ተአምራትና ፈውሶች በአዲስ ኪዳን

አዲስ ኪዳን በተአምራትና ፈውሶች ታሪክ የተሞላ ነው። በተለይ ደግሞ በወንጌላትና በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ የዚህን እውነትነት እንመለከታለን። ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ተአምራት ማየት አለብን በሚሉ ሰዎች እነዚህ ተአምራት በምሳሌነት ሲጠቀሱ እንመለከታለን። ሰዎች የመፈወስ መንፈሳዊ ስጦታ እንዳላቸው እንዲናገሩ የገፋፋቸውም ይህ ነው። ፈውስ የአገልግሎታቸው ማዕከል ይሆናል። እጅግ ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበት ማንኛውም ሰው ከማንኛውም ዓይነት በሽታ እንዲፈወስ ያውጃሉ። ከእነዚህ ወንጌላውያን እንዳንዶቹ በቴሌቪዥንና በቪዲዮ ይህ አለን የሚሉትን የፈውስ ኃይላቸውን ሀብትና ክብር ለማግኘት ይጠቀሙበታል። የፈውስ መንፈሳዊ ስጦታ የተሰጠበት ዓላማ በእርግጥ ይህ ነውን? 

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተአምራትንና የፈውስን ስፍራ ወደየት ሄደን መመልከት አለብን? ወደ መጽሐፍ ቅዱስ መመለስ አለብን። መጽሐፍ ቅዱስ የፈውስ ስጦታ እንዴት በሥራ ላይ መዋል እንዳለበት በልሳናት የመናገርና የትንቢትን ያህል ዝርዝር መመሪያ አይሰጥም። በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስጦታው የነበረ ቢሆንም ከፍተኛ ትኩረት ግን አልተሰጠበትም ነበር። የእነርሱ ትኩረት የነበረው በልሳን በመናገር ስጦታ ላይ ነበር። 

ተአምራት በአዲስ ኪዳን ውስጥ በኢየሱስ ሕይወትና በሐዋርያት አገልግሎት ያላቸውን ስፍራ ብንመለከት ዛሬ ለዚህ ስጦታ ሊኖረን ስለሚገባ አካሄድ ፍንጭ እናገኛለን። እግዚአብሔር ለመፈወስና ተአምራትን ለማድረግ ሲመርጥ አንድ መመሪያ ይከተላል ወይም ከዚህ ቀደም በሠራበት ተመሳሳይ መንገድ ይሠራል። መንፈስ ቅዱስ ከዚህ በፊት ከሠራበት መንገድ በከፍተኛ ደረጃ የሚለይ ማንኛውም አሠራር በጥንቃቄ ሊመረመር ይገባል። «የፈውስ አገልግሎት ሰዎች ከእግዚአብሔር ይልቅ አገልግሎቱን በሚያካሂደው ሰው ላይ እንዲያተኩሩ የሚያደርግ ከሆነ ይህ የዚያን ሰው አገልግሎት እንድንጠራጠር ሊያደርገን ይገባል። 

ጥያቄ፡- «ተእምራትን» ማድረግ የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነው። ስለዚህ ማንኛውንም ዓይነት ተአምራት ካየን ከእግዚአብሔር መሆን አለበት። ይህ አባባል እውነት ይመስልሃል ወይስ ውሸት? መልስህን አብራራ። 

በኢትዮጵያ የሚገኝ አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ እንዲህ አለ። «ተአምራትን ማድረግ የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነው። ስለዚህ ማንኛውም ተአምራት ከእግዚአብሔር መሆን አለበት።» ይህ እውነት ነውን? ተአምራትን ማድረግ የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነውን? ሰይጣን ተአምራትን ማድረግ ይችላልን? ለዚህ በአዲስ ኪዳን ግልጽ የሆነ መረጃ እናገኛለን። እግዚአብሔር የተአምራት አምላክ ቢሆንም እንኳ ሰይጣንም ደግሞ ተአምራት የማድረግ ኃይል ያላውና ሰዎችም ተአምራት እንዲያደርጉ የሚያስችል ነው። የተአምራትና የፈውስ መኖር ከእግዚአብሔር ለመሆናቸው ማስረጃ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን በመጨረሻው ዘመን በምድር ላይ ሐሰተኛ አስተማሪዎችና ነቢያት ይነሣሉ። ከእነዚህ አንዱ ሰዎችን ከሙታን እስኪያስነሣ ድረስ ኃይል ይሰጠዋል (ራእይ 16፡14፤ 2ኛ ተሰ. 2፡9 ተመልከት)። የጠንቋዮችን ሥራ የሚያውቁ ሁሉ ጠንቋዮች ተአምራትን እንደሚያደርጉ ይገነዘባሉ። ሰይጣን ሰዎች እርሱንና ተከታዮቹን እንዲከተሉአቸው የሚያደርገው እንዴት ነው? ብዙ ጊዜ ሰዎች እንዲከተሉት ኃይሉን በማሳየት ነው። 

እንደ ብዙዎቹ መንፈሳዊ ስጦታዎች የተአምራትና የፈውስ ስጦታዎች መመዘን አለባቸው። ተአምራቱ ከእግዚአብሔር ዘንድ ለመሆናቸው እርግጠኞች መሆን አለብን። ስለዚህ ተአምራት በኢየሱስና በመጀመሪያዎቹ ሐዋርያት የነበራቸውን ስፍራ በመመርመር ጥናታችንን እንጀምር። ብዙ ሰዎች ዛሬ ተአምራትንና ፈውስን የሚለማመዱባቸው መንገዶች ከአዲስ ኪዳን መንገድ የሚለዩት በዓይነት ሳይሆን በዝንባሌ ነው። ልንጠይቃቸው ከሚገቡ እጅግ አስፈላጊ ጥያቄዎች አንዱ ኢየሱስ ተአምራትን ለምን አደረገ? የሚለው ነው። ይህ ጥያቄ እጅግ አስፈላጊ የሚሆንበት ምክንያት እግዚአብሔር ዛሬ ተአምራት የሚያደርግበት ምክንያት ከዚህ ቀደም ለኢየሱስና ለመጀመሪያይቱ ቤተ ከርስቲያን ካደረገበት ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ነው። ልንከተላቸው የሚገቡ ምሳሌዎች ናቸው። ተመሳሳይ የልምምድ ዓላማዎች፥ ዝንባሌዎችና አቀራረቦች የሌላቸው ነገሮች ከእግዚአብሔር እንጂ ከሰይጣን አለመሆናቸው በጥንቃቄ መመርመር አለበት። 

ተአምራትና ፈውሶች በክርስቶስ ዘመን 

ጥያቄ፡- የሚከተሉትን ጥቅሶች በማንበብ ኢየሱስ የፈጸማቸውን የተለያዩ ተአምራት ዘርዝር። ሉቃ. 4፡38-41፤ 5፡12-14፤ 17-26፤ 6፡6-11፤ 7፡1-7፤ 8፡26-58፤ 9፡10-17። 

በወንጌል ውስጥ ስለ ኢየሱስ ታሪክ በምናነብበት ጊዜ በእያንዳንዱ ገጽ ኢየሱስ ስለፈጸማቸው ተአምራት የተጻፈ ነገር አለ ለማለት ያስደፍራል። ተአምራቱ ብዙ ዓይነት ነበሩ። የፈውስ፥ እውርን የማብራት፥ደንቆሮን የመክፈት፥ ሙታንን የማስነሣት፥ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን የመመገብ፥ ወዘተ… ተአምራት ነበሩ። 

ኢየሱስ ተአምራትን ያደረገባቸው ምክንያቶች ምን ምን ነበሩ? ምከንያቶቹን በሙሉ ባናውቅም እንኳ አዲስ ኪዳን የሚከተሉትን አሳቦች ይጠቁማል። 

1. ኢየሱስ ተአምራትን ያደረገው በብሉይ ኪዳን ዘመን እንደሚመጣ የተነገረለት መሢሕ እርሱ እንደሆነ ለሕዝቡ ለማሳየት ነበር (ዮሐ 10፡25-26፤ 14፡11)። 

2. ተአምራትና ፈውሶች ብዙ ጊዜ የተደረጉት ኢየሱስ እግዚአብሔር መሆኑን ለማሳየት ነበር። በተፈጥሮ፥ በበሽታ፥ በሰይጣን፥ በቦታ ርቀት፥ ወዘተ… ላይ ሥልጣን እንዳለው የሚያሳዩ ነበሩ። 

3. ኢየሱስ ለሕዝቡ ይራራ ስለነበር አንዳንድ ጊዜ በዚህ ምክንያት ተአምራትን አድርጓል። ለምሳሌ አምስት ሺህ ሰዎችን የመገበው ምግብ እንዳልነበራቸው በማየት ነበር (ዮሐ 6፡1-13)። ከኢየሱስ ተአምራት አብዛኛዎቹ ድሆችን፥ ያልታደሉትን፥ የተናቁትንና የተጣሉትን፥ ወዘተ… ለመርዳት ከነበረው ፍላጐት አንጻር የተደረጉ ነበሩ። 

4. ኢየሱስ በሰይጣን ላይ ያለውን ኃይል ለማሳየት ብዙ ጊዜ አጋንንትን ያወጣ ነበር። አጋንንት ከሰዎች በማስወጣት ኃይሉ ጥያቄ ለነበራቸው ፈሪሳውያንን ያደረጋቸው ተአምራት ሰይጣንን ለማሸነፍና ድል ለመንሳት የመጣ መሆኑን እንደሚያሳዩ ነግሮአቸዋል (ሉቃ 11፡14-26)። 

5. የኢየሱስ ተአምራት ንጉሥ በመካከላቸው የመኖሩ ማረጋገጥ ነበር። የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ቀረበች የሚያስረዳ ነበር (ሉቃስ 11፡20)። 

ጥያቄ፡– በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዛሬም ተአምራት ይፈጸም ዘንድ ከላይ ከተጠቀሱት ዓላማዎች የትኞቹ ምክንያቶች ትክክለኞች ሊሆኑ ይችላሉ? 

ኢየሱስ ያደረጋቸውን ፈውሶችና ተአምራት ስንመለከት የሚከተለውን እንነዘባለን። 

1. ኢየሱስ ሰዎችን ለማስደነቅ ብሎ ተአምራትን አድርጐ አያውቅም። ሰዎች ምልክት ወይም ተአምራት ያደርግ ዘንድ በጠየቁት ጊዜ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል (ማቴ. 12፡38-39)። ኢየሱስ አምስት ሺህ ሰዎችን ከመገበ በኋላ እንደመጡት ዓይነት ሰዎች ለግል የስግብግብነት ዓላማቸው ተአምራት ያደርግላቸው ዘንድ በፈለጉ ጊዜ ተአምራትን ለማድረግ ፈቃደኛ አልነበረም። ተአምራቱ ሕዝቡን ለማስገረምና ግርግር ለመፍጠር ሳይሆን ግልጽ የሆነ ዓላማ ነበራቸው። 

2. ኢየሱስ በርካታ ሰዎችን በአንድ ጊዜ በተሰበሰቡበት ፈውሶ ከሆነም “ሁላችሁም ተፈውሳችኋል” ሲል ከስንት አንዴ ነው የምንመለከተው። ፈውስ ባከናወነባቸው ጊዜያት ሁሉ አንድ በአንድ እንዳደረገ ነው። ይህ እንግዲህ ዛሬ በዘመናችን በርካታ ሰዎች በአንድ ጊዜ እንደ ተፈወሱ ከሚናገሩት ሰዎች አሳብ ተቃራኒ ነው። 

3. ኢየሱስ ለፈውስ የገንዘብ ክፍያ የተቀበለበት ጊዜ ፈጽሞ አልነበረም። ፈውስን ለግል ጥቅሙ የተጠቀመበት ወቅትም ፈጽሞ አልነበረም። 

4. ኢየሱስ ያደረጋቸው ተአምራቶች ፈውሶች በሙሉ ስኬታማ ነበሩ። እንድን ሰው ለመፈወስ ሞክሮ ያልተሳካበት ወይም ከፊል ፈውስ የሰጠበት ወቅት ፈጽሞ አልነበረም። 

5. ተፈዋሾቹ ምንም እምነት እንደነበራቸው ሳይጠቅስ ኢየሱስ ሰዎችን የፈወሰበት ወቅት ነበረ። በእርግጥ ግልጽ የሆነ ተቃውሞና ያለማመን በነበረበት ስፍራ ፈውስን ከመፈጸም ተቆጥቧል። ነገር ግን ኢየሱስ ፈውስን አውጆ ያልተሳካበትና ለዚህም እምነት ጉድለት እንደ ምክንያት ያቀረበበት የለም። ስለዚህ ኢየሱስ ፈውስን ለመፈጸም ወይም ላለመፈጸሙ የእምነት ቅድመ–ሁኔታ አልነበረም። ነገር ግን እንዳንድ ጊዜ ላመፈወስ ፈቃደኝነቱ ቅድመ-ሁኔታ ይሆን ነበረ። 

6. የኢየሱስ አገልግሎት ትኩረት የእግዚአብሔርን ቃል ማወጅ ነበር። ያደረጋቸው ተአምራት አብዛኛዎቹ ከነበረው የማስተማር አገልግሎት ጋር የተያያዙ ነበር። ተአምራቱ ትምህርቱን ያጠናክሩለት ነበር። ከትምህርቱ ውጭ የሚደረጉ አልነበሩም። ተአምራት በተለይ ደግሞ ፈውስ ኢየሱስ ለሕዝቡ የነበረው ፍቅር ተፈጥሮአዊ መግለጫዎች ነበሩ። ኢየሱስ ግን በማስተማር ላይ በማተኮር ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸው ግንኙነት ትክክለኛ እንዲሆን ሞክሯል። ተአምራት አድራጊ በመባል እንዲታወቅ አይፈልግም ነበር። ደግሞ የእውነት አስተማሪ ከመባል ይልቅ ተአምራት አድራጊ የመባል ዝናው እየናረ ከመጣ ያንን አካባቢ ለቅቆ ይሄድ ነበር (ማር. 1፡32-38)። እንዲያውም ለአንዳንዶች ያደረገላቸውን ተአምራት ለሌሎች እንዳይነግሩ አስጠንቅቆአቸው ነበር (ማር. 1፡44)። 

7. ኢየሱስ ያደረጋቸው ተአምራት መሢሕ መሆኑን የሚያረጋግጡ ቢሆኑም ሊያሳምኑ የቻሉት ጥቂት ሰዎችን ብቻ ነበር። ተአምራት በራሳቸው ሰዎች በእርሱ ላይ እምነት እንዲኖራቸው ፈቃደኞች አላደረጉአቸውም። ይልቁኑ ሰዎች በራስ ወዳድነት መንፈስ እንዲከተሉት የሚያደርጉ ነበሩ ( ዮሐ 6፡30-48)። ስለዚህ ሰዎች አስቸጋሪ ምርጫ ያደርጉ ዘንድ የሚያስገድድ ነገር ማድረግ ወይም አንድ ነገር ማስተማር ነበረበት። ለእነርሱ ከሚያደርግላቸው ነገር ይልቅ በማንነቱ ላይ በመመርኮዝ በልባዊ ውሳኔ መከተልን እንዲመርጡ ለማስገደድ የተአምራት አድናቆትን ከእነርሱ ማስወገድ ነበረበት። ተአምራትን አይተው ኢየሱስን የተከተሉ በስደት ጊዜ ለመፈርጠጥ የመጀመሪያዎቹ ነበሩ። 

8. ኢየሱስ ካደረጋቸውና የሰዎችን ሥጋዊ ሕይወት ከለወጡት ተአምራት የድነት (ደኅንነት) ተአምር ከሁሉ የላቀ አስፈላጊ ነው። ባደረጋቸው ተአምራት ሰዎች ሲደነቁ ከማየት ይልቅ የእምነት እርምጃ ሲወስዱና በእርሱ ሲያምኑ ኢየሱስ የበለጠ ይደሰት ነበር (ሉቃስ. 10፡2)። 

ጥያቄ፡- ሀ) ስለ ተአምራት ከኢየሱስ ሕይወት የምንመለከታቸው መርሆዎች ዛሬ ብዙ ሰዎች ከሚያስተምሩትና ከሚለማመዱት የሚለየው እንዴት ነው? ለ) የፈውስ አገልግሎት በሚኖርበት ጊዜ ዛሬ ተግባራዊ ልናደርጋቸው የሚገቡ፥ ከእነዚህ እውነቶች የመነጩ መርሆዎችን ዘርዝር። 

የሐዋርያት ሥራና ተአምራት 

ወደ ሰማይ ከማረጉ ጥቂት ቀደም ብሎ ኢየሱስ እርሱ ከሠራው ይልቅ የበለጠ እንደሚሠሩ ለደቀ መዛሙርቱ ነግሮአቸው ነበር (ዮሐ 14፡12)። ስለዚህ የሐዋርያት አገልግሎት የኢየሱስ አገልግሎት ተከታይ መሆኑ ነበር። ኢየሱስ ለሕዝቡ ሊያስተምራቸው ይፈልግ የነበረው ትምህርት ብቻ ሳይሆን ሲያደርጋቸው የነበሩትን ሥራዎች ወይም ተአምራት መቀጠል ነበረባቸው። 

ነገር ግን እነዚህ ተአምራት አብላጫ የሚሆኑት በምን መንገድ ነበር? የተአምራቱ ብቃት ወይም መጠን የበለጠ እንደሚሆን የሚያመለክት ነገር የለም። በጥቂት ዳቦና አሣዎች አምስት ሺህ ሰው የመገበ ደቀ መዝሙር አንድም አልነበረም። ወይም በውኃ ላይ የተራመደ ደቀ መዛሙርት አልነበረም። ስለዚህ የኢየሱስ አባባል የተአምራቱ መጠን የበለጠ ይሆናል ማለቱ አልነበረም። ነገር ግን የበለጠ የሚሆኑበት በሁለት ሌሎች ምክንያቶች ነበር። 

1. በቁጥር የበለጠ ይሆናሉ። ኢየሱስ አንድ ሰው ብቻ ሲሆን ሐዋርያት ቀን አሥራ ሁለት ነበሩ። ስለዚህ በሐዋርያት አገልግሎት የሚፈጸሙት ተአምራት ኢየሱስ ከፈጸማቸው ተአምራት በቁጥር የላቁ እንደሚሆኑ ነበር። 

2. ኢየሱስ ከፈጸማቸው ተአምራት ትልቅና የተስፋፉ እንደሚሆኑ ነበር። የኢየሱስ ተአምራት የተፈጸመው በከነዓን ምድር ብቻ ነበር። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ተአምራት ግን ወንጌል በደረሰበት ስፍራ ሁሉ የሚደርስ ነበር። ጳውሎስ ለገላትያ ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር ዘንድ ብዙ ተአምራትን እንዳዩ የጻፈላቸው ለዚህ ነበር (ገላ. 3፡5)። 

በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የተጻፉትን ታሪኮች ስናነብ ተአምራት በተደጋጋሚ ተጠቅሰው እንመለከታለን። ጴጥሮስና ዮሐንስ በኢየሩሳሌም የነበረ አንድ ሽባ ፈውሰዋል የሐዋ. 3፡1-10)። ጳውሎስ አንድን ሰው ከሞት አሥነስቷል (የሐዋ. 20፡7-12)። በአንድ ወቅት የጴጥሮስ ጥላው እንኳ ፈውስን አምጥቶ ነበር (የሐዋ. 5፡12–16)። የሚያስገርመው ነገር ግን ተአምራት ተዘውትረው መደረጋቸው የተጠቀሰ ቢሆንም በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍም ሆን በመልእክቶች ተአምራት የትኩረት ማዕከል አልነበሩም። ተአምራት ሁልጊዜ የተጠቀሱት በእግረ መንገድ ነበር። የትኩረት ማዕክሉ የወንጌል መሰበክና የሰዎች ማመን በዚህም ሥርጭት እየተስፋፋ የመሄዱ ጉዳይ ላይ ነበር። 

ጥያቄ፡- የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከት። የሐዋ. 3፡1-9፤ 5፡12-16 8፡39፤ 9፡17-18፤12፡6-1፤ 16፡16-18፤ 20፡7-12። ሀ) በእነዚህ ስፍራዎች የተጠቀሱትን የተለያዩ ዓይነት ተአምራት ዘርዝር። ለ) እነዚህ ተአምራት የሚያሳዩት ምንን ነበር? ሐ) እነዚህ ተአምራት ኢየሱስ ከፈጸማቸው ተአምራት ተመሳሳይ የሆኑት ወይም የተለዩት በምን መንገድ ነበር? መ) ዛሬ ብዙ ሰዎች ከሚፈጽሙአቸው ተአምራት የሚለዩት በምን መንገድ ነው? 

በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ በአጠቃላይና በመልእክቶች የሚከተሉትን እውነቶች ለመመልከት እንችላለን። 

1. ተአምራት በደቀ መዛሙርት አገልግሎት በተደጋጋሚ የሚታዩ ክፍሎች ነበሩ። 

2. ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ ያደረገውን ያህል የተለያዩ ተአምራት አድርገዋል። እነዚህ ተአምራት የፈውስ፥ ሙታንን የማስነሣት፥ ከአጋንንት ቀንበር ነፃ የማድረግ፥ ወዘተ… ነበሩ። 

3. ልክ እንደ ኢየሱስ የደቀ መዛሙርት አትኩሮት ተአምራትን በማድረግ ላይ ሳይሆን ቃሉን በመስበክ ላይ ነበር። ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ለመሳብ ተአምራት አድራጊ ወይም ፈዋሽ ብሎ እራሱን የጠራ ደቀ መዝሙር እናገኝም። ሐዋርያት ተአምራት በሚፈጸምበት ጊዜ የመተንፈስን ያህል እንደተለመደ ነገር አድርገው በመውሰድ ቢደረግም ባይደረግም ልዩነት እንደሌለ አድርገው ይቆጥሩ ነበር። የእነርሱንም ሆነ የሰዎችን አስተሳሰብ በተአምራት ላይ ከማድረግ ይልቅ በኢየሱስ ላይ አድርገው ነበር። 

4 ያደረጉት ተአምራት ሐዋርያት የኢየሱስን ኃይል መውረሳቸውን የሚያሳይ ነበር። መልእክታቸው ከእግዚአብሔር እንደነበር ለሰዎች አረጋግጧል (ገላ. 3፡5)። 

5. ደቀ መዛሙርቱ ተአምራት ለማድረግ ችሎታቸው ክፍያ የተቀበሉበት ጊዜ ፈጽሞ አልነበረም። ጠንቋዩ ስምዖን (የሐዋ. 8፡9-14) በከፍተኛ ስግብግብነት ተሞልቶ ሰዎችን ተአምራትን ለማስደረግ ይችል ዘንድ መንፈስ ቅዱስን ለፈለገው ማደል የሚችልበት ኃይል እንዲሰጠው ሲጠይቅ ጴጥሮስ እጅግ አጥብቆ ገሠጸው። 

6. ሐዋርያት ይፈጸም ዘንድ ተናግረውት ያልተከናወነ ፈውስ ፈጽሞ የለም። ይልቁኑ ሐዋርያት አንድ ሰው እንዲፈወስ በሚናገሩበት ወቅት ኢየሱስ ሰውን ሲፈውስ እንደነበረው ሰዎች ወዲያውኑ ይፈወሱ ነበር። ፈውስ ደረጃ በደረጃ ስለመፈጸሙ ወይም በከፊል ላለመከናወኑ የሚጠቁም ነገር ፈጽሞ የለም። 

7. በአንድ ሰው የመፈወስ ችሎታና ፈውስን በሚቀበል ሰው እምነት መካከል የቅርብ ግንኙነት ስለመኖሩ አመላካች የሆነ አሳብ ፈጽሞ እናገኝም። ሐዋርያት ተአምራት ለመፈጸም አስበው ተአምራቱ በሚደረግለት ሰው እምነት ማጣት ምክንያት ተአምራት ያልተፈጸመበትንም ሁኔታ ፈጽሞ አናገኝም። 

8. ሐዋርያት ተአምራትን ለግል ጥቅማቸው አውለው አያውቁም። ሰዎችን ከበሽታቸው ለመፈወስ ያልቻሉበት ወቅት ነበር። ለምሳሌ ከጳውሎስ ጋር ለመሥራት ከመጡት ሰዎች አንዱ እስከ ሞት ድረስ ታሞ ነበር። ጳውሎስ ሊፈውሰው ቢፈልግ እንኳ አልቻለም ነበር (ፊል 2፡27)። ጳውሎስ እራሱም ታሞ በነበረበት ወቅት ለራሱ ፈውስን ሊያመጣ አልቻለም ነበር። ይልቁኑ ከነበረበት ችግር ጋር አብሮ በመቆየት ለዕለታዊ ብርታት በእርሱ ላይ መታመን እንዳለበት እግዚአብሔር አሳወቀው (2ኛ ቆሮ. 12፡7-10)። ደቀ መዛሙርት፥ ክርስቲያኖችን ሁሉ በጤንነት እንዲኖሩ በበሽታ ምክንያት እንዳይሞቱ የሚያደርግ ልዕለ ተፈጥሮአዊ ችሎታን መቀበላቸውን የሚያመላክት አንዳችም ነገር የለም። ክርስቲያኖች ወደ ቤተ ክርስቲያን በመምጣት ፈውስን ይቀዳጁ ዘንድ የተመቻቸ የፈውስ አገልግሎት ስለመኖሩ የተጻፈ አንዳችም ነገር አናገኝም። መንፈስ ቅዱስ በምድር ላይ ለሚኖሩ ሰዎች ተለምዶአዊ ከሆኑ እንደ በሽታና ሞት፥ ድካም፥ ወዘተ… ከመሳሰሉ ነገሮች ሰዎችን ስለመከላከሉ የሚያመለክት አሳብ አናገኝም። የተፈወሱ ክርስቲያኖች ለመኖራቸው የሚያጠራጥር ነገር ፈጽሞ የለም። ክርስቲያኖች ከችግርች ሁሉ ልዕለ ተፈጥሮአዊ በሆነ መንገድ ጥበቃ የሚደረግላቸው መሆኑን የሚያመለክት አሳብ ፈጽሞ አናገኝም። በጳውሎስም ሆነ በሌሎች ደቀ መዛሙርት ትምህርት ውስጥ ከእነዚህ አንዳቸውንም አናገኝም። 

9. በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ከምናገኛቸው የተአምራት ታሪኮች አብዛኛዎቹ በቤተ ክርስቲያን ምሥረታ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት የተፈጸሙ ናቸው። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ታሪክ የሚያካትተው የመጀመሪያዎቹን 30 ዓመታት የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ነው። ተአምራት በብዛት የሚታዩት አብያተ ክርስቱያናት ከተጠናክሩ በኋላ ሳይሆን በተመሠረቱ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ነው። ቤተ ክርስቲያን በሚገባ ከተመሠረተች በኋላ እንደ መጀመሪያዎቹ ዓመታት ተአምራት ለመቀጠላቸው የምናገኘው ማስረጃ በጣም አነስተኛ ነው። እንዲያውም የጥንት ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊዎች እንደዘገቡት ከሐዋርያት ሞት በኋላ ከአስደናቂ ተአምራት አብዛኛዎቹ እንዳከተሙ ነው። ሆኖም ግን በየትኛውም የታሪክ ክፍል ውስጥ እግዚአብሔር ተአምራት ያደረገባቸው ጊዜያት አሉ። 

የቤተ ክርስቲያን ታሪክን በምናስስበት ወቅት እግዚአብሔር ተአምራትን በብዛት ያደረገባቸው ሁለት ጊዜያት የነበሩ ይመስላል። በመጀመሪያ፣ ወንጌል ከዚህ በፊት ወዳልደረሰባቸው አዳዲስ ስፍራዎች በሚደርስበት ጊዜ እግዚአብሔር ኃይሉን ለመግለጥ ተአምራትን ያደርጋል። ባለፉት 70 ዓመታት ከአንዱ ጐሣ ወደ ሌላው ወንጌል በተስፋፋበት በደቡብ ኢትዮጵያ ይህ ተፈጽሟል። ሆኖም ግን ቤተ ክርስቲያን በሚገባ ከተመሠረተች በኋላ የተአምራቱ ቁጥር እየቀነሰ መጣ። እግዚአብሔር የተአምራቱ ቁጥር እየቀነሰ እንዲሄድ የሚፈቅደው ሰዎች እምነታቸውን በተአምራት ላይ እንዳያደርጉ ወይም እምነታቸውን ለማሳደግ ተአምራትን እንዳይሹ ነገር ግን እግዚአብሔርን መታመን እንዲማሩ ለማድረግ ይሆናል። 

ሁለተኛ፣ ወንጌል ጠልቆ ቢገባም እንኳ ቤተ ክርስቲያን እየደከመች በምትሄድበት ስፍራ እግዚአብሔር ሌላ ትልቅ ሥራ ለመሥራት ሲዘጋጅ መንፈሱ በሥራ ላይ መሆኑን ለማሳየት ብዙ ጊዜ ተአምራትን ያደርጋል። በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ በሙሉ እምነት ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ ሲመጣ ሰዎች ለእግዚአብሔር ያላቸውን ፍቅር ያጣሉ። በኢየሱስ ላይ የሚደረግ እምነት ሥርዓት ብቻ ይሆናል። ከእግዚአብሔር ጋር የግል ግንኙነት አይኖርም። ይህን አደገኛ ሁኔታ ለመስብር እግዚአብሔር ተአምራትን በማድረግና መንፈስ ቅዱስን በኃይል በመላክ ቤተ ክርስቲያኑን ያነቃል። 

10. የጴጥሮስ ጥላና የጳውሎስ መሃረብ ፈውስን እንዳመጡ ተጽፎአል ( የሐዋ. 5፡5፣ 9፡12)። እነዚህ ያልተለመዱ ክስተቶች የተጠቀሱበት ሁኔታ መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ፈውስን ለማምጣት ከተጠቀመበት ተለምዶአዊ መንገድ የተለየ እንግዳ ክስተት መሆኑን እንድንረዳ ያደርገናል። 

11. በሐዋርያት ሥራም ሆነ በመልእክቶች ውስጥ በአንድም ስፍራ እንኳ ሐዋርያት ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት ቆመው ለሁሉም ሰው ፈውስን ያወጁበት ጊዜ የለም። ግልጽ በሆኑ ስብሰባዎች ሰዎች ለመፈወስ ወደፊት ስለመምጣታቸው የሚያመለክት አንዳችም መረጃ እናገኝም። ደግሞም ሐዋርያት በቤተ ክርስቲያን ስብሰባ ላይ ሰዎችን እያንዳንዳቸውን ለመፈወስ የተለየ ጊዜ ስለመያዛቸውም የምንመለከተው ነገር ፈጽሞ የለም። ሐዋርያት በፈውስ ላይ ያተኮሩበት አንዳችም ጊዜ የለም። አትኩሮታቸው ወንጌልን በመስበክና በማስተማር ላይ ነበር። ለእነርሱ ተአምራትን ማድረግ የአገልግሎታቸው ትልቁ አካል አልነበረም። እግዚአብሔር አንድን ሰው ለመፈወስ ከፈለገ ፈውሱ እንዳይከናወን አይቃወሙም። ሆኖም ግን ተአምራትንና ፈውስን ፍለጋ አልተቅበዘበዙም፤ እግዚአብሔር ድንቀኛ በሆነ መንገድም እንዲሠራ ጥያቄ አላነሡም። 

12. እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያን መሠረት ይሆኑ ዘንድ 12 ሐዋርያትን መረጠ። የእግዚአብሔር አገልግሎት ተለምዶአዊ አሠራር የተወሰኑ ሰዎችን ለይቶ ተአምራትንና ፈውስ እንዲያደርጉ ልዩ ኃይል በመስጠት ቢሆን ኖሮ ችሎታ ለአንድ ሰው ይሰጠው እንደነበር እንጠብቅ ነበር። ወንጌል እየተስፋፋ ሲሄድና ወንጌላውያንም ወደተለያዩ ስፍራዎች ሲሰራጩ ከመካከላቸው እንዳንዶቹ ከሌሎች ይበልጥ ተአምራት በማድረግ ላይ አትኩሮት ይስጡ እንደነበር እንጠብቅ ነበር። ነገር ግን ፈውስን የማወጅ ኃይል የአንድ ሰው አገልግሎት ተደርጐ የተተኮረበትን ሁኔታ ግን ፈጽሞ አንመለከትም። 

ጥያቄ፡– ስለ ፈውስ አገልግሎቶችና መንፈስ ቅዱስ ከእነዚህ እውነቶች ጋር በተለመደ ሁኔታ እንዴት እንደሚሠራ ምን ልንማር እንችላለን?

ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

One thought on “ተአምራትና ፈውሶች በአዲስ ኪዳን

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.