ስለ ለይጣን ትምህርት

ሰይጣን አለን? 

ስለ መላእክት ሕልውና መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ለማይቀበል ሰው፥ የሰይጣንን መኖር ማረጋገጡ የዚያኑ ያህል ያስቸግር ይሆናል። ማስረጃው ግን አይገድም፤ የተትረፈረፈ ነው። 1. በስፋት ተገልጧል (ቢያንስ በብሉይ ኪዳን ሰባት መጻሕፍትና በአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ሁሉ ተጠቅሷል)። 2. በራሱ በክርስቶስ ቃል ላይ የተመሠረተ ነው (ማቴ. 13፡39፤ ሉቃስ 10፡18፤ 11፡18)። ክርስቶስ እነዚህን ቃላት የተናገረው የእምነት መሀይምናን ለሆኑ ሰዎች እንዳልሆነ ከነበረው ሁኔታ እንረዳለን። 

ሰይጣን ምን ይመስላል? 

ሰይጣን አካል ያለው ፍጡር ነው። ሰይጣን በእርግጥ እውቀት እንዳለው (2ኛ ቆሮ. 11፡3)፥ ስሜት እንዳለው (ራእይ 12፡17)፥ ፈቃድ እንዳለው (2ኛ ጢሞ. 2፡26) ላይ ተጠቅሷል። በእግዚአብሔር ዘንድም አካል እንዳለው ፍጥረት እና ለሚያደርገው ተግባርም ተጠያቂ እንደሚሆን እንጂ፥ እንደ ግዑዝ ነገር አይደለም የሚታየው (ማቴ. 25፡41)። 

ሰይጣን ፍጡር እንጂ ፈጣሪ አይደለም (ሕዝ. 28፡14)። ስለሆነም እግዚአብሔር ብቻ ያለው ባሕርይ፥ ለምሳሌ በሁሉ ስፍራ የመገኘት፥ ሁሉን የማወቅ፥ ሁሉን የማድረግ ተፈጥሮ የለውም። ውሱን ተፈጥሮ ነው ያለው። ያም ሆኖ ተፈጥሮው ከሰው ይልቃል። ፍጡር በመሆኑም ፈጣሪ ውሱን ሊያደርገው እንደሚችልና እንዳደረገውም በተደጋጋሚ ታይቷል (ኢዮብ 1፡12)። 

ሰይጣን መንፈስ የሆነ ፍጡር ነው። ኪሩቤል ከተባሉት የመላእክት ወገን ነበር (ኤፌ. 6፡11-12፤ ሕዝ. 28 ፡14)። ከተፈጠሩት መላእክት ሁሉ ከፍተኛው ነበር (ሕዝ. 28፡12)፤ ይህም በመሆኑ ከውድቀቱ በኋላ እንኳን ከፍተኛ ኃይል አለው (“የዚህ ዓለም አምላክ”፥ 2ኛ ቆሮ. 4፡4፥ ተብሎ መጠራቱንና፥ “በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ” መባሉን፥ ኤፌ. 2፡2 ያስተውሉ)። 

ሰይጣን የእግዚአብሔርና የሕዝብ ጠላት ነው። የስሙ ትርጉም ራሱ ባላጋራ ማለት ነው (1ኛ ጴጥ. 5፡8)። ዲያቢሎስ ማለት ደግሞ ከሳሽ ማለት ነው (ራእይ 12፡10)። እኩይ ባሕርያቱ በመጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ ቦታዎች በተጠቀሱት ስሞቹ ተገልጠዋል። ክፉ (1ኛ ዮሐ. 5፡19)፥ ፈታኝ (1ኛ ተሰ. 3፡5)፥ ነፍሰ ገዳይ (ዮሐ. 8፡44)፥ ሐሰተኛ (ዮሐ. 8፡44)፤ የታወቀ ኃጢአተኛ (1ኛ ዮሐ. 3፡8) የሚሉ ስያሜዎች ተሰጥተውታል። የጠላትነት ተግባሩን ለማከናወንም በእባብ መልክ (ራእይ 12፡9)፥ በቁጡ ዘንዶ መልክ (ራእይ 12፡3)፥ በሚማርክ የብርሃን መልአክ አምሳያ (2ኛ ቆሮ. 11፡14) ይታያል። እነዚህን ሁሉ ችሎታዎቹን ለዕቅዱ ማከናወኛ በማታለያነት ይጠቀምባቸዋል። 

የሰይጣን ኃጢአት ምን ነበር? 

ሰይጣን ኃጢአት የፈጸመው ክብርና ሥልጣን በነበረው ወቅት ነው። ኃጢአት ከማድረጉ በፊት የእግዚአብሔር በረከት ተሳታፊ ነበር። ሕዝቅኤል 28፡11-15 ሰይጣን ኃጢአትን ሲፈጽም የነበረበትን አሰደናቂ የክብር ስፍራ ይገልጥልናል። የምንባቡ ክፍል የሚያስረዳው ስለ ሰይጣን እንጂ፥ ከአሕዛብ ስለፈለቀና የተጋነነ የምሥራቃውያን አፈ ታሪክ ወይም ተረት እንዳልሆነ ግልጥ ከሆኑት ቃላቱ መረዳት ይቻላል። ሕዝቅኤል የጢሮስ ንጉሥ በተለያየ መንገድ የቀዳውን የሰይጣን የተንኮል ሥራ እና እንቅስቃሴ ነበር ያየው። ሰይጣን ከነበሩት መብቶች መካከል፡- 1. የላቀ ጥበብ (ቁ. 2)፥ 2. ፍጹም ውበት (ቁ. 2)፥ 3. ያማረ መልክ (ቁ. 3)፥ 4. እንደተቀባ ኪሩብ በመሆን የእግዚአብሔርን ዙፋን በመሸፈን ልዩ ስፍራ ማግኘቱ ይገኙበት ነበር። የተቀባ ኪሩብ (ቁ. 14) መሆኑም ዋናው ነገር ነበር። ቁጥር 15 ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኃጢአት መነሻ የሚገልጠውን በመጥቀስ “በደል እስከተገኘብህ ድረስ” በማለት ይናገራል። ይህ አባባል ሰይጣን ፍጹም ሆኖ የተፈጠረ እንደነበር ያመለክታል። ለውድቀቱ መነሻ የሆነውን ኃጢአት እንዲሠራ እግዚአብሔር አላስገደደውም፤ በራሱ ፈቃድ ለፈጸመው ድርጊት ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ ነው። ምክንያቱም ከተሰጠው ሥልጣንና መብት አኳያ ሲታይ ኃጢአት የፈጸመው በሙሉ እውቀቱ እንደሆነ ግልጥ ነውና። 

የሰይጣን ኃጢአት ትዕቢት ነበር (1ኛ ጢሞ. 3፡6)። ይህ ትዕቢት እንዴት እንደገነፈለ በኢሳይያስ 14፡13-14 በዝርዝር የተገለጠ ሲሆን፥ “በልዑል እመሰላለሁ” (ቁ. 14) ማለቱ ትዕቢቱን ያጎላዋል። 

ሰይጣን ተፈርዶበታል፥ ወይስ ገና ይፈረድበታል? 

ሰይጣን ተፈርዶበታል፥ እንደገናም ይፈረድበታል። የተወሰኑበት ወይም የሚወሰኑበት ስድስት ፍርዶች አሉ። 1. ከሰማያዊ ማዕረጉ ተሽሯል (ሕዝ. 28፡16)፤ 2. አዳምንና ሔዋንን ከፈተነ በኋላ ተፈርዶበታል (ዘፍጥ. 3፡14-15)፤ 3. ማዕከላዊው ፍርድ የተከናወነው (የሌሎቹም ፍርዶች መሠረት ነውና) በመስቀል ላይ ነበር (ዮሐ 12፡31)፤ 4. በፍዳ ዘመን ወደ ሰማይ ከመውጣት ይታገዳል (ራእይ 12፡13)፤ 5. በሺህ ዓመቱ ግዛት መጀመሪያ ላይ ታሥሮ በጥልቁ ውስጥ ይጣላል (ራእይ 20፡2)፤ 6. በሺህ ዓመቱ አገዛዝ መጨረሻ ለዘላለም ወደ እሳት ባሕር ይጣላል (ራእይ 20፡10)። 

ሰይጣን ምን ያደርጋል? 

የሰይጣን ዓላማ በየትኛውም ቦታና በማንኛውም መንገድ የእግዚአብሔርን ዕቅድ ማጣመም ወይም ማደናቀፍ ነው። ይህን ለማከናወንም አለቃ በሆነበት ዓለም የራሱን ሥርዓት መሥርቶ የእግዚአብሔርን ገዥነት ለመቃወምና ለመቀናቀን ይጥራል። ይህን የሚያደርገው ግልጥና ተቃራኒ የሆነ መንግሥት በማቋቋም ሳይሆን፥ የእግዚአብሔርን ዕቅድ በማስመሰል ነው። 

1. በክርስቶስ የቤዛነት ተግባር ወቅት በመስቀሉ ላይ ሳይሰቃይ ቤዛ የሚሆንበትን አማራጭ በማቅረብ ጌታን ፈተነው (ማቴ. 4፡1-11 እንዲሁም ማቴ. 2፡16፥ ዮሐ. 8፡44፥ ማር. 16፡23 እና ዮሐ. 13፡27 ላይ የክርስቶስን ዓላማ ለማክሸፍ ያደረጋቸውን ሙከራዎች ይመልከቱ)። 

2. የዓለም መንግሥታትን በተመለከተ፥ እግዚአብሔር ብቻ የሚያደርገውን እነርሱም ማድረግ እንደማይሳናቸው በማሳየት ያታልላቸዋል (ራእይ 20፡3)። በፍዳ ዘመን መጨረሻ ላይም ወደ አርማጌዶን ለጦርነት ያስከትታቸዋል (ራእይ 16፡13-14)። 

3. የማያምኑ ወገኖች ወንጌልን እንዳይቀበሉ አእምሯቸውን ያሳውረዋል (2ኛ ቆሮ. 4፡4)። ይህን የሚያደርገው ማንኛውም መንገድ ወደ መንግሥተ ሰማያት ያደርሳል የሚለውን አሳብ በማሳየት ነው። የእግዚአብሔር ቃል ሲዘራም፥ እያደባ ከሰዎች ልብ ይለቅማል (ሉቃስ 8፡12)። 

4. እንዲዋሽ አማኙን ይፈትነዋል (ሐዋ. 5፡3)። በሐሰት ይከሰዋል (ራእይ 12፡10)፤ ለእግዚአብሔር እንዳይሠራ ያደናቅፈዋል (1ኛ ተሰ. 2፡18)፤ ክርስቲያንን ለማሸነፍ በአጋንንቱ ይጠቀማል (ኤፌ. 6፡11-12)፤ በኃጢአት እንዲወድቅ ይፈትነዋል (1ኛ ቆሮ. 7፡5)፤ አማኞችን ለማታለል መካከላቸው እንክርዳድ ይዘራል (ማቴ. 13፡38-39)፤ አንዳንዴም ስደት ያስነሳባቸዋል (ራእይ 2፡10)። ከነዚህ ሌላ ክርስቲያን እውነተኛውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ትቶ አስመሳይ ዕቅድ እንዲከተል ያደርገዋል። የሚቻል ከሆነም ማታለሉ እንዳይነቃበት “ደግ” ማድረግን ይጨምራል (ፍጹም መልካሙን አይደለም)። ሆኖም አንዳንዴ ዕኩይ ተግባራትን ያከናውናል። 

አማኝ ከሰይጣን ጥቃት ራሱን የሚከላከለው እንዴት ነው? 

1. አዲስ ኪዳን፥ ሁለት ቦታዎች ላይ ጌታ በሰማይ ሆኖ ለሕዝቡ እንደሚማልድ ይናገራል (ሮሜ 8፡34፤ ዕብ. 7፡25)። ይህ ምልጃ አብ ልጆቹን ከክፉ ሁሉ እንዲጠብቅለት መጠየቅን ይጨምራል (ዮሐ. 17፡15)። 

2. እግዚአብሔር አንዳንዴ ለአማኙ የተለየ ትምህርት ለመስጠት በሰይጣን እንደሚጠቀምም ማስተዋል ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን የክርስቲያኑ መከላከያ እግዚአብሔር የሚያስተምረውን በሚገባ መረዳት ይሆናል። ይህ ነበር በኢዮብና በጳውሎስ የደረሰው (2ኛ ቆሮ. 12፡7-10)። 

3. ስለ ሰይጣን ተገቢ የሆነ አመለካከት ሊኖረን ይገባል። የእግዚአብሔር ኃይል ከእኛ ወገን ቢሆንም፥ ወዲያውኑ ድል እናገኛለን ብሎ ማሰብ ብልህነት አይደለም። የሰይጣንን ኃይል አቃለው አይናገሩ፥ ይልቁንም በጌታ ድል መታመንን ይማሩ (ይሁዳ 8-9)። 

4. አማኝ ስለ ሰይጣን አሠራር ማወቅ አለበት፥ መጠንቀቅም ይገባዋል (1ኛ ጴጥ. 5፡8)። 

5. ቆራጥ አቋም ሊኖረው ይገባል (ያዕ. 4፥7)፤ ይህን አቋም በጠላታችን ላይ ለምናደርገው ቀጣይ ጦርነት እንደ ውጊያ ምሽግ ልንጠቀምበት ይገባል። 

6. እግዚአብሔር መከላከያ የጦር ዕቃ ሰጥቶናል (ኤፈ. 6፡11-18)። እያንዳንዱ ትጥቅ በጣም ጠቃሚና ለተለየ ዓላማ የሚውል ነው። ስለዚህ በተሰጠን የጦር ዕቃ በመጠቀም ራሳችንን መከላከል አለብን።

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading