ክርስቲያኖች እንደ መንፈስ ቅዱስ ባሉ መሠረታዊ የክርስትና አስተምህሮዎች ላይ ባላቸው አመለካከት ልዩነት የሚያሳዩት ለምንድን ነው?

መኮንን እና ተስፋዩ በአንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚያገለግሉ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ነበሩ። መኮንን የ55 ዓመት ሰው ሊሆን ለረጅም ዘመን ክርስቲያን ነበር። ወደ ክርስትና ከመምጣቱ በፊት መናፍስትን ያመልክ የነበረ ሲሆን ክርስቲያን ሊሆን ክቀድሞ አምልኮው ጋር የተያያዙ ነገሮችን በሙሉ እቆመ። ይኸውም በሚዘምርበትና ርኩሳን መናፍስትን በሚያመልክበት ወቅት ያደርግ የነበረውን ማጨብጨብና መወዛወዝ ማለት ነው። የአንድ ቤተ ክርስቲያን አባል ከመሆኑ ባሻገር ለዚያች ቤተ ክርስቲያን በሕይወት ዘመኑ በሙሉ ታማኝ ነበር። በዚያ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ያመልክ የነበረ ሲሆን የእነርሱን አባላት ወደ ራሳቸው ቤተ ክርስቲያን በሚወስዱ ሰዎች ላይ እጅግ ይቆጣ ነበር። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰዎች አብዝተው እያጨበጨቡ ሊዘምሩ፥ ሲወዛወዙና በልሳናት ሲናገሩ ሲሰማ ድሮ ዲያብሎስን ያመልክ የነበረበትን ሁኔታ ስለሚያስታውሰው ደስ አይሰኝም። ከእነዚህ ልምምዶች እንዳንዶቹ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ሲገቡ፥ ትክክለኛነታቸውን ስለማያምን፥ በቤተ ክርስቲያኑ ያለውን የአምልኮ ሁኔታ በዚህ ለመለወጥ የሚጥሩትን ሁሉ ይቃወማቸዋል። መኮንን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሁሉ የላቀው አስፈላጊ ነገር ስብከት እንደሆነ ያምናል። ምክንያቱም ለሕይወቱ ብርታት የሚሰጠው የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ስለሚያምን ነበር። በመኮንን እምነት አንድ ሰው መንፈሳዊነቱን የሚያጠነክረው ቃሉን በማጥናት የሚያሳየው ትጋት ደግሞ ቃሉን በመታዘዝ መደበኛ የሆኑትን የቤተክርስቲያን ልምምዶች በመሳተፍ (የሚያሰክር መጠጥ ባለመጣጣት፥ ፊልም ቤት ባለመሄድ፥ ወዘተ…) እንዲሁም በገላትያ 5፡22-23 የተዘረዘሩትን የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች በማሳየት ነው። ለረጅም ዘመን ክርስቲያን የነበሩ በተለይ በዕድሜ የገፉ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች መኮንን ለቀድሞው የእምነትና የአምልኮ ሥርዓት መጠበቅ በሚያደርገው ትግል አጋሮቹ ነበሩ። 

ተስፋዩ የ30 ዓመት ሰው ሲሆን የክርስትና ዕድሜውም 5 ዓመት ብቻ ነበር። በጊታሮችና በጭብጨባ የሚታጀቡ ዘመናዊ ዜማዎችን ይወዳል። ወደ ተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት የሚሄድ ከመሆኑም ሌላ በተለይ ደግሞ በአምልኮ ጊዜ ልዩ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አዳዲስ የሙዚቃ ቡድኖችን በጣም ይከታተል ነበር። ተስፋዩ አንዳንድ ሰዎች በልሳን በመናገር መንፈሳዊ መስለው ሊቀርቡት በጣም ይነካ ነበር። እርሱም ይህን መንፈሳዊ ስጦታ በመሻት በልሳን መናገር ቻለ። ይህ እግዚአብሔርን በተሻለ ሁኔታ እንዲያመልክ እንደረዳውም አመነ። ስለዚህ በቤተ ክርስቲያኑ ያሉ ሰዎችን በእርግጥ መንፈሳዊ መሆን ከፈለጉ በልሳን መናገር እንዳለባቸውና በአምልኮ ጊዜም መንፈስ ቅዱስ የፈለገውን ያደርግ ዘንድ ነፃነት መስጠት እንደሚገባቸው ያስተምር ጀመር። እምልኮው እውነተኛ እንዲሆንና መንፈስ ቅዱስ በመካከላቸው መኖሩ እንዲታወቅ ማጨብጨብ፥ እልል ማለትና እጅን መዘርጋት ያስፈልጋል ብሎ ያስተምር ጀመር። በአምልኮ ጊዜ በሙሉ ስሜታቸው የማይሳተፉ ሰዎች መንፈሳዊ ያልሆኑ ነገር ግን በመንፈስ የሞቱ ናቸው ብሎ አሰበ። ለተስፋዩ በአምልኮ ጊዜ ከሁሉ የላቀው ነገር የስብከት ጊዜ ሳይሆን የመዝሙር ጊዜ ነው። ከአምልኮ ጊዜያችን ውስጥ በሙሉ ስሜታችን የምንሳተፈው እና ከልባችን ለእግዚእብሔር ክብር የምንሰጠው በዚህ ጊዜ ነው ብሎ ያምናል። ተስፋዬንና ትምህርቱን ብዙ ወጣቶች ተከተሉት። 

ጥያቄ፡- ሀ) በአንተ ወይም በሌላ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ዓይነቱን መከፋፈል እንዴት ታዘብነው? ለ) የክፍፍሉ (ልዩነቱ) ሥረ መሠረት ምንድን ነበር? ሐ) በዚህ መከፋፈል የሚከሰተው ግጭት የመሠረተ እምነት ትምህርት አስተምህሮ ጉዳይ ነው ወይስ የአምልኮ ልምምዶች ጉዳይ? 

መልስህን አብራራ። መ) መጽሐፍ ቅዱስ የሚደግፈው የትኛውን አቋም ይመስልሃል? ለምን? ሠ) መኮንንን በዚህ ሁኔታ ምን ትመክረዋለህ? ረ) ለተስፋዬስ ምን ትመክረዋለህ? ሰ) በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንድነት እንዲኖር ከእነዚህ ሁለቱ ሰዎች የሚጠበቀው መንፈሳዊ ባሕርይ ምንድን ነው? ሸ) በዚህ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የምታገለግል ሌላ የቤተ ክርስቲያን መሪ ብትሆን ኖሮ እነዚህን ሁለት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንዴት ትመክራቸው ነበር? 

በዘመናችን ከሚታዩት ባሕርያት አንዱ በአብያተ ክርስቲያናትና በእንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንኳ ሳይቀር መከፋፈል መኖሩ ነው። አንዳንዶቹ ክፍፍሎች በእምነት ክፍሎች መካከል ባሉ የመሠረተ እምነት ትምህርት ልዩነቶች ምከንያት የሚመጡ ናቸው። ለምሳሌ፥ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ሕፃናትን ያጠምቃሉ። ሌሎቹ ደግሞ እዋቂዎችን ብቻ ያጠምቃሉ። እንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት እውነተኛ ክርስቲያኖች በልሳን መናገር አለባቸው ሲሉ፣ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ በልሳን የመናገር ስጦታ በአንደኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ አብቅቷል ይላሉ። ነገር ግን አብዛኛዎቹ ክፍፍሎች የሚፈጠሩት በጥቃቅን ምክንያቶች ነው። ለምሳሌ፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መዝሙር ሲዘመር ማጨብጨብ መኖር እለበት የለበትም፤ ሰዎች እጃቸውን አንስተው ሃሌሉያ ብለው መጮኽ አለባቸው የላባቸውም የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው። 

አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪን ከፊት ለፊቱ ተደቅነው ከሚገዳደሩት ችግሮች እንዱ እነዚህን ልዩነቶች እንዴት ማስረዳት እንዳለበት ማወቁ ላይ ነው። ሕጎችና ደንቦችን መጠቀም ነው? ወይስ እንደ ቤተ ክርስቲያን መሪነቱ ያለውን ሥልጣን በመጠቀም ለእርሱ የማይስማማውን መከልከል ነው ያለበት? ወይስ ማንኛውም የቤተ ክርስቲያን አባል መልካም ነው ብሎ የሚያመጣውን ልምምድ ሁሉ ማስተናገድ አለበት? የመሠረተ እምነት ትምህርት መመሪያዎችን ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስን ምን ያህል ማጥናት አለበት? ወይስ የተለያዩ ልምምዶችን ያስተካክል ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እንዲሠራ መፍቀድ ያላበት መቼ ነው? በዛሬው ትምህርታችን እንደ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች እነዚህን ልዩነቶች ለመረዳት የምንችልበትንና የምናስተናግድበትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መፍትሔ ለመመልከት እንሞክራለን። 

የብሉይ ኪዳን ነቢያት የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት የሚለወጥበት ጊዜ እንደሚመጣ እመልክተው ነበር። ይህም እገልግሎቱ የተደበቀ ወይም የተወሰነ መሆኑ የሚያከትምበት ወቅት ነበር። ይልቁኑ በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር ልጆች በሙሉ ሕይወታቸው ተለውጦ እግዚአብሔርን በመታዘዝ መኖር እስካሚችሉ ደረስ በመንፈስ ቁጥጥር ሥር የሚሆኑበት ጊዜ ነው። ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ሲፈጽም በቅርቡ ስለሚመጣው ስለ መንፈስ ቅዱስ አስታውቆ ነበር። እርሱም ሲመጣ የደቀ መዛሙርትን ሕይወት በመለወጥ በዓለም ሁሉ ብርቱና የተሳካላቸው የክርስቶስ ምስክሮች ያደርጋቸዋል። ኢየሱስ ይህን ብሎ ወደ ሰማይ ከዐረገ በኋላ ኀምሳ ቀናት እስኪያልፉ መንፈስ ቅዱስ አልወረደም ነበር። በበዓለ አምሳ ቀን በድንገት የደቀ መዛሙርት ሕይወትና ታሪክ በሙሉ ተለወጠ። በእነርሱ ላይ የወረደው መንፈስ ቅዱስ እጅግ ፈሪ የነበሩትን የክርስቶስ ተከታዮች በዘመናቸው የነበረውን ትውልድ የለወጡ ታላቅ አገልጋዮች እደረጋቸው። በደቀ መዛሙርት ሕይወትና በዓለም ታሪክ የታየው ታላቅ ለውጥ የተከሰተው መንፈስ ቅዱስ በእግዚአብሔር ሰዎች ላይ በአዲስ መንገድ በመውረዱ ነው። 

የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የሚናገረው መንፈስ ቅዱስ በሚቀጥሉት ሠላሳ ወይም ሠላሳ አምስት ዓመታት የሠራውን ሥራ ነው። ነገር ግን ይህን በደቀ መዛሙርት ላይ የወረደውን የመንፈስ ቅዱስን እሠራር ለመረዳት አስቸጋሪ ነው። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የምናያቸው ታሪኮች በተላይ ተአምራታዊ ክስተቶች፥ ዛሬ ቤተ ክርስቲያን መሆን ስለሚገባት ምሳሌዎች ናቸው ወይስ የዚያ ዘመን ብቻ ልዩ ባሕርያት ናቸው? መንፈስ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስላሚሠራው ሥራ የሚሰጡ የተለያዩ ትምህርቶች በዘመናችን መንፈስ ቅዱስ መፈጸም ስላለበት ተግባር ክርስቲያኖችን ግልጽና አንድ ወደሆነ መረዳት ከማምጣት ይልቅ ውዥንብርና አለመጣጣም ውስጥ ከትተዋቸዋል። አለመግባባቱ የሚከሰተው በአብዛኛው በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ የተደረገውን በመረዳት ጉዳይ ሳይሆን የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ መንፈስ ቅዱስ በዘመናት ሁሉ የሚሠራው በዚህ መልክ መሆኑን ለማሳየት እንደሆነና እንዳልሆነ፥ እኛም ዛሬ መጠበቅ ያለብን ተመሳሳይ ሁኔታዎችን ስለመሆን አለመሆኑ ለማወቅ በሚደረገው ሙከራ ላይ ነው። ይህ የአሳብ ልዩነት ‹ካሪዝማቲክ› ወይም «ፔንትኮስታል› የሚባሉ አብያተ ክርስቲያናትን በአንድ ወገን ነጥሎ ሲያስቀምጥ፥ መንፈስ ቅዱስ ዛሬ የሚሠራው በሐዋርያት ዘመን በሠራበት መንገድ አይደለም የሚሉ አብያተ ክርስቲያናትን ደግሞ በሌላ ወገን አስቀምጦአቸዋል። 

ትክክለኛው አመለካከት የትኛው ነው? መልሱ የሐዋርያትን ሥራ መጽሐፍን በምንረዳበት መንገድ ይወሰናል። የመንፈስ ቅዱስን ሥራ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ በተገለጠው መንገድ በዝርዝር ከመመልከታችን በፊት «ክርስቲያኖች በመሠረታዊ የእምነት ትምህርት ሳይስማሙ ሲቀሩ ምን ማድረግ አለባቸው?» የሚለውን አስፈላጊ ጥያቄ መጠየቅ አለብን። 

ጥያቄ፡– በኢትዮጵያ ያሉ ክርስቲያኖች መንፈስ ቅዱስን በሚመለከት ትምህርት ላይ የማይስማሙባቸውን መንገዶች ዝርዝር። 

እስካሁን ድረስ ስለ መንፈስ ቅዱስ በተመለከትናቸው ጥናቶች ክርስቲያኖች ከሞላ ጐደል አንድ እምነት አላቸው። በጠቅላላው ክርስቲያኖች ሁሉ መንፈስ ቅዱስ ኃይል ሳይሆን አካል ያለው ግፃዌ መለኮት አባልና ከሥላሴ አካላት አንዱ እንደሆነ ያምናሉ። በብሉይ ኪዳንና በኢየሱስ ሕይወት የነበረውን አገልግሎት ይቀበላሉ። አንድ ሰው ጌታን አምኖ በሚድንበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በሕይወቱ ስለሚሠራቸው አብዛኛው ተግባራት በሚሰጡት ትምህርቶች ብዙዎች ክርስቲያኖች ይስማማሉ። ደግሞም ክርስቲያን በምድር በሚኖርበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በሕይውቱ ስለሚሠራቸው ሥራዎች በአብዛኛው ይስማማሉ። 

ሆኖም ግን ክርስቲያኖች መንፈስ ቅዱስ በክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ስላለው አገልግሎት የሚለያዩባቸው፥ አንዳንድ ጊዜም እጅግ በጣም የሚለያዩባቸው ሦስት ዋና አቅጣጫዎች አሉ። 

1. የመንፈስ ቅዱስ «ጥምቀት» ና «ሙላት» ልዩነት ምንድን ነው? አንድ ሰው በመንፈስ ቅዱስ የሚጠመቀው በሚድንበት ጊዜ ነው? ወይስ መንፈስ ቅዱስ በሁለተኛ ደረጃ የሚሠራው የጸጋ ሥራ ነው። 

2. በዚህ ዘመን ባለች ቤተ ክርስቲያን እንደ በልሳን መናገር፥ ፈውስና መገላጥና ትንቢት የመሳሰሉት ተአምራታዊ ስጦታዎች ሚና ምንድን ነው? 

3. መንፈስ ቅዱስ በክርስቲያን ሕይወት ስለሚሠራው የተለመደ አገልግሎት የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ምን ያስተምረናል?

ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.