ውድ መዝገብ አለን (2ኛ ቆሮ. 4፡7-12)

ጳውሎስ ንጽጽሩን ከአዲስ ፍጥረት ክብር ወደ ሸክላው ዕቃ ውርደት ያሻግራል። አማኙ «የሸክላ ዕቃ» ሲሆን፥ ውድ የሚያደርገው በሸክላው ውስጥ የተቀመጠው ዕቃ (መዝገብ) ክቡርነት ነው። የዕቃው ምስል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተደጋግሞ የተገለጸ በመሆኑ፥ ከዚህ ውስጥ ብዙ ነገሮችን ልንማር እንችላለን። 

በመጀመሪያ ደረጃ፥ እግዚአብሔር በእኛነታችን የፈጠረን፥ እንድንፈጽመው የሚፈልግብንን ሥራ ለማከናወን እንድንችል ነው፡ እግዚአብሔር ስለ ጳውሎስ ሲናገር፥ «ይህ በአሕዛብ …. ዘንድ ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና» (የሐዋ. 9፡15) ብሏል። ማንኛውም ክርስቲያን ስጦታዎች ወይም ችሉታዎች እንደ ሌሉት በመግለጽ፥ ወይም በውስንነቶቹ ወይም በአካለ-ስንኩልነቱ ምክንያት በእግዚአብሔር ላይ ማንጎራጎር የለበትም። መዝሙር (139)፡13-16 የዝርያ መዋቅራችን በእግዚአብሔር እጆች ውስጥ እንዳለ ይናገራል። እያንዳንዳችን እኛነታችንን ተቀብለን በእኛነታችን መኖር አለብን። 

ስለ ዕቃው የሚፈለገው ነገር ቢኖር ንጹሕ፥ ባዶና ለአገልግሎት ተዘጋጅቶ መቅረቡ [መገኘቱ ነው። እያንዳንዳችን «ለክብር የሚሆን፥ የተቀደሰም [የተለየ]፥ ለጌታውም የሚጠቅም ለበጎም ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ዕቃ» (2ኛ ጢሞ. 2፡21) ለመሆን መጣር አለብን። እኛ እግዚአብሔር የሚጠቀምብን ዕቃዎች ነን። ሸክላ ዕቃዎች ስለ ሆንን፥ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን ኃይል አንደገፍም። 

በመሆኑም በዕቃው ውስጥ ባለው መዝገብ ላይ እንጂ በዕቃው ላይ ማተኮር የለብንም። እንግዲህ ጳውሎስ በበኩሉ መዝገቡን እስከ ጠበቀ ጊዜ ድረስ፥ እግዚአብሔር ዕቃውን እንደሚጠብቅ ስለሚያውቅ፥ የሚደርስበትን ሥቃይ ወይም መከራ አልፈራም ነበር (1 ጢሞ. 1፡11፤ 6፡20 ተመልከት)። እግዚአብሔር መከራዎች እንዲመጡ ይፈቅዳል፤ እግዚአብሔር መከራዎችን ይቆጣጠራል፤ እንዲሁም እግዚአብሔር መከራዎችን ለራሱ ክብር ይጠቀምባቸዋል። እግዚአብሔር በደካማ ዕቃዎች በኩል ክብርን ያገኛል። የቻይናን ማዕከላዊ ክፍል ለወንጌል የከፈቱት ሚስዮናዊ ጄ. ሃድሰን ቴይለር፥ «የእግዚአብሔርን ሥራ ያከናወኑት ሰዎች ሁሉ እርሱ ከእነርሱ ጋር እንዳለ በመተማመን ብቻ ታላላቅ ተግባራትን የፈጸሙ ደካማ ሰዎች ነበሩ» ብለዋል። 

አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር ዕቃዎቹ ከያዟቸው መዛግብት ጢቂት በመፍሰስ ሌሉችን እንዲያንጹ ዕቃዎቹ እንዲጋጩ ይፈቅዳል። መከራ የሰውን ደካማነት ብቻ ሳይሆን፥ ዳሩ ግን የእግዚአብሔርንም ክብር ይገልጻል። ጳውሎስ በዚህ በተጠቀሰው አንቀጽ ውስጥ የተቃራኒ ነገሮችን ዝርዝር ያስቀምጣል፡- ሸክላ ዕቃዎች – የእግዚአብሔር ክብር፤ የኢየሱስ ሞት – የኢየሱስ ሕይወት፤ ሞት በሥራ ላይ – ሕይወት በሥራ ላይ። ይሁን እንጂ ተፈጥሮአዊ አእምሮ የዚህ ዓይነቱን መንፈሳዊ እውነት ሊረዳ ስለማይችል፥ ለምን ክርስቲያኖች በመከራ ላይ ድልን እንደሚቀዳጁ ለመረዳት ያዳግተዋል። 

በዕቃው ሳይሆን በመዝገቡ ላይ ማተኮር እንደሚገባን ሁሉ፥ እንደዚሁም በአገልጋዩ ላይ ሳይሆን በጌታ ላይ ማተኮር አለብን። መከራ ብንቀበል፥ ስለ ኢየሱስ ብለን ነው። እኔነታችንን የምንገድለው፥ የክርስቶስ ሕይወት እንዲገለጽብን ነው። በመከራ ውስጥ ብናልፍ፥ ክርስቶስ እንዲከብርብን ነው። ይህ ሁሉ ደግሞ ለሌሎችም ጥቅም ነው። ክርስቶስን ስናገለግል፥ ሞት በእኛ ላይ ይሠራል፤ ዳሩ ግን ለምናገለግላቸው ሰዎች ሕይወት ይሆንላቸዋል። 

ዶክተር ጆን ሄንሪ ጆውት፥ «ምንም ዋጋ የማያስከፍል አገልግሎት፥ ምንም ነገር አይሠራም» ብለዋል። ትክክል ናቸው። አንድ ጊዜ እኔና በመጋቢነት የሚያገለግሉ ወዳጄ አንድ ወጣት ግሩም ስብከት ሲያቀርብ ሰምተን ነበረ፤ ሆኖም ስብከቱ አንድ የሚጎድለው ነጥብ ስለ ነበረ፥ ለወዳጄ፥ «አንድ ነገር ይጎድለዋል» ስል አሳቤን እካፈልኩት። እርሱም ፥ «አዎን» ብሉ መለሰና በማከልም ፥ «የወጣቱ ልብ እስካልተሰበረ ድረስ ጉድለቱ ሊሟላ አይችልም። ለአፍታ ያህል መከራ ከተቀበለ በኋላ ግን፥ ተስማሚ ስብከት የማዘጋጀት ብቃት ይኖረዋል» በማለት መለሰልኝ። 

የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች መከራ አልተቀበሉም። በመሆኑም ደኅንነት ያላገኙትን ነፍሳት ለመማረክ በመጣር ፈንታ፥ ጳውሎስ በመሠረታቸው አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚገኙትን የዳኑትን ሰዎች በአቋራጭ ይሰርቁ ነበር። ለሕዝቡ መሥዋዕት በመሆን ፈንታ፥ ሕዝቡ ለእነርሱ መሥዋዕትነት እንዲከፍል ያደርጉ ነበር (11፡20)። እነኝህ የሐሰት አስተማሪዎች ለሌሉች የሚያካፍሉት መዝገብ አልነበራቸውም። ከእጃቸው ውስጥ የሚገኙ ነገሮች ቢኖሩ ስለ ቀድሞው ኪዳን የሚያወሩ አንዳንድ የመዘክር ቁርጥራጮች፥ የሰውን ሕይወት ሊመግቡ የማይችሉ የደበዘዙ ቅርሳ ቅርሶች ብቻ ነበሩ። 

በበኩሌ፥ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት አንድ መጋቢ ሕዝቡን በሚያገለግልበት ጊዜ ለጌታ ታማኝ ለመሆን ስለሚከፍለው ዋጋ ምንም ነገር እንደማያውቁ ተገንዝቤአለሁ። ይህም ርዕስ በ2ኛ ቆሮንቶስ ውስጥ ከተጠቀሱትና የጳውሎስን መከራዎች ከሚዘረዝሩት ሦስት ክፍሉች አንደኛው ነው። ሌሎቹ ሁለቱ ክፍሎች 6፡1-10 እና 11፡16-12:10 ናቸው። የእውነተኛ አገልግሎት መፈተኛው ሽልማት ሳይሆን ጠባሳ ነው። «እኔ የኢየሱስን ማኅተም ጠባሳዎች] በሥጋዩ ተሸክሜአለሁና ከእንግዲህ ወዲህ አንድ ስንኳ አያድክመኝ» (ገላ. 6፡17)። 

ተስፋ ቆርጦ ከማቆም እንዴት እንድናለን? የምንድነው፥ በሸክላ ዕቃዎቻችን ውስጥ የወንጌሉ መዝገብ እንዲቀመጥ ዕድል እንደ ተሰጠን በማስታወስ ነው!

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading