የሕይወት እንጀራ

መጽሐፈ ኢዮብ

ኢዮብ 32-42

በከፍተኛ ችግርና ሥቃይ ውስጥ በምናልፍበት ጊዜ ምንም ዓይነት ችግር ይሁን ብዙ ጊዜ የሚኖረን የመገረም ጥያቄ «ለምን?» የሚል ነው። ይህ ወደ አእምሮአችን የሚመጣ ግራ መጋባት የሚያሳየው የእግዚአብሔርን መንገዶችና ዓላማዎች ለመረዳት ብቁ አለመሆናችንን ነው፡፡ ይህ እጅግ የሚያስፈራ ነገር ነው። በተለይ በዚያ ችግር ውስጥ እያለን «ለምን?» ብለን ለምንጠይቀው ጥያቄ በአብዛኛው መልስ እናገኝም። መልሱ በእግዚአብሔር ጥበብና ዓላማ ውስጥ የተሰወረ ብዙ ጊዜ ዓመታት አልፈው ወደኋላ ስንመለከት ነው እግዚአብሔር ያደርጋቸው ከነበሩት ነገሮች ውስጥ አንዳንዶቹን የምንገነዘበው።  እኛ ክርስቲያኖች ጨርሶ ልንዘነጋው የማይገባ አንድ የተስፋ ቃል አለን። እግዚአብሔር በቃሉ የሚከተለውን ተስፋ ሰጥቶናል። «እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን» (ሮሜ 8፡28-29)። እግዚአብሔር ወደ ሕይወታችን ምንም ዓይነት ክፉ ነገር ይመጣ ዘንድ እንደማይፈቅድ አይናገርም። ስደት፥ ሞት፥ በሽታ ይኖራል። እምነታችንን ልንጥልበት የሚገባን ነገር ግን እነዚህን ክፉ ነገሮች እግዚአብሔር በሕይወታችን መልካም ነገርን ለማምጣት የሚጠቀምባቸው መሆኑ ነው።  የውይይት ጥያቄ፥ ክርስቲያን በመከራ ውስጥ በሚያልፍበት ጊዜ ይህን ታላቅ የተስፋ ቃል ማወቅ ጠቃሚ የሚሆነው እንዴት ነው?  የውይይት ጥያቄ፥ ኢዮብ 32-42 አንብብ። ሀ) የኤሊሁን የመከራከሪያ አሳብ አሳጥረህ ጻፍ። ለ) እግዚአብሔር ለኢዮብ የሰጠውን መልስ አሳጥረህ ጻፍ። ሐ) ኢዮብ ለእግዚአብሔር የሰጠው ምላሽ ምን ነበር? መ) ኢዮብ በሕይወቱ ዘመን መጨረሻ የተባረከው እንዴት ነበር? ) እግዚአብሔር ስለ ኢዮብ ወዳጆች ክርክር የተናገረው ነገር ምን ነበር?  ኢዮብ 32-37 የኤሊሁ ንግግር  ኤሊሁ ወጣት ስለነበር ለረጅም ሰዓታት ቁጭ ብሎ በኢዮብና ታላላቆቹ በሆኑት በሦስቱ ወዳጆች መካከል የተደረገውን ውይይት አዳመጠ። ሦስቱ የኢዮብ ወዳጆች የወከሉት በዕድሜ የገፉ ሰዎችን ጥበብ ሲሆን ጥበባቸው ምን ያህል ደካማ እንደሆነም እንመለከታለን። ኤሊሁ አንዳንድ ጊዜ በዕድሜ ከገፋ ሰዎች ይልቅ ወጣቶች ጠቢባን ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ኤሊሁ፥ በኢዮብም ሆነ በሦስቱ ወዳጆቹ ላይ እጅግ ተቆጣ። ኤሊሁ በእርሱ አመለካከት ኢዮብ ጻድቅ ሰው እንደሆን ያምን ነበር፤ ነገር ግን ቢያንስ እግዚአብሔርን በመክሰሱ ምክንያት የተሳሳተ መስሎታል፡፡ ሦስቱ የኢዮብ ወዳጆቹ አንዳችም ማስረጃ ሳያግኙ ኢዮብን በመክሰሳቸው ጥፋተኞች እንደሆኑ ይናገራል።  ኤሊሁ የኢዮብን ስሕተት ለማረጋገጥ ሞክሯል። ኤሊሁ፥ እግዚአብሔር ሁልጊዜ ጻድቅ እንደሆነና ዓለምንም የሚገዛው በቅን ፍርድ እንደሆነ ተናግሯል። እግዚአብሔር ለጽድቅ ዋጋ እንደሚሰጥና ክፋትን እንደሚቀጣ ከሚያመለክተው መመሪያ ጋር ተስማምቷል፤ ዳሩ ግን መከራ ሁሉ የእግዚአብሔር ቅጣት አይደለም የሚል አሳብ አክሉበታል። ይልቁንም እግዚአብሔር አንዳንድ ጊዜ ቅጣትን ሰው ወደተሳሳተ ተግባር እንዳይሄድ ለመመለስ ይጠቀምበታል። መከራ የምሕረት ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡ እግዚአብሔር በታላቅ ጥበቡ ሰዎች በከፍተኛ ደረጃ ፈሪሀ-እግዚአብሔር እንዲያድርባቸው ለማድረግ መከራን ይጠቀምበታል። እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች በመከራቸው ጊዜ ሳይቀር፥ እግዚአብሔርን መታመናቸውና መደገፋችውን መቀጠል አለባቸው።  ኢዮብ 38-41 የእግዚአብሔርና የኢዮብ ንግግር  በመጨረሻ እግዚአብሔር ራሱን ለኢዮብ ገለጠ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የኢዮብን ጥያቄ አልመለሰለትም፤ ወይም መከራ የሚቀበለው ለምን እንደሆነ አልገለጠለትም። ስለ ሰይጣን ክስ እንኳ አነገረውም። እግዚአብሔር ቅን ፍርድን እንዳላደረገ በኢዮብ የቀረበበትን ክስ ለማስተባበል አልሞከረም። እግዚአብሔር ኢዮብን ስሕተት ሠርቷል ብሎ በቀጥታ አልወነጀለውም፤ ነገር ግን ኢዮብ የእግዚአብሔርን ሥራ በመጠየቁ እንደተሳሳተ ትንሽ ፍንጭ ሰጥቷል። ኢዮብን በኃጢአት በመክሰሳቸውና ንስሐ እንዲገባ ለማድረግ በመሞከራቸው ሦስቱ ወዳጆቹ እንደተሳሳቱ እግዚአብሔር ተናግሯል።  እግዚአብሔር በመጀመሪያ ታላቅ ኃይሉን በማሳየት ወደ ኢዮብ ቀረበ። እግዚኣብሔር በታላቅ ዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ወደ ኢዮብ መጣ። እግዚአብሔር ምን ያህል ታላቅና ኃያል እንደሆነ ለኢዮብ ሊያስታውሰው ፈልጎ ነበር። እግዚአብሔር ሊፈራና ሊከበር እንጂ በሚያደርገው ነገር የጥርጥር ጥያቄ ሊነሳበት የማይገባ ታላቅና ኃይለኛ እንደሆነ ለኢዮብ ለማስታወስ ፈልጎ ነበር። ፈጣሪ እግዚአብሔር በፍጥረታቱ የጥርጥር ጥያቄ ሊሰነዘርበት አይገባም። እግዚአብሔር ስለተግባሩ በችሎት ፊት ቀርቦ አይመረመርም። እግዚአብሔር ፈራጅ ነው፤ የሰው ልጅም ለእርሱ መልስ ሊሰጥ የሚገባው ነው፡፡  ቀጥሉ እግዚአብሔር ለኢዮብ ጥበቡን አስታወሰው። እግዚአብሔር የማንንም ጥበብ ሳይፈልግ ዓለምን በሙሉ ፈጥሯል። በመከራ ውስጥ ይህን ለምን አደረገ? ብሉ እግዚአብሔርን መጠየቅ ጥበባችን ከእግዚአብሔር ጥበብ እኩል ነው ወይም ይበልጣል ብሎ መገመት ነው። የሰው ልጅ ጥበብ እጅግ ውሱንና ከእግዚአብሔር ጥበብ ጋር ጨርሶ የማይወዳደር ነው። ኢዮብና ሦስቱ ወዳጆቹ ግን የማያውቁትን ነገር ለመናገር በመሻታቸው ስሕተት ሠርተዋል።  ኢዮብ 42 ማጠቃለያ  ኢዮብ የእግዚአብሔርን ኃይል አይቶ ዝም ማለት ሲገባው በንግግር ለሠራው ስሕተት ኃጢአተኛነቱን አመነ። በመከራ ውስጥ ቢሆንም እንኳ በእግዚአብሔር ላይ ጥያቄ ማንሣቱ ስሕተት ነበር። ጸጥታ በሰፈነበት አክብሮት ወደ መሬት ወድቆ ለእግዚአብሔር ሰገደ።  እግዚአብሔር ኢዮብን ወደ ቀድሞ ክብሩ መለሰው። ጻድቃን በመከራ ውስጥ እንኳ በታማኝነት እንደሚቆዩ በማሳየት እግዚአብሔር የሰይጣንን ስሕተት አረጋገጠ። ኢዮብም ከዚህ ቀደም ከነበረው የላቀ ብዙ ሀብትና በረከትን አገኘ።  የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በዚህኛው የመጽሐፈ ኢዮብ ክፍል የሚገኙትን እጅግ ጠቃሚ እውነቶች ዘርዝር። ለ) ከዚህ ንባብና ጥናት ስለ መከራ ምክንያቶችና በመከራ ውስጥ ያሉ ሰዎችን እንዴት መምከር እንደሚገባ ምን ልንማር እንችላለን?  (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

ኢዮብ 32-42 Read More »

ኢዮብ 15-31

እግዚአብሔር መከራ እንድንቀበል ከሚፈቅድባቸው ዓላማዎች አንዱ ሌሎች መከራ በሚቀበሉበት ጊዜ ማስተዛዘንና ማጽናናት እንድንችል ነው (2ኛ ቆሮንቶስ 1፡3-7 ተመልከት)። እግዚአብሔር ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን በማጣቱ ስለተሠቃየና ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ በመስቀል ላይ በተቀበለው መከራ ስለተሠቃየ፥ በመከራችን ጊዜ እንዴት እንደሚያጽናናን ያውቃል (ዕብራውያን 2፡17-18)። እኛም ደግሞ መከራና ሥቃይ በምንቀበልበት ጊዜ፥ በዙሪያችን ያሉ መከራ የሚቀበሉ ሰዎችን ለመርዳት እንችላለን።  የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) መከራ የተቀበለ ሰው መከራ የሚቀበሉ ክርስቲያኖችን ለማጽናናት ከሌሎች የሚሻልባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ለ) ይህ ነገር በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ በአሁኑ ጊዜ መከራ በመቀበል ላይ ያሉትን ሰዎች ለማጽናናት ከዚህ በፊት መከራ በተቀበሉ ሰዎች ምሳሌነት ስለ መጠቀም ምን ያስተምረናል?  የኢዮብ ወዳጆች እንደ እርሱ መከራ አልተቀበሉም ነበር፤ ስለዚህ ሊራሩለት አልቻሉም። ለኢዮብ የሰጡት መልስ ሊታገሱት ያለመቻላቸው ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን የሚያሳይ ነበር። እነርሱ ለኢዮብ አጽናኞቹ ሳይሆኑ ከሳሾቹ ሆኑ። መልካም የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ቢጠቀሙም ትክክል አልነበሩም። አሳባቸውም ጥፋተኛ ያልነበረውንና ያለ ኃጢአቱ መከራ የተቀበለውን የኢዮብን ሕይውት የሚመለከት አልነበረም።  የውይይት ጥያቄ፥ ኢዮብ 15-31 አንብብ። ሀ) የኢዮብ ወዳጆች በኢዮብ ላይ የቀረቡትን ክስ አሳጥረህ አቅርብ። ለ) ኢዮብ ለክሶቹ የሰጣቸውን መልሶች አሳጥረህ አቅርብ። ሐ) ከዚህኛው የመጽሐፈ ኢዮብ ክፍል የምትማራቸውን መንፈሳዊ እውነቶችን ዘርዝር።  ኢዮብ 15-31 በኢዮብና በወዳጆቹ መካከል የተደረጉ ሁለተኛና ሦስተኛ ዙር ክርክሮች  ኢዮብ 15፥ የኤልፋዝ ክስ፡- ኢዮብ ለወዳጆቹ በሚሰጠው ምላሽ እጅግ ቍጠኛ እየሆነ በመጣ ቁጥር፥ የወዳጆቹም ትዕግሥት እየቀነሰ መጣ። በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ የምናገኛቸው የወዳጆቹ ንግግሮች ትሕትና የጐደላቸው ናቸው። ኢዮብ ራሱን ለመከላከል በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ሞኝነትንና ጻድቅ ያለመሆንን እንደሚታይበት በመግለጥ ኤልፋዝ ከሶታል። የኃጥአንን የመጨረሻ ዕድል በማስታወስ፥ ኢዮብን ንስሐ እንዲገባ አበረታትቶታል።  ኢዮብ 16-17 የኢዮብ ምላሽ፡- ኤልፋዝ የኢዮብ ችግር ኃጢአተኝነቱ እንደሆነ አድርጎ በማቅረቡ፥ ኢዮብ ሁለት ዋና ዋና እውነቶችን መሠረት በማድረግ ምላሹን አቀረበ። በመጀመሪያ፥ ሊወነጀልበት የሚገባ ጉልህ የሆነ ኃጢአት እንደሌለበት ተናግሯል። በሁለተኛ ደረጃ፣ እግዚአብሔር የሚፈልገውን ነገር የማድረግ ችሎታ እንዳለውና ኢዮብን በደዌ መምታት እንኳ እንደሚችል ተናግሯል፤ ዳሩ ግን ኢዮብን ጎዳው፤ ምክንያቱም አሁን እርሱ ላይ የሚያደርገው ነገር ወዳጁ ሳይሆን ጠላቱ እንደሆነ የሚያስመስል በመሆኑ ነው፡፡ ኢዮብ 18፣ የበልዳዶስ ክስ፡- የበልዳዶስ ንግግር ያተኮረው በኃጥአት እጣ ፈንታ ላይ ነበር፡፡ ኢዮብን ክፉና ኃጢአተኛ ነህ ብሎ በቀጥታ ባይናገረውም እንኳ፣ የሚያመለክተው ግን ያንኑ ነበር፡፡ የኃጥአን ዕጣ ፈንታ በማሳየትና ኢዮብ ንስሐ ካልገባ በስተቀር የሚጠብቀውን ነገር በማመልከት አስጠንቅቆታል።  ኢዮብ 19፥ የኢዮብ ምላሽ፡- ኢዮብ አሁንም ጥፋተኛ አለመሆኑን በመግለጽ ለበልዳዶስ ክስ ምላሽ ሰጥቶአል። ኢዮብ አሁን ያለበትን ስንመለከት በእግዚአብሔር እንደተፈረደበት ኃጢአተኛ ሰው ቢመስልም፣ ያልተናዘዘው ኃጢአት ግን አልነበረም። አሁን ተስፋ የቆረጠ ቢመስል፣ የሚቤዥው ሕያው እግዚአብሔር ስለሆነ፥ የሦስቱ ወዳጆቹ አስተሳሰብ ምንም ይሁን ምን እግዚአብሔር በመጨረሻ ሁሉን ግልጽ በማድረግ እንደሚያቆመው ተናግሯል (ኢዮብ 19፡25)።  ኢዮብ 20፥ የሶፋር ክስ፡- የሶፋር ንግግር የሁለቱ ወዳጆቹ ንግግር ድግግሞሽ ነበር። እርሱም ስለ ኃጢአተኞች ዕጣ ፈንታ በመናገር ንስሓ እንዲገባ ኢዮብን አበረታትቶታል።  ኢዮብ 21፥ የኢዮብ ምላሽ፡- ኢዮብ በዚህ ምላሹ ቀደም ሲል ወዳጆቹ የተናገሩትን ነገር ሁሉ በመከለስ ተቃውሞአቸዋል። በኢዮብና በወዳጆቹ መካከል የተደረገው ሁለተኛ ዙር ክርክር እንደተጠቃለለ፥ የኢዮብ ወዳጆች እያንዳንዳቸው የመጨረሻ ንግግራቸውን ያቀረቡበት ሦስተኛ ዙር ክርክር ቀጥሉአል (ኢዮብ 22-31)። በዚህ ዙር ንግግር ሶፋር አንዳችም ነገር አለማለቱ የሚያስገርም ነው። ኢዮብ በዚህ ዙር ለእያንዳንዳቸው መልስ በመስጠት፥ ለምን መከራ በመቀበል ላይ እንዳለ በመጠየቅና ከእግዚአብሔር ምን እንደሚፈልግ በመናገር አጠቃልሏል።  ኢዮብ 22፥ የኤልፋዝ ክስ፡- ከኢዮብ ሦስት ወዳጆቹ ደጉና ምናልባትም በዕድሜ የላቀው ኤልፋዝ፥ አንድ ጻድቅ ሰው አንዳችም ጥፋት ሳይኖርበት ለምን መከራ እንደሚቀበል ለመረዳት አልቻለም ነበር። ስለሆነም እንደገና ኢዮብ ከኃጢአቱ ጋር እንዲፋጠጥና ንስሐ እንዲገባ ለማድረግ ሞከረ።  ኢዮብ 23-24፥ የኢዮብ ምላሽ፡ – ኢዮብ ለኤልፋዝ ሲመልስ፥ እርሱ የሚፈልገው ጉዳዩን ያይለት ዘንድ እግዚአብሔርን ለመገናኘት እንደሆን ገልጿል። እግዚአብሔር ነፃ እንደሚያደርገው እርግጠኛ ነበር። ችግሩ ግን እግዚአብሔር የማይደረስበት መሆኑና ጉዳዩን ለእግዚአብሔር ለማቅረብ እመቻሉን መግለጹ ነበር። ሰይጣን እንደፈለገው፥ ኢዮብ እግዚአብሔርን ባይረግምም እንኳ፥ ቅንና ጻድቅ የሆነ ፍርድ እንዳላደረገ በመናገር እግዚአብሔርን ወቅሶታል። ለኢዮብ ትልቁ ተስፋ አስቆራጭ የሆንበት ጸሎቱንና ክሱን ባለመመለስ እግዚአብሔር ዝም በማለቱ ነበር።  ኢዮብ 25 የበልዳዶስ ክስ፡- ወዳጆቹ በኢዮብ ላይ የሚያቀርቡት ክስ ተጠናቅቆ ነበር። ቢሆንም በልዳዶስ የመጨረሻ ንግግር የማድረግ ዕድል አግኝቶአል። ቀደም ሲል በኢዮብ ላይ ከቀረቡት ክሶቹ አንዳንዶቹን ደግሞ ተናግሮአቸዋል፤ አዲስ ትምህርቱ ግን ጥቂት ነው። ከዚህ በኋላ ሶፋር የሚናገረው አንዳችም ነገር አልነበረውም፤ ስለዚህ ዝም አለ።  ኢዮብ 26-31፥ የኢዮብ የመጨረሻ ምላሽ፡- በመጨረሻ ኢዮብ የወዳጆቹ ክስ ሁሉ ስሕተት እንደሆነ አጠር አድርጎ ተናግሯል። ኢዮብ ጻድቅ መሆኑን ያውቅ ነበር። እንዲሁም እግዚአብሔር ትክክለኛ እንደሆንም ያውቅ ነበር። እነዚህ ሁለት እውነቶች እንዴት ሊስማሙ እንደሚችሉ ግን አያውቅም ነበር። ኢዮብ አሁን ካለበት መከራ፥ ችግርና ሥቃይ ይልቅ እጅግ የተሟላ በረከት የነበረበትን የቀድሞውን የደስተኛነት ሕይወቱን አስታወሰ። ኢዮብ በብርቱ ሥቃይና በድህነት ውስጥ የሆነው በኃጢአቱ ምክንያት እንዳልሆነ እርግጠኛ ነበር።  የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከእነዚህ ምዕራፎች የምትማራቸውን አንዳንድ እውነቶች ዘርዝር። ለ) የኢዮብ ወዳጆች ክስ ከብዙ ክርስቲያኖች አስተሳሰብ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ሐ) የተሳሳቱት እንዴት ነው? መ) ኢዮብን ለማበረታታት ማድረግ የነበረባቸው ነገር ምን ይመስልሃል? ያኔ አንተ ብትኖር ኖሮ ኢዮብን እንዴት ትመክረው ነበር? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡) የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

ኢዮብ 15-31 Read More »

ኢዮብ 1-14

የውይይት ጥያቄ፥ ኤፌሶን 6፡10-18 አንብብ። ሀ) ክርስቲያን የሚዋጋው ከማን ጋር ነው? ለ) የምንዋጋባቸው መሣሪያዎች ምንድን ናችው? ሐ) በጦርነቱ ውስጥ ከለላ የሚሆኑን ነገሮች ምንድን ናችው? መ) የዚህ ዓይነቱ መንፈሳዊ ጦርነት በመካሄድ ላይ እንዳለ የተሰማህን ሁኔታ ግለጽ። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጆች በማያቋርጥ ጦርነት ውስጥ መሆናቸውን ይናገራል። ይህ ጦርነት ከማያምኑ ሰዎች ወይም ከጨቋኝ መንግሥታት ጋር የሚደረግ ሥጋዊ ጦርነት አይደለም፤ ይልቁንም ጦርነቱ መንፈሳዊ ነው። የክርስቲያን ዋና ጠላቶችም ሰይጣንና ተከታዮቹ አጋንንት ናችው። መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያን ለጦርነቱ ዝግጁ መሆን እንዳለበት ያስጠነቅቃል። ጠላታችንን ሁልጊዜ የምናሸንፍበት ችሎታ ሊሰጠን ቃል ስለተገባልን ብርታት ይሰማናል፤ ነገር ግን ከሰይጣን ጥቃት እንዲጠብቁን የሚከላከሉልንን ነገሮች ለመጠቀም መቻል አለብን፤ እነዚህም፡- እውነት፥ ጽድቅ፥ ለምስክርነት መዘጋጀት፥ እምነትና የደኅንነታችን ዋስትና ናቸው። እንዲሁም ሰይጣንን ለማሸነፍ የምንችልባቸውን የጦር መሣሪያዎች ለመጠቀም መቻል አለብን፤ እነዚህም፡- የእግዚአብሔር ቃልና ጸሉት ናቸው። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) አንድ ክርስቲያን ከላይ የተመለከትናቸውን መከላከያዎች በመጠቀም ራሱን ከሰይጣን ጥቃት የሚከላከልባቸውን መንገዶች ግለጽ። ለ) አንድ ክርስቲያን ሰይጣንን ለማጥቃት በመንፈሳዊ የጦር መሣሪያዎች የሚጠቀምባቸውን መንገዶች ግለጽ። በመጽሐፈ ኢዮብ ስለዚህ መንፈሳዊ ጦርነት እንድናውቅ ተጽፎልናል። አብዛኛው የመጽሐፉ ክፍል የሚናገረው ኢዮብ ከመከራ ጋር ስላደረገው ትግልና በመከራው ውስጥ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ የት እንዳለ በማሰብ ስለ መደነቁ ቢሆንም፥ መጽሐፉን ለምናነብ ለእኛ ግን ምክንያቱ የኢዮብን ጽድቅ ለማጥፋት የፈለገው የኢዮብ ከሳሽና ባላጋራ ሰይጣን እንደሆነ ተነግሮናል። መጽሐፈ ኢዮብን ለመረዳት፥ በእግዚአብሔርና በሰይጣን መካከል በሰማይ ምን እንደተደረገ ለኢዮብም ሆነ ለወዳጆቹ ግልጸ እንዳልነበረ መገንዘብ ያስፈልጋል። እኛም ዛሬ በእግዚአብሔርና በሰይጣን መካከል በሚካሄደው መንፈሳዊ ጦርነት ምን በመደረግ ላይ እንዳለ አናውቅም፤ ዳሩ ግን የዚያ ጦርነት ውጤት ለኢዮብ እንደተሰማው፤ ለእኛም እንዲሁ ይሰማናል። የውይይት ጥያቄ፥ ኢዮብ 1-2 አንብብ። ሀ) በኢዮብ 1፡1 ኢዮብ የተገለጠው እንዴት ነው? ለ) ዛሬ አንድ ክርስቲያን እንዲህ ዓይነቱን ምስክርነት የሚያገኘው እንዴት ነው? ሰዎች መልካም ምስክርነትን ሊያገኙ የሚችሉባቸውን መንገዶች የሚያመለክቱ ምሳሌዎችን ጥቀስ። ሐ) ኢዮብ የተፈተነው የመጀመሪያ ፈተና ምን ነበር? ለዚህ ፈተና የሰጠው ምላሽ ምን ነበር? መ) ኢዮብ የተፈተነው ሁለተኛ ፈተና ምን ነበር? ለዚህ ፈተና የሰጠው ምላሽ ምን ነበር?  ብዙ ክርስቲያኖች መከራ ሁልጊዜ የኃጢአት ውጤት እንደሆነ ይመስላቸዋል። አንድ ሰው ሲታመም ወይም ከሌሎች ይልቅ ከፍተኛ መከራ ሲያጋጥመው፥ ይህ በሰውዬው ላይ የደረሰ የእግዚአብሔር ፍርድ ነው በማለት ወዲያውኑ ይወስናሉ። መጽሐፈ ኢዮብ የተጻፈው የዚህ ዓይነቱን አስተሳሰብ ለመቃወም ነው። መጽሐፈ ኢዮብ የሚያተኩረው መከራን በተቀበለ ኃጢአተኛ ላይ ሳይሆን፥ በጻድቁ ኢዮብ ላይ ነው።  ኢዮብ 1-2 መጽሐፈ ኢዮብ 1-2 ኢዮብን ያስተዋውቀናል። እንዴትና ለምን መከራ እንደተቀበለ መግለጽ ይጀምራል። ኢዮብ በዖፅ አገር የሚኖር ሰው ነበር። ዖፅ በኤዶም ወይም በደቡብ ዐረቢያ የነበረ አገር ሳይሆን አይቀርም። ኢዮብ እስራኤላዊ አልነበረም፤ ዳሩ ግን እግዚአብሔርን እጅግ የሚወድ ሰው ነበር። ኢዮብ እንደ ሁላችንም ኃጢአተኛ ቢሆንም እንኳ የሕይወት ባሕርይው ግን በምሳሌነት የሚታይ ነበር። ነቀፋ የሌለበት ፍጹም ቅን ሰው እንደነበር ተገልጾአል። ኢዮብን በኃጢአቱ ሊከሰው የሚችል ማንም አልነበረም። የቅርብ ወዳጆቹ እንኳ በኃጢአት ሊከሱት አይችሉም ነበር። ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚፈራና በሕይወቱም እርሱን የሚያከብር ሰው ነበር። ኃጢአት እግዚአብሔርን ደስ እንደማያሳኝ ያውቅ ስለነበር ክፋትን ይጠላ ነበር። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በሁላችንም ሕይወት እግዚአብሔር ስለሚፈልገው ነገር ይህ ጥሩ ገለጻ የሚሆነው እንዴት ነው? ለ) የዚህ ዓይነት ሕይወት ያላቸው ክርስቲያኖች ቁጥር ጥቂት የሆነው ለምንድን ነው? ሐ) እግዚአብሔርን በመፍራታቸው የሚታወቁና ይህንን መግለጫ የሚያሟሉትን የቤተ ክርስቲያንህን ሰዎች በምሳሌነት ጥቀስ። መ) በሕይወታቸው እንደ ኢዮብ እንዲሆኑ ያደረጋቸው የተለየ ነገር ምንድን ነው? ኢዮብ ፍጹም ጻድቅ ሰው ስለነበር፥ አይሁድ ሀብታምነቱ እንደተጠበቀ የሚኖር አድርገው ያስቡ ነበር። ቁሳዊ ሀብትና ጽድቅ አብረው የሚሄዱ ነገሮች እንደሆኑ፥ መከራና ኃጢአትም ጎን ለጎን የሚጓዙ ይመስላቸው ነበር። የኢዮብ የመጀመሪያ ፈተና፡- የእግዚአብሔርና የልጆቹ ከሳሽ የሆነው ሰይጣን ወደ እግዚአብሔር ቀርቦ፥ ኢዮብ እግዚአብሔርን ያከበረው ከእርሱ ስለተቀበለው በረከት ብቻ እንደሆነ ተናገረ። ሰይጣን ከኢዮብ ሀብቱን ቢወስድበት እንደሚረግመው ለእግዚአብሔር ተናገረ። እግዚአብሔርም ኢዮብ ያለውን ነገር ሁሉ ሰይጣን ይወስድበት ዘንድ ፈቀደ። በእርሱ ላይ ግን አንዳች ነገር እንዳያደርስበት አስጠነቀቀው። ወዲያውኑ ሁለት ነገሮች ሆኑ፡-  1. የኢዮብ ቁሳዊ ብልጽግና ሁሉ ወደመና እጅግ ድሀ ሰው ሆነ።  2. ከሚስቱ በስተቀር የኢዮብ ቤተሰብ በሙሉ ተገደሉና ያለቤተሰብ ብቻውን ቀረ። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህ ነገር በእነርሱ ላይ ቢደርስባቸው፥ የአብዛኛዎቹ ክርስቲያኖች ምላሽ ምን ይሆን ነበር? ፤ ለ) አንተ ኢዮብን ብብትሆን ኖሮ፥ ምላሽህ ምን ይሆን ነበር?  ኢዮብ በሰማይ ምን እንደተደረገ አላወቀም ነበር። የመከራውን ውጤት ተመለከተና ሥቃዩን ተቀበለ። በእግዚአብሔር ላይ የነበረው እምነት ጥልቅ ነበር፤ ስለዚህ «እግዚአብሔር ሰጠ፥ እግዚአብሔርም ነሳ፣ የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን» (ኢዮብ 1፡21) በማለት እግዚአብሔርን አከበረ።  የኢዮብ ሁለተኛ ፈተና፡- ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሰይጣን እንደገና ኢዮብን ከሰሰ። ክሱ፡- ኢዮብ እግዚአብሔርን የተከተለው ለግል ጥቅሙ ነው የሚል ነበር። ሰይጣን ለሰው ልጅ እጅግ አስፈላጊው ነገር ጤንነቱ እንደሆነ ያውቅ ነበር! ስለዚህ ሰይጣን ኢዮብን በደዌ ቢመታው ኢዮብ እግዚአብሔርን እንደሚረግም ተናገረ። ሰይጣንን ይህን ያደርግ ዘንድ እግዚአብሔር ፈቀደለት፤ ኢዮብን እንዲገድል ግን አልፈቀደለትም ነበር።  ኢዮብም ወዲያውኑ ከራሱ እስከ እግሩ ድረስ ሰውነቱ በሙሉ በከፋ ቍስል ተመታ። ሚስቱ ሳትቀር እግዚአብሔርን ሰድቦ እንዲሞት መከረችው። የኢዮብ ምላሽ ግን «ከእግዚአብሔር እጅ መልካሙን ተቀበልን፤ ክፉ ነገርንስ አንቀበልምን?» (ኢዮብ 2፡10) የሚል ነበር።  ኤልፋዝ፥ በልዳዶስና ሶፋር የሚባሉ ሦስቱ ወዳጆቹ ስለ ሕመሙና ስለደረሰበት ክፉ ነገር ሰምተው ኢዮብን ለማጽናናት መጡ። እንደ መልካም ወዳጆች ለሰባት ቀናትና ሌሊት የኢዮብን ሕመም በጸጥታ ተካፈሉ። እነዚህ ሦስቱ የኢዮብ ወዳጆች በችግርና በመከራ ጊዜ ከሚያውቁት ነገር በላይ አሳብ እንደሚሰነዝሩና መልስ እንደሚሰጡ መልካም መሳይ ክርስቲያኖች ይመሰላሉ። እነዚህ ሦስት ወዳጆቹ በተሳሳተ መንገድ ኢዮብን በኃጢአት በመክሰስ ሌላ የሥቃይ ምንጭ ሆኑበት። ኤሊሁ ለምን እንዳልተጠቀሰ አናውቅም። ወጣት ስለነበር የእርሱን ስም በዚህ ደረጃ መጥቀስ የማያስፈልግ ሆኖ ይሆናል፤ ወይም ደግሞ ኢዮብን ለመጠየቅ የመጣው ምናልባት ቆይቶ ይሆናል፤ ዳሩ ግን በንግግራቸው ሁሉ ውስጥ ኤሊሁ ከኢዮብና ከወዳጆቹ ጋር እንደነበረ ይመስላል።  ኢዮብ 3  መጽሐፈ ኢዮብ ምዕራፍ 3 የሚጀምረው በኢዮብ የብሶት ንግግር ነው። ኢዮብ እግዚአብሔርን ባይራገምና እምነቱን ባይክድም እንኳ የጠለቀ ኃዘንና ተስፋ መቍረጥ ደርሶበታል። ኃዘኑንና ሥቃዩን ለመሸሽ ባይወለድ ወይም ቢሞት ይሻለው እንደነበርና ያንንም እንደተመኘ እንመለከታለን።  ኢዮብ 4-14 በኢዮብና በወዳጆቹ መካከል የተደረገ የመጀመሪያ ዙር ክርክር  ኢዮብ 4-5፥ የኤልፋዝ ክስ፡- ኤልፋዝ፥ የኢዮብን ቁጣና መራርነት ከሰማ በኋላ፥ በሕይወቱ ውስጥ ኃጢአት እንዳለ ይነግረው ነበር። ኢዮብ የተቀጣበት ምክንያት ይህ ነበር ይላል። የኤልፋዝ ንግግር ከመሠረታዊ የእምነት ትምህርት አንጻር አንዳችም ስሕተት አልነበረበትም። ችግሩ ግን ይህ መሠረታዊ የእምነት ትምህርት እውነታ ኢዮብን በተመለከተ ትክክል አልነበረም። ኢዮብ ሥቃይን የተቀበለው በኃጢአቱ ምክንያት ሳይሆን በጽድቁ ምክንያት ነበር።  ኢዮብ 6-7፥ የኢዮብ ምላሽ፡- ኢዮብ እርሱ የሚያውቀውና ያልተናዘዘው ኃጢአት በሕይወቱ እንደሌለ ይመልስ ነበር፤ ስለዚህ መከራና ሥቃይ የሚቀበለው በኃጢአት ምክንያት አልነበረም። ይልቁንም በዚህ በወደቀ ዓለም ውስጥ እስካሉ ጊዜ ድረስ መከራ የሰው ልጆች ሁሉ ዕጣ ፈንታ እንደሆነ ይናገር ነበር።  ኢዮብ 8፥ የበልዳዶስ ክስ፡- በልዳዶስ እግዚአብሔር ጻድቅ ስለሆነ በጻድቅ ሰው ሕይወት ላይ መከራን ጨርሶ አያመጣም ብሎአል። ስለዚህ ይህ ሁሉ ሥቃይና መከራ የደረሰበት ኢዮብ በሕይወቱ ኃጢአት እንደሚኖር በመግለጽ ምሕረት ቢጠይቅ፥ መሐሪው እግዚአብሔር ኢዮብን እንደሚያድስ ተናግሯል።  ኢዮብ 9-10፥ የኢዮብ ምላሽ፡- ፍጹም ቅዱስ በሆነው እግዚአብሔር ፊት ሰው ጻድቅ ሊሆን እንደማይችል ኢዮብ ተስማምቷል፤ ነገር ግን ያልተናዘዘው ኃጢአት በሕይወቱ አለመኖሩን አሁንም መናገሩን ቀጥሎ ነበር።  ኢዮብ 11፥ የሶፋር ክስ፡- ሶፋር፥ የደረሰበትን ጥልቅ ኃዘን ሳይገነዘብ በኢዮብ ላይ በቁጣ ተናግሯል። ልክ እንደ ሌሎቹ፥ ሶፋርም ኢዮብን ስለ ኃጢአቱ ከሶታል።  ኢዮብ 12-14፥ የኢዮብ ምላሽ፡- በዚህ ስፍራ ኢዮብ የሚሰጠው ምላሽ በእርሱና በወዳጆቹ

ኢዮብ 1-14 Read More »

ከመጽሐፈ ኢዮብ የምናገኛቸው ልዩ ትምህርቶች

1. የሰይጣን ሥራ፡- ቀደም ሲል በኦሪት ዘፍጥረት ውስጥ ሰይጣን በእባብ ተመስሉ ሔዋንን እንዳታለላትና ወደ ኃጢአት እንደመራት የሚያሳየውን የሰይጣንን ሥራ ተመልክተናል፤ ዳሩ ግን በዚያ ታሪክ ውስጥ አይሁድ ከምርኮ እስኪመለሱ ድረስ ስለ ሰይጣን የተገለጠው ነገር እጅግ አነስተኛ ነበር። በዘካርያስ መጽሐፍ ውስጥ አይሁድ ስለ ሰይጣን አካላዊ ህልውና የነበራቸው እውቀት እያደገ መምጣቱን መመልከት እንጀምራለን። በኢሳይያስ 14ና በሕዝቅኤል 28 ስለ አንድ ታላቅ የክፋት ኃይል የሚናገር ፍንጭ እንመለከታለን፤ ዳሩ ግን እነዚህ ጥቅሶች በግልጽ ወደ ሰይጣን አያመለክቱም። በመጽሐፈ ኢዮብ የዚህ የክፋት ኃይል ማንነት ተገልጾልናል። ከዚያም በኋላ በከፍተኛ ደረጃ በሚታወቅበት «ሰይጣን» በተባለ ስሙ ተጠርቶ እናገኛለን። ሰይጣን ማለት «ባላጋራ» ማለት ነው። ሰይጣን የእግዚአብሔርና የልጆቹ ባላጋራ ነው። ሰይጣን ከእግዚአብሔርና ከዕቅዱ በተቃራኒ የሚሠራ ነው፥ በተለይ ቅዱሳንን በእግዚአብሔር ፊት የሚከስ ሆኖ ተገልጾአል።  2. የእግዚአብሔር ልጆች ጠበቃ አላቸው (ኢዮብ 5፡1፤ 9፡33፤ 16፡19-21)። ኢዮብ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ባያውቅም እንኳ እግዚአብሔርን ግን ያውቅ ነበር። ስለ እግዚአብሔር የነበረው እውቀት እግዚአብሔር ጠበቃው እንደሚሆንለት ዋስትና ሰጠው። ኢዮብ በሰማይ ስላለ የፍርድ ቤት ችሎት ያስብ ነበር። በዘላለማዊው ፈራጅ ፊት ጠበቃ ሆኖ ከማንኛውም ጥፋት ነፃ በማድረግ ጻድቅ መሆኑን እንደሚያረጋግጥለት እርግጠኛ ነበር። በአዲስ ኪዳን እውነተኛው ጠበቃ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ግልጽ ሆኖአል (1ኛ ጢሞቴዎስ 2፡5 ተመልከት)። ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክ እንደመሆኑና የኃጢአታችንን ዋጋ በመስቀል ላይ በመሞት ሙሉ በሙሉ በመክፈሉ፥ ዘላለማዊ ዳኛ በሆነው በእግዚአብሔር ፊት ለመቆምና እኛን ለማጽደቅ የሚችል ኢየሱስ ብቻ ነው። እግዚአብሔር «በደለኞች አይደላችሁም» የሚለውን ቃል ስለ እኛ መናገሩ የሚረጋገጥልን ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሠራው ሥራ ብቻ ሳይሆን፥ ጠበቃችን እንደ መሆኑ መጠን ያለማቋረጥ በሚሠራው ሥራ ጭምር ነው። ኢዮብ ስለ ጠበቃ ያቀረበው ጩኸት በኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት ተፈጽሟል።  የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ኢየሱስ ክርስቶስ ጠበቃችን መሆኑን መገንዘባችን ማበረታቻ የሚሆነን እንዴት ነው? ለ) በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በምናልፍበት ጊዜ ኢዮብ በመከራ ውስጥ ሲያልፍ ካሳየው ዝንባሌ የምንማራቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? ኢዮብ ከፍተኛ ጽናትን አሳይቷል። እንደ እውነቱ ኃጢአት እንደሠራና በኃጢአቱ ምክንያትም እንደተቀጣ ለወዳጆቹ ቢናገር እጅግ ይቀለው ነበር፤ ነገር ግን ኢዮብ ንጹሕ እንደሆነ ያውቅ ስለነበር ከወዳጆቹ ንትርክ ለመዳን ብሎ ለመዋሸት ፈቃደኛ አልሆነም። ዛሬም ቢሆን ራሳቸውን በሚገባ የሚያውቁ፡ በማንኛውም ሰው ፊት በማስመሰል የማይቆሙና እውነትን በግልጽ የሚናገሩ ወንዶችና ሴቶች ያስፈልጉናል።   (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ከመጽሐፈ ኢዮብ የምናገኛቸው ልዩ ትምህርቶች Read More »

የመጽሐፈ ኢዮብ ዓላማ

በመከራና በክፋት መካከል ያለው ግንኙነት መጽሐፈ ኢዮብ የተጻፈው፥ በዚህ ዓለም ላይ ያለውን መከራና ሥቃይ፥ በተለይም ደግሞ ቅዱሳን ወንዶችና ሴቶች ለምን መከራ እንደሚቀበሉ ለማስረዳት ነው። የምንኖረው መከራና ሥቃይ በሞላበት ዓለም ውስጥ ነው። መከራ የሚመጣው ከየት ነው? እግዚአብሔር ሉዓላዊና ጻድቅ ከሆነ፥ በምድር ላይ መከራና ሥቃይ የሚኖረው ለምድን ነው? የውይይት ጥያቄ፥ ቅዱስ የሆነው እግዚአብሔር በምድር ላይ መከራ እንዲኖር ለምን እንደሚፈቅድ አንድ ሰው ቢጠይቅህ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር እንዴት ትመልስለታለህ? የሰው ልጅ ባለፈበት የዓለም ታሪክ ውስጥ ሁሉ ከመከራና ከክፋት ጋር ሲታገል ኖሯል። መከራና ክፋት በብዙ ልዩ ልዩ ዓይነት መንገዶች ይመጣሉ። መከራና ሥቃይን የሚያመጡ እንደ ጐርፍና ድርቅ ያሉ የተፈጥሮ አደጋዎች አሉ፤ በተጨማሪ በሽታም አለ። እንደ አስገድዶ ሴትን መድፈር፥ ነፍስ መግደል፥ ጦርነት፥ ወዘተ ያሉ ሰው-ሠራሽ መከራዎችና ሥቃዮችም አሉ። እነዚህ ነገሮች ሁሉ የሚመነጩት ከየት ነው? እግዚአብሔር እነዚህ ነገሮች ይቀጥሉ ዘንድ ለምን ፈቀደ? የተለያዩ ሰዎችና የሃይማኖት ክፍሎች ስለ መከራ ያላቸው አስተሳሰብ ወይም የሚሰጡት መልስ የተለያየ ነው። 1. አንዳንዶች፡- እግዚአብሔር መከራን ለመቆጣጠር ብቁ አይደለም፤ ይልቁንም የእግዚአብሔርን ያህል ኃይል ያለው፥ እንደ ዲያብሎስ ያለ የክፋት ኃይል አለ፤ ስለዚህ እግዚአብሔርን በማሸነፍ ክፋትን ወደ ምድር ያመጣል ይላሉ። አብዛኛዎቹ የምሥራቅ ሃይማኖቶች (የሂንዱ፤ የቡድሀ ሃይማኖት) አስተሳሰብ የዚህ ዓይነት ነው።  2. ሌሎች ደግሞ፡- እግዚአብሔር በእርግጥ ጻድቅ አምላክ አይደለም፤ ስለዚህ ያለ አንዳች ምክንያት ክፋትን ወደ ሕይወታችን ያመጣል ይላሉ። እግዚአብሔር በጣም ተለዋዋጭ አምላክ ነው። አንዳንድ ጊዜ ደግ ይሆናል፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ ያላንዳች ምክንያት ክፉ ነገርን ያመጣል። እኛ በምንፈጽመው ተግባርና እግዚአብሔር ወደ ሕይወታችን በሚያመጣው ነገር መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት የለም። የብዙ ሙስሊሞች አስተሳሰብ ይህ ነው። እግዚአብሔር ኃይል እንዳለው የሚያውቁት እነዚህ ሙስሊሞች መከራና ክፋትን የሚያመጣው እግዚአብሔር ራሱ እንደሆነና በዚህም ምክንያት ፍትሐዊ እንዳልሆነ ለመቀበል ተገድደዋል። 3. አንዳንድ ሰዎች ብዙ ዓይነት አማልክት ወይም መናፍስት እንዳሉ ይናገራሉ። ከነዚህም አንዳንዶቹ መልካም፥ ሌሎቹ ደግሞ ክፉዎች ናቸው። በእነዚህ ሁለት ዓይነት አማልክት መካከል የማያቋርጥ ትግል ይካሄዳል። ሰዎቹ ክፉ የሆኑት አማልክት እንዳይጐዱአቸው የእህልና የመጠጥ መሥዋዕት በማቅረብ ደስ ሊያሰኙአቸው ይገባል። ሰዎች ከአማልክት ችሮታን ለመግዛት ይፈልጋሉ። በመላው ዓለም ላይ የነገድ ሃይማኖት የሚከተሉ ሰዎች የተለመደ አመለካከት ይህ ነው።  4. አንዳንድ ሰዎች፡- እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረ በኋላ እንዲሁ እንደተዋት ያስተምራሉ፤ ስለዚህ ክፉ ነገሮች የየትኛውም የእግዚአብሔር ተግባር ውጤት አይደሉም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በማይቆጣጠርበት ወይም በኃላፊነት በማይጠየቅበት መንገድ ሰውና ተፈጥሮ ባደረጉት ተፈጥሮአዊ ግንኙነት የሚፈጸም ነው ይላሉ። የአብዛኛዎቹ ምዕራባውያን ምሁራን አመለካከት ይህ ነው። 5. እግዚአብሔር የለም የሚል እምነት ያላቸው (ኤቲስቶችና እግኖስቲኮች)፡ መከራ በተፈጥሮ ሥርዓት የሚከሠት እንደሆነ ለማመን ተገድደዋል። መከራ ምንም ዓላማ የለውም፤ ከእርሱም የማምለጥ መንገድ የለም። የእኛ ኃላፊነት የሚያደርስብንን ተጽዕኖ ውሱን ለማድረግ መጣር ብቻ ነው።  የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ስለ መከራ ከላይ ከተመለከትናቸው አመለካከቶች ውስጥ በአንዱ የሚያምኑ የምታውቃቸው ሰዎችን በምሳሌነት ጥቀስ። ለ) ስለዚህ አመለካከታቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ የምትሰጠው መልስ ምንድን ነው? ከአመለካከቶቹ አንዱን ውሰድና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መልስ ጻፍ። በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መሠረት ከፍ ሲል የተመለከትናቸው አምስቱ አመለካከቶች በሙሉ ስሕተት ናቸው። እግዚአብሔር ራሱ በሰጠው መገለጥ መሠረት አይሁድና ክርስቲያኖች የሚከተሉትን እውነተች ያምናሉ፡- 1. እግዚአብሔር የዓለም ፈጣሪና በውስጥዋ ላይ የሚገኙ ነገሮች ሁሉ ተቆጣጣሪ ነው። በእያንዳንዱ ሰው ሕይወትና በዓለም ክሥተቶች ውስጥ ራሱን የሚያገልል አምላክ አይደለም። ሕይወት እግዚአብሔር ወደ መልካም ፍጻሜ በሚመራው በጎ ዓላማ የተሞላ እንጂ ትርጕም የለሽ አይደለም።  2. እግዚአብሔር ታላቅ ኃይል ያለው ነው፤ ስለዚህ ክፋትን ሁሉ ለመቈጣጠር ይችላል። ክፋት ግን እርሱን ሊቈጣጠረው አይችልም። ደግሞም እግዚአብሔር ጻድቅ ስለሆነ በባሕርይው ክፉ የሆነውን ነገር ሊያደርግ አይችልም።  3. እግዚአብሔር በዓለማት ሁሉ «ሰው የሚዘራውን ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤» (ገላትያ 6፡7 ተመልከት) የሚል መመሪያ መሥርቷል። ይህ ማለት አንድ ሰው መልካም ሕይወትን ከኖረ ከእግዚአብሔር ሽልማቱን ይቀበላል፤ የኃጢአት ሕይወት ከኖረ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ቅጣትን ይቀበላል ማለት ነው። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህ የመጨረሻ ሥነ-ምግባራዊ መመሪያ በሕይወት ውስጥ እውን የሆነው እንዴት ነው? ለ) የዚህን መመሪያ ተግባራዊነት ያየኸው እንዴት ነው? ምሳሌዎችን ጥቀስ። ከኦሪት ዘዳግም ጥናታችን እንደምታስታውሰው፥ ያኛው የሙሴ ሕግ ክፍል ለእግዚአብሔር ለሚታዘዙ በረከትን፥ ለማይታዘዙት ደግሞ መርገምን የሚያመጣ እንደሆነ የሚያሳይ ነበር። አይሁድ በዚህ የሥነ-ምግባራዊ ሕግ መመሪያ ላይ ሌላ ከራሳቸው ጨመሩበት። እግዚአብሔር ሉዓላዊ ከሆነ፥ መከራና ሥቃይ የሚመጣው ከእርሱ ብቻ ነው በማለት አይሁድ ይከራከሩ ነበር። እንዲሁም እግዚአብሔር ጻድቅ ስለሆነ መከራና ሥቃይ ከርሱ ዘንድ የሚመጣ ቅጣት ነው። እግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ ጻድቅ ከሆነ፥ መከራውና ሥቃዩ ከሚቀበለው ሰው ኃጢአተኝነት ጋር ተመጣጣኝ መሆን እንዳለበት ያስቡ ነበር። አንድ ሰው ያለው ሀብትና በረከት የሰውዬውን ጻድቅነት የሚያረጋግጥ ነው። የሚደርስበት መከራና ሥቃይ ደግሞ የኃጢአተኝነቱ ማረጋገጫ ነው የሚል እምነት ነበራቸው። አንድ ሰው ሀብታም ከሆነ በእግዚአብሔር ፊት ትክክለኛ ነው ማለት ነው፤ ዳሩ ግን አንድ ሰው በሕመምና በደዌ የሚሠቃይ ከሆነ በኃጢአቱ ምክንያት እግዚአብሔር እየቀጣው ነው ማለት ነው፤ ዳሩ ግን ጻድቃን ሆነው መከራን የሚቀበሉ፥ ኃጥአን ሆነው መልካም ነገርን የሚለማመዱ ሰዎች ስላሉ፥ ይህኛው አቀራረባቸው ስሕተት ነበር። የውይይት ጥያቄ፥ ዮሐንስ 9፡1-3 አንብብ። ሀ) ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን በጠየቁት ጥያቄ ውስጥ ስለ መከራ የነበራቸው አስተሳስብ የዚህ ዓይነት መሆኑን እንዴት ታያለህ? ለ) የዚህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ዛሬም በበርካታ ክርስቲያኖች የሚደገፈው እንዴት ነው?  4. በጎነት ሽልማትን፥ ከፋት ደግሞ ፍርድን ማምጣቱ ዓለም አቀፋዊ መመሪያ ቢሆንም፥ እግዚአብሒር ሽልማት ወይም ፍርድ መቼ እንደሚመጣ አይናገርም። አንዳንድ ጊዜ ወዲያውኑ ይሆናል። እግዚአብሔርንና ቤተ ክርስቲያንን በመቃወማቸው የተመቱ ሰዎች እንዳሉ ሁላችንም ምስክሮች ነን። ይሁን እንጂ፥ ሀብታሞች የሆኑ ብዙ ኃጥአን እንዳሉና ድሆች የሆኑ ብዙ ጻድቃን እንዳሉ ለሁላችንም ግልጽ ነው፤ ስለዚህ ኃጥአን ሁሉ ወዲያውኑ ይቀጣሉ ጻድቃንም ወዲያውኑ ሽልማታቸውን ያገኛሉ ማለት አንችልም። እግዚአብሔር የመጨረሻውን ሽልማት ወይም ቅጣት ለዘላለም ይሰጣል። ክርስቲያኖች እንደ መሆናችን መጠን «እገሌ ሀብታም ነውና እግዚአብሔር ሸልሞታል፤ ወይም እገሌ ታሞአልና በሕይወቱ ኃጢአት አለ» ብለን ከመናገር መቆጠብ አለብን (መዝሙር (73) ተመልከት)። ክፉ ሰዎች ብዙ ጊዜ የክፋታቸውን ያህል አይቀጡም፤ መልካም ሰዎችም እንደ መልካምነታቸው አይሸለሙም። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) አንዳንድ ክርስቲያኖች የታመመ፥ ወይም ድሀና አካለ-ስንኩል የሆነ ክርስቲያን ሲያዩ፡- እንደዚህ የሆነው በሕይወቱ ኃጢአት ስላለ ነው ሲሉ ሰምተህ ታውቃለህን? ሁኔታውን ግለጽ። ለ) ይህ አባባል ትክክል ነውን? ሐ) ይህንን በምትሰማበት ጊዜ ለእነርሱ የምትሰጠው መልስ ምንድን ነው? 5. መከራ በብዙ ልዩ ልዩ ምክንያቶች ሊመጣ ይችላል። ምክንያቶቹ ሁሉ ግን በእግዚአብሔር ቁጥጥር ሥር ናቸው፤ ዳሩ ግን መከራ ሁሉ የኃጢአት ውጤት ነው ለማለት አንችልም። መከራ ሊመጣ የሚችልባቸውን የሚከተሉትን ሁኔታዎች ተመልከት፡- ሀ. የተፈጥሮ አደጋዎች፡- አንዲት አገር በድርቅ ከተመታች እግዚአብሔር ቀጣት ማለት ነውን? አንዴትስ አገር ስትበለጽግ ከሌሎች የበለጠ ጻድቅ ነች ማለት ነውን? አይደለም። እንዲህ ብለን መናገር አንችልም። ድርቅ ወይም ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች ሲኖሩ፥ አብዛኛዎቹ በአዳምና በሔዋን ኃጢአት የተነሣ በዓለም ላይ በደረሰው መርገም ምክንያት የመጡ ናቸው። እነዚህ ነገሮች ሰዎች ንስሐ መግባት እንዳለባቸው ለማስታወስ በምድር ላይ ይሆኑ ዘንድ በእግዚአብሔር የተፈቀዱ ቢሆኑም፥ ሁልጊዜ በአንድ አገር ውስጥ ካለ በጎነት ወይም ኃጢአት ጋር በቀጥታ የተዛመዱ አይደሉም። የሰው ልጅ የኃጢአት ውድቀት ውጤት ስለሆነው በሽታም ተመሳሳይ ነገር ማለት ይቻላል። ሁላችንም ብንሆን እንታመማለን ደግሞም እንሞታለን። ይህም ተፈጥሮአዊ ሂደት እንጂ በእኛ ዘንድ ካለ ኃጢአት ጋር ሁልጊዜ የሚያያዝ አይደለም። ለ. በሰው ልጅ ክፋት ወይም መጥፎ ውሳኔ ምክንያት የሚከሠቱ የተፈጥሮ አደጋዎች፡- የመጨረሻ ምሳሌ የሆነው ጦርነት የሚመጣው በሰው ልጅ ራስ ወዳድነትና በኃጢአት ምክንያት እንጂ በእግዚአብሔር ሊመካኝ የሚችል አይደለም። ስለዚህ እኛም በሠራናቸው ስሕተቶች ወይም ባደረግናችው መጥፎ ውሳኔዎች ምክንያት ብዙ ጊዜ

የመጽሐፈ ኢዮብ ዓላማ Read More »

የመጽሐፈ ኢዮብ መግቢያ

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ክርስቲያን አንዳንድ ጊዜ መከራ የሚቀበልባቸውን ምክንያቶች ጥቀስ። ለ) በክርስቲያን ላይ የሚደርሰው መከራ ሁልጊዜ የኃጢአት ውጤት ነውን? መልስህን አብራራ። ሐ) አንድ ክርስቲያን በበሽታ በሚሠቃይበት ወይም የሚወደው ሰው በሞት በሚለይበት ጊዜ የምትሰጠው ምክር ወይም ማበረታቻ ምንድን ነው? የምንኖረው መከራና ሥቃይ በሞላበት ዓለም ውስጥ ነው። ትንንሽ ልጆች ራሳቸውን በሕይወት ለማቆየት የሚችሉበትን ዕድል ሙሉ በሙሉ በማጣት፥ በየቀኑ በበሽታና በራብ ይረግፋሉ። ወታደሮች ብቻ ሳይሆኑ ብዙ ሰላማዊ ሰዎች የሚያልቁባቸው በርካታ ጦርነቶች በምድራችን ይካሄዳሉ። እግዚአብሔር በከፍተኛ ደረጃ የሚጠቀምባቸው ታላላቅና ታዋቂ ክርስቲያኖች ይታመማሉ ይሞታሉም። ይህ ሁሉ ክርስቲያኖችን «ለምን?» የሚል ጥያቄ እንዲሰነዝሩ ያስገድዳቸዋል። ለመረዳት በጣም አስቸጋሪ ከሆኑ ነገሮች አንዱ መከራን የመቀበል ጉዳይ ነው። እጅግ ጻድቅ የሚመስሉ ሰዎች መከራን የሚቀበሉት ለምንድን ነው? በሌላ አንጻር ደግሞ እጅግ ክፉ የሆኑ ሰዎች መልካም ሕይወትን የሚኖሩት ለምንድን ነው? ይህ ጉዳይ እንዴት ትክክል ሊሆን ይችላል? እግዚአብሔር ምንም ሳናደርግ በዚች ዓለምና በሕይወታችን ላይ ብዙ መከራ እንዲመጣ በማድረጉ ትክክል ነውን? የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ከተፈጠረና በኃጢአት ከወደቀ ጀምሮ ይህ ጥያቄ ራስ ምታት ሆኖበታል። ጉዳዩ በጣም የተወሳሰበ ስለሆነ ሰዎችን ሁሉ የሚያረካ መልስ መስጠት እጅግ አዳጋች ነው። በተለይ ደግሞ መከራን ለሚቀበሉ ሰዎች ለዚህ ጉዳይ መልስ መስጠት ከባድ ነው። እግዚአብሔር መጽሐፈ ኢዮብን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲጨመር ያደረገው ይህንን መከራ መቀበልን በሚመለከት የሚሰነዘር የምንጊዜም ጥያቄ ለመመለስ ይረዳ ዘንድ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፥ ሰዎች በተለይ ደግሞ ጥፋተኛ ያልሆኑት መከራ ስለሚቀበሉበት ምክንያት ሁሉ መልስ ባይሰጥም፥ በመከራ ጊዜ በእምነታችን ጸንተን እንድንኖር የሚያደርጉንን የተወሰኑ መልሶች ይሰጠናል። መጽሐፈ ኢዮብ ስለ አንድ ጻድቅ ሰው መከራ መቀበል የሚናገር ነው። ይህ ሰው ሁሉን ነገር ቢያጣም እንኳ በእግዚአብሔር ላይ ስለነበረው ጽኑ እምነት እናነባለን። በተጣማሪም በመከራ ውስጥ ሳለ ስለ እግዚአብሔር የጽድቅ ፍርድ ቢገረምም በግሉ ስለ ፈጸመው ትግል እንመለከታለን።  የመጽሐፈ ኢዮብ ጸሐፊ በመጽሐፈ ኢዮብ ውስጥ የምናገኘው ታሪካዊ ዘገባ አነስተኛ በመሆኑ መቼ እንደተጻፈና ማን እንደጻፈው ለመናገር አንችልም። ልናደርግ የምንችለው የመመራመር ግምትን ማቅረብ ነው። የመጽሐፈ ኢዮብ አጻጻፍ በሁለት ደረጃዎች የተከናወነ ሳይሆን አይቀርም። በመጀመሪያ፥ የመጽሐፈ ኢዮብን ታሪካዊ ድርጊት እናገኛለን። መጽሐፉን በጥንቃቄ በምንመለከትበት ጊዜ የምንረዳው ነገር፥ ኢዮብ እስራኤላዊ እንዳልሆነና በኤዶም ወይም በዓረብ ምድር የኖረ ሰው እንደሆነ ነው። ኢዮብ የኖረው የእስራኤል ሕዝብ አባቶች የሚባሉት አብርሃም፥ ይስሐቅና ያዕቆብ በኖሩበት ዘመን ይመስላል። ይህ ማለት መጽሐፈ ኢዮብ የተጻፈው ከ3000-2000 ዓ.ዓ. ባለው ጊዜ ውስጥ ነበር ማለት ነው። ብዙ ምሁራን ይህን አቋም የያዙባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ፡-  1) የኢዮብ ዕድሜ በኦሪት ዘፍጥረት ውስጥ ከምናያቸው የእስራኤል ሕዝብ አባቶች ዕድሜ ጋር ተቀራራቢ ነው።  2) ኢዮብ ከብት አርቢ ነበርና ሀብቱም በከብቶቹ ላይ የተመሠረተ ነበር፤ ይህም ከአብርሃም ጋር ይመሳሰላል።  3) ኢዮብ ቤተሰቡን እንደ ሊቀ ካህን የሚያገለግልና እንደ አብርሃም መሥዋዕት የሚያቀርብ ሰው ነበር።  4) በመጽሐፈ ኢዮብ ውስጥ ስለ ሙሴ ሕግ፥ ስለ መገናኛው ድንኳን ወይም ስለ ቤተ መቅደሱ የሚናገር አንዳችም ነገር አልተጠቀሰም። 5) በነቢያት ዘመን እንደነበረው የእግዚአብሔርን ቃል ያስተምሩ ስለነበሩ የአይሁድ ነቢያት የተጠቀሰ አንዳችም ነገር የለም፤ ስለዚህ ኢዮብ ይኖር የነበረው ከክርስቶስ ልደት በፊት በሁለተኛው ሺህ ዓመት ይመስላል።  ሁለተኛው፥ መጽሐፈ ኢዮብ ከፍተኛ ትምህርትና ችሎታ በነበረው በአንድ ባልታወቀ ሰው የመጻፉ ነገር ነው። መጽሐፈ ኢዮብ በጥንታዊ ዓለም ከተገኙ ከፍተኛ የሥነ-ጽሑፍ ሥራዎች ወይም ግጥሞች ውስጥ አንዱ ነው። ጸሐፊው መልእክቱን ለማስተላለፍ የሚያስችለውን ግጥም ለመጻፍ ከፍተኛ ችሉታውን ተጠቅሟል። እንደ አንዳንዶቹ ግምት ደግሞ መጽሐፈ ኢዮብ የተጻፈው ከሙሴ እስከ ዕዝራ ባለው ዘመን (1440-450 ዓ.ዓ.) በማንኛውም ጊዜ ውስጥ ሊሆን ይችላል። እንዲያውም አንዳንድ ምሁራን የመጽሐፉ ጸሐፊ ሙሴ እንደሆነ ቢናገሩም፥ ለዚህ አመለካከት ምንም ማስረጃ የለንም። ጸሐፊው ማን እንደሆነ አይታወቅም ማለቱ የተሻለ ነው። መጽሐፉ በአይሁድ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተካተተ ጸሐፊው እስራኤላዊ እንደሆነ መገመት እንችላለን። ጽሑፉንና የተጻፈበትን ቋንቋ ስንመለከት፥ ጸሐፊው በጣም የተማረ ሰው እንደነበረ እንገነዘባለን። ጸሐፊው ስለ መከራና እግዚአብሔርም ከመከራ ጋር ስላለው ግንኙነት የሚያስብ ፈላስፋ ነበር። እርግጠኞች መሆን ባንችልም፥ ጸሐፊው ይህንን ታሪክ በቃል ሲወርድ ሲዋረድ ከመጣ ትውፊት ሰምቶታል ወይም የተጠቀመበት ሌላ መጽሐፍ አለ። ብዙ ምሁራን መጽሐፉ የተጻፈው ከንጉሥ ሰሎሞን በኋላ (970 ዓ.ዓ.) ከእስራኤል ምርኮ በፊት (586 ዓ.ዓ.) እንደሆነ ይመስላቸዋል።  የመጽሐፉ ርእስ መጽሐፈ ኢዮብ የተሰየመው በታሪኩ ዋና ገጸ ባሕርይ ስም ነው። መጽሐፉ የሚናገረው በመከራ ውስጥ ስላለፈው፥ ስለ ጻድቁ ሰው ስለ ኢዮብ ነው። ታሪኩ የሚያንጸባርቀው ኢዮብ በመከራ ውስጥ እያለ የጠየቃቸውን ጥያቄዎችና ሌሎች ሰዎች ስለ መከራ የሰጡዋቸውን የተለመዱ መልሶች ነው። መጽሐፈ ኢዮብ በሥነ-ጽሑፍነቱ መጽሐፈ ኢዮብ፡- በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ከሚገኙ እጅግ ምርጥ ከሆኑ የግጥም መጻሕፍት መካከል አንዱ ቢሆንም፥ ለመተርጐም እጅግ አስቸጋሪ ከሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አንዱ ነው። ምሁራን ስለ ትርጕማቸው እርግጠኞች ያልሆኑባቸው በርካታ ቃላትና ዐረፍተ ነገሮች የሚገኙበት መጽሐፍ ነው። ስለተለያዩ የመጽሐፈ ኢዮብ ትርጒሞች ያሰብን እንደሆነ በትርጕም ብዙ የሚለያዩበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው። መጽሐፈ ኢዮብ ባለሙያ በሆነ ጸሐፊ በጥንቃቄ ታቅዶ የተጻፈ መጽሐፍ ነው። ጽሑፉ በአብዛኛው በሕጋዊ የችሎት ክርክር መልክ የቀረበ ሲሆን፥ በዚህ ክርክር ጸሐፊው ኢዮብን ከሳሽ አድርጎ በማቅረብ የእግዚአብሔርን ቅን ፍርድ ያሳያል። መጽሐፈ ኢዮብን በምታነብበት ወቅት የሚከተሉትን ነገሮች አስተውል፡- 1. መጽሐፈ ኢዮብ የሚጀምረው የግጥም መልክ በሌለው የአጻጻፍ ስልት ሲሆን (ኢዮብ 1-2)። የሚጠቃለለውም በዚሁ ዓይነት ሥነ-ጽሑፍ ነው (ኢዮብ 42)፤ ዳሩ ግን በመካከል ያሉት ምዕራፎች በሙሉ በግጥም መልክ የቀረቡ ናቸው።  2. በመጽሐፉ መጀመሪያ ላይ ኢዮብን የምናገኘው እጅግ ደስተኛና በረከት የበዛለት ሆኖ ሲሆን (ኢዮብ 1፡1-5)። በመጽሐፉም መጨረሻ የምናገኘው በዚሁ መልክ ነው (ኢዮብ 42፡7-17)። በመካከል ያሉት ምዕራፎች ግን ስለ ኢዮብ መከራ ይናገራሉ።  የመጽሐፈ ኢዮብ አስተዋጽኦ 1. የታሪኩ መግቢያ (ኢዮብ 1-2)  2. ኢዮብ ከሦስቱ ጓደኞቹ ጋር ያደረጋቸው ንግግሮች (ኢዮብ 3-31) ሀ. የመጀመሪያው ውይይት ዑደት (ኢዮብ 4-14) 1. የኢዮብ እንጉርጉሮ መግቢያ (ኢዮብ 3)  2. የኤልፋዝ ንግግር (ኢዮብ 4-5)  3. የኢዮብ መልስ (ኢዮብ 6-7)  4. የበልዳዶስ ንግግር (ኢዮብ 8)  5. የኢዮብ መልስ (ኢዮብ 9-10) 6. የሶፋር ንግግር (ኢዮብ 11) 7. የኢዮብ መልስ (ኢዮብ 12-14)  ለ. ሁለተኛው የውይይት ዑደት (ኢዮብ 15-21) 1. የኤልፋዝ ንግግር (ኢዮብ 15) 2. የኢዮብ መልስ (ኢዮብ 16-17)  3. የበልዳዶስ ንግግር (ኢዮብ 18)  4. የኢዮብ መልስ (ኢዮብ 19)  5. የሶፋር ንግግር (ኢዮብ 20) 6. የኢዮብ መልስ (ኢዮብ 2)  ሐ. ሦስተኛው የውይይት ዑደት (ኢዮብ 22-31) 1. የኤልፋዝ ንግግር (ኢዮብ 22)  2. የኢዮብ መልስ (ኢዮብ 23-24)  3. የበልዳዶስ ንግግር (ኢዮብ 25) 4. የኢዮብ መልስ (ኢዮብ 26-3)  3. የኤሊሁ ንግግር (ኢዮብ 32-37)  4. የእግዚአብሔር ንግግርና የኢዮብ መልስ (ኢዮብ 38-41)  5. ማጠቃለያ (ኢዮብ 42)  (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመጽሐፈ ኢዮብ መግቢያ Read More »

የጥበብ ሥነ-ጽሑፎች

አብዛኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሥነ ግጥማዊ የአጻጻፍ ስልት መጻፉን ቀደም ሲል ተመልክተናል። ይህ በተለይ በመዝሙረ ዳዊት፥ በመኃልይ መኃልየ ዘሰሎሞን፥ እንዲሁም በአንዳንድ የትንቢት መጻሕፍት ውስጥ የምናየው እውነታ ነው። የጥበብ ጽሑፎች የሥነ- ግጥምና ቅኔ ጽሑፎች ክፍል ቢሆኑም፥ «የጥበብ» ጽሑፎች ብለን ልንጠራቸው የምንችለው ልዩ ዓይነት ግጥሞች ናቸው። ከመዝሙረ ዳዊት አንዳንድ ክፍሎችና እንደዚሁም አብዛኛዎቹ የመጽሐፈ መክብብና የመጽሐፈ ምሳሌ ክፍሎች የጥበብ ጽሑፎች የሚገኙባቸው ናቸው። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በአማርኛ ቋንቋ «ጥበብ» የምንለው ቃል ትርጉም ምንድን ነው? ለ) በኅብረተሰብህ ውስጥ እንደ ጠቢብ የሚቆጠር አንድ ሰው ጥቀስ። ሐ) ጠቢብ ያደረገው ምንድን ነው? መ) ከሌሎች ሰዎች የሚለየው እንዴት ነው? ባለንበት ዘመን፥ ብዙዎቻችን ጥበብ የሚገኘው በትምህርት ቤት እንደሆነ አድርገን እናስባለን። ጥበብ የበርካታ እውነቶች ስብስብ እውቀት እንደሆነ እንቆጥራለን፤ ስለዚህ ጥበብ የሚገኘው ባልተማሩ ሳይሆን፥ በሚገባ በተማሩ ሰዎች ዘንድ እንደሆነ አድርገን እንገምታለን። አይሁድ ግን «ጥበብ» ሲሉ ይህን ማለታቸው አይደለም። የብሉይ ኪዳን ጸሐፊዎች «ጥበብ» የሚለውን ቃል በተለያዩ መንገዶች ተጠቅመውበታል፡- 1. የተለየ ሙያ ወይም ችሎታ ስላላቸው ሰዎች ለመናገር አገልግሏል። ለምሳሌ የመገናኛውን ድንኳን የሠሩት ባስልኤልና ኤልያብ የተባሉት ሁለት ሰዎች «ጠቢባን» የተባሉት ድንኳኑን በመሥራት ረገድ ልዩ ችሎታ ስለነበራቸው ነው (ዘጸአት 31፡1-11)።  2. አንዳንድ ጊዜ ይህ ቃል አገልግሎት ላይ ውሎ የምናየው ለጐበዞችና ጥሩ የአእምሮ ችሎታ ላላቸው ሰዎች ነው (ኢዮብ 38፡36)።  3. ጥበብ የሚለው ቃል ጥሩ የተፈጥሮ እውቀት ላላቸውና አንድን ጉዳይ አመዛዝኖ በማቅረብ ችሎታቸው ጠቢባን ተብለው ለተጠሩ ሰዎች አገልግሉአል (ኢዮብ 32፡7)።  4. ከሁሉ በላይ ግን፥ ጥበብ እውቀትን በትክክለኛ መንገድ የመጠቀም ችሎታ ነው (ምሳሌ 1፡5)። አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ የተሳካ ኑሮ ለመኖር የሚችለው ጠንቃቃና ሚዛናዊ የመሆን ችሉታ ሲኖረው ነው። ይኸውም ትክክለኛና ሚዛናዊ የሆኑ ነገሮችን ማድረግ ሲችል ነው (ምሳሌ 3፡1-6)። የውይይት ጥያቄ፥ መዝሙረ ዳዊት (11)፡10፤ ምሳሌ 1፡7፤ 2፡5-6፤ 19፡10፤ ያዕቆብ 1፡5፤ 3፡17 አንብብ። ሀ) የጥበብ መጀመሪያ ምንድን ነው? ለ) እውነተኛ ጥበብ የሚመጣው ከየት ነው? ሐ) የዚህ ዓይነቱ ጥበብ በሕይወትህ ለመኖሩ ማስረጃ የሚሆኑ መንገዶችን ግለጽ።  ስለዚህ የጥበብ ሥነ-ጽሑፎች የምንላቸው ለሕይወታችን ጥቅም በሚያስገኙ መንገዶች እንዴት መኖር እንዳለብን የሚያስተምሩን የብሉይ ኪዳን ሥነ-ጽሑፎች ናቸው። የተመሠረቱትም ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት በማድረግ ሲሆን፥ ያለዚህ ግንኙነት ለእግዚአብሔር ፍርድ የተጋለጥንና እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኝ መንገድ ለመኖር የማንችል ነን። የጥበብ ሥነ-ጽሑፍ ሕይወታችንን ስለሚለውጥ፥ ተግባራዊ ነው። ለሕይወታችን ያለው ጠቀሜታ ከሁሉም የላቀ ነው። እውነተኛ እውቀትን ከሕይወታችን ጋር በማዛመድ እንዴት የተሻለ ሕይወት መኖር እንዳለብን ለመማር የሚያስችለን ነው። የጥበብ ሥነ-ጽሑፍ ዓላማ የአንድን ሰው ዝንባሌ፥ ባሕርይና አኗኗር በመለወጥ፥ በልቡ ውስጥ ሊኖር የሚገባውን ፈሪሀ እግዚአብሔር እንዲያንጸባርቅ የሚያደርግ ነው። ይህም ወደ በጎነት ሕይወት ይመራል (ምሳሌ 2፡20)። ጥበብና እውቀት እንደ ሰው ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ካለው ግንኙነት ጋር በጥብቅ የተቆራኙ መሆናቸውን አይሁድ ተገንዝበው ነበር። እግዚአብሔር የጥበብ ሁሉ ምንጭ በመሆኑ ለእርሱና ለፈቃዱ ታዝዘው ለመኖር ለወሰኑ ሰዎች ሁሉ ጥበብን ለመስጠት ቃል ገብቶአል (ኢዮብ 12:13፤ ምሳሌ 2፡5-6)፤ ስለዚህ ማንኛውም ሰው ጥበብን ለማግኘት ወደ ትምህርት ቤት አልሄደም፤ ወይም ጥበበኞችን አላማከረም፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጋር በመነጋገር እንደፈቃዱ ተጓዘ። ስለዚህ ሰው በእውነት ጠቢብ ነው የሚባለው መሠረታዊ በሆነ ጉዳይ ነው። የውይይት ጥያቄ፥ ይህ ጥበብ በትምህርት ቤት ከምንማረው «ጥበብ» የሚለየው እንዴት ነው? የመጽሐፍ ቅዱስን ጥበብ ለመረዳት መሠረቱ፡- ሕይወት ሁለት ዋና ዋና መንገዶችን የያዘች መሆንዋን መገንዘብ ነው። ወደ ጽድቅ የሚያደርስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መንገድ አለ፤ ወይም ወደ ጥፋት የሚያደርስ የኃጢአት መንገድ አለ (ማቴዎስ 7፡13-14)። አንደኛው መንገድ የጠቢብ (ምሳሌ 10፡8፥14)፥ የቅንና (ምሳሌ 11፡3) የጻድቅ መንገድ ነው (ምሳሌ 10፡16)። ሌላው የሞኞች ወይም የሰነፎች (ምሳሌ 10፡1፥8፥14)፤ የኃጥአንና (ምሳሌ 10፡3) ታማኝ ያልሆኑ ሰዎች ወይ የወስላቶች መንገድ ነው (ምሳሌ 11፡3)። የጥበብ መጻሕፍትን በምንተረጕምበት ጊዜ ልናስታውሳቸው የሚገባን ሁለት ዓይነት የጥበብ ሥነ-ጽሑፎች አሉ። መጀመሪያ፥ ልንከተላቸው የሚገባን ተግባራዊ ጥበባትን የሚያስተምሩን ምሳሌዎችና አባባሎች አሉ። እነዚህ ጥሩ ልማዶችን፥ ጥሩ ሙያዎችንና መልካም ባሕርያትን የሚያስተዋውቁን ናቸው (ለምሳሌ፥ ምሳሌ 21፡23፤ 22፡3)። ሁለተኛ፥ በዚያን ዘመን ይነገሩ የነበሩ ምርጥ አባባሎችን የሚያንጸባርቁ፥ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ግን ሊከተላቸው የማያስፈልጉ ምሳሌዎች አሉ፤ ወይም እነዚህ ከቀረው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ጋር የማይስማማ ፍልስፍና የሚያንጸባርቁ ናቸው። መጽሐፈ ኢዮብና መክብብ ከያዛቸው የጥበብ አነጋገሮች መካከል ትክክል ያልሆኑና ልንከተላቸው የማያስፈልጉ ዐረፍተ ነገሮች ይገኛሉ። የኢዮብ ወዳጆች ለኢዮብ ያካፈሉት ምክር በአብዛኛው ትክክለኛ አልነበረም። በመጽሐፈ መክብብ ውስጥ የምናገኛቸው የሰሎሞን አስተሳሰቦች ላይ ላዩን በምንመለከታቸው ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት በትክክል የሚያንጸባርቁ አይደሉም። በውስጡ የሚገኘውን የጥበብ ትምህርት የምናስተውለው መጽሐፉን በተገቢው መንገድ ስንረዳ ነው። የጥበብ ሥነ-ጽሑፎችን ብዙ ጊዜ በተሳሳተ መንገድ የምንተረጉምበት አንዱ ምክንያት በውስጡ ያሉትን ልዩ ቃላት ካለመረዳታችን ነው። ቀጥለን በእነዚህ ጽሑፎች ውስጥ ያሉትን ዋና ዋና ቃላት እንመለከታለን፡- 1. ጥበብ፡- ልዩ እውቀትን ማግኘት ማለት አይደለም፤ ነገር ግን ያገኘነውን እውቀት እግዚአብሔርን ለማስከበር በሚያስችል ትክክለኛ መንገድ ለመኖር መጠቀም ማለት ነው።  2. ጠቢብ ሰው:- በመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዛት መሠረት የሚኖር ሰው ማለት ነው።  3. ሞኝ ወይም ሰነፍ፡- ያልሠለጠነና ማንም ሰው በቀላሉ ሊያሞኘው የሚችል (ምሳሌ 14፡15)፣ ሕይወቱን በብልሃት የማይመራ፥ ዓመፀኛና ያልተገራ፥ ተግሣጽን የማይቀበልና እግዚአብሔርን የማይፈራ ሰው ነው። ሞኝ ወይም ሰነፍ በአእምሮው ደካማ የሆነ ሰው ማለት ሳይሆን እግዚአብሔርን በሕይወቱ የማያከብር ሰው ማለት ነው። 4. ኃጥእ፡- ሆን ብሉ እግዚአብሔርንና ቃሉን ያልተቀበለ፥ በእግዚአብሔር ትእዛዛት ላይ ያመፀና ሌሉችም ከእውነት እንዲርቁ የሚፈልግ ሰው ነው።  5. ፌዘኛ ወይም ቀልደኛ፡- እውነትን በተጠራጣሪነት የሚጠይቅ፥ ተግሣጽንና ምክርን የሚጠላ ሰው ነው። የጥበብ ሥነ-ጽሑፎች ዓይነቶች የተለያዩ ናቸው። በመጀመሪያ፥ እንዴት መኖር እንዳለብን የሚያስረዱ «ተግባራዊ ጥበባት አሉ።» ይህ በተለይ የሚገኘው በመጽሐፈ ምሳሌ ነው። ሁለተኛው፥ የከንቱነት ጥበብ የምንለው ሲሆን፥ ትንሽ አዎንታዊ ትምህርት ኖሮት ነገር ግን የዚህን ዓለም ጥበብና ዘይቤ እንዳንከተል የሚያስጠነቅቀን ነው። ይህን የምናገኘው በመጽሐፈ መክብብ ውስጥ ነው። ሦስተኛ፣ «መከራ የሚኖረው ለምንድን ነው? መከራ ሁልጊዜ የኃጢአት ውጤት ነውን? » የሚሉትንና የመሳሰሉትን ዐበይት ጥያቄዎች የሚመረምር የፍልስፍና ጥበብ አለ። ይህም የሚገኘው በመጽሐፈ ኢዮብ ውስጥ ነው። የተለያዩ የመዝሙር ዓይነቶች እንዳሉ ሁሉ፥ የጥበብ ጽሑፎችም በዓይነታቸው የተለያዩ ናቸው። 1. ምሳሌ፡- በጥበብ ሥነ-ጽሑፍ ውስጥ ከሁሉም የላቀ አስፈላጊና የተለመደው መሣሪያ ምሳሌያዊ አነጋገር ነው። ምሳሌ፥ ሰፊ የሆነ እውነትን በአጭር አነጋገር የሚገልጽ ነው። በምሳሌ ውስጥ ያለውን እውነት ሰዎች በቀላሉ ሊያስታውሱት በሚችሉት መንገድ በአጭሩ የቀረበ የቃላት ቅንብር ነው። የሕይወትን ሰፊ ክፍል በመውሰድ ዓለም አቀፋዊ በሆነ መመሪያ አሳጥሮ ለማቅረብ ይሞክራል። ብዙውን ጊዜ ምሳሌያዊ አነጋገርን ለመረዳት ቀላል ቢሆንም፥ እውነቱ ግን በጣም ጥልቅና በርካታ የሕይወት ተዛምዶዎችን ሊያካትት የሚችል ነው። ምሳሌያዊ አነጋገር ብዙ ጊዜ ነገሮችን በማነጻጸር ውይም በማመሳሰል ይቀርባል። ለምሳሌ፡- «እንቁላል ቀስ በቀስ በእግሩ ይሄዳል» በሚለው የተለመደ የአማርኛ ምሳሌያዊ አነጋገር ውስጥ እንቁላሉ በሕይወት ውስጥ ያለውን የተለመደ መሠረታዊ እውነታ ለመግለጥ የቀረበ ነው። ይህም መሠረታዊ እውነታ ነገሮች በመሆን ሂደት ውስጥ ለማለፍ ጊዜን ይጠይቃሉ ማለት ነው። ምሳሌዎች የሰውን ሕይወትና እውነት በአጭሩ ስለሚያቀርቡ መቶ በመቶ ትክክል ሊሆኑ አይችሉም። ይልቁንም አጠቃላይ የሆኑ መግለጫዎች ወይም የሕይወት ዝንባሌዎች ናቸው። ለምሳሌ፡- በፍጥነት የሚፈጸሙ ጉዳዮች አሉ። ሁሉም ነገር በዝግታ የሚፈጸም አይደለም፤ ይህም ማለት ከላይ የተመለከትነው ምሳሌ ሙሉ በሙሉ ትክክል ሊሆን አይችልም።  የውይይት ጥያቄ ሀ) ከምታውቃቸው የኢትዮጵያ ምሳሌዎች አምስቱን ጥቀስ። ) ምሳሌነቱ ምንድን ነው? ሐ) ምሳሌው ሊገልጠው የሚፈልገው የሕይወት መሠረታዊ እውነታ ምንድን ነው? ልዩ ልዩ ዓይነት ምሳሌያዊ አነጋገሮች አሉ። አንዳንዶቹ እንደሞኝ ወይም ሰነፍ ሰው በኃጢአት እንዳንወድቅ ልንጠነቀቅባቸው ስለሚገባን ነገሮች የሚያሳስቡ ናቸው (ምሳሌ 6፡20-35)። ሌላው ዓይነት ምሳሌ ሥልጣን ያለው እውነት ሆኖ የቀረበ ነው

የጥበብ ሥነ-ጽሑፎች Read More »

የግጥም መጻሕፍት መግቢያ

የውይይት ጥያቄ፡ ሀ) በራስህ ባህል ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ የአጻጻፍ ወይም የአነጋገር ዓይነቶችን ዘርዝር። ለ) ከእነዚህ የአጻጻፍ ወይም የአነጋገር ስልቶች ውስጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ምን ያህሎቹ ናቸው? በእያንዳንዱ ባህል ውስጥ የተለያዩ የአጻጻፍ ወይም የአነጋገር ስልቶች ይገኛሉ። ለምሳሌ፥ ከጓደኞቻችን ጋር በምንነጋገርበት ጊዜ የምንጠቀምበት የተለመደ የአነጋገር ዘይቤ አለ፤ ነገር ግን ለተናገርነው ጉዳይ አትኩሮት ለመስጠት ምሳሌያዊ አነጋገሮችን የምንጠቀምበትም ጊዜ አለ። ብዙዎቻችን በልጅነታችን የተለያዩ ተረቶችን ሰምተናል። በተለይ በኢትዮጵያ ብቻ የሚነገር የ«ሰምና ወርቅ» የአነጋገር ዘይቤ አለ። ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ሰዎች፥ በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚጽፉት፥ በንግግር የሚያቀርቡት ግጥም በመባል የሚታወቅ የአጻጻፍና አነጋገር ስልት አለ። በመጨረሻ መዝሙር በመባል የሚታወቁ በሙዚቃ ተቀናብረው የሚቀርቡ የተለዩ የግጥም ዓይነቶችም አሉ። የውይይት ጥያቄ፥ እነዚህ ሁሉ የአነጋገር ዓይነቶች በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ እንዴት በጥቅም ላይ ሊውሉ እንደሚችሉ የሚያስረዱ ምሳሌዎችን ጥቀስ። ብሉይ ኪዳን በእነዚህ የአጻጻፍ ስልቶች በሙሉ ይጠቀማል። እስካሁን ድረስ ባካሄድነው የብሉይ ኪዳን ጥናታችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በርካታ የተለያዩ የአጻጻፍ ስልቶች መኖራቸውን ተመልክተናል። እግዚአብሔር በሲና ተራራ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ሕግጋት አሉ። በእስራኤል ሕዝብ ላይ የደረሰውን ታሪክ ቀጥተኛ በሆነ ቋንቋ የሚናገሩ ታሪኮችን እናገኛለን። ከዚያም በብዙ ሌሎች ቋንቋዎች ውስጥ የማይገኙ የነቢያት ጽሑፎች ብለን የምንጠራቸው፥ ለየት ባለ የአጻጻፍ ስልት የተጻፉ ጽሑፎች አሉ። ከመጽሐፈ ኢዮብ እስከ መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን የሚገኙትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የሚያካትተው ሦስተኛው ክፍል በአመዛኙ ሁለት ዓይነት የአጻጻፍ ስልቶችን ይጠቀማል። የመጀመሪያው፥ በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ የምናገኘው ዓይነት የግጥም ምንባብ ሲሆን፥ ሁለተኛው ደግሞ፥ በመጽሐፈ ምሳሌ ውስጥ የምናገኘውን ዓይነት የጥበብ ክፍል ያካተተ ነው። ምንም እንኳ ብዙውን ጊዜ የጥበብ ጽሑፍ በመባል የሚጠራው ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ባመዛኙ ግጥም፥ ቅኔና ምሳሌዎችን ያካተተ ቢሆንም፥ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ባሉት በእያንዳንዱ መጻሕፍት ውስጥ የተወሰኑ ግጥሞች፥ ቅኔዎችና ምሳሌዎች አይጠፉም። እንዲያውም የብሉይ ኪዳን አንድ ሦስተኛው ግጥም ነው። ይህ ግጥም፡- አጭር ምንባብ (ለምሳሌ ዘፍ. 4፡23-24) ወይም ሙሉ ምዕራፉ (ለምሳሌ ዘጻ.15፡1-18) ወይም (እንደ መዝሙረ ዳዊት) ሙሉ መጽሐፍ ሊሆን ይችላል። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) አብዛኛው የብሉይ ኪዳን ክፍል በግጥም አጻጻፍ ስልት የተጻፈው ለምን ይመስልሃል? ለ) ሰዎች እንደ ጌታችን የልደት በዓል ባሉት ልዩ ቀናት ግጥም ማንበብ የሚወዱት ለምንድን ነው? ሐ) ሰዎች በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ የሚገኙ ግጥሞችን የሚወዱት ለምን ይመስልሃል? እግዚአብሔር ከቃሉ አብዛኛውን ክፍል ለሰው ልጆች ያስተላለፈበት የሥነ ጽሑፍ መንገድ ግጥምና ቅኔ መሆኑን መገንዘብ የሚያስደንቅ ነገር ነው። ምናልባት ምክንያት ሊሆን የሚችለው ነገር ከተለመዱ ቀጥተኛ የአጻጻፍ ስልቶች ይልቅ የግጥምና የቅኔ የአጻጻፍ ስልቶች ልብን የሚያነቃቁ መሆናቸው ነው። በየትኛውም ባህል ውስጥ የሚገኙ የአብዛኛዎቹ ክርስቲያኖች ተወዳጅ መጽሐፍ መዝሙረ ዳዊት የሆነው በዚህ ምክንያት ነው። የመዝሙረ ዳዊት ግጥም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኝ ከማንኛውም መጽሐፍ የበለጠ ስሜቶቻችንን ይገልጻል። ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅርና አክብሮት ይገልጻል፤ ሞት ወይም የተለያዩ ችግሮች በገጠሙን ጊዜ የሚሰማንን ኃዘን ይገልጻል፤ ሰዎች በተሳሳተ መንገድ ሊጠቀሙብን በሚሞከሩ ጊዜ የሚሰማንን የቁጣ ስሜት ይገልጻል። ሆኖም ግን ችግሩ መዝሙረ ዳዊት ከግጥምና ከቅኔ መጻሕፍት የሚመደብና መተርጐምም ያለበት በዚሁ መልክ መሆኑን አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያኖች መዘንጋታቸው ነው። ስለዚህ በርካታ ክርስቲያኖች በመዝሙረ ዳዊትና በሌሉች የቅዱሳት መጻሕፍት ሥነ-ግጥማዊና ቅኔያዊ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙትን ትምህርቶች በተሳሳተ መንገድ ይተረጒሙአቸዋል። በሥነ-ግጥምና በቅኔ የሚገለጹ ነገሮች ብዙ ጊዜ ምሳሌያዊ ወይም ሥዕላዊ መሆናቸውን በመዘንጋት በቀጥታ ሊተረጕሟቸው ይሞክራሉ። ብዙ ምሁራን የግጥምና የቅኔ መጻሕፍትን በሁለት ዐበይት ክፍሎች ይከፍሏቸዋል። የመጀመሪያው ክፍል፥ በባሕርያቸው ባመዛኙ ሥነ-ግጥማዊ የሆኑት ናቸው፤ ስለዚህ እነዚህን የግጥም መጻሕፍት ይሏቸዋል። መዝሙረ ዳዊትና መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን በአብዛኛው የግጥም መጻሕፍት ናቸው። በሁለተኛው ክፍል፥ የጥበብ መጻሕፍት የሚባሉት ናቸው፤ እዚህም የተጻፉት በግጥም ሥነጽሑፍ መልክ ቢሆንም፥ ትኩረት የሚያደርጉት ግን በጥበብና ብዙውን ጊዜ ደግሞ በምሳሌያዊ አነጋገሮች ላይ ነው። መጽሐፈ ምሳሌና መክብብ ለጥበብ መጻሕፍት ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው።  የዕብራውያን ሥነ-ግጥምና ቅኔ የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) አጠር ያለ አንድ ግጥም ወይም ቅኔ ጻፍ። ለ) አንድ ደብዳቤ በመጻፍና አንድ ግጥም ወይም ቅኔ በመጻፍ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ሐ) ሰዎች ግጥምን ለመጻፍ የሚጠቀሙባቸውን የተለያዩ ሕግጋት ጥቀስ (ምሳሌ፡- በየስንኙ መጨረሻ ቤት የመምታት ጉዳይ)።  እያንዳንዱ ባህል ስለ ግጥም ይዘት የራሱ የሆነ አመለካከት አለው። በብሉይ ኪዳን የምናገኘው የዕብራውያንን ግጥም ነው። የዕብራውያን የግጥም አጻጻፍ በእኛ ባህል ውስጥ ካለው የሥነ-ግጥም አጠቃቀም የተለየ ስለሆነ፤ የዕብራውያን የግጥም ይዘትና ሥን-ግጥማቸውን ለመቅረጽ አሳቦችንና ድምፆችን እንዴት እንደሚያቀናብሩ መረዳት አስፈላጊ ነው። የዕብራውያን የሥነ- ግጥም ቅንብር ከእኛ ባህል የሥነ-ግጥም ቅንብር የተለያየ ስለሆነ በቀጥታ ይዘቱን ሳይቀይር መተርጐም አስቸጋሪ ነው። የዕብራውያንን ሥነ ግጥም ትክክለኛና ተገቢ በሆነ መንገድ ለመተርጐም፤ አይሁድ ግጥማቸውን የሚጽፉባቸውን የተለየ መንገዶችና ከእኛ ግጥም እንዴት እንደሚለይ መረዳት አስፈላጊ ነው። ሥነ-ግጥም ማለት የግጥም ጥበብ ማለት ነው። አይሁድ የተለያዩ የጽሑፍ አደረጃጀቶችን በመጠቀም አስደናቂ የሆኑ ሥነ- ግጥሞችን ይጽፉ ነበር። እነዚህ የተለያዩ የአጻጻፍ መሣሪያዎች በትርጕም ሂደት ውስጥ ስለጠፉ በአማርኛም ሆነ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ውስጥ ውበታቸውን ለማየት አለመቻላችን የሚያሳዝን ነው። ይህም ቢሆን እንኳ የዕብራውያን ግጥም በተለያዩ ሂደቶች ውስጥ አልፎ በእግዚአብሔር ፊት ስሜታችንን ይገልጻል፤ ይነካናልም። በመጀመሪያ ደረጃ የዕብራውያን ግጥም የተቀናበረው በተመሳሳይ ድምፆች ነበር። ይህ የእያንዳንዱን ስንኝ የመጨረሻ ቃል አንዱ ከሌላው ጋር በድምፅ እንዲስማማ ከሚያደርገው ከእኛ ግጥም ጋር ተመሳሳይ ነው። በሁለተኛ ደረጃ፥ አይሁድ በግጥሞቻቸው ውስጥ አሳቦች አንድ ዓይነት ሂደት እንዲኖራቸው አድርገው ያቀናብሯቸዋል። ይህ በጽሑፉ ውስጥ «ፓራላሊዝም» ተነጻጻሪነት በመባል ይታወቃል። ለምሳሌ፦ መዝሙር (103)፡10 በዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደተጻፈው በቀጥታ ብንተረጕመው የሚነበበው እንደሚከተለው ነው፡- «እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም፤ እንደ በደላችን አልከፈለንም።»  የዚህ መዝሙር ጸሐፊ አንድ ዓይነት ድምፅ ያላቸውን ቃላት ማቀናበር ብቻ ሳይሆን፥ የያዙትን አሳብ በማያያዝ እንዴት እንዳቀናጃቸው ልብ በል። አይሁድ ግጥምን በሚጽፉበት ጊዜ አሳባቸውን የሚያቀርቡበት አራት መንገዶች አሉ፡- የመጀመሪያ ደረጃ፥ እጅግ የተለመደው መንገድ አንድን አሳብ በጣም ተቀራራቢ በሆኑ ቃላት መድገም ነው። ይህ «ሲኖኒመስ ፓራለሊዝም» (ተመሳሳይ የሆነ ተነጻጻሪነት) ሊባል ይችላል። ይህን ቅንብር በመዝሙር (103)፡10 እናገኛለን። በዚህ ስፍራ የግጥሙ ጸሐፊ ለአንድ አሳብ ሁለት የተለያዩ፥ ነገር ግን በእጅጉ የተያያዙ ቃላትን ይጠቀማል፤ እነዚህም ኃጢአትና በደል የሚሉ ናቸው። መዝሙረ ዳዊትን በምናነብበት ጊዜ ይህን ነገር በአትኩሮት መመልከት በጣም አስፈላጊ ነው። ጸሐፊው ለማስተላለፍ የፈለገው መልእክት አንድ ሆኖ ሳለ ብዙ ሰዎች ለእነዚህ ቃላት የተለያዩ ትርጕሞችን ይፈልጋሉ። ለምሳሌ፥ ጸሐፊው መዝሙር (103):3 የዚህ ዓይነቱን የግጥም ስልት ይጠቀማል፤ እዚህ ላይ «ኃጢአት» እና «ደዌ» የሚሉት ቃላትም አንድን አሳብ የሚገልጹ ናቸው።  በሁለተኛ ደረጃ፥ እጅግ የተለመደው መንገድ ሁለተኛው ስንኝ ከመጀመሪያው ስንኝ ተቃራኒ ወይም ተነጻጻሪ ሆኖ መቅረቡ ነው፡፡ (ይህ አንቲቴቲክ ፓራለሊዝም) ተቃራኒ የሆነ ተነጻጻሪነት ይባላል። ለዚህ ዓይነቱ ሥነ-ግጥም በጣም ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው መዝሙረ ዳዊት 1፡6 ነው። በዚህ ስፍራ ጸሐፊው በመጀመሪያው ስንኝ የጻድቃንን መንገድ፣ በሁለተኛው ስንኝ ደግሞ የክፉዎችን መንገድ ያነጻጽራል።  በሦስተኛ ደረጃ፥ አንዳንድ ጊዜ ጸሐፊዎች በመጀመሪያው ስንኝ ምሳሌያዊ አነጋገር ወይም ተምሳሌት ይጠቀሙና በሁለተኛው ስንኝ ደግሞ ያንኑ አሳብ በቀጥተኛ ቋንቋ ይገልጹታል። ይህንንም «ሲምቦሊክ ፓራለሊዝም» ተምሳሌታዊ ተነጻጻሪነት ልንለው እንችላለን። ለምሳሌ መዝሙረ ዳዊት (42)፡1 ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ ስለ መናፈቁ በመጀመሪያው ስንኝ ይናገርና፤ በሁለተኛው ስንኝ ደግሞ ጸሐፊው ነፍሱ ወደ እግዚአብሔር እንደምትናፍቅ ይናገራል።  በአራተኛው ደረጃ፥ አንዳንድ ጊዜ ጸሐፊው የጻፈው እያንዳንዱ ስንኝ በመጀመሪያው መስመር ላይ ባለው አሳብ ላይ ጥቂት ነገርን ይጨምራል። (ኢንቴቲክ ፓራለሊዝም) ተጨማሪ የሆነ ተነጻጻሪነት ይባላል። በመዝሙረ ዳዊት (29)፡1-2 ለእግዚአብሔር ልንሰጠው ስለሚገባ ነገር በየስንኙ ጥቂት አሳቦችን ይጨምራል። የውይይት ጥያቄ፥ የሚከተሉትን ግጥሞች ተመልከትና ጸሐፊው የተጠቀመባቸውን የቅንብር ዓይነቶች ጥቀስ፡- ኢሳይያስ 44፡22፤ ሆሴዕ 7፡14፤ ምሳሌ 15፡1፤ አብድዩ 21፤ ምሳሌ 4፡23፤ መዝሙረ ዳዊት (49)፡1፤ ኤርምያስ 17፡11። አይሁድ

የግጥም መጻሕፍት መግቢያ Read More »

የታሪክ መጻሕፍት

መጽሐፈ ኢያሱ፡- መጽሐፈ ኢየሱ በጠላት ላይ ስለሚገኝ ድል የሚናገር መጽሐፍ ነው። እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን የከነዓንን ምድር ርስታቸው አድርጎ ሊሰጣቸው ቃል ኪዳን ገብቶላቸው ነበር፤ ነገር ግን በከነዓን ድል መነሣት የነበረባቸው በርካታ ጠላቶች ነበሩ። መጽሐፈ ኢያሱ ሕዝቡ ጠላቶቻቸውን እንዲያሸንፉና የተስፋይቱን ምድር እንዲወርሱ እግዚአብሔር እንዴት እንደረዳቸው ይገልጻል። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዛሬ ክርስቲያን ሊያሸንፋቸው ወይም ድል ሊያደርጋቸው የሚገባው ጠላቶች እነማን ናቸው? (ኤፌሶን 6፡12 ተመልከት)። ለ) እነዚህን ጠላቶች ልናሸንፍ የምንችልባቸውን መንገዶች ዘርዝር። መጽሐፈ መሳፍንት፡- መጽሐፈ መሳፍንት የእግዚአብሔርን ሕዝብ አለመታዘዝ የሚያሳይ አሳዛኝ ታሪክ ነው። ይህ መጽሐፍ «ሰውም ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር» (መሳፍንት 17፡6) በሚለው ቃል ሊጠቃለል ይችላል። እግዚአብሔር መንገዳቸውን የለቀቁ ልጆቹን በጠላቶቻቸው እንዲሸነፉና በባርነት ቀንበር እንዲወድቁ በማድረግ፥ የሥነ-ሥርዓት ቅጣትን እንዴት እንደቀጣቸው የሚያሳይ ታሪክ ነው፤ ነገር ግን መሳፍንትን በመጠቀም እግዚአብሔር ከጠላቶቻቸው የባርነት ቀንበር እንዴት ነፃ እንዳወጣቸው የሚናገርም ታሪክ ነው። የውይይት ጥያቄ፥ አንታዘዝም በምንልባቸው ጊዜያት እግዚአብሔር አንዳንዴ እንድንሸነፍ የሚፈቅደው እንዴት ነው? መጽሐፈ ሩት፡- በዘመነ መሳፍንት የተፈጸመው የሩት ታሪክ ከፍተኛ የክፋት ሥራ በሞላበት ሁኔታ ውስጥ ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆነው የሚኖሩ ሰዎች እንደሚገኙ የሚያሳይ ጥሩ ምሳሌ ነው። ሩት የተባለችው ከአሕዛብ ወገን የሆነች ሴት እግዚአብሔርን በመከተልዋ የታላቁ የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት አያት የመሆን ሽልማት እንዳገኘች የሚናገር ታሪክ ነው። የውይይት ጥያቄ፥ አብዛኛው ሕዝብ እግዚአብሔርን መከተል በተወበት ጊዜ እንኳ ለእግዚአብሔር ታማኞች መሆን ያለብን እንዴት ነው? 1ኛ ሳሙኤል (መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ)፡- መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ ከዘመነ መሳፍንት ጀምሮ እስራኤል በአንድ ንጉሥ ሥር እስከቆየችበት፥ እስከተባበረው የእስራኤል መንግሥት ድረስ ያለውን የሽግግር ወቅት ታሪክ የሚሸፍን ነው። የመጨረሻው መስፍን የነበረው የሳሙኤልና የመጀመሪያው ንጉሥ የነበረው የሳኦልን ታሪክ የሚናገር ነው። የመጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ አብዛኛው ክፍል ሳኦልን በእስራኤል ሕዝብ ላይ ይነግሥ ዘንድ ከተመረጠውና የመልካም ንጉሥ የላቀ ምሳሌ ከሆነው ከዳዊት ጋር ያወዳድረዋል። ሌሎች የእስራኤል ነገሥታት በሙሉ የሚመዘኑት ዳዊትን በመምሰላቸው ወይም ባለመምሰላቸው ነበር። መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ የሚጠናቀቀው በሳኦል ሞት ነው። 2ኛ ሳሙኤል (መጽሐፈ ሳሙኤል ካልዕ)፡- መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊና ካልዕ መጀመሪያ በታላቁ ንጉሥ በዳዊት ላይ የሚያተኩር አንድ መጽሐፍ ነበር። መጽሐፈ ሳሙኤል ካልዕ ስለ ዳዊት መንገሥ የሚናገር መጽሐፍ ነው። ዳዊት በአሕዛብ ሁሉ ላይ ስላገኛቸው ታላላቅ ድሎችና የእስራኤልን ድንበር ከግብፅ እስከ ኤፍራጥስ ድረስ እንዳሰፋ ይናገራል። የዳዊት ታሪክ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ዘላለማዊ ቃል ኪዳን በመግባቱ ሲሆን፥ በዚህ ቃል ኪዳን በእስራኤል ላይ ንጉሥ የመሆንን ሥልጣን ለዘሩ ሰጥቶአል። የመጽሐፈ ሳሙኤል ካልዕ ሁለተኛ ክፍል ግን ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር የፈጸመው ኃጢአት ያስከተላቸው ውጤቶች የተዘረዘሩበት ነው። ይህ ኃጢአት የቤርሳቤህ ባል የኦርዮንን ሞት አመጣ፤ በድጋሚም ከዳዊትና ከቤርሳቤህ የተወለደውን የመጀመሪያ ልጅ ቀሰፈ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በዳዊት ቤት ላይ ችግር በዛ። የዳዊት ሴት ልጅ በግድ ተደፈረች፤ አቤሴሉም ወንድሙን ገደለ፤ ቀጥሉም በአባቱ በዳዊት ላይ ዓመፀ፤ ከዚያም አቤሴሎም ተገደለ። ዳዊት እንደ እግዚአብሔር ልብ የሆነ ሰው ነበር (የሐዋርያት ሥራ 13፡22)። ይህ ማለት እግዚአብሔርን በከፍተኛ ደረጃ የሚወድና በሙሉ ልቡ እርሱን ለመከተል የጣረ ሰው ነበር ማለት ነው እንጂ ዳዊት ፍጹም ነበር ማለት አይደለም። የውይይት ጥያቄ፥ እንደ እግዚአብሔር ልብ መሆንን በሚመለከት ከዳዊት በሕይወት ውስጥ ከምንማራቸው ትምህርቶች አንዳንዶቹን ዘርዝር።  1ኛና 2ኛ ነገሥት (መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊና ካልዕ)፡- እነዚህ ሁለት መጻሕፍት የእስራኤል ነገሥታትን ታሪክ ይናገራሉ። ለእግዚአብሔር ትልቅ ቤተ መቅደስ ስለሠራው ስለ ሰሎሞን ታሪክ ይናገራሉ፤ ነገር ግን የሚያሳዝነው ሰሎሞን ሐሰተኞች አማልክትን ማምለክ ጀመረ። ከሰሎሞን ሞት በኋላ እግዚአብሔር በመፍረዱ መንግሥቱ በሰሜን- እስራኤል፥ በደቡብ-ይሁዳ ተብሎ ለሁለት ተከፈለ፡ እነዚህ መጻሕፍት በሁለቱም መንግሥታት የነበሩትን ነገሥታት ታሪክ እግዚአብሔርን ይወድ ከነበረው ንጉሥ ከዳዊት ጋር በተናጠል በማወዳደር ያጠቃልላሉ። እነዚህ መጻሕፍት የእግዚአብሔር ሕዝብ የእግዚአብሔርን ሕግ ባለመቀበላቸውና ባለመታዘዛቸው ምክንያት የሰሜኑ መንግሥት በአሦር፥ የደቡቡ መንግሥት ደግሞ በባቢሎን ስለ መጥፋታቸው ይናገራሉ። የውይይት ጥያቄ፥ ይህ እግዚአብሔርን ስለ መተውና እርሱን ባለመታዘዝ ስለ መኖር የሚያስጠነቅቀን እንዴት ነው? 1ኛና 2ኛ ዜና መዋዕል (መጽሐፍ ዜና መዋዕል ቀዳማዊና ካልዕ)፡- እንደ ሳሙኤልና ነገሥት መጻሕፍት፥ መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊና ካልዕም አንድ መጽሐፍ ነበሩ። እነዚህ መጻሕፍት የሳሙኤል ካልዕንና የነገሥት ቀዳማዊና ካልዕ መጽሐፍትን ታሪክ ይደግማሉ። የዳዊትን፥ የሰሎሞንና የይሁዳ ነገሥታትን ታሪክ በድጋሚ የሚናገሩ ናቸው። ይሁን እንጂ የዜና መዋዕል መጽሐፍ ታሪኩን የሚያቀርበው ከሃይማኖታዊ አመለካከት አንጻር ነው። በነገሥታቱ መንፈሳዊ ሕይወት ላይ ያተኩራል። በመልካም ምሳሌነቱ ዋና ተጠቃሽ ለሆነው ለንጉሥ ዳዊት በእስራኤል ስለሰጠው መንፈሳዊ አመራር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶአል። በተጨማሪ የሰሎሞን ቤተ መቅደሱን የመገንባቱ ታሪክ ተጽፎአል። ከነገሥታት መጻሕፍት በተቃራኒ የይሁዳ ነገሥታትን ታሪክ እንጂ የእስራኤልን ነገሥታት ታሪክ አይናገርም። ዕዝራ፡- የዕዝራ መጽሐፍ የሚናገረው ከባቢሎን ምርኮ ስለተመለሱ አይሁዶች ታሪክ ነው። አይሁዶች ቤተ መቅደሱን ለመሥራት ስለወሰዱት እርምጃ ፥ ስለገጠማቸው ተቃውሞና ስለ ቤተ መቅደሱ ሥራ መጠናቀቅ ይናገራል። በተጨማሪ በዕዝራ መሪነት ስለተካሄደው መንፈሳዊ መነቃቃት ይናገራል። መጽሐፈ ነህምያ፡- ይህ መጽሐፍ አስቀድሞ ከመጽሐፈ ዕዝራ ጋር በአንድነት ተጠቃልሉ ይገኝ የነበረ ነው። አይሁድ ከምርኮ ከተመለሱ በኋላ ስለነበረው ጊዜ ታሪክ መናገሩን ይቀጥላል። የመጽሐፈ ነህምያ ትኩረት በኢየሩሳሌም ቅጥር እንደገና መሠራትና በነህምያ መሪነት በኢየሩሳሌም በተካሄደው መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ላይ ነው። የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በአይሁድ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ፈሪሀ-እግዚአብሔር የተሞላበት አመራር የተጫወተው ሚና ምንድን ነው? ለ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ መንፈሳዊ መነቃቃትን ለማበረታታት የቤተ ክርስቲያንህ መሪዎች ምን ማድረግ አለባቸው? መጽሐፈ አስቴር፡- በብሉይ ኪዳን ውስጥ ከሚገኙ የታሪክ መጻሕፍት የመጨረሻው መጽሐፈ አስቴር ነው። በአቀማመጥ ቅደም ተከተል የመጨረሻው የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ቢሆንም፥ በብሉይ ኪዳን በእስራኤል ታሪክ ውስጥ የተፈጸመውን የመጨረሻ ክሥተት የሚናገር አይደለም። ይልቁንም የመጽሐፈ አስቴር ታሪክ የተፈጸመው በመጽሐፈ ዕዝራ ታሪክ መካከል ነበር። መጽሐፈ አስቴር አይሁዳውያን በፋርስ ሰዎች ሙሉ በሙሉ ከመደምሰሳቸው በፊት፥ እግዚአብሔር ፡ በአንዲት አይሁዳዊት ሴት በመጠቀም እንዴት እንዳዳናቸው ይናገራል። እግዚአብሔር ሕዝቡን ለመጠበቅ ኢምንት በሚመስሉ ድርጊቶች ውስጥ እንዴት እንደሚሠራ የሚያሳይ ታሪክ ነው። የውይይት ጥያቄ፥ ተራ በሚመስል ድርጊት ውስጥ የእግዚአብሔር እጅ ሕይወትህን ለመጠበቅ ሲሠራ ያየኸው እንዴት ነው? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የታሪክ መጻሕፍት Read More »

ፔንታቱክ፣ የብሉይ ኪዳን የክፍል አንድ ጥናት ክለሳ

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የተመደቡባቸውን አራት የተለያዩ ክፍሎች ጥቀስ። ለ) በእነዚህ አራት የተለያዩ ክፍሎች የሚመደቡትን መጻሕፍት ዘርዝር። ሠላሳ ዘጠኙ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የተጻፉት ከአንድ ሺህ ዓመታት በላይ በሆነ ጊዜ ውስጥ ነው። የመጀመሪያው መጽሐፍ ኦሪት ዘፍጥረት በሙሴ በ1400 ዓ.ዓ. ተጻፈ። የመጨረሻው መጽሐፍ ትንቢተ ሚልክያስ ደግሞ በ400 ዓ.ዓ. አካባቢ ተጻፈ። ብሉይ ኪዳን በአራት ዋና ዋና ክፍሎች ሊከፈል ይችላል፡- ፔንታቱክ ወይም የሙሴ መጻሕፍት፡- ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ኦሪት ዘዳግም ያሉት የመጀመሪያ አምስት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የተጻፉት በሙሴ ነው ተብሎ ይታመናል። አይሁድ እነዚህን አምስት መጻሕፍት እንደ አንድ ክፍል ያዩዋቸዋል። እነዚህ መጻሕፍት ለቀሪው የብሉይ ኪዳን ክፍል መሠረት ስለሚጥሉ እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ የብሉይ ኪዳን መጻሕት መካከል ነበሩ፡ የታሪክ መጻሕፍት፡- የሚቀጥሉት አሥራ ሁለቱ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ከኢያሱ ዘመን ጀምሮ የደቡቡ የይሁዳ መንግሥት ከምርኮ በመመለስ ቤተ መቅደሱንና የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች እስከሠራበት ጊዜ ያለውን የእስራኤልን ታሪክ የሚናገሩ ናቸው (ኢያሱ – ዕዝራና ነህምያ)። በመጀመሪያው የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ጥናታችን ውስጥ እነዚህን ሁለት ክፍሉች ተመልክተናል።  የግጥምና የቅኔ ወይም የጥበብ መጻሕፍት፡- ሦስተኛው የብሉይ ኪዳን ክፍል ሁለት ዐበይት መጠሪያዎች አሉት። አንዳንዶች የግጥምና የቅኔ መጻሕፍት ብለው ሲጠሩት፥ ሌሎች ደግሞ የጥበብ መጻሕፍት በማለት ይጠሩታል። ይህ ክፍል ከኢዮብ እስከ መኃልየ መኃልይ ዘሰለሞን ያሉትን አምስት መጻሕፍት ይይዛል።  ነቢያት፡- የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የመጨረሻ ዐቢይ ክፍል አሥራ ሰባት የነቢያት መጻሕፍትን ይዟል። እነዚህ አሥራ ሰባት የነቢያት መጻሕፍት በተጨማሪ በሁለት ክፍሎች ይከፈላሉ። የመጀመሪያው ክፍል አምስት ትልልቅ የነቢያት መጻሕፍትን የያዘ ሲሆን እነዚህ መጻሕፍት ከኢሳይያስ እስከ ዳንኤል ያሉት ናቸው። ትልልቅ የነቢያት መጻሕፍት የተባሉበት ምክንያት ረጃጅም ስለሆኑና መልእክታቸው ከሌሉች የነቢያት መጻሕፍት ይልቅ ጥልቀት ያለው ስለሆነ ነው። ሁለተኛው የነቢያት መጻሕፍት ክፍል ደግሞ ታናናሽ የነቢያት መጻሕፍት የሚባል ሲሆን፥ ከሆሴዕ እስከ ሚልክያስ ያሉ አሥራ ሁለት መጻሕፍትን የያዘ ነው።  የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የፔንታቱክን አምስት መጻሕፍት ዘርዝር። ለ) የእነዚህ መጻሕፍት ጸሐፊ ማን ነበር? ሐ) በእያንዳንዱ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው ዋና ታሪክ ወይም ትምህርት ምንድን ነው? ፔንታቱክ  ፔንታቱክ ወይም የመጀመሪያዎቹ አምስት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የተጻፉት በሙሴ እንደሆነ ይታመናል። እነዚህ መጻሕፍት የእስራኤልን ሕዝብ ታሪክ ከመጀመሪያው ከአብርሃም አንሥቶ፥ በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ፍጻሜ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት እስከተዘጋጁበት ጊዜ ድረስ ያለውን የሚያጠቃልሉ ናቸው። ኦሪት ዘፍጥረት፡- ኦሪት ዘፍጥረት ስለ ነገሮች ጅማሬ የሚናገር መጽሐፍ ነው። ኦሪት ዘፍጥረት የአብዛኛዎቹን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ትምህርቶች የሚያስተዋውቀን መጽሐፍ በመሆኑ፥ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረት የሚጥል መጽሐፍ ነው። ዓለም እንዴት በእግዚአብሔር እንደተፈጠረ፥ ኃጢአት ወደ ዓለም እንዴት እንደገባ፥ የተለያዩ ነገዶች የተገኙት እንዴት እንደሆነ ይገልጥልናል። ከሁሉም በላይ የእግዚአብሔር ምርጥ የሆነው የእስራኤል ሕዝብ ጅማሬ እንዴት እንደነበር ይገልጻል። የእስራኤል ሕዝብ አባትና የክርስቲያኖች መንፈሳዊ አባት ስለሆነው ስለ አብርሃም ይናገራል። እንዲሁም ስለ ሌሉቹ የእስራኤል ሕዝብ አባቶች ማለትም ስለ ይስሐቅና ያዕቆብ ይነግረናል። ያዕቆብ የአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች አባት ነው። የውይይት ጥያቄ፥ በኦሪት ዘፍጥረት ውስጥ ከሚገኙ ዐበይት መንፈሳዊ ትምህርቶች አንዳንዶቹን ጥቀስ። ኦሪት ዘጸአት፡- የኦሪት ዘጸአት መጽሐፍ የኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ ሲናገር የቆየውን የእስራኤልን ሕዝብ ታሪክ ከ400 ዓመታት ልዩነት በኋላ በመቀጠል ይተርካል። በግብፅ ስለነበረባቸው የባርነት ቀንበር፥ እግዚአብሔር ከባርነት እንዴት ነፃ እንዳወጣቸውና በሲና ተራራ ከእነርሱ ጋር በመገናኘት ቃል ኪዳንን እንዳደረገ ይናገራል። የኦሪት ዘጸአት ታሪክ ለእስራኤላውያን እጅግ ጠቃሚ ነበር። ስለሆነም የግጥምና የቅኔ እንዲሁም የነቢያት መጻሕፍት ጸሐፊዎች በተደጋጋሚ ከኦሪት ዘጸአት ይጠቅሱ ነበር። በመጀመሪያ ደረጃ፥ እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት በእግዚአብሔር የመዋጀታቸው ታሪክ እግዚአብሔር እንዴት ሕዝቡን ያለማቋረጥ ከመከራቸው እንደሚያድናቸው ለአይሁድ የሚያሳይ ምሳሌ ነበር። በሁለተኛ ደረጃ፥ እግዚአብሔር ሕዝቡን ነፃ ለማውጣት አሥር ተአምራትን የተጠቀመበት መንገድ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ አስደናቂ ተአምራትን በማድረግ ከጎናቸው እንደሚቆም ዋስትና ነበር። በሦስተኛ ደረጃ፥ እግዚአብሔር ታላቅነቱን ያሳየበትና ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን የጀመረበት የሲና ተራራ ገጠመኝ፥ እስራኤላውያንን የእግዚአብሔር ልዩ ሕዝብ እንደሆኑ በማሳየት አበረታትቶቸዋል። የውይይት ጥያቄ፥ ከላይ የተመለከትናቸው ሦስቱ እውነቶች በአዲስ ኪዳን ውስጥ ለክርስቲያኖች የሚታዩት እንዴት ነው? ኦሪት ዘሌዋውያን፡- ኦሪት ዘሌዋውያን ስለ አምልኮና ስለተቀደሰ አኗኗር ሕግጋት የሚናገር ነው። የኦሪት ዘሌዋውያን አብዛኛው ክፍል የሕግጋትን ዝርዝር የያዘ ነው። እስራኤላውያን እግዚአብሔርን ለማምለክ ማቅረብ ስለነበረባቸው የተለያዩ መሥዋዕቶች ይገልጻል። የአምልኮውን ሥርዓት ለመምራት ስለተመረጡት ካህናትና ሌዋውያን ይገልጻል። በመጨረሻም የእግዚአብሔር ሕዝብ በዙሪያው ከሚኖሩ ሕዝብ የሚለይባቸውን በርካታ የተለያዩ ሕግጋት ይሰጣል። እነዚህ ሕግጋት የእግዚአብሔርን ቅድስናና ሕዝቡም ቅዱሳን ይሆኑ ዘንድ እንደሚፈልግ ያሳያሉ። የውይይት ጥያቄ፥ 1ኛ ጴጥሮስ 1፡15-16 ኣንብብ። ሀ) በዚህ ስፍራ ከኦሪት ዘሌዋውያን ትምህርት ጋር ተመሳሳይ ሆኖ የተሰጠው ትእዛዝ ምንድን ነው? ለ) በዚህ ዘመን ክርስቲያኖች ቅዱሳን እንደሆኑ የሚያሳዩባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ኦሪት ዘኁልቁ፡- ኦሪት ዘኁልቁ እስራኤላውያን ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ መንከራተታቸውን ይገልጻል። የእስራኤልን ሕዝብ ዓመፀኛነት በሚያመለክቱ አሳዛኝ ታሪኮች የተሞላ ነው። እግዚአብሔር የሚቀጥለው የእስራኤል ትውልድ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዲገባ ከመፍቀዱ በፊት፥ የመጀመሪያው ትውልድ በሙሉ በምድረ-በዳ እንዳለቀ የሚናገር ታሪክ ነው።  የውይይት ጥያቄ፥ የክርስትና ሕይወትህ ብዙ ጊዜ የኦሪት ዘኁልቁን ታሪክ የሚመስለው እንዴት ነው? ኦሪት ዘዳግም፡- ኦሪት ዘዳግም በሲና ተራራ ለአይሁዳውያን የተሰጣቸው ሕግ በክለሳ መልክ የቀረበበት ነው። ሙሴ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ለተዘጋጀው ለአዲሱ ትውልድ ሕጉን ደግሞ ተናገረ። ሕዝቡ የእግዚአብሔርን ሕግ ካልታዘዙና እግዚአብሔርን ካላወቁት፥ እግዚአብሔር እንደሚቀጣቸውና የገባላቸውን የተስፋ ቃል እንደሚያጡ ሙሴ ያውቅ ስለነበር የእግዚአብሔርን ሕግ ማወቃቸውን ለማረጋገጥ ፈለገ። የውይይት ጥያቄ፥ ክርስቲያኖችም እግዚአብሔርን ካልታዘዙ በረከትን ሊያጡ የሚችሉት እንዴት ነው? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ፔንታቱክ፣ የብሉይ ኪዳን የክፍል አንድ ጥናት ክለሳ Read More »