2ኛ ቆሮ. 7:5-16

ጥያቄ 5. በቁጥር 5 ላይ “በውስጥ ፍርሃት” ሲል ምን ዓይነት ፍርሃት ነበረ? 

ጥያቄ 6. ከቁጥር 7-13 ባለው ክፍል ውስጥ የተጠቀሰውን በአጭሩ አብራራ። 

በቁጥር 5 ላይ ያለው ሃሳብ 2:13 ላይ የተወውን ሃሳብ እንደገና ይጀምራል። በ2:13 ላይ «ቲቶን ወንድሜን ስላላገኘሁት መንፈሴ እረፍት አልነበረውም። ነገር ግን ከእነርሱ ተሰናብቼ ወደ መቄዶንያ ወጣሁ»። አሁን ደግሞ ያንን ሃሳብ እንደገና አንሥቶ በ7:5 ላይ «ወደ መቄዶንያ በመጣን ጊዜ» ይልና የቲቶን መምጣት ይተርካል። እንግዲህ ከ2፡14 ጀምር እስከ 7:4 ድረስ የነበረው በሃሳቡ የመጣለት ስለነበረ ዋና ታሪኩን አሁን ይቀጥላል። ይህ ዓይነት አጻጻፍ በጳውሎስ መልእክቶች ውስጥ በብዙ ቦታ ይገኛል። ይህንንም በማድረጉ በተለይ በዚህ በ2ኛ ቆሮ. 2:14 እስከ 7፡4 ጥልቅ የሆነ የክርስትና ትምህርት ሰጠን! 

እንገዲህ የሃሳቡ አቅጣጫ ይህ ነው። ሐዋርያው ለወንጌል ሥራ ወደ ጢሮአዳ ይሄዳል፤ (2:12)። እዚያ ሳለ ስለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ጥሩ ያልሆነ ሪፖርት (ወሪ) ይደርሰዋል፤ (1ኛ ቆሮ. 1፡11ና 5፡1-2)። ከዚያ ከባድ ተግሣጽ ያዘለውን 1ኛ ቆሮንቶስን ይጽፍላቸዋል፤ (7፡8-9)። ይህንን ደብዳቤ በቲቶ እጅ ወደ ቆሮንቶስ ልኮ መልሱን በምጥ መጠባበቅ ይጀምራል፡፡ «የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በመልእክቱ ተገሥጸው ንሰሐ ይገቡ ይሆን ወይስ እንደዓለማውያን ተቆጥተው ከክርስትና መንገድ ያፈገፍጉ ይሆን?» በማለት ሐዋርያው የነበረውን ምጥ በ7:5 እና በ2፡13 ይገልጣል። በጢሮአዳ ምንም በር ቢከፈትለት ልቡ ስላላረፈለት የቆሮንቶስን ቤተ ክርስቲያን ወሬ በቅርብ ሆኖ እንዲያዳምጥ ተነሥቶ ወደ መቄዶንያ ይሄዳል፤ (2:13)። መቄዶንያ በነበረበት ጊዜ ጳውሎስ በውጭ ችግር ነበረበት፤ በውስጥም የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሰዎች የመጃመሪያውን መልእክቱን አይቀበሉትም ብሎ ፈርቶ ነበር። በዚህ ቦታ ላይ ጳውሎስ ተስፋ ቀርጦ ነበር። በመቄዶንያ ሳለ ቲቶ መልካም ወሬ ይዞለት መጣ፤ (7፡6-7)። በዚያን ጊዜ ነው «ኃዘንተኛን የሚያጽናና አምላክ በቲቶ መምጣት አጽናናንን ብሎ በ7:6 ላይ የተናገረው! 

የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በቲቶ በኩል የተላከላቸውን የሐዋርያውን ከባድ ተግሣጽ ያዘለ ደብዳቤ በተቀበሉ ጊዜ በታላቅ ኃዘን ንስሐ ይገባሉ። «ናፍቆታችሁንና ልቅሶአችሁን ስስእኔም ቅንዓታችሁን ሲነገረን …ደስ አለን፤› (ቁጥር 7)። 

ከቁጥር 8-12 ባለው ክፍል ውስጥ በደብዳቤው ምክንያት ስላዘኑ ማዘኑንና ግን ደግሞ ይህ ኃዘን ሕይወትን የሚሰጥ የንስሐ ኃዘን በመሆኑ መደሰቱን ይገልጽላቸዋል። በቁጥር 12 ላይ ስለ እኛ ያላችሁ ትጋታችሁ ከእናንተ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት እንዲገለጥ እንጂ ስለበዳዩ ወይ ስለተበዳዩ አልጻፍሁም» ሲል የአይሁዳውያን የአነጋገር ዘይቤ መሆኑን መገንዘብ አለብን። ሐዋርያው የጻፈው እርግጥ በደልን ስለፈጠረው ሰው መሆኑ አይካድም። ግን ከዚህም በላይ ዋናው ነጥብ የእነርሱ የልቦና መዘጋጀትና መታዘዝ መሆኑን ለማስረዳት ብሎ ነው ስለበዳዩ ወይም ስለተበዳዩ አልጽፍም ያለው። ተመሳሳይ ሃሳብ በሆሴዕ 6፡6 ላይ ተጽፎአል። 

«ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወዳለሁና» ሲል መሥዋዕትን እጠላለሁ ወይም እንዲያቀርቡ ያዘዛቸውን መሥዋዕት አልፈልግም ማለቱ አልበረም። ይህ ዓይነት አነጋገር የሚበልጠውን ሃሳብ ለመምረጥ አነሥተኛውን ሃሳብ ይተዋል። 

በዳዩ የአባቱን ሚስት የወሰደው ሲሆን ተበዳዩ ጸግዋ ሚስቱን የተቀማው አባትየው ነበር! (5:1-2)። በዳዩ ሰው ብቻ አልነበረም ስለኃጢአቱ የሚናዘዘው፤ የቆሮንቶስም ክርስቲያኖች ስለትዕቢታቸው፥ ስለመጋጨታቸውና ስለተሳሳተው የሥጦታ አጠቃቀማቸው ሁሉ ንስሐ ይገቡ ነበር። ጳውሎስ «እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ አዝናችኋልና» ይላቸዋል። ይህ ኃዘን ከልብ የሚመነጭ ሲሆን ያለንን አመለካከትና አረማመድ የሚያስቀይረን ነው። ዓለማዊ የሆነ ኃዘን ግን የአመለካከትም ሆነ የአረማመድ ለውጥ ስለማያመጣ መጨረሻው ሞት ነው። 

ጥያቄ 7. “እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሚመጣውን ኃዘን” ከዓለማዊ ኃዘን ጋር አነፃፅር። የእያንዳንዱ የመጨረሻ ውጤት ምንድነው? ልንለያያቸው የምንችለው እንዴት ነው?

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading