ስለ ተአምራትና ፈውሶች የሚሰጡ የተሳሳቱ አሳቦች

ተአምራትና ፈውሶች በዚህ ዘመን ስላላቸው ሚና ሁልጊዜ አከራካሪ አሳቦች ይነሣሉ። የሚያሳዝነው ነገር ብዙ ጊዜ ክርስቲያኖች በአንድ እቅጣጫ ማክረራቸውና ሰዎች የእነርሱን አመለካከት እንዲቀበሉ ለማስገደድ መሞከራቸው ነው። አቋማችንን በትሕትና መያዝ አለብን። ሆኖም ግን እንደማምነው ምንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌላቸውና ልንርቃቸው የሚገቡን አንዳንድ ትምህርቶች አሉ። 

1. ስለ መንፈስ ቅዱስ በምናደርገው ጥናት በተደጋጋሚ እንደተመለከትነው ተአምራትንና ፈውሶችን በተመለከተ ያሉት ክፍተኛ ችግርች ወደ ከረሩ አቅጣሚዎች መሄድ ነው። አንደኛው የከረረ አቋም እግዚአብሔር ፈውስን ለማምጣት ሰዎችን ዛሬ አይጠቀምም የሚል ነው። ከሐዋርያት ሞት በኋላ እግዚአብሔር ፈውስን መስጠት አቁሟል ማለት ወይም ዛሬ የምንመላከታቸው ፈውሶች ሁሉ ከዲያብሎስ ናቸው ወይም እውነተኛ ያልሆኑ ማስመሰያዎች ናቸው ማለት አደገኛ ነው። ከሐዋርያት ሞት ወይም አዲስ ኪዳን ተጽፎ ካለቀ በኋላ ተአምራት ቆመዋል የምንልበት ምንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የለንም። እንደዚህ ይነት ዐረፍተ ነገር በራስ አመለካከት የመንፈስ ቅዱስን ሥራ ለመቆጣጠር መፈለግን የሚያመለክት ነው። የመንፈስ ቅዱስን አገልግሎት በመገደብ በአንድ መንገድ ብቻ ይሠራል ከማለት መጠንቀቅ አለብን። 

2. ወደ ሌላኛው የከረረ አቋም ስንሄድ ሁልጊዜ ፈውሶችንና ተአምራትን መፈለግ ደሞ አደገኛ ነው። ብዙ ክርስቲያኖች በፈውሶች እጅግ ይደነቃሉ። ወደ ስብሰባዎች የሚሄዱት የእግዚአብሔርን ቃል ለመማር መሆኑ ብዙ ሳይቆይ ይቀርና በመንፈስ ቅዱስ ለመዝናናት ይሆናል። መንፈስ ቅዱስ ፈውስን እንዲያደርግ ይፈልጋሉ። አንዳንድ ጊዜም ፍላጐታቸው የማስገደድ ያህል ነው። ከእንደዚህ ዓይነት ክርስቲያኖች አብዛኛዎቹ እነርሱ በፈለጉት መንገድ እግዚአብሔር ተአምራትን ሳያደርግ ሲቀር እምነታቸውን ይተዋሉ። 

3. ሌላው አደጋ እምነታችንን በእግዚአብሔር ላይ ከማድረግ ይልቅ በተአምራት ላይ ማድረጋችን ነው። ተአምራትን ያለማቋረጥ መፈለግ የሰውን እምነት ለማሻሻሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው ማረጋገጫ አነስተኛ ነው። ታላላቅ ተአምራት በተፈጸሙባቸው ጊዜያት (እስራኤላውያን በምድረበዳ በነበሩበት ጊዜ፥ በኤልያስ፥ በኤልሳዕ ወይም በኢየሱስ ዘመን ብዙ ሰዎች እጅግ በርካታ ተአምራት እየተመላክቱ እንኳ ለማመን ፈቃደኞች አልነበሩም። ወይም ለጊዜው እጅግ ይደነና ወዲያውኑ እግዚአብሔርን ከመከተል ይልቅ በራሳቸው አሳብ ይጓዙ ነበር። በሕይወት ከምንማራቸው እጅግ ጠቃሚ ከሆኑ ትምህርቶች እንዱ ለማመናችን የሚታይ ውጫዊ ችሮታ ሳንፈል. እግዚአብሔርን መከተል መማር ነው። የተስፋይቱን ምድር እንዳልወረሰው እንደ አብርሃም የእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች በሙሉ ወደሚፈጸሙበት ወደ ዘላላም ዓይኖቻችንን በማተኮር መማር አለብን (ዕብ. 11፡8-10፥16)። 

4. «እግዚአብሔር በሽታዎችን ሁሉ ይፈውስ ዘንድ ቃል ገብቶልናል።» ይህ አሳብ በክርስቲያኖች መካከል በከፍተኛ ደረጃ የተሳሳተ መረዳትን ያስከተለ ጉዳይ ነው። በአዲስ ኪዳን የጳውሎስ ወዳጆች ታመው ጳውሎስ ፈውስን ሊያመጣላቸው ያልቻለበት ጊዜያት ነበሩ። (ለምሳሌ አፍሮዲጡ (ፊልጵ. 2፡27)። ጢሞቲዎስ (1ኛ ጢሞ. 5፡23)፥ ጥሮፊሞስ (2ኛ ጢሞ. 4፡20)። ጳውሎስ እራሱም (ገላ. 4፡13-14)። ስለዚህ እግዚአብሔር ፈውስን ሁልጊዜ እንደማያከናውን ግልጽ ነው። እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እንድትናገር በልብህ ሳያስቀምጥ አንድ ሰው እንደሚፈወስ መናገር የአጉል መተማመን ኃጢአት ነው። የእግዚአብሔር መንገዶች ዓላማዎች ከእኛ የራቁ ናቸው። እግዚአብሔር ሊፈውስ እንደሚችል እናውቃለን ደግሞ ይፈውስ ይሆናል። ነገር ግን አንድ ሰው እንደሚፈወስ እግዚአብሔር ካልነገረን ይፈወሳል ብሎ መናገር ስሕተት ነው። እግዚአብሔር ልጆቹ በሕመም እንዲሰቃዩ ደግሞም እንዲሞቱ ብዙ ጊዜ ይፈቅዳል። ነገር ግን የትንሣኤ ዋስትና ላለን በሽታና ሞት ለክርስቲያን ቋሚ ችግርች እንዳልሆኑ እናውቃለን። 

5. ክርስቲያኖች ለታመመ ሰው ሊናገሩት የሚችሉት እጅግ ዘግናኝና ጐጂ አባባል አንዱ «ያልተፈወስከው እምነት ስለሌለህ ወይም በሕይወትህ ኃጢአት ስላለ ነው» የሚል ነው። ይህ አባባል ከፊል እውነት አለው። የእምነት ማነስ ወይም የኃጢአት በሕይወታችን መኖር ፈውስ እንዳንቀበል ሊያግደን ይችላል። እነዚህ ፈውስ ላለመኖሩ አንደኛዎቹ ምክንያቶች ናቸው። ነገር ግን ብቸኛዎቹ ምክንያቶች አይደሉም። ብዙ ሰዎች ለመፈወስ እምነት እያላቸው አይፈወሱም። ብዙ ሰዎች ንስሐ ያልገቡበት ኃጢአት በሕይወታቸው ባይኖርም ፈውስን ግን አይቀበሉም። ስለዚህ አንድ ሰው ፈውስን ያልተቀበለው በኃጢአት ወይም ባለማመን ምክንያት መሆኑን እግዚአብሔር በልዩ ሁኔታ ካልተናገረህ በስተቀር በጭራሽ በጭራሽ በጭራሽ ያልተፈወስኸው በኃጢአት ባለማመን ምክንያት ነው አትበል። የሰውን ልብ የሚያውቅ እግዚአብሔር ብቻ ስለሆነ የፍርድን ቃል መናገር ተገቢ አይደለም። እግዚአብሔር እንደ እምነታችን ለመሥራት የተወሰነ አይደለም። ኢየሱስ እምነት እንደነበራቸው ምንም ምልክት የማይታይባቸውን ሰዎች ፈውሷል። 

6. ሌላው አባባል «መንፈስ ቅዱስን ተአምራት እንዲያደርግ ላዝዘው እችላላሁ፤ እምነት ካለኝ ይህን ለማድረግ አያቅተኝም» የሚል ነው። ማንም ሰው መንፈስ ቅዱስን ተአምራት ያደርግ ዘንድ ለማዘዝ አይችልም። መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ነው። አንድን ነገር እንዲያደርግልን ለማስገደድ ፈጽሞ መሞከር የለብንም። እርሱ ጌታ ነውና ለእርሱ ተገዝተን መኖር አለብን። በማንኛውም ወቅት መንፈስ ቅዱስ ቢሠራ የተደረገው ነገር በእርሱ ምሕረት እንጂ የሚገባን ስለሆንን አይደለም። የሚፈጸመው የተአምራት መጠን በእምነት መጠን አይደለም። ማንኛውም ተአምራት በእግዚአብሔር ማንነት መጠን ላይ የሚወሰን ነው። እንደ ክርስቲያን የምናገለግለው ታላቅ አምላክ ስለሆነ ወደ እርሱ ከተመለከትን ሁልጊዜ ከግምታችን በላይ በሆኑ መንገዶች ይሠራል። 

7. «እግዚአብሔር አንድ ሰው እንደሚፈወስ እናገር ዘንድ መብት ከሰጠኝ ሁሉም ሰው ይፈወስ ዘንድ የመናገር ኃይል አለኝ ማለት ነው። ስለዚህ ትላልቅ የአደባባይ ስብሰባዎችን በማዘጋጀት ሁሉንም ሰው መፈወስ አለብኝ» የሚል አመለካከትም አለ። እግዚአብሔር ለአንድ ሰው ብዙ ሰዎችን የመፈወስ ኃይል እንደ ሰጠ መጽሐፍ ቅዱስ የትም ቦታ አያመለክትም። ኢየሱስም እንኳ የተሰበሰቡትን ሰዎች በሙሉ የፈወሰበት ጊዜ አንዴም አልነበረም። 

8. «እግዚአብሔር ደረጃ በደረጃ ይፈውሳል። አሁን በከፊል ይፈውሰኛል። ጸሎቴን በቀጠልኩ ቁጥር የበለጠ እየተፈወስኩ እሄዳለሁ።» በአንድ በኩል እግዚአብሔር ይህን ያደርግ ዘንድ የሚያግደው የለም። ነገር ግን እንዲህ ዓይነት ሰውን ደረጃ በደረጃ የመፈወስ አሠራር መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም። እግዚአብሔር አንድን ሰው እንደ ፈወሰ ተናግሮ ፍጹም ያልዳነበት ወቅት የለም። እንደዚህ ዓይነት ልምድ ፈጽሞ ስላልነበረ እንደዚህ ይሆናል ብለን ከመናገር መቆጠብ አለብን። 

ጥያቄ፡- ሀ) በአሁኑ ጊዜ ባሉ ቤተ ክርስቲያኖች ከላይ ከጠቀስናቸው የተሳሳቱ አመለካከቶች የትኞቹ ዘወትር ይንጸባረቃሉ? ለ) በከፊል እውነት የሚሆኑት በምን ዓይነት መንገድ ነው? 

ጥያቄ፡- ሀ) የቤተ ክርስቲያን መጋቢ ነህ። ከአባላትህ አንዱ ታምሟል እንበል። በዚህ ትምህርት የተጠቀሱትን መርሆዎች በመጠቀም ምን እንደምታደርግ አስረዳ።

ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading