ክርስቲያኖች በጌታ እራት ላይ ያላቸው የግንዛቤ ልዩነት

ሁሉም ክርስቲያኖች የጌታ እራት አስፈላጊና ኢየሱስን በመታዘዝ ሊያደርጉት የሚገባ መሆኑን ያምናሉ። አብዛኞቹም «የጌታ እራት ምን ማለት ነው?» ለሚለው ጥያቄ የተሰጡትን አሥር ነጥቦች ያምኑባቸዋል። ይሁን እንጂ የጌታን እራት መረዳታችንና ልምምዳችን በቤተ እምነቶች መካከል ይለያያል። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ይህ ልዩነት አንዳንድ ጊዜ ቤተ ክርስቲያንን ወደሚጎዳ መከፋፈል ያደርሳል። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና ስለ ጌታ እራት ምን እንደሚያስተምር መረዳት አስፈላጊ ቢሆንም፥ ከእኛ የተለየ አመለካከት ያላቸውን ማቃለል ግን ተገቢ አይደለም። እንዲያውም፥ ይህ አመለካከት «ሳይገባን» የጌታን እራት ወደ መብላት ይመራናል። በሚያለያየን ላይ ከማትኮር ይልቅ፥ በሚያስማማን ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባናል። 

በክርስቲያን ቤተ እምነቶች መካከል ያሉ ዋና ዋናዎቹ ልዩነቶች ምንድን ናቸው? 

ሥርዓቱ ሲካሄድ እንጀራውና ወይኑ ምን ይሆናል በሚለው ላይ የክርስቲያኖች እምነት ይለያያል። ኢየሱስ «ይህ ሥጋዬ ነው» እንዲሁም «ይህ ደሜ ነው» ሲል ምን ማለቱ ነበር? 

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ እንደምናየው ሰዎች ይህን የኢየሱስ ዓረፍተ ነገር በአራት የተለያዩ መንገዶች ተረድተውታል። 

ሀ) የሮማ ካቶሊክና የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ይህን የኢየሱስ ዓረፍተ ነገር የሚረዱት ቃል በቃል ነው። ስለዚህ ካህኑ ሲጸልይ ቁራሹ እንጀራና ወይኑ በተአምር ወደ ትክክለኛው የኢየሱስ ሥጋና ደም ይለወጣል ብለው ያስተምራሉ። ኅብስቱ የክርስቶስ ሥጋ ይሆናል። ወይኑም የኢየሱስ ደም ይሆናል። ይህን በሚበሉበት በእያንዳንዱ ወቅት ኢየሱስ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ሆኖ ይሞታል ማለት ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች የጌታን እራት ማን መስጠት እንዳለበት ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያደርጉትም ከዚህ የተነሣ ነው። ሕብስቱና ፅዋው የተዘጋጁባቸው ነገሮች እንዲለወጡ ለማድረግ ሥልጣን ያለው ካህኑ ብቻ ነው። ስለዚህም ነው የጌታን እራት መውሰድ የኃጢአት ይቅርታ ያስገኛል የሚሉት። ምእመኑ በግሉ ሊያደርግ ስለሚገባው ዝግጅት ትኩረት አይሰጡም። ይልቁንም፥ ተቀባዩ ባይዘጋጅም እንኳን ሥጋውና ደሙ እማኙን የመለወጥ ኀይል አላቸው ይላሉ። የኦርቶዶክስና የካቶሊክ ክርስቲያኖች የጌታን እራት በመውሰድ ጉዳይ ላይ የሚለያዩት ኅብስቱ እርሾ የሌለበት ይሁን ወይም እርሾ ያለበት ይሁን በሚለው ነው። 

ለ) የመካነ ኢየሱስና የሉተራን ክርስቲያኖችም የኢየሱስን ዓረፍተ ነገር የሚረዱት ቃል በቃል ነው። ይሁን እንጂ፥ አካላዊ ነገሩ እንደሚለወጥ ወይም ሁልጊዜ ሥጋ ወደሙ ሲበላ፥ ኢየሱስ ዴጋግሞ እንደሚሞት አያምኑም። ከዚህ ይልቅ፥ የኢየሱስ ሥጋና ደም ኅብስትና ወይኑን ምሥጢራዊ በሆነ መንገድ ይከብበዋል ይላሉ። በሆነ መንገድ የኢየሱስ ሥጋ ኅብስቱ ውስጥ ሲኖር፥ ደሙም ከወይኑ ውስጥ ይገኛል። ክርስቲያኖች ይህን ነገር ሲበሉ መንፈሳዊ ዝግጅት ካደረጉ በተለየ መንገድ ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ያደርጋሉ። ኃጢአታቸው ይቅር ይባላል፥ በኢየሱስ ላይ ያላቸው እምነትም እንደገና ይረጋገጣል። በመካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ቁርባን በተገቢው መንገድ እንዲሰጥ የቄሱ መገኘት አስፈላጊ ነው። 

ሐ) የፕሬስቢቴሪያን ቤተ ክርስቲያን፥ በኢትዮጵያ ውስጥ የመካነ ኢየሱስ ክፍል የሆኑት (ቤቴል ሲኖድ) ሲሆኑ፥ የኢየሱስን ዓረፍተ ነገር በተለየ መንገድ ነው የሚረዱት። ሕብስቱና ፅዋው የተዘጋጀበት ነገር ትክክለኛው የኢየሱስ ሥጋና ደም መሆኑን አያምኑም። ሥጋና ደሙም በሆነ መንገድ ከሕብስቱና ፅዋው ጋር ይቀላቀላሉ ብለው አያምኑም። ይልቁንም፥ ክርስቲያኖች ሕብስቱንና ፅዋውን ሲወስዱ፥ ኢየሱስ በመንፈስ ሊገናኛቸው እንደሚመጣ ያስተምራሉ። መንፈስ ቅዱስ ከኢየሱስ ጋር እንዲተባበሩ ይረዳቸዋል። ተቀባዮቹ መንፈሳዊ ዝግጅት ካደረጉ፥ መንፈሳዊ እድገት እንዲያገኙ መንፈስ ቅዱስ ይረዳቸዋል። ከሌሉቹ ጊዜያት በበለጠ፥ በኢየሱስ ሞት ምክንያት ይቅር እንደተባሉ መንፈስ ቅዱስ ያረጋግጥላቸዋል። በእግዚአብሔር ፍቅር እንደታተሙ ሲያስገነዝባቸው፥ የኪዳኑ ቃል ወራሾች እንደመሆናቸውም መጠን፥ ኢየሱስ ቃል የገባላቸውንም በረከቶች ይቀበላሉ። አማኞችም ኢየሱስን ለመከተል በድጋሚ ራሳቸውን ሲያቀርቡ እንደ አዳኛቸውና ጌታቸው ሊታዘዙት ቃል ይገባሉ። 

መ) በኢትዮጵያ አብዛኞቹ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት (ለምሳሌ፡- ቃለ ሕይወት የሕይወት ብርሃን፥ ሙሉ ወንጌል) የኢየሱስ ቃላት በምሳሌያዊነት መወሰድ እንዳለባቸው ያምናሉ። የተቆረሰው ኅብስት የተወጋውን የኢየሱስን አካል ይወክላል። ወይኑም የፈሰሰውን የኢየሱስን ደም ይወክላል። ኢየሱስም እነዚህ ምሳሌዎችና ሥርዓት የሰጠን ስለ እኛ ብሎ መሞቱን እንድናስታውስ ነው። እምነታችን ኢየሱስ በመስቀል ላይ ስለ እኛ ባደረገው ነገር ላይ መሆኑን እንድናስታውስ የሚረዳን የማስተማሪያ መሣሪያ ነው። እራሳችንን እንድንመረምርና ኢየሱስን ለመከተል እንደገና ራሳችንን እንድንሰጥ ያግዘናል። የጌታ እራት ሥርዓት ለእኛ ጥቅም እንዲሆን ካስፈለገ፥ መንፈሳዊ ዝግጅት ያስፈልገናል። 

እንግዲህ ትክክለኛው አመለካከት የቱ ነው? ሁሉም የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት በጌታ እራት ከሮም ካቶሊክና ከኦርቶዶክስ እመለካከት ጋር በተለያየ ምክንያቶች አይስማሙም። አንደኛ፥ በየጊዜው የጌታ እራት ሥርዓት ሲከበር ኢየሱስ ለሕዝቡ ኃጢአት እንደገና ይሞታል በሚለው አይስማሙም። ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሲሞት «ተፈጸመ» ብሎ ጮኾአል (ዮሐ 19፡30)። ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሰው መንገድ በቋሚነት ተከፍቷል። ኢየሱስ እንደገና ለመሥዋዕትነት መሞት የለበትም። ዕብ 9፡5-28 እና 10፡10-14 ኢየሱስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መሞቱን ያስተምራል። ሁለተኛ፥ ሥጋ ወደሙ መብላት ኃጢአትን እንደሚያስተሰርይ አዲስ ኪዳን አያስተምርም። ይልቁንም ተቀባዩ ኢየሱስ በምትኩ እንደሞተ በግል እምነት ሊኖረው እንደሚያስፈልግ ያስተምራል። እያንዳንዱ ሰውም ለኃጢአቱ ይቅርታ ለማግኘትና በሕይወቱ እግዚአብሔርን እያስከበረ መኖር እንዲችል ለውጥ እንዲኖረው እግዚአብሔርን ሊጠይቅ እንደሚያስፈልግ ያስተምራል። ሦስተኛ፥ ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት እንጀራውና ወይኑ ሥጋውና ደሙ መሆኑን ተናግሮ ነበር። «ይህ እንጀራና ወይን በቅርቡ (የወደፊት ጊዜ) ደኅንነታችሁን የሚያመጣ ሥጋዩና ደሜ ይሆናል» ብሎ አልተናገረም። የኢየሱስን ቃል እንዳለ መውሰድ ቢያስፈልግ ኖሮ ማለት የነበረበት ያንን ነበር። በምትኩ ግን፥ «ይህ ሥጋዩ ነው» እና «ይህ ደሜ ነው» (የአሁን ጊዜ) የሚሉትን ቃላት ነበር የተጠቀመው። ይህም ቃሉን እንዳለ ሳይሆን፥ በምሳሌያዊነቱ እንድንረዳው ያስገነዝበናል። አራተኛ፥ የኢየሱስን አባባል ቃል በቃል መረዳቱ የኢየሱስ ቃላት በብሉይ ኪዳን ውስጥ ካለው ከእግዚአብሔር ግልጽ ትእዛዛት ጋር እንዲቃረኑ ያደርጋል። በዚያም አይሁዶች ደም በጭራሽ እንዳይጠጡ ተነግሮአቸው ነበር (ዘሌዋ. 17፡10-16)። 

የኢየሱስን አነጋገር አንዳንድ ክርስቲያኖች እንደሚረዱት ከመረዳት ይልቅ፥ («ይህ ደሜ ነው») የሚለውን የኢየሱስን ቃል በምሳሌያዊነት መረዳት ይሻላል። ኢየሱስ አብዛኛውን ጊዜ መንፈሳዊ እውነትን ለማስረዳት ምሳሌዎችን ተጠቅሟል። እራሱን እንደ «ሕይወት እንጀራ»፥ ወይም «በር»፥ ወይም «ወይን»፥ ወይም «እረኛ» ሰይሟል (ዮሐ 6፡35፥ 19፡7-9፥ 10፡14 እና 6፡1)። እነዚህ ዓረፍተ ነገሮች ኢየሱስ ወደ እግዚአብሔር የሚያደርስ መንገድ፥ የመንፈሳዊ ሕይወታችን ምንጭ፥ ለፍላጎታችን ሁሉ የሚጠነቀቅ እርሱ እንደሆነ እና ወደ እርሱ ስንቀርብ መንፈሳዊ ምግብ እንደሚመግበን የሚያስገነዝቡ ናቸው። በተመሳሳይ መንገድ ኢየሱስ በጌታ እራት ጊዜ፥ ከፋሲካ ሥርዓት መብል ሁለት ተፈጥሮአዊ ነገሮችን ይኸውም ያልቦካ ኅብስት እና በዋንጫ ያለ ወይንን በተምሳሌትነት በመጠቀም ሞቱ ለአዲስ ኪዳን የቱን ያህል ማዕከላዊ እንደሆነ አስረድቷል። በእንጀራውና በወይኑ የተመሰለው ስለ እኛ መሞቱ፥ ከእግዚአብሔር ለምንቀበላቸው መንፈሳዊ በረከቶች ሁሉ መሠረት ነው። ያለን ነገር ሁሉ ተጠብቆ በመንፈሳዊ ጤንነታችን የምንቆየው፥ ያለን ሁሉ በኢየሱስ ሞት ምክንያት ያገኘነው የእግዚአብሔር ጸጋ ውጤት እንደሆነ እውቀን ስንኖር ነው። 

2. ኅብስቱና ወይኑን መቀበል ምን ሊፈጸም እንደሚችል ባለው አሳብ ላይ ክርስቲያኖች የተለያየ አቋም አላቸው። ካቶሊኮችና ኦርቶዶክሶች የጌታን እራት ወሳጁ ከኢየሱስ ጋር ያለው መንፈሳዊ ግንኙነት የተስተካከለ ባይሆንም እንኳን፥ እንጀራውንና ወይኑን መውሰዱ ይቅርታ ያመጣለታል ብለው ያምናሉ። ነገር ግን 1ኛ ቆሮ. 11፡27-38 ግልጽ እንደሚያደርገው እንጀራውንና ወይኑን መብላት ብቻ ምንም ለውጥ አያመጣም። ራስ ወዳድ እና የተከፋፈሉት የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች አዘውትረው ይመገቡ ነበር። ነገር ግን ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች ይኖሩ ነበር። ይህ ምንባብ እንደሚያስተምረው፥ የጌታ እራት ትርጉም እንዲኖረው ልባችን መስተካከል ይኖርበታል። ሕይወታችንም እናምናለን ብለን የምንናገረውን ማንጸባረቅ አለበት። በአግባቡ ስንዘጋጅ፥ ይህን የመታሰቢያ እና የማወጂያ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስን እውን (ግልጽ) ላማድረግና ወደ እርሱን ወደመምሰል እንድናድግ ለመርዳት ይጠቀምበታል። 

3. የጌታን እራት ሥርዓት ማን መፈጸም እንዳለበትም ክርስቲያኖች አይስማሙም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የጌታን እራት ለመስጠት ማን ሥልጣን እንዳለው መመሪያዎች የሉም። የሮም ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፥ ኦርቶዶክስ እና መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን የጌታን እራት ለማካሄድ የሚያተኩሩት በቄሱ ሥልጣን ላይ ነው። ነገር ግን አዲስ ኪዳን ሁላችንም ስእግዚአብሔር ፊት ካህናት የመሆን መብት እንዳለን ይናገራል (1ኛ ጴጥ. 2፡9)። ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ኢየሱስን የሚከተሉ ሁሉም አማኞች የጌታን እራት ለማካሄድ እንደተፈቀደላቸው የሚያስተምሩት ከዚህ በመነሣት ነው። በመሠረቱ የጌታ እራት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚካሄደው በቤተ ክርስቲያን በተመረጡ ሰዎች ነው። እነዚህም መሪዎች በ1ኛ ጢሞ. 3፡1-12 የተገለጸውን መስፈርት (መመዘኛን ማሟላትና እና ከኢየሱስ ጋር መልካም ግንኙነት ሊኖራቸው ይገባል። 

4. ማን የጌታን እራት መውሰድ እንዳለበትም ክርስቲያኖች እይስማሙም። አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ማንም ክርስቲያን ነኝ የሚል የጌታን እራት መውሰድ ይችላል ብለው ይምናሉ። ግለሰቡ የቅድስና ሕይወት ኖረ አልኖረ አስፈላጊ አይደለም። ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ ሕፃናትም እንኳ ሳይቀሩ ሁሉም የአማኞች ልጆች የጌታን እራት እንዲወስዱ ይፈቅዳሉ። ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ አባሎቻቸው ብቻ የጌታን እራት በቤተ ክርስቲያናቸው ውስጥ እንዲወስዱ አጠንክረው ይናገራሉ። ወይም በመስፈርቶቻቸው መሠረት አማኙ አስቀድሞ መጠመቅ ይገባዋል ብለው ያሳስባሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ግን የጌታን እራት ማን መውሰድ እንዳለበት ጥቂት መመሪያዎችን ይሰጣል። የዚህ ጥናት ጸሐፊ አዲስ ኪዳን የሚከተሉትን መመሪያዎች ይሰጣል ብሎ ያምናል፡- 

ሀ. የጌታን እራት መካፈል የሚገባቸው ኢየሱስ ክርስቶስን በግል የሚያምኑና እርሱን በመታዘዝ የሚኖሩ ብቻ ናቸው። 

ለ. የጌታን እራት መውሰድ የሚገባቸው ምን እያደረጉ እንዳሉ ለመረዳት በሚችሉበት እድሜ ላይ የደረሱ መሆን አለባቸው። ኢየሱስ ስለ ኃጢአታቸው እንደ ሞተ ለመረዳትና ለማመስገንም እንዲችሉ ማመዛዘን በሚችሉበት ዕድሜ ላይ መሆን 

ያስፈልጋቸዋል። 

ሐ. እራሳቸውን መርምረው ኃጢአታቸውን የተናዘዙት ብቻ መብላት ይገባቸዋል። አማኙ ማልቀስና የተደበቀ ኃጢአት ለመፈለግ ጥረት ማድረግ አያስፈልገውም። ከዚህ ይልቅ፥ ለመንፈስ ቅዱስ ድምጽ ንቁ መሆንና ኃጢአት እንዳለ መንፈስ ቅዱስ ሲጠቁምም በንስሃ ማስተካከል ይኖርባቸዋል። ነገር ግን ግለሰቡ ያንን ኃጢአት ለማስወገድ ዝግጁ ካልሆነ፥ የጌታን እራት መውሰድ አይኖርበትም። 

መ. በቤተ ክርስቲያን ስለፈጸሙት ድርጊት የሥነ ሥርዓት እርምጃ የተወሰደባቸውና ኃጢአታቸውን ለመናዘዝ ፈቃደኛ ያልሆኑ የጌታን እራት እንዲወስዱ መፈቀድ የለበትም (1ኛ ቆሮ. 5) 

5. የጌታ እራት ሲወሰድ ክርስቲያኖች ምን ዓይነት ንጥረ ነገር መጠቀም እንደሚገባ አይስማሙም። ኢየሱስ በመጀመሪያ የጌታን እራት ሲሰጥ የተጠቀመው አጠገቡ በተገኙት ነገሮች ነበር። ነገሮቹም በፋሲካ በዓል ወቅት ጥቅም ላይ የሚውሉ ነበሩ። የተጠቀመው እርሾ የሌለበት ኅብስትና የተበረዘ ወይን ነበር። ኢየሱስ ያልቦካውን ኅብስት አንድ ቁራሽ አንስቶ የሥጋውን መቆረስ ምሳሌ እደረገው። አንድ ዋንጫም አንስቶ የሚፈስሰው ደሙ ተምሳሌት በማድረግ እንዲጠጡት ሰጣቸው። 

ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ምን ዓይነት ነገር መጠቀም እንዳለብን ቁርጥ ያለ መመሪያ አይሰጥም። እንዳንድ ክርስቲያኖች እንደሚያምኑት ኢየሱስ እንደተጠቀመባቸው ዓይነት ተመሳሳይ ነገሮች ቂጣ እና ተመሳሳይ ወይን መጠቀም እንደሚቻል ቢያስቡም፥ ማናቸውንም የኢየሱስን ሥጋና ደም ተምሳሌት ስብቃት የሚገልጽ ነገር ሊፈቀድ ይችላል። (ማስታወሻ፡- በ11ኛው ክፍለ ዘመን የካቶሊክና የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ምን ዓይነት ኅብስት መጠቀም እንዳለባቸው አይስማሙም ነበር። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ኢየሱስ የተጠቀመበት ያን ነው በማለት ያልቦካ ኅብስት ተጠቅማለች። የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ግን አይሁድ በፋሲካ በዓል ያልቦካ ኅብስት ስለሚጠቀሙ ከአይሁድ ጋር ያላቸውን ልዩነታቸውን ለማሳየት ስለፈለጉ በዚህ አልተጠቀሙም።) በአሁኑ ጊዜ፥ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ማናቸውንም የተገኘ ነገር እንደ ዳቦ፥ እንጀራ፥ ጣፋጭ መጠጥ፥ ወይም ብርዝ ይጠቀማሉ። ሌሎች ልዩ ያልቦካ ቂጣና ወይን ይጠቀማሉ። ለነገሩ ብዙ ልዩነቶች መኖራቸው እውነት መንፈስ ቅዱስ በዓለም ውስጥ ላሉ የተለያዩ ባህሎች የሰጠውን የሚስማሟቸውን ልዩ ልዩ ነገሮች የመጠቀም ነፃነት ያመለክታል። ይሁን እንጂ፥ የምንጠቀምበት ነገር ኢየሱስ ከተጠቀመበት ጋር የሚቀራረብ ተምሳሌት ማስተላለፍ ይኖርበታል። 

6. የጌታን እራት በየስንት ጊዜው መውሰድ እንዳለብን ክርስቲያኖች አይስማሙም። በየእሁዱ ይህን የጌታ እራት ሥርዓት የሚያካሂዱ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት አሉ። ሁልጊዜ የአምልኮ አገልግሎታቸው ክፍል ነው። ነገር ግን አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት አልፎ አልፎ (ለምሳሌ፥ በወር አንድ ጊዜ) ይወስዳሉ። በቀድሞዋ ቤተ ክርስቲያን ክርስቲያኖች ሥርዓቱን ያደረጉት በየእሁዱ ነበር። ለእነርሱ የጌታን እራት መውሰድ የአምልኮአቸው ክፍል ሆኖ እንደ መዘመርና ስብከት እንደ መስማት ድርሻ ነበረው። እንዲያውም፥ የአማኞች የመገናኘታቸው ዋነኛ ምክንያት «እንጀራውን በኅብረት ለመቁረስ» እንደነበረ ተነግሮናል (የሐዋ 20፡7)። ይህም ሉቃስ ለጌታ እራት የሰጠው ስያሜ ነበር። 

ነገር ግን በአዲስ ኪዳን ውስጥ የጌታን እራት በየስንት ጊዜው መውሰድ እንዳለብን ምንም የተለየ መመሪያ አልተሰጠንም። ሁለት ሊመሩን የሚችሉ መመሪያዎች አሉ። አንደኛ፥ የጌታን እራት አዘውትረን ያለ ልዩነት ስንወስድ፥ ምንነቱን ሳናስብ ሥርዓት ብቻ አለማድረጋችንን እርግጠኞች መሆን አለብን። ሁለተኛ፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት የእምነታችን መሠረት መሆኑን ለማስታወስ በበቂ ደረጃ አዘውትረን ማድረግ አለብን። የኢየሱስ ስለ እኛ መሞት እውነተኛነት እንዲጠበቅ እና በአሳባችን የክርስቶስ አካል ማለትም የቤተ ክርስቲያን ኅብረት ቀዳሚ ስፍራ ይይዝ ዘንድ የጌታን እራት መውሰድ ይገባናል። 

ምንጭ፡- “የጌታ እራት”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ ተሾመ ነጋሽ የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.