የሚራራ ልብ (2ኛ ቆሮ. 2፡1-11)

ከቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን አንዱ ጳውሎስን በእጅጉ አሳዝኖት ነበር። ይህ ሰው ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 5 ውስጥ የጠቀሰውና በግልጽ በዘማዊነት ኃጢአት የተጠመደው ሰው ይሁን፥ ወይም የጳውሎስን የሐዋርያነት ሥልጣን በይፋ የተፈታተነው ሌላው ሰው፥ በርግጠኛነት ልንናገር አንችልም። ጳውሎስ ይህንኑ ችግር ለመፍታት በፍጥነት ወደ ቆሮንቶስ የገሰገሰ ሲሆን (2ኛ ቆሮ. 2:14፤ 13፡1)፥ በተጨማሪም ስለ ሁኔታው የሚያሳዝን ደብዳቤ ጽፎላቸዋል። በዚህም ሁሉ፥ የርኅራኄ ልብ አሳይቷል። የጳውሎስን ፍቅር የሚያመለክቱትን የሚከተሉትን መረጃዎች ልብ በል። 

በመጀመሪያ፥ ለሌሎች ቅድሚያ ሰጥቷል (2ኛ ቆሮ. 2፡1-4)። ስለ ራሱ ስሜቶች ሳይሆን፥ በመጀመሪያ ለሌሎች ሰዎች ስሜቶች ያስብ ነበር። በክርስትና አገልግሎታችን፥ ትልቅ ደስታ የሚያመጡልን ሰዎች ትልቅ ሐዘንም ሊፈጥሩብን ይችላሉ፤ ጳውሎስም እያለፈበት የነበረው ይህንኑ ዓይነት ልምምድ ነበር። ከልቡ ከተሰማው ጭንቀት የፈለቀና በክርስቲያን ፍቅር የታጀበ ጠንካራ ደብዳቤ ይጽፋል። ዓቢይ መሻቱም ቤተ ክርስቲያኗ የእግዚአብሔርን ቃል እንድታከብር፥ አጥፊውን እንድትቀጣና ለማኅበረ-ምዕመናኑም ንጽሕናና ሰላም እንድታመጣ ነበር። 

«የወዳጅ ማቁሰል የታመነ ነው፤ የጠላት መሳም ግን የበዛ ነው» (ምሳሌ 27፡6)። ጳውሎስ የተጠቀማቸው ቃላት የሚወዳቸውን ወገኖች ሊያሳዝኑ እንደሚችሉ ያውቅ ስለነበር፥ ልቡ በሐዘን ተነክቶ ነበር። ዳሩ ግን (ማንኛውም አፍቃሪ አባት እንደሚያውቀው) ሰውን ስለ ፍቅር ብሎ በመጉዳትና በጠላትነት በማጥቃት መካከል ያለውንም ትልቅ ልዩነት ያውቅ ነበር። አንዳንድ ጊዜ የሚወዱን ሰዎች ራሳችንን እንዳንጎዳ ሲሉ ሊቀጡን ይገባል። 

ጳውሎስ ሐዋርያዊ ሥልጣኑን በመጠቀም ሰዎች እንዲያከብሩትና እንዲታዘዙት ለማድረግ ይችል ነበር፤ ይሁንና በፍቅርና በትዕግሥት ማገልገሉን መረጠ። እግዚአብሔር የጳውሎስ ዕቅዶች መለወጥ ቤተ ክርስቲያንን ከተጨማሪ ሕመም የመጠበቅ ዓላማ እንደ ነበረው ያውቅ ነበር (2ኛ ቆሮ. 1፡23-24)። ፍቅር ሁልጊዜም የሌሎችን ስሜቶች በማጤን ከማንኛውም ነገር በፊት ለእነርሱ የሚበጀውን ያስቀምጣል። 

እንዲሁም ፍቅር ለሌሎች ይሻሻሉና ያድጉ ዘንድ ለመርዳት ይሻል (2ኛ ቆሮ 2፡5-6)። እዚህ ላይ ጳውሎስ፣ የተቃወመውንና የቤተ ክርስትያንን ቤተሰብ የከፋፈለውን ሰው ስም እንዳልጠቀሰ ማስተዋል ጠቃሚ ነው። ይሁንና ጳውሎስ ለራሱ ለሰውየው ጥቅም ሲል ቤተ ክርስቲያኗ ይህንኑ ሰው እንድትቀጣ አሳስቧል። ይህ በ1ኛ ቆሮንቶስ 5 ውስጥ የተጠቀሰው ዘማዊው ሰው ከሆነ፥ ቤተ ክርስቲያን ጉባዔ ተቀምጣ እንደ ቀጣችውና እርሱም ከኃጢአቱ ንስሐ ገብቶ እንደ ተመለሰ እነዚሁ ቁጥሮች ያመለክታሉ። 

እውነተኛ ቅጣት የፍቅርን መኖር ያመለክታል (ዕብ 12 ተመልከት)። ልጆችን በማሳደጉ ረገድ «ዘመናዊ እይታ» ያላቸው አንዳንድ ወጣት ወላጆች ከመጠን በላይ እንደሚወዷቸው በመናገር፥ የማይታዘዙላቸውን ለመቅጣት አይፈልጉም። ዳሩ ግን በርግጥ ልጆቻቸውን ቢወዱ ኖሮ፥ ጥፋታቸውን በማሳየት እንዲታረሙ በረዷቸው ነበር። 

የቤተ ክርስቲያን የሥነ-ሥርዓት እርምጃ ተወዳጅነት ያለው ወይም በስፋት የሚሠራበት ዓይነት አይደለም። እጅግ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ይህን ዓይነቱ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ቅዱሳት መጻሕፍትን በመታዘዝ፥ «እውነትን በፍቅር በመናገር» (ኤፌ 4፡15) ምትክ፥ ብሉም ሁኔታውን በድፍረት ከመጋፈጥ የሚመርጡት፥ ነገሩ ወደ ጎን ገሸሽ አድርገው መተውን ነው። ንጽሕና ሳይኖር፥ እውነተኛ መንፈሳዊ ሰላም ሊኖር ስለማይችል፥ «የሆነውን ሁሉ ዋጋ ከፍሎ በሰላም መኖር» የሚለው መርሆ ጨርሶ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም (ያዕ.3፡15-18)። ወደ ጎን ገሸሽ ተደርገው የተተዉት ችግሮች በኋላ የመባዛትና ከቀድሞውም የከፉ ችግሮችን የመፍጠር ዕድል አላቸው። 

ጳውሎስ ያጋለጠውና ቤተ ክርስቲያን የቀጣችው ወንድም ፍቅር ያለበት አትኩሮት ተሰጥቶት ርዳታ አግኝቷል። ልጅ ሳለሁ፥ ምንም እንኳ ከተቀበልሁት የሚልቅ ቅጣት እንደሚገባኝ መናዘዝ ቢኖርብኝም፥ ቤተሰቦቼ የሚሰጡኝን ቅጣት ሁልጊዜም አልወድም ነበር። ዳሩ ግን አሁን ወደ ኋላ ተመልሼ ሳስብ፥ ራሴን ለባሰ ጥቃት እንዳላጋልጥ ለመከላከል ሲሉ ቤተሰቦቼ ከፍቅራቸው የተነሣ እስኪጎዱኝ ድረስ ጨክነው ሊቀጡኝ በመውደዳቸው እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። «ይህን ማድረጋችን አንተን ከሚጎዳው በላይ እኛንም ይጎዳናል» ሲሉ ይናገሩኝ የነበረው ምን ማለት እንደ ሆነ፥ አሁን በግልፅ ተረድቼዋለሁ። 

በመጨረሻም፥ ፍቅር ይቅር ይላል፤ ያበረታታልም (2ኛ ቆሮ. 2፡7-11)። ጳውሎስ የቤተ ክርስቲያኗ ቤተሰብ ያንን ሰው ይቅር እንዲል ያበረታታ ሲሆን፥ ይህንኑ ምክር ከሥራ ላይ እንዲያውሉት ጠንካራ ምክንያቶችን ያቀርባል። በመጀመሪያ ደረጃ፥ ለሰውየው ይቅርታ መደረጉ «ከልክ ባለፈ ኃዘን እንዳይዋጥ» (ቁ 7-8)፥ ለራሱ ጥቅም ሲባል ነበር። ይቅርታ የተሰበረውን ልብ ለመጠገን የሚረዳ መድኃኒት ነው። ቤተ ክርስቲያን ይህንኑ ንስሓ የገባ ሰው የፍቅሯ ተካፋይ የማድረጓን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነበር። 

በራሴ የመጋቢነት አገልግሎት ውስጥ፥ የሥነ-ሥርዓት እርምጃ የተወሰደባቸው አባላት ይቅርታ ተደርጎላቸው ወደ ኅብረቱ በተቀላቀሉባቸው ጉባዔዎች ላይ መልእክት አካፍያለሁ፤ እነዚህም በሕይወቴ ውስጥ ከፍተኛና የተቀደሱ ሰዓታት ነበሩ። የቤተ ክርስቲያኗ ቤተሰቦች ይቅርታ ለተደረገለት ወንድም ወይም እህት ኃጢአታቸው እንደ ተዘነጋና ወደ ኅብረቱ እንደ ተመለሱ ሲያረጋግጡላቸው አካባቢው ድንቅ በሆነ በጌታ ሕልውና ይሞላል። ልጁን የሚቀጣ ወላጅ ሁሉ ከቅጣቱ አስከትሉ ፍቅርና ይቅርታው ከልብ የመነጨ ለመሆኑ ዋስትና መስጠት አለበት፤ ይህ ካልሆነ ግን ቅጣቱ ከማቃናት ይልቅ የባሰ ጠማማነትን ያስከትላል። 

ክርስቲያኖች ለጌታ ሲሉ ይቅር ለተባለው ወንድም ፍቅራቸውን ያለማጓደል መለገስ አለባቸው (ቁ 9-10)። እንዲሁም ቅጣት ለወንድም መሰጠት ያለበት ግዴታ የመሆኑን ያህል፥ ለጌታም የመታዘዝ ኃላፊነትን ያቀፈ ጉዳይ ነው። ይህን የመሰለው ችግር የሚንፀባረቀው ባዘነው ሐዋርያና ኃጢአትን በፈጸመው ወንድም መካከል ብቻ ሳይሆን፥ ኃጢአትን በፈጸመው ወንድምና በሚያዝነው አዳኝ መካከልም ጭምር ነው። ያ ወንድም በእርግጥም በቤተ ክርስቲያን እና በጳውሎስ ላይ በደል ቢፈጽምም፥ ዳሩ ግን ከሁሉም በላይ በጌታ ላይ ኃጢአትን ሠርቷል። ፍርሃት የሚያጠቃቸው የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ይህን የመሳሰለውን ሁኔታ በታማኝነት በመጋፈጥ ምትክ «አለባብሰው» ሲያልፉት፥ የጌታን ልብ ያሳዝናሉ። 

ጳውሎስ ሦስተኛ ምክንያትም ሰጥቷል፡- ጥፋት የፈጸመውን ወንድም ለቤተ ክርስቲያኗ ደኅንነት ሲሉ ይቅር ማለት ነበረባቸው (ቁ 11)። ለኃጢአት ተገቢ የሆነ መጽሐፈ ቅዱሳዊ መፍትሔ እንዳይገኝለት ከምዕመናኑ አንዱ እንቅፋት ሲሆንና ይቅርታ ለማድረግ ሳይፈቅድ ሲቀር፥ ሰይጣን በማኅበረ-ምዕመናን ውስጥ ተልዕኮውን የሚፈጽምበት ቀላል «መነሻ» ያገኛል። ይቅርታን የማያደርግ መንፈስ ካለን፥ መንፈስ ቅዱስን በማሳዘን «ለዲያብሎስ ፈንታ» (ኤፌ 4፡27-32) እንሰጣለን። 

ከሰይጣን «ማታለያ ዘዴዎች» አንዱ ኃጢአት የሠሩ አማኞች ፍጹም ተስፋ እንዲቆርጡ መክሰስ ነው። በእኔም በኩል፥ ከሰይጣን ጭቆናና ክስ በታች በመውደቃቸው ምክንያት እርዳታ ሽተው ደብዳቤ የጻፉልኝ ወይም ስልክ የደወሉልኝ ሰዎች በብዛት አጋጥመውኛል። መንፈስ ቅዱስ የሚወቅሰን፥ ኃጢአታችንን ተናዝዘን ለመንጻት ወደ ክርስቶስ እንድንመለስ ሲሆን፥ ዳሩ ግን ሰይጣን ተስፋ ቆርጠን የእምነት ጉዞአችንን እንድንተው ይከሰናል። 

ያጠፋው ወንድም ወይም እህት ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ አኳያ ከተቀጡና ንስሐ ከገቡ በኋላ፥ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቤተሰብ ይቅርታ በማድረግ እንደ ቀድሞው ሊያቅፏቸው ይገባል፤ ነገሩም ዳግመኛ ላይታወስ መደምደም አለበት። (ዳግም ላይወሳ)። የቤተ ክርስቲያኒቱ ቤተሰብ ወይም ከቤተሰቡ ውስጥ ማንኛውም ሰው ይቅርታን የማያደርግ መንፈስ ካለው፥ ሰይጣን በቤተ ክርስቲያን ላይ አዳዲስ ጥቃቶችን ለማስከተል በዚሁ ቀዳዳ ይጠቀማል። 

ጳውሎስ ንጹሕ ሕሊናና የሚራራ ልብ ስለ ነበረው፥ ከፊቱ የተጋረጡትን ችግሮች ለማሸነፍ ችሏል። ዳሩ ግን ለድል ያበቃው ሦስተኛው መንፈሳዊ ሀብት ቀጥሎ የተጠቀሰው ነበር::

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading