የትዳር ጓደኛሞች ሁለቱም ክርስቲያኖች ሲሆኑ (1ኛ ቆሮ. 7፡1-11)

እስከዚህ ነጥብ ድረስ፥ ጳውሎስ ይገልጽ የነበረው በቆሮንቶስ ጉባኤ እንደሚገኙ የሚነገርላቸውን ኃጢአቶች ነበር። አሁን ግን ስለ ጋብቻ (7፡1፥25)፥ ለጣዖት ስለተሠዋ መብል (8፡1)፥ ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች (12፡1)፡ ስለ ሙታን ትንሣኤ (5፡1) እና ለአይሁድ ስለሚደረግ ሚሲዮናዊ መዋጮ (16፡) በጽሑፍ የጠየቁትን ጥያቄ ያነሣል። 

1ኛ ቆሮንቶስ 7ን በምታጠናበት ጊዜ፥ ጳውሎስ ምላሽ እየሰጠ ያለው ለተወሰኑ ጥያቄዎች መሆኑን ልብ በል። በአንድ ምዕራፍ የተሟላ የጋብቻ «ሥነ መለኮትን» እየገለጸ አይደለም። ይህን ተፈላጊ ርእስ በተመለከተ የተቀረው መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ማየት ተገቢ ነው። 

አንዳንድ ነፃ ሐያስያን ጳውሎስን የጋብቻና የሴቶች ተቃዋሚ ነው በማለት ከስሰውታል። በእርግጥ እነዚህ ክሶች ከእውነት የራቁ ናቸው። በቁጥር 6፥10፥12 እና 25 ላይ ስለጻፋቸው ነገሮች ጳውሎስ መለኮታዊ ምሪት ነበረኝ አላለም። ይልቁኑ፥ ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ወዳስተማረው ያመለክት ነበር (ማቴ. 19፡1-12፤ 5፡31-32፣ ማር. 10፡1-12፤ ሉቃ. 16፡18)። ኢየሱስ ጭራሽ ያላነሣቸውን አንዳንድ ጥያቄዎች ጳውሎስ መመለስ ነበረበት። ነገር ግን ጌታ ቀደም ብሎ ባስተናገደው ጉዳይ ላይ ጥያቄ ሲነሣ፥ ጳውሎስ የጌታን ቃል አጣቅሶአል። መለኮታዊ ምሪት እንዳጣ መናገሩ ሳይሆን፥ ጳውሎስ የገለጸው የጻፈው ነገር በሥልጣን ኢየሱስ ካስተማረው ጋር እኩል መሆኑን ነው። 

ጳውሎስ ክርስቲያናዊ ጋብቻን አስመልክቶ ስለ እግዚአብሔር ፈቃድ ገልጾአል፤ ምክሩንም ለሦስት የተለያዩ የአማኞች ቡድኖች አስተላልፎአል። 

የትዳር ጓደኛሞች ሁለቱም ክርስቲያኖች ሲሆኑ (1ኛ ቆሮ. 7፡1-11) 

ቤተ ክርስቲያን ትጠይቃቸው ከነበሩት ጥያቄዎች አንዱ፥ «አለማግባት ከጋብቻ የበለጠ መንፈሳዊነት አለው ወይ?» የሚል ይመስላል። ጳውሎስ ሲመልስ፥ ወንድ ወይም ሴት ሳያገቡ የመኖር ስጦታ ቢያገኙ ጥሩ ነው፤ አለማግባት ግን ከጋብቻ የተሻለ አይደለም፤ ለሁሉም ሰው የሚሆን የላቀ ደረጃ ም አይደለም ብሏል። ዶክተር ኬነት ወስት የጳውሎስን ምላሽ ሲተረጉሙ «በጽናት ሳያገቡ መኖር ለሰው ተገቢ፥ ክብሩ፥ እና ግብረገባዊ ብቃት ያለው ነው» ብለዋል። 

ቁጥር 6 ሳያገቡ መኖር የተፈቀደ እንደሆነ፥ ነገር ግን ትእዛዝ እንዳይደለ ይገልጻል፤ ቁጥር 7 ደግሞ ሁሉም ሳያገቡ የመኖር ስጦታ እንደሌላቸው ይነግረናል። ይህ ጌታችን በማቴዎስ 19፡10-12 ካስተማረው ትምህርት ጋር ይተሳሰራል፤ «ጃንደረቦች» የሚለው የሚያመለክተው ከጋብቻ የሚታቀቡትን ነው። «ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም» (ዘፍ 2፡18) በአጠቃላይ ለብዙ ሰዎች የሚሠራ እውነት ነው፤ ነገር ግን ጥቂቶች በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት ሳያገቡ ሊኖሩ የተጠሩ ናቸው። አለማግባታቸው «ያነሰ መንፈሳዊነት» ወይም «የላቀ መንፈሳዊነት» አይደለም። በአጠቃላይ በእግዚአብሔር ፈቃድ ላይ የሚወሰን ነው። 

የጋብቻ አንዱ ዓላማ «ከዝሙት ለመራቅ ነው»። ቁጥር 2 እግዚአብሔር በዚህ ጋብቻን ወይም ግብረ ሰዶማዊ «ጋብቻችን እንደማይደግፍ ግልጽ ያደርጋል። ከመጀመሪያው የነበረው የእግዚአብሔር ምሳሌ እና ትእዛዝ አንድ ሴት ለአንድ ወንድ መጋባቷ ነው። ይሁንና፥ ባል እና ሚስት ጤናማ የጋብቻ አካል የሆነውን የወሲብ ፍቅር መብታቸውን ያለ አግባብ መጠቀም የለባቸውም። የሚስት ሰውነት ላባል ነው፥ እንደዚሁ የባል ሰውነትም ለሚስት ነው፤ ደግሞም እያንዳንዱ ለሌላው አሳበ መሆን ይገባዋል። ወሲባዊ ፍቅር ውብ የመተናነጫ መሣሪያ እንጂ የመጠፋፊያ ጦር ዕቃ አይደለም። አንዱ ለሌላው ወሲብን መከልከሉ ንጥቂያ ማካሄድ (1ኛ ተሰ. 4፡6ን ተመልከት) እና የትዳር ጓደኛሞች ለእርካታቸው ወደ ውጭ እንዲመለከቱ የሚያደርግ ነው። 

ለሁሉም ነገር መሆን እንዳለበት ሁሉ መንፈሳዊው ሥጋዊውን መግዛት አለበት፤ ምክንያቱም ሰውነታችን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነውና። ባል እና ሚስት ሙሉ ፍላጎታቸውን ለጸሎት እና ለፆም ለመስጠት (7:5) ከወሲብ ይታቀቡ ይሆናል፤ ሆኖም ግን ይህንን ለረጅም ጊዜ መለያየት እንደ ምክንያት ሊጠቀሙበት አይገባም። ጳውሎስ ክርስቲያን ባለ ትዳሮች በመንፈሳዊውም በሥጋዊውም ነገር እርስ በርስ ስምምነት እንዲኖራቸው ያበረታታል። 

ከቁጥር 8-9 ባለው፥ ጳውሎስ በቁጥር 1 ስላላገቡት እና ስለ መበለቶች የተገለጸውን መርህ በማዛመድ ራሳችሁን መቆጣጠር የማትችሉ ከሆነ አግቡ ይላል። 

ቤተ ክርስቲያን የጠየቀችው ሳያገቡ ስለመኖር ብቻ አልነበረም፤ ነገር ግን ስለ መፋታትም ጳውሎስን ጠይቃለች። ኢየሱስ ይህን ጥያቄ አስተናግዶት ስለነበር፥ ጳውሎስ የእርሱን ትምህርት ጠቀሰ፡፡ ባል እና ሚስቶች መፋታት የለባቸውም (ቁጥር 39ን ተመልከት)። ፍቺ የሚፈጠር ከሆነ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወገኖች ሳያገቡ መኖር እለባቸው ወይም እርቅ መፈለግ አለባቸው። 

ለጋብቻ በጣም ተገቢው ይህ ነው። ኢየሱስ ከዚህ የሚወጣ አንድ ነገር አድርጎአል። ከሁለቱ ወገኖች አንዱ የዝሙት ወንጀለኛ ከሆነ፥ ይህ ለፍቺ መሠረት ይሆናል። ከዚህ በጣም የሚሻለው ንስሐ መግባት፥ ይቅርታ እና እርቅ መፍጠሩ ነው፤ ነገር ግን እነዚህ ከጥያቄ ውጭ ከሆኑ፥ ጥፋተኛ ያልሆነው ወገን ሊፈታ ይችላል። ይሁንና፥ ፍቺ የመጨረሻ አማራጭ ነው፤ በመጀመሪያ በተገኘው መንገድ ሁሉ ጋብቻውን መልሶ ለማቆም መፍትሔ መፈለግ አለበት። 

ባል እና ሚስት ለጌታ ራሳቸውን የሰጡ ሲሆን እና በጋብቻ ግንኙነታቸው አንዳቸው ሌላቸውን ለማስደሰት ሲጥሩ፥ ጋብቻው በጣም አርኪ ከመሆኑ የተነሣ ከሁለቱ ወገን የትኛውም በእርካታ ወደ ሌላ እንደማይቀላውጥ በመጋቢነት ልምምዴ የደረስሁበት እውነት ነው። አንድ ክርስቲያን አማካሪ አንድ ጊዜ፥ «በጋብቻ ውስጥ የወሲብ ችግሮች የሉም»፥ ያሉት ችግሮች «የወሲብ ችግርን እንደ አንድ ምልክታቸው አድርገው የሚከሰቱ የምልዐተ ባሕርያት ውዝግቦች ናቸው» አለኝ። ዛሬ በክርስቲያኖች (በቀሳውስቱ እንኳን ሳይቀር) እያሻቀበ ያለው አስፈሪ የፍቺ አዝማሚያ የእግዚአብሔርን ልብ የሚያሳዝን ነው። 

ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው 

Leave a Reply

%d bloggers like this: