ቤተ ክርስቲያን መቼ ተጀመረች?

የሥነ-መለኮትን ትምህርት የሚከፋፍለው መሠረታዊ ጥያቄ፥ ቤተ ክርስቲያን መቼ ተጀመረች? የሚለው ነው። “የቃል ኪዳን ሥነ-መለኮት [Covenant Theolog/ኮቨናንት ቲያሎጂ] የተሰኘው የትምህርት ክፍል፣ ቤተ ክርስቲያን በብሉይ ኪዳን (በተለይ በአብርሃም) ተጀምራ ለዘላለም ቀጥላለች ይላል። በዚህ አመለካከትና ትምህርት መሠረት፥ ዓለም አቀፋዊቷ ቤተ ክርስቲያን በየዘመናቱ የነበሩትን አማኞች ሁሉ ይዛለች (ቢያንስ ከአብርሃም) ጀምሮ። ሌሎች ቡድኖች ደግሞ ቤተ ክርስቲያን በመጥምቁ ዮሐንስ ጊዜ ተጀመረች ይላሉ። ለዚህም የሚያቀርቡት የመከራከሪያ ነጥብ ሰዎችን በማጥመቅ የመጀመሪያው ዮሐንስ ስለሆነና (ሌሎች የአይሁድ ጥምቀቶች ራስ በራስ ነበር የሚካሄዱት) ጥምቀት ቤተ ክርስቲያንን ከሌሎች ድርጅቶች የሚለያት መታወቂያ በመሆኑ ነው የሚል ነው። የሦስተኛው ቡድን አባላት ደግሞ፥ ቤተ ክርስቲያን በበዓለ አምሳ ዕለት የተጀመረች መሆኗን ያስተምሩና፥ አባላቷም ከዚያን ዕለት ጀምሮ እስካሁን ያሉት አማኞች ናቸው ይላሉ። ሌሎቹ ደግሞ፥ የክርስቶስ አካል የሆነችው ቤተ ክርስቲያን፥ ጳውሎስ አገልግሎት ከጀመረ በኋላ ተመሠረተች ይላሉ (ይህም ጳውሎስ ጌታን ባወቀ ጊዜ፥ በመጀመሪያው ሐዋርያዊ ጉዞው፥ ወይም በሮሜ የመጀመሪያ እሥራቱ ሊሆን እንደሚችል ነው፡- ማለት በሐዋርያት ሥራ 9፡13 ወይም 28 መሠረት)። ከዚያ በፊት ግን (ከበዓለ አምሳ እስከ ሐዋ. 9፣ 13፥ ወይም 28) የነበረችው የአይሁድ ቤተ ክርስቲያን እንጂ፥ የክርስቶስ አካል የሆነችው ቤተ ክርስቲያን አይደለችም ይላሉ። በእርግጥ ይህ እጅግ ወሳኝና የሚከፋፍል ጥያቄ ነው። 

በዓለ አምሳ የቤተ ክርስቲያን መጀመሪያ ዕለት መሆኑን የሚከተሉት ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ። 

1. ጌታ በማቴዎስ 16፡18 ላይ ቤተ ክርስቲያን ገና ወደፊት የምትመሠረት መሆኗን ተናገረ። በብሉይ ኪዳን ጊዜ ቤተ ክርስቲያን እንዳልነበረች ይህ ያሳያል። 

2. የክርስቶስ ትንሣኤና ዕርገቱ ለቤተ ክርስቲያን ተግባራዊነት አስፈላጊ ነበሩ። የተመሠረተችው በትንሣኤው ላይ ነው (ኤፌ. 1፡19-20)። ለሥራዋም የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ያስፈልጓት ነበር። ስጦታዎችን ይልክ ዘንድ ክርስቶስ ማረግ ነበረበት (ኤፈ. 4፡7-12)። ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው ከክርስቶስ ዕርገት በፊት ቢሆን ኖሮ ለተግባራዊነቷ አስፈላጊ የሆነው መሠረትና ኃይል ሊኖራት አይችልም ነበር። የቤተ ክርስቲያን ህልውናም ሆነ ተግባር የተመሠረተው በክርስቶስ ትንሣኤና ዕርገት ላይ መሆኑ ቤተ ክርስቲያንን እስካሁኑ ዘመን ድረስ ልዩ ያደርጋታል። 

3. ቤተ ክርስቲያን በበዓለ አምሳ ዕለት መመሥረቷን የሚያረጋግጥልን ዋና ማስገንዘቢያ ግን የመንፈስ ቅዱስ የማጥመቅ ሥራ ነው። ጌታ ከማረጉ በፊት ይህ ልዩ የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ወደፊት የሚከናወን መሆኑን አመልክቷል (ሐዋ. 1፡5)። በበዓለ አምሳ ዕለትም ለመጀመሪያ ጊዜ ተከናወነ (በሐዋርያት ሥራ 2 ላይ ያለው ጽሑፍ ይህን አይልም፤ በሐዋርያት ሥራ 11፡15-16 ያለው ግን ይናገራል)። ይህ የመንፈስ ጥምቀት ሥራ ምን ያደርጋል? የዚህ መልስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 12፡13 ላይ የሚገኝ ሲሆን ይህም እማኙን በክርስቶስ አካል ውስጥ የማኖር ተግባር ነው። ወደ ክርስቶስ አካል ለመግባት ይህ ብቸኛው መንገድ መሆኑ (በመንፈስ ቅዱስ የማጥመቅ ሥራ) እና እንዲሁም የመንፈስ ቅዱስ ሥራ በመጀመሪያ የተከናወነው በሰዓለ አምሳ ዕለት ስለሆነ ከዚህ ተነስተን የክርስቶስ አካል የሆነችው ቤተ ክርስቲያን በበዓለ አምሳ ዕለት ተጀምራላች ወደሚለው ድምዳሜ ልንደርስ እንችላለን። 

መቼ ነው ቤተክርስቲያን ከፍጻሜ የምትደርሰው? 

የክርስቶስ አካል የሆነች ቤተ ክርስቲያን በበዓለ አምሳ ዕለት ከተጀመረች ፍጻሜዋ ጌታ ወደ ራሱ በሚጠራት ወይም በመነጠቅ ጊዜ ይሆናል። ይህ ማለት ግን፥ ከዚያ በኋላ የሚድኑ ሰዎች አይኖሩም ማለት አይደለም። ልክ ከበዓለ አምሳ በፊት የተዋጁ እስራኤላውያን እንደነበሩ ሁሉ፥ ከቤተ ክርስቲያን መነጠቅ በኋላም የሚዋጁ ይኖራሉ። ይህ በከራው ዘመን እና በሺህ ዓመት ግዛት፥ በሁለቱም ጊዜ ይሆናል። እነዚህ አማኞች ምንም እንኳን የተዋጁና በመንግሥተ ሰማያት ቦታ ያላቸው ቢሆንም፥ የክርስቶስ (የቤተ ክርስቲያን) አካል የሆኑ አይመስልም፡፡

በግልጥ እንደተነገረን ሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም የመላእክት፥ የቤተ ክርስቲያን፥ የእግዚአብሔር፥ የኢየሱስ እና “የጻድቃን ነፍሳት” (የብሉይ ኪዳን ቅዱሳንን የሚያመለክት ይመስላል) መኖሪያ ነች። አሳቡ የሚያመለክተው የተለያዩ አማኝ ወገኖች በሰማይ እንደሚገኙ ነው። ፍጻሜውና መድረሻው አንድ ቢሆንም እንኳን፥ ልዩነቱ እንደተጠበቀ ይሆናል። 

ጎልቶ የሚታየው ሌላ ጉዳይ ደግሞ፥ በመከራው ዘመንም ሆነ በሺህ ዓመቱ ግዛት ወቅት፥ የመንፈስ ቅዱስ የማጥመቅ ተግባር አለመጠቀሱ ነው። ይህም የክርስቶስ አካል የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ፍጻሜ፥ የፍዳው ዘመን ከመጀመሩ በፊት እንደሚሆን ያመለክታል።

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: