መጽሐፍ ቅዱስ፡- መልእክቱና ዓላማው

ሀ. ኢየሱስ ክርስቶስ በመልእክትነት 

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና መልእክት ነው። ስለሆነም የክርስቶስን ማንነትና የሥራውንም ፍጹምነት በሚመለከት በብዙ መንገዶች የቀረበውን መግለጫ በትክክል ለማወቅ የሚቻለው፥ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን፡- 

1. ኢየሱስ ክርስቶስ ፈጣሪ ነው። የኦሪት ዘፍጥረት የመጀመሪያ ምዕራፎች እግዚአብሔር ዓለምን እንደፈጠረ የመዘገቡልን ሲሆን፥ ይህንንም “ኤሎሂም” በሚል የዕብራይስጥ ቃል ይገልጣሉ። ቃሉም አብን፥ ወልድን እና መንፈስ ቅዱስን ያመለክታል። አንድ ሰው ሁሉም ነገር የተፈጠረው በክርስቶስ መሆኑን የሚረዳው አዲስ ኪዳን (ዮሐ. 1፡3) ላይ ሲደርስ ነው። ቆላስይስ 1፡16-17 ውስጥ፥ “የሚታዩትና የማይታዩትም ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ፥ በእርሱ፥ ተፈጥረዋልና፤ ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር ነው፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል እርሱ ከሁሉም በፊት ነው ሁሉም በርሱ ተጋጥሞአል” በማለት ክርስቶስ የሁሉም ነገር ፈጣሪ መሆኑን ይመሰክራል። ይህ ማለት ደግሞ፥ እግዚአብሔር አብ እና እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በፍጥረት ሥራ ውስጥ ምንም ድርሻ አልነበራቸውም ማለት አይደለም። ነገር ግን በፍጥረት ሥራ ውስጥ ለክርስቶስ የዋና አድራጊነትን ስፍራ ይሰጠዋል። በዚህ መሠረት ዓለምና በዓለም ያሉት ሁሉ የክርስቶስን የእጅ ሥራ ፍጹምነት ይገልጣሉ። 

2. ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ዓለም ልዑል ገዥ። ኢየሱስ ክርስቶስ ፈጣሪ ስለሆነ በዓለማት ሁሉ ላይ ሉዓላዊ ገዥ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ልዕልና የእግዚአብሔር አብ መሆኑን ይናገራል። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ሁሉ ይገዛ ዘንድ የእግዚአብሔር አብ ፈቃድና ዓላማ ነው (መዝ. 2፡8-9)። ምላስ ሁሉ ክርስቶስ ጌታ መሆኑን እንዲመሰክር፥ ጉልበትም ሁሉ ለክርስቶስ ክብር እንዲሰግድና፥ እንዲንበረከክ የእግዚአብሔር ዓላማ ነው (ኢሳ. 45፡23፤ ሮሜ 14፡11፤ ፊሊ. 2፡9-11)። የሰው ዘር ታሪክ በእግዚአብሔር ላይ የማመፅ መዘክር ቢሆንም እንኳ (መዝ. 2፡1-2)፥ ክርስቶስ በመላው ዓለም ላይ በፍጹም ልዑልነቱ የሚገለጥበትን ጊዜም በመጠበቅ ላይ ነው (መዝ. 110፡1)። ጊዜውም ክርስቶስ ኢየሱስ በሁሉም ነገር ላይ ፍጹም ጌታ የሚሆንበት፥ በኃጢኣት ላይ የሚፈርድበት እና ገዥነቱ የሚረጋገጥበት ይሆናል (ራእይ 19፡15-16)። 

ዓላማውን በማከናወን ረገድ እግዚአብሔር የዓለም ነገሥታት በዙፋናቸው እንዲሆኑ ፈቅዷል። በየዘመናቱ ታላላቅ መንግሥታትና መሪዎቻቸው ተነሥተዋል፥ ወድቀዋል። ከእነዚህም ጥቂቶቹ ግብፅ፥ ሶርያ፥ ባቢሎን፥ ፋርስ፥ ግሪክ እና ሮም ይገኙባቸዋል። የመጨረሻው መንግሥት ግን ከሰማይ የሚመጣውና ክርስቶስ የሚገዛው ይሆናል (ዳን. 7፡13-14)። 

ክርስቶስ ኢየሱስ የሕዝቦች ገዢ መሆን ብቻ ሳይሆን፥ የዳዊት ልጅ እንደመሆኑ በዳዊት ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ የእስራኤል ንጉሥ ይሆናል (ሉቃስ 1፡31-33)። ይህ የሚረጋገጠው፥ ጌታ ዳግም ተመልሶ የሺህ ዓመት መንግሥቱን ሲመሠርትና በመላው ዓለምና በእስራኤል ላይ ሲነግሥ ነው። 

ሉዓላዊነቱም ራስ ከሆነላት ቤተ ክርስቲያን ጋር ባለው ኅብረት ይገለጣል (ኤፌ. 1፡22-23)። ክርስቶስ የዓለም፥ የእስራኤል እና የቤተ ክርስቲያንም ራስ (ኤፌ. 1፡20-21) እንደመሆኑ በሰው ሁሉ ላይ ልዑል ፈራጅ ነው (ዮሐ. 5፡27፤ ኢሳ. 9፡6-7፤ መዝ. 72፡1-2፥ 8፥ 11)። 

3. ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ የሆነ ቃል፡፡ በተለይ በአዲስ ኪዳን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ የሆነ ቃል መሆን ተገልጧል። እግዚአብሔር በአካል የተገለጠበት እና ባሕርይው፥ እንዲሁም ማንነቱ የተገለጠበት መሆኑን ነው ይህ የሚያሳየው። የእግዚአብሔር ባሕርያት ሁሉ በክርስቶስ ተገልጠዋል፤ በተለይም ጥበቡ፥ ኃይሉ፥ ቅድስናው እና ፍቅሩ። ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ምንነት የተገለጠበት ቃል ነው (ዮሐ. 1፡ 1)። ከሌላ ከማንኛውም መለኮታዊ መገለጥ ይልቅ፥ ሰዎች በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እግዚአብሔርን በትክክል ሊያውቁት ይችላሉ። ዕብራውያን 1፡3 ውስጥ እንደተገለጠው፥ “እርሱም የክብሩ መንፀባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ ሁሉን በሥልጣኑ ቃል እየደገፈ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ፥ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ”። የእግዚአብሔር ዋና ዓላማ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ራሱን ለፍጥረታቱ መግለጥ ነው። 

4. ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ አዳኝ። የመጽሐፍ ቅዱስ ዋናውና ታላቁ መልእክት፥ በሰው መፈጠርና በኃጢአት መውደቅ ጀምሮ በአዲስ ሰማይና አዲስ ምድር በሚያበቃው የሰው ዘር ታሪክ ክንዋኔ ውስጥ የሚገኘው የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የአዳኝነት ሥራ ነው። ክርስቶስ ሰይጣንን ድል የሚያደርግ የተስፋ ዘር ነበር (ዘፍ. 3፡15)። የዓለምን ኃጢአት የሚሸከም የያህዌ አገልጋይ መሆኑ በብሉይ ኪዳን ተመልክቷል (ኢሳ. 53፡4-6፤ ከዮሐ. 1፡29 ጋር ያመሳከሩት)። የኃጢአት መሥዋዕት ሆኖ የዓለምን ሁሉ የኃጢአት ፍርድ በመሽከም በመስቀል ላይ መሞት ነበረበት (1ኛ ቆሮ. 15፡3-4፤ 2ኛ ቆሮ. 5፡ 19-21፤ 1ኛ ጴጥ. 1፡ 18-19፤ 1ኛ ዮሐ. 2፡2፤ ራእይ 1፡5)። በአዳኝነቱ የኃጢአታችን መሥዋዕት ብቻ ሳይሆን፥ ሊቀ-ካህናችንም ነው (ዕብ. 7፡25-27)። 

በቅዱሳት መጻሕፍት ተደጋግሞ እንደተረጋገጠው፥ ከእግዚአብሔር ዋና ዋና ዓላማዎች አንዱ፥ ለጠፋው የሰው ዘር በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድነትን መስጠት ነው። በዚሁ መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ ከዘፍጥረት እስከ ራእይ በከፍተኛ ሁኔታ እንደብቸኛው አዳኝ ቀርቧል (ሐዋ. 4፡ 12)። 

ለ. የሰው ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ 

መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበት ዋና ዓላማ እግዚአብሔርን ለማክበር ሲሆን፥ ይህን ከመፈጸሙ አንጻር የሰውንም ታሪክ ያቀርባል። በመጀመሪያዎቹ የኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፎች የሚገኘው የፍጥረት ታሪክ በአዳምና ሔዋን መፈጠር ተደምድሟል። መጽሐፍ ቅዱስ በአጠቃላይ የሚገልጠው፥ እግዚአብሔር ለሰው ዘር ያለውን ዓላማ ነው። 

የሚቀጥሉት ምዕራፎች እንደሚገልጡት፥ እግዚአብሔር ለዓለም ሕዝቦች ያለው ሉዓላዊ ዓላማ በትውልዶች ታሪክ ውስጥ ተገልጧል። የአዳምና ሔዋን የቅርብ ትውልዶች በኖኅ ዘመን በጥፋት ውኃ ጠፉ። ዘፍጥረት 10 ውስጥ የኖኅ ትውልዶች ሦስቱን ዋና ዋና የሰው ዘር ክፍፍሎች እንደመሠረቱ ተመዝግቧል። የኖኅ ትውልዶች ከእግዚአብሔር መንገድ ተሰናከሉና በባቢሎን ግንብ ሥራ ወቅት ተቀጡ። ከዚያም እግዚአብሔር ራሱን በእስራኤል በኩል የሚገልጥበትን ዓላማ ለመፈጸም አብርሃምን መረጠ። ከኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 12 ጀምሮ ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና መልእክት የእስራኤል መንግሥት መመሥረትና የዚያ ታሪክ ነው። የብሉይ ኪዳን አብዛኛው ክፍል የሚገልጠው፥ በዙሪያዋ ከነበሩ አሕዛብ ጋር ስትነጻጸር እጅግ ትንሽ ስለነበረችው እስራኤል ነው። በእግዚአብሔር ዓላማ ውስጥ፥ በብሉይ ኪዳን ለአብርሃም በአንተ ዘር የሰው ዘር ሁሉ ይባረካል ተብሎ የተነገረለት ተስፋ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት ሙሉ በሙሉ እውን በመሆን በአዲስ ኪዳን ተፈጽሟል። 

ሌላ አዲስ የሰው ዘር ክፍፍል በአዲስ ኪዳን ውስጥ ይታያል። ይኸውም ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አዳኛቸው ያመኑ አረማውያንና፥ አይሁድን የያዘችው የክርስቶስ አካል ቤተ ክርስቲያን ናት። አዲስ ኪዳን፥ በተለይም በሐዋርያት ሥራና በመልእክቶች አማካይነት እግዚኣብሔር ከቤተ ክርስቲያን ጋር ያለውን ግንኙነት ያስገነዝባል። የራእይ መጽሐፍ የዚህ ሁሉ ታላቅ ፍጻሜ ነው። በግብፅና በሶሪያ በመጀመር በባቢሎን፥ በሜዶንና ፋርስ፥ በግሪክ፥ በሮም እያሉ የቀጠሉት ታላላቅ ተከታታይ መንግሥታት ሂደት፥ በክርስቶስ ዳግም ምጽአት ጊዜ ከሰማይ በሚመጣው መንግሥት ይደመደማል። በሺህ ዓመቱ መንግሥት ዘመን የሚገኙት፥ አይሁድም ሆኑ አረማውያን፥ እስራኤል በመሢሕ ንጉሥዋ ሥር በምትይዘው መሬት ላይ ሆና እና የዓለም ሕዝቦች ባጠቃላይ የሺህ ዓመቱን መንግሥት በረከት ይጋራሉ። 

መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ክርስቶስን ማዕከሉ የሚያደርግና የእግዚአብሔር ክብር በዓለም ታሪክ ጋር እንዴት እንደተገለጠ የሚያሳይ ሲሆን፥ በዚሁ መሠረት የእግዚአብሔር ዋና ዋና ሥራዎቹ በሕዝቦች ላይ ባለው የበላይነት፥ ለእስራኤል ባለው ታማኝነትና ለቤተ ክርስቲያን ባለው ጸጋ አማካይነት ተገልጧል። የዚህ ሁሉ መጨረሻ፥ ታሪክ በሚፈጸምበት፥ እንዲሁም ዘላለም በሚጀምርበት፥ በአዲሱ ሰማይና በአዲሱ ምድር፥ በአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ይሆናል። 

ሐ. የመጽሐፍ ቅዱስ ዓላማ 

በጽሑፍ በሰፈረው የእግዚአብሔር ቃል መሠረት፥ እግዚአብሔር ያደረገው ወይም የሚያደርገው ነገር፥ ከፍጥረት መጀመሪያ እስከ ዘላለም ያለው አንድ ታላቅ ዓላማ ተገልጧል። ይህ ታላቅ ዓላማ የእግዚአብሔር ክብር መገለጥ ነው። ለዚህ ዓላማ መላእክት ተፈጠሩ፥ ቁሳዊዎቹ ዓለማት ይህን ክብር ያንጸባርቁ ዘንድ ተፈጠሩ፥ እና ሰው በእግዚአብሔር መልክና አምሳል ተፈጠረ። በማይመረመረው የእግዚአብሔር ተግባራዊ ጥበብ ኃጢአት እንኳ ተፈቅዶ፥ ድነትም ተሰጥቷል። ይህ የሆነው የዚህን ታላቅ ዓላማ መፈጸም አስቀድሞ በማሰብ ነው። 

እግዚአብሔር ክብሩን ለመግለጥ መፈለጉ ትክክልና ተገቢ ነው። ሰው ራሱን ገናና ለማድረግ የሚያስችለው አንዳች ነገር የለውም። ምክንያቱም ፍጹምነት በርሱ ዘንድ አለመኖሩ ነው። እግዚአብሔር ክብሩን ገለጠ ማለት፥ ለፍጥረታት ሁሉ የማይወሰን በረከትን የሚያመጣ እውነትን ገለጠ እና አሳየ ማለት ነው። እግዚአብሔር በሕልውናው ዘላለማዊና በፍጹምነቱ ምሉእ እንደመሆኑ፥ ፍጹም ክብር ይገባዋል። ፍጥረቶቹ የሚገባውን ክብር ቢነፍጉት ግን ድርጊታቸው ሕገወጥ ነው። እግዚአብሔር ክብሩን የሚገልጠው ለራሱ ሳይሆን፥ ለፍጥረታቱ ጥቅም ነው። እግዚአብሔር ራሱን ለፍጥረታቱ መግለጡ፥ ለፍቅርና አምልኮ የሚያበቃ ነገር ሰጥቷቸዋል። እምነትና የአእምሮ ሠላም፥ እንዲሁም በጊዜና በዘላለም ውስጥ የድነትን ዋስትና አትርፎላቸዋል። ሰው የእግዚአብሔርን ክብር ይበልጥ በተረዳ ቁጥር፥ የሚያገኘው በረከት እየላቀ ይሄዳል። 

መጽሐፍ ቅዱስ ከእግዚአብሔር ለሰው የተሰጠ መልእክት እንደመሆኑ መጠን፥ ዓላማው የእግዚአብሔር ዓላማ፥ ማለት እግዚአብሔር ይከበር ዘንድ ነው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ፦ 

1. “የሚታዩትና የማይታዩትም ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል” በማለት ለክብሩ ይመሰክራል (ቆላ. 1፡16)። መላእክትና ሰዎች በዓለማት ያሉት ፍጥረታት በሙሉ ለክብሩ መፈጠራቸውን ያረጋግጣል። እንዲሁም “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል” (መዝ. 19፡ 1)። 

2. ሕዝበ እስራኤል ለእግዚአብሔር ክብር ነው(ኢሳ. 43፡7፥ 21፥ 25፤ 60፡ 1፥ 3፥ 21፤ 62፡3፤ ኤር. 13-11)። 

3. ድነት ለእግዚአብሔር ክብር ነው(ሮሜ. 9፡23)፤ ለእግዚአብሔር ጸጋ መገለጥ (ኤፌ. 2፡7)፥ አሁን ደግሞ የእግዚአብሔር ጥበብ መግለጫ ነው (ኤፌ. 3፡ 10)። 

4. አገልግሎት ሁሉ ለእግዚአብሔር ክብር መሆን አለበት (ማቴ. 5፡16፤ ዮሐ. 15፡8፤ 1ኛ ቆሮ.10፡31፤ 1ኛ ጴጥ. 2፡12፤ 4፡ 11፥ 14)። መጽሐፍ ቅዱስ፥ ራሱም እግዚአብሔር የራሱን ሰው ለበጎና ለመልካም ሥራ የሚያዘጋጅበት መሣሪያ ነው (2ኛ ጢሞ. 3፡ 16፥ 17)። 

5. አዲሱ የክርስቲያን ፍቅር እግዚአብሔር ይከብር ዘንድ ነው (ሮሜ. 5፡2)። 

6. የክርስቲያን ምት እንኳን እግዚአብሔርን ያከብራል (ዮሐ. 21፡19፤ ፊልጵ. 1፡20)። 

7. ድነትን ያገኘ ሰው የክርስቶስን ክብር ይካፈል ዘንድ ሥልጣን ተሰጥቶታል (ዮሐ. 17፡22፤ ቆላ. 3፡4)። 

በአጠቃላይ ሲታይ መጽሐፍ ቅዱስ በመልእክቱም ሆነ በዓላማው፥ በዓለም ከሚገኝ ከማንኛውም መጽሐፍ ፍጹም የተለየ ነው። የሰውን ሥራና የድነት ዕድል በማመልከት ረገድ ከሁሉ ይልቃል። የኢየሱስ ክርስቶስ ባሕርይና ሥራ፥ እንዲሁም ብቸኛ አዳኝነት፥ የእግዚአብሔርን ፍጹም ገናናነት በዝርዝር ይገልጣል። እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪን ለፍጥረቱ የሚገልጥ፥ ዕውን ደግሞ ከነጉድለቱ ፍጹም ሙሉ ከሆነው አምላክ ጋር የሚታረቅበትንና ዘላለማዊ ኅብረትን የሚፈጥርበትን መንገድ የሚያመለክት የሆነ፤ ብቸኛ የሆነ መጽሐፍ ነው።

ምንጭ፡- “ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጦች” መጽሐፍ በዶክተር ሉዊስ ስፔሪ ቼፈር የተጻፈ እና በተክሉ መንገሻ የተተረጎመ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ቅዱሳን ድንቅ ስራ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ማሳሰቢያ፡- ይህን ጽሁፍ መቀየርም ሆነ ለሽያጭ ማዋል በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.