የመዝሙረ ዳዊት ዓላማ እና ልዩ የሚያደርጉት ነገሮች

የመዝሙረ ዳዊት ዓላማ 

እያንዳንዱ መዝሙር የተለያየ ዓላማ ያለው ቢሆንም እንኳ መዝሙረ ዳዊት የመዝሙር መጽሐፍ እንዲሆን ተደርጎ መሰብሰቡን ማስታወስ ጠቃሚ ነው፡፡ አይሁድ ከምርኮ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ቤተ መቅደሱን እንደገና ከገነቡ በኋላ (በ520 ዓ.ዓ.) እነዚህ መዝሙራት በአይሁድ የአምልኮ ፕሮግራም ውስጥ ተካትተው ነበር። አይሁድ በቤተ መቅደስና በምኲራቦቻቸው እግዚአብሔርን በሚያመልኩበት ጊዜም ይጠቀሙባቸው ነበር። እነዚህ መዝሙራት በጥንት ቤተ ክርስቲያን የአምልኮ ጊዜ ያገለግሉ ነበር። 

መዝሙረ ዳዊት በመሠረቱ ወደ እግዚአብሔር የሚደረግ ጸሎትና ለእግዚአብሔር የሚቀርብ ምስጋና ያለበት መጽሐፍ ነው። የመጽሐፉ ትኲረት ሁልጊዜ ከእግዚአብሔርና ከልጆቹ ጋር ባለው ግንኙነት ላይ ነው፡፡

በየመዝሙራቱ ላይ የተጻፉ ርእሶች 

እንደ ቀድሞው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ባለ፥ በአብዛኛው መጽሐፍ ቅዱስ ትርጕም፥ ውስጥ ለአብዛኛዎቹ መዝሙራት የተሰጡ አርእስት አሉ። ሆኖም እነዚህ ርእሶች መዝሙራቱ በመጀመሪያ በተጻፉበት ወቅት ስለ መሰጠታቸው፤ ምሁራን ይከራከራሉ። ከ150 መዝሙራት መካከል 116ቱ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ርእሶች አሏቸው። ርእሶቹ ከሚከተሉት አንዱን ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ነገሮችን የሚገልጹ ናቸው:- 

1. ጸሐፊው ማን እንደነበር፥ 

2. ምን ዓይነት መዝሙር እንደሆነ (ለምሳሌ፡- ኃዘን፥ ምስጋና ወዘተ)፥ 

3. በምን ዓይነት የሙዚቃ መሣሪያ ይዘመር እንደነበር፥ 

4. በአምልኮ ጊዜ ውስጥ እንዴት አገልግሎት ላይ መዋል እንዳለበት፥ 

5. መዝሙራቱን ለማዘጋጀት ጸሐፊውን ያነሣሣው ታሪካዊ ድርጊት። 

መዝሙረ ዳዊትን ልዩ የሚያደርጉት ነገሮች፡- 

1. ከአብዛኛዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በተለየ ሁኔታ ይህ መጽሐፍ የተጻፈው ለልባችንና ለስሜታችን ይናገር ዘንድ ነው። ጸሐፊው ያለፈበትን፥ ለእግዚአብሔር የነበረውን ከፍተኛ ፍቅርና ውዳሴ እንድንለማመድ የተጻፈ ነው። በኃጢአት ወይም በጠላቶቹ በሚሸነፍበት ጊዜ ተሰምቶት የነበረውን የተስፋ መቍረጥ ስሜት እንድንለማመድ በሚያደርግ መንገድ የተጻፈ ነው፤ ነገር ግን እግዚአብሔር እንዴት ይቅር እንዳለው ወይም በጠላቶቹ ላይ ድልን እንደሰጠው በምናነብበት ጊዜ ልባችን ይነቃቃል። 

2. አብዛኛውን የዚህን መጽሐፍ ክፍል ለመረዳት የሚያስችል መሠረታዊ ነገር እግዚአብሔር ጻድቃንን እንደሚባርክና ኃጢአተኞችን ደግሞ እንደሚቀጣ የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ነው። ከመጽሐፈ ኢዮብ ጥናታችን እንደተረዳነው እግዚአብሔር የሚያከብሩትንና የሚታዘዙትን እንደሚባርክ የማይታዘዙትን ደግሞ እንደሚቀጣ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስተምራል። ነገር ግን አይሁድ ይህንን ትምህርት ከመጠን በላይ በማስፋት፥ አንድ ሰው ባለጠጋ ከሆነ ይህ ጻድቅ የመሆኑና እግዚአብሔር በእርሱ ደስ የመሰኘቱ ምልክት እንደሆነ፥ መከራና ሥቃይ ከደረሰበት ደግሞ የእግዚአብሔር የፍርድ ምልክት እንደሆነ ይመስላቸው ነበር። የበረከቱ ወይም የመከራው መጠን ሰውዬው ምን ያህል ጻድቅ ወይም ኃጢኣተኛ መሆኑን የሚያሳይ ይመስላቸው ነበር። መጽሐፈ ኢዮብ የተጻፈው ይህንን አሳብ ለመቃወም ነበር። 

በብሉይ ኪዳን ውስጥ ስለ መንግሥተ ሰማያትና ስለ ገሃነም የሚያስተምር ግልጽ ነገር አልነበረም። እግዚአብሔር ይህንን በግልጽ ያሳየው በአዲስ ኪዳን ዘመን ነው። ስለዚህ እግዚኣብሔር በረከቱንና ፍርዱን የሚገልጸው ሰው በሕይወት እያለ ብቻ ሳይሆን፥ ከሞተ በኋላም ሊገልጽ እንዳለው አይሁድ አልተረዱም ነበር። ስለዚህ አይሁድ ሰው በሕይወት እያለ እግዚአብሔር ጻድቅ ፍርዱን ወዲያውኑ በመስጠት ጻድቁን እንደሚባርከና ኃጢአተኛውን የሚቀጣ ይመስላቸው ነበር፡፡ 

አይሁድ እግዚአብሔር ኃጢአተኛ ሰውን ወዲያውኑ እንዲቀጣ የነበራቸው ፍላጎት በተለይ የሚታየው ጸሐፊዎቹ እግዚአብሔር ክፉዎችን እንዲደመስሥ በሚለምኑበት ክፍል ነው (መዝሙር [28]፡ 4፤ [137]፡9)። ኢየሱስ ጠላትን መውደድ እንደሚገባ (ማቴዎስ 5:43-48) ካስተማረው የሚቃረኑ ስለሚመስሉ እዚህን መዝሙራት መረዳት ለክርስቲያኖች አስቸጋሪ ነው። ዳሩ ግን በእነዚህ ሙዝሙራት ውስጥ የጸሐፊዎቹ ትኵረት በእግዚአብሔር ጻድቅ ፈራጅነት ላይ ነበር። እግዚአብሔር የራሱንና የልጆቹ ጠላቶች የነበሩትን በመቅጣት፥ ቅን ፍርዱን እንዳያሳይ ታማኝ የሆኑ ሰዎችንም እንዲባርክ ይፈልጉ ነበር። 

መዝሙረ ዳዊት የሚያስተምረው በዚህ ሕይወት እግዚአብሔር ድቃንን ለመባረክና ኃጥአንን ለመቅጣት ዝንባሌ ያለው መሆኑን ነው፤ ነገር ግን ይህ ሁሉንም ሰው በሁሉም ጉዳይ የሚመለከት አንደሆነ ጨርሶ አልተነገረም። ስለዚህ እነዚህን ዝንባሌዎች ማለትም ጻድቅ ሰው ክፋት እንደማይደርስበት ወይም ኃጢአተኞች ወዲያውኑ እንደሚፈረድባቸው ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደተሰጡ የተስፋ ቃሎች አድርገን መውሰድ የለብንም። በተለየ ሁኔታ ውስጥ እግዚአብሔር አንድን ሰው ማበልጸጉ ወይም ነፃ ማውጣቱ ምን ማድረግ እንደሚችል የሚያሳይ ምስክር እንጂ ሁልጊዜ የሚያደርገው ነገር ነው ማለት አይደለም። እነዚህን መዝሙራት እንዴት እንደምንተረጕማቸውና ከሕይወት ጋር እንደምናዛምዳቸው መጠንቀቅ አለብን። ይህም እነዚህን መዝሙራት በተሳሳተ መንገድ በመተርጐም፥ እግዚአብሔር ሁልጊዜ ከማናቸውም ጉዳት እንደሚጠብቀን አድርገን እንዳናስብ ያደርገናል። ከመጽሐፍ ቅዱሳችን በግልጽ እንደምንመለከተው፥ እግዚአብሔር ብዙውን ጊዜ መከራ እንድንቀበል ይፈቅዳል። በምድር ላይ የምንጠብቃችወ ሥጋዊ የሆኑ በረከቶችን ሳናገኝ እንድንሞት እንኳ ሊያደርግ ይችላል። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን ስለ በረከትና ቅጣት የተነገረው ይህ መንፈሳዊ እውነት በዘላለማዊ መንግሥት ውስጥ ተግባራዊ እንደሚሆን እናውቃለን። እግዚአብሔር ታማኝ የሆኑትን ሰዎች ይባርካችዋል። (ማቴዎስ 9፡20-21፣ 1ኛ ቆሮንቶስ 3፡12-15)። ክፉችን ደግሞ ይቀጣል (ራዕይ 20፡13-15)። ይህ እውነት ግን በምድር ላይ እያለን ሁልጊዜ 

አይታይም። 

የውይይት ጥያቄ፦ ጻድቃን መከራ እንዲቀበሉና እንዲጐሳቈሉ እግዚአብሔር እንደሚፈቅድ፥ ክፉና ኃጢአተኞች የሆኑትን ሰዎች ወዲያውኑ እንደማይቀጣ የሚለው እውነታ ከብዙ ክርስቲያኖች አስተሳሰብ የሚለየው እንዴት ነው? 

3. ከመዝሙራት ውስጥ ዘጠኙ የሚናገሩት ስለ እስራኤል ነገሥታት ነው። ከእነዚህ አብዛኛዎቹ በዳዊት የተጻፉ ወይም ስለ ዳዊትና ስለ ልጆቹ የተጻፉ ናቸው። መዝሙሮቹ በመጀመሪያ የሚናገሩት ፍጹም የሆነ የእስራኤል ንጉሥ ምሳሌ ስለሆነው ስለ ዳዊት ነው። አንዳንዶቹ ደግሞ በእግዚአብሔር ምሪት፥ ዋናውና ከዳዊት ዘር ስለሆነው ፍጹም ንጉሥ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ይናገራሉ። ከእነዚህ መዝሙራት ውስጥ ብዙዎቹ ሁለት ትርጕም አላቸው ለማለት እንችላለን። በመጀመሪያ ደረጃ፥ ስለ ዳዊት ወይም ስለ ሌሎቹ የእስራኤል ነገሥታት ይናገራሉ። በሁለተኛ ደረጃ፥ ደግሞ ስለ ኢየሱስ ይናገራሉ። 

የውይይት ጥያቄ፥ የሚከተሉትን ስለ ኢየሱስ የተነገሩ ትንቢቶች ከፍጻሜያቸው ጋር አወዳድር። በመዝሙራት ውስጥ የሚገኘው እያንዳንዱ ትንቢት በኢየሱስ ክርስቶስ እንዴት እንደተፈጸመ ዘርዝር። 

ሀ. መዝሙር 2፡7- ዕብራውያን 1፡5 

ለ. መዝሙር (16)፡9-10 – ሐዋርያት ሥራ 2፡31-32 

ሐ. መዝሙር (22)፡1 – ማቴዎስ 27፡46 

መ. መዝሙር 40፡6-8 – ዕብራውያን 10፡9 

ሠ. መዝሙር (41)፡9 – ዮሐንስ 13፡18 

ረ. መዝሙር(45)፡6 – ዕብራውያን 1፡8 

ሰ. መዝሙር(110)፡1 – ማቴዎስ 22፡43-45 

ሸ. መዝሙር(110)፡4 – ዕብራውያን 7:17 

ቀ. መዝሙር(118)፡22-23 – ማቴዎስ 21፡42 

አዲስ ኪዳን ከሌላ ከማንኛውም የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ይልቅ ከፍተኛ ደረጃ የጠቀሰው ከመዝሙረ ዳዊት ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ደምቀው የቀረቡትን ቃሎች ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ተመልከት። ከዚያም በመዝሙረ ዳዊት በቀረቡበት አኳኋን ተርጒማቸው። እግዚአብሔር ከእነዚህ ተምሳሌቶች አንዱን እንዴት በሕይወትህ እንደፈጸመ አሳይ፡- 

ሀ. እግዚአብሔር ዓለታችን ነው። 

ለ. እግዚአብሔር አምባችን ነው። 

ሐ. እግዚአብሔር እረኛችን ነው። 

መ. እግዚአብሔር ጋሻችን ነው። 

ሠ. እግዚአብሔር መሸሽጊያችን ነው። 

ረ. እግዚአብሔር የደኅንነታችን ቀንድ ነው። 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

https://forms.gle/TjDTQzmox733NsqS9

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading