ኢዮብ 1-14

የውይይት ጥያቄ፥ ኤፌሶን 6፡10-18 አንብብ። ሀ) ክርስቲያን የሚዋጋው ከማን ጋር ነው? ለ) የምንዋጋባቸው መሣሪያዎች ምንድን ናችው? ሐ) በጦርነቱ ውስጥ ከለላ የሚሆኑን ነገሮች ምንድን ናችው? መ) የዚህ ዓይነቱ መንፈሳዊ ጦርነት በመካሄድ ላይ እንዳለ የተሰማህን ሁኔታ ግለጽ።

መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጆች በማያቋርጥ ጦርነት ውስጥ መሆናቸውን ይናገራል። ይህ ጦርነት ከማያምኑ ሰዎች ወይም ከጨቋኝ መንግሥታት ጋር የሚደረግ ሥጋዊ ጦርነት አይደለም፤ ይልቁንም ጦርነቱ መንፈሳዊ ነው። የክርስቲያን ዋና ጠላቶችም ሰይጣንና ተከታዮቹ አጋንንት ናችው። መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያን ለጦርነቱ ዝግጁ መሆን እንዳለበት ያስጠነቅቃል። ጠላታችንን ሁልጊዜ የምናሸንፍበት ችሎታ ሊሰጠን ቃል ስለተገባልን ብርታት ይሰማናል፤ ነገር ግን ከሰይጣን ጥቃት እንዲጠብቁን የሚከላከሉልንን ነገሮች ለመጠቀም መቻል አለብን፤ እነዚህም፡- እውነት፥ ጽድቅ፥ ለምስክርነት መዘጋጀት፥ እምነትና የደኅንነታችን ዋስትና ናቸው። እንዲሁም ሰይጣንን ለማሸነፍ የምንችልባቸውን የጦር መሣሪያዎች ለመጠቀም መቻል አለብን፤ እነዚህም፡- የእግዚአብሔር ቃልና ጸሉት ናቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) አንድ ክርስቲያን ከላይ የተመለከትናቸውን መከላከያዎች በመጠቀም ራሱን ከሰይጣን ጥቃት የሚከላከልባቸውን መንገዶች ግለጽ። ለ) አንድ ክርስቲያን ሰይጣንን ለማጥቃት በመንፈሳዊ የጦር መሣሪያዎች የሚጠቀምባቸውን መንገዶች ግለጽ።

በመጽሐፈ ኢዮብ ስለዚህ መንፈሳዊ ጦርነት እንድናውቅ ተጽፎልናል። አብዛኛው የመጽሐፉ ክፍል የሚናገረው ኢዮብ ከመከራ ጋር ስላደረገው ትግልና በመከራው ውስጥ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ የት እንዳለ በማሰብ ስለ መደነቁ ቢሆንም፥ መጽሐፉን ለምናነብ ለእኛ ግን ምክንያቱ የኢዮብን ጽድቅ ለማጥፋት የፈለገው የኢዮብ ከሳሽና ባላጋራ ሰይጣን እንደሆነ ተነግሮናል። መጽሐፈ ኢዮብን ለመረዳት፥ በእግዚአብሔርና በሰይጣን መካከል በሰማይ ምን እንደተደረገ ለኢዮብም ሆነ ለወዳጆቹ ግልጸ እንዳልነበረ መገንዘብ ያስፈልጋል። እኛም ዛሬ በእግዚአብሔርና በሰይጣን መካከል በሚካሄደው መንፈሳዊ ጦርነት ምን በመደረግ ላይ እንዳለ አናውቅም፤ ዳሩ ግን የዚያ ጦርነት ውጤት ለኢዮብ እንደተሰማው፤ ለእኛም እንዲሁ ይሰማናል።

የውይይት ጥያቄ፥ ኢዮብ 1-2 አንብብ። ሀ) በኢዮብ 1፡1 ኢዮብ የተገለጠው እንዴት ነው? ለ) ዛሬ አንድ ክርስቲያን እንዲህ ዓይነቱን ምስክርነት የሚያገኘው እንዴት ነው? ሰዎች መልካም ምስክርነትን ሊያገኙ የሚችሉባቸውን መንገዶች የሚያመለክቱ ምሳሌዎችን ጥቀስ። ሐ) ኢዮብ የተፈተነው የመጀመሪያ ፈተና ምን ነበር? ለዚህ ፈተና የሰጠው ምላሽ ምን ነበር? መ) ኢዮብ የተፈተነው ሁለተኛ ፈተና ምን ነበር? ለዚህ ፈተና የሰጠው ምላሽ ምን ነበር? 

ብዙ ክርስቲያኖች መከራ ሁልጊዜ የኃጢአት ውጤት እንደሆነ ይመስላቸዋል። አንድ ሰው ሲታመም ወይም ከሌሎች ይልቅ ከፍተኛ መከራ ሲያጋጥመው፥ ይህ በሰውዬው ላይ የደረሰ የእግዚአብሔር ፍርድ ነው በማለት ወዲያውኑ ይወስናሉ። መጽሐፈ ኢዮብ የተጻፈው የዚህ ዓይነቱን አስተሳሰብ ለመቃወም ነው። መጽሐፈ ኢዮብ የሚያተኩረው መከራን በተቀበለ ኃጢአተኛ ላይ ሳይሆን፥ በጻድቁ ኢዮብ ላይ ነው። 

ኢዮብ 1-2

መጽሐፈ ኢዮብ 1-2 ኢዮብን ያስተዋውቀናል። እንዴትና ለምን መከራ እንደተቀበለ መግለጽ ይጀምራል። ኢዮብ በዖፅ አገር የሚኖር ሰው ነበር። ዖፅ በኤዶም ወይም በደቡብ ዐረቢያ የነበረ አገር ሳይሆን አይቀርም። ኢዮብ እስራኤላዊ አልነበረም፤ ዳሩ ግን እግዚአብሔርን እጅግ የሚወድ ሰው ነበር። ኢዮብ እንደ ሁላችንም ኃጢአተኛ ቢሆንም እንኳ የሕይወት ባሕርይው ግን በምሳሌነት የሚታይ ነበር። ነቀፋ የሌለበት ፍጹም ቅን ሰው እንደነበር ተገልጾአል። ኢዮብን በኃጢአቱ ሊከሰው የሚችል ማንም አልነበረም። የቅርብ ወዳጆቹ እንኳ በኃጢአት ሊከሱት አይችሉም ነበር። ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚፈራና በሕይወቱም እርሱን የሚያከብር ሰው ነበር። ኃጢአት እግዚአብሔርን ደስ እንደማያሳኝ ያውቅ ስለነበር ክፋትን ይጠላ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በሁላችንም ሕይወት እግዚአብሔር ስለሚፈልገው ነገር ይህ ጥሩ ገለጻ የሚሆነው እንዴት ነው? ለ) የዚህ ዓይነት ሕይወት ያላቸው ክርስቲያኖች ቁጥር ጥቂት የሆነው ለምንድን ነው? ሐ) እግዚአብሔርን በመፍራታቸው የሚታወቁና ይህንን መግለጫ የሚያሟሉትን የቤተ ክርስቲያንህን ሰዎች በምሳሌነት ጥቀስ። መ) በሕይወታቸው እንደ ኢዮብ እንዲሆኑ ያደረጋቸው የተለየ ነገር ምንድን ነው?

ኢዮብ ፍጹም ጻድቅ ሰው ስለነበር፥ አይሁድ ሀብታምነቱ እንደተጠበቀ የሚኖር አድርገው ያስቡ ነበር። ቁሳዊ ሀብትና ጽድቅ አብረው የሚሄዱ ነገሮች እንደሆኑ፥ መከራና ኃጢአትም ጎን ለጎን የሚጓዙ ይመስላቸው ነበር።

የኢዮብ የመጀመሪያ ፈተና፡- የእግዚአብሔርና የልጆቹ ከሳሽ የሆነው ሰይጣን ወደ እግዚአብሔር ቀርቦ፥ ኢዮብ እግዚአብሔርን ያከበረው ከእርሱ ስለተቀበለው በረከት ብቻ እንደሆነ ተናገረ። ሰይጣን ከኢዮብ ሀብቱን ቢወስድበት እንደሚረግመው ለእግዚአብሔር ተናገረ። እግዚአብሔርም ኢዮብ ያለውን ነገር ሁሉ ሰይጣን ይወስድበት ዘንድ ፈቀደ። በእርሱ ላይ ግን አንዳች ነገር እንዳያደርስበት አስጠነቀቀው። ወዲያውኑ ሁለት ነገሮች ሆኑ፡- 

1. የኢዮብ ቁሳዊ ብልጽግና ሁሉ ወደመና እጅግ ድሀ ሰው ሆነ። 

2. ከሚስቱ በስተቀር የኢዮብ ቤተሰብ በሙሉ ተገደሉና ያለቤተሰብ ብቻውን ቀረ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህ ነገር በእነርሱ ላይ ቢደርስባቸው፥ የአብዛኛዎቹ ክርስቲያኖች ምላሽ ምን ይሆን ነበር? ፤ ለ) አንተ ኢዮብን ብብትሆን ኖሮ፥ ምላሽህ ምን ይሆን ነበር? 

ኢዮብ በሰማይ ምን እንደተደረገ አላወቀም ነበር። የመከራውን ውጤት ተመለከተና ሥቃዩን ተቀበለ። በእግዚአብሔር ላይ የነበረው እምነት ጥልቅ ነበር፤ ስለዚህ «እግዚአብሔር ሰጠ፥ እግዚአብሔርም ነሳ፣ የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን» (ኢዮብ 1፡21) በማለት እግዚአብሔርን አከበረ። 

የኢዮብ ሁለተኛ ፈተና፡- ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሰይጣን እንደገና ኢዮብን ከሰሰ። ክሱ፡- ኢዮብ እግዚአብሔርን የተከተለው ለግል ጥቅሙ ነው የሚል ነበር። ሰይጣን ለሰው ልጅ እጅግ አስፈላጊው ነገር ጤንነቱ እንደሆነ ያውቅ ነበር! ስለዚህ ሰይጣን ኢዮብን በደዌ ቢመታው ኢዮብ እግዚአብሔርን እንደሚረግም ተናገረ። ሰይጣንን ይህን ያደርግ ዘንድ እግዚአብሔር ፈቀደለት፤ ኢዮብን እንዲገድል ግን አልፈቀደለትም ነበር። 

ኢዮብም ወዲያውኑ ከራሱ እስከ እግሩ ድረስ ሰውነቱ በሙሉ በከፋ ቍስል ተመታ። ሚስቱ ሳትቀር እግዚአብሔርን ሰድቦ እንዲሞት መከረችው። የኢዮብ ምላሽ ግን «ከእግዚአብሔር እጅ መልካሙን ተቀበልን፤ ክፉ ነገርንስ አንቀበልምን?» (ኢዮብ 2፡10) የሚል ነበር። 

ኤልፋዝ፥ በልዳዶስና ሶፋር የሚባሉ ሦስቱ ወዳጆቹ ስለ ሕመሙና ስለደረሰበት ክፉ ነገር ሰምተው ኢዮብን ለማጽናናት መጡ። እንደ መልካም ወዳጆች ለሰባት ቀናትና ሌሊት የኢዮብን ሕመም በጸጥታ ተካፈሉ። እነዚህ ሦስቱ የኢዮብ ወዳጆች በችግርና በመከራ ጊዜ ከሚያውቁት ነገር በላይ አሳብ እንደሚሰነዝሩና መልስ እንደሚሰጡ መልካም መሳይ ክርስቲያኖች ይመሰላሉ። እነዚህ ሦስት ወዳጆቹ በተሳሳተ መንገድ ኢዮብን በኃጢአት በመክሰስ ሌላ የሥቃይ ምንጭ ሆኑበት። ኤሊሁ ለምን እንዳልተጠቀሰ አናውቅም። ወጣት ስለነበር የእርሱን ስም በዚህ ደረጃ መጥቀስ የማያስፈልግ ሆኖ ይሆናል፤ ወይም ደግሞ ኢዮብን ለመጠየቅ የመጣው ምናልባት ቆይቶ ይሆናል፤ ዳሩ ግን በንግግራቸው ሁሉ ውስጥ ኤሊሁ ከኢዮብና ከወዳጆቹ ጋር እንደነበረ ይመስላል። 

ኢዮብ 3 

መጽሐፈ ኢዮብ ምዕራፍ 3 የሚጀምረው በኢዮብ የብሶት ንግግር ነው። ኢዮብ እግዚአብሔርን ባይራገምና እምነቱን ባይክድም እንኳ የጠለቀ ኃዘንና ተስፋ መቍረጥ ደርሶበታል። ኃዘኑንና ሥቃዩን ለመሸሽ ባይወለድ ወይም ቢሞት ይሻለው እንደነበርና ያንንም እንደተመኘ እንመለከታለን። 

ኢዮብ 4-14 በኢዮብና በወዳጆቹ መካከል የተደረገ የመጀመሪያ ዙር ክርክር 

ኢዮብ 4-5፥ የኤልፋዝ ክስ፡- ኤልፋዝ፥ የኢዮብን ቁጣና መራርነት ከሰማ በኋላ፥ በሕይወቱ ውስጥ ኃጢአት እንዳለ ይነግረው ነበር። ኢዮብ የተቀጣበት ምክንያት ይህ ነበር ይላል። የኤልፋዝ ንግግር ከመሠረታዊ የእምነት ትምህርት አንጻር አንዳችም ስሕተት አልነበረበትም። ችግሩ ግን ይህ መሠረታዊ የእምነት ትምህርት እውነታ ኢዮብን በተመለከተ ትክክል አልነበረም። ኢዮብ ሥቃይን የተቀበለው በኃጢአቱ ምክንያት ሳይሆን በጽድቁ ምክንያት ነበር። 

ኢዮብ 6-7፥ የኢዮብ ምላሽ፡- ኢዮብ እርሱ የሚያውቀውና ያልተናዘዘው ኃጢአት በሕይወቱ እንደሌለ ይመልስ ነበር፤ ስለዚህ መከራና ሥቃይ የሚቀበለው በኃጢአት ምክንያት አልነበረም። ይልቁንም በዚህ በወደቀ ዓለም ውስጥ እስካሉ ጊዜ ድረስ መከራ የሰው ልጆች ሁሉ ዕጣ ፈንታ እንደሆነ ይናገር ነበር። 

ኢዮብ 8፥ የበልዳዶስ ክስ፡- በልዳዶስ እግዚአብሔር ጻድቅ ስለሆነ በጻድቅ ሰው ሕይወት ላይ መከራን ጨርሶ አያመጣም ብሎአል። ስለዚህ ይህ ሁሉ ሥቃይና መከራ የደረሰበት ኢዮብ በሕይወቱ ኃጢአት እንደሚኖር በመግለጽ ምሕረት ቢጠይቅ፥ መሐሪው እግዚአብሔር ኢዮብን እንደሚያድስ ተናግሯል። 

ኢዮብ 9-10፥ የኢዮብ ምላሽ፡- ፍጹም ቅዱስ በሆነው እግዚአብሔር ፊት ሰው ጻድቅ ሊሆን እንደማይችል ኢዮብ ተስማምቷል፤ ነገር ግን ያልተናዘዘው ኃጢአት በሕይወቱ አለመኖሩን አሁንም መናገሩን ቀጥሎ ነበር። 

ኢዮብ 11፥ የሶፋር ክስ፡- ሶፋር፥ የደረሰበትን ጥልቅ ኃዘን ሳይገነዘብ በኢዮብ ላይ በቁጣ ተናግሯል። ልክ እንደ ሌሎቹ፥ ሶፋርም ኢዮብን ስለ ኃጢአቱ ከሶታል። 

ኢዮብ 12-14፥ የኢዮብ ምላሽ፡- በዚህ ስፍራ ኢዮብ የሚሰጠው ምላሽ በእርሱና በወዳጆቹ መካከል የነበረውን የመጀመሪያ ዙር ክርክር ያጠቃልለዋል። የኢዮብ ንግግር በእግዚአብሔር ታላቅነትና ኢዮብ በእግዚአብሔር ላይ በነበረው የማያቋርጥ እምነት ላይ ያተኮረ ነበር። በዚህ ስፍራ ኢዮብ ንስሐ ሊገባበት የሚችል ኃጢአት የሌለ መሆኑን በድጋሚ ተናግሯል። 

የውይይት ጥያቄ፥ ከዚህኛው የመጽሐፈ ኢዮብ ክፍል በቤተ ክርስቲያንህ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ማስተማር የሚገባህን ነገሮች ዝርዝር። 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: