ጳውሎስ ቀደም ሲል በቁጥር 8-9 ላይ ለዚህ ቡድን አጠር አድርጎ ተናግሮ ነበር፤ ነገር ግን በዚህ በመዝጊያ ምዕራፍ ላይ፥ በዝርዝር ያቀርበዋል። የእነርሱ ጥያቄ፥ «ክርስቲያን ማግባት አለበት ወይ? በቤተ ክርስቲያን ላያገቡ እያረጁ ያሉ ሴቶችስ ዕጣ ፈንታ እንዴት ነው?» የሚል ነበር። (ቁጥር 36ን ተመልከት።) ምናልባት ጳውሎስ ይህን የሚናገረው ለዓቅመ-ሔዋን ለደረሱ ልጃገረዶች ወላጆች ሳይሆን አይቀርም። ኢየሱስ በዚህ ርእስ ላይ ምንም ዓይነት የተለየ ትምህርት ዕላልሰጠ፥ ጳውሎስ ከጌታ እንደተማረ ሰው ምክሩን ሰጥቶአል። ለጋብቻ ውሳኔ በሚያደርጉበት ጊዜ ብዙ ሁኔታዎችን እንዲያጠኑ አሳሰባቸው።
በመጀመሪያ ያለህበትን ሁኔታ አጢን (7፡25-31)። ወቅቱ ዓለም በለውጥ ውስጥ የምታልፍበት (ቁ. 31) የጭንቀት (ቁ26) ጊዜ ነበር። ጌታን ለማገልገል የጊዜ ውጥረት ነበር (ቁ 29)። መረጃ ባይኖረንም በቆሮንቶስ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ውጥረት ነበር ማለት ያስችላል። ከችግሮቹ እኳያ ሲታይ፥ ሰው ባያገባ የሚመረጥበት ጊዜ ነበር። ይሁን እንጂ እንዲህ ሲባል ያገቡ ሰዎች ፍቺ ይፈልጉ ማለት አልነበረም (ቁ 27)። የጳውሎስ ምክር ያተኮረው ላላገቡት ነበር።
ይህም ማለት ማንም አያግባ የሚል ሳይሆን፤ ነገር ግን የሚያገቡ ሰዎች ከጋብቻው ጋር አብረው የሚመጡትን ፈተናዎች ለመቀበል የተዘጋጁ መሆን አለባቸው ማለት ነው (ቁ.28)። እንዲያውም፥ የተጋቡት እንኳ እንዳልተጋቡ ሆነው ለመኖር እስኪገደዱ ሁኔታው ከፍቶ የነበረ ይመስላል (ቁ. 29)። ምናልባት ጳውሎስ የሚናገረው ከኑሮ ጫና ወይም ከስደት የተነሣ እየተለያዩ ያሉትን ባል ና ሚስት ሳይሆን አልቀረም።
ሁኔታዎችን ማጤን ዛሬ ለተጫጩ ሰዎች መልካም ምክር ነው። የመጀመሪያ ጊዜ ተሞሻሪዎች አማካይ እድሜ እያሻቀበ ነው፤ ይህም እጮኛሞች ለመጋባት ብዙ መጠበቅ እንዳለባቸው ይጠቁማል። በመጋቢነት አገልግሎቴ በምሰጠው ቅድመ-ጋብቻ ምክር፥ ለእጮኛሞች የማሳስበው በሠርግ በጣም ርካሹ ነገር የጋብቻ የምስክር ወረቀት መሆኑን ነው። ከዚያ በኋላ የሁሉም ነገር ዋጋ ይንራል!
ሁለተኛ፥ ኃላፊነቶችን በቅንነት ቅረባቸው (7፡32-35)። በዚህ ስፍራ አጽንኦት ያረፈበት ቃል ሳትባክኑ የሚል ሲሆን፥ «ሳትጨነቁ፥ ከመጠበብ የተነሣ ሳትበጣጠቁ» ማለት ነው። ሁለት ሰዎች አንድ ወይም ሌላ ዓይነት ሽክም ሳይጫናቸው አብረው መኖር አይችሉም፤ ነገር ግን ወደ ጋብቻ ውስጥ ተደናብሮ በመግባት የባሰ ችግር መፍጠር አያስፈልግም። ጋብቻ የብስለት መለኪያን ይፈልጋል፤ ዕድሜ ደግሞ ለብስለት ዋስትናን አይሰጥም።
አሁንም እንደገና፥ ጳውሎስ ለጌታ መኖርን በአጽንኦት አሳሰበ። ወንድ ወይም ሴት አግብተው እግዚአብሔርን በተገቢው መንገድ ማገልገል አይችሉም የሚል አሳብ አልሰጠም፤ ምክንያቱም ይህ የተቻላቸው እጅግ ብዙ ሰዎች እንዳሉ እናውቃለን። ነገር ግን የገባው የእግዚአብሔር አገልጋይ ጓደኛውን ወይም ጓደኛዋን እንዲሁም እግዚአብሔር የሚሰጣቸውን ልጆች ማሰብ አለባቸው፤ ይህ ደግሞ የአሳብ መከፋፈልን ያመጣል። ጆን ዌስሊ እና ጆርጅ ዋይትፊልድ ሁለቱም ባያገቡ ኖሮ በጣም የተሻለ ሁኔታ ላይ መገኘታቸው የታሪክ እውነታ ነው፤ የዌስሊ ባለቤት መጨረሻ ላይ ጥላው ሄዳለች፤ ዋይትፊልድ በጣም ይጓዝ ስለነበር ባለቤቱ ለረጅም ጊዜ በብቸኝነት ትኖር ነበር።
ለክርስቶስ የተሰጠህና ቃሉን የምትታዘዝ ከሆነ ጌታንና የትዳር ጓደኛህን ማስደሰት ትችላለህ። ብዙዎቻችን ደስተኛ ቤተሰብና እርኪ ጋብቻ በክርስቲያናዊ የአገልግሎት ውጣ ውረዶች አስደናቂ መጽናኛ ሆነው አግኝተናል። ዝነኛው የስኮቲሽ ሰባኪ በአንድ ጉዳይ ላይ ከወሰደው አቋም የተነሣ የሕዝብ ተቃውሞ በጣም አስቸግሮት ነበር፥ በየቀኑ ለማለት ይቻላል በጋዜጦች ላይ ጎጂ ዘገባ ይቀርብበት ነበር። አንድ ጓደኛው አንድ ቀን እገኘውና «በዚህ ሁሉ ተቃውሞ ውስጥ እንዴት ልትቆም ቻልክ?» ሲል ጠየቀው። እርሱም ዝግ ብሎ «በቤቴ ደስተኛ ስለሆንኩ ነው» በማለት መለሰ።
እግዚአብሔርን ለማገልገል ጥሪ እንዳላቸው የሚሰማቸው ያላገቡ አማኞች ጋብቻ አገልግሎታቸውን ይደግፍ ወይም ያስተጓጉል እንደሆነ ለማየት የራሳቸውን ልብ መመርመር ያስፈልጋቸዋል። ተመሳሳይ ጥሪ ያላቸውን የትዳር ጓደኛ ለመምረጥም ጠንቃቃ መሆን አለባቸው። እያንዳንዱ ሰው የራሱ የሆነ ስጦታና ከእግዚአብሔርም ጥሪ ስላለው ለቃሉ መታዘዝ አለበት።
ሦስተኛ፥ እያንዳንዱ ሁኔታ ልዩ ነው (7፡36-38)። ጳ ውሎስ እዚህ ላይ የሚናገረው ላላገቡ ልጃገረዶች አባቶች ነው። በዚያን ዘመን፥ ጋብቻን የሚያቀናጁት ወላጆች፥ በተለይም አባቶች ነበሩ (2ኛ ቆሮ. 11፡2)። ጳውሎስ በቁጥር 35 ላይ ሁኔታዎችን ያላገናዘበ ሁሉም ሊከተለው የሚገባ «ብረት ለበስ» ሕግ እንደማያስቀምጥ ተናግሮአል። አሁን ደግሞ አባት ሴት ልጁን ለጋብቻ ለመስጠት ወይም ላለመስጠት ነፃ ፈቃድ እንደነበረው አብራራ።
ብዙ ጊዜ በቤተ ክርስቲያኖች ጋብቻዎች በ«ጣምራ» ሲመጡ አስተውያለሁ። አንዱ ጣምራ ትጭጭት እንደተፈጸመ ብዙ ሳይቆይ አራቱ ይከተላሉ። እነዚህ ሁሉ ትጭጭቶች በእግዚአብሔር ፈቃድ የሆኑ ከሆነ በጣም አስደሳች እና ድንቅ ልምምድ ነው፤ ነገር ግን እኔ የምፈራው አንዳንዶቹ የሚተጫጩት ባልንጀሮቻቸውን ለመምሰል ያህል እንዳይሆን ነው። አንዳንዴ በክርስቲያን ትምህርት ቤቶች ያሉ እጮኛሞች «የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ጭንቀት» ብዬ በምጠራው ሁኔታ ውስጥ ይገቡና ወዲያው እንደተመረቁ ከትጭጭት ተላቅቀው በጋብቻ ይቆራኛሉ። ይህን የሚያደርጉት «በቤተክርስቲያን ውስጥ ለመጠባበቅ» እንዳይዳረጉ በማስብ ነው። የሚያሳዝነው ከእነዚህ ጋብቻዎች የሚሳካላቸው የተወሰኑ ናቸው።
ምንም እንኳ ዘመናዊ የትጭጭትና የጋብቻ አካሄዳችን ለቆሮንቶሳውያን ባዕድ ቢሆንም፥ ጳውሎስ ለእነርሱ የሰጠው ምክር ዛሬም ይሠራል። እጮኛሞች ከወላጆቻቸውና ከቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጋር መመካከራቸው ብልህነት ነው አለበለዚያ በኋላ ወደሚጸጸቱበት ነገር ውስጥ ይዘፈቃሉ።
ጳውሎስ በቁጥር 36 ላይ «ማግባት ወደሚገባ ዕድሜ» (የዕድሜ አበባ) የሚለውን በጠቀሰ ጊዜ ቁልፍ የሆነ ችግርን ነበር የመታው። ይህ ልጃ ገረዲቱ እያረጀች ናት የሚል ጥንቃቄ የሚያስፈልገው አነጋገር ነው። ዶክተር ኬነት ወስት አባባሉን «የወጣትነት አበባዋን ያሳለፈች» በማለት ይተረጉሙታል። ይህች ሴት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ «ባለቤት የለሽ በረከቶች» እንዱ ወደመሆን ጉዞ ጀምራለች ማለት ነው። አደጋው ቆሞ መቅረትን ለማስቀረት ስትል ብቻ ጋብቻ ውስጥ ዘልላ ስለምትሰጥም፥ ስሕተት ትሠራ ይሆናል የሚል ነው። አንድ መጋቢ የሆነ ጓደኛዬ ለእጮኛሞች «በተጣመመ ጋብቻ ውስጥ ከመኖር፥ በብቸኝነት ላጤ ሆኖ መኖር ይሻላል!» ይል ነበር።
እያንዳንዱ ሁኔታ ልዩ ስለሆነ፥ ወላጆችና ልጆች የጌታን ፈቃድ መሻት አለባቸው። ደስተኛ ጋብቻን ለማምጣት ከሁለት በላይ ክርስቲያን ሰዎችን ይጠይቃል። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስለሆነ ብቻ ክርስቲያናዊ ጋብቻ ሁሉ ለዛ አለው ማለት አይደለም።
በመጨረሻም፥ ጋብቻ የዕድሜ ልክ መሆኑን አስታውስ (7፡39-40)። የጋብቻ ትስስር ዘላቂ፥ የሕይወት ዘመን ውሳኔ እንዲሆን የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። በክርስቲያናዊ ጋብቻ ውስጥ «የሙከራ ጋብቻ» የለም፤ በሌላ በኩል «አምልጦ መውጣት» የሚል አመለካከትም አይኖርም። «ይህ አመለካከት የማያዋጣን ከሆነ፥ ምን ጊዜም ፍቺ እንፈጽማለን» የሚል ነው።
በዚህ ምክንያት፥ ጋብቻ ክመልክ፥ ከገንዘብ፥ ከስሜታዊ እርካታና ከማኅበራዊ ተቀባይነት ይልቅ ጠበቅ ባለ ነገር ላይ መመሥረት አለበት። ክርስቲያናዊ መሰጠት፥ ፀባይ እና ብስለት መኖር አለባቸው። ለማደግ፥ እርስ በርስ ለመማማር፥ ይቅርታ ለማድረግና ለመርሳት፥ እርስ በርስ ለመገላገል ፈቃደኝነት መኖር አለበት። ሁለት ሕይወቶችን በአንድ ለማጣበቅ የሚያስፈልገው ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮ.13 የገለጸው ዓይነት ፍቅር ነው ።
ጳውሎስ ባል የሞተባቸው ሴቶች «በጌታ ይሁን እንጂ » (ቁ 39) ለማግባት ነፃ መሆናቸውን በመንገር ይህንን ክፍል ደመደመው። ይህም ማለት አማኞች ማግባት ብቻ ሳይሆን፥ ነገር ግን፥ በእግዚአብሔር ፈቃድ ማግባት አለባቸው ማለት ነው። (ከላይ በተሰጡት ምክንያቶች) የጳ ውሎስ ምክር ሳያገቡ እንዲቆዩ ነው፤ ሆኖም ግን ውሳኔውን ለራሳቸው ትቶላቸዋል።
እግዚአብሔር በጋብቻ ዙሪያ «ግድግዳ» ያቆመው እስር ቤት ሊያደርገው ፈልጎ ሳይሆን አስተማማኝ ምሽግ እንዲሆን ነው። ጋብቻን እስር ቤት አድርጎ የሚያስብ ሰው ማግባት የለበትም። ሁለት ሰዎች በፍቅርና በደስታ እርስ በርስ ሲሰጣጡና ለጌታም ሲሰጡ የጋብቻ ሕይወት መተናነጫና መልሚያ ይሆናል። አብረው ያድጋሉ፥ ደግሞም እንደ አንድ «ቡድን» በቤታቸውና በቤተ ክርስቲያን ጌታን የማገልገልን ብልጽግና ያገኛሉ።
ይህን ምዕራፍ በምትከልስበት ጊዜ ጋብቻ ምን ያህል ጽኑ እንደሆነ ሳታደንቅ አታልፍም። የጳውሎስ ምክር ግልጽ የሚያደርገው እግዚአብሔር ጋብቻን አክብዶ እንደሚመለከትና ይህን ቃሉን ጥሰን ከጎጂ ጦስ እንደማናመልጥ ነው። ጳውሎስም ሆነ ኢየሱስ ልዩ በሆኑ ሁኔታዎች ፍቺ እንደሚኖር ቢያመለክቱም፥ ይህ ለባለትዳሮች ፈጽሞ የእግዚአብሔር የመጀመሪያ ምርጫ አይሆንም። እግዚአብሔር መፋታትን ይጠላል (ሚል. 2፡14-16)። ስለዚህ ሁሉም የእርቅ ጎዳናዎች ታስሰው ሳያልቁ ማንም አማኝ በእውነቱ ፍቺን ማሰብ የለበትም።
ምንም እንኳ ፍቺ የገጠመው ሰው በመጋቢነት እና በድቁና ለማገልገል እቀባ ቢኖርበትም (1ኛ ጢሞ. 3፡2፥12)፥ በሌሎች አቅጣጫዎች ከማገልገል መከልከል የለበትም። ያወቅሁአቸው ከፍተኛ ሰው አጥማጆች ከመለወጣቸው አስቀድሞ በአሳዛኝ የፍቺ ማንካ ያለፉ ሰዎች ናቸው። ሰው አገልግሎት እንዲኖረው የድቁና ወይም የመጋቢነት ሥራ ብቻ አይደለም የሚጠብቀው።
በማጠቃለያም፥ እያንዳንዱ ሰው ጋብቻን የሚያስብ ከሆነ፥ የሚከተሉትን ነጥቦች ራሱን መጠየቅ አለበት።
1. ከእግዚአብሔር የተሰጠ ስጦታ ምንድን ነው?
2. የማገባው (የማገባት) አማኝ ነው (ናት)?
3. ጋብቻ እንዳደርግ ሁኔታዎች ይፈቅዳሉ?
4. ጋብቻ ለክርስቶስ የምሰጠውን አገልግሎት የሚነካው እንዴት ነው?
5. ወደዚህ ኅብረት ስገባ ዕድሜ ልክ ልቆይበት ተዘጋጅቻለሁን?
ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው