2ኛ ቆሮ. 5፡11-15

ጥያቄ 1. በቁጥር 11 «የጌታን ፍርሃት» ሲል ምን ዓይነት ፍርሃት ማለቱ ነው? 

ጥያቀ 2. በቁጥር 12 ላይ «በመልክ እንጂ በልብ ለማይመኩ» ሲል ስለነማን ነው የሚናገረው? 

በቁጥር 11 ላይ «የጌታ ፍርሃት» ማለት የማያምኑ የኩነኔ ፍርሃት ሳይሆን የእግዚአብሔር ልጆች ለእግዚአብሔር ያላቸው የአክብርት ፍርሃት ነው። «ሰዎችን ሁሉ እናስረዳለን» ማለትም ሕይወታችን በእውነት ለእግዚአብሔር አገልግሎት እንጂ ለግል ጥቅም የዋለ አለመሆኑን ለሰዎች ግልጽ አድርገን ሕይወታችንን እናሳያለን አንደብቅም ማለቱ ነው። ይህ የቅንነት ኑር ለእግዚአብሔር ብቻ ሳይሆን ለቆርንቶስም ቤተ ክርስቲያን የተሰወረ አለምሆኑን “ለእግዚአብሔር ግን የተገለጥን ነን፤ በሕሊናችሁም ደግሞ የተገለጥን እንደሆንን ተስፋ አደርጋለሁ” ማለት ይገልጻል። 

ጥያቄ 3. በሕይወታችን ዘመን በሙሉ በእግዚአብሔር ፍርሃት መኖሩ አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ምንድነው? 

ጥያቄ 4. መሪዎች ሕይወታቸውን በግልጽ እያሳዩ መምራት የሚገባቸው ለምንድነው? 

ቁጥር 12:- «በመልክ እንጂ በልብ ለማይመኩ» የሚላቸው በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሾልከው የገቡትን ሐሰተኛ አስተማሪዎች ነው፤ (2ኛ ቆሮ.11:13)። ለሰው ለመታየት ብቻ በውጭ አምረው ይታያሉ እንጂ በልባቸው የረከሱ ናቸው። ሐዋርያው ስለራሱ የሕሊና ንጽሕና የተናገረው የቆርንቶስ ክርስቲያኖች በእነዚህ ሐሰተኛች አስተማሪዎች በሐዋርያው ላይ የቀረበውን ክስ መመለስ እንዲችሉ ነው። ለዚህ እንደሆነም «በእኛ ልትመኩ ምክንያት እንሰጣችኋለን» በሚለው ዐረፍተ ነገር እንገነዘባለን፡፡ 

ቁጥር 13፡- «እብዶች ብንሆን ለእግዚአብሔር ነው» ሲል ይህ ዓይነት ክስ ወይም ሐሜት በጠላቶቹ የተሰነዘረበት መሆኑን ያመለክታል። እብድ የሚለው ከማር. 3፡21-31 ካለው በጌታ ላይ ከተሰነዘረው ክስ ጋር ይመሳሰላል፤ እርሱንም አበደ ብለው ነበርና! እንዲሁም በሐዋ.26፡24 ሐዋርያው ለወንጌል ካለው ፍቅር የተነሳ ዕብድ ተባለ፡፡ ስለ ክርስቶስ መሰደዱ በማያምኑ ዘንድ እውነትም እንደ እብደት ሊታይ ይችል ነበር፤ (2ኛ ቆሮ 11:23)። 

ጥያቄ 5. በኢትዮጵያ ውስጥ ክርስቲያኖች እንደ እብድ ሊታዩ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ምሳሌዎች በመስጠት አስረዳ፡ 

ቁጥር 14 እና 15፡- ይህ ለክርስቶስ በአንድ ልብ መኖሩ የክርስቶስ ፍቅር ግድ ስላለው እንጂ ስላበደ አልነበረም። ይህ ፍቅር ለእርሱ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም አማኞች ስለተሰጠ ሁሉ ለክርስቶስ በአንድ ልብ ራሳቸውን ሊሰጡ ይገባል፡፡ “አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ፤ እንገዲያስ ሁሉ ሞቱ”። በአዳም ሁሉም በኃጢአት አንደወደቁ በክርስቶስ ደግሞ ሁሉም አማኞች በሕይወት ይኖራሉ። የክርስቶስ ሞት ለእነርሱ ስለተቆጠረላቸው የክርስቶስ ሞት የእነርሱ ሞት ነው። 

እግዚአብሔርን በምናገለግልበት ጊዜ እነዚህን እውነታዎች ማስተዋልና መገንዘቡ አስፈላጊ ነው። አንደኛ፡- ለማገልገል የሚያነሣሣን ነገር ፍቅር መሆን አለበት። ይህም ለክርሰቶስ ያለን ፍቅር ነው። ሌሎችን እንድንወድ በልባችን ውስጥ ኢየሱስ ያስቀመጠውንም ፍቅር ያጠቃልላል። 

ክርስቲያኖችንና ያልዳኑትን በፍቅር ዓይን በመመልከት እነርሱን ለማገልገል መነሣሣት ይኖርብናል። ሁለተኛ፡- ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ስለሞትን (ሮሜ 6 ተመልከት )። ከአሁን ወዲያ ራሳችንን ለማስደሰት ሳይሆን ከሙታን በተነሣው በክርስቶስ ኃይል ተደግፈን ያዳነንን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕይወት ለመኖር መጣር ይገባናል። 

ጥያቄ 6. ሀ/ እነዚህ ሁለት እውነታዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስላለው መሪነት ያለንን አመለካከት የሚቀይሩት እንዴት ነው? ለ/ ብዙ መሪዎች እነዚህን ሁለት እውነታዎች በአእምሮአቸው ይዘው ይምራሉን? 

Leave a Reply

%d bloggers like this: