ሰው፡- ውድቀቱ

ኃጢአት ወደ ዓለም እንዴት ገባ የሚለው ጥያቄ ማንኛውም የአስተሳሰብ ሥርዓት የሚያነሣው ሲሆንም፥ ለእነዚህና ለመሳሰሉት ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ያለው ግን መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። ባለፉት ምዕራፎች ስለ መላእክት በተደረገው ጥናት እንደተመለከተው ሁሉ፥ ኃጢአት ወደ ዓለም የገባው፥ ሰው ከመፈጠሩ በፊትና በመጀመሪያ ቅዱሳን ሆነው በተፈጠሩ፥ በኋላ ግን ከሰይጣን ዓመፅ ጋር በተባበሩ መላእክት አማካይነት መሆኑን ለማስረዳት ተሞክሯል። የዘፍጥረት መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፎች አዳምና ሔዋን በኃጢአት መውደቃቸውን ያስረዳሉ። በእነዚህ ምዕራፎች ላይ ሰዎች የተለያዩ ትርጉሞችን ይሰጣሉ። ከእነዚህም መካከል የሰውን ዘር ኃጢአተኛ ድርጊት በቀጥታ የሚገልጥ ነው ብለው የሚረዱ ወይም እውነትነት የሌለው ተረት ነው በማለት የሚረዱ ይገኙባቸዋል። ትክክለኛው ትርጉም ግን፥ ድርጊቱ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተገለጠው ተከናውኗል የሚል ነው። 

የሰውን በኃጢአት መውደቅ ከሦስት አቅጣጫ ለማየት ይቻላል፡- (1) አዳም ከውድቀት በፊት፥ (2) አዳም ከውድቀት በኋላ፥ (3) የአዳም ውድቀት በሰው ዘር ላይ ያስከተለው ውጤት። 

ሀ. አዳም ከውድቀት በፊት 

አዳም የመጀመሪያው ሰው ሲሆን፥ ሔዋን ደግሞ እግዚአብሔር ለአዳም ረዳቱ እንድትሆንለት የፈጠራት ሴት መሆኗን መጽሐፍ ቅዱስ ድንቅና ግልጥ በሆኑ ቃላት ያስገነዝባል። ሁለቱ በኅብረት የሰው ዘር ሁሉ መሠረት በመሆን ከመውደቃቸው በፊት ከኃጢአት ነጻ ሆነው ይኖሩ ነበር። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመተላለፍ በበደሉ ጊዜ ግን፥ ኃጢአት ወደ ሰው ዘር ገባ። ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ገለጣ የሰው ዘር ውድቀት ተብሏል። 

አዳምና ሔዋን በኃጢአት ሳይወድቁ ለምን ያህል ጊዜ እንደቆዩ መጽሐፍ ቅዱስ ባይነግረንም፥ ከነበሩበት ቦታና ሁኔታ ጋር በመላመድ፥ ለእንስሳት ሁሉ ስም በማውጣት ሁም ከእግዚአብሔር ጋር በነበራቸው የአንድነት በረከት ውስጥ ለረጅም ጊዜ ኖረዋል። አዳምና ሔዋን ሲፈጠሩ እንደ ሌሎቹ የእግዚአብሔር ሥራዎች ሁሉ “መልካም” ነበሩ (ዘፍጥ. 1፡31)። ይህም ማለት ፈጣሪያቸውን ደስ የሚያሰኙ ነበሩ። መንፈሳዊ ሁኔታቸው ኃጢአት አያውቅም። ባሕርያቸው ግን ኃጢአት መሥራት ከማይቻለው እግዚአብሔር ባሕርይ ጋር ሲነጻጻር ከኃጢአት ነፃ ቢሆንም ኃጢአት ሊሠራ የሚችል ባሕርይ ነበር። 

ሰው በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ በመሆኑ፥ መልካምና ክፉውን የመለየት ችሎታ፥ እንዲሁም ሙሉ ሰብዕና ነበረው። ኃጢአት ማድረግ ከማይቻለው እግዚአብሔር ጋር ሲነጻጻሩ፥ ሰውም ሆነ መላእክት ኃጢአትን ሊሠሩ የሚያስችላቸው ፈቃድ አላቸው። ባለፈው ክፍል ስለ መላእክት እንዳጠናነው፥ ሰይጣን ኃጢአት ሠርቷል (ኢሳ. 14 ፡12-14፤ ሕዝ. 28፡15)። በሰይጣን ተግባር የተሳተፉ መላእክት ደግሞ “መኖሪያቸውን የተዉ” (ይሁዳ 6) ተብለዋል። ሰይጣንና የወደቁ መላእክት የመጀመሪያዎቹ ኃጢአተኞች በመሆናቸው፥ ሰው የኃጢአት ምንጭ ወይም መነሻ አይደለም፤ ኃጢአተኛ የሆነው በሰይጣን ተጽዕኖ ሳቢያ ነው (ዘፍጥ. 3፡4-7)። 

አዳምና ሔዋን እንዴት ኃጢአት እንደሠሩ ዘፍጥረት 3፡1-6 ውስጥ ተገልጧል። በዚህ ስፍራ እንደተገለጠው ሰይጣን የመጣው ያኔ እጅግ ውብና ማራኪ በነበረው እሳብ ተመስሎ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስረዳው፥ እግዚአብሔር አዳምና ሔዋንን የከለከላቸው አንድ ነገር፥ መልካሙንና ክፉውን ከምታስታውቀው የሕይወት ዛፍ ፍሬ እንዳይበሉ ነበር። ዘፍጥረት 2፡17 ውስጥ እንደተጠቀሰው “እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ ነገር ግን መልካሙንና ክፉን ከምታስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ” ብሎ አስጠነቀቃቸው። ይህ ቀላል ትእዛዝ የተሰጠው አዳም ወይም ሔዋን እግዚአብሔርን ይታዘዙት እንደሆን ለመፈተኛ ነበር። 

ሰይጣን ከሔዋን ጋር ስለ እግዚአብሔር ትእዛዝ ሲነጋገር፥ “በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዟልን?” (ዘፍጥ. 3፡1) በማለት የተከለከለውን ነገር አሳሰባት። የጥያቄው አዝማሚያ እግዚአብሔር አንድን መልካም ነገር እንደደበቃቸውና ክልከላውንም ጭካኔ በማስመሰል ነበር። ሔዋንም ለእባቡ ጥያቄ ስትመልስ “በገነት ካለው ከዛፍ ፍሬ እንበላለን፥ ነገር ግን ሰገነት መካከል ካለው ከዛፉ ፍሬ፥ እግዚአብሔር አለ፥ እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ፥ አትንኩም” (ዘፍጥ. 3፡2-3) ብሏል አለች። 

ሔዋን በዚህ መልዕዋ ሰይጣን ውጥመድ ውስጥ ገባች። ከዚያን ወዲህ የሰው ዘር ሰሙሉ የእግዚአብሔርን መልካምነት የማቃለልና ጨካኝነቱን የማጋነን ዝንባሌ አደረበት። ሔዋን በንግግርዋ ጌታ የሰጠውን ታላቅ የማስጠንቀቂያ ትእዛዝ ለወጥ እንዳደረገች ሰይጣን ወዲያውኑ ተረዳና፥ “ሞትን አትሞቱም፥ ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ፥ እንደ እግዚአብሔርም መልካሙንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ” (ዘፍጥ. 3፡4-5) አላት። 

ሰይጣን ከሴቲቱ (ሔዋን) ጋር ባደረገው ውይይት ዋና አታላይነቱ ተገልጧል። እግዚአብሔር ትእዛዙን ከጣሱ ስለሚደርስባቸው ቅጣት የተናገረውን አቃሎ በመናገር፥ እግዚአብሔር ለአዳምና ሔዋን የሰጠውን ቃል ውሸት አስመስሎ አቀረበ። አዳምና ሔዋን የተከለከለውን ፍሬ በመብሳት ዓይኖቻቸው መከፈቱ፥ እንዲሁም መልካምና ክፉውን መለየታቸው እውነት ነው። መልካምና ክፉ የመለየቱን ኃይል የሚያገኙት መልካም የማድረግ ኃይል ሳይኖራቸው መሆኑን ግን ሰይጣን አልገለጠላቸውም። 

ዘፍጥረት 3፡6 ውስጥ የአዳምና የሔዋን ኃጢአት መውደቅ እንደሚከተለው ተመዝግቦ እናገኛለን፡- “ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደሆነ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ፤ ለጥበብም መልካም እንደሆነ አየች፤ ከፍሬውም ወሰደችና በላች፤ ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው፤ እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ”። ሔዋን ራሷ ወደ መረዳት ትድረስ ወይም ሰይጣን ያመልክታት መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ነገር የለም። 

ይህንኑ የሚመስሉትና 1ኛ ዮሐንስ 2፡16 ውስጥ በግልጥ የተጠቀሱት ሦስት የፈተና ሁኔታዎች እንደዚህ ተመልክተዋል። የፍሬው ለመብልነት መልካም መሆን የሚያመለክተው “የሥጋ ምኞትን”፥ የፍሬው ዓይን የሚስብ መሆን ደግሞ “የዓይን አምሮትን ሲያመለክቱ የፍሬው ጥበብን የመስጠት ኃይል ደግሞ “በሥጋ መመካትን” ይገልጣል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰተፈተነ ጊዜ፤ ሰይጣን ያቀረበላት ተመሳሳይ ፈተና ነበር (ማቴ. 4፡1-11፤ ማር. 1፡12-13፤ ሉቃስ 4፡1-13)። ሔዋን ፍሬውን በመብላትዋ ተታለለች፤ አዳም ደግሞ ምንም እንኳ በቀጥታ ባይታለል የእርስዋን አርአያነት ተከትሏል (1ኛ ጢሞ. 2፡14)። 

ለ. አዳም ከወደቀ በኋላ 

አዳምና ሔዋን ኃጢአት በሠሩ ጊዜ የተባረከ ሥፍራቸውን አጡ፥ ለተለያዩ ችግሮችም ተገዢ ሆኑ። 

1. ለሥጋዊና መንፈሳዊ ሞት ተዳረጉ። እግዚአብሔር ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትምታለሁ”(ዘፍጥ. 2፡17)፤ ብለው መሠረት መለኮታዊ ፍርዱ ተከናወነ። ወዲያውኑ መንፈሳዊ ሞት ሞቱ፤ ማለት ከእግዚአብሔር ተለዩ። ኃጢአታቸው ሥጋቸው እንዲያረጅና በኋላም ነፍሳቸው ከሥጋቸው እንዲለይ አደረገ። 

2. የእግዚአብሔር ፍርድ በሰይጣንም ላይ ነበር፤ እሳብም በምድር እንዲሳብ ተረገመ (ዘፍጥ. 3፡14)። በእግዚአብሔርና በሰይጣን መካከል የሚካሄደው ጦርነት ከሰው ዘር ጋር በተገናኘ ሁኔታ ዘፍጥረት 3፡15 ውስጥ እንዲህ ተገልጧል፡- “በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል፥ ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱም ራስህን ይቀጠቅጣል አንተም ሰኮናውን ትነክሳለህ”። ይህ የሚያመለክተው፥ በክርስቶስና በሰይጣን መካካል ይነሣ የነበረውን ውጊያ ሲሆን፥ ክርስቶስ በመስቀል ላይ መሞቱን፥ ነገር ግን “ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ” በተባለው መሠረት ሞት የማይዘው መሆኑን ነበር። የሰይጣን የመጨረሻ መሸነፍ የተጠቆመው፥ “የሴቲቱ ዘር ጭንቅላትህን ይቀጠቅጣል” በተባለ፥ ማለት በዘላለማዊ ሞት የሚቀጣው መሆኑ በተገለጠበት ክፍል ነው። ይህ የሴቲቱ ዘር የሚለው ቃል የሚያመለክተው፥ ሞትና ትንሣኤው ሰይጣንን ድል ያደረገውን ኢየሱስን 

ነው። 

3. በሔዋን ላይ ልዩ ፍርድ፥ ማለት ልጅ በምትወልድበት ጊዜ በከባድ ምጥና ሥቃይ እንዲሆን፥ እንዲሁም የሰሏ ተገዥ እንድትሆን ተፈረዶባታል (ዘፍጥ. 3፡16)። የሞት መኖር የሰውን ዘር መዋለድና መባዛት አስፈላጊ አድርጎታል። 

4 . በአዳም ላይ የተፈረደበት ልዩ ፍርድ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ እሾህና ኩርንችት በምታበቅለው ምድር ላይ ሠርቶ ከፊቱ ዝና ከድካሙ ፍሬ እንዲበላ ነበር። ተፈጥሮ እራሷ በሰው ኃጢአት ሳቢያ ተለውጣለች (ሮሜ 8፡22)። መጽሐፍ ቅዱስ በኋላ እንደገለጠው፥ ሰውን በተመለከተ በክርስቶስ የድነት ሥራ አማካይነት የኃጢአት ኃይል በከፊል የሚቃለል መሆኑና እርግማኑም በሚመጣው የሺህ ዘመን እንዲሁ በከፊል የሚሻር መሆኑ ታውቋል። አዳምና ሄዋን ከገነት ተባረው፥ ከዚያ ወዲህ የሰው ዘር ሁሉ ዕጣ የሆነውን ሐዘንና ትግል የሞላበትን ሕይውት ይኖሩ ጀመር። 

ሐ. የአዳም ኃጢአት በሰው ዘር ላይ ያመጣው ውጤት 

ኃጢአት በእዳምና በሔዋን ላይ ያስከተለው ውጤት መንፈሳዊ ሞትና ለዚያ ዓይነት ሞት ተገዢ መሆን ነበር። የቀድሞ ተፈጥሯቸው ተገፏል፤ በመሆኑም ከዚያ ወዲህ የሰው ዘር ሁሉ በኃጢአት ባርነት ይኖራል። መጽሐፍ ቅዱስ ከሰው ዕድልና ከአካባቢው መለወጥ በተጨማሪ፥ እግዚአብሔር አዳምን በኃጢአት ተጠያቂ ያደረገበትንና ትውልዱ የሆነውን የሰው ዘር እንዲሁ የኃጢአት ባለ ዕዳ ያደረገበትንም ጥልቅ ትምህርት ያቀርባል። 

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሦስት የመተላለፍ ዓይነቶች ተገልጠዋል፡- (1) የአዳም ኃጢአት ለዘሮቹ ተላልፏል (ሮሜ 5፡12-14)፥ (2) የሰው ሁሉ ኃጢአት ወደ ክርስቶስ ተላልፏል (2ኛ ቆሮ. 5፡21)። (3) የእግዚአብሔር ጽድቅ ወደሚያምኑበት ሁሉ ተላልፏል (ዘፍጥ. 15፡6፤ መዝ. 32:2፤ ሮሜ 3፡22፤ 4፡3፥ 8፥ 21-25፤ 2ኛ ቆሮ. 5፡21፤ ፊሊሞና 17፥ 18)። 

የሰው ኃጢአት፥ ወደ ክርስቶስ መተላለፉ ግልጥ ነው። እግዚአብሔር አምላክ የሁላችንንም በደል በእርሱ ላይ አኖረ (ኢሳ. 53፡5፤ ዮሐ. 1፡29፤ 1ኛ ጴጥ. 2፡24፤ 3: 18)። በተመሳሳይ መንገድ የእግዚአብሔር ጽድቅ በርሱ ወደሚያምኑ ሁሉ በፍርድ ይተላለፋል (2ኛ ቆሮ. 5፡21)። ከዚህ ሌላ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን የሚያስገኝ ወይም ለጽድቅ የሚያበቃ መንገድ የለም። ይህ የጽድቅ መተላለፍ እዲሱ ፍጥረት ውስጥ ባለ ግንኙነት ይገኛል። በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት አማካይነት ከጌታ ጋር በመገናኘት (1ኛ ቆሮ. 6፡17፤ 12፡13፤ 2ኛ ቆሮ. 5፡17፤ ገላ. 3፡27)፥ ደግሞ እንደ አካሉ አባልነት ከክርስቶስ ጋር ይገናኛል (ኤፌ. 5፡30)። በዚህም የክርስቶስ የሆነ ጸጋ፥ አካሉ ወደሆኑ ሁሉ ይተላለፋል። አማኝ “ክርስቶስ ውስጥ” ስለሆነ የክርስቶስ የሆነውን ሁሉ ይጋራል። 

ማንኛውም ሰው ሲወለድ አዳማዊ ባሕርይ በውስጡ አለ። ስለዚህም በአዳም የነበረው አሮጌ ተፈጥሮ ወደ እርሱ ይተላለፋል። እንዲህ ያሉ ሰዎች አዳማዊውን ተፈጥሮ ስለሚወርሱ የአዳም ኃጢአት አለባቸው ይባላሉ። ይህ የሚያመለክተው፥ የአዳም ኃጢአት ለዘሩ ሁሉ የሚተላለፈው በመለኮታዊ ፍርድ እውነትነት መሠረት መሆኑን ነው። የእግዚአብሔርም ጽድቅ በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ላቅድስና ላሰው ሁሉ ይተላለፋል። ሰዎች እንደ አዳም በደሉም እልበደሉ ከእዳም የተላለፈ ኃጢአት ስላለባቸው ከመለኮታዊው ፍርድ በታች ናቸው። 

ምንም እንኳን ሰዎች እንደ ልማዳቸው አዳም ለሠራው ኃጢአት ተጠያቂ አይደለንም ቢሉ፥ መለኮታዊው መገለጥ የሚያመለክተው ግን፥ የሰው ዘር ሁሉ መጀመሪያ የሆነው አዳም ስለሆነና ሰው ሁሉ በቀጥታ ከእርሱ ስለተገኘ እግዚአብሔርም በእርሱ (በአዳም) መተሳሰፍ የተነሣ ዘሩን በሙሉ በኃላፊነት የሚጠይቅ መሆኑን ነው። የአዳም ኃጢአት ያለምንም ልዩነት በሰው ሁሉ ላይ በቀጥታ ሞት አስፈርዶበታል (ሮሜ 5፡12-14)። በዚህ ሁኔታ የአዳም ውድቀት፥ ማለት የመጀመሪያው ኃጢአቱ በኃጢአታዊ ተፈጥሮነት ለትውልድ ሁሉ ከአባት ወደ ልጅ ይተላለፋል። የውድቀቱ ውጤት ሁለንተናዊ ነው፥ መለኮታዊ ጸጋም እንዲሁ። 

ሰዎች አሁን የወደቁት፥ መጀመሪያ በሠሩት ኃጢአት ምክንያት ሳይሆን፥ በኃጢአት ከወደቀው እዳም በመወለዳቸው ነው። ኃጢአት በመሥራታቸው ኃጢአተኞች አይሆኑም፤ ነገር ግን በተፈጥሯቸው ኃጢአተኞች ስለሆኑ ኃጢአት ይሠራሉ። ማንኛውም ሕጻን መልካም እንዲሆን እንጂ፥ ኃጢአት የመሥራት ትምህርት አያስፈልገውም። 

በአዳም ኃጢአት ምክንያት የሰው ዘር ሁሉ ተጠያቂ ቢሆንም፥ ሕጻናትንና በኃላፊነት ለመጠየቅ ብቁ ላልሆኑት ሰዎች ግን የእግዚአብሔር መለኮታዊ ጸጋ እንደተዘጋጀላቸው ሊታወቅ ይገባል። የእግዚአብሔር ቅዱስ ፍርድ የሚያርፈው ከክርስቶስ ውጭ በሆኑት ሁሉ ላይ ነው። ይህ የሚሆነው፡- (1) ከአዳም ከተላለፈባቸው ኃጢአት የተነሣ፥ (2) ከወረሱት ኃጢአታዊ ተፈጥሮ የተነሣ፥ (3) ከኃጢአት በታች በመሆናቸው፥ 4. ራሳቸውም ከሚሠሩት ኃጢአት የተነሣ ነው። 

ይህ የእግዚአብሔር ቅዱስ ፍርድ ቢኖርም፥ ኃጢአተኛው በክርስቶስ በኩል ሊድን ይችላል። ይህ ነው የወንጌል የምሥራች። 

በአሮጌው ሰው ላይ የሚያርፉት ቅጣቶች፡- (1) አካላዊ ሞት፥ ማለት የነፍስ ከሥጋ መለየት፥ (2) መንፈሳዊ ሞት፥ ልክ እንደ አዳም ሁሉ በአሁኑ ጊዜ ያልዳነ ሕዝብ ነፍስ ከእግዚአብሔር የተሰየችና የጠፋች ናት (ኤፌ. 2፡1፤ 4፡18፥ 19)፥ (3) ሁለተኛው ሞት፥ ማለት የነፍስ ለዘላለም ከእግዚአብሔር መለየትና ለዘላለም መወገድ (ራእይ 2፡11፤ 20፡6፥ 14፤ 21፡8)።

ምንጭ፡- “ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጦች” መጽሐፍ በዶክተር ሉዊስ ስፔሪ ቼፈር የተጻፈ እና በተክሉ መንገሻ የተተረጎመ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ቅዱሳን ድንቅ ስራ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ማሳሰቢያ፡- ይህን ጽሁፍ መቀየርም ሆነ ለሽያጭ ማዋል በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: