ወንጌል የኢየሱስ ክርስቶስን ሞት ማዕከል ያደርጋል (1ኛ ቆሮ. 2፡1-5)

ባለቤቴ መኪናችንን እየነዳች አጠገቧ ተቀምጬ ወደ ቺካጎ እየሄድን ሳለ እንድ እሳታሚ እንድገመግመው የሰጠኝን የአንድ ደራሲ መጽሐፍ እነብብ ነበር። አልፎ አልፎ የማጉተምተም ከዚያም ማጉረምረም እይሉት ማቃሰት የሚመስል ድምፅ አሰማ ነበር፤ በመጨረሻም ራሴን ነቀነቅሁና፥ «ኦ፥ ፍጹም! ይህን አላምንም!» አልኩኝ። 

«መጽሐፉን ያልወደድህ መሰለኝ፥ የሆነ ችግር አለው?» አለችኝ። 

«አሳምሮ ነዋ!» አልኳት። «ሁሉም ነገር የተበላሸ ነው ማለት ይቻላል፤ ምክንያቱም ይህ ሰው የወንጌሉ መልእክት በእርግጥ ምን እንደሆነ አያውቅም!» 

ይሁንና ደራሲው ለወንጌል ታማኝ የነበረበት ጊዜ ነበር። ነገር ግን በዓመታት መካከል፥ ወንጌልን በፍልስፍናዊ (ይመስለኛል የፖለቲካ) አመለካከት ማየት ጀመረ። ውጤቱ ጭራሽኑ ወንጌል ያልሆነ ቅይጥ መልእክት ነበር። 

ጳውሎስ በቆሮንቶስ ያገለግል በነበረ ጊዜ፥ ከጌታችን የተቀበለውን ተልእኮ ይታዘዝና ወንጌልንም ይሰብክ ነበር። በማቴዎስ 28፡18-20 እና በሐዋርያት ሥራ 18፡ 1-11 መካከል ቆንጆ መመሳሰል አለ። 

ክርስቶስ የሰጠው ሥራ 

( ማቴ. 28፡18-20) «እንግዲህ ሂዱና» (ቁ. 19) «ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው» [አስተምሩ]ቁ.19) «እያጠመቃችኋቸው»(ቁ19) «እያስተማራችኋቸው» (ቁ.20) «እነሆም እኔ…ከእናንተ ጋር ነኝ» (ቁ 20) 

የጳውሎስ አገልግሎት (የሐዋ. 18፡1-11) ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ መጣ (ቁ 1). . . ብዙ በሰሙ ጊዜ እምነው (ቁ. 8) ተጠመቁ (ቁ. 8) በመካከላቸውም የእግዚአብሔርን ቃል እያስተማረ ዓመት ከስድስት ወር ተቀመጠ (ቁ.11) እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ (ቁ. 10)  

በቆሮንቶስ የሆነው ዛሬም በየአብያተ ክርስቲያናቱ እየሆነ ነው። ሰዎች ፍልስፍናን (የሰውን ጥበብ) ከተገለጠው የእግዚአብሔር መልእክት ጋር እየቀየጡት ነው። ይህ ደግሞ ግራ መጋባትን እና ክፍፍልን እየፈጠረ ነው። የተለያዩ ሰባኪያን ለእግዚአብሔር ቃል የተለየ እቀራረብ አላቸው። አንዳንዶቹማ የራሳቸውን ቃል እየፈለሰፉ ናቸው! 

ጳውሎስ የወንጌል መልእክት ሦስት ፍሬ እሳቦችን ካብራራ በኋላ አንባቢዎቹ ወደ እነዚህ ፍሬ እሳቦች እንዲመለሱ ያበረታታቸዋል። 

ወንጌል የኢየሱስ ክርስቶስን ሞት ማዕከል ያደርጋል (1ኛ ቆሮ. 2፡1-5) 

ጳውሎስ እቀራረቡን ለቆሮንቶሳውያን ያስታውሳቸዋል (2፡1-2)። «እኔም፥» የሚለው መክፈቻ ቃል ሊተረጎም የሚችለው በ 1፡31- በእግዚአብሔር ይመካ በሚለው መሠረት «እንዲስማማ» ሆኖ ነው። ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ የመጣው እግዚአብሔርን ለማክበር ወይም ከፍ ለማድረግ እንጂ ራሱን ከፍ ሊያደርግ (በእርሱ እንዲመኩበት) ወይም ሃይማኖታዊ «አሞካሾችን» ሊመሠርት አልነበረም። 

ተዘዋዋሪ ፈላስፋዎች እና አስተማሪዎች ተከታዮችን ለማፍራት በገዛ ጥበባቸው እና በማራኪ አነጋገራቸው ላይ ይመኩ ነበር። የቆሮንቶስ ከተማ እንዲህ ባሉ «ቀልብ ዘራፊዎች» የተሞላች ነበረች። ጳውሎስ ግን በማራኪ እነጋገር ወይም በቀልጣፋ ክርክሮች አልተመካም፣ እንዲሁ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የእግዚአብሔርን ቃል አወጀ። እርሱ አምባሳደር እንጂ «ክርስቲያን ደላላ» አልነበረም። 

ጳውሎስ አስደናቂ ንግግር እና ፍልስፍና ተጠቅሞ ቢሆን ኖሮ ራሱን ከፍ አድርጎ ለማወጅ ያቀደውን ክርስቶስን ይደብቀው ነበር! «የክርስቶስም መስቀል ከንቱ እንዳይሆን፥ በሰዎች የንግግር ጥበብ አልሰብክም» (1፡17- አዲሱ መደበኛ ትርጉም)። 

በአንድ ቤተ ክርስቲያን ከምስባኩ በስተጀርባ በውብ ቀለማት ያሸበረቀ የመስተዋት መስኮት ነበር። ኢየሱስ በመስቀል እንደተሰቀለ ተሥሎበታል። አንድ እሑድ ዕለት ዘወትር ከሚያገለግለው መጋቢ በጣም አጠር የሚል እንግዳ ሰው አገለገለ። በዚህ ጊዜ አንዲት ትንሽ ልጃገረድ ያን እንግዳ ሰው ለጥቂት ጊዜ ሲናገር ከሰማችው በኋላ፥ ወደ እናቷ ዘወር ብላ እንዲህ ስትል ጠየቀቻት፤ «ብዙ ጊዜ እዚያ ላይ ቆሞ ኢየሱስን ማየት እንዳንችል የሚያደርገው ሰው ዛሬ የት ሄደ?» 

በጣም ብዙ የሆኑ የቃሉ ሰባኪያን ራሳቸውን እና ስጦታቸውን ስለሚያጎሉ የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር ከመግለጥ ይጎድላሉ። ጳውሎስ በክርስቶስ መስቀል ስለተመካ (ገላ 6፡14) የመልእክቱ ማዕከል አደረገው። 

ከዚያም ጳውሎስ ስለ ዝንባሌው ቆሮንቶሳውያንን እሳሰባቸው (2፡3-4)። ሐዋርያ ቢሆንም፥ ጳውሎስ ወደ እነርሱ የመጣው እንደ ትሑት አገልጋይ ነበር። በራሱ አልተመካም ነበር፥ ክርስቶስ ሁሉን ይሆን ዘንድ ራሱን ባዶ አደረገ። በተከታይ ዓመታት፥ ጳውሎስ ይህን ነገር እንደገና እንሥቶ ቆሮንቶስን ከወረሯት የሐሰት አስተማሪዎች (2ኛ ቆሮ. 10፡1-12) ጋር ራሱን አነጻጽሮበታል። በሚደክምበት ጊዜ፤ እግዚአብሔር እንደሚያበረታው ጳውሎስ ተምሮአል። 

ጳውሎስ ይመካ የነበረው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ላይ ነው። ለአገልግሎቱ ኃይልን የሰጠው ልምምዱ ወይም ችሎታው አልነበረም፤ ይህ የእግዚአብሔር መንፈስ ሥራ ነበር። የእርሱ ስብከት «ጭብጥ መግለጫ» እንጂ «የድርጊት ስኬት» አልነበረም። ጭብጥ መግለጫ የሚለው ሐረግ ሲተረጎም «በችሎት የቀረበን ሕጋዊ ማረጋገጫ» ያመለክታል። መንፈስ ቅዱስ የጳውሎስን ስብከት ሕይወትን ለመለወጥ ተጠቅሞበታል፤ ስለሆነም መልእክቱ ከእግዚአብሔር ለመሆኑ የሚፈለገው ማረጋገጫ ይኸው ነበር። በክፋት የተሞሉ ኃጢአተኛች በእግዚአብሔር ኃይል ተለውጠዋል! (1ኛ ቆሮ. 6፡9-11)። 

ይሁን እንጂ፥ ጳውሎስ አገልጋዮች ሆን ብለው አድበስብሰው ይስበኩ፥ ወይም እግዚአብሔር የሰጣቸውን ስጦታዎች ይተዉ ማለቱ እንዳይደለ ልብ ልንል ይገባል። እንደነ ቻርልስ ስፐርጀን እና ጆርጅ ዋይትፊልድ ያሉ ሰዎች ኃይል የተላበሱ ቃላትን የሚያዥጎደጉዱ ተናጋሪዎች ነበሩ፤ ሆኖም ግን በተፈጥሮአዊ ችሎታዎቻቸው አልተመኩም። በአድማጮቻቸው ልብ መንፈስ ቅዱስ እንዲሠራ ተማመኑ፤ እርሱም ደግሞ ሠራ። ቃሉን የሚያገለግሉ መዘጋጀትና እግዚአብሔር የሰጣቸውን ማንኛውንም ስጦታ መጠቀም አለባቸው ሆኖም ግን ትምክህትን በራሳቸው ላይ ማኖር የለባቸውም። (2ኛ ቆሮ. 3፡5ን ተመልከት።) 

በመጨረሻም፥ ጳውሎስ ስለ ዓላማው እሳሰባቸው (2፡5)። በእግዚአብሔር እንጂ እግዚአብሔር በላከው መልእክተኛ እንዳይተማመኑ ፍላጎቱ ነበር። በሰብአዊ ጥበብ ላይ ተመክቶ የደኅንነትን ዕቅድ እንደ እንድ ሥርዓተ ፍልስፍና አቅርቦት ቢሆን ኖሮ፥ ያኔ ቆሮንቶሳውያን እምነታቸውን በገለጻ ላይ ባደረጉ ነበር። ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ቃል በእግዚአብሔር ኃይል ስላወጀ፥ በእርሱ አማካኝነት ያመኑት እምነታቸውን ያሳረፉት ጭብጥ መግለጫ ላይ ስለነበር እግዚአብሔር በሕይወታቸው መሥራቱን ተለማምደውታል። 

ከዓመታት በፊት፥ እንድ ብልኅ ክርስቲያን እንዲህ አለኝ፥ «ሰዎችን ወደ ክርስቶስ በምትመራበት ጊዜ፥ የዳናችሁት ይህን ወይም ያን ስላደረጋችሁ ነው ብለህ ከቶ አትንገራቸው። ለሰዎች እንደዳኑ መመስከር የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነው። እርሱ በሥራ ላይ ካልሆነ ደኅንነት ሊመጣ አይችልም።» እውነትም በሳል ምክር ነው! 

በመጋቢነት እገለግል በነበርኩበት ቤተክርስቲያን በጣም ጥሩ የሆነ በታማኝነት የሚከታተል ባለሙያ ሰው ነበረ ይህ ሰው ያልዳነ ሆኖም ግን ወንጌልን የማይቃወም ነበር። እርሱ የእግዚአብሔርን ቃል ማድመጡን ቀጥሎ ሳለ ብዙዎቻችን እንጸልይለት ነበር። አንድ ቀን የእርሱ ጓደኛ የሆነ ክርስቲያን ሰው ወደ ክርስቶስ እመልሰዋለሁ ወይ ይለይለታል ብሎ ወሰነ! ለበርካታ ሰዓታት የክርክር ውርጅብኝ አወረደበት እና ሰውየው በመጨረሻ «የኃጢአተኛ ሰው ጸሎት ጸለየ።» ከዚያም ወደ ቤተ ክርስቲያን መምጣቱን አቆመ! ለምን? ምክንያቱም እውነት ያልሆነን ነገር እንዲቀበል ስለነዘነዘው እና እስከ መጨረሻ ሊቀጥል አለመቻሉን ስለተገነዘበ ነበር። በኋላ ግን ክርስቶስን አመነ እና በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት፤ የደኅንነትን ማረጋገጫ አገኘ። እስከዚያ ድረስ፥ ድነሃል ወይ ብሎ ማንም ቢጠይቀው፥ «እዎ=ቶም ድነሃል! ብሎኛል» ይል ነበር። መንፈስ ማረጋገጫ በሚሰጥበት ጊዜ አቤት ያለው ልዩነት! 

ወንጌል ዛሬም የሰዎችን ሕይወት የሚለውጥ ኃይል ነው (ሮሜ 1፡16)። የወንጌል ስርጭት ስኬታማነት በክርክራችን ወይም በአባባይ «ሽወዳችን» ላይ የሚመረኮዝ ሳይሆን፥ በሕይወታችን በሚሠራው የእግዚአብሔር መንፈስና በምናካፍለው ቃሉ ላይ የሚደገፍ ነው።

ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው 

Leave a Reply

%d bloggers like this: