2ኛ ቆሮ.3:12-18

ጥያቄ 14. በቁጥር 12 ላይ ገልጠን እንናገራለን ሲል ምን ማለቱ ነው? መልስህን ካለፈው ጥናት ጋር አገናኝ። 

ጥያቄ 15. በቁጥር 14 ላይ “በክርስቶስ ብቻ የተሻረ ነውና” ያለው ምኑን ነው? 

በቁጥር 12 ላይ ተስፋ የሚለው ከላይ የተዘረዘረውን የአዲስ ኪዳንን ተስፋ ነው። የአዲስ ኪዳን ተስፋ ሕይወትን መስጠት ነው። 

እስራኤላውያን የሙሴን ፊት እስከመጨረሻ ትኩር ብለው እንዳይመለክቱ ሕጉን አንብቦ ከጨረሰ በኋላ መጋረጃ በፊቱ ላይ አደረገ፤ (ዘፀ.34:33-35)። ይህም መጋረጃ የልቦናቸው አለማመንና ድንደኔ ምልክት ሆነ። «ነገር ግን ሃሳባቸው ደነዘዘ»። ይህም ማለት አእምሮአቸው የእግዚአብሔርን ክብር በእምነት ከማየት ደነዘዘ ማለት ነው። ይህ የአለማመን ወይም የመደንዘዝ ምልክት የሆነው መጋረጃ የተሻረው ወይም የተገለጠው በክርስቶስ ብቻ ነው። ሰው በክርስቶስ ሲያምን የእግዚአብሔርን ክብር ያለመጋረጃ ያያል። በማቴ.27:51 ላይ ጌታ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ ቀስተ የመቅደሱ መጋረጃ ተሰነጠቀ። ይህም በክርስቶስ ሰው ወዶ እግዚአብሔር መቅረብና የእግዚአብሔርን ክብር ማየት ከዚህ ጊዜ በኋላ አይከለከልም ማለት ነው፡፡ 

ጥያቄ 16. የማያምኑ ሰዎች አስተሳሰብ ዛሬ እንዴት እንደሚገልጽ ምሳሌ በመስጠት አስረዳ። 

ከቁጥር 15-16፡- ጌታ ኢየሱስን ሳይቀበል ሰው ብሉይ ኪዳንን ቢያነብ ብሉይ ኪዳን ለእርሱ የተሸፈነ መጽሐፍ ነው። ግን ብሉይ ኪዳን ስለ ክርስቶስ ስለሚናገር በክርስቶስ አምኖ ለሚያነበው ሰው ብሉይ ኪዳን ያለመጋረጃ የሚነበብ መጽሐፍ ነው። የእግዚአብሔርንም ክብር በክርስቶስ በኩል ከብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ማየት ይቻላል፤ (ዮሐ.5፡46 እና 47፤ ሉቃ.24:44-47)። ስለዚህ ሐዋርያው እንዲህ አለ፡- «ያ መጋረጃ በልባቸው ይኖራል፤ ወደ ጌታ ግን ዘወር ባለ ጊዜ ሁሉ መጋረጃው ይወሰዳል»። (ቁጥር 16) 

ቁጥር 17 እና 18፡- “ጌታ ግን መንፈስ ነው” ማለት ወልድና መንፈስ ቅዱስን ያለመለየት አነጋገር አይደለም፡፡ ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው ሲል አስቀድሞ ገልጿል፡፡ ያ መንፈስም የሚሠሪው ሰው በጌታ በኢየሱስ ሲያምን ብቻ ነው። ይህን ሃሳብ በአጭሩ ለማለት የጌታንና የመንፈስ ቅዱስን ሥራ በማቀናበር ጌታ ግን ሕጉ ሳይሆን ሕይወት የሚሰጠው መንፈስ ነው አለ። 

ሐዋርያው ይህን ያለመጋረጃ በመገለጥ መሆንን ለአገልገሎቱም አዋለው። የሐዋርያት አገልግሎት ስውርነት የበዛበት በመጋረጃ የተከደነ አገልግሎት አልነበረም። ስለዚህ በስውር ሳይሆን «ገልጠን እንናገራለንና» ሲል በቁጥር 12 ላይም ጽፏል፤ ( 4:2)። የክርስቲያንም ሕይወት እንደዚህ መሽፋፈን የሞላበት ሳይሆን በጌታ ፊት ግልጥ የሆነና የጌታን ክብር በመቀበል በክብር ከደረጃ ወደ ደረጃ ይራመዳል። 

ሰዎች በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያምኑ፥ ልባቸውን የጋረደው ነገር ይገፈፋል። እግዚአብሔር ለእርሱ በእነርሱም በኩል ለሌሎች ይገለጻል። ስለዚህ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ቅድስና፥ ፍቅር፥ ድድቅ፥ ወዘተ ማንፀባረቅ አለባቸው። ይህንን ስናንፀባርቅ ሕይወታችን ይለወጣል። ኢየሱስ ክርስቶስን እንመስላለን። ይህ ክርስቶስን የመምሰል ጉዳይ የሕይወታችንን ዘመን ሁሉ የሚፈጅብንና ያልተቋረጠ ዕድገትን የሚጠይቅ ነው። የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን በሕይወታችን መጨረሻ ኢየሱስን በምንገናኝበት ጊዜ እርሱን እንደምንመስል ነው፤ (1ኛ ዮሐ.3፡2)። 

ጥያቄ 17. ሕይወትህ “ጌታን እየመሰለ ከክብር ወደ ክብር የሚለወጠው” እንዴት ነው?

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading