ቤተሰብ -በብስለት ማደግ (1ኛ ቆሮ. 3፡1-4)

ብሪታኒያዊው የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ ዶክተር ጂ. ካምቤል ሞርጋን እራት ወንድ ልጆች ነበሯቸው፤ አራቱም ወንጌል አገልጋዮች ሆኑ። አንዱ ሰው ከልጅ ልጆቻቸው እንዱን እርሱም የወንጌል እገልጋይ ይሆን እንደሆነ ሲጠይቀው፥ «የለም፥ እኔ ለኑሮዩ ለመሥራት ነው ዕቅዴ» በማለት መለሰለት። 

አንድ መጋቢ ማድረግ የሚጠበቅበት ምንድን ነው? «የወንጌል አገልግሉት ሥራ በእርግጥ ምንድን ነው»? ይህን ካላወቅን የወንጌል አገልጋዩን ሥራ ከቶውንም መገምገም አንችልም። በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ከዚህ የበለጠ በርካታ ችግሮችን የሚፈጥር ሌላ ጉዳይ ምናልባት አይኖርም፥ መጋቢውና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በእርግጥ ሥራቸውን እየሠሩ እንዳሉ የምናውቀው እንዴት ነው? 

ጳውሎስ በዚህ ምዕራፍ ሦስት የቤተ ክርስቲያን ምስሎችን ይሥላል። እነዚህኑ ምስሎች በመጠቀም የወንጌል አገልግሎት ምን መፈጸም እንደሚገባው አመልክቶአል። ቤተ ክርስቲያን ቤተሰብ ናት እናም ዓላማዋ እድገት ነው (3፡1-4)። ቤተ ክርስቲያን ማሣ ናት እናም ዓላማዋ ብዛት ነው (3፡5-9)። ቤተ ክርስቲያን ቤተ መቅደስ ናት እናም ዓላማዋ ጥራት ነው (3፡9-23)። 

ቤተሰብ -በብስለት ማደግ (1ኛ ቆሮ. 3፡1-4) 

ጳውሎስ በዓለም ላይ ሁለት ዓይነት ሰዎች እንዳሉ ቀደም ሲል ገልጾአል- ተፈጥሮአዊ (ያልዳህ እና መንፈሳዊ (የዳነህ። አሁን ደግሞ ሁለት ዓይነት የዳኑ ሰዎች እንዳሉ ያብራራል – በሳልና ጨቅላ (ሥጋዊ)። ክርስቲያን የሚያድገው መንፈስ ቃሉን በመመገብ እንዲያስተምረው ሲፈቅድ ነው። ጨቅላው ክርስቲያን የሚኖረው ለሥጋዊ ነገሮች ስለሆነ ለመንፈሳዊ ነገሮች ያለው ፍላጎት አነስተኛ ነው። በእርግጥ አንዳንድ ክርስቲያኖች የዳኑት ቅርብ ጊዜ ስለሆነ ጨቅላ ናቸው። ነገር ግን ጳውሎስ እዚህ ላይ የሚናገረው ስለ እነዚህ አይደለም። 

ጳውሎስ ይህንን ቤተሰብ ወደ ሕልውና ያመጣ «መንፈሳዊ አባት» ነው (4፡15)። በቆሮንቶስ ባገለገለባቸው 18 ወራት፥ ጳውሎስ መንፈሳዊ ልጆቹን በመመገብና በእምነት እንዲያድጉ በመርዳት ጥሮአል። በሰብአዊ ቤተሰብ ውስጥ ያለ አዲስ ሕፃን እንዲያድግ እና እንዲጠነክር ሁሉም ሰው እንደሚያግዝ ሁሉ –በእግዚአብሔር ቤተሰብ መንፈሳዊ ብስለት እንዲመጣ ማበረታታት ይገባናል። 

የብስለት ምልክቶች ምንድን ናቸው? አንደኛው መንገድ፥ በሳል ሰውን በሚመገበው ምግብ ማወቅ ትችላለህ። ይህን ምዕራፍ በምንጽፍበት ጊዜ ወንድ የልጅ ልጃችንና ሴት የልጅ ልጃችን ሲያድጉ እየተከታተልን ነበር። ቤኪን ገና እናቷ እያጠገበቻት ናት፥ ዮናታን ግን አሁን በጠረጴዛው አጠገብ ተቀምጦ ትንሿን መጠጫውን እና የመመገቢያ መሣሪያዎቹን ይዞ በመውተርተር ይሞካክራል። ልጆች እያደጉ በሄዱ ቁጥር፥ የተለያዩ ምግቦች መመገብ ይማራሉ። ከወተት ወደ ሥጋ (የጳውሎስን ቃላት ልጠቀምና) ይሸጋገራሉ። 

ልዩነቱ ምንድን ነው? ተለምዶአዊ ምላሽ «ወተት» በቃሉ ውስጥ ያሉትን ቀላል ነገሮች ሲወክል፥ «ሥጋ» ደግሞ ጠንካራ ዶክትሪንን ይወክላል። እኔ ግን በዚህ ተለምዶአዊ አገላለጽ አልስማማም፤ ማስረጃ ዬ ደግሞ ዕብራውያን 5፡10-14 ነው። ምንባቡ «ወተት» ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር እያለ ያደረጋቸውን እንደሚወክል፥ «ሥጋ» ደግሞ አሁን በመንግሥተ ሰማይ ሆኖ የሚያደርገውን እንደሚወክል የሚያስተምር ይመስላል። የዕብራውያን ጸሐፊ የአሁኑን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰማያዊ ክህነት ለማስተማር የፈለገ ሲሆን አንባቢያኑ ግን በጣም ጨቅላ ከመሆናቸው የተነሣ ሊያደርገው አልቻለም (ዕብ 6፡1 4ን ተመልከት)። 

የእግዚአብሔር ቃል መንፈሳዊ ምግባችን ነው – ወተት (1ኛ ጴጥ. 2፡2)፥ እንጀራ (ማቴ. 4፡4)፥ ሥጋ (ዕብ 5፡11-14) እና ማርም ጭምር [መዝ. (118)፡103] ነው። የውጪኛው ሰው በሰውነቱ ጤናማ እንዲሆን የተመጣጠነ ምግብ እንደሚያስፈልገው ሁሉ፥ የውስጠኛውም ሰው የተመጣጠነ መንፈሳዊ ምግብ ያስፈልገዋል። ሕፃን በወተት ይጀምራል፤ ነገር ግን ባደገና ጥርሶቹም በጎለበቱ መጠን ጠንካራ ምግብ ያስፈልገዋል። 

የአንድ እማኝን መንፈሳዊ ብስለት ወይም ጨቅላነት ለማወቅ አስቸጋሪ አይደለም፤ የሚጠይቀው ምን ዓይነት «ምግብ» እንደሚወድ ማወቅን ነው። ጨቅላው እማኝ ክርስቶስ አሁን በሰማይ ስላለው አገልግሎት የሚያውቀው ጥቂት ነው። በምድር ስለነበረው የጌታችን ሕይወት እና አገልግሎት ሐቆችን ያውቃል፤ ነገር ግን አሁን በሰማይ ስላለው አገልግሎት ጭብጦችን አያውቅም። የሚኖረው «በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች» እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ዶክትሪኖች አይደለም። የ 1ኛ ቆሮ. 2፡6-7 አስተውሎት የለውም። 

በዝውውር አገልግሎቴ በመቶዎች ለሚቆጠሩ አብያተ ክርስቲያናት እና ኮንፈረንሶች ሰብኬአለሁ። በእነዚህ ጊዜያት ለመዝናናት ሳይሆን አብርሆትን ለማግኘት ና ለመታነጽ ፍላጎት ለነበራቸው ምእመናን ምስጋናዬ ሁሌም ከፍ ያለ ነበር። ለጠፉት ወንጌልን መስበካችን አስፈላጊ ነው፤ ነገር ግን ለዳኑትም ደግሞ ወንጌልን መተርጎማችን እኩል አስፈላጊ ነው። አዲስ ኪዳን እንዳለ የወንጌል ትርጉም ና ተዛምዶ ነው። ለምሳሌ ጳውሎስ የሮሜን መልእክት የጻፈው ሮማውያን እንዴት መዳን እንዳለባቸው ለመንገር አልነበረም- ምክንያቱም እነርሱ የዳኑ ቅዱሳን ነበሩ። ደኅንነታቸው በመሠረቱ ምን እንደሚያካትት ለመግለጽ ጻፈላቸው። ይህ «የእግዚአብሔር ጥልቅ ነገሮች» በዕለታዊ ኑሮም እንዴት እንደሚተገበሩ ማብራሪያ ነበር። 

ብስለትን ማወቂያ ሌላም መንገድ አለ፤ በሳል ክርስቲያን ፍቅርን ይለማመዳል፤ ከሌሎችም ጋር መግባባትን ይፈልጋል። ጨቅላዎች ግን አለመስማማትና ኩርፊያ ይቀናቸዋል፤ በተራ ነገርም ስሜታዊነት ያጠቃቸዋል። ጨቅላዎች ብዙ ጊዜ ራሳቸውን ከጀግኖች፥ የስፖርት ጀግኖችም ይሁኑ የፊልም ጀግኖች፥ ጋር ማዛመድ ያምራቸዋል። በቆሮንቶስ የነበሩ «ጨቅላዎችም»፥ ታላቁ ሰባኪ የትኛው ነው ጳውሎስ፥አጵሎስ፥ ወይስ ጴጥሮስ በማለት ይፋተጉ ነበር። በመጫወቻ ስፍራ ያሉ ሕፃናት ሥራ ይመስል ነበር – «አባቴ አባትህን ያሸንፋል! አባቴ ከአባትህ ይበልጥ ሀብታም ነው!» 

መንፈሳዊ እውቀት የሌላቸው ጨቅላ ክርስቲያኖች በቤተ ክርስቲያን የመሪነትን ስፍራ ሲቆናጠጡ አደጋ ይከሰታል። ከአንድ በላይ የሆኑ ልባቸው የተሰበረባቸው መጋቢዎች፥ ንግግራቸው ተራራ ኑሮአቸው (ሕይወታቸው) ግን ተራ የሆኑ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን ምን እናድርጋቸው! ሲሉ በጽሑፍ ወይም በስልክ ይጠይቃሉ። (እንደ እውነቱ ከሆነ አንዳንዴ ያልበሰለ መጋቢ ሲያጋጥም፥ ምን እናድርግ ብለው የሚጠይቁት ሽማግሌዎች የቤተ ክርስቲያን ሹማምንት ናቸው ማለት አለብኝ!) 

የመጋቢ ሥራ ቤተ ክርስቲያን በመንፈሳዊ ነገር እንድታድግ በጌታም እንድትጠነክር መርዳት ነው። ይህ ደግሞ የሚሆነው በማያቋርጥ፥ በተመጣጠነ የቃሉ አገልግሎት ነው። ኤፌሶን 4፡1-16 ይህ ጉዳይ እንዴት እንደሚከናወን ያብራራል። ይኸውም እያንዳንዱ የአካል ክፍል የራሱን ድርሻ ማበርከት አስፈላጊው ስለመሆኑ ነው። 

እግዚአብሔር መንፈሳዊ ስጦታዎችን ለሕዝቡ ያድላል፤ ከዚያም እነዚህን በስጦታ የበለጸጉ ሰዎች ቅዱሳንን እንዲያንጹ ለተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ይሰጣል። አማኞች በሚያድጉበት ጊዜ ቤተ ክርስቲያንን ያንጹእታል። 

ጳውሎስ ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች በ 1ኛ ቆሮ. 12-14 ብዙ ይናገራል፤ ይሁን እንጂ የሚከተለው አሁን እዚሁ መነገር ይገባዋል። የበሰለ ክርስቲያን ስጦታዎቹን የማነጫ መሣሪያ አድርጎ ይጠቀምባቸዋል፤ ጨቅላው አማኝ ግን ስጦታዎቹን እንደ መጫወቻ አሻንጉሊቶች ወይም እንደ መመጻደቂያ ሽልማት አድርጎ ይጠቀምባቸዋል። አብዛኛዎቹ የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን አባላት በስጦታዎቻቸው «መመጻደቅ» ይወድዱ ነበር፤ ነገር ግን አንዳቸው ሌላውን ለማገልገል ና ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽ ፍላጎት አልነበራቸውም። 

የወንጌል አገልግሎት ዓላማው ምንድን ነው? ልጆቹ በእምነት እንዲጠነክሩ ና የበለጠ ኢየሱስን እንዲመስሉ፥ የእግዚአብሔርን ቤተሰብ ማፍቀር፥ መመገብ፥ እና መግራትን ያካትታል።

ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው 

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading