የመዝሙረ ዳዊት መግቢያ

ከቤተ ክርስቲያን የጥንት ጽሑፎች መካከል አንዱ የሆነው «ዌስትሚኒስተር ሾርተር ካታኪዝም» የተሰኘው አጭር የክርስትና ትምሕርት መጽሐፍ “የሰው ልጅ ዋና ፍጻሜ (ዓላማ) ምንድን ነው?” በሚል ጥያቄ ይጀምራል። 

የውይይት ጥያቄ፥ ይህን ጥያቄ እንዴት ትመልሰዋለህ? 

ይህንን ጥያቄ በተለያየ መንገድ ለመመለስ ብንችልም፥ የክርስትና ትምህርት መጽሐፍ (ካታኪዝም) ጸሐፊዎች ግን በዚህ መልኩ መልሰውታል፡- «የሰው ልጅ ዋና ዓላማ እግዚአብሔርን ማክበርና በእርሱ ደስ ተሰኝቶ መኖር ነው።» እግዚአብሔርን ከምናከብርባቸው ዐበይት መንገዶች አንዱ እርሱን ማምለክ ነው። እግዚአብሔር፥ እርሱን በሚያከብር መንገድ እናመልከው ዘንድ ካዘጋጀልን እጅግ ጠቃሚ 

መሣሪያዎች አንዱ መዝሙረ ዳዊት ነው። መዝሙረ ዳዊት በችግር ላይ በምንሆንበት ጊዜ እንዴት ወደ እግዚአብሔር መጸለይ እንዳለብን ያስተምረናል። እግዚአብሔርን እንዴት እንደምናመልክም ያስተምረናል። የመዝሙረ ዳዊትን መጽሐፍ ለኅብረት አምልኮአችንም ሆነ በግል የጸሎት ጊዜያችን መጠቀም አለብን። 

መዝሙረ ዳዊት እጅግ ተወዳጅና ተነባቢ ከሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አንዱ ነው። ከየትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በላይ 

መዝሙረ ዳዊት የልባችንን ስሜቶች በግልጽ ያንጸባርቃል። በመዝሙረ ጻዊት ውስጥ ፍርሃት፥ ጥላቻ፥ ፍቅር፥ አምልኮ፥ ምስጋና ደስታ ወዘተ የመሳሰሉ ሰው የሚያዘወትራቸው ስሜቶች ሁሉ ተገልጸዋል፤ ስለዚህ ሰው የየትኛውም ነገድ አባል ይሁን እነዚህ መዝሙሮች ስሜቱንና አስተሳሰቡን ሊገልጹለት ይችላሉ። 

የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) ለአንተ እጅግ ተወዳጅ የሆነው የመዝሙረ ዳዊት ክፍል የቱ ነው? ለ) ይህን ከፍል የምትወደው ለምንድን ነው? 

ሐ) በዚያ መዝሙር ውስጥ ከሁሉም በላቀ ሁኔታ የተገለጸው ስሜት የትኛው ነው? 

መዝሙረ ዳዊት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካለ ከማንኛውም መጽሐፍ የተለየ ነው። እስራኤላውያን እግዚአብሔርን በሚያመልኩበት ጊዜ ወደሚዘምሩት መዝሙራት የተለወጡ በርካታ ግጥሞችና ቅኔዎች ያሉበት መጽሐፍ ነው። ብዙ የተለያዩ ጸሐፊዎች ያዘጋጁት መዝሙረ ዳዊት አሁን ያለበትን መልክ ለመያዝ አንድ ሺህ ዓመታት ወስዶበታል። እያንዳንዱ የመዝሙረ ዳዊት ክፍል ራሱን የቻለ በመሆኑ፥ መጽሐፉን አጣምሮ የሚይዝ አንድ መሪ አሳብ ወይም ዓላማ የለውም። ይልቁንም የተለያዩ መዝሙሮች ያሉበት አንድ ትልቅ የመዝሙር መጽሐፍ አድርገን ልንቆጥረው ይገባናል። 

የመዝሙረ ዳዊት ርእስ 

የውይይት ጥያቄ፥ ይህ መጽሐፍ በአማርኛ መዝሙረ ዳዊት ለምን ተባለ? 

ብዙውን ጊዜ ስለ መዝሙረ ዳዊት ጸሐፊ ስናስብ ወደ አእምሮአችን የሚመጣው ዳዊት ነው። አብዛኛው የመዝሙረ ዳዊት ክፍል በዳዊት እንደተጻፈ የተረጋገጠ ቢሆንም፥ በሌሎች ጸሐፊዎች የተጻፉ በርካታ መዝሙራትም አሉ፤ ስለዚህ ይህንን መጽሐፍ «መዝሙረ ዳዊት» ብለን መሠየም ትክክል አይደለም። «መዝሙራት» ወይም አይሁድ እንደሠየሙት «የምስጋና መዝሙራት» ሊባል ይገባል። ብዙዎቹ መዝሙራት የተጻፉት እግዚአብሔርን ለማመስገን እንደሆነ ይህ ርእስ ይገልጻል። 

የመዝሙረ ዳዊት ጸሐፊ 

ስለ መዝሙረ ዳዊት ጸሐፊ በምንናገርበት ጊዜ፥ መዝሙረ ዳዊት በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ከሚገኙ ከሌሎች መጻሕፍት ሁሉ የተለየ መሆኑን እንመለከታለን። የአንድ ጸሐፊ የሥራ ውጤት ከመሆን ይልቅ በመቶ ዓመታት ልዩነት የኖሩ የብዙ ጸሐፊዎች የሥራ ውጤት ነው። ስለ መዝሙረ ዳዊት ዝግጅት በምንነጋገርበት ጊዜ ሁለት ጥያቄዎችን መጠየቅ ያስፈልገናል፡- በመጀመሪያ፥ በመጽሐፉ ውስጥ ያሉትን መዝሙራት በተናጠል የጻፋቸው ማን ነው? የሚል ሲሆን፤ ሁለተኛው፥ ደግሞ መዝሙራቱን በሙሉ ሰብስቦ በአንድ መጽሐፍ የጠረዛቸው ማን ነው? የሚል ይሆናል። መዝሙረ ዳዊትን አቀነባብሮ ያዘጋጀው ማን ነው? 

በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ ከምናገኛቸው 150 መዝሙራት መካከል 100ዎቹ መዝሙራት በማን እንደተጻፉ ይናገራሉ። ይህ ማለት የ50 መዝሙራት ጸሐፊ ማን እንደነበረ አናውቅም ማለት ነው፡፡ ከ 150 መዝሙራት መካከል 73 መዝሙራት የተጻፉት በዳዊት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ከሌሉቹ ጸሐፊዎች ሁሉ ይልቅ ብዙ መዝሙራትን የጻፈው ዳዊት ነው ማለት ነው። ነገር ግን ሙሴ (መዝሙር 90)፥ ሰሎሞን (መዝሙር 72፤127)፣ አሳፍ (መዝሙር 50)፥ ኤማን (መዝሙር 88)፣ ኤታን (መዝሙር 89) እንዲሁም የቆሬ ልጆች (መዝሙር 42፣ 44-49) የመዝሙር ጸሐፊዎች ነበሩ። 

እርግጠኞች ለመሆን ባንችልም እንኳ መዝሙረ ዳዊት አሁን ባለበት መልኩ ተሰብስቦ የተደራጀው በ400 ዓ.ዓ. ይመስላል። የመዝሙረ ዳዊት የመጀመሪያ ዋና ክፍል የተሰበሰበው በዳዊት ዘመን ሳይሆን አይቀርም። ዳዊት የመዝሙራት ዋና ጸሐፊ ነው (1ኛ ዜና 15-16)። ከዚህ የላቀው የዳዊት አስተዋጽኦ፥ መዝሙራት በአይሁድ የአምልኮ ሥርዓት እንዲለመዱ ማስጀመሩ ነበር (1ኛ ዜና 6፡31)። ከዳዊት ጊዜ ጀምሮ አይሁድ ከምርኮ እስከተመለሱበት እስከ 539 ዓ.ዓ. ድረስ የተለያዩ ግለሰቦች እግዚአብሔርን የማምለኪያ መዝሙራት መጻፍ ቀጥለው እንደነበር ጥርጥር የለውም። አንድ ያልታወቀ ሰው እስከዚያ ጊዜ ድረስ የነበሩትን መዝሙራት ሁሉ ሰብስቦ በልዩ ቅደም ተከተል እስካስቀመጠበት እስከ 400 ዓ.ዓ. ድረስ መሰብሰባቸውን ቀጥለው ነበር። ከዚያ በኋላ ይህ መጽሐፍ «መዝሙር» በመባል ታወቀ። 

የመዝሙረ ዳዊት ቅንብር (አስተዋጽኦ) 

መዝሙረ ዳዊት 150 ልዩ ልዩ መዝሙራትን ይዟል። ሆኖም ግን የተለያዩ ትርጕሞች እነዚህ 150 መዝሙራት የትኞቹ እንደሆነና አከፋፈላቸውንም በሚመለከት ይለያያሉ። የእንግሊዝኛው መጽሐፍ ቅዱስ የዕብራይስጡን መጽሐፍ ቅዱስ አከፋፈል ይከተላል፡፡ የእንግሊዝኛው መጽሐፍ ቅዱስ አከፋፈል በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ በቅንፍ ውስጥ የሚገኘው ነው፡፡ የቀድሞው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጕም የምዕራፍ አከፋፈሉን የወሰደው ከግሪኩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጒም ነው። በግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ (እንዲሁም አማርኛ) መዝሙር 9እና 10 እንዲሁም መዝሙር 114 እና 115 እንደ አንድ መዝሙር ተዋሕደው ቀርበዋል፤ ዳሩ ግን ቀድሞ አንድ መዝሙር የነበሩት 116 እና 147 እያንዳንዳቸው ለሁለት መዝሙራት ተከፍለዋል። በግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ በድምሩ 150 መዝሙራት ለማድረግ በተጨማሪ አንድ ሌላ መዝሙር አክለዋል። 

ከጥንት ጀምሮ መዝሙረ ዳዊት በአምስት ትናንሽ መጽሐፍት ተከፍሏል፡፡

1ኛ መጽሐፍ፡- መዝሙር 1-41 (በአብዛኛው የዳዊት መዝሙራት ናቸው)። 

2ኛ መጽሐፍ፡- መዝሙር 42-72 (በአብዛኛው የዳዊትና የቆሬ ልች መዝሙራት ናቸው)። 

3ኛ መጽሐፍ፡- መዝሙር 73-89 (በአብዛኛው የአሳፍ መዝሙራት ናቸው)። 

4ኛ መጽሐፍ፡- መዝሙር 90-106 (በአብዛኛው ጸሓፊያቸው የማይታወቅ መዝሙራት ናቸው)፡፡ 

5ኛ መጽሐፍ፡- 107-150 (በአብዛኛው የዳዊት መዝሙራት ናቸው)፡፡ 

እነዚህ አምስት መጻሕፍት እያንዳንዳቸው እግዚአብሔር ስለ ታላቅነቱ በማወደስ በምስጋና መዝሙር የሚጠቃለሉ ናቸው። 

አንዳንድ ምሁራን 1ኛ መጽሐፍ በሰሎሞን ወይም በዳዊት (መዝሙር 72፡20)፣ 2ኛና 3ኛ መጻሕፍት በ710 ዓ.ዓ. በንጉሥ ሕዝቅያስ (2ኛ ዜና 29፡30)፥ 4ኛና 5ኛ መጻሕፍት በ430 ዓ.ዓ. በዕዝራ እንደተሰበሰቡ ያስባሉ። ሆኖም ይህን በሚመለከት የተጨበጠ ማረጋገጫ የለም። 

ምናልባት ከ1ኛ-3ኛ ያሉት መጻሕፍት ከ4ኛና 5ኛ መጻሕፍት በፊት ሳይሆኑ አይቀሩም። እጅግ ጥንታዊ በሆኑ ረቂቅ ጽሑፎች ሁሉ ውስጥ ከ1ኛ-3ኛ ያሉት መጻሕፍት በአሁኑ ወቅት በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ባሉበት መልክ ተቀምጠው ነበር፤ ዳሩ ግን በ4ኛና በ5ኛ ውስጥ መጻሕፍት ውስጥ የበርካታ ልዩነቶች መኖር፥ ዘግይተው መሰብሰባቸውን የሚጠቁም ነው። 

ብዙ ምሁራን በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ አምስት መጻሕፍት መኖራችው፥ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት መሠረት የሆኑት የሙሴ መጻሕፍት አምስት መሆናቸውን የሚያንጸባርቅ ነው ብለው ያስባሉ። 

በርካታ ምሁራን፥ መዝሙረ ዳዊትን በመጨረሻ ያቀናበረው ሰው፣ አሠራሩ ለአንድ ልዩ የሥነ-መለኮት ዓላማ እንደሆነ ያስባሉ። መዝሙራቱ ግልጽ የሆነ አንድ አካሄድ ስለሌላችው፥ ይህን የሥነ-መለኮት ትምህርት ዓላማ መወሰን አስቸጋሪ ነው። ቀጥሉ በአንድ ምሁር ግምት የመዝሙረ ዛዊት አጠናቃሪ የሆነ ሊቅ መዝሙረ ዳዊትን እንዴት እንዳቀናበረው እንመለከታለን፡- 

1. የመዝሙረ ዳዊት መግቢያ (መዝሙር 1-2) 

ሀ. መዝሙር 1 – እግዚአብሔር የጻድቅን ሰው ጽድቅ ያረጋግጣል 

ለ. መዝሙር 2 – እግዚአብሔር የእስራኤልን ንጉሥ ይመርጣል፤ ይከላከልለታልም። 

2. ዳዊት ከሳኦል ጋር ስለነበረው ግጭት የሚናገሩ መዝሙራት (መዝሙር 3-41) 

3. ስለ ዳዊት ንጉሥነት የሚናገሩ መዝሙራት (መዝሙር 42-72) 

4. ከአሦር ጋር ስለተደረገው ጦርነት የሚናገሩ መዝሙራት (መዝሙር 73-89) 

5. ስለ ቤተ መቅደሱ መደምሰስና ስለ ምርኮ የሚናገሩ መዝሙራት (መዝሙር 90-106) 

6. እግዚአብሔር እስራኤልን ከምርኮ በመመለስ እንደሚያድስ የሚናገሩ የምስጋና መዝሙራት (መዝሙር 107-145) 

7. ለእግዚአብሔር ምስጋና የሚሰጡ የማጠቃለያ መዝሙራት (146-150) 

ዋና ዋና የመዝሙራት ዓይነቶች 

እጅግ በርካታ የመዝሙራት ወይም የግጥም ዓይነቶች ቢኖሩም እንኳ በሦስት ዋና ዋና ዓይነቶች ሊመደቡ ይችላሉ። 

1. የምስጋና መዝሙራት፡- እነዚህ የምስጋና መዝሙራት የግል ወይም የቡድን ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አንዳንዶቹ መዝሙራት በእግዚአብሔር ላይ በማተኮር፣ ስለ ማንነቱ፣ ባሕሪያቱያመሰኙታል፡፡ ሌሎች መዝሙራት ደግሞ እግዚአብሔር ለግለሰብ ወይም ለቡድን ስላደረጋቸው፥ በተናጠል ስለሚታዩ ጉዳዮች እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔርን ስለ ባሕርዩ ማመስገን የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? ለ) ይህ በአምልኮ ውስጥ ሊኖር የሚገባ ዐቢይ ነገር የሆነው እንዴት ነው? ሐ) በእግዚአብሔር ባሕርይ ላይ የሚያተኩሩ እና ስለ ባሕርዩ የሚያመሰግኑት ሦስት የአማርኛ መዝሙራትን ጥቀስ፡፡ መ) እግዚአብሔርን ስላደረገልን ነገሮች የሚያመሰግኑ ሦስት የአማርኛ መዝሙራትን ጥቀስ። ሠ) በርካታ መዝሙራትን የምናገኘው አላደረገልን ነገሮች እግዚአብሔርን በሚያመሰግን መልኩ እንጂ ስለ ባሕርዩ በማመስገን ያልሆነው ለምንድን ነው? 

2. የጥበብ መዝሙራት፡- እነዚህ መዝሙራት እንደ መጽሐፈ ምሳሌ በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ጠቢባን እንደምንሆን የሚናገሩ ናቸው፡፡ እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኝ መንገድ እንዴት መመላለስ እንዳለብን ያስተምሩናል። ለዚህም መዝሙር 1. ጥሩ ምሳሌ ነው። 3. የኃዘን ወይም የሰቆቃ መዝሙራት፡- እነዚህ መዝሙራት ብዙ ጊዜ የሚጀምሩት «አቤቱ» በሚል ቃል ነው (መዝሙር 3-7)። እነዚህ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ችግርና ኃዘን የሚገልጡ የግል ወይም የጉባኤ መዝሙራት ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ መዝሙራት አንድ ዓይነት አካሄድ እንዳላቸው ማየቱ አስደናቂ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ጸሐፊው ያለውን አቤቱታ፥ የደረሰበትን ችግር ሲገልጽ እናያለን። ሁለተኛ ደረጃ፣ ጸሐፊው ለእግዚአብሔር የሚያቀርበው ጥያቄ አለ። በሶስተኛ ደረጃ፥ ጸሐፊው በመከራ ውስጥ በእግዚአብሔር እንደሚታመን የሚገልጽ ኑዛዜ ያቀርባል። በአራተኛ ደረጃ፣ እግዚአብሔር ጸሎቱን ከመለሰለት እንደሚያመሰግነው ጸሐፊው የገባውን ቃል ኪዳን እናገኛለን። 

ልዩ ልዩ መዝሙራት በተለያዩ ክፍሎች የሚመደቡባቸው በርካታ መንገዶች አሉ። መዝሙራት ሊመደቡ ከሚችሉባቸው መንገዶች አንዱ ቀጥሎ በምሳሌነት ቀርቧል፡- 

1. አንድ ግለሰብ እግዚአብሔር እንዲረዳው የሚያቀርባቸው ጸሎቶች (መዝሙር 3፡7-8) 

2. አንድ ግለሰብ እግዚአብሔር ስለረዳው የሚያቀርበው ምስጋና (መዝሙር 30፤ 34) 

3. አንድ ማኅበረሰብ በጋራ የሚያቀርበው ጸሎት (መዝሙር 12፣ 44) 

4. አንድ ማኅበረሰብ ስለ እግዚአብሔር እርዳታ በጋራ የሚያቀርበው ምስጋና (መዝሙር 66፤ 75) 

5. ከእግዚአብሔር ይቅርታ የመጠየቂያ መዝሙራት (መዝሙር 32፤ 51)  

6. ስለ እግዚአብሔር ግርማና ታላቅነት የሚቀርቡ የምስጋና መዝሙራት (መዝሙር 8፤ 19) 

7. የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ አገዛዝ የሚገልጹ መዝሙራት (መዝሙር 47፣ 93-99) 

8. ስለ ኢየሩሳሌም ከተማ፥ ስለ ጽዮን የቀረቡ መዝሙራት (መዝሙር 46፤ 48) 

9. ስለ እስራኤል ነገሥታት የቀረቡ መዝሙራት (መዝሙር 2፤ 18፤ 20) 

10. ወደ ኢየሩሳሌም ለአምልኮ ጉዞ በሚደረግበት ጊዜ በጉዞ ላይ የሚደረጉ መዝሙራት (መዝሙር 120-134) 

11. በቤተ መቅደስ ውስጥ ለሚደረግ አምልኮ የተጻፉ መዝሙራት (መዝሙር 15፤ 24) 

12. ለሰዎች አስፈላጊ የሆኑ መንፈሳዊ እውነቶችን ለማስተማር የተጻፉ መዝሙራት (መዝሙር 1፤34) 

13. ስለ መሢሑ የሚናገሩ መዝሙራት (መዝሙር 22፤ 110)  

14. የእስራኤልን ታሪክ በድጋሚ የሚናገሩ መዝሙራት (መዝሙር 78፤ 105) 

የውይይት ጥያቄ፥ ከአሥራ አራቱ ዓይነት መዝሙራት አንድ አንድ አንብብ። 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: