዊ መንገድ በመጠቀም መንፈስ ቅዱስን ማሳዘናቸው አለመታደላቸው ነው። ክቡር መሣሪያ እንደያዙ በሳሉች ሳይሆኑ እሻንጉሊት እንደሚያስፈልጋቸው ልጆች ስለ ነበሩ ገና ማደግ ያስፈልጋቸው ነበር። 

አንድነት – የመንፈስ ስጦታ (1ኛ ቆሮ. 12፡1-13) 

በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ክፍፍል ስለነበረ፥ ጳውሎስ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት አጉልቶ በማሳየት ጀመረ። አራት አስደናቂ የመንፈሳዊ አንድነት ጥምረቶችን አመላከተ። 

አንዱን ጌታ እናውጃለን (12፡1-3)። ከመለወጣቸው አስቀድሞ በጣዖት አምላኪነት የነበራቸውን ልምምድ አሁን ከነበራቸው ክርስቲያናዊ ልምምድ ጋር አነጻጸረ። ሙት ጣዖታትን ያመልኩ ነበር፤ ነገር ግን አሁን የሕያው እግዚአብሔር ንብረት ሆኑ። ጣዖቶቻቸው ከቶውንም አናግረዋቸው አያውቁም። አሁን ግን እግዚአብሔር በመንፈሱ እና እንዲያውም በትንቢት ስጦታቸው አማካኝነት በራሳቸውም በኩል ይናገራቸው ነበር። ጠፍተው እያሉ በአጋንንት ቁጥጥር ሥር ነበሩ (10፡20) ባዝነውም («ተወስደው» ቁ 2) ነበር። አሁን ግን የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጣቸው በመኖር ይመራቸዋል። 

አንድ ሰው በእውነት «ኢየሱስ ጌታ ነው» ለማለት የሚችለው በመንፈስ አማካኝነት ነው። አላጋጭ ኃጢአተኛ ቃላቱን ይናገር ይሆናል፤ ነገር ግን እውነተኛውን የእምነት መግለጫ እየሰጠ አይደለም። (ምናልባት ጳውሎስ እያጣቀሰ የነበረው ከመለወጣቸው በፊት በአጋንንት ኃይል ተነድተው ስለተናገሩአቸው ነገሮች ነበር።) መንፈስ ቅዱስ በሚሠራበት ወቅት (14፡32) አማኙ ራሱን የሚገዛ መሆኑን ማጤን ጠቃሚ ነው፤ ምክንያቱም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን ስለሚቆጣጠር ነው። ሰውን ራስን ከመግዛት የሚያስጥል ማንኛውም «የመንፈስ መገለጥ» ተብዩ ነገር ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ምክንያቱም «የመንፈስ ፍሬ . . . ራስን መግዛት» (ገላ. 5፡22-23) ነው። 

ኢየሱስ ክርስቶስ በእርግጥ በሕይወታችን ጌታ ከሆነ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንድነት ይኖራል። በእግዚአብሔር ሕዝቦች መካከል መከፋፈል ና መለያየት ካለ ለጠፋው ዓለም የሚያደርጉትን የጋራ ምስክርነት ያዳክማል (ዮሐ 17፡20-21)። 

በአንድ እግዚአብሔር ላይ እንመካለን (12፡4-6)። እዚህ ላይ አሓዱ ሥሉሳዊ አጽንኦት ይታያል (አንድ መንፈስ . . . አንድ ጌታ. . . አንድ እግዚአብሔር።» እያንዳንዳችን የተለያዩ ስጦታዎች፥ አገልግሎቶች ና የአሠራር ዘይቤዎች ሊኖሩን ይችላል። ነገር ግን «ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእናንተ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና» (ፊልጵ. 2፡13)። የስጦታው ምንጭ እግዚአብሔር ነው፤ ስጦታውን የማስተዳደር ፍላጎቱም የሚመጣው ከእግዚአብሔር ነው፤ ደግሞም ስጦታውን የመጠቀም ኃይሉም የሚገኘው ከእግዚአብሔር ነው። ታዲያ ስለ ምን ሰዎችን እናከብራለን? ለምንስ እርስ በርስ እንፎካከራለን? 

የምናገለግለው አንዱን አካል ነው (12፡7-11)። ስጦታዎቹ የተሰጡት ለመላው ቤተ ክርስቲያን ነው – ለግል መደሰቻ ሳይሆኑ፥ ለጋራ ጥቅም የሚሠሩ ናቸው። በተለይ ቆሮንቶሳውያን ይህ ማሳሰቢያ ያስፈልጋቸው ነበር፤ ምክንያቱም መንፈሳዊ ስጦታዎቻቸውን በራስ ወዳድነት ራሳቸውን ለማስተዋወቅ እንጂ ቤተ ክርስቲያንን ለማዳበር አይጠቀሙም ነበር። ስጦታዎቻችንን በትሕትና በምንጠቀምበት ጊዜ፥ መላው ቤተ ክርስቲያንን የሚረዳ አንድነትን ለማዳበር እንገለገልባቸዋለን። 

ልዩ ልዩ ስጦታዎች በ 12፡8-10 እና 28፥ በኤፌ 4፡11 እና ሮሜ 12፡6-8 በስም ተዘርዝረዋል። እነዚህ ዝርዝሮች አንድ ላይ ሲጠቃለሉ 19 የተለያዩ ስጦታዎችን ና ኃላፊነቶችን እናገኛለን። በሮሜ ያለው ዝርዝር በቆሮንቶስ ካለው የተለየ ስለሆነ፥ ጳውሎስ በሁለቱም ምንባቦች ርእሰ ጉዳዩን የጨረሰ አይመስለንም። በስም የተዘረዘሩት እነዚህ ስጦታዎች ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ብቁ ሲሆኑ፥ እግዚአብሔር ግን በእነዚህ ዝርዝሮች የተወሰነ አይደለም። ሌሎችንም ስጦታዎች እንደወደደ ይሰጣል። 

ቀደም ብለን ስለ ሐዋርያት አውስተናል (9፡1-6)። ነቢያት መልእክቶቻቸው በቀጥታ በመንፈስ አማካኝነት ከእግዚአብሔር የሚመጣላቸው የአዲስ ኪዳን የእግዚአብሔር አፈቀላጤዎች ነበሩ። አገልግሎታቸው ማነጽ፥ ማበረታታት እና ማጽናናት ነበር (14፡3)። መልእክቶቻቸው ከእግዚአብሔር ለመሆን ላለመሆናቸው በአድማጮች ይመዘኑ ነበር (14፡29፣ 1ኛ ተሰ. 5፡19-20። ኤፌ. 4፡11-12 ግልጽ እንደሚያደርገው ሐዋርያት ና ነቢያት የቤተ ክርስቲያንን መሠረት ለመጣል አብረው ሠርተዋል፤ ያ መሠረት ከተፈጸመ ወዲያ ተፈላጊ አይደሉም ብለን ነው የምንገምተው። 

አስተማሪዎች (መጋቢ-አስተማሪዎች) ለአማኞች የክርስትና ሕይወት ዶክትሪናዊ (መሠረታዊ) እውነቶችን አስተምረዋል። ያስተማሩት ከቃሉ ና ከሐዋርያት ትምህርቶችም (ትውፊት) ነው። እንደ ነቢያቱ መልእክቶቻቸውን በቀጥታ ከመንፈስ የተቀበሉ አልነበሩም፤ ሆኖም ግን መንፈስ በትምህርቶቻቸው ረድቶአቸዋል። ያዕቆብ 3፡1 አስተማሪነት ከበድ ያለ ጥሪ እንደሆነ ያሳያል። 

ወንጌላዊ ዋና ሥራው የደኅንነትን የምሥራች ለጠፉት ማካፈል ነው። ሁሉም አገልጋዮች የወንጌላውያንን ሥራ መሥራት እና የጠፉትን ለመማረክ መፈለግ አለባቸው (2ኛ ጢሞ. 4፡5)፤ ነገር ግን እንዳንድ ሰዎች ወንጌላዊነትን እንደ ልዩ ጥሪ ተቀብለውታል። 

በጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን ተአምራት የእግዚአብሔር ባሪያዎች ባሕርያት አንዱ ክፍል ነበሩ (ዕብ 2፡1-4)። እንዲያውም፥ ተአምራት፥ ፈውሶች እና ልሳኖች ሥነ መለኮታውያን «የምልክት ስጦታዎች» በሚሉአቸው ሲጠቃለሉ፥ በልዩ ሁኔታ ከቤተ ክርስቲያን ጨቅላነት ጋር የተያያዙ ነበሩ።

ልግሥና እና አመራር ሌሎችን የማገልገልን እና ቤተ ክርስቲያንን የመሥራትን ጉዳይ ይመለከታሉ። ያለ መንፈሳዊ አመራር የቤተ ክርስቲያን አካሄድ የመደናበር ነው። አገልግሎት (ሮሜ 12፡7) እና አገዛዝ በአንድ ፈርጅ ይመደባሉ። በሦስቱ የፓስተርነት (የመጋቢነት) ሥልጠናዎቼ የልግሥና እና የአመራር ስጦታዎች ለነበሩአቸው ሰዎች ምስጋናዩ የከበረ ነበር። 

«የመናገር ስጦታዎች» በርካታ ነበሩ። ልሳን እና የልሳናት ትርጉም (ወደ ኋላ ብዙ የሚባልለት)፥ የጥበብ ቃል እና የእውቀት ቃል (የእግዚአብሔርን ቃል ለአንድ የተወሰነ ሁኔታ የመጠቀም ችሎታን፥ እና ምክር (ማበረታታት፥ ካስልፈለገም ግሣጼ) ናቸው። 

መስጠት እና ምሕረት ማድረግ ለሌላቸው እና በአገልግሎት ላይ ላሉ የእግዚአብሔር ባሪያዎች ቁሳዊ እርዳታን ከማካፈል ጋር የተዛመደ ነው። የእምነት ስጦታ እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ሊፈጽመው ስለሚፈልገው፥ ራሱ እንደሚመራ እና ተፈላጊውን ሁሉ እንደሚያዘጋጅ ማመን ነው። መናፍስትን መለየት በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን አስፈላጊ ነበር። ምክንያቱም ሰይጣን የእግዚአብሔርን ሥራ እና ቃል በማመሳሰል ለማሳሳት ይጥር ስለነበር ነው። ዛሬ መንፈስ ለእኛ ለይቶ ማወቅን የሚሰጠን በተለይ የተጻፈውን የእግዚአብሔር ቃል በመጠቀም ነው (1ኛ ዮሐ 2፡18-24፤ 4፡1-6)።

አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ልዩ ልዩ ስጦታዎችን የንግግር ስጦታዎች፥ የምልክት ስጦታዎች እና የአገልግሎት ስጦታዎች ብለው ከፋፍለዋቸዋል። ይሁንና በእያንዳንዱ ስጦታ በጣም በመወሰድ ጳውሎስ ስጦታዎችን የዘረዘረበትን ዕቢይ ምክንያት እንዳንዘነጋ፥ ይኸውም ስጦታዎች በአገልግሎቶቻችን አማካኝነት ወደ አንዱ አካል እንደሚያስተሳስሩን ማሳሰብ ነው። እኛ እንደምንፈልገው ሳይሆን መንፈስ ቅዱስ «እንደ ወደደ» እነዚህን ስጦታዎች ያድላል። ማንም ክርስቲያን ስለ ራሱ ስጦታ ማጉረምረም ወይም መመጻደቅ የለበትም። እኛ በአንድ አካል ውስጥ ያለን እርስ በርስ የምንገላገል ብዙ ብልቶች ነን፡፡ 

አንድ ጥምቀት ወስደናል (12፡12-13)። «የመንፈስ ጥምቀት» የሚለው ሐረግ ከመጀመሪያው የአዲስ ኪዳን ትርጉሙ ማፈንገጡ የሚያሳዝን ነው። እግዚአብሔር ለእኛ የተናገረው ግራ ልንጋባ በማይገባን መንፈስ ወለድ ቃላት ነው (1ኛ ቆሮ. 2፡12-13)። በመንፈስ መጠመቅ የሚከናወነው በሚያምነው ኃጢአተኛ ውስጥ መንፈስ ሲገባ፥ አዲስ ሕይወት ሲሰጠው እና የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አካል ሲያደርገው በሚከሰተው ለውጥ ወቅት ነው። ሁሉም አማኞች ይህን አንዴ እና ለሁሌ የሚሆነውን ጥምቀት ተቀብለውታል (12፡13)። አንዴ የተለማመድነው ስለሆነ እና መደጋገም ስለሌለበት፥ መጽሐፍ ቅዱስ በየትኛውም ስፍራ እንድንሻ ው አያዝዘንም። 

«በመንፈስ መሞላት» (ኤፌ. 5፡18) ማለት ሕይወታችን በመንፈስ ቁጥጥር ሥር መሆኑ ማለት ነው። (በመጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ነገር መሞላት ማለት በዚያ ነገር ቁጥጥር ሥር መሆን» ነው።) እንድንሞላ ታዝዘናል፤ ሁሉንም ለክርስቶስ ካስገዛን እና የመንፈስን ሙላት ከጠየቅነው ልንሞላ እንችላለን። ይህ ተደጋጋሚ የሚሆን ልምምድ ነው። ምክንያቱም ክርስቶስን ማክበር ከፈለግን ያለማቋረጥ በመንፈሳዊ ኃይል መሞላት አለብን። በመንፈስ መጠመቅ ማለት ወደ ክርስቶስ አካል መጠቃለል ማለት ነው። በመንፈስ ተሞላን ማለት ብልቶቻችን ለክርስቶስ ተገዙ ማለት ነው። 

በመለወጥ ጊዜ መንፈስ የማጥመቁ ማረጋገጫ በውስጥ የሚሰማ የመንፈስ ምስክርነት ነው (ሮሜ. 8፡14-16)። «በልሳኖች መናገር» አይደለም። በቆሮንቶስ ጉባኤ የነበሩ አማኞች በሙሉ በመንፈስ ተጠምቀው ነበር፤ ነገር ግን ሁላቸውም በልሳኖች አልተናገሩም (12፡30)። የመንፈስ ሙላት ማረጋገጫዎች ለመመስከር ኃይል ማግኘት (የሐዋ. 1፡8)፥ ደስታ እና ራስን መስጠት (ኤፌ. 5፡18)፥ ክርስቶስን መምሰል (ገላ. 5፡22-26)፥ እና እያደገ የሚሄድ የቃሉ እውቀት (ዮሐ 16፡12-15) ናቸው። 

በመለወጥ ወቅት ባገኘነው የመንፈስ ስጦታ አማካኝነት ሁላችንም የክርስቶስ ብልቶች ነን። ዘር፥ ማኅበራዊ አቋም፥ ሀብት፥ ፆታም እንኳ ቢሆን (ገላ 3፡28) ከጌታ ጋር ኅብረት ስናደርግ እና ስናገለግለው የሚጠቅሙን ወይም የሚጎድሉብን ነገሮች አይደሉም።

ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው

Leave a Reply

%d bloggers like this: